የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 8

      ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?

      አንድ አባት ወደ ጉባኤ ስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ልጁን ሲያለባብስ

      አይስላንድ

      አንዲት እናትና ልጇ ወደ ስብሰባ ለመሄድ ሲዘጋጁ

      ሜክሲኮ

      ጥሩ አለባበስ ያላቸው በጊኒ ቢሳው ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች

      ጊኒ ቢሳው

      በፊሊፒንስ ያለ አንድ ቤተሰብ ወደ ስብሰባ ሲሄድ

      ፊሊፒንስ

      የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ጥሩ አለባበስ እንደሚኖራቸው አስተውለሃል? በዚህ ብሮሹር ላይ ያሉትን ሥዕሎች ስትመለከትም ይህን ልብ ብለህ ይሆናል። ለአለባበሳችን ይህን ያህል ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?

      ለአምላካችን አክብሮት እንዳለን ለማሳየት። አምላክ ከውጫዊው ገጽታችን ባሻገር ልባችንን እንደሚመለከት የተረጋገጠ ነው። (1 ሳሙኤል 16:7) ይሁን እንጂ አምላክን ለማምለክ በምንሰበሰብበት ወቅት ለእሱም ሆነ ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት ማሳየት እንፈልጋለን። ፍርድ ቤት ብንቀርብ ለዳኛው ሥልጣን አክብሮት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ እንደምንለብስ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ወደ ስብሰባዎች ስንሄድ የሚኖረን አለባበስ “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነውን ይሖዋ አምላክንና የአምልኮ ቦታውን ምን ያህል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ያሳያል።—ዘፍጥረት 18:25

      የምንመራባቸውን እሴቶች በአለባበሳችን ለማሳየት። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች “በልከኝነትና በማስተዋል” እንዲለብሱ ያበረታታል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) “በልከኝነት” መልበስ ሲባል አላስፈላጊ ትኩረት የሚስብ ይኸውም የይታይልኝ መንፈስ የሚንጸባረቅበት፣ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ወይም ሰውነት የሚያሳይ ልብስ አለመልበስ ማለት ነው። “በማስተዋል” መልበስ ሲባል ደግሞ የሚያምር ሆኖም ቅጥ ያጣ ወይም ዝርክርክ ያልሆነ አለባበስ ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። እርግጥ ነው፣ በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ብንመራም በአለባበስ ረገድ የየራሳችን የተለያዩ ምርጫዎች ይኖሩናል። አለባበሳችን የሚያምርና ሥርዓታማ መሆኑ ‘አዳኛችን የሆነውን አምላክ ትምህርት’ ያለ ምንም ቃል ‘ውበት የሚያጎናጽፈው’ ከመሆኑም ሌላ ‘አምላክን ያስከብራል።’ (ቲቶ 2:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:12) ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት መስጠታችን ሌሎች ለይሖዋ አምልኮ ባላቸው አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል።

      ያም ሆኖ አለባበስህ ለስብሰባ እንደማይመጥን በማሰብ ወደ ስብሰባ አዳራሽ ከመምጣት ወደኋላ አትበል። ሥርዓታማ፣ ንጹሕና የሚማርክ ልብስ መልበስ ብዙ ገንዘብ አይጠይቅም።

      • ለአምላክ በምናቀርበው አምልኮ ረገድ አለባበሳችን ምን ቦታ አለው?

      • ከአለባበሳችን ጋር በተያያዘ የምንመራባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

  • ለስብሰባዎች ጥሩ አድርገን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 9

      ለስብሰባዎች ጥሩ አድርገን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

      አንድ የይሖዋ ምሥክር ለጉባኤ ስብሰባ ሲዘጋጅ

      ካምቦዲያ

      አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለጉባኤ ስብሰባ ስትዘጋጅ
      አንዲት የይሖዋ ምሥክር በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተሳትፎ ስታደርግ

