ምዕራፍ ስምንት
ቤተሰባችሁን ጎጂ ከሆኑ ተጽዕኖዎች ጠብቁ
1-3. (ሀ) በቤተሰብ ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጎጂ ተጽዕኖዎች የሚመነጩት ከየት ነው? (ለ) ወላጆች ቤተሰባቸውን በመጠበቅ ረገድ ሚዛናቸውን መጠበቅ ያለባቸው እንዴት ነው?
ትንሹ ልጃችሁ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄድበት ሰዓት ደርሷል፤ ሆኖም ዶፍ ዝናብ እየጣለ ነው። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋላችሁ? የዝናብ ልብስ ሳታለብሱት እንዲሁ ትሰዱታላችሁ? ወይስ ዝናቡን እንዲከላከልለት በሚል መንቀሳቀስ እስኪያቅተው ድረስ የልብስ መዓት ትደርቱበታላችሁ? ሁለቱንም እንደማታደርጉ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ዝናቡ እንዳያበሰብሰው የሚከላከል ልብስ ብቻ ታለብሱታላችሁ።
2 በተመሳሳይም ወላጆች ቤተሰባቸው ከብዙ አቅጣጫዎች ማለትም ከመዝናኛው ኢንዱስትሪ፣ ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከእኩዮችና አልፎ ተርፎም ከትምህርት ቤቶች የሚፈልቁ ጎጂ ተጽዕኖዎች እንዳይዘንቡበት የሚከላከል ሚዛናዊ የሆነ ዘዴ መዘየድ አለባቸው። አንዳንድ ወላጆች ቤተሰባቸውን ለመጠበቅ እምብዛም ጥረት አያደርጉም። ሌሎቹ ደግሞ ሁሉም ውጫዊ ተጽዕኖ ጎጂ እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡ ልጆቻቸው ዕድገታቸው እንደተገታ ሆኖ እስኪሰማቸው ድረስ በጣም ጥብቅ ይሆኑባቸዋል። በዚህ ረገድ ሚዛናዊ መሆን ይቻላልን?
3 አዎ፣ ይቻላል። በጣም ጥብቅ መሆን ምንም ፋይዳ የሌለው ከመሆኑም በላይ አደጋ ሊጋብዝ ይችላል። (መክብብ 7:16, 17) ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወላጆች ቤተሰባቸውን በመጠበቅ ረገድ ትክክለኛ ሚዛናቸውን መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚከተሉትን ሦስት መስኮች እንመልከት:- ትምህርት፣ ጓደኝነትና መዝናኛ።
ልጆቻችሁን የሚያስተምረው ማን ነው?
4. ክርስቲያን ወላጆች ለትምህርት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
4 ክርስቲያን ወላጆች ለትምህርት ከፍ ያለ ግምት ይሰጣሉ። ልጆቻቸው መማራቸው ማንበብ፣ መጻፍና ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እንዲሁም ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ እንደሚረዳቸው ያውቃሉ። በተጨማሪም እንዴት መማር እንደሚችሉ ሊያሠለጥናቸው ይገባል። ልጆች በትምህርት ቤት የሚቀስሙት እውቀትና ችሎታ በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል። በተጨማሪም ጥሩ ትምህርት የተሻለ ሥራ ማከናወን እንዲችሉ ሊረዳቸው ይችላል።—ምሳሌ 22:29
5, 6. በትምህርት ቤት የሚማሩ ልጆች ፆታን በተመለከተ የተሳሳተ አስተሳሰብና ትምህርት ሊቀስሙ የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ይሁን እንጂ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት በሚሄዱበት ጊዜ የተዛባ አመለካከት ካላቸው ብዙ ልጆች ጋር ይገናኛሉ። ለምሳሌ ያህል ፆታንና ሥነ ምግባርን በተመለከተ ያላቸውን አስተሳሰብ ተመልከቱ። በናይጄርያ በአንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የምትማርና ልቅ የፆታ ብልግና የምትፈጽም አንዲት ልጅ አብረዋት የሚማሩትን ተማሪዎች ፆታን በተመለከተ አንዳንድ ነገር ትመክራቸው ነበር። ወሲባዊ ፍላጎት በሚቀሰቅሱ ጽሑፎች ላይ ያየችውንና ያነበበችውን ርካሽ የሆነ ነገር ትነግራቸው የነበረ ቢሆንም በከፍተኛ ጉጉት ይሰሟት ነበር። አንዳንዶቹ ልጆች እንዳለቻቸው አደረጉ። በዚህም የተነሳ ከእነዚህ ልጆች አንዷ ከጋብቻ ውጪ ከመጸነሷም በላይ ፅንሱን ራሷ ለማስወረድ ባደረገችው ሙከራ ሕይወቷን አጥታለች።
