የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ገጽ 272-ገጽ 281 አን. 4
  • ልናውጀው የሚገባ መልእክት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልናውጀው የሚገባ መልእክት
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ”
  • ‘ስለ ኢየሱስ መመሥከር’
  • “ይህ የመንግሥት ወንጌል”
  • ክርስቶስን መከተል ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • “የማይፈርስ መንግሥት”
    እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
  • የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀምሯል
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • የይሖዋ ምሥክሮች
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ገጽ 272-ገጽ 281 አን. 4

ልናውጀው የሚገባ መልእክት

ይሖዋ “እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፣ . . . እኔም አምላክ ነኝ” በማለት የእርሱ ምሥክሮች የመሆን መብትም ኃላፊነትም ሰጥቶናል። (ኢሳ. 43:​12 ) በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለሌሎች የምናውጅ ምሥክሮች እንጂ እጃችንን አጣጥፈን የተቀመጥን አማኞች አይደለንም። በዚህ ዘመን ይሖዋ ለሌሎች እንድናውጀው የሰጠን መልእክት ምንድን ነው? ስለ ይሖዋ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለ መሲሐዊው መንግሥት የሚገልጽ መልእክት ነው።

“እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ”

ከክርስትና ዘመን ከረጅም ጊዜ በፊት ይሖዋ ‘የምድር አሕዛብ ሁሉ’ ራሳቸውን የሚባርኩበት አንድ ዝግጅት እንደሚያደርግ ለአብርሃም ነግሮት ነበር። (ዘፍ. 22:​18) እንዲሁም ይሖዋ፣ ሰሎሞን በመንፈስ ተነሳስቶ “ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን [“እውነተኛውን አምላክ፣” NW ] ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ” በማለት እያንዳንዱ ሰው ሊያሟላው ስለሚገባ መሠረታዊ ግዴታ እንዲጽፍ አድርጓል። (መክ. 12:​13) ይሁን እንጂ ሰዎች ሁሉ ይህን ሊያውቁ የሚችሉት እንዴት ነው?

በየትኛውም ዘመን በአምላክ ቃል የሚያምኑ ሰዎች እንደነበሩ አይካድም። ሆኖም ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ብሔራት የሚዳረሰው “በጌታ ቀን” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህ “የጌታ ቀን” ደግሞ የጀመረው በ1914 ነው። (ራእይ 1:​10) በ⁠ራእይ 14:​6, 7 ላይ የሚገኘው ትንቢት ይህን ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር በመላእክት እገዛ ‘ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ’ የሚታወጅ ወሳኝ የሆነ መልእክት እንደሚኖር ይገልጻል። “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት” የሚል ማሳሰቢያ ይነገራቸዋል። አምላክ ይህ መልእክት እንዲታወጅ ይፈልጋል። እኛም በዚህ ሥራ የመካፈል መብት አግኝተናል።

‘እውነተኛው አምላክ።’ ይሖዋ “እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ” ሲል የተናገረው እውነተኛው አምላክ ማን ነው? የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ በተነሳበት ወቅት ነበር። (ኢሳ. 43:​10) የሚታወጀው መልእክት ሰዎች ሃይማኖት ወይም አንድ የሚያመልኩት አምላክ ሊኖራቸው ይገባል የሚል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ስለሆነው እውነተኛ አምላክ ማወቅ የሚችሉበትን አጋጣሚ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው። (ኢሳ. 45:​5, 18, 21, 22፤ ዮሐ. 17:​3) ስለ ወደፊቱ ጊዜ ዝንፍ የማይል ትንቢት ሊናገር የሚችለው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ ጥንት የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ወደፊት እንደሚፈጸሙ ቃል የገባቸው ነገሮች በሙሉ እውን መሆናቸው እንደማይቀር የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እንደሆኑ ለሌሎች የማሳወቅ መብት አግኝተናል።​—⁠ኢያሱ 23:​14፤ ኢሳ. 55:​10, 11

ችእርግጥ የምንመሠክርላቸው ብዙዎቹ ሰዎች ሌሎች አማልክትን የሚያመልኩ አሊያም የትኛውንም አምላክ እንደማያመልኩ የሚናገሩ ናቸው። ስለዚህ ለመልእክታችን ጆሯቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ በቅድሚያ በጋራ የሚያግባባንን ሐሳብ ማንሳት ያስፈልገን ይሆናል። በ⁠ሥራ 17:​22-31 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ ጥሩ ትምህርት ሊሆነን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎቹን ያነጋገራቸው በዘዴ ቢሆንም እያንዳንዱ ሰው ሰማይና ምድርን በፈጠረው አምላክ ፊት ተጠያቂ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦላቸዋል።

የአምላክን ስም ማሳወቅ። የእውነተኛውን አምላክ ስም ከማ​ሳወቅ ወደኋላ አትበል። ይሖዋ ስሙን ይወደዋል። (ዘጸ. 3:​15፤ ኢሳ. 42:​8) ሰዎች ስሙን እንዲያውቁ ይፈልጋል። ክብራማ ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ7, 000 ጊዜ በላይ እንዲጠቀስ አድርጓል። እኛም ይህንን ስም ለሰዎች የማሳወቅ ኃላፊነት ተጥሎብናል።​—⁠ዘዳ. 4:​35

መላው የሰው ዘር የተሻለ የሕይወት ተስፋ እንዲኖረው ይሖዋን ማወቅና ስሙን በእምነት መጥራት ይኖርበታል። (ኢዩ. 2:​32፤ ሚል. 3:​16፤ 2 ተሰ. 1:​8) ይሁንና ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን እውነተኛ አምላክ እናመልካለን የሚሉትን ጨምሮ አብዛኞቹ ሰዎች ይሖዋን አያውቁም። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖራቸውና ሊያነብቡት ቢችሉም የአምላክ ስም በጊዜያችን ካሉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ስለወጣ የግል መጠሪያ ስሙ ማን እንደሆነ አያውቁም። አንዳንዶቹም ቢሆኑ ስለ አምላክ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት የሃይማኖት መሪዎቻቸው በዚህ ስም መጠቀም የለባችሁም እያሉ ሲናገሩ ነው።

