የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ጥር 2018
ከጥር 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 1–3
“መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል”
(ማቴዎስ 3:1, 2) በዚያ ወቅት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ፤ 2 “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” ይል ነበር።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማቴ 3:1, 2
እየሰበከ፦ “መስበክ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የሕዝብ መልእክተኛ በመሆን አዋጅ ማወጅ” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። ቃሉ አዋጁ በሚነገርበት መንገድ ላይ ያተኩራል፦ አብዛኛውን ጊዜ ለተወሰኑ ሰዎች መስበክን ሳይሆን በአደባባይ ለሕዝብ ሁሉ ማወጅን ያመለክታል።
መንግሥት፦ ባሲሌያ የሚለው የግሪክኛ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው እዚህ ቦታ ላይ ሲሆን ቃሉ ንጉሣዊ መንግሥትን እንዲሁም የአንድን ንጉሥ ግዛትና በሥሩ የሚተዳደሩትን ሕዝቦች ያመለክታል። ይህ የግሪክኛ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 162 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 55ቱ የሚገኙት በማቴዎስ ዘገባ ውስጥ ነው፤ ቃሉ አብዛኛውን ጊዜ የተሠራበት በሰማይ ያለውን የአምላክ አገዛዝ ለማመልከት ነው። ማቴዎስ ይህን አገላለጽ በተደጋጋሚ ከመጠቀሙ የተነሳ ወንጌሉ የመንግሥቱ ወንጌል ተብሎ ሊጠራ ይችላል።
መንግሥተ ሰማያት፦ ይህ አገላለጽ የሚገኘው በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ሲሆን ወደ 30 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። በማርቆስና በሉቃስ ወንጌል ውስጥ “የአምላክ መንግሥት” በሚለው ሐረግ ተገልጿል፤ ይህም “የአምላክ መንግሥት” የሚገኘው በመንፈሳዊው ሰማይ እንደሆነና ከዚያው ሆኖ እንደሚገዛ ይጠቁማል።—ማቴ 21:43፤ ማር 1:15፤ ሉቃስ 4:43፤ ዳን 2:44፤ 2ጢሞ 4:18
ስለቀረበ፦ እዚህ ላይ ይህ አገላለጽ በሰማይ በሚገኘው የአምላክ መንግሥት ላይ ወደፊት ንጉሥ ሆኖ የሚሾመው ገዢ የሚገለጥበት ጊዜ መቅረቡን ያመለክታል።
(ማቴዎስ 3:4) ዮሐንስ ከግመል ፀጉር የተሠራ ልብስ ይለብስ፣ ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ይታጠቅ ነበር። ምግቡ አንበጣና የዱር ማር ነበር።
nwtsty ሚዲያ
የአጥማቂው ዮሐንስ አለባበስና ውጫዊ ገጽታ
ዮሐንስ ከግመል ፀጉር የተሠራ ልብስ ይለብስ የነበረ ሲሆን ወገቡ ላይ የቆዳ ቀበቶ ወይም መቀነት ይታጠቅ ነበር፤ ቀበቶው አነስ ያሉ ዕቃዎችን ለመያዝ ሊያገለግል ይችላል። ነቢዩ ኤልያስም ተመሳሳይ ልብስ ይለብስ ነበር። (2ነገ 1:8) በዚያ ዘመን ከግመል ፀጉር የተሠራ ሸካራ ልብስ የሚለብሱት በአብዛኛው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ነበሩ። በአንጻሩ ግን ከሐር ወይም ከተልባ እግር የተሠሩ ለስላሳ ልብሶችን የሚለብሱት ሀብታሞች ነበሩ። (ማቴ 11:7-9) ዮሐንስ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ናዝራዊ ስለነበር ፀጉሩን ተቆርጦ ላያውቅ ይችላል። የዮሐንስ አለባበስና ውጫዊ ገጽታ፣ ሙሉ በሙሉ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ ቀላል ሕይወት እንደሚመራ የሚያሳይ ነበር።
አንበጣ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አንበጣ” የሚለው ቃል አጭር አንቴና ያላቸውን የፌንጣ ዝርያዎች ሁሉ የሚያጠቃልል ሲሆን በተለይ ደግሞ በመንጋ ሆነው የሚጓዙትን ፌንጣዎች ያመለክታል። በኢየሩሳሌም የተደረገ አንድ ጥናት፣ የበረሃ አንበጦች 75 በመቶ ፕሮቲን እንዳላቸው ይጠቁማል። በዛሬው ጊዜ ሰዎች አንበጦችን የሚመገቡት የአንበጦቹን ጭንቅላት፣ እግር፣ ክንፍና ሆድ ዕቃ አስወግደው ነው። የቀረው ማለትም ደረታቸው አካባቢ ያለው ክፍል ጥሬውን ወይም በስሎ ሊበላ ይችላል። እነዚህ ነፍሳት ሽሪምፕ ከተባለው የዓሣ ዝርያ ወይም ከሸርጣን ጋር ተመሳሳይ ጣዕም እንዳላቸውና በፕሮቲን የበለጸጉ እንደሆኑ ይነገራል።
የዱር ማር
ሥዕሉ ላይ የሚታየው የዱር ንቦች የሠሩት የማር እንጀራና (1) እና ማር የሚያንጠባጥብ የማር እንጀራ (2) ነው። ዮሐንስ ይበላ የነበረው ማር፣ አፒስ ሜሊፌራ ሲሪያካ ተብለው በሚጠሩ በዚያ አካባቢ የሚገኙ የዱር ንብ ዝርያዎች የተሠራ ሳይሆን አይቀርም። ተናዳፊ የሆኑት እነዚህ የንብ ዝርያዎች የይሁዳ በረሃን ሞቃታማና ደረቅ የአየር ንብረት ተቋቁመው መኖር ይችላሉ፤ ሆኖም እነዚህን የንብ ዝርያዎች ቀፎ ውስጥ አስገብቶ ማርባት አስቸጋሪ ነው። ይሁንና በዘጠነኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በእስራኤል የሚኖሩ ሰዎች ንቦችን በሞላላ ሸክላዎች ውስጥ በማስቀመጥ ያረቡ ነበር። በዮርዳኖስ ሸለቆ ውስጥ በሚገኝ በወቅቱ ከተማ በነበረ አንድ አካባቢ ላይ (በአሁኑ ጊዜ ቴል ረኾቭ ተብሎ ይጠራል) የእነዚህ ሸክላዎች ስብርባሪ በብዛት ተገኝቷል። ሰዎች በእነዚህ ቀፎዎች ውስጥ ማር የሚሠሩትን የንብ ዝርያዎች ያስመጡ የነበረው በአሁኑ ጊዜ ቱርክ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሳይሆን አይቀርም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 1:3) ይሁዳ ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስ ኤስሮንን ወለደ፤ ኤስሮን ራምን ወለደ፤
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 1:3
ትዕማር፦ ማቴዎስ በጻፈው የመሲሑ የትውልድ ሐረግ ዝርዝር ውስጥ ከተጠቀሱት አምስት ሴቶች መካከል የመጀመሪያዋ። የቀሩት አራቱ ደግሞ እስራኤላዊ ያልሆኑት ረዓብና ሩት (ቁ. 5)፤ ‘የኦርዮ ሚስት’ የሆነችው ቤርሳቤህ (ቁ. 6) እና ማርያም (ቁ. 16) ናቸው። ማቴዎስ በአብዛኛው የወንዶችን ስም በያዘው የትውልድ ሐረግ ዝርዝሩ ውስጥ የእነዚህን ሴቶች ስም ያካተተው ሁሉም የኢየሱስ ቅድመ አያት ለመሆን የበቁት በአስገራሚ መንገድ ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም።
(ማቴዎስ 3:11) እኔ በበኩሌ ንስሐ በመግባታችሁ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይበረታል፤ እኔ ጫማውን ለማውለቅ እንኳ ብቁ አይደለሁም። እሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 3:11
