የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—መጋቢት 2018
ከመጋቢት 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 20-21
“ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል”
(ማቴዎስ 20:3) በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈተው የቆሙ ሌሎች ሰዎች አየ፤
nwtsty ሚዲያ
የገበያ ቦታ
በስብሰባው አስተዋጽኦ ላይ እንደሚታዩት ያሉ አንዳንድ የገበያ ቦታዎች የሚገኙት መንገድ ዳር ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ነጋዴዎች መተላለፊያ እስኪጠፋ ድረስ ብዙ ሸቀጣ ሸቀጦችን መንገድ ላይ ዘርግተው ይሸጡ ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎች የተለመዱ የቤት ቁሳቁሶችን፣ የሸክላ ዕቃዎችን፣ ውድ የሆኑ የብርጭቆ ዕቃዎችን እንዲሁም ያልቆዩ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን መግዛት ይችሉ ነበር። በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ማቀዝቀዣ ስላልነበራቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለመግዛት በየቀኑ ገበያ መውጣት ነበረባቸው። እንዲህ ባሉ ቦታዎች ገበያተኞች ከነጋዴዎች ወይም ወደዚህ ሥፍራ ከመጡ ሌሎች ሰዎች አዳዲስ ወሬዎችን የመስማት አጋጣሚ ነበራቸው። በተጨማሪም በዚህ ስፍራ፣ የሚጫወቱ ልጆችንና ሥራ ፍለጋ የወጡ ሰዎችን ማየት የተለመደ ነበር። ኢየሱስ በገበያ ቦታ የታመሙትን ፈውሷል፤ ጳውሎስም በዚያ ለሚያገኛቸው ሰዎች ሰብኳል። (ሥራ 17:17) በተቃራኒው ግን ኩሩ የነበሩት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን እንዲህ ባሉ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ሰዎች ትኩረት እንዲሰጧቸውና እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጉ ነበር።
(ማቴዎስ 20:20, 21) ከዚያም የዘብዴዎስ ሚስት ከልጆቿ ጋር ወደ እሱ ቀርባ እየሰገደች አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው። 21 እሱም “ምንድን ነው የፈለግሽው?” አላት። እሷም መልሳ “በመንግሥትህ እነዚህን ሁለቱን ልጆቼን፣ አንዱን በቀኝህ አንዱን ደግሞ በግራህ አስቀምጥልኝ” አለችው።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማቴ 20:20, 21
የዘብዴዎስ ሚስት፦ የሐዋርያቱ ያዕቆብና ዮሐንስ እናት። የማርቆስ ዘገባ ኢየሱስን ቀርበው ያነጋገሩት ያዕቆብና ዮሐንስ እንደሆኑ ይገልጻል። ሆኖም ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ሐሳቡን ያመነጩት እነሱ ቢሆኑም ጥያቄያቸውን ያቀረቡት በእናታቸው በሰሎሜ በኩል ነው፤ ሰሎሜ የኢየሱስ አክስት ሳትሆን አትቀርም።—ማቴ 27:55, 56፤ ማር 15:40, 41፤ ዮሐ 19:25
አንዱን በቀኝህ አንዱን ደግሞ በግራህ፦ እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ቦታዎች የክብርና የሥልጣን ቦታን የሚያመለክቱ ቢሆኑም የበለጠ ክብር ያለው በቀኝ በኩል የሚገኘው ቦታ ነው።—መዝ 110:1፤ ሥራ 7:55, 56፤ ሮም 8:34
(ማቴዎስ 20:25-28) ሆኖም ኢየሱስ ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የዚህ ዓለም ገዢዎች በሕዝባቸው ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቅ ሰዎችም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ። 26 በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤ 27 እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ባሪያችሁ ሊሆን ይገባል። 28 የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም።”
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማቴ 20:26, 28
አገልጋያችሁ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ዲያኮኖስ የሚለውን የግሪክኛ ቃል በአብዛኛው የሚጠቀምበት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሌሎችን በትሕትና የሚያገለግልን ሰው ለማመልከት ነው። ቃሉ ክርስቶስን (ሮም 15:8)፣ የክርስቶስ አገልጋዮችን (1ቆሮ 3:5-7፤ ቆላ 1:23)፣ የጉባኤ አገልጋዮችን (ፊልጵ 1:1፤ 1ጢሞ 3:8)፣ ቤት ውስጥ የሚያገለግሉ ሰዎችን (ዮሐ 2:5, 9) እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናትን (ሮም 13:4) ለማመልከት ተሠርቶበታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 21:9) በተጨማሪም ከፊት ከፊቱ የሚሄደውና ከኋላው የሚከተለው ሕዝብ “የዳዊትን ልጅ እንድታድነው እንለምንሃለን! በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! በሰማይ የምትኖረው ሆይ፣ እንድታድነው እንለምንሃለን!” ብሎ ይጮኽ ነበር።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 21:9
