ምዕራፍ አሥራ አምስት
አረጋውያን ወላጆቻችንን ማክበር
1. ወላጆቻችን ምን ውለታ ውለውልናል? በመሆኑም ለወላጆቻችን ምን ዓይነት ስሜት ሊኖረንና ምን ልናደርግላቸው ይገባል?
ከረጅም ዘመናት በፊት ይኖር የነበረው ጠቢቡ ሰው “የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ምሳሌ 23:22) ‘ኧረ፣ እንዲህስ አላደርግም!’ ትሉ ይሆናል። አብዛኞቻችን እናቶቻችንንም ሆነ አባቶቻችንን ከመናቅ ይልቅ ከልብ እንወዳቸዋለን። ብዙ ውለታ እንደዋሉልን እናውቃለን። በመጀመሪያ ደረጃ ወላጆቻችን ሕይወት ሰጥተውናል። የሕይወት ምንጭ ይሖዋ ቢሆንም እንኳ ወላጆቻችን ባይኖሩ ኖሮ እኛም አንኖርም ነበር። ለወላጆቻችን የሕይወትን ያህል ውድ የሆነ ምንም ነገር ልንሰጣቸው አንችልም። አንድን ልጅ ከሕፃንነት ወደ ጉልምስና ማሸጋገር የሚጠይቀውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ፣ ከፍተኛ እንክብካቤ፣ ወጪና ፍቅራዊ አሳቢነት እስቲ ለአንድ አፍታ አስቡት። እንግዲያው የአምላክ ቃል “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር” የሚል ምክር መስጠቱ ምንኛ ምክንያታዊ ነው!—ኤፌሶን 6:2, 3
ስሜታዊ ፍላጎታቸውን መረዳት
2. ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች ‘ተገቢውን ብድራት’ መመለስ የሚችሉት እንዴት ነው?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ልጆች ወይም የልጅ ልጆች . . . አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም [“ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው፣” የ1980 ትርጉም] ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና።” (1 ጢሞቴዎስ 5:4) ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች ወላጆቻቸውና አያቶቻቸው ለብዙ ዓመታት ያሳዩአቸውን ፍቅር እንዲሁም የዋሉላቸውን ውለታና ያደረጉላቸውን እንክብካቤ በማድነቅ ይህን “ብድራት” ይመልሳሉ። ልጆች ይህን ማድረግ እንዲችሉ አንዱ የሚያስፈልጋቸው ነገር እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ በዕድሜ የገፉ ሰዎችም ፍቅርና ማጽናኛ የሚያሻቸው መሆኑን መረዳት ነው፤ እንዲያውም ይህ ብዙውን ጊዜ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች በጣም አንገብጋቢ ነገር ነው። እኛ ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጠን እንደምንፈልግ ሁሉ እነሱም በሌሎች ዘንድ ከፍ ተደርገው መታየት ይፈልጋሉ። ሕይወታቸው ዋጋማ እንደሆነ እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል።
3. ወላጆቻችንንና አያቶቻችንን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?
3 ስለዚህ ወላጆቻችንና አያቶቻችን እንደምናፈቅራቸው እንዲያውቁ በማድረግ ልናከብራቸው እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 16:14) ወላጆቻችን አብረውን የማይኖሩ ከሆነ በሆነ መንገድ ስለ እኛ ደህንነት ማወቃቸው በጣም ያስደስታቸዋል። ደስ የሚል ደብዳቤ ብንጽፍላቸው፣ ስልክ ብንደውልላቸው ወይም ደግሞ ሄደን ብንጠይቃቸው እጅግ ይደሰታሉ። በጃፓን የምትኖረው ሚዮ የ82 ዓመት ሴት በነበረችበት ጊዜ የሚከተለውን ጽፋለች:- “ሴት ልጄ [ባሏ ተጓዥ አገልጋይ ነው] ‘እማዬ እባክሽ አብረሽን “ተጓዢ”’ ትለኛለች። በየሳምንቱ የሚሄዱበትን ቦታና በሚሄዱበት ቦታ የሚጠቀሙበትን ስልክ ቁጥር ትነግረኛለች። ስለዚህ ካርታዬን እዘረጋና ‘አሁን እዚህ አካባቢ ናቸው ማለት ነው!’ እላለሁ። ይሖዋ ይቺን የመሰለች ልጅ በመስጠት ስለባረከኝ ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ።”
በቁሳዊ ነገሮች መርዳት
4. የአይሁድ ሃይማኖታዊ ወግ ሰዎች በአረጋውያን ወላጆቻቸው ላይ ምን ዓይነት የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያበረታታ ነበር?
