የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሚያዝያ 2018
ከሚያዝያ 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 26
“ፋሲካ እና የመታሰቢያው በዓል ያላቸው ተመሳሳይነትና ልዩነት”
(ማቴዎስ 26:17-20) የቂጣ በዓል በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጥተው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። 18 እሱም “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህሩ “የተወሰነው ጊዜዬ ደርሷል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ” ብሏል’ በሉት” አላቸው። 19 ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ለፋሲካ በዓሉም ዝግጅት አደረጉ። 20 በመሸም ጊዜ ከ12 ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።
nwtsty ሚዲያ
የፋሲካ ማዕድ
በፋሲካ ማዕድ ላይ መቅረብ ያለባቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፦ የተጠበሰ በግ (አጥንቶቹ መሰበር የለባቸውም) (1)፤ ቂጣ (2) እንዲሁም መራራ ቅጠል (3)። (ዘፀ 12:5, 8፤ ዘኁ 9:11) ሚሽና እንደሚለው ከሆነ እዚህ ላይ የተጠቀሰው መራራ ቅጠል እንደ ሰላጣ ያሉ አትክልቶችን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል፤ እስራኤላውያን ይህን ቅጠል በሚበሉበት ወቅት ግብፅ ውስጥ በባርነት ያሳለፉትን መራራ ሕይወት ሳያስታውሱ አይቀሩም። ኢየሱስ ቂጣው ፍጹም የሆነውን ሥጋውን እንደሚያመለክት ተናግሯል። (ማቴ 26:26) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ኢየሱስን “የፋሲካችን በግ” በማለት ጠርቶታል። (1ቆሮ 5:7) በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ የወይን ጠጅም (4) በፋሲካ ማዕድ ላይ ይቀርብ ነበር። ኢየሱስ የወይን ጠጁን፣ መሥዋዕት ሆኖ የሚፈሰውን ደሙን ለማመልከት ተጠቅሞበታል።—ማቴ 26:27, 28
(ማቴዎስ 26:26) እየበሉም ሳሉ ኢየሱስ ቂጣ አንስቶ ከባረከ በኋላ ቆረሰው፤ ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት “እንኩ፣ ብሉ። ይህ ሥጋዬን ያመለክታል” አለ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 26:26
ያመለክታል፦ “ማለት ነው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። የግሪክኛው ቃል ኤስቲን (ቃል በቃል “ነው” የሚል ትርጉም አለው) “ያመለክታል፤ ይወክላል” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ሐዋርያቱም ቢሆኑ ቃሉን በዚህ መንገድ እንደተረዱት ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ወቅት ፍጹም የሆነውን የኢየሱስን አካልም ሆነ የቀረበላቸውን ቂጣ ፊት ለፊት እየተመለከቱ ነበር። በመሆኑም ቂጣው ቃል በቃል ሥጋው እንዳልሆነ መረዳት አይከብዳቸውም። ማቴ 12:7 ላይም የገባው ይኸው የግሪክኛ ቃል ሲሆን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቃሉን “ማለት እንደሆነ” ብለው እንደተረጎሙት ልብ ማለት ያስፈልጋል።
(ማቴዎስ 26:27, 28) ጽዋ አንስቶም አምላክን ካመሰገነ በኋላ ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፦ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ 28 ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈሰውን ‘የቃል ኪዳን ደሜን’ ያመለክታል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 26:28
የቃል ኪዳን ደሜ፦ በይሖዋና በቅቡዓን ክርስቲያኖች መካከል የተደረገው አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራ ላይ የዋለው በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። (ዕብ 8:10) ኢየሱስ፣ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እንደ መካከለኛ ሆኖ በማገልገል የሕጉ ቃል ኪዳን ሥራውን እንዲጀምር ባደረገበት ጊዜ የተጠቀመበትን አገላለጽ ተጠቅሟል። (ዘፀ 24:8፤ ዕብ 9:19-21) የወይፈኖችና የፍየሎች ደም አምላክ ከእስራኤል ብሔር ጋር የገባውን የሕጉን ቃል እንዲጸና እንዳደረገው ሁሉ የኢየሱስ ደምም ይሖዋ ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር የገባውን አዲሱን ቃል ኪዳን እንዲጸና አድርጎታል። ይህ ቃል ኪዳን ሥራ ላይ የዋለው ከ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ ዕለት ጀምሮ ነው።—ዕብ 9:14, 15
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 26:17) የቂጣ በዓል በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጥተው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 26:17
