የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 4/15 ገጽ 5-7
  • ዘላቂ ሰላም በእርግጥ የሚመጣው መቼ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዘላቂ ሰላም በእርግጥ የሚመጣው መቼ ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰላምን ሊያመጣ የሚችል
  • ወደ ዘላቂው ሰላም የሚመሩ ክንውኖች
  • የመጨረሻው ምልክት
  • እውነተኛ ሰላም—ከየት ይገኛል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • “የአምላክ ሰላም” ልባችሁን ይጠብቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • እውነተኛውን ሰላም ፈልጉ፣ ተከተሉትም!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ‘ሰላም የሚሆንበት ጊዜ’ ቀርቧል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 4/15 ገጽ 5-7

ዘላቂ ሰላም በእርግጥ የሚመጣው መቼ ነው?

“ጦርነት በታሪክ ውስጥ ምን ጊዜም ከሚኖሩት ነገሮች አንዱ ነው፤ ስልጣኔ ወይም ዲሞክራሲ ቢኖርም እየቀነሰ አልመጣም” በማለት ዊል እና ኤሪየል ዱራንት ከታሪክ የምናገኛቸው ትምህርቶች በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ጽፈዋል። “ሰላም የበላይነትን አምኖ በመቀበል ወይም እኩል ኃይል በመያዝ ሊጠበቅ የሚችል ተለዋዋጭ የሆነ የኃይል ሚዛን ነው።”

በእውነቱ ከፍተኛ ጥረቶች ቢደረጉም ዘላቂ ሰላም ለሰው ዘር አልጨበጥለት ብሏል። ለምን ቢባል የጦርነት መነሻ ምክንያቶች ላይ ላዩን የሚታዩት የፖለቲካ፣ የግዛት ጥያቄ ወይም የማኅበራዊ ትግሎች ብቻ ስላልሆኑ ነው፤ ምክንያቶቹ ከእነዚህ ነገሮች የበለጠ ጥልቅ ናቸው። ዊልና ኤሪየል ዱራንት፦ “የጦርነት መነሻ ምክንያቶች በግለሰቦች መካከል ፉክክር እንዲኖር ከሚያደርጉት ምክንያቶች የተለዩ አይደሉም፤ እነርሱም የኔ የኔ እያሉ መስገብገብ፣ የጠበኝነት ጠባይና ኩራት እንዲሁም ምግብ፣ መሬት፣ ንብረት፣ ነዳጅ፣ የበላይነት ለማግኘት የሚደረገው ፉክክር ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በግለሰቦችም ሆነ በትልቅ ደረጃ ለጠብና ለጦርነት ምክንያት የሚሆነውን ሥር ለይቶ ይገልጻል። እንዲህ እናነባለን፦ “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፣ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ።”​—ያዕቆብ 4:1, 2

ስለዚህ ነገሩ ባጭሩ እንደሚከተለው ሊገለጽ ይችላል፦ እውነተኛ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ችግር መኖሩን የሚያሳዩት እንደ ጦርነቶች፣ ሕዝባዊ አመጾች፣ የመንግሥት ግልበጣዎች፣ አብዮቶች ብቻ ሳይሆን መንስዔ የሆኑት ጥርጣሬ፣ ስስት፣ ጥላቻ፣ ጠበኛነት ከሰው ሁሉ መወገድ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ነገሮች እንደ ፍቅር፣ ደግነት፣ መተማመንና ደግነት ባሉ ከስስት ነፃ በሆኑ ጠባዮች መተካት ይኖርባቸዋል። ይህን ለውጥ ለማምጣት የሚችል ሊገኝ ይችላልን? ነገሩ የተመካው ፍጹም ባልሆኑ ምድራዊ ሰዎች ላይ ብቻ ቢሆን ኖሮ መልሱ አይችልም የሚል ይሆን ነበር። ሆኖም ይህ ነገር በጣም ከባድ የማይሆንበት አንድ አለ። እርሱም ሰላም የሚመጣው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱን የያዘው ነው።