የአምላክን ስም ለሰዎች ማሳወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ስሙን ከመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ደግሞ ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ከማሳየት የተሻለ ዘዴ አይኖርም። በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ይህ ስም በሺህ የሚቆጠር ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። በሌሎች ትርጉሞች ውስጥ ደግሞ እንደ መዝሙር 83:​18 ወይም ዘጸአት 6:​3-6 ባሉት ጥቅሶች አሊያም በ⁠ዘጸአት 3:​14, 15 ወይም ዘጸ 6:​3 የግርጌ ማስታወሻ ላይ ብቻ ተጠቅሶ ይገኛል። በበርካታ ትርጉሞች ውስጥ በመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች የአምላክ ስም ተጠቅሶ የሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ “ጌታ” እና “እግዚአብሔር” የሚሉት ምትክ ስያሜዎች ለየት ባለ አጻጻፍ ሰፍረው ይገኛሉ። ተርጓሚዎቹ የአምላክን ስም ሙሉ በሙሉ አውጥተውት ከሆነ ለሰውዬው ለማስረዳት ቆየት ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መጠቀም ያስፈልግህ ይሆናል። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ መለኮታዊውን ስም የያዙ ሃይማኖታዊ መዝሙሮችን ወይም ስሙ ተቀርጾ የሚገኝባቸውን ሕንጻዎች እንደ ማስረጃ ልትጠቅስ ትችላለህ።

ኤርምያስ 10:​10-13 (እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ) ሌሎች አማልክትን የሚያመልኩ ሰዎችን ሳይቀር ለመርዳት ጥሩ ማስረጃ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ይህ ጥቅስ የአምላክን ስም ከመያዙም ሌላ ማንነቱን ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል።

እንደ ሕዝበ ክርስትና “እግዚአብሔር” እና “ጌታ” የሚሉትን ስያሜዎች እየተጠቀምህ የአምላክን የግል ስም ከመጥራት ወደኋላ ማለት የለብህም። ይህ ሲባል ግን ከሰዎች ጋር ስትወያይ ገና ከመጀመሪያው አንስቶ የአምላክን ስም ትጠቀማለህ ማለት ላይሆን ይችላል። እንዲህ ብታደርግ አንዳንድ ሰዎች ካላቸው የተዛባ አመለካከት የተነሳ ውይይቱን ወዲያው ሊያቋርጡ ይችላሉ። ጥቂት ከተወያያችሁ በኋላ ግን መለኮታዊውን ስም ለመጠቀም ማመንታት የለብህም።

መጽሐፍ ቅዱስ “ጌታ” እና “አምላክ” የሚሉትን ቃላት የተጠቀመባቸው ቦታዎች አንድ ላይ ቢደመሩ እንኳ ቁጥራቸው የአምላክ የግል ስም ከተጠቀሰበት ብዛት ጋር የማይተካከል መሆኑ ልብ ሊባል የሚ​ገባው ጉዳይ ነው። ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በየዓረፍተ ነገሩ መለኮታዊውን ስም ለማስገባት አልሞከሩም። እንደ አመቺነቱና እንደ አስፈላጊነቱ ለዛ ባለው መንገድ ተጠቅመውበታል። ይህ ለእኛም ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።

የዚህ ስም ባለቤት የሆነው አምላክ። አምላክ የግል መጠሪያ ስም እንዳለው ማወቅ ትልቅ ነገር ቢሆንም ይህ ብቻ በቂ ነው ማለት አይደለም።

ሰዎች ለይሖዋ ፍቅር እንዲኖራቸውና በእምነት እንዲጠሩት ካስፈለገ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ ስሙን ለሙሴ በገለጠለት ጊዜ “ይሖዋ” የሚለውን ቃል ብቻ ተናግሮ ዝም አላለም። ግሩም የሆኑትን ባሕርያቱን ዘርዝሮለታል። (ዘጸ. 34:​6, 7 NW ) እኛም ይህንን ምሳሌ ልንኮርጅ ይገባል።

በአገልግሎት ካገኘሃቸው ሰዎች ጋር ስትወያይም ሆነ በጉባኤ ንግግር ስታቀርብ የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች በምትጠቅስበት ጊዜ እነዚህን ተስፋዎች ስለሰጠው አምላክ ምን መረዳት እንደሚቻል አያይዘህ መግለጽ ይኖርብሃል። በተጨማሪም ስለ ትእዛዛቱ ስትጠቅስ በዚያ ላይ የተንጸባረቀውን የአምላክ ጥበብና ፍቅር ጎላ አድርገህ ልትገልጽ ይገባል። የአምላክ ትእዛዛት ለጥቅማችን የተሰጡ እንጂ ሸክም እንዳልሆኑ አስረዳ። (ኢሳ. 48:​17, 18፤ ሚክ. 6:​8) ይሖዋ ኃይሉን ከገለጠባቸው መንገዶች ስለ እርሱ ባሕርይ፣ ስለ መስፈርቶቹና ስለ ዓላማው ምን ትምህርት ማግኘት እንደሚቻል ግለጽ። ይሖዋ ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ የተለያዩ ባሕርያቱን እንዴት እንደሚያንጸባርቅ አብራራ። በውስጥህ ለይሖዋ ያለህን ስሜት አውጥተህ መግለጽ ይኖርብሃል። አንተ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ሌሎችም ለእርሱ ተመሳሳይ ፍቅር እንዲያድርባቸው ሊያነሳሳ ይችላል።