አጠምቃችኋለሁ፦ ወይም “አጠልቃችኋለሁ።” ባፕቲዞ የሚለው የግሪክኛ ቃል “መንከር፤ መዝፈቅ” የሚል ትርጉም አለው። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፣ ጥምቀት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅን እንደሚያመለክት ይጠቁማሉ። በአንድ ወቅት ዮሐንስ በዮርዳኖስ ሸለቆ ውስጥ በሳሊም አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ቦታ “ብዙ ውኃ በመኖሩ” ሰዎችን ያጠምቅ ነበር። (ዮሐ 3:23) ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ባጠመቀው ጊዜ “ሁለቱም ወርደው ውኃው ውስጥ [እንደገቡ]” እናነባለን። (ሥራ 8:38) የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም 2ነገ 5:14 ላይ በሚገኘው ንዕማን “ዮርዳኖስ ውስጥ ሰባት ጊዜ [እንደጠለቀ]” በሚናገረው ዘገባ ላይ ይህንኑ የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 1:1-17) የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ፦2 አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብ ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤ 3 ይሁዳ ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስ ኤስሮንን ወለደ፤ ኤስሮን ራምን ወለደ፤ 4 ራም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤ 5 ሰልሞን ከረዓብ ቦዔዝን ወለደ፤ ቦዔዝ ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድ እሴይን ወለደ፤ 6 እሴይ ንጉሥ ዳዊትን ወለደ። ዳዊት ከኦርዮ ሚስት ሰለሞንን ወለደ፤ 7 ሰለሞን ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓም አቢያህን ወለደ፤ አቢያህ አሳን ወለደ፤ 8 አሳ ኢዮሳፍጥን ወለደ፤ ኢዮሳፍጥ ኢዮራምን ወለደ፤ ኢዮራም ዖዝያን ወለደ፤ 9 ዖዝያ ኢዮዓታምን ወለደ፤ ኢዮዓታም አካዝን ወለደ፤ አካዝ ሕዝቅያስን ወለደ፤ 10 ሕዝቅያስ ምናሴን ወለደ፤ ምናሴ አምዖንን ወለደ፤ አምዖን ኢዮስያስን ወለደ፤ 11 ኢዮስያስ አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን በተጋዙበት ዘመን ኢኮንያንን እና ወንድሞቹን ወለደ። 12 ወደ ባቢሎን ከተጋዙ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያል ዘሩባቤልን ወለደ፤ 13 ዘሩባቤል አብዩድን ወለደ፤ አብዩድ ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄም አዞርን ወለደ፤ 14 አዞር ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅ አኪምን ወለደ፤ አኪም ኤልዩድን ወለደ፤ 15 ኤልዩድ አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛር ማታንን ወለደ፤ ማታን ያዕቆብን ወለደ፤ 16 ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ፤ ዮሴፍም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደችው የማርያም ባል ነበር። 17 ስለዚህ ጠቅላላው ትውልድ፣ ከአብርሃም እስከ ዳዊት 14 ትውልድ፣ ከዳዊት አንስቶ አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን እስከተጋዙበት ጊዜ ድረስ 14 ትውልድ እንዲሁም ወደ ባቢሎን ከተጋዙበት ዘመን እስከ ክርስቶስ ድረስ 14 ትውልድ ነው።
ከጥር 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 4-5
“ከኢየሱስ የተራራ ስብከት የምናገኘው ትምህርት”
(ማቴዎስ 5:3) “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 5:3
ደስተኞች፦ ‘ደስታ’ የሚለው ቃል አንድ ሰው አስደሳች ጊዜ በሚያሳልፍበት ወቅት የሚሰማውን ጥሩ ስሜት ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከሰዎች ጋር በተያያዘ ሲሠራበት፣ አንድ ሰው የአምላክን በረከትና ሞገስ በማግኘቱ የሚሰማውን ስሜት ያመለክታል። በተጨማሪም ይህ ቃል አምላክንና በሰማይ ክብር ያገኘውን ኢየሱስን ለመግለጽ ተሠርቶበታል።—1 ጢሞ 1:11፤ 6:15
መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ፦ ወይም “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ።” “ንቁ የሆኑ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ ቃል በቃል “ድሆች የሆኑ (የተቸገሩ፤ ያጡ፤ የሚለምኑ)” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በዚህ አገባቡ የተሠራበት የጎደላቸው ነገር እንዳለ በሚገባ የተገነዘቡ ሰዎችን ለማመልከት ነው። ይኸው ቃል ሉቃስ 16:20, 22 ላይ አልዓዛር የሚባለውን “ለማኝ” ለመግለጽ ተሠርቶበታል። በአንዳንድ ትርጉሞች ላይ “በመንፈስ ድሆች የሆኑ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ በመንፈሳዊ ድሆች እንደሆኑና ከአምላክ አመራር ውጭ መኖር እንደማይችሉ በሚገባ የተገነዘቡ ሰዎችን ያመለክታል።
(ማቴዎስ 5:7) “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 5:7
መሐሪዎች፦ “መሐሪ” እና “ምሕረት” ተብለው የተተረጎሙት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ አገባባቸው በደልን ይቅር ከማለት ወይም ቅጣትን ከማቅለል ያለፈ ትርጉም አላቸው። አብዛኛውን ጊዜ፣ ችግር ላይ የወደቀን ሰው ለመርዳት የሚያነሳሳንን የርኅራኄና የአዘኔታ ስሜት ያመለክታሉ።
(ማቴዎስ 5:9) “ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ የአምላክ ልጆች ይባላሉና።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 5:9
ሰላም ፈጣሪዎች፦ ይህ አገላለጽ ሰላማዊ ሁኔታ ተጠብቆ እንዲቀጥል ከማድረግ ባለፈ ሰላም በሌለበት ቦታ ሰላም ለማስፈን ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ያመለክታል።
ልጆቻችሁ ሰላማውያን እንዲሆኑ አስተምሯቸው
ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው ‘ሰላምን እንዲፈልጉና እንዲከተሉ’ አስፈላጊውን ማሠልጠኛ የመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። (1 ጴጥሮስ 3:11) የጥርጣሬ፣ የፍርሃትና የጥላቻ ስሜቶችን ለማሸነፍ በመጣር ደስታ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም ሰላም ፈጣሪ በመሆን የሚገኘው ደስታ ግን ከዚያ የላቀ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 4:9) ከዚያም “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 4:9
አንድ ጊዜ . . . ብታመልከኝ፦ “ማምለክ” ተብሎ ሊተረጎም የሚችለው የግሪክኛ ግስ እዚህ ላይ የሚያመለክተው ቀጣይ የሆነ ድርጊትን ሳይሆን አንድ ጊዜ ብቻ የሚከናወን ድርጊትን ነው። ይህ ቃል “አንድ ጊዜ . . . ብታመልከኝ” ተብሎ መተርጎሙ ዲያብሎስ ኢየሱስን የጠየቀው በቀጣይነት እንዲያመልከው ሳይሆን አንድ ጊዜ ብቻ ‘እንዲያመልከው’ እንደሆነ ያመለክታል።