ሰላምን ሊያመጣ የሚችል

ከ28 መቶ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚከተለው ብሎ እንዲናገር በመንፈስ ተመርቶ ነበር፦ “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ (መስፍን) ተብሎ ይጠራል። አለቅነቱ ይበዛል ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”​—ኢሳይያስ 9:6, 7

የማያልቅ ሰላም የሚያመጣው የዚህ መስፍን ማንነት “የልዑል ልጅ” ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን እንደማይችል ከጊዜ በኋላ ተገልጧል። (ሉቃስ 1:30-33፤ ማቴዎስ 1:18-23) ይሁን እንጂ ሁሉም ሌሎች መሣፍንትና ገዥዎች ያላሳኩትን ነገር እርሱ ማሳካት የሚችለው ለምንድን ነው? እዚህ ላይ ይህ ተስፋ የተደረገበት “ሕፃን” አንዳንዶች እንደሚያስቡት ለዘላለም ራሱን መርዳት የማይችል ሕፃን ሆኖ እንደማይቀር ማስታወስ ይገባል። ከዚህ ይልቅ የሰውን ዘር ለዘላለም ለመባረክ “የሰላም መስፍን” በመሆን ‘መስፍናዊ የመግዛት’ ሥልጣን ይይዛል።

የኢየሱስ አገዛዝ ሌላም የሚጨምረው ነገር አለ። “ድንቅ መካር” እንደመሆኑ መጠን የሰውን ባሕርይ በተለየ መንገድ የመረዳት፣ እጅግ በጣም ልዩ የሆነ ችሎታ ስላለው የአስቸጋሪ ጉዳዮችን ሥነ መሠረት ለማግኘትና በዛሬው ጊዜ ያሉትን ዓለማዊ መሪዎች ያጋጠሙአቸውን ተስፋ የሚያስቆርጡ እንደ እሾህ የሚዋጉ ችግሮች ለመፍታት ይችላል። (ማቴዎስ 7:28, 29፤ ማርቆስ 12:13-17፤ ሉቃስ 11:14-20) አሁን መሲሐዊ ንጉሥ በመሆን በሰማይ ነግሦ ያለው ከሞት የተነሣው አምላክ መሰሉ ኢየሱስ ክርስቶስ “ኃያል አምላክ” እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የፈጸማቸውን ተዓምራቶች ማለትም ሊድን የማይችል በሽታ የነበረባቸውን መፈወስ፣ ብዙ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ምግብና መጠጥ ማቅረብ፣ የአየር ንብረቱን መቆጣጠር ያሉትን ነገሮች በከፍተኛ ስፋት ይደግማቸዋል። (ማቴዎስ 14:14-21፤ ማርቆስ 4:36-39፤ ሉቃስ 17:11-14፤ ዮሐንስ 2:1-11) “የዘላለም አባት” እንደመሆኑም ኢየሱስ ሞተው ያሉትን ለማስነሣትና የዘላለም ሕይወት ሊሰጣቸው ኃይል አለው። እርሱም ራሱ ቢሆን ለዘላለም የሚኖር በመሆኑ ለአገዛዙና ለሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም።​—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 11:25, 26፤ ሮሜ 6:9

ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ ሁሉ ብቃቶች ስላሉት ሥር የሰደዱትን የጦርነትና የጥላቻ መነሻ ምክንያቶች ለማስወገድ የሚችለው እርሱ እንደሆነ ግልጽ ነው። እርሱ ጦርነት ቢነሣ የሚፈርስ፣ በሰላም አብሮ የመኖር ስምምነት የሚባል አንድ ዓይነት የሰላም ቃል ኪዳን ወይም ዕቅድ ለብሔራት አያዘጋጅም። ከዚህ ይልቅ የሰውን ዘር በሙሉ በአንድ አገዛዝ ይኸውም በመሲሐዊው መንግሥቱ ሥር በማድረግ በፖለቲካ፣ በግዛት፣ በማኅበራዊና በኤኮኖሚ ረገድ እኩልነት የጐደለውን ነገር ሁሉ ያስወግዳል። ሁሉንም ሰዎች ወደ አንዱ እውነተኛ አምላክ ወደ ይሖዋ አምልኮ በመምራት አብዛኛውን ጊዜ ለጦርነት ማና መነሻ ምክንያት የሆነውን የሐሰት ሃይማኖት ያጠፋል። የሰላም መስፍን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን እንደሚያከናውን ምንም አያጠራጥርም። ጥያቄው ይህንን የሚያደርገው መቼ ነው? የሚል ነው።

ወደ ዘላቂው ሰላም የሚመሩ ክንውኖች

በ33 እዘአ ከሞት ከተነሣና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ኢየሱስ እርምጃ የሚወስድበትን የተወሰነውን ጊዜ መጠበቅ ነበረበት። ይህም ይሖዋ “ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው። [ይሖዋ (አዓት)] የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ” ሲል ከሰጠው ትዕዛዝ ጋር የሚስማማ ነው። (መዝሙር 110:1, 2፤ ሉቃስ 22:69፤ ኤፌሶን 1:20፤ ዕብራውያን 10:12, 13) ይህ የሚሆነው መቼ ነው? የይሖዋ ምስክሮች ኢየሱስ በሰማይ በአምላክ መንግሥት ከ1914 ጀምሮ መግዛት እንደጀመረ የሚገልጸውን የምሥራች ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት በዓለም ዙሪያ ሲሰብኩ ቆይተዋል።a

ነገር ግን ‘ከ1914 ጀምሮ ምንም ሰላም አልነበረም። እንዲያውም ሁኔታዎች በተቃራኒው ወደተባባሰ ሁኔታ ሄደዋል’ ትል ይሆናል። ምንም አልተሳሳትክም። ይህ በትክክል የሚያሳየው ነገሮች በትንቢት እንደተነገረው በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዓለም መንግሥት የጌታችንና የእርሱ ክርስቶስ መንግሥት’ በሚሆንበት ጊዜ ‘አሕዛብ እንደሚቆጡ’ ይነግረናል። (ራእይ 11:15, 18) ለይሖዋ አምላክና ለእርሱ የሰላም መስፍን በመገዛት ፋንታ ብሔራት ዓለምን ለመግዛት ወደ ተጧጧፈ ትግል ውስጥ ገቡ። በተለይ ስለ ተቋቋመችው የአምላክ መንግሥት ይመሠክሩ በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ ተቆጡ።

ኢየሱስ የመንግሥት ሥልጣኑን ሲይዝ ወዲያው ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ለማስወገድ እርምጃ እንደሚወስድ የራእይ መጽሐፍም ያሳያል፦ “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፣ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።” ውጤቱስ ምን ሆነ? ትንቢቱ ቀጥሎ እንዲህ ይላል፦ “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”​—ራእይ 12:10, 12

የመጨረሻው ምልክት

ይህ ሁኔታ ብሔራት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ለምን ሰላምን ለማምጣት እንዳልቻሉ እንድናስተውል ይረዳናል። አሕዛብ በመቆጣታቸው የተንፀባረቀው የዲያብሎስ ታላቅ ቁጣ ዓለምን በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ፍርሃትና ብጥብጥ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል። ይህ ሁሉ የሚያበቃው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጠቃሚ የሆነ ፍንጭ ይሰጠናል፦ “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል።”​—1 ተሰሎንቄ 5:3