4 ወላጆችን ማክበር በቁሳዊ ነገሮች መርዳትንም ሊጨምር ይችላልን? አዎ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግንም ይጨምራል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም ንብረቱን “ለእግዚአብሔር መባ አድርጌ አቅርቤአለሁ” ካለ ወላጆቹን የመጦር ኃላፊነት የለበትም የሚል ወግ ነበራቸው። (ማቴዎስ 15:3-6 የ1980 ትርጉም) እንዴት ያለ ጭካኔ ነው! እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተዘዋዋሪ መንገድ ሰዎች ወላጆቻቸውን ከማክበር ይልቅ በራስ ወዳድነት መንፈስ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በመንፈግ በንቀት እንዲመለከቷቸው እያበረታቱ ነበር። እኛ ግን እንዲህ የማድረግ ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሯችን ሊመጣ አይገባም!—ዘዳግም 27:16
5. በአንዳንድ አገሮች ምንም እንኳ መንግሥት አረጋውያንን ለመርዳት አንዳንድ ዝግጅቶች ያደረገ ቢሆንም ወላጆችን ማክበር አንዳንድ ጊዜ በቁሳዊ ነገሮችም መርዳትን የሚጨምረው ለምንድን ነው?
5 በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ በመንግሥት የሚደጎሙ ማኅበራዊ ፕሮግራሞች እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያሉ ለአረጋውያን የሚያስፈልጉ አንዳንድ ቁሳዊ እርዳታዎች ይሰጣሉ። ከዚህም በተጨማሪ አረጋውያኑ ራሳቸው ለእርጅና ዘመናቸው ብለው ያስቀመጡት ጥሪት ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም ይህ ጥሪታቸው ከተሟጠጠ ወይም በቂ ሆኖ ካልተገኘ ልጆች ወላጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ለወላጆቻቸው ያላቸውን አክብሮት ያሳያሉ። እንዲያውም በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መጦር ለአምላክ ያደሩ መሆንን፣ በሌላ አነጋገር አንድ ሰው የቤተሰብ ዝግጅት መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ያደረ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
ፍቅርና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ
6. አንዳንዶች ወላጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ሲሉ ምን ዓይነት ዝግጅቶች አድርገዋል?
6 ለአካለ መጠን የደረሱ ብዙ ልጆች አቅመ ደካማ ለሆኑ ወላጆቻቸው ፍቅርና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በማሳየት ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። አንዳንዶቹ ወላጆቻቸውን ወደ ራሳቸው ቤት ወስደዋቸዋል፤ ወይም ደግሞ ቤታቸውን ቀይረው በአቅራቢያቸው መኖር ጀምረዋል። ሌሎቹ ደግሞ ቤታቸውን ለቅቀው ከወላጆቻቸው ጋር መኖር ጀምረዋል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች ለወላጆቹም ሆነ ለልጆቹ በረከት ሆነው ተገኝተዋል።
7. አረጋውያን ወላጆችን በተመለከተ ለውሳኔ መቸኮል ጥሩ ያልሆነው ለምንድን ነው?