እንድታድነው እንለምንሃለን፦ ቃል በቃል “ሆሳዕና።” ይህ የግሪክኛ ቃል “እንድታድነው እንጸልያለን” ወይም “እባክህ አድነው” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ አገላለጽ የመጣ ነው። ይህ አገላለጽ እዚህ ላይ የገባው አምላክ መዳን ወይም ድል እንዲሰጥ ለመማጸን ነው፤ “እባክህ መዳን ስጠው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በጊዜ ሂደት አገላለጹ የጸሎትና የውዳሴ ክፍል ሆኖ ይሠራበት ጀመር። የዕብራይስጡ አገላለጽ በፋሲካ ወቅት ዘወትር ከሚዘመሩት የሃሌል መዝሙሮች መካከል አንዱ በሆነው በመዝ 118:25 ላይ ይገኛል። በመሆኑም በፋሲካ ወቅት ብዙ ሰዎች ይህን አገላለጽ ያስታውሱት ነበር። አምላክ የዳዊትን ልጅ እንዲያድነው የቀረበለትን ይህን ጸሎት የመለሰበት አንዱ መንገድ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት ነው። ማቴ 21:42 ላይ ኢየሱስ ራሱ መዝ 118:22, 23 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ጠቅሶ ሐሳቡ በመሲሑ ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ ገልጿል።
የዳዊትን ልጅ፦ ይህ አገላለጽ ሰዎቹ ለኢየሱስ የዘር ሐረግ እውቅና እንደሰጡና ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን አምነው እንደተቀበሉ የሚያሳይ ነው።
(ማቴዎስ 21:18, 19) በማለዳም ወደ ከተማዋ እየተመለሰ ሳለ ተራበ። 19 በመንገድ ዳር አንድ የበለስ ዛፍ አየና ወደ እሷ ሄደ፤ ሆኖም ከቅጠል በቀር ምንም ስላላገኘባት “ከእንግዲህ ወዲህ ፍሬ አይገኝብሽ” አላት። የበለስ ዛፏም ወዲያውኑ ደረቀች።
በበለስ ዛፍ ተጠቅሞ ስለ እምነት ማስተማር
ይሁንና ኢየሱስ ዛፏ እንድትደርቅ ያደረገው ለምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ምክንያቱን ገልጿል፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ እኔ በበለስ ዛፏ ላይ ያደረግኩትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆንላችኋል። እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ታገኛላችሁ።” (ማቴዎስ 21:21, 22) ይህን ሲል እምነት ተራራን እንደሚያንቀሳቅስ ከዚህ በፊት የተናገረውን ሐሳብ መድገሙ ነው።—ማቴዎስ 17:20
ስለዚህ ኢየሱስ ዛፏ እንድትደርቅ በማድረግ፣ ሐዋርያቱ በአምላክ ማመን እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ሠርቶ ማሳያ አቀረበላቸው። “በጸሎት የምትጠይቁትንና የምትለምኑትን ነገር ሁሉ እንዳገኛችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ደግሞም ታገኙታላችሁ” አላቸው። (ማርቆስ 11:24) ይህ ለሁሉም የኢየሱስ ተከታዮች የሚሆን እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ነው! በተለይ ደግሞ ሐዋርያቱ በቅርቡ ከሚያጋጥሟቸው ከባድ ፈተናዎች አንጻር ይህን ማለቱ ተገቢ ነው! ሆኖም የበለስ ዛፏ መድረቅ ከእምነት ጋር የሚያያዝበት ሌላም መንገድ አለ።
እንደዚህች የበለስ ዛፍ ሁሉ የእስራኤል ብሔርም አሳሳች መልክ አለው። ሕዝቡ ከአምላክ ጋር በቃል ኪዳን ተዛምዷል፤ እንዲሁም ሕጉን የሚጠብቅ ይመስላል። ይሁንና ብሔሩ በአጠቃላይ እምነት የለሽና መልካም ፍሬ የማያፈራ መሆኑ ታይቷል። ሌላው ቀርቶ የአምላክን ልጅ እንኳ ለመቀበል አሻፈረኝ ብሏል! በመሆኑም ኢየሱስ ፍሬያማ ያልሆነችው የበለስ ዛፍ እንድትደርቅ ማድረጉ፣ ፍሬ የማያፈራውና እምነተ ቢስ የሆነው የዚህ ብሔር የመጨረሻ ዕጣ ምን እንደሆነ ያሳያል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 20:1-19) “መንግሥተ ሰማያት በወይን እርሻው ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ማልዶ ከወጣ የእርሻ ባለቤት ጋር ይመሳሰላል። 2 በቀን አንድ ዲናር ሊከፍላቸው ከተዋዋለ በኋላ ሠራተኞቹን ወደ ወይን እርሻው ላካቸው። 3 በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈተው የቆሙ ሌሎች ሰዎች አየ፤ 4 እነዚህንም ሰዎች ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሂዱ፤ ተገቢውንም ክፍያ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው። 5 እነሱም ሄዱ። ዳግመኛም በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። 6 በመጨረሻም በ11 ሰዓት ገደማ ወጥቶ ቆመው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ አላቸው። 