6 ልጆች በትምህርት ቤት ስለ ፆታ የተሳሳተ ነገር የሚማሩት ከዕኩዮቻቸው ብቻ ሳይሆን ከአስተማሪዎችም ጭምር መሆኑ ያሳዝናል። ትምህርት ቤቶች ስለ ፆታ ሲያስተምሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችንና ኃላፊነትን በተመለከተ ምንም ነገር የማይጠቅሱ መሆናቸው ብዙ ወላጆችን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከቷቸዋል። የ12 ዓመት ሴት ልጅ ያለቻት አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- “የምንኖረው ሃይማኖታዊና ወግ አጥባቂ የሆኑ ሰዎች ባሉበት አካባቢ ነው፤ ሆኖም በዚሁ አካባቢ የሚገኝ አንድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተማሪዎቹ ኮንዶም እያደለ ነው!” የዕድሜ እኩዮቿ የሆኑ ወንዶች ልጆች ልጃቸውን ለፆታ ግንኙነት እንደጠየቋት ሲሰሙ እሷና ባሏ በጣም ነው የደነገጡት። ወላጆች ቤተሰባቸውን እንዲህ ካሉ መጥፎ ተጽዕኖዎች መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው?
7. ፆታን በተመለከተ የሚተላለፈውን የተሳሳተ መረጃ መከላከል የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ምንድን ነው?
7 ልጆችን ከእንዲህ ዓይነቱ ተጽዕኖ ለመጠበቅ በእነሱ ፊት ስለ ፆታ ጉዳዮች ጨርሶ አለማንሣቱ የተሻለ ይሆን? አይደለም። ልጆቻችሁን እናንተ ራሳችሁ ስለ ፆታ ብታስተምሯቸው የተሻለ ነው። (ምሳሌ 5:1) እርግጥ ነው፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ብዙ ወላጆች ይህን ርዕሰ ጉዳይ ፈጽሞ አያነሱትም። በተመሳሳይም በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እምብዛም ስለ ፆታ አይወያዩም። በሴራ ሊዮን የሚኖር አንድ አባት “እንዲህ ማድረግ በአፍሪካውያን ባህል ነውር ነው” ሲል ተናግሯል። አንዳንድ ወላጆች ልጆችን ስለ ፆታ ማስተማር የፆታ ብልግና እንዲፈጽሙ ማነሳሳት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ አምላክ በዚህ ረገድ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
አምላክ ስለ ፆታ ያለው አመለካከት
8, 9. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፆታን በተመለከተ ምን ግሩም ትምህርት አለ?
8 መጽሐፍ ቅዱስ ተገቢ በሆነ መንገድ ስለ ፆታ መወያየት ምንም ስህተት እንደሌለው በግልጽ ያሳያል። በእስራኤላውያን ዘመን “ሕፃናቶችን” ጨምሮ የአምላክ ሕዝብ በሙሉ ተሰብስቦ የሙሴ ሕግ ሲነበብ እንዲሰማ ታዝዞ ነበር። (ዘዳግም 31:10-12፤ ኢያሱ 8:35) ሕጉ የወር አበባን፣ የወንድ ዘር መፍሰስን፣ ዝሙትን፣ ምንዝርን፣ ግብረ ሰዶምን፣ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትንና ከእንስሳት ጋር የሚደረገውን የፆታ ግንኙነት ጨምሮ የፆታ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ብዙ ሐሳቦችን በግልጽ የሚጠቅስ ነበር። (ዘሌዋውያን 15:16, 19፤ 18:6, 22, 23፤ ዘዳግም 22:22) ስለ እነዚህ ጉዳዮች የሚገልጸው ሕግ ከተነበበ በኋላ ወላጆች በጥያቄ ለሚያጣድፏቸው ልጆቻቸው ብዙ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ጥርጥር የለውም።
9 በምሳሌ መጽሐፍ ምዕራፍ አምስት፣ ስድስትና ሰባት ላይ ወደ ፆታ ብልግና ስለሚመሩ አደገኛ ሁኔታዎች ፍቅራዊ የሆነ የወላጅ ምክር ተሰጥቷል። እነዚህ ጥቅሶች የፆታ ብልግና አንዳንድ ጊዜ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ያሳያሉ። (ምሳሌ 5:3፤ 6:24, 25፤ 7:14-21) ሆኖም የፆታ ብልግና ተገቢ ያልሆነ ድርጊት መሆኑንና አደገኛ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል የሚገልጹ ከመሆኑም በላይ ወጣቶች በሥነ ምግባር ብልሹ ከሆኑ መንገዶች እንዲርቁ የሚረዳ መመሪያ ይሰጣሉ። (ምሳሌ 5:1-14, 21-23፤ 6:27-35፤ 7:22-27) ከዚህም በተጨማሪ በትዳር ውስጥ አግባብ ባለው መንገድ የሚፈጸመው የፆታ ግንኙነት የሚያስገኘው እርካታ ከጾታ ብልግና ጋር ያለው ልዩነት ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። (ምሳሌ 5:15-20) ወላጆች ሊከተሉት የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም የማስተማሪያ ዘዴ ነው!