7 ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ እርምጃዎች ጥሩ ውጤት ሳያመጡ ይቀራሉ። ለምን? ምናልባት ውሳኔዎቹ የተወሰዱት በችኮላ ወይም ደግሞ በስሜታዊነት በመሆኑ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” ሲል ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (ምሳሌ 14:15) ለምሳሌ ያህል አረጋዊት እናትህ ብቻዋን መኖር አልቻለች ይሆናል፤ በመሆኑም ከአንተ ጋር ብትኖር የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ተሰምቶህ ይሆናል። የምትወስዳቸውን እርምጃዎች ጥበብ በተሞላበት መንገድ በጥሞና በማሰብ የሚከተሉትን ጉዳዮች ትመረምር ይሆናል:- በእርግጥ የሚያስፈልጓት ነገሮች ምንድን ናቸው? ተቀባይነት ያለው አማራጭ መፍትሔ ሊያስገኙ የሚችሉ የግል ወይም የመንግሥት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይኖራሉን? እሷስ ከአንተ ጋር መኖር ትፈልጋለች? የምትፈልግ ከሆነ ይህ በሕይወቷ ላይ ምን ለውጦች ያመጣል? የምትለያቸው ጓደኞች ይኖራሉን? ይህ በስሜቷ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል? ስለ እነዚህ ጉዳዮች አነጋግረሃታልን? እናትህ ከአንተ ጋር መኖሯ በትዳር ጓደኛህና በልጆችህ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል? እናትህ ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋት ከሆነ ይህን እንክብካቤ የሚያደርግላት ማን ነው? ኃላፊነቱን መከፋፈል ይቻላልን? ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተሃልን?
8. አረጋውያን ወላጆቻችሁን መርዳት የምትችሉበትን መንገድ በተመለከተ ማንን ልታማክሩ ትችላላችሁ?
8 እንክብካቤ የማድረጉ ኃላፊነት በቤተሰቡ ውስጥ ያሉትን ልጆች ሁሉ የሚመለከት በመሆኑ ሁሉም በሚወሰዱት ውሳኔዎች ላይ የበኩላቸውን ሐሳብ እንዲሰጡ ቤተሰቡ አንድ ላይ ተሰብስቦ ቢወያይ ጥሩ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌዎችን ወይም ተመሳሳይ ሁኔታ የገጠማቸውን ጓደኞች ማማከሩ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል፤ “መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል።”—ምሳሌ 15:22
የሌላውን ሰው ስሜት መጋራትና ችግሩን መረዳት
አስቀድሞ ራሱን ወላጁን ሳያማክሩ እሱን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ማድረግ ተገቢ አይደለም
9, 10. (ሀ) አረጋውያን ወላጆች ምንም እንኳ ዕድሜያቸው እየገፋ ቢሄድም ምን ዓይነት አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል? (ለ) ለአካለ መጠን የደረሰ ልጅ ለወላጆቹ ሲል ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ በሚወሰድበት ጊዜ ሁሉ ምን ሊያደርግ ይገባዋል?
9 አረጋውያን ወላጆቻችንን ማክበር ስሜታቸውን መጋራትና ችግራቸውን መረዳት ይጠይቃል። በእርጅና ዘመን ላይ የሚገኙ ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ መራመድ፣ መብላትና ማስታወስ እየተሳናቸው ይሄዳል። እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ልጆች ለወላጆቻቸው ደህንነት ከሚገባው በላይ በማሰብ መመሪያ ሊሰጧቸው ይሞክራሉ። ሆኖም አረጋውያን የብዙ ዓመታት ጥበብና ልምድ ያካበቱ እንዲሁም ዕድሜ ልካቸውን ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩና የራሳቸውን ውሳኔዎች ሲያደርጉ የኖሩ ዐዋቂ ሰዎች ናቸው። ወላጆችና ዐዋቂዎች መሆናቸው ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸውና በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያዳብሩ አድርጓቸዋል። ሕይወታቸው በልጆቻቸው ቁጥጥር ሥር እንደወደቀ ሆኖ የሚሰማቸው ወላጆች የመንፈስ ጭንቀት ሊያድርባቸውና ሊበሳጩ ይችላሉ። አንዳንዶች ሲደረግ የሚያዩትን ነገር የራሳቸውን ሕይወት በራሳቸው የመምራት መብታቸውን ለመጋፋት የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ አድርገው በመረዳት ቅር ሊሰኙና ተቃውሟቸውን ሊገልጹ ይችላሉ።