የዚህን ማስጠንቀቂያ ትርጉም ተገንዝበኸዋልን? ባለፈው ርዕሰ ትምህርት ላይ በዝርዝር እንደገለጽናቸው ያሉ የዓለም ሁኔታዎች መሪዎችና ብዙ ሰዎች ስለ ሰላም እንደሚነጋገሩና ከምንጊዜውም የበለጠ ሊጨብጡት እየተጣጣሩ እንዳሉ አሳይተውናል። አንዳንዶችም ቀዝቃዛው ጦርነት ካበቃ የኑክሌር እልቂት ይኖራል የሚለው ስጋት ያለፈ ነገር ሆኖ እንደሚቀር ሆኖ ተሰምቷቸዋል። አዎን ብሔራት ስለ ሰላምና ደኅንነት ብዙ እየተናገሩ ነው። ይሁን እንጂ የዓለም ሁኔታ በእርግጥ ወደዚያ አቅጣጫ እያመራ ነውን? ኢየሱስ ከ1914 ጀምሮ ባሉት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ስለሚኖሩት ሰዎች የተናገረው ትዝ ይበልህ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ብሏል። (ማቴዎስ 24:34) አዎን፤ ሰላም በዚህ ትውልድ ውስጥ ይመጣል፤ ሆኖም ብሔራት በሚያደርጓቸው ጥረቶች አይደለም። ይሖዋ አምላክ ቃል የገባለትና ጥብቅ መሠረት ያለው፣ ትክክለኛና ጻድቅ የሆነው ሰላም ሊመጣ የሚችለው እየመጣ ባለው በእርሱ የሰላም መስፍን በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ብቻ ነው።​—ኢሳይያስ 9:7

ሰላም በእርግጥ የሚመጣበትንና ከምትወዳቸው ሰዎች ጋር በሰላም የምትኖርበትን ቀን በጉጉት የምትጠብቅ ከሆነ ትኩረትህን ወደ ሰላሙ መስፍን አድርገህ ዋስትና የሚሰጡትን የሚከተሉትን ቃላት አስታውስ፦ “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁልጊዜ ትጉ።”​—ሉቃስ 21:36

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አቆጣጠርና ተፈጻሚነት ስላገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ዝርዝር ሐሳብ ለማግኘት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተመውን “መንግሥትህ ትምጣ” የተባለ መጽሐፍ ከምዕራፍ 12 እስከ 14 ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሰላም ትርጉም

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ሰላም ሲባል የጦርነት ወይም የሁከት መወገድ ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ለቃሉ የሚሰጥ በጣም ጠባብ ፍቺ ብቻ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን “ሰላም” (በዕብራይስጥ ሻሎም) የሚለው ቃል ወይም “ሰላም ይኑርህ!” የሚለው አባባል የተለመደ ሰላምታ ሆኖ ይሠራበት ነበር። (መሳፍንት 19:20፤ ዳንኤል 10:19፤ ዮሐንስ 20:19, 21, 26) በግልጽ እንደሚታየው ይህ አባባል የጦርነትን አለመኖር አያመለክትም። የሰላም ጽንሰ ሐሳብ የተባለው መጽሐፍ ስለዚህ ነጥብ የተናገረውን ተመልከት፦ “ሻሎም የተሰኘውን ቃል ለሰላም መጠቀም በተጀመረበት ጊዜ በቃሉ መጀመሪያ የተጠቀሙበት ሰዎች የነበራቸው አስተሳሰብ ሙላት፣ አንድነት፣ ኅብረት ያለው የዓለም ወይም የሰብዓዊ ኅብረተሰብ ሁኔታ ነበር። . . . ሰላም ካለ ሙላትና በእርሱ ሥር ያሉት የተለያዩ ክፍሎቹ ወደ ከፍተኛውና የመጨረሻው ደረጃ ይደርሳሉ።” አምላክ ሰላምን በሚያመጣበት ጊዜ ሰዎች ‘ጦርነትን ከእንግዲህ ወዲህ አለመማር’ ብቻ ሳይሆን ‘እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል።’​—ሚክያስ 4:3, 4

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ሰዎች የሰላም መጥፋት በጣም እየተሰማቸው መጥቷል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