7 እነሱም ‘የሚቀጥረን ሰው ስላጣን ነው’ ሲሉ መለሱለት። እሱም ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሄዳችሁ ሥሩ’ አላቸው። 8 “በመሸም ጊዜ የወይኑ እርሻ ባለቤት የሠራተኞቹን ተቆጣጣሪ ‘ሠራተኞቹን ጠርተህ በመጨረሻ ከተቀጠሩት አንስቶ በመጀመሪያ እስከተቀጠሩት ድረስ ደሞዛቸውን ክፈላቸው’ አለው። 9 በ11 ሰዓት የተቀጠሩት ሰዎች መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 10 በመሆኑም በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲመጡ እነሱ የበለጠ የሚከፈላቸው መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን እነሱም የተከፈላቸው አንድ አንድ ዲናር ነበር። 11 ክፍያውን ሲቀበሉ በእርሻው ባለቤት ላይ ማጉረምረም ጀመሩ፤ 12 እንዲህም አሉት፦ ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት ሰዎች አንድ ሰዓት ብቻ ነው የሠሩት፤ ያም ሆኖ አንተ ቀኑን ሙሉ ስንደክምና በፀሐይ ስንቃጠል ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግካቸው!’ 13 እሱ ግን ከመካከላቸው ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ‘የኔ ወንድም፣ ምንም የበደልኩህ ነገር የለም። የተስማማነው አንድ ዲናር እንድከፍልህ ነው፣ አይደለም እንዴ? 14 ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ። በመጨረሻ ለተቀጠሩት ለእነዚህ ሰዎችም ለአንተ የሰጠሁትን ያህል መስጠት ፈለግኩ። 15 በገዛ ገንዘቤ የፈለግኩትን የማድረግ መብት የለኝም? ወይስ እኔ ደግ በመሆኔ ዓይንህ ተመቀኘ?’ 16 ስለሆነም ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞች ደግሞ ኋለኞች ይሆናሉ።” 17 ወደ ኢየሩሳሌም እየወጡ ሳሉ ኢየሱስ 12ቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ነጥሎ ወሰዳቸው፤ በመንገድ ላይ ሳሉም እንዲህ አላቸው፦ 18 “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል። እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ 19 እንዲሁም እንዲያፌዙበት፣ እንዲገርፉትና በእንጨት ላይ እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል።”
ከመጋቢት 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 22-23
“ሁለቱን ታላላቅ ትእዛዛት ጠብቁ”
(ማቴዎስ 22:36-38) “መምህር፣ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” 37 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ 38 ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 22:37
ልብ፦ ይህ ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሲሠራበት የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት በአጠቃላይ ያመለክታል። ሆኖም ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ቃሉ “ነፍስ” እና “አእምሮ” ከሚሉት ቃላት ጋር አብሮ ሲጠቀስ በዋነኝነት የግለሰቡን ስሜትና ፍላጎት ያመለክታል። እዚህ ላይ የገቡት ሦስት ቃላት (ልብ፣ ነፍስና አእምሮ) ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮችን የሚያመለክቱ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ አንዱ ቃል የሚያስተላልፈው ሐሳብ ሌላው ቃል ከሚያስተላልፈው ሐሳብ ጋር በተወሰነ ደረጃ ተመሳሳይነት አለው። ተቀራራቢ ትርጉም ያላቸው እነዚህ ሦስት ቃላት አንድ ላይ መጠቀሳቸው አምላክን በተሟላ ሁኔታ የመውደድን አስፈላጊነት ይበልጥ ጎላ አድርጎ ይገልጻል።
ነፍስ፦ ወይም “ሁለንተና።”
አእምሮ፦ የማሰብ ችሎታን ያመለክታል። አንድ ሰው አምላክን ለማወቅና ለእሱ ፍቅር ለማዳበር የማሰብ ችሎታውን መጠቀም አለበት። (ዮሐ 17:3፤ ሮም 12:1) ይህ ጥቅስ ከዘዳ 6:5 ላይ የተወሰደ ሲሆን እዚያ ላይ የዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ‘ልብ፣ ነፍስና ኃይል’ የሚሉትን አገላለጾች ይጠቀማል። ይሁንና የማቴዎስ ዘገባ የግሪክኛው ጽሑፍ “ኃይል” በሚለው ቃል ፋንታ “አእምሮ” የሚለውን ቃል ይጠቀማል። ይህ የሆነባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛ፣ የጥንቱ ዕብራይስጥ “አእምሮ” የሚል ቃል ባይኖረውም “ልብ” ለማለት የሚሠራበት ቃል አብዛኛውን ጊዜ “አእምሮ” የሚለውንም ሐሳብ በውስጡ ይዟል። ይህ ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሲሠራበት የአንድን ሰው ስሜትና ፍላጎት ጨምሮ ውስጣዊ ማንነቱን በአጠቃላይ ያመለክታል። (ዘዳ 29:4፤ መዝ 26:2፤ 64:6፤ ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀውን ልብ የሚለውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።) በዚህም ምክንያት የዕብራይስጡ ጽሑፍ “ልብ” የሚለውን ቃል በሚጠቀምበት ቦታ ላይ የግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀመው “አእምሮ” የሚል ትርጉም ያለውን የግሪክኛ ቃል ነው። (ዘፍ 8:21፤ 17:17፤ ምሳሌ 2:10፤ ኢሳ 14:13) ማቴዎስ፣ ዘዳ 6:5ን ሲጠቅስ “ኃይል” በሚለው ቃል ፋንታ “አእምሮ” የሚል ትርጉም ያለውን የግሪክኛ ቃል የተጠቀመበት ሌላው ምክንያት ደግሞ “ኃይል” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል አካላዊ ጥንካሬንም ሆነ የማሰብ ወይም አእምሮን የመጠቀም ችሎታን ስለሚያካትት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ የወንጌል ጸሐፊዎች ከዘዳግም ላይ ሲጠቅሱ እዚያው ላይ ያሉትን ቃላት ያልተጠቀሙት በዕብራይስጡና በግሪክኛው ጽሑፍ ላይ የገቡት አገላለጾች በሚያስተላልፉት መልእክት ረገድ የሚጋሩት ሐሳብ ስላለ ሊሆን ይችላል።
(ማቴዎስ 22:39) ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 22:39
ሁለተኛው፦ ኢየሱስ ለፈሪሳዊው የሰጠው ቀጥተኛ መልስ በማቴ 22:37 ላይ ይገኛል፤ ሆኖም ኢየሱስ ፈሪሳዊው ለጠየቀው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ በመስጠት ብቻ ሳይወሰን ሁለተኛው ትእዛዝ (ዘሌ 19:18) የቱ እንደሆነም ተናግሯል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሁለቱ ትእዛዛት አንዳቸው ከሌላው ሊነጣጠሉ እንደማይችሉና መላው ሕግም ሆነ የነቢያት ቃል በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት እንደሚጠቃለሉ አስተምሯል።—ማቴ 22:40
ባልንጀራ፦ እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም “አጠገብ ያለ ሰው” የሚል ሲሆን ቃሉ “ጎረቤት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ሆኖም ይህ አገላለጽ በአቅራቢያችን የሚኖሩ ሰዎችን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። አንድ ሰው በተለያየ አጋጣሚ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ሰዎች በሙሉ ሊያመለክት ይችላል።—ሉቃስ 10:29-37፤ ሮም 13:8-10
(ማቴዎስ 22:40) መላው ሕግም ሆነ የነቢያት ቃል በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተመሠረቱ ናቸው።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 22:40
ሕግም ሆነ የነቢያት ቃል፦ “ሕግ” የሚለው ቃል ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ያመለክታል። “የነቢያት ቃል” የሚለው ደግሞ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን የትንቢት መጻሕፍት ያመለክታል። ሆኖም እነዚህ ሁለት አገላለጾች አብረው ሲጠቀሱ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሙሉ ያመለክታሉ።—ማቴ 7:12፤ 22:40፤ ሉቃስ 16:16
የተመሠረቱ፦ እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ግስ ቃል በቃል “መንጠልጠል” የሚል ትርጉም አለው። በመሆኑም ኢየሱስ ይህን ቃል የተጠቀመው አሥርቱን ትእዛዛት የያዘው የሙሴ ሕግ ብቻ ሳይሆን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በሙሉ በፍቅር ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ለማመልከት ነው።—ሮም 13:9
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 22:21) እነሱም “የቄሳር” አሉ። እሱም “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 22:21
የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፦ ኢየሱስ ስለ ሮም ንጉሠ ነገሥት ጠቅሶ የተናገረበት ብቸኛው በጽሑፍ የሰፈረ ዘገባ የሚገኘው ኢየሱስ በሰጠው በዚህ ምላሽ ላይ ሲሆን ይህ ዘገባ በማር 12:17 እና በሉቃስ 20:25 ላይም ይገኛል። ‘የቄሳር የሆኑት’ ነገሮች ዓለማዊ መንግሥታት ለሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች የሚከፈሉ ክፍያዎችን እንዲሁም ለመንግሥት ባለሥልጣናት ሊሰጥ የሚገባውን ክብርና አንጻራዊ ተገዢነት ያካትታሉ።—ሮም 13:1-7
የአምላክ የሆነውን . . . ለአምላክ፦ ‘የአምላክ የሆኑት’ ነገሮች በሙሉ ልብ የሚቀርብ አምልኮን፣ በሙሉ ነፍስ የሚገለጽ ፍቅርን እንዲሁም ከታማኝነት የመነጨ ፍጹም ታዛዥነትን ያካትታሉ።—ማቴ 4:10፤ 22:37, 38፤ ሥራ 5:29፤ ሮም 14:8
(ማቴዎስ 23:24) እናንተ ዕውር መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ!