10 እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች በቀላሉ መፍታት አይቻልም፤ ሆኖም አረጋውያን ወላጆች በተቻለ መጠን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲረዱና የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ መፍቀዱ የደግነት መግለጫ ነው። መጀመሪያ እነሱን ሳታማክሩ ለእነሱ የተሻለ ነው ብላችሁ ያሰባችሁትን ውሳኔ ባትወስኑ ጥሩ ነው። በእርጅና ሳቢያ ብዙ ነገሮች አጥተው ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ባላቸው ነገር እንዲጠቀሙ ፍቀዱላቸው። በተቻለ መጠን ነፃነት የምትሰጧቸው ከሆነ በመካከላችሁ የተሻለ ዝምድና ይኖራል። እነሱም ይደሰታሉ፤ እናንተም ትደሰታላችሁ። በአንዳንድ ጉዳዮች ለእነርሱ ጥቅም ስትሉ ግፊት ማሳደሩ አስፈላጊ ቢሆንም ለወላጆቻችሁ ያላችሁ አክብሮት የሚገባቸውን ቦታና ከፍ ያለ ግምት እንድትሰጧቸው ያደርጋችኋል። የአምላክ ቃል “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር” የሚል ምክር ይሰጣል።—ዘሌዋውያን 19:32
ትክክለኛ አመለካከት መያዝ
11-13. ለአካለ መጠን የደረሰ አንድ ልጅ በልጅነት ዘመኑ ከወላጆቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበረው ባይሆን እንኳ ወላጆቹ በዕድሜ በገፉበት ዘመን እነርሱን በመጦር ረገድ የሚገጥመውን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት የሚችለው እንዴት ነው?
11 አንዳንድ ጊዜ ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ማክበር የሚያስቸግራቸው ልጆች በነበሩበት ጊዜ ከወላጆቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ነው። ምናልባት አባታችሁ ወዳጃዊ ስሜትና ፍቅር ያልነበረው ይሆናል፤ እናታችሁ ደግሞ ኃይለኛና ጥብቅ የነበረች ልትሆን ትችላለች። ወላጆችህ አንተ የምትፈልገውን ዓይነት ስላልነበሩ አሁንም ድረስ ትበሳጭና ትናደድ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ በደል እንደፈጸሙብህ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን ስሜት መቋቋም ትችላለህን?a
12 በፊንላንድ ውስጥ ያደገው ባስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የእንጀራ አባቴ በናዚ ጀርመን ውስጥ የኤስ ኤስ መኮንን ነበር። ግልፍተኛ ነበር፤ ከዚያ በኋላ የሚያደርገውን አያውቅም። እናቴን ብዙ ጊዜ እፊቴ ደብድቧታል። አንድ ቀን በጣም ተናድዶ ቀበቶውን አውልቆ ሲገርፈኝ የቀበቶው ዘለበት ፊቴን መታኝ። ምቱ ኃይለኛ ስለነበር አልጋ ላይ ተዘረርኩ።”
13 ሆኖም ለዚህ ባሕሪው አስተዋጽኦ ያደረጉ ነገሮች ነበሩ። ባስ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል:- “በሌላ በኩል ግን ተግቶ ይሠራ የነበረ ከመሆኑም በላይ ቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር በሚገባ ያሟላ ነበር። አባታዊ ፍቅሩን ገልጾልኝ የማያውቅ ቢሆንም የስሜት ጠባሳ እንደነበረው አውቅ ነበር። እናቱ ከቤት ያባረረችው ገና ትንሽ ልጅ እያለ ነው። እየተደባደበ ያደገ ከመሆኑም በላይ ወደ ጦርነት የገባው በጣም ወጣት እያለ ነው። ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ስለምረዳለት አልፈርድበትም። ትልቅ ሰው ከሆንኩ በኋላ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ እሱን ለመርዳት የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ጥሬያለሁ። ይህን ማድረጉ ቀላል አልነበረም፤ ቢሆንም የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ። እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ ጥሩ ልጅ ሆኜ ለመገኘት ሞክሬያለሁ፤ እሱም እንደዚህ እንደተሰማው አምናለሁ።”
14. አረጋውያን ወላጆችን መጦርን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ ጨምሮ በሁሉም ሁኔታዎች የሚሠራው የትኛው ጥቅስ ነው?
