የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—የካቲት 2018
ከየካቲት 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 12-13
“የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ”
(ማቴዎስ 13:24-26) ደግሞም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር ከዘራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። 25 ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26 እህሉ አድጎ ፍሬ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም አብሮ ታየ።
“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”
2 በገበሬው እርሻ ላይ የተከናወኑት ነገሮች ኢየሱስ የስንዴውን ክፍል ማለትም በመንግሥቱ ከእሱ ጋር የሚገዙትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከመላው የሰው ዘር መካከል የሚሰበስበው እንዴትና መቼ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ዘሩ መዘራት የተጀመረው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነው። የመሰብሰቡ ሥራ የሚጠናቀቀው ደግሞ በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ በሕይወት ያሉት ቅቡዓን የመጨረሻው ማኅተም ሲደረግባቸውና ከዚያም ወደ ሰማይ ሲሄዱ ነው። (ማቴ. 24:31፤ ራእይ 7:1-4) አንድ ሰው የተራራ ጫፍ ላይ መቆሙ ዙሪያ ገባውን ለማየት እንደሚያስችለው ሁሉ ይህ ምሳሌም ወደ 2,000 ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በስፋት ለመቃኘት ያስችለናል። ታዲያ እዚህ ምሳሌ ላይ ቆመን ነገሮችን ስንቃኝ ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙትን የትኞቹን ክንውኖች ማስተዋል እንችላለን? ምሳሌው ስንዴውና እንክርዳዱ የሚዘሩበት፣ አብረው የሚያድጉበትና የመከር ወቅት እንደሚኖር ይገልጻል። ይህ ርዕስ ግን በዋነኝነት የሚያተኩረው በመከሩ ላይ ነው።
በኢየሱስ ጥበቃ ሥር መሆን
3 በእንክርዳድ የተመሰሉት አስመሳይ ክርስቲያኖች ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መባቻ አንስቶ፣ በእርሻ በተመሰለው ዓለም ላይ ብቅ ማለት ጀመሩ። (ማቴ. 13:26) በእንክርዳድ የተመሰሉት ክርስቲያኖች ቁጥር በአራተኛው መቶ ዘመን ላይ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች በጣም በልጦ ነበር። በምሳሌው ላይ ባሪያዎቹ እንክርዳዱን ለመንቀል እንዲፈቅድላቸው ጌታቸውን ጠይቀውት እንደነበር አስታውስ። (ማቴ. 13:28) ታዲያ ጌታው ምን ምላሽ ሰጠ?
(ማቴዎስ 13:27-29) ስለሆነም የቤቱ ጌታ ባሪያዎች፣ ወደ እሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፣ በእርሻህ ላይ የዘራኸው ጥሩ ዘር አልነበረም እንዴ? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። 28 እሱም ‘ይህን ያደረገው ጠላት ነው’ አላቸው። ባሪያዎቹም ‘ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ አሉት። 29 እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ስለምትችሉ ተዉት።
“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”
4 ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ ሲናገር “ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ” (አ.መ.ት) ብሏል። ይህ መመሪያ እንደሚያስገነዝበን ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በምድር ላይ ምንጊዜም የተወሰኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይኖራሉ። ኢየሱስ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት መናገሩ ይህን ያረጋግጥልናል። (ማቴ. 28:20) በመሆኑም ኢየሱስ እስከ ሥርዓቱ ፍጻሜ ድረስ ምንጊዜም ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ይሁንና ቅቡዓኑ በእንክርዳድ በተመሰሉ ክርስቲያኖች ስለተዋጡ በዚህ ረጅም ጊዜ ውስጥ የስንዴው ክፍል የሆኑት እነማን እንደነበሩ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። የመከሩ ወቅት ከመጀመሩ ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ግን የስንዴው ክፍል የሆኑት እነማን እንደሆኑ መለየት ጀመረ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
(ማቴዎስ 13:30) እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብረው ይደጉ፤ በመከር ወቅት አጫጆቹን፣ በመጀመሪያ እንክርዳዱን ሰብስቡና እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ከዚያም ስንዴውን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡ እላቸዋለሁ።’”
“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”
10 የመጀመሪያው እንክርዳዱን መሰብሰብ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የመከር ወቅት ሲደርስ አጫጆቹን፣ በመጀመሪያ እንክርዳዱን ሰብስቡና . . . በየነዶው እሰሩ፤ . . . እላቸዋለሁ።” ከ1914 በኋላ ግን መላእክት በእንክርዳድ የተመሰሉትን ክርስቲያኖች “የመንግሥቱ ልጆች” ከሆኑት ከቅቡዓን በመለየት ‘ይሰበስቧቸዋል።’—ማቴ 13:30, 38, 41
11 የመሰብሰቡ ሥራ ወደፊት እየገፋ ሲሄድ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ ፍንትው ብሎ መታየት ጀመረ። (ራእይ 18:1, 4) በ1919 ታላቂቷ ባቢሎን እንደወደቀች ግልጽ ሆነ። ለመሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአስመሳዮቹ ክርስቲያኖች ይበልጥ እንዲለዩ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው? የስብከቱ ሥራ ነው። በወቅቱ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ወንድሞች፣ የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩ ሥራ ላይ ሁሉም ክርስቲያኖች መካፈል እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው መናገር ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ (እንግሊዝኛ) የተሰኘ በ1919 የታተመ ቡክሌት ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከቤት ወደ ቤት በመሄድ እንዲሰብኩ አሳስቦ ነበር። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሥራው ሰፊ ቢመስልም የጌታ ሥራ በመሆኑ እሱ በሚሰጠን ኃይል እንወጣዋለን። በዚህ ሥራ የመካፈል መብት አግኝታችኋል።” ታዲያ ምን ምላሽ ተገኘ? የ1922 መጠበቂያ ግንብ እንደገለጸው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የስብከት እንቅስቃሴያቸውን አጧጧፉት። ብዙም ሳይቆይ ከቤት ወደ ቤት መስበክ የእነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች መለያ ሆነ፤ ይህ የስብከት ዘዴ እስከ ዛሬ ድረስ መለያችን ሆኗል።