      ዩክሬን

      ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ ከሆነ የምታጠኑትን ክፍል ቀደም ብለህ ሳትዘጋጅ አትቀርም። ከጉባኤ ስብሰባዎችም የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ስብሰባ ከመሄድህ በፊት ተመሳሳይ ዝግጅት ብታደርግ ጥሩ ነው። ለስብሰባዎች በመዘጋጀት ረገድ ጥሩ ልማድ ካዳበርን የተሻለ ጥቅም ማግኘት እንችላለን።

      የምትዘጋጅበትን ጊዜና ቦታ ወስን። ትኩረትህ ሳይከፋፈል መዘጋጀት የምትችለው መቼ ነው? የቀኑን ሥራ ከመጀመርህ በፊት ማለዳ ላይ መዘጋጀት ይሻልሃል ወይስ ምሽት ላይ ልጆች ሁሉ ከተኙ በኋላ? ረዘም ላለ ጊዜ ማጥናት ባትችል እንኳ ለዝግጅት ምን ያህል ጊዜ ልትመድብ እንደምትችል ወስን፤ ከዚያም ያንን ጊዜ ምንም ነገር እንዳይሻማብህ ለማድረግ ሞክር። ጸጥ ያለ ቦታ ምረጥ፤ እንዲሁም ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ሞባይል ስልክህን በማጥፋት ትኩረትህን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ነገሮችን አስወግድ። ጥናትህን ከመጀመርህ በፊት መጸለይህ በቀን ውሎህ ያሳለፍካቸውን ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ለመርሳትና በአምላክ ቃል ላይ ትኩረት ለማድረግ ይረዳሃል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

      በጽሑፍህ ላይ ምልክት በማድረግ ሐሳብ ለመስጠት ተዘጋጅ። መጀመሪያ ላይ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ጠቅለል ያለ ግንዛቤ እንዲኖርህ ለማድረግ ሞክር። ስለ ትምህርቱ ወይም ስለ ምዕራፉ ርዕስ ቆም ብለህ አስብ፤ እያንዳንዱ ንዑስ ርዕስ ከትምህርቱ ጭብጥ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ለማስተዋል ሞክር፤ እንዲሁም ሥዕሎቹንና ዋና ዋና ነጥቦቹን የሚያጎሉትን የክለሳ ጥያቄዎች ተመልከት። ከዚያም እያንዳንዱን አንቀጽ እያነበብክ የጥያቄውን መልስ ለማግኘት ሞክር። ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥተህ አንብብ፤ እንዲሁም ከትምህርቱ ጋር እንዴት እንደሚያያዙ ቆም ብለህ አስብ። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) የጥያቄውን መልስ አንቀጹ ውስጥ ስታገኘው ምልክት አድርግበት፤ ቁልፍ በሆኑ ቃላት ወይም ሐረጎች ላይ ማስመርህ በኋላ ላይ መልሱን በቀላሉ ለማስታወስ ይረዳሃል። ከዚያም ስብሰባው ላይ ሐሳብህን መግለጽ የምትፈልግ ከሆነ እጅህን አውጥተህ በራስህ አባባል አጠር ያለ መልስ መስጠት ትችላለህ።

      በየሳምንቱ በስብሰባዎቻችን ላይ ውይይት የሚደረግባቸውን የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በመመርመር የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት በምታስቀምጥበት “ሀብት ማከማቻ” ውስጥ አዳዲስ ትምህርቶችን ትጨምራለህ።—ማቴዎስ 13:51, 52

      • ለስብሰባዎች በመዘጋጀት ረገድ ምን ዓይነት ልማድ ማዳበር ትችላለህ?

      • በስብሰባ ላይ ሐሳብ ለመስጠት መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ከላይ በተገለጸው ዘዴ በመጠቀም ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወይም ለጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተዘጋጅ። በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ የምትሰጠውን ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያስጠናህ ሰው ጋር ተዘጋጅ።

  • የቤተሰብ አምልኮ ምንድን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 10

      የቤተሰብ አምልኮ ምንድን ነው?