የቂጣ በዓል በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን፦ የቂጣ በዓል የሚከበረው ከኒሳን 15 ማለትም ከፋሲካ (ኒሳን 14) ማግስት ጀምሮ ሲሆን በዓሉ ለሰባት ቀናት ይቆያል። (ተጨማሪ መረጃ ለ15ን ተመልከት።) ኢየሱስ በኖረበት ዘመን ግን ፋሲካ ከቂጣ በዓል ጋር በጥብቅ ከመቆራኘቱ የተነሳ ከኒሳን 14 ጀምሮ ያሉት ስምንት ቀናት በሙሉ “የቂጣ በዓል” ተብለው የተገለጹባቸው ጊዜያት አሉ። (ሉቃስ 22:1) “በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን” የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ “ከመከበሩ በፊት ያለው ቀን” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። (ከዮሐ 1:15, 30 ጋር አወዳድር፤ “መጀመሪያ” የሚለው የግሪክኛ ቃል ማለትም ፕሮቶስ እዚህ ጥቅስ ላይ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ የገባ ሲሆን ቃሉ “በፊት” ተብሎ ተተርጉሟል፤ ጥቅሱ “ከእኔ በፊት [ፕሮቶስ] ስለነበረ” ይላል።) በመሆኑም ከመጀመሪያው የግሪክኛ ጽሑፍም ሆነ ከአይሁዳውያን ልማድ በመነሳት ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ይህን ጥያቄ የጠየቁት ኒሳን 13 ላይ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ደቀ መዛሙርቱ “ከመሸ በኋላ” ማለትም ኒሳን 14 ሲጀምር ለሚከበረው የፋሲካ በዓል ዝግጅት ያደረጉት ኒሳን 13 በቀኑ ክፍለ ጊዜ ነበር።—ማር 14:16, 17
(ማቴዎስ 26:39) ትንሽ ወደ ፊት ራቅ በማለት በግንባሩ ተደፍቶ “አባቴ ሆይ፣ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ። ሆኖም እንደ እኔ ፈቃድ ሳይሆን እንደ አንተ ፈቃድ ይሁን” ብሎ ጸለየ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 26:39
ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጽዋ” የሚለው ቃል የአምላክን ፈቃድ ወይም ለአንድ ሰው “የተመደበለትን ድርሻ” ለማመልከት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። ኢየሱስ አምላክን በመሳደብና በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማስነሳት ተወንጅሎ መገደሉ በአምላክ ላይ የሚያመጣው ነቀፋ በጣም እንዳስጨነቀው ጥርጥር የለውም፤ ይህም ‘ጽዋው’ ከእሱ እንዲያልፍ እንዲጸልይ አነሳስቶታል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 26:1-19) ኢየሱስ ይህን ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 2 “እንደምታውቁት ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ ይከበራል፤ የሰው ልጅም በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አልፎ ይሰጣል።” 3 በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ቀያፋ ተብሎ በሚጠራው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተሰብስበው 4 የተንኮል ዘዴ በመጠቀም ኢየሱስን ለመያዝና ለመግደል ሴራ ጠነሰሱ። 5 ይሁን እንጂ “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይፈጠር በበዓሉ ወቅት መሆን የለበትም” ይሉ ነበር። 6 ኢየሱስ በቢታንያ፣ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በነበረው በስምዖን ቤት ሳለ 7 አንዲት ሴት በጣም ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እሱ ቀረበች፤ እየበላ ሳለም ዘይቱን ራሱ ላይ ታፈስ ጀመር። 8 ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲያዩ ተቆጥተው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? 9 ይህ ዘይት እኮ በውድ ዋጋ ተሸጦ ለድሆች ሊሰጥ ይችል ነበር።” 10 ኢየሱስ ስለ ምን እየተነጋገሩ እንዳለ አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? እሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች። 11 ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም። 12 ይህች ሴት ዘይቱን በሰውነቴ ላይ ስታፈስ እኔን ለቀብር ማዘጋጀቷ ነው። 13 እውነት እላችኋለሁ፣ በመላው ዓለም ይህ ምሥራች በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ይህች ሴት ያደረገችውም መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” 14 ከዚህ በኋላ፣ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ 15 “እሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነሱም 30 የብር ሳንቲሞች ሊሰጡት ተስማሙ። 16 ስለዚህ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ አጋጣሚ ይፈልግ ነበር። 17 የቂጣ በዓል በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጥተው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። 18 እሱም “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህሩ “የተወሰነው ጊዜዬ ደርሷል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ” ብሏል’ በሉት” አላቸው። 19 ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ለፋሲካ በዓሉም ዝግጅት አደረጉ።
ከሚያዝያ 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማቴዎስ 27-28
“ሂዱና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ—ለምን፣ የት እና እንዴት?”