12 ሁለተኛው ስንዴውን መሰብሰብ ነው። ኢየሱስ “ስንዴውን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡ” በማለት መላእክቱን አዝዟቸዋል። (ማቴ. 13:30) ከ1919 ጀምሮ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደ ገና ወደተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ሲሰበሰቡ ቆይተዋል። በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ በሕይወት ከሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘ የመጨረሻው የመሰብሰብ ሥራ የሚካሄደው ወደ ሰማይ በመሄድ ሽልማታቸውን ሲያገኙ ነው።—ዳን 7:18, 22, 27
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 12:20) ፍትሕን በአስተማማኝ ሁኔታ እስኪያሰፍን ድረስ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 12:20
የሚጨስ የጧፍ ክር፦ በወቅቱ በቤት ውስጥ ብርሃን ለመስጠት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው በወይራ ዘይት የተሞላ የሸክላ ኩራዝ ነበር። ከተልባ እግር የተሠራው ክር ዘይቱን እየሳበ ኩራዙ መብራቱን እንዲቀጥል ያደርጋል። “የሚጨስ የጧፍ ክር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ እሳቱ በመክሰሙ ምክንያት የሚጨስን ግን ሙሉ በሙሉ ያልጠፋን ክር ያመለክታል። በኢሳይያስ 42:3 ላይ የሚገኘው ትንቢት የኢየሱስን ርኅራኄ የሚገልጽ ነው፤ ኢየሱስ ምስኪኖችና የተጨቆኑ ሰዎች የቀራቸውን የተስፋ ጭላንጭል አያጠፋም።
(ማቴዎስ 13:25) ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ።
ይህን ያውቁ ኖሯል?
በጥንት ዘመን አንድ ሰው በሌላ ሰው እርሻ ላይ እንክርዳድ መዝራቱ በእርግጥ ሊፈጸም የሚችል ነገር ነው?
በማቴዎስ 13:24-26 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር ከዘራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። እህሉ አድጎ ፍሬ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም አብሮ ታየ።” የተለያዩ ጸሐፊዎች ይህ ምሳሌ በእውነታው ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ጥያቄ አንስተዋል፤ ይሁንና ጥንታዊ የሮም የሕግ መዛግብት ምሳሌው በእውነታ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፦ “በበቀል ተነሳስቶ በሌላ ሰው እርሻ ላይ እንክርዳድ መዝራት . . . በሮም ሕግ እንደ ወንጀል ይቆጠር ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ሕግ መውጣቱ፣ እንዲህ ያለ ድርጊት ይፈጸም እንደነበር ይጠቁማል።” አለስተር ኬር የተባሉ የሕግ ምሁር፣ ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ጀስቲንያን በ533 ዓ.ም አንድ ጽሑፍ (ዳይጀስት) እንዳዘጋጀ ተናግረዋል፤ ጽሑፉን ያዘጋጀው ከሮም ሕግና ክላሲካል ፔሬድ ኦቭ ሮማን ሎው ተብሎ በሚጠራው ጊዜ (ከ100-250 ዓ.ም ገደማ) የነበሩ የሕግ ባለሙያዎች ካዘጋጇቸው ጽሑፎች የተውጣጡ ነገሮችን አንድን ላይ በማጠናቀር ነው። ይህ ጽሑፍ (Digest, 9.2.27.14) ኧልፒያን የተባለው የሕግ ባለሙያ ስለዘገበው አንድ ታሪክ ያወሳል፤ በታሪኩ ላይ፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረ ሴልሰስ የተባለ ሮማዊ የፖለቲካ ሰው ስለዳኘው አንድ የፍርድ ሂደት ተጠቅሷል። አንድ ግለሰብ፣ በሌላ ሰው እርሻ ላይ እንክርዳድ በመዝራቱ ምክንያት ሰብሉ ተበላሸ። ጽሑፉ፣ ይህ ወንጀል የተፈጸመበት የእርሻ ባለቤት ወይም ጭሰኛ ከበዳዩ ካሳ ለማግኘት የሚያስችሉትን ሕጋዊ ዝግጅቶች ይገልጻል።
በጥንት ዘመን በሮም ግዛት ውስጥ እንዲህ ያለ የተንኮል ድርጊት የተፈጸመ መሆኑ፣ ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ነገር በገሃዱ ዓለም ሊያጋጥም የሚችል እንደሆነ ይጠቁማል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 12:1-21) በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል አለፈ። ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ስለነበር እሸት እየቀጠፉ መብላት ጀመሩ። 2 ፈሪሳውያን ይህን ባዩ ጊዜ “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር እያደረጉ ነው” አሉት። 3 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት እሱና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁም? 4 ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር እሱም ሆነ ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች እንዲበሉ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት አልበሉም? 5 ደግሞስ ካህናት የሰንበትን ሕግ እንደሚተላለፉና ይህም እንደ በደል እንደማይቆጠርባቸው በሕጉ ላይ አላነበባችሁም? 6 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ከቤተ መቅደሱ የሚበልጥ እዚህ አለ። 7 ይሁንና ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም ተረድታችሁ ቢሆን ኖሮ ምንም በደል ባልሠሩት ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። 8 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” 9 ከዚያ ስፍራ ከሄደ በኋላ ወደ ምኩራባቸው ገባ፤ 10 በዚያም እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበር። እነሱም ኢየሱስን መክሰስ ፈልገው “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል?” ሲሉ ጠየቁት። 