ዛሬ ሰዎች አምላክን እንዲፈሩ አጣዳፊ ጥሪ እየቀረበ ነው። የምንናገረው መልእክት ሰዎች ፈሪሃ አምላክ እንዲያዳብሩ የሚረዳ መሆን ይኖርበታል። ይህ ለእርሱ ካለን አክብሮት የሚመነጭ ጤናማ ፍርሃት ነው። (መዝ. 89:​7) ታላቁ ፈራጅ ይሖዋ እንደሆነና የወደፊቱ ሕይወታችንም የተመካው የእርሱን ሞገስ በማግኘታችን ላይ እንደሆነ መገንዘብን ይጨምራል። (ሉቃስ 12:​5፤ ሮሜ 14:​12) እንዲህ ያለው ፍርሃት ለይሖዋ ካለን ፍቅርና እርሱን ላለማስከፋት ካለን ጠንካራ ፍላጎት ጋር የተሳሰረ ነው። (ዘዳ. 10:​12, 13) ከዚህም በተጨማሪ ፈሪሃ አምላክ ክፉ የሆነውን ነገር እንድንጠላ፣ የአምላክን ትእዛዛት እንድንጠብቅ እንዲሁም በሙሉ ልባችን እርሱን እንድናመልክ ያነሳሳናል። (ዘዳ. 5:​29፤ 1 ዜና 28:​9፤ ምሳሌ 8:​13) በዓለም ያሉትን ነገሮች መውደድና ይሖዋን ማገልገል አብረው የማይሄዱ ነገሮች መሆናቸውን አስተውለን እንድንመላለስ ይረዳናል።​—⁠1 ዮሐ. 2:​15-17

የአምላክ ስም “ጽኑ ግምብ ነው።” ይሖዋን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች የእርሱን ጥበቃ ያገኛሉ። ይህን ጥበቃ ማግኘት የሚችሉት የግል መጠሪያ ስሙን ስላወቁ ወይም አንዳንድ ባሕርያቱን መጥቀስ ስለቻሉ ብቻ አይደለም። በይሖዋ ስለሚታመኑ ነው። ምሳሌ 18:​10 [አ.መ.ት ] እንዲህ ዓይነት ሰዎችን በሚመለከት ሲናገር “የእግዚአብሔር ስም ጽኑ ግምብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” በማለት ይገልጻል።

ያገኘኸውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመህ ሌሎች በይሖዋ እንዲታመኑ አበረታታ። (መዝ. 37:​3፤ ምሳሌ 3:​5, 6) እንዲህ ያለው ትምክህት በይሖዋና በተስፋዎቹ ላይ እምነት እንዳለን ያሳያል። (ዕብ. 11:​6) ሰዎች ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን ተገንዝበው ‘ስሙን በእምነት ከጠሩ፣’ ለትእዛዛቱ ፍቅር ካዳበሩ እንዲሁም የእውነተኛ መዳን ምንጭ እርሱ ብቻ መሆኑን ከልባቸው ካመኑ መዳን እንደሚያገኙ መጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና ይሰጠናል። (ሮሜ 10:​13, 14) ሌሎችን በምታስተምርበት ጊዜ በማንኛውም የሕይወታቸው ዘርፍ ይህን ዓይነት እምነት እንዲያዳብሩ እርዳቸው።

ብዙ ሰዎች የሚያስጨንቋቸው የራሳቸው ችግሮች አሉባቸው። በዚያ ላይ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁ ይሆናል። የይሖዋን ፈቃድ እንዲማሩ፣ በእርሱ እንዲታመኑና የተማሩትን ነገር እንዲሠሩበት አሳስባቸው። (መዝ. 25:​5) የአምላክን እርዳታ ለማግኘት አጥብቀው እንዲጸልዩ እንዲሁም ላደረገላቸው ነገር እንዲያመሰግኑት አበረታታቸው። (ፊልጵ. 4:​6, 7) ከይሖዋ ጋር ያላቸው ትውውቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ባነበቧቸው ነገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን ይሖዋ ለሰዎች የገባው ቃል በራሳቸው ሕይወት ውስጥ ፍጻሜውን ሲያገኝ በመመልከት ባዳበሩት እምነት ላይ ጭምር የተመሠረተ ከሆነ የይሖዋ ስም ያለውን እውነተኛ ትርጉም ከመረዳት የሚመነጭ የመረጋጋት ስሜት ይኖራቸዋል።​—⁠መዝ. 34:​8፤ ኤር. 17:​7, 8

ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን መፍራታቸውና ትእዛዛቱን መጠበቃቸው ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ጣር።

‘ስለ ኢየሱስ መመሥከር’

ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ሲል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ሥራ 1:​8) ዛሬ ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም ‘ስለ ኢየሱስ የሚመሰክሩ’ ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 12:​17) አንተ በዚህ የመመስከር ሥራ ምን ያህል በትጋት እየተካፈልህ ነው?

ብዙ ሰዎች በኢየሱስ እናምናለን ቢሉም ሰው ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕይወት ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ሰብዓዊ ሕይወት ይዞ እንደኖረ አይገነዘቡም። የአምላክ ልጅ ነው የሚለውን አባባል ትርጉም አይረዱትም። በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ምንም አያውቁም። በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገ እንዳለ አያውቁም፤ ወደፊት የሚያደርገውም ነገር ቢሆን የእነርሱን ሕይወት የሚነካው እንዴት እንደሆነ አይገነዘቡም። አልፎ ተርፎም የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ አያምኑም የሚል የተሳሳተ አመለካከት ይኖራቸው ይሆናል። እነዚህን ነጥቦች በተመለከተ ለሰዎች እውነቱን ለማሳወቅ ልንጥር ይገባል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ኢየሱስ በገሃዱ ዓለም የኖረ ሰው እንደሆነ የማያምኑ ሰዎችም አሉ። አንዳንዶች ኢየሱስ እንዲሁ በአንድ ወቅት የነበረ ታላቅ ሰው ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ብዙዎች የአምላክ ልጅ ነው የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉም። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ላላቸው ሰዎች ‘ስለ ኢየሱስ መመሥከር’ ብዙ ጥረት፣ ትዕግሥትና ዘዴኛነት ይጠይቃል።