(ማቴዎስ 4:23) ከዚያም በምኩራቦቻቸው እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 4:23
እያስተማረ . . . እየሰበከ፦ ማስተማር ከስብከት የሚለየው አንድ አስተማሪ መልእክቱን ከማወጅ የበለጠ ነገር ስለሚያደርግ ነው፤ አንድ አስተማሪ መመሪያ ይሰጣል፣ ያብራራል እንዲሁም ማስረጃ ያቀርባል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 5:31-48) “በተጨማሪም ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ይስጣት’ ተብሏል። 32 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ምንዝር ለመፈጸም እንድትጋለጥ ያደርጋታል፤ እንዲሁም በዚህ መንገድ የተፈታችን ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። 33 “ከዚህም ሌላ በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤ ይልቁንም ለይሖዋ የተሳልከውን ፈጽም’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 34 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ፈጽሞ አትማሉ። በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የአምላክ ዙፋን ነውና፤ 35 በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግሩ ማሳረፊያ ነችና፤ በኢየሩሳሌምም ቢሆን አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነችና። 36 በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከፀጉርህ አንዷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ማድረግ አትችልምና። 37 ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው ነው። 38 “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 39 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት። 40 አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሊያቀርብህና እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢፈልግ መደረቢያህንም ጨምረህ ስጠው፤ 41 እንዲሁም አንድ ባለሥልጣን አንድ ኪሎ ሜትር እንድትሄድ ቢያስገድድህ ሁለት ኪሎ ሜትር አብረኸው ሂድ። 42 ለሚለምንህ ስጥ፤ ሊበደርህ የሚፈልገውንም ሰው ፊት አትንሳው። 43 “‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 44 እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤ 45 ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል። 46 የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ? ቀረጥ ሰብሳቢዎችስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 47 ደግሞስ ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 48 በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።
ከጥር 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 6-7
“ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት ፈልጉ”
(ማቴዎስ 6:10) መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።
ወደ አምላክ የመጸለይ ውድ መብት
12 በጸሎታችን ውስጥ ልንጠቅሳቸው የሚገቡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው? ከይሖዋና ከእሱ ፈቃድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው። ስላደረገልን ነገሮች በሙሉ ይሖዋን ከልብ ልናመሰግነው ይገባል። (1 ዜና መዋዕል 29:10-13) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማራቸው ጸሎት ይህን ግልጽ ያደርግልናል። (ማቴዎስ 6:9-13ን አንብብ።) ኢየሱስ በቅድሚያ የአምላክ ስም እንዲቀደስ መጸለይ እንዳለብን አስተምሯል። በመቀጠልም የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና የይሖዋ ፈቃድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲፈጸም መጸለይ እንዳለብን ተናግሯል። ኢየሱስ ስለ ግል ጉዳዮቻችን መጸለይ ያለብን በጣም አስፈላጊ ስለሆኑት ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከጸለይን በኋላ መሆን እንዳለበት አስተምሯል። በጸሎታችን ውስጥ ለይሖዋና ከእሱ ፈቃድ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ከሁሉ በላይ የሚያሳስበን ይህ እንደሆነ እናሳያለን።
(ማቴዎስ 6:24) “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 6:24
ባሪያ፦ የግሪክኛው ግስ፣ ባሪያ ሆኖ ማለትም የአንድ ጌታ ብቻ ንብረት ሆኖ ማገልገልን ያመለክታል። እዚህ ላይ ኢየሱስ አንድ ክርስቲያን ቁሳዊ ሀብትን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት እየመራ ለአምላክ ሊሰጠው የሚገባውን የሙሉ ነፍስ አምልኮ ማቅረብ እንደማይችል እየተናገረ ነበር።
(ማቴዎስ 6:33) “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 6:33
ፈልጉ፦ የግሪክኛው ግስ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት የሚያመለክት ሲሆን “በቀጣይነት ፈልጉ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ለተወሰነ ጊዜ መንግሥቱን ሲፈልጉ ከቆዩ በኋላ ወደ ሌሎች ጉዳዮች ዞር አይሉም። ከዚህ ይልቅ በሕይወታቸው ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ምንጊዜም ቅድሚያ ይሰጣሉ።
ጽድቅ፦ የአምላክን ጽድቅ የሚፈልጉ ሰዎች የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም እንዲሁም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ያወጣውን መሥፈርት ለመጠበቅ ፈቃደኞች ናቸው። ኢየሱስ ያስተማረው ይህ ትምህርት፣ የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ይሞክሩ የነበሩት ፈሪሳውያን ካላቸው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ ነበር።—ማቴ 5:20
ቁሳዊ ነገሮችን ሳይሆን የአምላክን መንግሥት ፈልጉ