11 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው ሰው ቢኖርና በሰንበት ቀን ጉድጓድ ውስጥ ቢገባበት በጉን ጎትቶ የማያወጣው ይኖራል? 12 ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥም? ስለዚህ በሰንበት መልካም ነገር ማድረግ ተፈቅዷል።” 13 ከዚያም ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም እንደ ሌላኛው እጁ ደህና ሆነለት። 14 ፈሪሳውያኑ ግን ወጥተው እሱን ለመግደል አሴሩ። 15 ኢየሱስም ይህን ሲያውቅ አካባቢውን ለቆ ሄደ። ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤ እሱም የታመሙትን ሁሉ ፈወሳቸው፤ 16 ሆኖም የእሱን ማንነት ለሌሎች እንዳይገልጹ በጥብቅ አዘዛቸው፤ 17 ይህን ያደረገው በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦ 18 “እነሆ፣ የምወደውና ደስ የምሰኝበት የመረጥኩት አገልጋዬ! መንፈሴን በእሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነም ለብሔራት ያሳውቃል። 19 አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ድምፁን የሚሰማ አይኖርም። 20 ፍትሕን በአስተማማኝ ሁኔታ እስኪያሰፍን ድረስ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም። 21 በእርግጥም ብሔራት በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”
ከየካቲት 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 14-15
“በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን መመገብ”
(ማቴዎስ 14:16, 17) ይሁን እንጂ ኢየሱስ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አላቸው። 17 እነሱም “ከአምስት ዳቦና ከሁለት ዓሣ በስተቀር እዚህ ምንም ነገር የለንም” አሉት።
በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን መመገብ
2 ኢየሱስ ሕዝቡን ሲመለከት አዘነላቸው፤ ከዚያም ከእነሱ መካከል የታመሙትን ፈወሰ፤ እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት ብዙ ነገር አስተማራቸው። እየመሸ ሲሄድ ግን ደቀ መዛሙርቱ ሰዎቹን እንዲያሰናብት ነገሩት፤ ይህንንም ያሉት ሰዎቹ በአቅራቢያው ወዳሉ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ አስበው ነው። ይሁንና ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የሚበሉት ነገር እናንተ ስጧቸው” አላቸው። ሆኖም የተናገረው ነገር ለደቀ መዛሙርቱ እንቆቅልሽ ሳይሆንባቸው አልቀረም፤ ምክንያቱም በእጃቸው ያለው ምግብ አምስት ዳቦና ሁለት ዓሣ ብቻ ነበር።
(ማቴዎስ 14:18, 19) እሱም “ያለውን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። 19 ሕዝቡንም ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። ከዚያም አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ቀና በማለት ባረከ፤ ዳቦውን ከቆረሰ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እነሱ ደግሞ ለሕዝቡ ሰጡ።
በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን መመገብ
3 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በርኅራኄ ተነሳስቶ አንድ ተአምር ፈጸመ፤ ይህ ደግሞ በአራቱም ወንጌሎች ውስጥ በመጠቀስ ረገድ ብቸኛው ተአምር ነው። (ማር. 6:35-44፤ ሉቃስ 9:10-17፤ ዮሐ. 6:1-13) ኢየሱስ ሕዝቡን መቶ መቶና፣ ሃምሳ ሃምሳ እያደረጉ በቡድን እንዲያስቀምጡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ምግቡን ከባረከ በኋላ ዳቦውንና ዓሣውን መቆራረስ ጀመረ። ከዚያም ምግቡን በቀጥታ ለሕዝቡ ከመስጠት ይልቅ “ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው”፤ እነሱም ‘ለሕዝቡ አቀረቡ።’ የሚገርመው ነገር ሁሉም ከበሉ በኋላ ብዙ ምግብ ተረፈ! ኢየሱስ በጥቂቶች ማለትም በደቀ መዛሙርቱ ተጠቅሞ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መመገቡ ትኩረት የሚስብ ነው።
(ማቴዎስ 14:20, 21) ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ። 21 የበሉትም ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች ሌላ 5,000 ወንዶች ነበሩ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 14:21
ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች፦ ይህን ተአምራዊ ክንውን ሲዘግብ ስለ ሴቶችና ትናንሽ ልጆች የጠቀሰው ማቴዎስ ብቻ ነው። በዚህ ወቅት ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተመገቡት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ከ15,000 በላይ ሊሆን ይችላል።
በጥቂቶች ተጠቅሞ ብዙኃኑን መመገብ
እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። (ማቴዎስ 14:14-21ን አንብብ።) ጊዜው በ32 ዓ.ም. ከተከበረው የማለፍ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ ነው። ሴቶችና ልጆች ሳይቆጠሩ 5,000 ገደማ የሚሆኑ ወንዶች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በሰሜናዊው የገሊላ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው በቤተሳይዳ አቅራቢያ ባለ አንድ ራቅ ያለ አካባቢ ተሰባስበዋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 15:7-9) እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፦ 8 ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። 9 የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 15:7
ግብዞች፦ ሂፖክሪተስ የሚለው የግሪክኛው ቃል መጀመሪያ ላይ ይሠራበት የነበረው ድምፅን እንዲያጎሉ ታስበው የተዘጋጁ ትላልቅ ጭንብሎችን አጥልቀው የሚተውኑ የግሪክ (በኋላም የሮም) የመድረክ ተዋናዮችን ለማመልከት ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይህ አገላለጽ፣ በማታለል ወይም በማስመሰል ዓላማውን አሊያም ትክክለኛ ማንነቱን የሚደብቅን ሰው ለማመልከት የሚያገለግል ምሳሌያዊ አነጋገር ሆነ። እዚህ ላይ ኢየሱስ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎችን “ግብዞች” በማለት ጠርቷቸዋል።—ማቴ 6:5, 16