10. ፆታን በተመለከተ ለልጆች አምላካዊ እውቀት መስጠት የፆታ ብልግና ወደ መፈጸም የማይመራቸው ለምንድን ነው?
10 እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ልጆች የፆታ ብልግና እንዲፈጽሙ ይገፋፋቸዋልን? አይገፋፋቸውም፤ እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒው መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ” ሲል ያስተምራል። (ምሳሌ 11:9) ልጆቻችሁን ከዚህ ዓለም ተጽዕኖዎች ለመታደግ አትፈልጉም? አንድ አባት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ልጆቻችን ገና በጣም ትንንሾች ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ፆታ በግልጽ እንነግራቸው ነበር። በመሆኑም ሌሎች ልጆች ስለ ፆታ ሲናገሩ በሚሰሙበት ጊዜ ለማወቅ የሚያጓጓቸው ምንም ነገር አልነበረም። አዲስ ነገር አይሆንባቸውም።”
11. ልጆችን ቀስ በቀስ ስለ ፆታ ጉዳዮች ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?
11 ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተገለጸው የፆታ ትምህርት አስቀድሞ መጀመር አለበት። ትንንሽ ልጆቻችሁን የአካል ክፍሎቻቸውን ስም ስታስተምሯቸው አሳፋሪ ነገር እንደሆነ በማሰብ የፆታ ብልቶቻቸውን ስሞች ሳታስተምሯቸው ማለፍ የለባችሁም። የእነዚህን ብልቶች ትክክለኛ ስሞች ንገሯቸው። ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ የፆታ ብልቶችን በተመለከተ ያሉትን ገደቦች አስተምሯቸው። እነዚህ የአካል ክፍሎች ልዩ እንደሆኑና ሌሎች ሰዎች ሊነኳቸው ወይም ሊያዩአቸው እንደማይገባ እንዲሁም ስለ እነዚህ የአካል ክፍሎች ጸያፍ የሆነ ወሬ ማውራት ተገቢ እንዳልሆነ ሁለቱም ወላጆች ቢያስተምሯቸው የተሻለ ነው። ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ግንኙነት ፈጥረው እንዴት ልጅ እንደሚጸነስ ሊነገራቸው ይገባል። ወደ ጉርምስና የዕድሜ ክልል ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ በአካል ክፍሎቻቸው ላይ የሚከሰቱትን ለውጦች በሚገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በምዕራፍ 5 ላይ እንደተገለጸው እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ልጆች በፆታ የማስነወር ድርጊት እንዳይፈጸምባቸው ሊረዳቸው ይችላል።—ምሳሌ 2:10-14
የወላጆች የቤት ሥራ
12. ብዙውን ጊዜ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ምን ዓይነት የተሳሳቱ ትምህርቶች ይሰጣሉ?