18 ማቴዎስ 6:33ን አንብብ። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምንጊዜም መንግሥቱን ማስቀደም ይኖርባቸዋል። እንዲህ ካደረግን ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ‘እነዚህ ነገሮች ሁሉ ይሰጡናል።’ ኢየሱስ እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ቀደም ባለው ቁጥር ላይ “በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ [ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች] ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ እያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከራሳችን እንኳ አስቀድሞ ያውቃል። (ፊልጵ. 4:19) የትኛው ልብሳችን እያለቀ እንደሆነ፣ ምን ዓይነት ምግብ እንደሚያስፈልገን እንዲሁም ለቤተሰባችን የሚበቃው ምን ዓይነት መጠለያ እንደሆነ ያውቃል። ደግሞም የሚያስፈልገንን ነገር ማግኘት አለማግኘታችንን በትኩረት ይከታተላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 7:12) “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው። ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል የሚሉት ይህንኑ ነው።
በአገልግሎታችሁ ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ አድርጉ
14 አንድ ቀን የሆነ ሰው ስልክ ደወለልን እንበል፤ ሆኖም ሰውየው ማን እንደሆነ በድምፁ መለየት አልቻልንም። ደዋዩ ማንነቱን ሳይነግረን ስለምንወዳቸው የምግብ ዓይነቶች ይጠይቀናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ሰውየው ማን እንደሆነና ምን እንደሚፈልግ ማሰባችን አይቀርም። አክብሮት ለማሳየት ስንል ግለሰቡን ለተወሰነ ጊዜ ብናነጋግረውም ትንሽ ቆይተን ግን ውይይቱን ማቆም እንደምንፈልግ እንጠቁመው ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የደወለው ሰው ማንነቱን ወዲያውኑ ከነገረን በኋላ ሙያው ከአመጋገብ ጋር የተያያዘ እንደሆነና አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን ሊያካፍለን እንደሚፈልግ በአክብሮት ገለጸልን እንበል። እንዲህ ዓይነቱን ሰው ለማዳመጥ ይበልጥ ፈቃደኞች ልንሆን እንችላለን። ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በቀጥታ ሆኖም አክብሮት በተሞላበት መንገድ ቢነግሩን ደስ ይለናል። ታዲያ እኛስ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች እንዲህ ያለ አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
15 በብዙ ቦታዎች ሰዎች ወደ እነሱ የሄድንበትን ምክንያት በግልጽ እንድንነግራቸው ይፈልጋሉ። እርግጥ ነው፣ እኛ የያዝነው መልእክት ጠቃሚ ሲሆን ሰዎች ደግሞ ይህን መልእክት አያውቁትም፤ ሆኖም ራሳችንን በደንብ ሳናስተዋውቅ “በዓለም ላይ ያለ ማንኛውንም ችግር መፍታት ቢችሉ ኖሮ እርስዎ የትኛውን ችግር ያስወግዱ ነበር?” እንደሚለው ዓይነት ጥያቄ በማንሳት በድንገት ውይይቱን ብንጀምር የቤቱ ባለቤት ምን ይሰማዋል? እኛ ለግለሰቡ እንዲህ ያለ ጥያቄ የምናቀርብበት ዓላማ የሰውየውን አመለካከት ለመረዳትና ውይይቱን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለመምራት እንደሆነ እናውቃለን። ይሁንና የቤቱ ባለቤት ‘ይሄ ደግሞ ማነው? እንዲህ ብሎ የሚጠይቀኝ ለምንድን ነው? እያወራ ያለው ስለምንድን ነው?’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ስለዚህ የቤቱ ባለቤት ተረጋግቶ እንዲያዳምጠን ለማድረግ መጣር አለብን። (ፊልጵ. 2:3, 4) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
16 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን አቀራረብ ውጤታማ ሆኖ አግኝቶታል። ከቤቱ ባለቤት ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የተባለውን ትራክት እያሳየ እንዲህ ይለዋል፦ “ዛሬ በዚህ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይህንን ትራክት እየሰጠን ነው። ትራክቱ ብዙ ሰዎች የሚያነሷቸውን ስድስት ጥያቄዎች የሚያብራራ ነው። እርስዎም ይህን ትራክት መውሰድ ይችላሉ።” አብዛኞቹ ሰዎች ለምን እንደመጣን ሲያውቁ ዘና ማለት እንደሚጀምሩ ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ተናግሯል። ከዚህ በኋላ ውይይቱን መቀጠል ብዙውን ጊዜ ቀላል ይሆናል። ቀጥሎም ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ “እነዚህን ጥያቄዎች አስበውባቸው ያውቃሉ?” በማለት የቤቱን ባለቤት ይጠይቀዋል። የቤቱ ባለቤት ከጥያቄዎቹ አንዱን ከመረጠ ወንድም ትራክቱን ገልጦ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚያ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ያወያየዋል። ግለሰቡ ዝም ካለ ደግሞ ወንድም ሰውየው እንዳይሸማቀቅ እሱ ራሱ አንዱን ጥያቄ ይመርጥና ውይይቱን ይቀጥላል። እርግጥ ነው፣ ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ በርካታ መንገዶች አሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች፣ የመጣንበትን ዓላማ ከመናገራችን በፊት ከባሕሉ አንጻር የሚጠበቁብን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ዋናው ነገር፣ በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች እንድናነጋግራቸው በሚፈልጉት መንገድ አቀራረባችንን ማስተካከላችን ነው።
(ማቴዎስ 7:28, 29) ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤ የሚያስተምራቸው እንደ እነሱ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነበርና።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማቴ 7:28, 29
እጅግ ተደነቁ፦ የግሪክኛው ግስ “ከፍተኛ በሆነ የአድናቆትና የአግራሞት ስሜት መዋጥ” የሚል ትርጉም ያስተላልፋል። እዚህ ላይ ቀጣይነትን የሚያመለክት ግስ መግባቱ ንግግሩ በአድማጮቹ ላይ ዘላቂ የሆነ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው ያሳያል።
በትምህርት አሰጣጡ፦ ይህ አገላለጽ ኢየሱስ ያስተማረበትን መንገድ እንዲሁም የተጠቀመባቸውን የማስተማሪያ ዘዴዎች ያመለክታል፤ ይህም በተራራው ስብከት ላይ ያስተማረውን ትምህርት በአጠቃላይ ይጨምራል።
እንደ እነሱ ጸሐፍት ሳይሆን፦ ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት ጸሐፍት ያደርጉ እንደነበረው የታዋቂ ረቢዎችን ንግግር ጠቅሶ ከመናገር ይልቅ ትምህርቱ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ የይሖዋ ወኪል መሆኑን በሚያሳይ መንገድ እንደ ባለሥልጣን ይናገር ነበር።—ዮሐ 7:16