(ማቴዎስ 15:26) እሱም መልሶ “የልጆችን ዳቦ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ተገቢ አይደለም” አለ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 15:26
የልጆችን . . . ለቡችሎች፦ በሙሴ ሕግ መሠረት ውሾች ርኩስ ነበሩ፤ በመሆኑም ‘ውሻ’ የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተሠራበት የተጠላ ወይም የተናቀ ነገርን ለማመልከት ነው። (ዘሌ 11:27፤ ማቴ 7:6፤ ፊልጵ 3:2፤ ራእይ 22:15) ይሁንና ኢየሱስ ከሴትየዋ ጋር ስላደረገው ውይይት በሚናገሩት የማርቆስም (7:27) ሆነ የማቴዎስ ዘገባዎች ላይ ቃሉ ትንሽነትን የሚያመለክት ቅጥያ ስለተጨመረበት “ቡችላ” ወይም “የቤት ውሻ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፤ ይህ ደግሞ ‘ውሻ’ የሚለው ቃል የሚያስተላልፈውን አሉታዊ ስሜት ያለዝበዋል። ምናልባትም ኢየሱስ እዚህ ላይ የተጠቀመው የቤት እንስሳ ያላቸው አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች እንስሶቻቸውን ለመጥራት የሚጠቀሙበትን ፍቅር የሚንጸባረቅበት ቃል ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ እስራኤላውያንን ‘ከልጆች’ ጋር፣ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችን ደግሞ ‘ከቡችሎች’ ጋር ያመሳሰለው ቅድሚያ የሚሰጠው ለየትኞቹ እንደሆነ ለማመልከት ፈልጎ ሳይሆን አይቀርም። ልጆችና ውሾች ባሉበት ቤት ውስጥ በቅድሚያ ምግብ የሚሰጠው ለልጆች እንደሆነ ግልጽ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 15:1-20) ከዚያም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ 2 “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ የሚጥሱት ለምንድን ነው? ለምሳሌ፣ ሊበሉ ሲሉ እጃቸውን አይታጠቡም።” 3 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ትእዛዝ የምትጥሱት ለምንድን ነው? 4 ለምሳሌ አምላክ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ እንዲሁም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ይገደል’ ብሏል። 5 እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘ማንኛውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን “እናንተን መጦር የምችልበት፣ ያለኝ ነገር ሁሉ ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ ነው” ካለ 6 አባቱን የማክበር ግዴታ የለበትም።’ በመሆኑም ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ቃል ሽራችኋል። 7 እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፦ 8 ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። 9 የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’” 10 ከዚያም ሕዝቡን ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ፤ ደግሞም ይህን ቃል አስተውሉ፦ 11 ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፉ የሚገባው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው ነው።” 12 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው “ፈሪሳውያን በተናገርከው ነገር ቅር እንደተሰኙ አውቀሃል?” አሉት። 13 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። 14 ተዉአቸው፤ እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው። ስለዚህ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።” 15 ጴጥሮስም መልሶ “ምሳሌውን አብራራልን” አለው። 16 በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተም እስካሁን ማስተዋል ተስኗችኋል? 17 ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ እንደሚዘልቅና ከዚያም ወጥቶ ወደ ጉድጓድ እንደሚገባ አታውቁም? 18 ይሁን እንጂ ከአፍ የሚወጣ ሁሉ ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው። 19 ለምሳሌ ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ የፆታ ብልግና፣ ሌብነት፣ በሐሰት መመሥከርና ስድብ ይወጣሉ። 20 ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ነገሮች ናቸው፤ እጅን ሳይታጠቡ መብላት ግን ሰውን አያረክስም።”
ከየካቲት 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 16-17
“የምታስቡት የማንን ሐሳብ ነው?”
(ማቴዎስ 16:21, 22) ከዚያን ጊዜ አንስቶ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እጅ ከባድ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ እንደሚገባው ብሎም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር። 22 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” እያለ ይገሥጸው ጀመር።
ባሎች—የራስነት ሥልጣንን በመጠቀም ረገድ ክርስቶስን ምሰሉ
17 በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድና “በዚያም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በኦሪት ሕግ መምህራን እጅ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣ ዘንድ እንደሚገባው” ለሐዋርያቱ ገለጸላቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ወደ ጐን ሳብ አድርጎ “ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” እያለ ይገሥጸው ጀመር። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጴጥሮስ ስሜታዊ ሆኖ ነበር። ስለሆነም እርማት አስፈልጎት ነበር። ኢየሱስም “አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለ ሌለ መሰናክል ሆነህብኛል!” አለው።—ማቴዎስ 16:21-23
(ማቴዎስ 16:23) እሱ ግን ጀርባውን በመስጠት ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” አለው።
ንቁ ሆናችሁ ኑሩ—ሰይጣን ሊውጣችሁ ይፈልጋል!