12 ወላጆች በትምህርት ቤቶች የሚሰጡትን እንደ ዝግመተ ለውጥ፣ ብሔራዊ ስሜት ወይም ደግሞ ፍጹም እውነት የሆነ ነገር የለም እንደሚሉት ያሉ ዓለማዊ ፍልስፍናዎችንና የሐሰት ትምህርቶችን ለመከላከል ዝግጁ መሆን አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 3:19፤ ከዘፍጥረት 1:27፤ ከዘሌዋውያን 26:1፤ ከዮሐንስ 4:24 እና ዮሐንስ 17:17 ጋር አወዳድሩ።) ብዙ የትምህርት ቤት ባለ ሥልጣናት በቅን ልቦና ተነሳስተው ተጨማሪ ትምህርት መከታተል በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ከሚገባው በላይ አጋንነው ይናገራሉ። ምንም እንኳ ተጨማሪ ትምህርት መከታተል የግል ምርጫ ቢሆንም አንዳንድ አስተማሪዎች የተሳካ ሕይወት መምራት የሚፈልግ ሰው ሁሉ ሊከተለው የሚገባ አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ አድርገው ሲናገሩ ይሰማል።a—መዝሙር 146:3-6
13. በትምህርት ቤት የሚማሩ ልጆችን ከተሳሳቱ አስተሳሰቦች መጠበቅ የሚቻለው እንዴት ነው?
13 ወላጆች የተሳሳተን ወይም የተዛባን ትምህርት መከላከል እንዲችሉ ልጆቻቸው ምን ትምህርት እየተሰጣቸው እንዳለ ማወቅ አለባቸው። ስለዚህ ወላጆች እናንተም የቤት ሥራ እንዳላችሁ አስታውሱ! ልጆቻችሁ የሚማሩትን ትምህርት በሚገባ ተከታተሉ። ከትምህርት ቤት ሲመጡ አወያዩአቸው። ምን እየተማሩ እንዳሉ፣ በጣም የሚወዱት ትምህርት ምን እንደሆነና በጣም ከባድ ሆኖ ያገኙት የትኛውን እንደሆነ ጠይቋቸው። የተሰጣቸውን የቤት ሥራ፣ በደብተራቸው የጻፉትን ማስታወሻና ያገኙትን የፈተና ውጤት ተመልከቱ። አስተማሪዎቻቸውን ለማወቅ ጣሩ። አስተማሪዎቹ ሥራቸውን እንደምታደንቁላቸውና በምትችሉት መንገድ ሁሉ ልትረዷቸው እንደምትፈልጉ እንዲገነዘቡ አድርጉ።
የልጆቻችሁ ጓደኞች
14. በአምላካዊ ትምህርት ተኮትኩተው ያደጉ ልጆች ጥሩ ጓደኞች መምረጣቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 “ለመሆኑ ይሄን ከየት ነው የተማርከው?” ልጃቸው ፈጽሞ ከጠባዩ ውጪ የሆነ ነገር በመናገሩ ወይም በማድረጉ በጣም ደንግጠው ይህን ጥያቄ የጠየቁ ወላጆች ስንቶቹ ይሆኑ? ከትምህርት ቤት ወይም ከሠፈር ጓደኛዬ የሚል መልስ የሚሰጣቸውስ ምን ያህል ጊዜ ይሆን? አዎ፣ ትንንሾችም ሆን ትልልቆች ጓደኞቻችን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ምሳሌ 13:20) በተለይ ወጣቶች ለእኩዮች ተጽዕኖ በጣም የተጋለጡ ናቸው። ራሳቸውን የመጠራጠር ዝንባሌ ያላቸው ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቻቸውን ለማስደሰትና ተወዳጅነትን ለማትረፍ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል። እንግዲያው ጥሩ ጓደኞች መምረጣቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!
15. ወላጆች ጓደኞችን በመምረጥ ረገድ ልጆቻቸውን ሊመሯቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
15 ማንኛውም ወላጅ እንደሚያውቀው ልጆች ጥሩ ምርጫ የማያደርጉባቸው ጊዜያት አሉ፤ ስለዚህ መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። ጓደኞቻቸውን እናንተ ልትመርጡላቸው ይገባል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እያደጉ ሲሄዱ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዲኖራቸውና ምን ዓይነት ባሕርያት ያላቸውን ልጆች ጓደኛ አድርገው መምረጥ እንደሚገባቸው አስተምሯቸው። ጓደኛ አድርገው የሚመርጧቸው ልጆች በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋን የሚወዱና በእሱ ፊት ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ መሆን አለባቸው። (ማርቆስ 12:28-30) ሐቀኞች፣ ደጎች፣ ለጋሶችና ትጉዎች የሆኑትን እንዲወዱና እንዲያከብሩ አሠልጥኗቸው። በቤተሰብ ጥናታችሁ ወቅት ልጆቻችሁ እንዲህ ዓይነት ባሕርያት ያሏቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ባሕርያት ለይተው እንዲያውቁና በጉባኤ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ባሕርያት ካላቸው ጋር እንዲወዳጁ እርዷቸው። እናንተም ጓደኞቻችሁን ስትመርጡ ይህንኑ ዓይነት መስፈርት በመጠቀም ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኗቸው።
16. ወላጆች የልጆቻቸውን የጓደኛ ምርጫ መከታተል የሚችሉት እንዴት ነው?
