የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 32 ገጽ 194-ገጽ 196 አን. 4
  • በእርግጠኝነት መናገር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በእርግጠኝነት መናገር
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጽኑ እምነት በመያዝ ምሥራቹን መስበክ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2000
  • በእርግጠኝነት መናገር
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • ጽኑ እምነት በመያዝ ምሉዓን ሆናችሁ ቁሙ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ወላጆች—“ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲያገኙ ልጆቻችሁን እርዷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 32 ገጽ 194-ገጽ 196 አን. 4

ጥናት 32

በእርግጠኝነት መናገር

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

የምትናገረውን ነገር እውነተኝነት እንዲሁም አስፈላጊነት ከልብ እንደምታምንበት በሚያሳይ መንገድ ተናገር።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አንተ በእርግጠኝነት መናገርህ ሌሎች ጉዳዩን በቁም ነገር እንዲያስቡበትና እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሳቸዋል።

አንድ ሰው በእርግጠኝነት የሚናገር ከሆነ አድማጮቹ ጉዳዩን ከልብ እንደሚያምንበት ይሰማቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስም ሲያገለግል እንዲህ ዓይነት የእርግጠኝነት ስሜት አንጸባርቋል። በተሰሎንቄ ለነበሩት አማኞች ሲጽፍ “ወንጌላችንን ያበሠርንላችሁ በቃል ብቻ ሳይሆን . . . ስለ ወንጌልም እውነት እርግጠኞች በመሆን ነው” ብሏል። (1 ተሰ. 1:​5 የ1980 ትርጉም ) ይህ ስሜቱ በአነጋገሩም ሆነ በአኗኗሩ ግልጽ ሆኖ ታይቷል። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ስናካፍል አነጋገራችን በእርግጠኝነት እንደምናምንበት የሚያሳይ ሊሆን ይገባል።

በእርግጠኝነት መናገር ማለት ሐሳበ ግትር ወይም ቀኖናዊ መሆን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ከአምላክ ቃል ጠቅሶ በሚያስረዳበት ጊዜ ጠንካራ እምነት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ ይናገራል ማለት ነው።​—⁠ዕብ. 11:​1

በእርግጠኝነት መናገር የሚያስፈልግባቸው ጊዜያት። በአገልግሎት ከሰዎች ጋር በምትወያይበት ጊዜ በእርግጠኝነት መናገርህ በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎች ከመልእክትህ በተጨማሪ የምትናገርበትን መንገድም ያስተውላሉ። ስለምትናገረው ነገር በውስጥህ ምን እንደሚሰማህ ይገምታሉ። መልእክትህ ጠቃሚ መሆኑን ይበልጥ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው የቃላት ምርጫህ ብቻ ሳይሆን በእርግጠኝነት መናገርህ ጭምር ነው።

ለእምነት ወንድሞችህ ንግግር ስታቀርብም ቢሆን በእርግጠኝነት መናገርህ አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ አነሳሽነት የመጀመሪያ መልእክቱን ሲጽፍ “ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልመሰክርላችሁ ብዬ ነው” ብሏል። በመልእክቱም ወንድሞቹን “በዚህ ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (1 ጴጥ. 5:​12) ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኘው ጉባኤ የእርግጠኝነት ስሜቱን የሚያንጸባርቅ ደብዳቤ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ 8:​38, 39) ጳውሎስ የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት በተመለከተ አሳማኝ በሆነ መንገድ የጻፈ ሲሆን እርሱ ራሱ በዚህ ሥራ በቅንዓት መካፈሉ አስፈላጊነቱን ከልብ እንዳመነበት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። (ሥራ 20:​18-21፤ ሮሜ 10:​9, 13-15) ዛሬም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከአምላክ ቃል በሚያስተምሩበት ጊዜ ስለ ጉዳዩ ያላቸው እርግጠኝነት በዚህ መንገድ ግልጽ ሆኖ ሊታይ ይገባል።