16 ዲያብሎስ፣ ቀናተኛ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮችን እንኳ ሊያታልል ይችላል። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ሊገደል እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው ምን እንደተፈጠረ እንመልከት። ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” አለው፤ ጴጥሮስ ይህን ያለው ለኢየሱስ አስቦ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን!” በማለት ጠንከር ያለ መልስ ሰጠው። (ማቴ. 16:22, 23) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን “ሰይጣን” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ በቅርቡ ምን እንደሚከናወን ያውቃል። ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ የሚሞትበትና ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን የሚያረጋግጥበት ጊዜ ተቃርቧል። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት ኢየሱስ “በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን” ሊባል አይገባም። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ከተዘናጋ ሰይጣን የሚፈልገው ነገር ተሳካለት ማለት ነው።
17 እኛም ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረብን በመሆኑ የምንኖረው ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው። ሰይጣን እንድንዘናጋ ይኸውም ‘በራሳችን ላይ ከመጨከን’ ይልቅ በዚህ ዓለም ውስጥ ለእኛ ተስማሚ የሆነውን ቦታ ለማግኘት በመጣር የጥድፊያ ስሜታችንን እንድናጣ ይፈልጋል። ይህ እንዲደርስባችሁ አትፍቀዱ! ከዚህ ይልቅ “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ማቴ. 24:42) ሰይጣን፣ መጨረሻው ሩቅ እንደሆነ ወይም ጨርሶ እንደማይመጣ ለሚያስፋፋው አታላይ ፕሮፓጋንዳ ፈጽሞ ጆሮ አትስጡ።
(ማቴዎስ 16:24) ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።
‘ሂዱና እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’
9 የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ የኢየሱስን ፈለግ መከተል ምንን ይጨምራል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 16:24) ኢየሱስ ልናደርጋቸው የሚገቡንን ሦስት ነገሮች እዚህ ጥቅስ ላይ አመልክቷል። በመጀመሪያ ራሳችንን ‘እንክዳለን።’ በሌላ አነጋገር ራስ ወዳድና ኃጢአተኛ ለሆነው ዝንባሌያችን ፊት አንሰጥም፤ በተቃራኒው የአምላክን ምክርና መመሪያ እንታዘዛለን። ሁለተኛ፣ ‘መስቀላችንን’ ወይም የመከራችንን እንጨት እንሸከማለን። በኢየሱስ ዘመን የመከራ እንጨት የውርደትና የሥቃይ ምልክት ነበር። ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ለምሥራቹ ስንል አንዳንድ ጊዜ ችግር ሊደርስብን እንደሚችል አምነን እንቀበላለን። (2 ጢሞቴዎስ 1:8) ዓለም ቢያፌዝብንና ቢነቅፈን እንኳን፣ አምላክን እያስደሰትን እንዳለን በማወቃችን ምክንያት የምናገኘው ደስታ ልክ እንደ ክርስቶስ የሚደርስብንን ‘ውርደት ንቀን’ እንድናልፍ ያስችለናል። (ዕብራውያን 12:2) በመጨረሻም፣ ኢየሱስን ሁልጊዜ እንከተላለን።—መዝሙር 73:26፤ 119:44፤ 145:2
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 16:18) ደግሞም እልሃለሁ፦ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህች ዓለት ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ፤ የመቃብር በሮችም አያሸንፏትም።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 16:18
አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህች ዓለት ላይ፦ በተባዕታይ ፆታ የተነገረው ፔትሮስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ትንሽ ዓለት፤ ድንጋይ” የሚል ትርጉም አለው። እዚህ ላይ ይህ ቃል የተጸውኦ ስም (ጴጥሮስ) ሆኖ የገባ ሲሆን ኢየሱስ ለስምዖን የሰጠው ስም ግሪክኛ አጠራር ነው። (ዮሐ 1:42) አንስታይ ፆታ የሆነው ፔትራ የሚለው ቃል ደግሞ “ዓለት” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን ንጣፍ ድንጋይን፣ ቋጥኝን ወይም ትልቅ ዓለትን ሊያመለክት ይችላል። ይህ የግሪክኛ ቃል ማቴ 7:24, 25፤ 27:60፤ ሉቃስ 6:48፤ 8:6፤ ሮም 9:33፤ 1ቆሮ 10:4፤ 1ጴጥ 2:8 ላይም ይገኛል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ጴጥሮስ ራሱን ኢየሱስ ጉባኤውን የሚገነባበት ዓለት አድርጎ እላሰበም፤ ምክንያቱም 1ጴጥ 2:4-8 ላይ አምላክ ራሱ የመረጠው አስቀድሞ የተነገረለት “የማዕዘን የመሠረት ድንጋይ” ኢየሱስ እንደሆነ ገልጿል። ሐዋርያው ጳውሎስም ኢየሱስን “መሠረት” እና “መንፈሳዊ ዓለት” ሲል ጠርቶታል። (1ቆሮ 3:11፤ 10:4) ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ኢየሱስ ጴጥሮስን በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲህ እያለው ነበር፦ ‘ጴጥሮስ ማለትም ትንሽ ዓለት ብዬ የጠራሁህ አንተ፣ የክርስቲያን ጉባኤ መሠረት የሚሆነውን “የዚህን ዓለት” ማለትም የክርስቶስን ትክክለኛ ማንነት አውቀሃል።’