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 6:1-18) “ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ በሰማያት ካለው አባታችሁ ምንም ብድራት አታገኙም። 2 በመሆኑም ምጽዋት በምትሰጡበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በምኩራቦችና በጎዳናዎች ላይ አስቀድመው መለከት እንደሚያስነፉ ግብዞች አትሁኑ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 3 አንተ ግን ምጽዋት ስትሰጥ ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ፤ 4 ይህም ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ያስችላል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል። 5 “በተጨማሪም በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነሱ ሰዎች እንዲያዩአቸው በምኩራቦችና በየአውራ ጎዳናው ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 6 አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል። 7 በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ጸሎታቸው የሚሰማላቸው ይመስላቸዋል። 8 ስለዚህ እንደ እነሱ አትሁኑ፤ አባታችሁ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና። 9 “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ “‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። 10 መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም። 11 የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን፤ 12 የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን። 13 ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’ 14 “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤ 15 እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም። 16 “በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ እነሱ መጾማቸው በሰው ዘንድ እንዲታወቅላቸው ፊታቸውን ያጠወልጋሉ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 17 አንተ ግን ስትጾም ራስህን ተቀባ፤ ፊትህንም ታጠብ፤ 18 እንዲህ ካደረግክ የምትጾመው በሰው ለመታየት ሳይሆን በስውር ላለው አባትህ ስትል ብቻ ይሆናል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።
ከጥር 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 8-9
“ኢየሱስ ሰዎችን ይወድ ነበር”
(ማቴዎስ 8:1-3) ከተራራው ከወረደ በኋላ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 2 በዚህ ጊዜ በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደ እሱ መጥቶ በመስገድ “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። 3 ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። ወዲያውኑ ከሥጋ ደዌው ነጻ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 8:3
ዳሰሰው፦ የሙሴ ሕግ የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው ሌሎችን እንዳይበክል ከሰው ተገልሎ እንዲኖር ያዝዝ ነበር። (ዘሌ 13:45, 46፤ ዘኁ 5:1-4) ይሁንና የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ሌሎች ተጨማሪ ሕጎችን አውጥተው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ማንኛውም ሰው የሥጋ ደዌ ካለበት ሰው ቢያንስ 1.8 ሜትር መራቅ እንዳለበት የሚገልጽ ሕግ ነበራቸው። ነፋስ እየነፈሰ ከሆነ ደግሞ ርቀቱ 45 ሜትር መሆን እንዳለበት ሕጉ ያዛል። እንዲህ ያሉት ሕጎች የሥጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጸምባቸው ምክንያት ሆነዋል። ለምሳሌ አንድ ረቢ የሥጋ ደዌ ካለባቸው ሰዎች መደበቁን፣ ሌላ ረቢ ደግሞ የሥጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች እንዳይጠጉት ድንጋይ መወርወሩን እንደ ጥሩ ተግባር አድርጎ የሚገልጽ የአይሁዳውያን ታሪክ አለ። በተቃራኒው ግን ኢየሱስ በሥጋ ደዌ የተያዘው ሰው ሁኔታ በጣም ስላሳዘነው ሰውየውን ለመዳሰስ ተነሳስቷል፤ ሌሎች አይሁዳውያን እንዲህ ያለውን ነገር ጨርሶ ሊያስቡት እንኳ አይችሉም። ኢየሱስ እንዲህ ያደረገው ሰውየውን መንካት ሳያስፈልገው በቃል ብቻ ሊፈውሰው እንደሚችል እያወቀ ነው።—ማቴ 8:5-12
እፈልጋለሁ፦ ኢየሱስ የሰውየውን ጥያቄ ከመቀበል ባለፈ የተጠየቀውን ነገር የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፤ ይህም ኢየሱስ ሰውየውን የፈወሰው ግዴታው እንደሆነ ስለተሰማው ብቻ እንዳልሆነ ያመለክታል።
(ማቴዎስ 9:9-13) ኢየሱስ ከዚያ ተነስቶ እየሄደ ሳለ ማቴዎስ የሚባል ሰው በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየና “ተከታዬ ሁን” አለው። በዚህ ጊዜ ተነስቶ ተከተለው። 10 በኋላም በማቴዎስ ቤት እየበላ ሳለ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይበሉ ጀመር። 11 ፈሪሳውያን ግን ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላው ለምንድን ነው?” አሏቸው። 12 ኢየሱስም የተናገሩትን ሰምቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም። 13 እንግዲያው ሄዳችሁ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነውና።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 9:10
እየበላ፦ ‘መብላት’ ወይም ‘በማዕድ መቀመጥ።’ አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር በማዕድ መቀመጡ በሁለቱ መካከል ቅርርብ እንዳለ ይጠቁማል። በመሆኑም በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን አይሁዳዊ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ፈጽሞ በማዕድ ሊቀመጡ ወይም አብረው ሊመገቡ አይችሉም ነበር።
ቀረጥ ሰብሳቢዎች፦ ለሮም ባለሥልጣኖች ቀረጥ የሚሰበስቡ በርካታ አይሁዳውያን ነበሩ። እነዚህ ሰዎች እንደ ጠላት ይታይ ከነበረ የውጭ ኃይል ጋር ተባብረው ከመሥራት በተጨማሪ በሕግ ከተተመነው በላይ ቀረጥ በመሰብሰብ ሕዝቡን ይዘርፉ ስለነበር በሰዎች ዘንድ የተጠሉ ነበሩ። ሌሎች አይሁዳውያን፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችን ከኃጢአተኞችና ከዝሙት አዳሪዎች ጋር በመፈረጅ ይርቋቸው ነበር።—ማቴ 11:19፤ 21:32