የአድማጮችህ አመለካከት ምንም ይሁን ምን አምላክ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ካደረገው ዝግጅት መጠቀም እንዲችሉ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ ይኖርባቸዋል። (ዮሐ. 17:​3) የአምላክ ፈቃድ ሕይወት ያለው ሁሉ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ እንዲመሰክርና’ ለእርሱ ሥልጣን እንዲገዛ ነው። (ፊልጵ. 2:​9-11) ስለሆነም ይህ ግትር ያለና የተሳሳተ ወይም ጭራሽ የተዛባ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ስናገኝም ቢሆን አድበስብሰን ልናልፈው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ያም ሆኖ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ስንነጋገር ገና በመጀመሪያው ውይይታችን ሳይቀር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አንስተን በነፃነት ልንናገር እንችላለን። ከሌሎች ጋር ስንወያይ ደግሞ ሰዎቹ ስለ ኢየሱስ በትክክል እንዲያስቡ የሚያደርጋቸውን ሐሳብ በዘዴ ጠቆም ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል። ሌላ ጊዜ ተገናኝተን ስንወያይ ስለዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ተጨማሪ ሐሳብ ልናካፍላቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነም ማሰብ ያስፈልገን ይሆናል። ይሁን እንጂ ሰውዬውን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት እስካልጀመርን ድረስ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መንገር አንችል ይሆናል።​—⁠1 ጢሞ. 2:​3-7

ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያለው ቁልፍ ሚና። ኢየሱስ “መንገድ” ስለሆነና ‘በእርሱ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ’ ስለሌለ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት ሳይኖራቸው ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንደማይችሉ እንዲገነዘቡ መርዳት ይኖርብናል። (ዮሐ. 14:​6) አንድ ሰው ይሖዋ ለአንድያ ልጁ የሰጠውን ቁልፍ ቦታ እስካልተገነዘበ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት አይችልም። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ የሚጫወተው ሚና ወሳኝ በመሆኑ ነው። (ቆላ. 1:​17-20) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ናቸው። (ራእይ 19:​10) የሰይጣን ዓመፅና የአዳም ኃጢአት ያስከተሏቸው ችግሮች በሙሉ መፍትሔ የሚያገኙት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው።​—⁠ዕብ. 2:​5-9, 14, 15

አንድ ሰው ክርስቶስ የሚጫ​ወተውን ሚና ለመረዳት የሰው ልጆች ካሉበት አሳዛኝ ሁኔታ በራሳቸው ሊላቀቁ እንደማይችሉ መገንዘብ ይኖርበታል። ሁላችንም የተወለድነው በኃጢአት ነው። ይህ ደግሞ በሕይወት ዘመናችን በተለያዩ መንገዶች ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። ውሎ አድሮም ወደ ሞት እንደሚመራን የታወቀ ነው። (ሮሜ 3:​23፤ 5:​12) በአገልግሎት ላይ ለምታነጋግራቸው ሰዎች ይህን እውነታ ግልጽ አድርግላቸው። ከዚያም ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በዝግጅቱ ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚሆኑበትን መንገድ እንዳዘጋጀ ግለጽ። (ማር. 10:​45፤ ዕብ. 2:​9) ይህም ፍጹም የሆነ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በር ይከፍትላቸዋል። (ዮሐ. 3:​16, 36) ይህን ሕይወት ለማግኘት የሚያስችል ሌላ አማራጭ የለም። (ሥራ 4:​12) መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠናም ይሁን በጉባኤ ስታስተምር ይህንን እውነት መናገርህ ብቻ በቂ አይሆንም። አድማጮችህ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛ በመሆን ስለተጫወተው ሚና አድናቆት እንዲያድርባቸው በደግነትና በትዕግሥት መርዳት ይኖርብሃል። ለዚህ ዝግጅት ያላቸው አድናቆት በአመለካከታቸው፣ በአኗኗራቸውና በሕይወታቸው በሚያወጧቸው ግቦች ላይ ይንጸባረቃል።​—⁠2 ቆሮ. 5:​14, 15

እርግጥ ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ የሰጠው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። (ዕብ. 9:​28) ሆኖም በዛሬው ጊዜ በሊቀ ካህንነት በማገልገል ላይ ይገኛል። ሌሎች ሰዎች ይህ ነገር ምን ትርጉም እንዳለው እንዲገነዘቡ እርዳቸው። ሰዎች በሚፈጽሙባቸው በደል ምክንያት ጭንቀት፣ ሐዘን፣ ሥቃይ ወይም ችግር ደርሶባቸዋል? ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስላሳለፈ ዛሬ እኛ ምን እንደሚሰማን ያውቃል። ኃጢአት በመሥራታችን ምክንያት የአምላክ ምሕረት እንደሚያስፈልገን ይሰማናል? በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅርታ እንዲያደርግልን ወደ አምላክ ብንጸልይ ኢየሱስ ‘በአብ ዘንድ እንዳለ ረዳት’ ይሆንልናል። በርኅራኄ ‘ይማልድልናል።’ (1 ዮሐ. 2:​1, 2፤ ሮሜ 8:​34) በኢየሱስ መሥዋዕትና ሊቀ ካህናት ሆኖ በሚያከናውነው አገልግሎት አማካኝነት እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ወደ ይሖዋ ‘የጸጋ ዙፋን’ መቅረብ እንችላለን። (ዕብ. 4:​15, 16) ፍጹማን ሰዎች ባንሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ የሚያከናውነው አገልግሎት በንጹሕ ሕሊና አምላክን ለማገልገል ያስችለናል።​—⁠ዕብ. 9:​13, 14