ጉባኤ፦ ኤክሌሲያ የሚለው የግሪክኛ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበት ቦታ። “መውጣት” የሚል ትርጉም ካለው ኤክ ከሚለው ቃልና “መጥራት” የሚል ትርጉም ካለው ካሌኦ ከሚለው ቃል የተገኘ ነው። ቃሉ ለአንድ ዓላማ ወይም ተግባር አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ የተጠሩ ሰዎችን ያመለክታል። (የቃላት መፍቻውን ተመልከት።) በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ ስለ ክርስቲያን ጉባኤ መቋቋም አስቀድሞ እየተናገረ ነበር፤ ይህ ጉባኤ ‘እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እየተገነቡ’ ባሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተዋቀረ ነው። (1ጴጥ 2:4, 5) ይህ የግሪክኛ አገላለጽ በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ በተደጋጋሚ የተሠራበት “ጉባኤ” ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ቃል ለመግለጽ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የአምላክን ሕዝብ ያቀፈውን ብሔር በአጠቃላይ ያመለክታል። (ዘዳ 23:3፤ 31:30) ሥራ 7:38 ላይ ከግብፅ የተጠሩት እስራኤላውያን “ጉባኤ” ተብለው ተጠርተዋል። ‘ከጨለማ የተጠሩት’ እንዲሁም ‘ከዓለም የተመረጡት’ ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ መንገድ “የአምላክ ጉባኤ” ተብለዋል።—1ጴጥ 2:9፤ ዮሐ 15:19፤ 1ቆሮ 1:2
(ማቴዎስ 16:19) የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈታው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 16:19
የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በቃልም ሆነ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ለአንድ ሰው ቁልፍ መሰጠቱ ግለሰቡ የተወሰነ ሥልጣን እንደተሰጠው ያመለክታል። (1ዜና 9:26, 27፤ ኢሳ 22:20-22) በመሆኑም “ቁልፍ” የሚለው ቃል ሥልጣንና ኃላፊነትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ጴጥሮስ በኃላፊነት የተሰጡትን እነዚህን “ቁልፎች” ለአይሁዳውያን (ሥራ 2:22-41)፣ ለሳምራውያን (ሥራ 8:14-17) እና ለአሕዛብ (ሥራ 10:34-38) የአምላክን መንፈስ የሚቀበሉበትንና ወደ ሰማያዊው መንግሥት የሚገቡበትን አጋጣሚ ለመክፈት ተጠቅሞባቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 16:1-20) ከዚያም ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እሱ መጡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። 2 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ሲመሽ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ 3 ጠዋት ላይ ደግሞ ‘ሰማዩ ቢቀላም ደመና ስለሆነ ዛሬ ብርድ ይሆናል፣ ዝናብም ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን መልክ በማየት መተርጎም ትችላላችሁ፤ የዘመኑን ምልክት ግን መተርጎም አትችሉም። 4 ክፉና አመንዝራ ትውልድ ሁልጊዜ ምልክት ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት አይሰጠውም።” ይህን ከተናገረ በኋላ ትቷቸው ሄደ። 5 ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻገሩ፤ በዚህ ጊዜ ዳቦ መያዝ ረስተው ነበር። 6 ኢየሱስ “ተጠንቀቁ፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው። 7 እነሱም እርስ በርሳቸው “ዳቦ ስላልያዝን ይሆናል” ይባባሉ ጀመር። 8 ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ዳቦ ስላልያዝን ነው ብላችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? 9 አሁንም ነጥቡ አልገባችሁም? ወይስ አምስቱ ዳቦ ለ5,000ዎቹ ሰዎች በቅቶ ከዚያ የተረፈውን ምን ያህል ቅርጫት እንደሰበሰባችሁ አታስታውሱም? 10 ወይስ ሰባቱ ዳቦ ለ4,000ዎቹ ሰዎች በቅቶ ከዚያ የተረፈውን በትላልቅ ቅርጫት ምን ያህል እንደሰበሰባችሁ ትዝ አይላችሁም? 11 ታዲያ የነገርኳችሁ ስለ ዳቦ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? እንግዲህ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” 12 በዚህ ጊዜ ተጠንቀቁ ያላቸው ከዳቦ እርሾ ሳይሆን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንደሆነ ገባቸው። 13 ኢየሱስ ወደ ቂሳርያ ፊልጵስዩስ አካባቢ በመጣ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው። 14 እነሱም “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። 15 እሱም “እናንተስ ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ?” አላቸው። 16 ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ፣ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ” ብሎ መለሰለት። 17 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ “የዮናስ ልጅ ስምዖን፣ ይህን የገለጠልህ ሥጋና ደም ሳይሆን በሰማያት ያለው አባቴ ስለሆነ ደስ ይበልህ። 18 ደግሞም እልሃለሁ፦ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህች ዓለት ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ፤ የመቃብር በሮችም አያሸንፏትም። 19 የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈታው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” 20 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አዘዛቸው።
ከየካቲት 26–መጋቢት 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 18-19
“ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን እንዳታሰናክሉ ተጠንቀቁ”
(ማቴዎስ 18:6, 7) ሆኖም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከትናንሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ጥልቅ ባሕር ውስጥ ቢሰጥም ይሻለዋል። 7 “ይህ ዓለም ሰዎችን የሚያሰናክል ነገር ስለሚያስቀምጥ ወዮለት! እርግጥ ማሰናከያ መምጣቱ የማይቀር ነው፤ ነገር ግን በእሱ ጠንቅ ሌሎች እንዲሰናከሉ ለሚያደርግ ሰው ወዮለት!