(ማቴዎስ 9:35-38) ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ በየከተማውና በየመንደሩ ይዞር ጀመር። 36 ሕዝቡንም ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው። 37 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “አዎ፣ አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። 38 ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 9:36
አዘነላቸው፦ እዚህ ላይ የገባው ስፕላግክኒዞማይ የሚለው የግሪክኛ ግስ “አንጀት” (ስፕላግክና) የሚል ትርጉም ካለው ቃል ጋር ተዛማጅነት ያለው ሲሆን ውስጥ አካላችን ድረስ ዘልቆ የሚገባን ኃይለኛ ስሜት ያመለክታል። ይህ ቃል በግሪክኛ ቋንቋ በጣም ጥልቅ የሆነ የርኅራኄ ስሜትን ለመግለጽ ከሚያገለግሉት ቃላት መካከል አንዱ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 8:8-10) መኮንኑም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ፣ አንተ ወደ ቤቴ ትገባ ዘንድ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን እዚሁ ሆነህ አንድ ቃል ተናገር፣ አገልጋዬም ይፈወሳል። 9 እኔ ራሴ የምታዘዛቸው የበላይ አዛዦች አሉ፤ ለእኔም የሚታዘዙ የበታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” 10 ኢየሱስ ይህን ሲሰማ በጣም ተገርሞ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት ያለው አንድም ሰው አላገኘሁም።
“ምሳሌ ትቼላችኋለሁ”
16 በተመሳሳይም ከአሕዛብ ወገን እንደሆነ የሚገመት አንድ ሮማዊ የጦር መኮንን በሕመም የሚሰቃይ አገልጋዩን እንዲፈውስለት ሲጠይቀው ኢየሱስ ይህ ወታደር መጥፎ ጎኖች እንዳሉት ያውቅ ነበር። በዚያን ዘመን አንድ የጦር መኮንን በብዙ የጭካኔ ድርጊቶች፣ በደም መፋሰስ እንዲሁም በሐሰት አምልኮ ሥርዓቶች ይካፈል እንደነበረ ይገመታል። ሆኖም ኢየሱስ ያተኮረው ሰውዬው ባለው ጥሩ ጎን ይኸውም ባሳየው ከፍተኛ እምነት ላይ ነበር። (ማቴዎስ 8:5-13) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ከጎኑ የተሰቀለውን ወንጀለኛ ባነጋገረበት ወቅት ሰውዬውን ከዚያ ቀደም ስለሠራው ወንጀል አልወቀሰውም። ከዚህ ይልቅ በፊቱ ስለሚጠብቀው ተስፋ በመንገር አበረታቶታል። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ የሌሎችን ደካማ ጎን አንስቶ መተቸት ተስፋ ከማስቆረጥ ሌላ ምንም ፋይዳ እንደማይኖረው ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ የሌሎችን በጎ ጎን መመልከቱ ብዙ ሰዎች ከበፊቱ የተሻለ እንዲያደርጉ ረድቷቸው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
(ማቴዎስ 9:16, 17) በአሮጌ ልብስ ላይ ውኃ ያልነካው አዲስ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም፤ አዲሱ ጨርቅ ሲሸበሸብ ልብሱን ስለሚስበው ቀዳዳው የባሰ ይሰፋልና። 17 ደግሞም ሰዎች ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ አያስቀምጡም። እንዲህ ቢያደርጉ አቁማዳው ይፈነዳል፤ ወይኑ ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን ሰዎች አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጡት በአዲስ አቁማዳ ነው፤ በመሆኑም ሁለቱም ሳይበላሹ ይቆያሉ።”
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድን ነው?
ኢየሱስ፣ በአይሁድ እምነት ውስጥ ያሉ ያረጁ ሥርዓቶችን ለምሳሌ በዘልማድ የሚደረገውን ጾም የእሱ ደቀ መዛሙርት እንዲከተሉ ማንም ሊጠብቅባቸው እንደማይገባ ለመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ማስረዳቱ ነው። እሱ ወደ ምድር የመጣው፣ ያረጀውንና የነተበውን እንዲሁም በቅርቡ የሚወገደውን የአምልኮ ሥርዓት ለመጣፍና ዕድሜውን ለማራዘም አይደለም። በዘመኑ የነበረውንና በሰው ወጎች የተሞላውን የአይሁድ እምነት መከተልን እያበረታታም አይደለም። ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ ጨርቅ ለመጣፍ ወይም ባረጀና በደረቀ አቁማዳ ውስጥ አዲስ የወይን ጠጅ ለማስቀመጥ አልሞከረም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 8:1-17) ከተራራው ከወረደ በኋላ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 2 በዚህ ጊዜ በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደ እሱ መጥቶ በመስገድ “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። 3 ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። ወዲያውኑ ከሥጋ ደዌው ነጻ። 4 ከዚያም ኢየሱስ “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ። ካህናቱም ማስረጃውን ይመለከታሉ” አለው። 5 ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ አንድ የጦር መኮንን ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ ሲል ተማጸነው፦ 6 “ጌታዬ፣ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ ቤት ተኝቷል፤ በጣም እየተሠቃየ ነው።” 7 እሱም “መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። 8 መኮንኑም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ፣ አንተ ወደ ቤቴ ትገባ ዘንድ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን እዚሁ ሆነህ አንድ ቃል ተናገር፣ አገልጋዬም ይፈወሳል። 9 እኔ ራሴ የምታዘዛቸው የበላይ አዛዦች አሉ፤ ለእኔም የሚታዘዙ የበታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” 10 ኢየሱስ ይህን ሲሰማ በጣም ተገርሞ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት ያለው አንድም ሰው አላገኘሁም። 11 ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማያትም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር በማዕድ ይቀመጣሉ። 12 የመንግሥተ ሰማያት ልጆች ግን ውጭ ወዳለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ።” 13 ከዚያም ኢየሱስ መኮንኑን “ሂድ። እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ። 14 ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ሲመጣ የጴጥሮስ አማት ትኩሳት ይዟት ተኝታ አገኛት። 15 እጇንም ሲዳስሳት ትኩሳቱ ለቀቃት፤ ተነስታም ታገለግለው ጀመር። 16 ከመሸ በኋላ ሰዎች አጋንንት ያደሩባቸውን ብዙ ሰዎች ወደ እሱ አመጡ፤ መናፍስቱንም በአንድ ቃል አስወጣ፤ እየተሠቃዩ የነበሩትንም ሁሉ ፈወሰ፤ 17 ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ “እሱ ሕመማችንን ተቀበለ፤ ደዌያችንንም ተሸከመ” ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።