(ማቴዎስ 28:18) ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።
‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’
4 ኢየሱስ በጉባኤው ላይ ሥልጣን የነበረው ሲሆን ከ1914 ወዲህ ደግሞ አዲስ በተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ላይ ሥልጣን ተሰጥቶታል። (ቆላስይስ 1:13፤ ራእይ 11:15) የመላእክት አለቃ እንደመሆኑ መጠን በሰማይ ያሉ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የመላእክት ሠራዊት በእርሱ ሥር ናቸው። (1 ተሰሎንቄ 4:16፤ 1 ጴጥሮስ 3:22፤ ራእይ 19:14-16) የጽድቅ መመሪያዎችን የሚጻረር “ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ” እንዲደመስስ ከአባቱ ሥልጣን ተሰጥቶታል። (1 ቆሮንቶስ 15:24-26፤ ኤፌሶን 1:20-23) ኢየሱስ ሥልጣን ያለው በሕያዋን ላይ ብቻ አይደለም። “በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ” ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ በሞት ያንቀላፉትን ለማስነሣት መለኮታዊ ኃይል አለው። (የሐዋርያት ሥራ 10:42፤ ዮሐንስ 5:26-28) እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ ሥልጣን ያለው አካል የሰጠው ትእዛዝ ትልቅ ክብደት ሊሰጠው እንደሚገባ እሙን ነው። በመሆኑም ክርስቶስ ‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ ሲል የሰጠንን ትእዛዝ በአክብሮትና በፈቃደኝነት መንፈስ እንፈጽማለን።
(ማቴዎስ 28:19) ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማቴ 28:19
ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን፦ ቃል በቃል “ሁሉም ብሔራት” የሚል ትርጉም ያለው ቢሆንም ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው ብሔራትን ሳይሆን ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ እንደሆነ ከአገባቡ መረዳት ይቻላል፤ ምክንያቱም እያጠመቃችኋቸው በሚለው አገላለጽ ውስጥ ያለው “እነሱን” የሚለው የግሪክኛ ተውላጠ ስም የሚያመለክተው ሰዎችን እንጂ ብሔራትን አይደለም። ክርስቲያኖች “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን” ፈልገው ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ የተሰጠው ይህ ትእዛዝ አዲስ ነበር። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በነበረው ጊዜ፣ አሕዛብ ይሖዋን ማምለክ ከፈለጉ ወደ እስራኤላውያን በመምጣት ከእነሱ ጋር መቀላቀል ይችሉ እንደነበር ቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቁማሉ። (1ነገ 8:41-43) ኢየሱስ በዚህ ትእዛዝ አማካኝነት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው ተልእኮ ግን ክርስቲያኖች በትውልድ አይሁዳውያን ለሆኑ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎችም መስበክ እንዳለባቸው ይጠቁማል፤ ይህም ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ዓለም አቀፍ ይዘት እንዳለው አጉልቶ ያሳያል።—ማቴ 10:1, 5-7፤ ራእይ 7:9፤ ለማቴ 24:14 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።
ደቀ መዛሙርት አድርጉ፦ ማቴቴዉኦ የሚለው የግሪክኛ ግስ “ማስተማር” ተብሎ ሊተረጎም የሚችል ሲሆን ተማሪ ወይም ደቀ መዝሙር የማፍራት ግብ ይዞ ማስተማርን ያመለክታል። (ከማቴ 13:52 ጋር አወዳድር፤ እዚህ ጥቅስ ላይ ቃሉ “የተማረ” ተብሎ ተተርጉሟል።) “እያጠመቃችኋቸው” እና “እያስተማራችኋቸው” የሚሉት ግሶች “ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለውን ትእዛዝ መፈጸም ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ያሳያሉ።
(ማቴዎስ 28:20) ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው። እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 28:20