16 የልጆቻችሁን ጓደኞች ታውቋቸዋላችሁ? ልጆቻችሁ ጓደኞቻቸውን እቤት ይዘው መጥተው በደንብ እንዲያስተዋውቋችሁ ለምን አታደርጉም? በተጨማሪም ሌሎች ልጆች ለልጆቻችሁ ጓደኞች ምን ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ራሳቸውን ልጆቻችሁን ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። በአቋም ጽናታቸው የሚታወቁ ናቸው ወይስ ሁለት ዓይነት ኑሮ የሚኖሩ? ሁለት ዓይነት ኑሮ የሚኖሩ ከሆነ ልጆቻችሁ እንዲህ ዓይነቱ ጓደኝነት እንዴት ሊጎዳቸው እንደሚችል እንዲገነዘቡ እርዷቸው። (መዝሙር 26:4, 5, 9-12) በልጃችሁ ጠባይ፣ አለባበስ፣ አመለካከት ወይም አነጋገር ረገድ ተገቢ ያልሆነ ለውጥ ከተመለከታችሁ ስለ ጓደኞቹ ወይም ጓደኞቿ ልታነጋግሯቸው ይገባል። ምናልባት ልጃችሁ መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድርበት ጓደኛ ጋር መዋል ጀምሮ ይሆናል።—ከዘፍጥረት 34:1, 2 ጋር አወዳድሩ።
17, 18. ወላጆች ልጆቻቸው ከመጥፎ ጓደኞች እንዲርቁ ከማስጠንቀቅ በተጨማሪ ምን ተግባራዊ እርዳታ ሊሰጧቸው ይችላሉ?
17 ሆኖም ልጆቻችሁ ከመጥፎ ባልንጀሮች እንዲርቁ ማስተማሩ ብቻ በቂ አይደለም። ጥሩ ጓደኞች ማግኘት እንዲችሉ እርዷቸው። አንድ አባት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ሁልጊዜ ልጃችን በመጥፎ ጓደኞች ፋንታ ጥሩ ጓደኞች ማግኘት የሚችልበትን መንገድ እንፈልጋለን። ስለዚህ ልጃችን የትምህርት ቤቱ የእግር ኳስ ቡድን አባል እንዲሆን ጥሪ በቀረበለት ጊዜ ባለቤቴና እኔ ከልጃችን ጋር ቁጭ ብለን በጉዳዩ ላይ ተወያየንበት። ከሌሎች ልጆች ጋር ጓደኝነት እንዲፈጥር የሚያደርገው በመሆኑ ይህን ማድረጉ ጥሩ እንዳልሆነ ገለጽንለት። ሆኖም በዚህ ፋንታ በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ልጆችን ሰብስበን ወደ አንድ መናፈሻ በመሄድ ኳስ እንዲጫወቱ ለማድረግ ወሰንን። ይህም ችግሩን ለማቃለል ረድቶናል።”
18 ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ጓደኞች እንዲያገኙና ከእነርሱ ጋር ጤናማ በሆነ መዝናኛ እንዲዝናኑ ይረዷቸዋል። ይሁን እንጂ ለብዙ ወላጆች መዝናኛ ራሱ፣ የራሱ የሆኑ ፈታኝ ሁኔታዎች ይፈጥርባቸዋል።
ምን ዓይነት መዝናኛ?
19. ቤተሰቦች የሚያስደስቱና የሚያዝናኑ ነገሮች ማድረጋቸው ኃጢአት እንዳልሆነ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ያሳያሉ?