በተጨማሪም ኢየሱስ የጉባኤው ራስ ሆኖ በአምላክ ስለተሾመ ከፍተኛ ሥልጣን አለው። (ማቴ. 28:​18፤ ኤፌ. 1:​22, 23) ይህንን ሥልጣኑን ተጠቅሞ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ አመራር ይሰጣል። ሌሎችን ስታስተምር የጉባኤው ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ሌላ ማንም ሰው እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ እርዳቸው። (ማቴ. 23:​10) በአገልግሎት ላይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስታገኝ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች እየታገዝን መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናባቸው የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ከመጀመሪያው ውይይታችሁ አንስቶ ልትጋብዛቸው ትችላለህ። ስለ ኢየሱስ የራስነት ሥልጣን እንዲገነዘቡ ‘ባሪያው’ ማን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን የጌታውን ማንነት ጭምር ልታስረዳቸው ይገባል። (ማቴ. 24:​45-47) ከሽማግሌዎች ጋር አስተዋውቃቸውና እነዚህ ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጹትን የትኞቹን ብቃቶች ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አብራራላቸው። (1 ጢሞ. 3:​1-7፤ ቲቶ 1:5-9) ጉባኤው የሽማግሌዎች እንዳልሆነ ሆኖም የክርስቶስን ፈለግ እንድንከተል እንደሚያግዙን አስረዳቸው። (ሥራ 20:​28፤ ኤፌ. 4:​16፤ 1 ጴጥ. 5:​2, 3) እነዚህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በክርስቶስ የሚመራ የተደራጀና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ድርጅት እንዳለ እንዲያስተውሉ እርዳቸው።

በወንጌል ዘገባዎች ላይ እንደምናነበው ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት በፊት ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው” በማለት አወድሰውታል። (ሉቃስ 19:​38) ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት የሚያጠኑ ሰዎች ይሖዋ ለኢየሱስ ብሔራትን በሙሉ የሚያጠቃልል የመግዛት ሥልጣን እንደሰጠው መገንዘባቸው አይቀርም። (ዳን. 7:​13, 14) በጉባኤ ንግግር ስትሰጥ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና አድማጮችህ የክርስቶስ ሥልጣን ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም ሊኖረው እንደሚገባ አስተውለው ልባቸው እንዲነካ መርዳት ይኖርብሃል።

አኗኗራችን በኢየሱስ ንግሥና የምናምን መሆን አለመሆኑን እንዲሁም ለሥልጣኑ ለመገዛት ፈቃደኛ መሆን አለመሆናችንን እንደሚያሳይ አበክረህ ግለጽ። ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ከተቀባ በኋላ ለተከታዮቹ ስለሰጣቸው ሥራ አብራራ። (ማቴ. 24:​14፤ 28:​18-20) ድንቅ መካር የተባለው ኢየሱስ በሕይወታችን ቅድሚያ ልንሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች ምን እንዳለ ተናገር። (ኢሳ. 9:​6, 7፤ ማቴ. 6:​19-34) የሰላሙ መስፍን ተከታዮቹ ስለሚኖራቸው ባሕርይ የተናገረውን ሐሳብ ጎላ አድርገህ ግለጽ። (ማቴ. 20:​25-27፤ ዮሐ. 13:​35) ሌሎች ሰዎች ለክርስቶስ ንግሥና ራሳቸውን ያስገዙት እስከምን ድረስ እንደሆነ እንዲመረምሩ አበረታታ እንጂ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እያደረጉ መሆናቸውን በተመለከተ በእነርሱ ላይ ለመፍረድ አትሞክር።

ክርስቶስን መሠረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት የማፍራቱን ሥራ ኢየሱስ ክርስቶስን መሠረት በማድረግ ሕንጻ ከመገንባት ጋር ያመሳስለዋል። (1 ቆሮ. 3:​10-15) ኢየሱስን መሠረት አድርጎ ለመገንባት ስለ እርሱ ማንነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን እውነት በትክክል እንዲያውቁ መርዳት ያስፈልጋል። የአንተ ደቀ መዝሙር እንደሆኑ አድርገው እንዳያስቡ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። (1 ቆሮ. 3:​4-7) ከዚህ ይልቅ መሪያቸው ኢየሱስ መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዳቸው።

ጥሩ መሠረት ከጣልን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ክርስቶስ ‘ፍለጋውን እንድንከተል’ ምሳሌ እንደተወልን ይገነዘባሉ። (1 ጴጥ. 2:​21) በዚህ መሠረት ላይ ለመገንባት ተማሪዎቹ ወንጌሎችን እንደ እውነተኛ ታሪክ አድርገው በመመልከት ብቻ ሳይሆን ሊከተሉት የሚገባቸውን ጎዳና የሚጠቁሙ መጻሕፍት እንደሆኑ በማሰብ እንዲያነቧቸው አበረታታ። የኢየሱስን አስተሳሰብና ባሕርይ ልብ ብለው እንዲያስተውሉ እርዳቸው። ኢየሱስ ለአባቱ ምን ዓይነት አመለካከት እንደነበረው፣ የገጠሙትን ፈተናዎች እንዴት እንደተወጣ፣ ለአምላክ ታዛዥ መሆኑን እንዴት እንዳሳየ እንዲሁም የተለያየ ሁኔታ ካላቸው ሰዎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደነበረው እያስተዋሉ እንዲያነብቡ አበረታታቸው። የኢየሱስ ሕይወት በምን ሥራ የተጠመደ እንደነበር ጎላ አድርገህ ግለጽ። እንዲህ ካደረግህ ተማሪው በሕይወቱ ውስጥ ችግር ሲገጥመው ‘ኢየሱስ ቢሆን ኖሮ ምን ያደርግ ነበር? እኔ የምከተለው ጎዳና እርሱ ላደረገልኝ ነገር ያለኝን አድናቆት የሚያሳይ ነውን?’ ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል።