ከጥር 29–የካቲት 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 10-11
“ኢየሱስ የእረፍት ምንጭ ነበር”
(ማቴዎስ 10:29, 30) ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም። 30 የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማቴ 10:29, 30
ድንቢጦች፦ ስትሮውቲዮን የሚለው የግሪክኛ ቃል ትንሽነትን የሚያመለክት ቅጥያ የተጨመረበት የትኛውንም አነስተኛ ወፍ ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። አብዛኛውን ጊዜ ግን ለምግብነት ከሚሸጡ ወፎች መካከል ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸውን ድንቢጦችን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም፦ ቃል በቃል “አሳሪዮን፣” የአንድ ሠራተኛ የ45 ደቂቃ ደሞዝ። (ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።) ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ገሊላ በሄደበት በዚህ ወቅት፣ ሁለት ድንቢጦች በአንድ አሳሪዮን እንደሚሸጡ ተናግሯል። በሌላ ጊዜ ደግሞ (ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በይሁዳ እያገለገለ በነበረበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም) አምስት ድንቢጦች በሁለት አሳሪዮን እንደሚሸጡ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:6) እነዚህን ሁለት ዘገባዎች በማነጻጸር ድንቢጦች በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ከመሆናቸው የተነሳ ነጋዴዎች አምስተኛዋን ድንቢጥ በምርቃት መልክ ይጨምሯት እንደነበር እንገነዘባለን።
የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል፦ በሰው ጭንቅላት ላይ ያለው ፀጉር በአማካይ ከ100,000 በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ጥቃቅን ነገሮች እንኳ ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑ ለእያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳያል።
nwtsty ሚዲያ
ድንቢጥ
ድንቢጦች ለምግብነት ይሸጡ ከነበሩ ወፎች መካከል በዋጋ ዝቅተኛ የሆኑት ናቸው። አንድ ሰው ለ45 ደቂቃ ሠርቶ በሚያገኘው ደሞዝ ሁለት ድንቢጦችን መግዛት ይችል ነበር። የግሪክኛው ቃል በዛሬው ጊዜም እስራኤል ውስጥ በብዛት የሚገኙትን የተለመዱ የቤት ድንቢጦች (ፓሴር ዶመስቲከስ ቢብሊከስ) እና ስፓኒሽ ድንቢጦች (ፓሴር ሂስፓኒዮሌንሲስ) ጨምሮ የተለያዩ ትናንሽ ወፎችን ሊያመለክት ይችላል።
(ማቴዎስ 11:28) እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 11:28
ሸክም የከበዳችሁ፦ ኢየሱስ ወደ እሱ እንዲመጡ የጋበዛቸው ሰዎች፣ ባለባቸው ጭንቀትና ድካም ምክንያት ‘ሸክም ከብዷቸው’ ነበር። ሰዎች በሙሴ ሕግ ላይ በጨመሯቸው ወጎች የተነሳ ለይሖዋ የሚያቀርቡት አምልኮ ሸክም ሆኖባቸው ነበር። (ማቴ 23:4) እረፍት ሊሰጣቸው ይገባ የነበረው የሰንበት ዝግጅትም እንኳ ጫና ፈጥሮባቸዋል።—ዘፀ 23:12፤ ማር 2:23-28፤ ሉቃስ 6:1-11
እረፍት እሰጣችኋለሁ፦ “እረፍት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ ቃል በቃል እረፍት ማድረግንም ሆነ (ማቴ 26:45፤ ማር 6:31) ኃይልን ለማደስ ሲባል፣ አድካሚ ከሆነ ነገር ፋታ ማግኘትን (2ቆሮ 7:13፤ ፊልሞና 7) ሊያመለክት ይችላል። የጥቅሱ ሐሳብ እንደሚያሳየው የኢየሱስን ‘ቀንበር’ (ማቴ 11:29) መሸከም እረፍት ማድረግን ሳይሆን ማገልገልን የሚጠይቅ ነው። እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛው አድራጊ ግስ፣ ኢየሱስ ለደከሙት ብርታት በመስጠትና ኃይላቸውን በማደስ የእሱን ቀላልና ልዝብ ቀንበር የመሸከም ፍላጎት እንዲያድርባቸው እንደሚያደርግ ያመለክታል።
(ማቴዎስ 11:29, 30) ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። 30 ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 11:29
ቀንበሬን ተሸከሙ፦ ‘ቀንበር’ በእንስሳ አንገት ላይ ተደርጎ አንድን ዕቃ ለመጎተት የሚያገለግል መሣሪያ ነው። ቃሉ መጀመሪያ ላይ በተጻፈበት ቋንቋ ሰዎች በሁለት በኩል ዕቃ ለመሸከም ሲሉ ትከሻቸው ላይ የሚያደርጉትን እንጨትም ሊያመለክት ይችላል። ኢየሱስ ‘ቀንበር’ የሚለውን ቃል በምሳሌያዊ መንገድ የተጠቀመበት ለሥልጣን ወይም ለመመሪያ መገዛትን ለማመልከት ነው። ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ሁለት እንስሳት አንድ ላይ ተጠምደው የሚጎትቱትን ቀንበር በአእምሮው ይዞ ከሆነ አምላክ ለእሱ የሰጠውን ቀንበር ደቀ መዛሙርቱ አብረውት እንዲሸከሙ መጋበዙ ነው፤ እንዲህ ካደረጉ ኢየሱስ ያግዛቸዋል ማለት ነው። ኢየሱስ የተናገረው እንዲህ ስላለው ቀንበር ከሆነ ይህ ሐሳብ “ቀንበሬን አብራችሁኝ ተሸከሙ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ በአእምሮው የያዘው፣ እሱ ራሱ ሌሎች እንዲሸከሙ የሚያደርገውን ቀንበር ከሆነ ጥቅሱ የሚያመለክተው የእሱ ደቀ መዝሙር በመሆን ለክርስቶስ ሥልጣንና መመሪያ ራስን ማስገዛትን ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 11:2, 3) ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ ስላከናወናቸው ሥራዎች ሲሰማ ደቀ መዛሙርቱን በመላክ “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀው።
ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ጥያቄ አቀረበ
ዮሐንስ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማቅረቡ ይገርማል? ይህ ታማኝ ሰው ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ኢየሱስን ባጠመቀበት ጊዜ የአምላክ መንፈስ በኢየሱስ ላይ ሲወርድ የተመለከተ ከመሆኑም ሌላ አምላክ በኢየሱስ ደስ እንደሚሰኝ ሲናገር ሰምቷል። በመሆኑም የዮሐንስ እምነት እንደተዳከመ ለማሰብ የሚያበቃ ምክንያት የለንም። እምነቱ ተዳክሞ ቢሆን ኖሮ በዚህ ወቅት ኢየሱስ እሱን አድንቆ ባልተናገረ ነበር። ታዲያ ዮሐንስ ጥርጣሬ ካላደረበት ስለ ኢየሱስ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ለምንድን ነው?