19 መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስደስትና የሚያዝናና ነገር ማድረግን ያወግዛልን? በፍጹም! መጽሐፍ ቅዱስ “ለመሳቅም ጊዜ አለው . . . ለመዝፈንም [“ለመጨፈርም፣” የ1980 ትርጉም] ጊዜ አለው” ይላል።b (መክብብ 3:4) በጥንት እስራኤል ዘመን የአምላክ ሕዝቦች በዘፈን፣ በጭፈራ፣ በጨዋታና በእንቆቅልሾች ይዝናኑ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ትልቅ የሠርግ ድግስ ላይና ማቴዎስ ሌዊ ባዘጋጀለት “ታላቅ ግብዣ” ላይ ተገኝቶ ነበር። (ሉቃስ 5:29፤ ዮሐንስ 2:1, 2) ኢየሱስ ሌሎችን ደስታ የሚያሳጣ እንዳልነበረ በግልጽ መረዳት ይቻላል። በቤተሰባችሁ ውስጥ ሳቅና ጨዋታ ፈጽሞ እንደ ኃጢአት መቆጠር የለበትም!
ይህ ቤተሰብ እንዳደረገው ዓይነት ሽርሽር፣ በሚገባ ታስቦበት የተመረጠ መዝናኛ ልጆች ትምህርት እንዲያገኙና በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ሊረዳቸው ይችላል
20. ወላጆች ለቤተሰባቸው መዝናኛ በማዘጋጀት ረገድ የትኞቹን ነገሮች ማስታወስ ይኖርባቸዋል?
20 ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ስለዚህ ይሖዋን ማምለክ ደስታ የሚያሳጣ ሳይሆን የሚያስደስት ነገር መሆን አለበት። (ከዘዳግም 16:15 ጋር አወዳድሩ።) ልጆች በተፈጥሯቸው ፍልቅልቆች ከመሆናቸውም በላይ በጨዋታና በመዝናኛ ወቅት ሊወጣ የሚችል የታመቀ ኃይል አላቸው። በሚገባ ታስቦበት የተመረጠ መዝናኛ ከደስታም ሌላ የሚያስገኘው ነገር አለ። አንድን ልጅ እንዲማርና እንዲጎለምስ ያደርገዋል። አንድ የቤተሰብ ራስ መዝናኛን ጨምሮ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ የማሟላት ኃላፊነት አለበት። ይሁን እንጂ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል።
21. በዛሬው ጊዜ መዝናኛ ምን ዓይነት አደጋዎች አሉት?
21 በእነዚህ አስጨናቂ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተተነበየው ‘ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን በሚወዱ’ ሰዎች የተሞላ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በብዙዎች ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ነገር መዝናኛ ነው። ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች በቀላሉ ጊዜ እንድናጣ ሊያደርገን የሚችል ብዙ መዝናኛ አለ። በተጨማሪም በዘመናችን ያሉት ብዙዎቹ መዝናኛዎች የፆታ ብልግናን፣ ጠበኝነትን፣ አደንዛዥ ዕፆች መጠቀምንና ሌሎች እጅግ ጎጂ የሆኑ ድርጊቶችን የሚያራምዱ ናቸው። (ምሳሌ 3:31) ወጣቶችን ጎጂ ከሆኑ መዝናኛዎች ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይቻላል?
22. ወላጆች ልጆቻቸው መዝናኛን በተመለከተ ጥበብ የተሞላባቸው ውሳኔዎች እንዲያደርጉ ሊያሠለጥኗቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
22 ወላጆች ገደቦችና እገዳዎች ማውጣት አለባቸው። ከዚህ ይበልጥ ግን ልጆቻቸው ጎጂ መዝናኛን ለይተው ማወቅ እንዲችሉና መዝናኛ በዛ ሊባል የሚችለው ምን ያህል ጊዜ ሲወስድ እንደሆነ ማወቅ እንዲችሉ ሊያስተምሯቸው ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ ማሠልጠኛ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። አንድ ምሳሌ ተመልከቱ። ሁለት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ አባት የመጀመሪያ ልጁ አንድ አዲስ የሬዲዮ ጣቢያን አዘውትሮ መስማት እንደጀመረ አስተዋለ። ስለዚህ አንድ ቀን ከባድ መኪናውን እየነዳ ወደ ሥራ ሲሄድ ይህንኑ ጣቢያ ከፍቶ መስማት ጀመረ። አልፎ አልፎ ቆም እያለ የአንዳንዶቹን ዘፈኖች ግጥሞች በማስታወሻ ያዘ። በኋላ የሰማውን ነገር ለልጆቹ ነገራቸው። “ምን ይመስላችኋል?” የሚል ጥያቄ በማንሳት አንዳንድ የአመለካከት ጥያቄዎች እየጠየቀ የሚሰጡትን መልስ በጥሞና አዳመጠ። ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ በጉዳዩ ላይ በሚገባ ካወያያቸው በኋላ ልጆቹ ይህን ጣቢያ መስማት እንደሌለባቸው ተስማሙ።