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 23:24
ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ፦ በእስራኤላውያን ዘንድ ርኩስ ተደርገው ከሚታዩት ፍጥረታት መካከል በጣም ትንሿ ትንኝ ስትሆን በጣም ትልቁ ደግሞ ግመል ነው። (ዘሌ 11:4, 21-24) ኢየሱስ እዚህ ላይ ምጸት የታከለበት ግነታዊ ዘይቤ እየተጠቀመ ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ በሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው መሠረት ርኩስ ላለመሆን ሲሉ ከሚጠጡት ነገር ውስጥ ትንኝን አጥልለው ያወጡ ነበር። ሆኖም በሕጉ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ነገሮች ጨርሶ ችላ በማለት ግመልን ከመዋጥ የማይተናነስ ድርጊት ይፈጽማሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 22:1-22) በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ሲል በምሳሌ ነገራቸው፦ 2 “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ከደገሰ ንጉሥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። 3 ንጉሡም ወደ ሠርጉ የተጋበዙትን እንዲጠሩ ባሪያዎቹን ላከ፤ ተጋባዦቹ ግን ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም። 4 በድጋሚ ሌሎች ባሪያዎች ልኮ ‘ተጋባዦቹን “የምሳ ግብዣ አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። ወደ ሠርጉ ኑ” በሏቸው’ አለ። 5 እነሱ ግን ግብዣውን ችላ በማለት አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ 6 ሌሎቹ ደግሞ ባሪያዎቹን ይዘው ካንገላቷቸው በኋላ ገደሏቸው። 7 “ንጉሡም እጅግ ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች ገደለ እንዲሁም ከተማቸውን አቃጠለ። 8 ከዚያም ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ሠርጉ ተደግሷል፤ የተጋበዙት ግን የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም። 9 ስለዚህ በየአውራ ጎዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ጥሩ።’ 10 በዚህ መሠረት ባሪያዎቹ ወደ አውራ ጎዳናዎች ሄደው ክፉውንም ጥሩውንም፣ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰበሰቡ፤ የሠርጉ አዳራሽም በተጋባዦች ተሞላ። 11 “ንጉሡ እንግዶቹን ለማየት ሲገባ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየ። 12 በዚህ ጊዜ ‘ወዳጄ ሆይ፣ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልክ?’ አለው። ሰውየውም የሚለው ጠፋው። 13 ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። እዚያም ሆኖ ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል’ አላቸው። 14 “የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።” 15 ከዚያም ፈሪሳውያን ሄደው በንግግሩ ሊያጠምዱት ሴራ ጠነሰሱ። 16 ስለዚህ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ጋር ወደ እሱ በመላክ እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና የአምላክን መንገድ በትክክል እንደምታስተምር እንዲሁም ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ እናውቃለን። 17 እስቲ ንገረን፣ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” 18 ኢየሱስ ግን ክፋታቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? 19 እስቲ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም አሳዩኝ።” እነሱም አንድ ዲናር አመጡለት። 20 እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። 21 እነሱም “የቄሳር” አሉ። እሱም “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው። 22 ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ከዚያም ትተውት ሄዱ።
ከመጋቢት 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 24
“በመጨረሻዎቹ ቀናት ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁዎች ሁኑ”
(ማቴዎስ 24:12) ክፋት እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል።
it-2-E 279 አን. 6
ፍቅር
ፍቅር ሊቀዘቅዝ ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት ስለሚፈጸሙት ነገሮች ለደቀ መዛሙርቱ ሲገልጽ በአምላክ እናምናለን የሚሉ ብዙ ሰዎች ፍቅራቸው (አጋፔ) እንደሚቀዘቅዝ ተናግሯል። (ማቴ 24:3, 12) ሐዋርያው ጳውሎስ ለመቋቋም አስቸጋሪ የሆነው መጪው ዘመን ስላሉት ገጽታዎች ሲናገር ሰዎች ‘ገንዘብን የሚወዱ’ እንደሚሆኑ ገልጿል። (2ጢሞ 3:1, 2) ከዚህ መረዳት እንደምንችለው አንድ ሰው ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማየት ሊሳነውና በአንድ ወቅት የነበረው ትክክለኛ ፍቅር ደብዝዞ ሊጠፋ ይችላል። በመሆኑም በአምላክ ቃል ላይ በማሰላሰል እንዲሁም ሕይወታችንን በአምላክ መመሪያዎች መሠረት በመቅረጽ ፍቅራችንን ያለማቋረጥ በተግባር ማሳየታችንና ማሳደጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ኤፌ 4:15, 22-24
(ማቴዎስ 24:39) የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።
በአምላክ ፊት ያለባችሁን ሁለንተናዊ ግዴታ እየፈጸማችሁ ነውን?