በጉባኤ ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ወንድሞች በኢየሱስ ስለሚያምኑ ብቻ ስለ እርሱ ያን ያህል ጎላ አድርጎ መግለጽ አያስፈልግም ብለህ አታስብ። በዚህ ረገድ ያላቸውን እምነት ብትገነባላቸው ይበልጥ ይጠቀማሉ። ስለ ስብሰባዎች በምትናገርበት ጊዜ ጉዳዩን ክርስቶስ የጉባኤው ራስ ከመሆኑ ጋር አያይዘህ ግለጽ። ስለ አገልግሎት የምትናገር ከሆነ ደግሞ ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን ስላሳየው መንፈስ ልታብራራ እንዲሁም ንጉሥ ከሆነ በኋላ በአዲሱ ዓለም የሚኖሩትን ሰዎች ለመሰብሰብ እያከናወነው ካለው ሥራ ጋር አያይዘህ ልትገልጽ ትችላለህ።

ስለ ኢየሱስ መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ማወቅ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሰዎች እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን በእርሱ ላይ እምነት ሊኖራቸውና ከልባቸው ሊወድዱት ይገባል። እንዲህ ያለው ፍቅር በታማኝነት እንዲታዘዙ ያነሳሳቸዋል። (ዮሐ. 14:​15, 21) ሰዎች ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስባቸው በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ፣ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የክርስቶስን ፈለግ እንዲከተሉ እንዲሁም ጎልማሳ ክርስቲያኖች በመሆን ‘ሥር እንዲሰድዱ’ ያስችላቸዋል። (ኤፌ. 3:​17) እንዲህ ያለው ጎዳና የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት የሆነውን ይሖዋን ያስከብራል።

“ይህ የመንግሥት ወንጌል”

ኢየሱስ በሥልጣኑ የሚገኝበትንና ይህ ሥርዓት የሚደመደምበትን ጊዜ የሚጠቁሙትን ምልክቶች ሲዘረዝር እንዲህ በማለት ተንብዮአል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”​—⁠ማቴ. 24:​14

ይህን ያህል በሰፊው የሚታወጀው መልእክት ምንድን ነው? ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለን በጸሎታችን እንድንጠቅሰው ስላስተማረን መንግሥት የሚገልጽ መልእክት ነው። (ማቴ. 6:​10) የዚህ መንግሥት የመግዛት ሥልጣን ከይሖዋ የመነጨ በመሆኑና ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ክርስቶስ ስለሆነ ራእይ 11:​15 [አ.መ.ት] ስለዚህ መንግሥት ሲገልጽ “የዓለም መንግሥት፣ የጌታችንና [የይሖዋና] የእርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች” ይላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በእኛ ዘመን እንደሚታወጅ የተናገረለት መልእክት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ተከታዮቹ ካከናወኑት የስብከት ዘመቻ በበለጠ ስፋት እንደሚታወጅ ልብ በል። በዚያ ዘመን “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች” እያሉ ለሰዎች ይናገሩ ነበር። (ሉቃስ 10:​9) ንጉሥ ሆኖ የተቀባው ኢየሱስ በወቅቱ በመካከላቸው ነበር። ሆኖም በ⁠ማቴዎስ 24:​14 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚፈጸም ሌላ አንድ ታላቅ ክንውን በዓለም ዙሪያ እንደሚታወጅ ትንቢት ተናግሯል።

ይህንን ክንውን በተመለከተ ነቢዩ ዳንኤል አንድ ራእይ አይቷል። “የሰው ልጅ” ማለትም ኢየሱስ ክር​ስቶስ ‘በዘመናት ከሸመገለው’ ከይሖዋ አምላክ “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም” እንደተ​ቀበለ ተመልክቷል። (ዳን. 7:​13, 14) በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ይህ ነገር በሰማይ የተከናወነው በ1914 ነበር። ከዚያ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ምድር ተጥለዋል። (ራእይ 12:​7-10) ይህ አሮጌ ሥርዓት የሚደመደምበት ጊዜ ቀርቧል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ከመወገዱ በፊት የይሖዋ መሲሐዊ መንግሥት በሰማይ ሆኖ እየገዛ እንዳለ የሚገልጸው መልእክት በምድር ዙሪያ በመታወጅ ላይ ነው። በየትኛውም የምድር ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ይህ መልእክት እየደረሳቸው ነው። ለመልእክቱ የሚሰጡት ምላሽ ልዑሉ “በሰዎች መንግሥት ላይ” ያለውን ሥልጣን በተመለከተ ምን አመለካከት እንዳላቸው ይጠቁማል።​—⁠ዳን. 4:​32

ይሁንና ገና ሌሎች ብዙ ክንውኖችም ከፊታችን ይጠብቁናል! አሁንም “መንግሥትህ ትምጣ” እያልን እንጸልያለን። ይህ ሲባል ግን መንግሥቱ ገና አልተቋቋመም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰማያዊው መንግሥት እንደ ዳንኤል 2:​44 እና ራእይ 21:​2-4 ያሉትን ትንቢቶች የሚያስፈጽም ወሳኝ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃችን ነው። ምድር አምላክን በሚወዱና እርስ በርሳቸው በሚፋቀሩ ሰዎች የተሞላች ገነት እንድትሆን ያደርጋል። ‘ይህን የመንግሥት ወንጌል’ በምንሰብክበት ጊዜ ወደፊት እነዚህን በረከቶች እንደምናገኝ እንናገራለን። ሆኖም ይሖዋ ለልጁ ዛሬም ቢሆን ሙሉ የመግዛት ሥልጣን እንደሰጠው በትምክህት እናውጃለን። ስለ አምላክ መንግሥት በምትሰብክበት ጊዜ ይህን ምሥራች ጎላ አድርገህ ትገልጻለህን?