      አንድ ቤተሰብ፣ የቤተሰብ አምልኮ ሲያደርግ

      ደቡብ ኮሪያ

      አንድ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ሲያጠኑ

      ብራዚል

      አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና

      አውስትራሊያ

      አንድ ቤተሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ውይይት ሲያደርግ

      ጊኒ

      ይሖዋ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ ጊዜ በማሳለፍ መንፈሳዊነታቸውን እንዲያጠናክሩና እርስ በርስ ይበልጥ እንዲቀራረቡ እንደሚፈልግ ገልጿል። (ዘዳግም 6:6, 7) የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ቤተሰቦችም በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ የሚያደርጉበት ጊዜ የሚመድቡት ለዚህ ነው፤ በእነዚህ ወቅቶች ቤተሰቦች በሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ዘና ባለ መንፈስ ይወያያሉ። ብቻህን የምትኖር ቢሆንም እንኳ እንዲህ ያለው ፕሮግራም በምትፈልገው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ለማጠናከር አጋጣሚ ይፈጥርልሃል።

      ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ያስችላል። “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።” (ያዕቆብ 4:8) በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ስላደረጋቸው ነገሮች በጥልቀት መማራችን ስለ እሱ ይበልጥ ለማወቅ ያስችለናል። ለመጀመሪያ ጊዜ የቤተሰብ አምልኮ ስታደርጉ መጽሐፍ ቅዱስን አብራችሁ ማንበብ ትችላላችሁ፤ ለምሳሌ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ የሚወጣውን ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም መከተል ይቻላል። በምታነብቡበት ጊዜ ሁሉም የቤተሰብ አባል የተወሰነ ክፍል እንዲደርሰው ማድረግ ትችላላችሁ፤ ከዚያም ከንባቡ ባገኛችሁት ነገር ላይ ተወያዩ።

      የቤተሰብ አባላት እርስ በርሳቸው እንዲቀራረቡ ያደርጋል። ባሎችና ሚስቶች እንዲሁም ወላጆችና ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ ማጥናታቸው ይበልጥ እንዲቀራረቡ ያደርጋቸዋል። የአምልኮ ፕሮግራማቸው ሁሉም በጉጉት የሚጠብቁት እንዲሁም አስደሳችና ሰላማዊ ሊሆን ይገባል። ወላጆች የልጆቻቸውን ዕድሜ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሊወያዩባቸው የሚችሉ ጠቃሚ ርዕሶችን ሊመርጡ ይችላሉ፤ ምናልባትም በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ወይም jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ የሚወጡ ዓምዶችን መጠቀም ይፈልጉ ይሆናል። ልጆቻችሁ በትምህርት ቤት ስላጋጠማቸው ችግር አንስታችሁ እንዴት ሊቋቋሙት እንደሚችሉ መወያየት ትችላላችሁ። በJW ብሮድካስት (tv.jw.org) ላይ የሚተላለፈውን ፕሮግራም ከተመለከታችሁ በኋላ ለምን አትወያዩበትም? እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ የሚዘመሩ መዝሙሮችን መለማመድ የምትችሉ ሲሆን ከቤተሰብ አምልኮው በኋላም ቀለል ያሉ ምግቦችን በማቅረብ አብራችሁ ጊዜ ልታሳልፉ ትችላላችሁ።

      በየሳምንቱ አብራችሁ ይሖዋን በማምለክ የምታሳልፉት ይህ ልዩ ጊዜ የቤተሰባችሁ አባላት በሙሉ በአምላክ ቃል እንዲደሰቱ ያደርጋል፤ ይሖዋም ጥረታችሁን አብዝቶ ይባርክላችኋል።—መዝሙር 1:1-3

      • ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ የምንመድበው ለምንድን ነው?

      • ወላጆች ይህ ጊዜ ለሁሉም የቤተሰብ አባላት አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      በጉባኤ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ጠይቃቸው። በተጨማሪም ልጆችህን ስለ ይሖዋ ለማስተማር የሚጠቅሙህ ጽሑፎች ከፈለግክ ከስብሰባ አዳራሽ መውሰድ ትችላለህ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