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማቴ 18:6, 7
የወፍጮ ድንጋይ፦ ወይም “በአህያ የሚዞር የወፍጮ ድንጋይ።” ቃል በቃል “የአህያ የወፍጮ ድንጋይ።” ስፋቱ ከ1.2-1.5 ሜትር ሊደርስ የሚችለው ይህ የወፍጮ ድንጋይ በጣም ትልቅና ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሊሽከረከር የሚችለው በአህያ እየተጎተተ ነው።
የሚያሰናክል ነገር፦ “የሚያሰናክል ነገር” ተብሎ የተተረጎመው ስካንዳሎን የሚለው የግሪክኛ ቃል የመጀመሪያ ፍቺ ወጥመድን እንደሚያመለክት ይገመታል፤ አንዳንዶች ቃሉ የሚያመለክተው በወጥመድ ውስጥ ምግቡ የሚቀመጥበትን ቀጭን እንጨት እንደሆነ ይናገራሉ። ከጊዜ በኋላ ቃሉ የሚያሰናክልን ወይም አደናቅፎ የሚጥልን ማንኛውንም ነገር ለማመልከት ይሠራበት ጀመር። ይህ ቃል በምሳሌያዊ መንገድ ሲሠራበት አንድ ሰው የተሳሳተ ጎዳናን እንዲከተል፣ በሥነ ምግባር እንዲሰናከል አሊያም በኃጢአት እንዲወድቅ ምክንያት የሚሆንን ድርጊት ወይም ሁኔታ ያመለክታል። ማቴ 18:8, 9 ላይ “ማሰናከል” ተብሎ የተተረጎመው ስካንዳሊዞ የሚለው ተዛማጅ ግስ “ወጥመድ መሆን፤ ኃጢአት እንዲሠራ ማድረግ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።
nwtsty ሚዲያ
የወፍጮ ድንጋይ
የወፍጮ ድንጋይ እህል ለመፍጨትና የወይራ ዘይት ለመጭመቅ ያገለግል ነበር። አንዳንዶቹ የወፍጮ ድንጋዮች አነስ ያሉ ስለሆኑ በእጅ ሊዞሩ ይችላሉ፤ ሌሎቹ ግን በጣም ትልቅ ከመሆናቸው የተነሳ የሚሽከረከሩት በእንስሳ እየተጎተቱ ነበር። ፍልስጤማውያን ሳምሶንን እንዲያሽከረክር ያስገደዱት እንዲህ ያለውን ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ ሳይሆን አይቀርም። (መሳ 16:21) በእንስሳ እየተጎተተ የሚሽከረከረው ወፍጮ በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በሮም ግዛት ውስጥ ባሉ በርካታ አካባቢዎችም የተለመደ ነበር።
የላይኛውና የታችኛው የወፍጮ ድንጋይ
እዚህ ላይ እንደሚታየው ያለ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚሽከረከረው እንደ አህያ ባሉ የቤት እንስሳት እየተጎተተ ሲሆን እህል ለመፍጨት ወይም የወይራ ፍሬ ለመጨፍለቅ ያገለግላል። የላይኛው የወፍጮ ድንጋይ ስፋት እስከ 1.5 ሜትር ሊደርስ ይችላል፤ ይህ የወፍጮ ድንጋይ፣ የበለጠ ስፋት ባለው በታችኛው የወፍጮ ድንጋይ ላይ ይሽከረከራል።
(ማቴዎስ 18:8, 9) እንግዲያው እጅህ ወይም እግርህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው። ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለማዊ እሳት ከምትወረወር ጉንድሽ ወይም አንካሳ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል። 9 እንዲሁም ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ እሳታማ ገሃነም ከምትወረወር አንድ ዓይን ኖሮህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 18:9
ገሃነም፦ ቃሉ ጌህ እና ሂኖም ከሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም “የሂኖም ሸለቆ” ማለት ነው፤ ይህ ቦታ ከጥንቷ ኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምዕራብ ይገኝ ነበር። (ከተጨማሪ መረጃ ለ12 ላይ “ኢየሩሳሌምና አካባቢዋ” የሚለውን ካርታ ተመልከት።) በኢየሱስ ዘመን የሂኖም ሸለቆ ቆሻሻ ማቃጠያ ቦታ ሆኖ ስለነበር “ገሃነም” የሚለው ቃል ሙሉ በሙሉ መጥፋትን ለማመልከት የተሠራበት መሆኑ ተገቢ ነው።
nwtstg የቃላት መፍቻ
ገሃነም
ከጥንቷ ኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምዕራብ ይገኝ ለነበረው ለሂኖም ሸለቆ የተሰጠ ከግሪክኛ ቃል የተገኘ ስም ነው። (ኤር 7:31) አስከሬን የሚጣልበት ቦታ እንደሚሆን ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ኤር 7:32፤ 19:6) እንስሳት ወይም ሰዎች በሕይወት እያሉ ወደዚያ ተጥለው እንዲቃጠሉ ወይም እንዲሠቃዩ ይደረግ እንደነበር የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። በመሆኑም የሰው ነፍስ ለዘላለም በእሳት የሚሠቃይበት በዓይን የማይታይ ቦታ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ ተገቢ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ‘በሁለተኛው ሞት’ የተመሰለውን ዘላለማዊ ቅጣት ይኸውም ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተጠቅመውበታል።—ራእይ 20:14፤ ማቴ 5:22፤ 10:28
(ማቴዎስ 18:10) በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው በሰማይ ባለው አባቴ ፊት ዘወትር ስለሚቀርቡ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 18:10
አባቴ ፊት . . . ስለሚቀርቡ፦ ወይም “አባቴ ወዳለበት መግባት ስለሚችሉ።” አምላክ ወዳለበት መግባት የሚችሉት መንፈሳዊ ፍጥረታት ብቻ ስለሆኑ የአምላክን ፊት ማየት የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው።—ዘፀ. 33:20
መንፈሳዊ ፍጥረታት ሊጠቅሙን ወይም ሊጎዱን ስለሚችሉበት መንገድ
ኢየሱስ፣ የአምላክ አገልጋዮች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንዲጠብቁ የመርዳት ኃላፊነት ለመላእክት እንደተሰጠ ጠቁሟል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ሌሎችን እንዳያሰናክሉ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ “በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው ዘወትር በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ስለሚያዩ ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ” ብሏል። (ማቴዎስ 18:10) ኢየሱስ ይህን ሲናገር እያንዳንዱ የእሱ ተከታይ ጠባቂ መልአክ ይኖረዋል ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ጋር የሚሠሩ መላእክት ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ትኩረት እንደሚሰጡ መግለጹ ነበር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 18:21, 22) ከዚያም ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” አለው። 22 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ 77 ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 18:22