ስለ አምላክ መንግሥት ማብራራት። ስለ አምላክ መንግሥት የማወጅ ተልእኳችንን መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው? የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ሰዎችን ለውይይት መጋበዝ የምንችል ቢሆንም መልእክታችን ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጽ መሆኑን ወዲያው እንዲገነዘቡ ማድረግ ይኖርብናል።

በዚህ ጊዜ አንዱ ዋና ተግባራችን ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጹ ጥቅሶችን ማንበብ ወይም በቃል መጥቀስ ነው። ስለ አምላክ መንግሥት በምትናገርበት ጊዜ የምታነጋግራቸው ሰዎች የዚህን መንግሥት ምንነት መረዳታቸውን ለማስተዋል ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። የአምላክ መንግሥት ራሱን የቻለ መስተዳድር መሆኑን መግለጹ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች አንድን የማይታይ ነገር እንደ መስተዳድር አድርገው ማሰብ ሊከብዳቸው ይችላል። እንዲህ ያሉትን ሰዎች በተለያየ መንገድ ልታስረዳቸው ትችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የስበት ኃይል በዓይን የሚታይ ነገር ባይሆንም በሕይወታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አለው። የስበትን ሕግ ያስቀመጠውን አካል በዓይናችን ልናየው ባንችልም ታላቅ ኃይል እንዳለው ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዘላለም ንጉሥ’ በማለት ይጠራዋል። (1 ጢሞ. 1:​17) ወይም በሌላ ምሳሌ ለማስረዳት በአንድ ሰፊ አገር ውስጥ ዋና ከተማውን አይተው ወይም የአገሩን ገዥ በአካል አግኝተው የማያውቁ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ ልትጠቅስ ትችላለህ። ስለ እነዚህ ነገሮች የሚሰሙት በዜና ብቻ ነው። በተመሳሳይም ከ2, 200 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥት የመግዛት ሥልጣን የተሰጠው ማን እንደሆነና አሁን ይህ መንግሥት ምን እያደረገ እንዳለ ይገልጽልናል። በየጊዜው እየታተሙ ከሚወጡት መጽሔቶች ሁሉ ይበልጥ በብዙ ቋንቋዎች የሚዘጋጀው መጠበቂያ ግንብ በሽፋኑ ላይ እንደተገለጸው ዋና ተግባሩ ‘ስለ አምላክ መንግሥት ማወጅ’ ነው።

ሰዎች የአምላክ መንግሥት ምን ዓይነት እንደሆነ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ከአንድ መንግሥት የሚጠብቋቸውን አንዳንድ ነገሮች ልትጠቅስላቸው ትችላለህ። አንድ መንግሥት የኑሮ ዋስትናን፣ ሰላምን፣ ትምህርትን፣ ጤናን፣ ከወንጀል ስጋት ነፃ መሆንንና ሁሉም ብሔሮች በእኩል ዓይን የሚታዩበት አስተዳደር መፍጠርን ግብ አድርጎ እንዲሠራ ይጠብቃሉ። እነዚህና ሌሎችም የሰው ልጅ በጎ ፍላጎቶች የሚሟሉት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ብቻ እንደሆነ ግለጽ።​—⁠መዝ. 145:​16

ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድረው መንግሥት ሥር ተገዢዎች ሆነው የመኖር ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ጣር። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተዓምራት በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ለሚያከናውናቸው ነገሮች እንደ ናሙና እንደሆኑ ግለጽ። ስላሳያቸው ማራኪ ባሕርያት ደግመህ ደጋግመህ ተናገር። (ማቴ. 8:​2, 3፤ 11:​28-30) ለእኛ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ እንደሰጠና አምላክም ከሞት አስነስቶ በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት እንደሰጠው አስረዳ። ንጉሥ ሆኖ የሚገዛውም ከሰማይ ነው።​—⁠ሥራ 2:​29-35

የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ከሰማይ ሆኖ እያስተዳደረ እንዳለ ጎላ አድርገህ ግለጽ። ይሁን እንጂ ዛሬ አብዛኞቹ ሰዎች የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው እንዲሉ የሚያደርግ ተጨባጭ ነገር እንደማይታያቸው መዘንጋት የለብህም። ምን ማለት እንደፈለጉ መረዳትህን ከገለጽህ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ እንደ ማስረጃ አድርጎ የጠቀሳቸውን ሁኔታዎች ያውቁ እንደሆነ ጠይቃቸው። በ⁠ማቴዎስ ምዕራፍ 24፣ በ⁠ማርቆስ ምዕራፍ 13 ወይም በ⁠ሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ ካሉት ብዙ ዝርዝር ምልክቶች መካከል አንዳንዶቹን ልትጠቅስ ትችላለህ። ከዚያም ክርስቶስ በሰማይ ሥልጣን ሲይዝ በምድር ላይ እንዲህ ዓይነት ነገሮች የሚከናወኑት ለምን እንደሆነ ጠይቅና ራእይ 12:​7-10, 12⁠ን አንብብ።

ዛሬ የአምላክ መንግሥት ምን እያከናወነ እንዳለ ተጨባጭ ማስረጃ ለማቅረብ ማቴዎስ 24:​14⁠ን አንብብና በዓለም ዙሪያ እየተከናወነ ስላለው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር መርሐ ግብር ግለጽ። (ኢሳ. 54:​13) የይሖዋ ምሥክሮች ሥልጠና የሚያገኙባቸውን ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱና ያለ ክፍያ የሚካሄዱ ትምህርት ቤቶች በተመለከተ ልትናገር ትችላለህ። ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ከምናከናውነው ስብከት በተጨማሪ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በግለሰብም ይሁን በቤተሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንደምናስተምር አስረዳ። ለዜጎቹ ብቻ ሳይሆን በምድር ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች በሙሉ ይህን ያህል ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር ዘርግቶ ሊያስተምር የሚችል የትኛው ሰብዓዊ መንግሥት ነው? እንዲህ ያለው ትምህርት የሰዎችን ሕይወት እንዴት እየለወጠ እንዳለ እንዲያስተውሉ ለመርዳት በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎችና በሌሎች ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጋብዛቸው።​—⁠ኢሳ. 2:​2-4፤ 32:​1, 17፤ ዮሐ. 13:​35