23. ወላጆች ልጆቻቸውን ጤናማ ካልሆነ መዝናኛ ሊጠብቋቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
23 ጥበበኛ የሆኑ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው የሚስቧቸውን ሙዚቃዎች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የቪዲዮ ክሮች፣ የቀልድ መጽሐፎች፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችና ፊልሞች በሚገባ ይመረምራሉ። በሽፋኖቻቸው ላይ ያሉትን ምስሎች፣ ግጥሞቹንና የክሮቹን መያዣዎች ይመለከታሉ፤ በተጨማሪም በጋዜጦች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችንና በመጽሐፎቹ ወይም በክሮቹ ጀርባዎች ላይ በከፊል ተወስደው የተጻፉትን ምንባቦች ያነባሉ። አንዳንዶች በዛሬው ጊዜ ልጆች የሚከታተሏቸው ወይም የሚጠቀሙባቸው አንዳንድ “መዝናኛዎች” በጣም አስደንግጠዋቸዋል። ልጆቻቸውን ብልሹ ከሆኑ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ የሚፈልጉ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ የመሰሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችንና በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን ርዕሶች በመጠቀም የእነዚህን ተጽዕኖዎች አደገኛነት ከቤተሰባቸው ጋር አንድ ላይ ሆነው ይወያያሉ።c ወላጆች ጥብቅ የሆኑ ገደቦች በማውጣት በአቋማቸው ሲጸኑና ምክንያታዊ ሲሆኑ በአብዛኛው ጥሩ ውጤቶች ማግኘታቸው አይቀርም።—ማቴዎስ 5:37፤ ፊልጵስዩስ 4:5 NW
24, 25. ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ሊዝናኑባቸው የሚችሉ አንዳንድ ጤናማ የመዝናኛ ዓይነቶች ምንድን ናቸው?
24 እርግጥ፣ ልጆች ጎጂ ከሆኑ መዝናኛዎች እንዲርቁ ማድረጉ ብቻ በቂ አይደለም። መጥፎውን በጥሩ መከላከል ያስፈልጋል፤ አለዚያ ግን ልጆች ወደ መጥፎ ጎዳና ሊያመሩ ይችላሉ። ብዙ ክርስቲያን ቤተሰቦች ወደ አንድ ቦታ ለሽርሽር መሄድ፣ ረጅም የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ለሽርሽር ወደ አንድ ቦታ ሄዶ በድንኳን ውስጥ የተወሰኑ ቀናት ማሳለፍ፣ የተለያዩ ጨዋታዎችንና ስፖርቶችን መጫወትና ዘመዶችን ወይም ወዳጆችን ሄዶ መጠየቅን በመሳሰሉ መዝናኛዎች በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሆነው በመዝናናት በርካታ አስደሳች ትዝታዎች አሳልፈዋል። አንዳንዶች ራስን ዘና ለማድረግ እንዲሁ አንድ ላይ ተሰባስቦ ጮክ ብሎ ማንበብ በጣም የሚያስደስትና የሚያጽናና ሆኖ አግኝተውታል። ሌሎች ቤተሰቦች አንዳንድ አስቂኝ ቀልዶችን ወይም የሚስቡ ታሪኮችን በማውራት ይዝናናሉ። ሌሎቹ ደግሞ የእንጨት ሥራንና ሌሎች ሙያዎችን በመሥራት እንዲሁም የሙዚቃ መሣሪያዎችን በመጫወት፣ ሥዕል በመሳል ወይም ደግሞ የአምላክን ፍጥረታት በማጥናት በአንድነት የሚያከናውኗቸውን የተለያዩ ልማዶች አዳብረዋል። በእነዚህ መዝናኛዎች መጠቀም የለመዱ ልጆች ብልሹ ከሆኑ መዝናኛዎች የሚጠበቁ ከመሆኑም በላይ መዝናኛ ሲባል እንዲሁ ዝም ብሎ ተቀምጦ መመልከት ብቻ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ብዙውን ጊዜ እንዲሁ ቁጭ ብሎ ከመመልከት ይልቅ ተሳትፎ ማድረጉ የበለጠ ደስታ ይሰጣል።
25 ለመጫወት ሲባል በርከት ብሎ መገናኘትም በጣም አስደሳች የሆነ መዝናኛ ነው። ጥሩ ቁጥጥር ከተደረገባቸውና ያልተንዛዙ ወይም ደግሞ ጊዜ የማይሻሙ ከሆኑ ልጆቻችሁ የሚያገኙት ጥቅም ደስታ በማግኘት ብቻ የተወሰነ አይሆንም። በጉባኤያችሁ ውስጥ ያለውን ፍቅር ለማጠንከርም አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ።—ከሉቃስ 14:13, 14 እና ከይሁዳ 12 ጋር አወዳድሩ።
ቤተሰባችሁ ዓለምን ሊያሸንፍ ይችላል
26. ቤተሰብን ጤናማ ካልሆኑ ተጽዕኖዎች በመጠበቅ ረገድ ከሁሉ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ባሕርይ የትኛው ነው?