ዮሐንስ፣ ኢየሱስ መሲሕ ስለ መሆኑ ከራሱ ማረጋገጫ ማግኘት ፈልጎ ይሆናል። ይህ በእስር ቤት እየማቀቀ ያለውን ዮሐንስን በጣም ያበረታታዋል። ጥያቄው ሌላም ትርጉም ያለው ይመስላል። አምላክ የቀባው ሰው፣ ንጉሥና አዳኝ እንደሚሆን የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ዮሐንስ ያውቃል። ይሁንና ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙ ወራት ቢያልፉም ዮሐንስ ከእስር አልተፈታም። በመሆኑም ዮሐንስ፣ መሲሑ እንደሚፈጽማቸው አስቀድሞ በትንቢት የተነገሩትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ኢየሱስን ተክቶ የሚመጣ ሌላ ሰው ይመጣ እንደሆነ መጠየቁ ነው።
(ማቴዎስ 11:16-19) “ይህን ትውልድ ከማን ጋር ላመሳስለው? በገበያ ስፍራ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየተጣሩ እንዲህ ከሚሉ ልጆች ጋር ይመሳሰላል፦ 17 ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ እናንተ ግን በሐዘን ደረታችሁን አልደቃችሁም።’ 18 በተመሳሳይም ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘ጋኔን አለበት’ አሉ። 19 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘እዩ፣ ይህን ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉ። የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል።”
መልእክቱን ለማይቀበል ትውልድ ወዮለት
ኢየሱስ ለመጥምቁ ዮሐንስ ከፍ ያለ ግምት አለው፤ ይሁንና ብዙዎች ዮሐንስን የሚመለከቱት እንዴት ነው? ኢየሱስ በዘመኑ ስላለው ትውልድ ሲናገር እንደሚከተለው ብሏል፦ “በገበያ ስፍራ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየተጣሩ እንዲህ ከሚሉ ልጆች ጋር ይመሳሰላል፦ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ እናንተ ግን በሐዘን ደረታችሁን አልደቃችሁም።’”—ማቴዎስ 11:16, 17
ኢየሱስ ምን ማለቱ ነው? ሐሳቡን እንዲህ በማለት አብራርቷል፦ “ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘ጋኔን አለበት’ አሉ። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘እዩ፣ ይህን ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉ።” (ማቴዎስ 11:18, 19) ዮሐንስ የናዝራውያን ዓይነት ቀላል ሕይወት መርቷል፤ ሌላው ቀርቶ የወይን ጠጅ እንኳ አልጠጣም፤ ያም ቢሆን ሰዎቹ ጋኔን እንዳለበት ተናግረዋል። (ዘኁልቁ 6:2, 3፤ ሉቃስ 1:15) ኢየሱስ ደግሞ የኖረው እንደ ማንኛውም ሰው ነው። የሚበላውና የሚጠጣው ልከኝነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ቢሆንም ሰዎች መጠኑን እንዳለፈ ተናግረዋል። በእርግጥም ሕዝቡን ማስደሰት አስቸጋሪ ነው!
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 11:1-19) ኢየሱስ ለ12 ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ በሌሎች ከተሞች ለማስተማርና ለመስበክ ሄደ። 2 ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ ስላከናወናቸው ሥራዎች ሲሰማ ደቀ መዛሙርቱን በመላክ 3 “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀው። 4 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ነገር ለዮሐንስ ንገሩት፤ 5 ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ ሙታን እየተነሱ ነው፤ ድሆችም ምሥራቹ እየተነገራቸው ነው። 6 በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።” 7 መልእክተኞቹ ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ይናገር ጀመር፦ “ወደ ምድረ በዳ የሄዳችሁት ምን ለማየት ነበር? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆ? 8 ታዲያ ምን ለማየት ነበር የሄዳችሁት? ምርጥ ልብስ የለበሰ ሰው ለማየት? ምርጥ ልብስ የለበሱማ የሚገኙት በነገሥታት ቤት ነው። 9 ታዲያ ለምን ሄዳችሁ? ነቢይ ለማየት? አዎ፣ እላችኋለሁ፣ ከነቢይም የሚበልጥ ነው። 10 ‘እነሆ፣ ከፊትህ እየሄደ መንገድህን እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ!’ ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ነው። 11 እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ዝቅተኛ የሆነው እንኳ ይበልጠዋል። 12 መንግሥተ ሰማያት ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሰዎች የሚጋደሉለት ግብ ሆኗል፤ በተጋድሏቸው የሚጸኑም ያገኙታል። 13 ነቢያትና ሕጉ በሙሉ እስከ ዮሐንስ ዘመን ድረስ ተንብየዋልና፤ 14 እንግዲህ ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆናችሁ ‘ይመጣል የተባለው ኤልያስ’ እሱ ነው። 15 ጆሮ ያለው ይስማ። 16 “ይህን ትውልድ ከማን ጋር ላመሳስለው? በገበያ ስፍራ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየተጣሩ እንዲህ ከሚሉ ልጆች ጋር ይመሳሰላል፦ 17 ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ እናንተ ግን በሐዘን ደረታችሁን አልደቃችሁም።’ 18 በተመሳሳይም ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘ጋኔን አለበት’ አሉ። 19 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘እዩ፣ ይህን ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉ። የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል።”