14 የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሌሎች ጉዳዮች እንደሚሠራ ሁሉ በቤተሰብ ሁኔታም ይሠራል:- “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።”—ቆላስይስ 3:12, 13
ጧሪዎችም እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል
15. ወላጆችን መጦር አንዳንድ ጊዜ በጣም የሚያስጨንቀው ለምንድን ነው?
15 አቅመ ደካማ የሆኑ ወላጆችን መጦር ብዙ ኃላፊነት የሚያስከትልና ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ነው። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ይበልጥ የሚከብደው በስሜት ላይ የሚፈጥረው ጫና ነው። ወላጆቻችሁ ጤናቸውን፣ የማስታወስ ችሎታቸውንና ራሳቸውን በራሳቸው የመምራት ብቃታቸውን ሲያጡ መመልከቱ በጣም ይረብሻል። የፖርቶ ሪኮዋ ሳንዲ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “እናቴ የቤተሰባችን ምሰሶ ነበረች። ስትሰቃይ እያዩ እሷን ማስታመሙ በጣም ከባድ ነበር። በመጀመሪያ ማነከስ ጀመረች፤ ከዚያም ከዘራ መጠቀም ጀመረች፤ በኋላ ምርኩዝ አስፈለጋት፤ ቀጥሎ ደግሞ ተሽከርካሪ ወንበር ለመጠቀም ተገደደች። ከዚህ በኋላ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በጣም እየባሰባት ሄዶ ነበር። የአጥንት ካንሠር ይዟት ስለነበር ሌት ተቀን ማስታመም ያስፈልግ ነበር። እናጥባታለን፣ እናበላታለን እንዲሁም እናነብላታለን። ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር፤ በተለይ በስሜታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። እናቴን በጣም እወዳት ስለነበር ልትሞት በምታጣጥርበት ጊዜ አለቀስኩ።”
16, 17. ወላጁን የሚያስታምም አንድ ሰው ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው የትኛው ምክር ሊረዳው ይችላል?
16 እናንተም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ካላችሁ ችግሩን ለመቋቋም ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አማካኝነት ይሖዋን መስማትና በጸሎት አማካኝነት ማነጋገር በጣም ይረዳል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ተመጣጣኝ ምግብ መመገብና በቂ እንቅልፍ መተኛት ይኖርባችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ የታመመውን ወላጃችሁን ለማስታመም በስሜታዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ የተሻለ ብቃት ይኖራችኋል። ምናልባት አልፎ አልፎ ከተለመደው የዕለት ተዕለት ተግባራችሁ ማረፍ የምትችሉበት ዝግጅት ማድረግ ትችሉ ይሆናል። ረዘም ያለ ዕረፍት መውሰድ የምትችሉበት ሁኔታ ባይኖር እንኳ ለጥቂት ጊዜ መዝናናት የምትችሉበት ፕሮግራም ማውጣታችሁ ጠቃሚ ነው። ዕረፍት ማድረግ የምትችሉበት ጊዜ እንድታገኙ የታመመውን ወላጃችሁን በቅርብ ሆኖ የሚረዳ ሰው ልታዘጋጁ ትችሉ ይሆናል።
17 ወላጆቻቸውን የሚጦሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ምክንያታዊ ያልሆኑ ነገሮችን ከራሳቸው ይጠብቃሉ። ሆኖም ማድረግ ባልቻላችሁት ነገር የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማችሁ አይገባም። በአንዳንድ ሁኔታዎች ወላጅህን ለአንድ እንክብካቤ መስጫ ተቋም መስጠት ሊያስፈልግህ ይችላል። ወላጅህን የምታስታምም ከሆንክ ከራስህ ምክንያታዊ ያልሆኑ ነገሮች አትጠብቅ። የወላጆችህን ብቻ ሳይሆን የልጆችህን፣ የባለቤትህንና የራስህንም ፍላጎቶች ማሟላት አለብህ።
ከወትሮው የላቀ ብርታት
18, 19. ይሖዋ ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል? ይህን ቃሉን እንደሚጠብቅስ የትኛው ተሞክሮ ያሳያል?