26 ቤተሰባችሁን ከዓለም ጎጂ ተጽዕኖዎች መጠበቁ ትጋት የተሞላበት ጥረት እንደሚጠይቅ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ከምንም ነገር በላይ ይህን ጥረታችሁን የተሳካ ለማድረግ የሚያስችል አንድ ነገር አለ። ይህ ነገር ፍቅር ነው! በቤተሰባችሁ መካከል የጠበቀ የፍቅር ማሰሪያ መኖሩ ለቤተሰባችሁ ጥበቃ ከመሆኑም በላይ በመካከላችሁ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር በር ይከፍታል፤ ይህ ደግሞ መጥፎ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ሌላ ዓይነት ፍቅር ማዳበር ማለትም ይሖዋን መውደድ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ቤተሰቡ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ካለው ልጆቹ ለዓለማዊ ተጽዕኖ በመንበርከክ አምላክን ማሳዘን ከባድ ወንጀል ሆኖ ይታያቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋን ከልባቸው የሚወዱ ወላጆች የይሖዋን ፍቅራዊ፣ ምክንያታዊና ሚዛናዊ ስብዕና ለመኮረጅ ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌሶን 5:1፤ ያዕቆብ 3:17) ወላጆች ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ልጆቻቸው የይሖዋ አምልኮ በእገዳዎች ብቻ የተሞላ ወይም ደግሞ ጨዋታና ሳቅ የራቀው የሕይወት መንገድ እንደሆነ አድርገው በማሰብ በተቻለ መጠን በፍጥነት ከዚህ ለመላቀቅ የሚነሳሱበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ከዚህ ይልቅ አምላክን ማምለክ ከምንም በላይ የሚያስደስትና የሚያረካ የሕይወት መንገድ እንደሆነ ይገነዘባሉ።
27. አንድ ቤተሰብ ዓለምን ማሸነፍ የሚችለው እንዴት ነው?
27 አቋምን ከሚያጎድፉት ከዚህ ዓለም ተጽዕኖዎች ተጠብቀው “ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ” ለመኖር ከልባቸው ጥረት በማድረግ ለአምላክ በሚያቀርቡት አስደሳችና ሚዛናዊ የሆነ አገልግሎት በአንድነት የተሳሰሩ ቤተሰቦች የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛሉ። (2 ጴጥሮስ 3:14፤ ምሳሌ 27:11) እንዲህ ዓይነቶቹ ቤተሰቦች፣ የሰይጣን ዓለም አቋሙን ለማጉደፍ ያደረገውን ጥረት ሁሉ የተቋቋመውን የኢየሱስ ክርስቶስን ዱካ ይከተላሉ። ኢየሱስ በሰብዓዊ ሕይወቱ መገባደጃ ላይ “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ለማለት ችሏል። (ዮሐንስ 16:33) የእናንተም ቤተሰብ ዓለምን በማሸነፍ ለዘላለም ሕይወት እንዲበቃ እንመኛለን!
a ተጨማሪ ትምህርት መከታተልን በተመለከተ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው የይሖዋ ምሥክሮችና ትምህርት በተባለው (የእንግሊዝኛ) ብሮሹር ከገጽ 4-7 ላይ የተሰጠውን ማብራሪያ ተመልከቱ።
b እዚህ ላይ “መሳቅ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “መጫወት፣” “ማዝናናት፣” “እንደ ግብዣ ያለ አስደሳች ዝግጅት ማድረግ” ወይም ደግሞ “የሚያስደስት ነገር ማድረግ” ተብሎ በሌሎች መንገዶችም ሊተረጎም ይችላል።
c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ።