ትንቢት
ፍቺ:- በመንፈስ አነሣሽነት የተነገረ መልእክት ወይም መለኮታዊውን ፈቃድና ዓላማ የሚያስታውቅ መግለጫ ነው። ትንቢት ወደ ፊት ስለሚፈጸም ነገር በቅድሚያ የተነገረ ቃል ወይም በመንፈስ አነሣሽነት የተነገረ የሥነ ምግባር ትምህርት ወይም መለኮታዊውን ትእዛዝና ፍርድ የሚያስታውቅ መግለጫ ሊሆን ይችላል።
ከአሁን በፊት ፍጻሜአቸውን ያገኙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡ ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው?
አንዳንድ ምሳሌዎችን ለመመልከት “መጽሐፍ ቅዱስ”፣ “የመጨረሻ ቀኖች”፣ “የዘመናት ስሌት” የሚሉትን ዋና ዋና ርእሶች በተጨማሪም “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው ” የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 343–346 ተመልከት።
ገና ወደ ፊት የሚፈጸሙ ጐላ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ምንድን ናቸው?
1 ተሰ. 5:3:- “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።”
ራእይ 17:16:- “ያየሃቸውም አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን [ታላቂቱን ባቢሎን] ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።”
ሕዝ. 38:14–19:- “ጎግንም እንዲህ በለው:- ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- በዚያ ቀን ሕዝቤ [መንፈሳዊ] እስራኤል ሳይፈራ በተቀመጠ ጊዜ አንተ አታውቅምን? አንተም፣ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ሁላችሁ . . . ታላቅ ወገንና ብርቱ ሠራዊት፣ ከሰሜን ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ። . . . በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ።”
ዳን. 2:44 የ1980 ትርጉም:- “[አምላክ ያቋቋመው] ይህ መንግሥት ሌሎችን [ሰብዓዊ] መንግሥታት እስከ መጨረሻው ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”
ሕዝ. 38:23:- “ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
ራእይ 20:1–3:- “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል።”
ዮሐ. 5:28, 29:- “በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”
ራእይ 21:3, 4:- “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ:- እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”
1 ቆሮ. 15:24–28:- “መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ . . . ፍጻሜ ይሆናል። . . . ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።”
ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች በጉጉት መከታተል የሚገባቸው ለምንድን ነው?
ማቴ. 24:42 የ1980 ትርጉም:- “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ።”
2 ጴጥ. 1:19–21:- “እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ [ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ፊት በተአምር በተለወጠ ጊዜ በተፈጸመው ነገር የተነሣ] . . . ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ [“ተጠንቅቃችሁ በመጠበቃችሁ” አዓት] መልካም ታደርጋላችሁ። . . . ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”
ምሳሌ 4:18:- “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።”
ማቴ. 4:4:- “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም።” (ይህም ታላላቅ ትንቢታዊ የተስፋ ቃሎቹን ይጨምራል።)
2 ጢሞ. 3:16:- “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ስለዚህ ተጽፎ የሚገኘው ጠቅላላው የአምላክ ቃል በጥሞና ሊጠና የሚገባው ነው።)
አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-
‘ለትንቢት ከሚገባ በላይ ብዙ ትኩረት ትሰጣላችሁ። የሚፈለገው ክርስቶስን እንደ አዳኝ አድርጎ መቀበልና ጥሩ ክርስቲያን ሆኖ መኖር ብቻ ነው’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘የኢየሱስ ክርስቶስን ሚና መገንዘብና መቀበል በእርግጥም አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁድ ኢየሱስን እንዳይቀበሉ ዕንቅፋት ከሆኑባቸው ነገሮች አንዱ ለትንቢቶች ተገቢ ትኩረት አለመስጠታቸው እንደሆነ ያውቃሉ?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘በዕብራይስጥ በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች የሚገኙ ትንቢቶች መሲሑ (ክርስቶስ) መቼ እንደሚገለጥ ምን እንደሚያደርግ ተንብየው ነበር። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን በአጠቃላይ እነዚህ ትንቢቶች ለሚናገሯቸው ነገሮች ትኩረት አልሰጡም። መሲሑ ምን እንደሚያደርግና ምን ማድረግ እንደሚገባው የራሳቸው አስተሳሰብ ስለነበራቸው የአምላክን ልጅ ሳይቀበሉ ቀሩ። (ገጽ 212, 213 ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)’ (2) ‘ዛሬ የምንኖረው ክርስቶስ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበትና አሕዛብን ሁሉ ለሕይወት አለዚያም ለጥፋት በየወገናቸው በሚለይበት ዘመን ላይ ነው። (ማቴ. 25:31–33, 46) አብዛኞቹ ሰዎች ግን የሚጠብቁት ከዚህ የተለየ ነገር ነው።’
ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ጥሩ ክርስቲያን መሆን አስፈላጊ እንደሆነ እኔም እስማማለሁ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ያስተማራቸውን አንዳንድ ነገሮች እየፈጸምኩ በሕይወታችን ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡትን ነገሮች ችላ ብል ጥሩ ክርስቲያን እሆናለሁ? . . . እዚህ ማቴዎስ 6:33 ላይ የተመዘገበውን የኢየሱስ ቃል ልብ ይበሉ።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትጨምር ትችላለህ:- ‘ኢየሱስ ስለዚህች መንግሥት እንድንጸልይ አስተምሮን የለም? እንዲያውም ኢየሱስ አዳኛችን መሆኑን በማመናችን ምክንያት ከምናገኘው የኃጢአት ሥርየት እንኳን አስቀድመን ስለዚህች መንግሥት እንድንጸልይ አስተምሮ የለም? (ማቴ. 6:9–12)’