5 ኢየሱስ ክርስቶስ የምንኖርበትን አስጨናቂ ዘመን በተመለከተ እንደሚከተለው ብሏል:- “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:37-39) በልከኝነት እስከሆነ ድረስ መብላትም ሆነ መጠጣት ምንም ስህተት የለውም። ጋብቻም ቢሆን አምላክ ራሱ ያቋቋመው ዝግጅት ነው። (ዘፍጥረት 2:20-24) ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የተለመደ የዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳይ እንደሆነ ከተገነዘብን ለምን ይህን በተመለከተ አንጸልይም? ይሖዋ የመንግሥቱን ጉዳዮች እንድናስቀድም፣ ትክክል የሆነውን ነገር እንድናደርግና በእሱ ፊት ያለብንን ግዴታ እንድንፈጽም ሊረዳን ይችላል።—ማቴዎስ 6:33፤ ሮም 12:12፤ 2 ቆሮንቶስ 13:7
(ማቴዎስ 24:44) ስለዚህ እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።
ሐዋርያቱ ምልክት እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠየቁት
ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምንጊዜም ንቁና ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ተናገረ። ይህን ማስጠንቀቂያ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽም ሌላ ምሳሌ ተጠቀመ፦ “ይህን እወቁ፦ አንድ ሰው ሌባ በየትኛው ክፍለ ሌሊት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀና ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር። ስለዚህ እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።”—ማቴዎስ 24:43, 44
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 24:8) እነዚህ ነገሮች ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 24:8
የምጥ ጣር፦ የግሪክኛው ቃል ቀጥተኛ ፍቺ አንዲት ሴት ምጥ በሚይዛት ጊዜ የሚሰማትን ከባድ ሕመም ያመለክታል። ይህ አገላለጽ እዚህ ላይ የገባው ጭንቀትን፣ ሕመምንና ሥቃይን ለማመልከት ቢሆንም ቃሉ በማቴ 24:21 ላይ የተጠቀሰው ታላቅ መከራ ከመምጣቱ በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በትንቢት የተነገረው ሥቃይና መከራ የሚከሰትበት ፍጥነትም ሆነ የክስተቱ ክብደትና ርዝማኔ ልክ እንደ ምጥ እየተፋፋመ እንደሚሄድም ሊጠቁም ይችላል።
(ማቴዎስ 24:20) ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 24:20
በክረምት፦ በዚህ ወቅት የሚጥለው ኃይለኛ ዝናብ፣ የሚከሰተው ጎርፍና የሚኖረው ቀዝቃዛ አየር ከቦታ ወደ ቦታ መጓጓዝም ሆነ ምግብና መጠለያ ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርጋል።—ዕዝራ 10:9, 13
በሰንበት ቀን፦ እንደ ይሁዳ ባሉ አካባቢዎች ከሰንበት ሕግ ጋር ተያይዘው የሚጣሉት ገደቦች አንድ ሰው ረጅም ርቀት መጓዝም ሆነ ከባድ ዕቃዎችን መሸከም አስቸጋሪ እንዲሆንበት ያደርጋሉ፤ በተጨማሪም በሰንበት ቀን የከተማዋ በሮች ዝግ ይሆናሉ።—ሥራ 1:12ን እና ተጨማሪ መረጃ ለ12ን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 24:1-22) ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ እየሄደ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ወደ እሱ ቀረቡ። 2 እሱም መልሶ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አላቸው። 3 በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ መጥተው “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት። 4 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤ 5 ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ። 6 ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ። በዚህ ጊዜ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው። 7 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል። 8 እነዚህ ነገሮች ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። 9 “በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል እንዲሁም በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 10 በተጨማሪም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ። 11 ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤ 12 ክፋት እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል። 13 እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል። 14 ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል። 15 “ስለዚህ ነቢዩ ዳንኤል በተናገረው መሠረት ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’ በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፤ 16 በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ። 17 በጣሪያ ላይ ያለ ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለመውሰድ አይውረድ፤ 18 በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ አይመለስ። 19 በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! 20 ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 21 ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል። 22 እንዲያውም ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ሆኖም ለተመረጡት ሲባል ቀኖቹ ያጥራሉ።