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አንድ ላይ በሚያጠኑበት ጊዜም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች መንፈሳዊ ነገሮችን ሲወያዩ ሐሳባቸውን በእርግጠኝነት ስሜት መግለጽ ይኖርባቸዋል። ይህም ወላጆች ራሳቸው ለአምላክና ለትእዛዛቱ በልባቸው ውስጥ ፍቅር መኮትኮት ይጠይቅባቸዋል። ‘አፍ የሚናገረው ከልብ ሙላት ስለሆነ’ ለልጆቻቸው ከልብ እንደሚያምኑበት በሚያሳይ መንገድ መናገር የሚችሉት ይህን ካደረጉ ነው። (ሉቃስ 6:​45፤ ዘዳ. 6:​5-7) ወላጆች እንዲህ ያለ ጽኑ እምነት ካላቸው ‘ግብዝነት የሌለበት እምነት’ በማሳየት ረገድ ምሳሌ ሆነው ይገኛሉ።​—⁠2 ጢሞ. 1:​5

በተለይ እምነትህን በተመለከተ ፈታኝ ጥያቄ ሲቀርብልህ በእርግጠኝነት መናገርህ በጣም አስፈላጊ ነው። አብሮህ የሚማር ልጅ፣ መምህርህ ወይም የሥራ ባልደረባህ በአንዳንድ በዓላት የማትካፈለው ለምን እንደሆነ ተገርመው ይጠይቁህ ይሆናል። አሳማኝ የሆነ ምክንያት በማቅረብ ቁርጥ ያለ መልስ መስጠትህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋምህን እንዲያከብሩልህ ሊረዳቸው ይችል ይሆናል። አንድ ሰው እንደ ማጭበርበር፣ አደገኛ ዕፅ እንደ መውሰድ ወይም የፆታ ብልግና እንደ መፈጸም በመሳሰሉ መጥፎ ድርጊቶች እንድትካፈል ሊያባብልህ ቢሞክርስ? እንዲህ ባለው ድርጊት ጨርሶ እንደማትካፈልና ምንም ዓይነት ጉትጎታ ሐሳብህን እንደማያስቀይርህ በማያሻማ መንገድ መናገርህ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህም እንዲህ ዓይነቱን ግብዣ እንደማትቀበል ስትገልጽ አስረግጠህ መናገርን ይጠይቅብሃል። ዮሴፍ የጲጥፋራ ሚስት ከእርሷ ጋር የፆታ ብልግና እንዲፈጽም ያቀረበችለትን ግብዣ እንደማይቀበል ሲገልጽ “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” ሲል ቁርጥ አድርጎ ተናግሯል። መወትወቷን በቀጠለች ጊዜ ግን ቤቱን ጥሎላት ሸሸ።​—⁠ዘፍ. 39:​9, 12

እርግጠኛ መሆናችን የሚንጸባረቅባቸው መንገዶች። የምትጠቀምባቸው ቃላት በጉዳዩ ላይ ከልብ እንደምታምንበት በማሳየት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ወሳኝ የሆነ ነጥብ ከመጥቀሱ በፊት ‘እውነት እውነት እላችኋለሁ’ የሚለውን መግለጫ ያስቀድም ነበር። (ዮሐ. 3:​3, 5, 11፤ 5:​19, 24, 25) ጳውሎስ እርግጠኛ መሆኑን ለማሳየት “ተረድቼአለሁ፣” “በጌታ በኢየሱስ ሆኜ አውቄአለሁ ተረድቼአለሁም” እንዲሁም “እውነት እናገራለሁ፤ አልዋሽም” የሚሉትን መግለጫዎች ተጠቅሟል። (ሮሜ 8:​39፤ 14:​14፤ 1 ጢሞ. 2:​7) ይሖዋ ቃሉ እንደሚፈጸም ሲገልጽ ነቢያቱ “በእርግጥ ይመጣል” ብለው እንዲናገሩ ያደረገባቸው ጊዜያት አሉ። (ዕን. 2:​3) አንተም እነዚህን ትንቢቶች ስትጠቅስ ተመሳሳይ አገላለጾችን ልትጠቀም ትችላለህ። በራስህ ሳይሆን በይሖዋ የምትታመንና ለሌሎች አክብሮት እንዳለህ በሚያሳይ መንገድ የምትናገር ከሆነ እንደ ነቢያቱ በእርግጠኝነት ስሜት መናገርህ ጠንካራ እምነት እንዳለህ የሚያሳይ ይሆናል።

