በቅርብ አስቀምጡት
የደም ክፍልፋዮችንና የራሴን ደም በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎችን በተመለከተ ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብኛል?
መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘ከደም እንዲርቁ’ ያዛል። (ሥራ 15:20) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን ደምም ሆነ አራቱን የደም ዋና ዋና ክፍሎች ማለትም ቀይ የደም ሕዋሳትን፣ ነጭ የደም ሕዋሳትን፣ ፕሌትሌትንና ፕላዝማን አይወስዱም። ከዚህም ባሻገር ለሌሎች ደም አይሰጡም ብሎም በሌላ ጊዜ ለሕክምና እንዲጠቀሙበት ደማቸውን አያስቀምጡም።—ዘሌ. 17:13, 14፤ ሥራ 15:28, 29
የደም ክፍልፋዮች የሚባሉት ምንድን ናቸው? እነርሱንስ በተመለከተ እያንዳንዱ ክርስቲያን የግሉን ውሳኔ ማድረግ ያለበት ለምንድን ነው?
የደም ክፍልፋዮች፣ ፍራክሽኔሽን በሚባለው ሂደት አማካኝነት ከደም ውስጥ ተለይተው የሚወጡ ንጥረ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ከአራቱ የደም ዋና ዋና ክፍሎች ውስጥ የሚመደበው ፕላዝማ በሚከተሉት ንጥረ ነገሮች ሊከፋፈል ይችላል:- ከፕላዝማ ውስጥ 91 በመቶ ገደማ ያህሉ ውኃ ሲሆን 7 በመቶ የሚሆነው ደግሞ እንደ አልቡሚን፣ ግሎቡሊንና ፋይብሪነጅን የመሳሰሉ ፕሮቲኖችን የያዘ ነው። አልሚ ምግቦች፣ ሆርሞኖች፣ የምንተነፍሳቸው ጋዞች፣ ቪታሚኖች፣ ቆሻሻዎችና ኤሌክትሮላይቶች ደግሞ 1.5 በመቶ ይሆናሉ።
ከደም እንድንርቅ የተሰጠው ትእዛዝ የደም ክፍልፋዮችንም ይጨምራል? እንደዚያ ብለን መናገር አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ከደም ውስጥ ተነጥለው የወጡ ክፍልፋዮችን አስመልክቶ ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም። እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ክፍልፋዮች የሚወሰዱት ለሕክምና ዓላማ እንዲውል ከተለገሰ ደም ነው። እያንዳንዱ ክርስቲያን በእነዚህ ንጥረ ነገሮች በመጠቀም የሚሰጥ ሕክምናን ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ ማድረግ አለበት።
ይህን የተመለከቱ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል:- ሁሉንም የደም ክፍልፋዮች ላለመውሰድ ስወስን ቫይረስንና በሽታን ለመዋጋት የሚያስችለኝን የመከላከያ አቅም ከፍ ለማድረግ ወይም ደግሞ የደም መፍሰስን ለማስቆም ተብለው የሚሰጡ ደምን የሚያረጉ አንዳንድ መድኃኒቶችን መውሰድ እንደማልፈልግ መግለጼ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ? አንዳንዶቹን የደም ክፍልፋዮች ለምን እንደማልወስድ ወይም ሌሎቹን ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆንኩበትን ምክንያት ለሐኪሞች ማስረዳት እችላለሁ?
የራሴን ደም በመጠቀም የሚካሄዱ የሕክምና ሂደቶችን በተመለከተ የግል ውሳኔ ማድረግ ያለብኝ ለምንድን ነው?
ክርስቲያኖች ደማቸውን የማይሰጡ ወይም ደግሞ ሌላ ጊዜ ተመልሶ እንዲሰጣቸው በማሰብ ደማቸውን የማያስቀምጡ ቢሆንም የራስን ደም በመጠቀም የሚካሄዱ አንዳንድ የሕክምና ሂደቶች ወይም ምርመራዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሰፈሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በቀጥታ አይጋጩም። በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ደም በመጠቀም የሚደረጉ አንዳንድ የሕክምና ሂደቶችን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል ማስተዋል የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።
ይህን መሰል ውሳኔዎችን ስታደርግ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- የተወሰነ ደም ከሰውነቴ ወጥቶ በሌላ መስመር እንዲያልፍ የሚደረግና ዝውውሩ ለተወሰነ ጊዜ የሚቋረጥ ከሆነ ይህን ደም የሰውነቴ ክፍል እንደሆነና ‘መሬት ላይ መፍሰስ’ እንደማይገባው አድርጌ ለመመልከት ሕሊናዬ ይፈቅድልኛል? (ዘዳ. 12:23, 24) በአንዳንድ የሕክምና ሂደቶች ላይ እንደሚደረገው ከሰውነቴ ውስጥ የተወሰነ ደም ከተወሰደ በኋላ የተወሰኑ ለውጦች ተደርገውበት ተመልሶ ወደ ሰውነቴ ቢገባ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናዬ ይቀበለዋል? የራሴን ደም በመጠቀም የሚሰጡ ሁሉንም የሕክምና ሂደቶች እንደማልፈልግ ስገልጽ እንደ ሂሞዳያሊስስ ያሉ (የሕመምተኛው ደም በመሣሪያ ውስጥ አልፎ ከተጣራ በኋላ ተመልሶ ወደ ሰውነቱ እንዲገባ ማድረግ) አሊያም በኸርት-ላንግ መሺን አማካኝነት የሚሰጡ ሕክምናዎችን (ደም ለጊዜው እንደ ልብ/ሳንባ በሚያገለግል መሣሪያ ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ የሚከናወን ሕክምና) እንደማልፈልግ ማመልከቴ መሆኑን በግልጽ ተረድቻለሁ? ውሳኔ ከማድረጌ በፊት ጉዳዩን በጸሎት አስቤበታለሁ?
የግል ውሳኔዬ ምንድን ነው?
በሚቀጥሉት ገጾች ላይ ያሉትን ሁለት ቅጾች በቁም ነገር አስብባቸው። ቅጽ 1 ከደም ውስጥ ተለይተው የወጡ አንዳንድ የደም ክፍልፋዮችን ዝርዝር የያዘ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በመድኃኒትነት የሚወሰዱት በምን መልኩ እንደሆነም ይገልጻል። እነዚህን ክፍልፋዮች መውሰድ ትፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመግለጽ በክፍት ቦታዎቹ ላይ ምልክት አድርግ። ቅጽ 2 ላይ የራስህን ደም በመጠቀም የሚከናወኑ አንዳንድ የተለመዱ የሕክምና ሂደቶች ተዘርዝረዋል። እነዚህን ሕክምናዎች ትቀበላቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ለመግለጽ በክፍት ቦታዎቹ ላይ ምልክት አድርግ። እነዚህ ቅጾች ሕጋዊ ሰነዶች አይደሉም። ሆኖም ለእነዚህ መጠይቆች የሰጠኸውን መልስ፣ የሕክምና መመሪያ ካርድህን ለመሙላት ልትጠቀምበት ትችላለህ።
ውሳኔ ማድረግ ያለብህ አንተ ራስህ ነህ፤ ሌላ ሰው እንዲወስንልህ ማድረግ አይኖርብህም። እንዲሁም ማንኛውም ክርስቲያን የሌላውን ውሳኔ መንቀፍ የለበትም። በዚህ ጉዳይ “እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋል።”—ገላ. 6:4, 5
[የግርጌ ማስታወሻዎች ]