ከመጋቢት 26–ሚያዝያ 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 25
“ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ”
(ማቴዎስ 25:1-6) “በተጨማሪም መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ ከወጡ አሥር ደናግል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። 2 አምስቱ ሞኞች፣ አምስቱ ደግሞ ልባሞች ነበሩ። 3 ሞኞቹ መብራታቸውን ቢይዙም መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር፤ 4 ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በዕቃ ዘይት ይዘው ነበር። 5 ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። 6 እኩለ ሌሊት ላይ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጫጫታ ተሰማ።
(ማቴዎስ 25:7-10) በዚህ ጊዜ ደናግሉ ሁሉ ተነስተው መብራቶቻቸውን አዘጋጁ። 8 ሞኞቹ ደናግል ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ ከያዛችሁት ዘይት ላይ ስጡን’ አሏቸው። 9 ልባሞቹም ‘ለእናንተ ከሰጠናችሁ ለእኛም ለእናንተም ላይበቃን ስለሚችል ወደ ሻጮች ሄዳችሁ ለራሳችሁ የተወሰነ ዘይት ብትገዙ ይሻላል’ ብለው መለሱላቸው። 10 ሊገዙ ሄደው ሳሉም ሙሽራው ደረሰ። ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግልም ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።
(ማቴዎስ 25:11, 12) በኋላም የቀሩት ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን!’ አሉ። 12 እሱ ግን ‘እውነቴን ነው የምላችሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 25:31-33) “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። 32 ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። 33 በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል።
የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት መደገፍ
7 በአሁኑ ጊዜ የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ በተመለከተ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አለን። በምሳሌው ላይ ስለተገለጹት ሰዎችና ቡድኖች ማንነት እንመልከት፤ “የሰው ልጅ” ወይም ንጉሥ የተባለው ኢየሱስ ነው። ንጉሡ “ወንድሞቼ” ያላቸው ሰዎች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙ በመንፈስ የተቀቡ ወንዶችና ሴቶች ናቸው። (ሮም 8:16, 17) “በጎቹ” እና “ፍየሎቹ” የተባሉት ደግሞ ከሕዝቦች ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ አይደሉም። ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ፍርድ የሚካሄደው በቅርቡ ይኸውም በታላቁ መከራ መደምደሚያ አካባቢ ነው። በሰዎች ላይ በግ ወይም ፍየል የሚለውን ፍርድ ለማስተላለፍ መሠረት የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? ይህ ፍርድ የሚሰጠው፣ ሰዎች በምድር ላይ ላሉት በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ወንድሞች ያደረጉትን ነገር መሠረት በማድረግ ነው። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም በቀረበበት በአሁኑ ወቅት ይሖዋ ይህ ምሳሌ እንዲሁም በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ የሚገኙት ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ምሳሌዎች ደረጃ በደረጃ ግልጽ እንዲሆኑልን በማድረጉ ምንኛ አመስጋኞች ነን!
(ማቴዎስ 25:40) ንጉሡም መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል።
“ወዳጆቼ ናችሁ”
16 ተስፋህ በአምላክ መንግሥት ሥር በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ከሆነ የክርስቶስ ወንድሞች ወዳጅ መሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ይህንን ማሳየት የምትችልባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ፣ በስብከቱ ሥራ በሙሉ ልብ በመካፈል ነው። ክርስቶስ ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ እንዲሰብኩ ለወንድሞቹ ትእዛዝ ሰጥቷል። (ማቴ. 24:14) ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የቀሩት የክርስቶስ ወንድሞች፣ አጋሮቻቸው የሆኑትን የሌሎች በጎችን እገዛ ሳያገኙ ይህን ኃላፊነት መወጣት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ ሰዎች በስብከቱ ሥራ በሚካፈሉበት ጊዜ ሁሉ የክርስቶስ ወንድሞች የተሰጣቸውን ቅዱስ ተልእኮ እንዲወጡ እየረዷቸው ነው ማለት ይቻላል። እንደ ክርስቶስ ሁሉ ታማኝና ልባም ባሪያም የወዳጅነት መግለጫ የሆነውን ይህን ተግባር ያደንቃል።
17 ሌሎች በጎች የክርስቶስ ወንድሞችን መርዳት የሚችሉበት ሁለተኛው መንገድ የስብከቱን ሥራ በገንዘብ በመደገፍ ነው። ኢየሱስ “በዓመፅ ሀብት” ለራሳቸው ወዳጆች እንዲያፈሩ ተከታዮቹን አበረታቷቸው ነበር። (ሉቃስ 16:9) ይህ ሲባል የኢየሱስን ወይም የይሖዋን ወዳጅነት በገንዘብ መግዛት እንችላለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቁሳዊ ሀብታችንን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመደገፍ በማዋል ወዳጅነታችንንና ፍቅራችንን በቃል ብቻ ሳይሆን “በተግባርና በእውነት” መግለጽ እንችላለን ማለት ነው። (1 ዮሐ. 3:16-18) እንዲህ ዓይነቱን ቁሳዊ ድጋፍ የምናደርገው በስብከቱ ሥራ በመካፈል፣ የአምልኮ ቦታዎቻችንን ለመገንባትና ለመጠገን የሚውል ገንዘብ በማዋጣት እንዲሁም ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ ነው። የምንሰጠው የገንዘብ መጠን ምንም ያህል ቢሆን ይሖዋና ኢየሱስ በደስታ የምናደርገውን ልግስና እንደሚያደንቁት ምንም ጥርጥር የለውም።—2 ቆሮ. 9:7
18 ሁላችንም የክርስቶስ ወዳጆች መሆናችንን የምናሳይበት ሦስተኛው መንገድ የጉባኤ ሽማግሌዎች የሚሰጡንን መመሪያ ተቀብለን በመታዘዝ ነው። ክርስቶስ የጉባኤው ራስ ስለሆነና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጉባኤውን ስለሚመራ እነዚህ ሰዎች የተሾሙት በመንፈስ ቅዱስ ነው። (ኤፌ. 5:23) ሐዋርያው ጳውሎስ “በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 13:17) አንዳንድ ጊዜ የጉባኤያችን ሽማግሌዎች የሚሰጡንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ መታዘዝ ይከብደን ይሆናል። እነዚህ ወንድሞች ጉድለት እንዳለባቸው ማስተዋላችን አይቀርም፤ ይህ ደግሞ ለሚሰጡን ምክር የተዛባ አመለካከት እንዲኖረን ሊያደርግ ይችላል። ያም ቢሆን የጉባኤው ራስ የሆነው ክርስቶስ ፍጽምና በጎደላቸው በእነዚህ ሰዎች ለመጠቀም እንደመረጠ ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም ለእነሱ ሥልጣን ያለን አመለካከት ከክርስቶስ ጋር ያለንን ወዳጅነት በቀጥታ ይነካዋል። ሽማግሌዎች በሚሠሯቸው ስህተቶች ላይ ሳናተኩር የሚሰጡንን መመሪያ በደስታ የምንታዘዝ ከሆነ ለክርስቶስ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 25:1-23) “በተጨማሪም መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ ከወጡ አሥር ደናግል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። 2 አምስቱ ሞኞች፣ አምስቱ ደግሞ ልባሞች ነበሩ። 3 ሞኞቹ መብራታቸውን ቢይዙም መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር፤ 4 ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በዕቃ ዘይት ይዘው ነበር። 5 ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። 6 እኩለ ሌሊት ላይ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጫጫታ ተሰማ። 7 በዚህ ጊዜ ደናግሉ ሁሉ ተነስተው መብራቶቻቸውን አዘጋጁ። 8 ሞኞቹ ደናግል ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ ከያዛችሁት ዘይት ላይ ስጡን’ አሏቸው። 9 ልባሞቹም ‘ለእናንተ ከሰጠናችሁ ለእኛም ለእናንተም ላይበቃን ስለሚችል ወደ ሻጮች ሄዳችሁ ለራሳችሁ የተወሰነ ዘይት ብትገዙ ይሻላል’ ብለው መለሱላቸው። 10 ሊገዙ ሄደው ሳሉም ሙሽራው ደረሰ። ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግልም ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። 11 በኋላም የቀሩት ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን!’ አሉ። 12 እሱ ግን ‘እውነቴን ነው የምላችሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው። 13 “እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ። 14 “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ባሪያዎቹን ጠርቶ ንብረቱን ለእነሱ በአደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ከተነሳ ሰው ጋር ይመሳሰላል። 15 ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፣ ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሄደ። 16 አምስት ታላንት የተቀበለው ሰው ወዲያው ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት ታላንት አተረፈ። 17 በተመሳሳይም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። 18 አንድ ታላንት ብቻ የተቀበለው ባሪያ ግን ሄዶ መሬት ቆፈረና ጌታው የሰጠውን ገንዘብ ቀበረ። 19 “ከረጅም ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባሪያዎች ጌታ መጥቶ ሒሳቡን ከባሪያዎቹ ጋር ተሳሰበ። 20 ስለዚህ አምስት ታላንት የተቀበለው ባሪያ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ ‘ጌታ ሆይ፣ አምስት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሌላ አምስት ታላንት አተረፍኩ’ አለ። 21 ጌታውም ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። 22 ቀጥሎም ሁለት ታላንት የተቀበለው ባሪያ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ፣ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሌላ ሁለት ታላንት አተረፍኩ’ አለ። 23 ጌታውም ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።