በአነጋገርህ የሚንጸባረቀው ቁርጠኝነትም ምን ያህል እርግጠኛ እንደሆንክ የሚያሳይ ይሆናል። ፊት ላይ የሚነበበው ስሜትና አካላዊ መግለጫዎች ከሰው ወደ ሰው የሚለያዩ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ያለህ ጠንካራ እምነት እንዲንጸባረቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በተፈጥሮህ ዓይን አፋር ወይም ለስለስ ያለ አነጋገር ያለህ ብትሆን እንኳ የምትናገረው ነገር እውነት እንደሆነና ሌሎች ሊሰሙት እንደሚገባ ከልብ የምታምን ከሆነ የእርግጠኝነት ስሜትህ በግልጽ ይታያል።

እርግጥ፣ ጉዳዩን እንደምናምንበት ለማሳየት የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች እውነተኛ ስሜታችንን የሚገልጹ መሆን ይኖርባቸዋል። የሚያዳምጡን ሰዎች ከልባችን እየተናገርን ሳይሆን ለማስመሰል እየጣርን እንዳለ ከተሰማቸው ለመልእክታችን የሚሰጡት ክብደት ሊቀንስ ይችላል። እንግዲያው ከሁሉ በፊት አነጋገርህ ልባዊ መሆን አለበት። እንደ አድማጮችህ ብዛት ድምፅህን ከፍ አድርገህ በግለት መናገር ሊያስፈልግህ ይችላል። ሆኖም ዋናው ግብህ በራስህ ተፈጥሮአዊ አነጋገር ከልብ በመነጨ ስሜት መናገር ሊሆን ይገባል።

በእርግጠኝነት ስሜት ለመናገር የሚረዱ ነገሮች። በእርግጠኝነት መናገርህ ለትምህርቱ ካለህ ስሜት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ጥሩ ዝግጅት ማድረግህ ወሳኝ ነው። ሐሳቡን ከጽሑፍ ላይ ገልብጦ በቀጥታ ማስተላለፉ ብቻ በቂ አይሆንም። ትምህርቱ በደንብ ገብቶህ በራስህ አባባል መግለጽ መቻል ይኖርብሃል። መልእክቱ እውነት እንደሆነና አድማጮችንም እንደሚጠቅማቸው ከልብ ልታምንበት ይገባል። ይህም ንግግሩን በምትዘጋጅበት ጊዜ የአድማጮችህን ሁኔታ፣ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያላቸውን ግንዛቤ ወይም ስሜት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል ማለት ነው።

ንግግራችን ቅልጥፍና ካለው አድማጮቻችን በእርግጠኝነት እየተናገርን እንዳለን በቀላሉ ማስተዋል ይችላሉ። እንግዲያው ስለ ነጥቦቹ ብቻ ሳይሆን ስለ አቀራረብህም ልታስብ ይገባል። አስረግጠህ ማቅረብ የምትፈልጋቸውን ነጥቦች ስትናገር ማስታወሻህን ለማየት እንዳትገደድ በዝግጅትህ ወቅት ልዩ ትኩረት ልትሰጣቸው ይገባል። ይሖዋ ጥረትህን እንዲባርክልህ መጸለይ እንዳለብህም አትዘንጋ። እንደዚህ ካደረግህ የመልእክትህን እውነተኛነትና አስፈላጊነት በተመለከተ እርግጠኛ መሆንህን በሚያንጸባርቅ መንገድ ለመናገር የሚያስችል ‘ድፍረት ከአምላክ ታገኛለህ።’​—⁠1 ተሰ. 2:​2

በእርግጠኝነት ስሜት መናገር የሚቻለው እንዴት ነው?

  • ስትናገር ለርዕሰ ጉዳዩ የሚስማማ ስሜት ልታንጸባርቅ ይገባል።

  • እርግጠኛ መሆንህን የሚያሳዩ ቃላት ተጠቀም።

  • ትምህርቱ በደንብ እስኪገባህና በራስህ አባባል ልትገልጸው እስክትችል ድረስ ደጋግመህ አጥናው። የትምህርቱን እውነተኝነትና ለአድማጮች ያለውን ጥቅም ከልብ ልታምንበት ይገባል።

መልመጃ፦ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መርምር:- ዘጸአት 14:​10-​14፤ 2 ነገሥት 5:​1-3፤ ዳንኤል 3:​13-​18፤ ሥራ 2:​22-​36። በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ የአምላክ አገልጋዮች ያላቸው የእርግጠኝነት ስሜት የተንጸባረቀው እንዴት ነው? በዚህ መንገድ እንዲናገሩ ያስቻላቸው ምንድን ነው? ዛሬስ አንተ በዚህ ዓይነት ስሜት መናገር የምትችለው እንዴት ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