18 ይሖዋ በዕድሜ የገፉ ወላጆቹን የሚጦርን ሰው በእጅጉ ሊረዳ የሚችል መመሪያ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ይሰጣል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚሰጠው እርዳታ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። “እግዚአብሔር . . . ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው” ሲል መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ ጽፏል። “ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም።” ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች በሚገጥሟቸው ጊዜ እንኳ ሳይቀር ያድናቸዋል ወይም ይጠብቃቸዋል።—መዝሙር 145:18, 19
19 በፊሊፒንስ የምትኖረው ሚርና በአንጎል ውስጥ በሚከሰት የደም መፍሰስ ችግር ሳቢያ ሽባ የሆነችውን እናቷን በምታስታምምበት ጊዜ ይህን ልትገነዘብ ችላለች። “የምትወዱት ሰው የት ቦታ እንደሚያመው መናገር እንኳ ተስኖት ሲሰቃይ ከማየት የበለጠ የሚያስጨንቅ ነገር የለም” ስትል ሚርና ጽፋለች። “ሁኔታው፣ ቀስ በቀስ ውኃ ውስጥ ስትሰጥም እያየሁ ምንም ማድረግ እንዳልቻልኩ ያህል ነበር ማለት ይቻላል። ኃይሌ ምን ያህል እንደተሟጠጠ በመግለጽ ብዙ ጊዜ ተንበርክኬ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። እንባውን በአቁማዳ ውስጥ እንዲያጠራቅምለትና እንዲያስታውሰው በመለመን ይሖዋን እንደተማጸነው እንደ ዳዊት ጮኼያለሁ። ይሖዋም ቃል በገባው መሠረት የሚያስፈልገኝን ብርታት ሰጥቶኛል። ‘ይሖዋ ደገፋዬ ሆነ።’”—መዝሙር 18:18 NW
20. ወላጆቻቸውን ሲያስታምሙ የነበሩ ሰዎች ሲያስታምሙት የነበረው ሰው ቢሞት እንኳ የወደፊቱን ጊዜ በሙሉ ትምክህት እንዲጠባበቁ የሚያደርጓቸው የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ናቸው?
20 በዕድሜ የገፉ ወላጆችን ማስታመም “አሳዛኝ ፍጻሜ ያለው ታሪክ ነው” የሚል አባባል አለ። አስታማሚው ምንም ያህል ቢጥር በዕድሜ የገፉ ሰዎች ልክ እንደ ሚርና እናት ሊሞቱ ይችላሉ። ሆኖም በይሖዋ የሚታመኑ ሁሉ ሞት የታሪኩ መደምደሚያ እንዳልሆነ ያውቃሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” ብሏል። (ሥራ 24:15) አረጋውያን ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁሉ አምላክ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋና ‘ሞት የማይኖርበት’ አስደሳች አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ በገባው ቃል ሊጽናኑ ይችላሉ።—ራእይ 21:4
21. አረጋውያን ወላጆችን ማክበር ምን ጥሩ ውጤቶች ያስገኛል?
21 የአምላክ አገልጋዮች ለወላጆቻቸው ጥልቅ አክብሮት አላቸው። ወላጆቻቸው በዕድሜ ከገፉ በኋላም ቢሆን ለእነሱ ያላቸው አክብሮት አይቀንስም። (ምሳሌ 23:22-24) ለወላጆቻቸው ከፍ ያለ ግምት አላቸው። እንዲህ በማድረጋቸውም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የሚከተለው ምሳሌ በእነሱም ላይ ይፈጸማል:- “አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፣ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት።” (ምሳሌ 23:25) ከሁሉ በላይ ደግሞ አረጋውያን ወላጆቻቸውን የሚያከብሩ ሰዎች ይሖዋ አምላክንም ደስ የሚያሰኙ ከመሆኑም በላይ ለእሱ ያላቸውን አክብሮት ያሳያሉ።
a እንዲህ ስንል ወላጆች ሥልጣናቸውን ወይም የተጣለባቸውን አደራ አላግባብ በመጠቀም በወንጀለኛነት ሊያስጠይቅ የሚችል ድርጊት ስለፈጸሙባቸው ሁኔታዎች መናገራችን አይደለም።