77 ጊዜ፦ ቃል በቃል “70 ጊዜ 7።” ይህ የግሪክኛ አገላለጽ “70 እና 7” (77 ጊዜ) ወይም “70 ጊዜ 7” (490 ጊዜ) ማለት ሊሆን ይችላል። የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ዘፍ 4:24 ላይ የሚገኘውን የዕብራይስጥ አገላለጽ “77 ጊዜ” በማለት የተረጎመው ሲሆን ይህም “77 ጊዜ” የሚለውን አተረጓጎም የሚደግፍ ነው። ይህን አገላለጽ የምንረዳበት መንገድ ምንም ይሁን ምን የሰባት ቁጥር መደጋገም፣ ለመግለጽ የተፈለገው ነገር “በቁጥር ያልተወሰነ” ወይም “ገደብ የሌለው” መሆኑን ያመለክታል። ጴጥሮስ ሰባት ጊዜ ይቅር ለማለት ሲጠይቅ ኢየሱስ 77 ጊዜ ይቅር ሊል እንደሚገባ መናገሩ ተከታዮቹ አንድን ሰው ይቅር ለማለት ገደብ ማስቀመጥ እንደሌለባቸው ያሳያል። በተቃራኒው ግን የባቢሎናውያን ታልሙድ (ዮማ 86ቢ) እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ቢበድል በመጀመሪያው፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ጊዜ ይቅር ይባላል፤ በአራተኛው ጊዜ ግን ይቅርታ አይደረግለትም።”
(ማቴዎስ 19:7) እነሱም “ታዲያ ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት ያዘዘው ለምንድን ነው?” አሉት።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 19:7
የፍቺ የምሥክር ወረቀት፦ ሕጉ ፍቺ ለመፈጸም የሚያስብ ሰው ሕጋዊ ሰነድ እንዲያዘጋጅ ምናልባትም ሽማግሌዎችን እንዲያማክር ያዝዝ ነበር፤ ይህ ሕግ ግለሰቡ እንዲህ ያለውን ከባድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ጊዜ ይሰጠዋል። የዚህ ሕግ ዓላማ ሰዎች በችኮላ ፍቺ እንዳይፈጽሙ ማድረግ እንዲሁም ሴቶች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኙ መርዳት ነው። (ዘዳ 24:1) ይሁንና በኢየሱስ ዘመን የሃይማኖት መሪዎች ፍቺ መፈጸም ቀላል ነገር እንዲሆን አድርገው ነበር። የመጀመሪያው መቶ ዘመን የታሪክ ምሁር የነበረውና እሱ ራሱ ከሚስቱ የተፋታው ፈሪሳዊው ጆሴፈስ “በማንኛውም ምክንያት (ደግሞም ወንዶች ሚስቶቻቸውን ለመፍታት ብዙ ሰበቦችን ያቀርባሉ)” መፋታት እንደሚቻል ተናግሯል።
nwtsty ሚዲያ
የፍቺ የምሥክር ወረቀት
ይህ በ71 ወይም በ72 ዓ.ም በአረማይክ ቋንቋ የተጻፈ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ነው። የምሥክር ወረቀቱ የተገኘው ዋዲ ሙራባት ከተባለው ደረቅ ወንዝ በስተ ሰሜን ሲሆን ይህ ወንዝ በይሁዳ ምድረ በዳ ውስጥ ይገኛል። ይህ የፍቺ ወረቀት አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ ባመፁበት በስድስተኛው ዓመት የናክሳን ልጅ ዮሴፍ፣ በማሳዳ ከተማ የሚኖረው የዮናታን ልጅ የሆነችውን ሚርያምን እንደፈታት ይገልጻል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 18:18-35) “እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር የምታስሩት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈቱት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። 19 ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር ላይ ከእናንተ መካከል ሁለታችሁ አንድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ለመለመን ብትስማሙ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል። 20 ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁና።” 21 ከዚያም ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” አለው። 22 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ 77 ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም። 23 “ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ መተሳሰብ ከፈለገ አንድ ንጉሥ ጋር ይመሳሰላል። 24 ሒሳቡን መተሳሰብ በጀመረ ጊዜም 10,000 ታላንት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው አቀረቡለት። 25 ሆኖም ሰውየው ዕዳውን የሚከፍልበት ምንም መንገድ ስላልነበረው ጌታው እሱም ሆነ ሚስቱ እንዲሁም ልጆቹና ያለው ንብረት ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል አዘዘ። 26 ባሪያውም ወድቆ በመስገድ ‘ጌታዬ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። 27 ጌታውም እጅግ አዘነለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ሰረዘለት። 28 ሆኖም ይህ ባሪያ ወጥቶ ከሄደ በኋላ 100 ዲናር ያበደረውን እንደ እሱ ያለ ባሪያ አግኝቶ ያዘውና አንገቱን አንቆ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ’ አለው። 29 ባልንጀራው የሆነው ያ ባሪያም እግሩ ላይ ወድቆ ‘ወንድሜ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ይለምነው ጀመር። 30 እሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ሄዶ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍል ድረስ ወህኒ ቤት አሳሰረው። 31 ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሪያዎች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ነገር ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። 32 በዚህ ጊዜ ጌታው አስጠራውና እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ ስለተማጸንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ። 33 ታዲያ እኔ ምሕረት እንዳደረግኩልህ ሁሉ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው ባሪያ ምሕረት ልታደርግለት አይገባም ነበር?’ 34 ጌታውም በዚህ እጅግ ተቆጥቶ ያለበትን ዕዳ ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለወህኒ ቤት ጠባቂዎቹ አሳልፎ ሰጠው። 35 እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”