ይሁንና የምታነጋግረው ሰው የአምላክ መንግሥት የእርሱን ሕይወት የሚነካው እንዴት እንደሆነ ይገነዘባል? እያንዳንዱ ሰው የአምላክ መንግሥት ተገዥ ሆኖ ለመኖር መምረጥ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለውና ስለዚሁ ጉዳይ ልታወያየው እንደሄድህ በዘዴ ልትነግረው ትችል ይሆናል። አንድ ሰው ይህን ምርጫ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? አምላክ ምን እንደሚፈልግበት በመማርና ሳይውል ሳያድር አኗኗሩን ከዚያ ጋር በማስማማት ነው።​—⁠ዘዳ. 30:​19, 20፤ ራእይ 22:​17

በሕይወታቸው የአምላክን መንግሥት እንዲያስቀድሙ መርዳት። አንድ ሰው ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት ከተቀበለም በኋላ በሕይወቱ ውስጥ ሊያደርጋቸው የሚገቡ አንዳንድ ውሳኔዎች ይኖራሉ። በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ መንግሥት የሚሰጠው ቦታ ምንድን ነው? ኢየሱስ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት . . . ፈልጉ” ሲል ደቀ መዛሙርቱን አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 6:​33) ክርስቲያን ወንድሞቻችን ይህን እንዲያደርጉ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችን ጥሩ ምሳሌ ሆነን በመገኘትና ያሉትን አማራጮች እንዲያስተውሉ በመርዳት ነው። አንዳንድ አማራጮችን አስበውባቸው እንደሆነ በመጠየቅና የሌሎችን ተሞክሮ በማካፈል ይህን ማድረግ ይቻል ይሆናል። ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግ በሚረዳ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን አንስቶ ማወያየት እንዲሁም መንግሥቱ እውን መሆኑን ጎላ አድርጎ መግለጽ ይቻላል። ስለ አምላክ መንግሥት የማወጁ ሥራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ መግለጽም ያስፈልግ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት የሚኖረው ምን ማድረግ እንዳለባቸው መንገሩ ሳይሆን ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ ነው።

ሁላችንም ልናውጀው የሚገባው ዋና መልእክት በይሖዋ አምላክ፣ በኢየሱስ ክርስቶስና በመንግሥቱ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ እውነቶች በአገልግሎታችን፣ በጉባኤ ስብሰባዎቻችንና በግል ሕይወታችን በጉልህ ሊንጸባረቁ ይገባል። በዚህ መንገድ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የምናገኘው ሥልጠና በእርግጥ እየተጠቀመን እንዳለ እናሳያለን።

ሰዎች ሁሉ ሊሰሙት የሚገባ መልእክት

  • ይሖዋ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ነው።

  • እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ ነው።

  • ይሖዋ ወደር የሌለው ፍቅር የሚያሳይ፣ ታላቅ ጥበብ ያለው፣ ፍትሑ ፍጹም የሆነና ኃይሉ አቻ የማይገኝለት አምላክ ነው።

  • ለምናደርገው ለእያንዳንዱ ነገር በይሖዋ ፊት ተጠያቂዎች ነን።

ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ . . .

  • በፍቅር ተነሳስተን የምናደርገው ሊሆን ይገባል።

  • በዓለም ያሉትን ነገሮች በመውደድ በተከፈለ ልብ ሳይሆን በሙሉ ልብ ልናደርገው ይገባል።

  • በእርሱ ፊት ሞገስ ማግኘት ለእኛ ምን ያህል ውድ ነገር እንደሆነ የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይገባል።

ሰዎች የሚከተሉትን ነጥቦች እንዲያስተውሉ እርዳቸው:-

  • ከአምላክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት የሚቻለው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ብቻ ነው።

  • ከኃጢአትና ከሞት ነፃ መውጣት የሚቻለው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው።

  • የአምላክ ፈቃድ ሰው ሁሉ ክርስቶስ ጌታ መሆኑን አምኖ ይቀበል ዘንድ ነው። ይህ ደግሞ የሚገለጸው ጌታ ብሎ በመጥራት ብቻ ሳይሆን ትእዛዛቱን በመጠበቅ ነው።

  • ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እውነት ቢሆንም ሕዝበ ክርስትና ስለ እርሱ የምታስተምረው አብዛኛው ነገር የተዛባ ነው።

እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:-

  • ኢየሱስ ክርስቶስ የጉባኤው ራስ መሆኑን በግልጽ እንደምገነዘብ አሳያለሁን?

  • ለክርስቶስ መሥዋዕት ያለኝ አድናቆት በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታልን?

  • አስተሳሰቤንና ድርጊቴን የአምላክ ልጅ ከተወው ምሳሌ ጋር ይበልጥ ማስማማት የምችለው እንዴት ነው?

ሰዎች ሁሉ ሊሰሙት የሚገባ መልእክት

  • የአምላክ መንግሥት ዛሬ በሰማይ እየገዛ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ሰብዓዊ አገዛዝን በሙሉ አስወግዶ ምድርን ማስተዳደር ይጀምራል።

  • የአምላክ መንግሥት ምድር አምላክን በሚወዱና እርስ በርሳቸው በሚፋቀሩ ሰዎች የተሞላች ገነት እንድትሆን ያደርጋል።

  • የሰው ልጅ በጎ ፍላጎቶች በሙሉ የሚሟሉት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ብቻ ነው።

  • ዛሬ የምናደርገው ነገር የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች መሆን የምንፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:-

  • አኗኗሬ በሕይወቴ ውስጥ የአምላክን መንግሥት እንደማስቀድም ያሳያልን?

  • ይህንን በተሟላ መንገድ ለማድረግ በሕይወቴ ውስጥ ላስተካክላቸው የምችላቸው ነገሮች ይኖራሉን?

  • ሌሎች በሕይወታቸው የአምላክን መንግሥት እንዲያስቀድሙ ለማነሳሳት ምን ላደርግ እችላለሁ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