እያስተማራችኋቸው፦ “ማስተማር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል መመሪያ መስጠትን፣ ማብራራትን፣ አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳትንና ማስረጃ ማቅረብን ያጠቃልላል። (ለማቴ 3:1፤ 4:23 የተዘጋጁትን ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች ተመልከት።) ኢየሱስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ ማስተማር ትምህርቶቹን ማሳወቅን፣ ትምህርቶቹ ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ መግለጽንና ሌሎች የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ መርዳትን የሚያካትት ቀጣይ የሆነ ሂደት ነው።—ዮሐ 13:17፤ ኤፌ 4:21፤ 1ጴጥ 2:21
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማቴዎስ 27:51) በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጣጠቁ።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማቴ 27:51
ቤተ መቅደሱ፦ ናኦስ የሚለው የግሪክኛ ቃል ቅድስቱና ቅድስተ ቅዱሳኑ የሚገኙበትን ማዕከላዊ ሕንፃ ያመለክታል።
መጋረጃ፦ ይህ ያጌጠ ጨርቅ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን ከቅድስቱ ይለይ ነበር። የአይሁድ ወግ እንደሚጠቁመው ይህ ክብደት ያለው ጨርቅ 18 ሜትር ርዝመት፣ 9 ሜትር ስፋትና 7.4 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ነበረው። ይሖዋ መጋረጃው ለሁለት እንዲቀደድ በማድረግ በልጁ ገዳዮች ላይ እንደተቆጣ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰማይ የሚያስገባው መንገድ እንደተከፈተም አሳይቷል።—ዕብ 10:19, 20፤ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
(ማቴዎስ 28:7) ስለሆነም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት እንደተነሳ ንገሯቸው፤ ‘እነሆ፣ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል። እዚያም ታዩታላችሁ’ በሏቸው። እነሆ ነግሬአችኋለሁ።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማቴ 28:7
ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት እንደተነሳ ንገሯቸው፦ እነዚህ ሴቶች ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የተነገራቸው የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ናቸው፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ይህን ዜና ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት እንዲናገሩ የታዘዙትም እነሱ ናቸው። (ማቴ 28:2, 5, 7) ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ በሌለው የአይሁድ ወግ መሠረት አንዲት ሴት የምትሰጠው ምሥክርነት በፍርድ ቤት ተቀባይነት አልነበረውም። ከዚህ በተቃራኒ የይሖዋ መልአክ ይህን አስደሳች ኃላፊነት በመስጠት እነዚህን ሴቶች አክብሯቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማቴዎስ 27:38-54) በዚያን ጊዜ ሁለት ዘራፊዎች ከእሱ ጋር፣ አንዱ በቀኙ ሌላው ደግሞ በግራው በእንጨት ላይ ተሰቅለው ነበር። 39 በዚያ የሚያልፉም ይሰድቡት ነበር፤ ራሳቸውንም እየነቀነቁ 40 “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ፣ እስቲ ራስህን አድን! የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት ላይ ውረድ!” ይሉት ነበር። 41 የካህናት አለቆችም እንደዚሁ ከጸሐፍትና ከሽማግሌዎች ጋር ሆነው እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ጀመር፦ 42 “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። 43 በአምላክ ታምኗል፤ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’ ብሎ የለ፤ አምላክ ከወደደው እስቲ አሁን ያድነው።” 44 ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ የተሰቀሉት ዘራፊዎችም እንኳ ሳይቀሩ ልክ እንደዚሁ ይነቅፉት ነበር። 45 ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አገሩ በሙሉ በጨለማ ተሸፈነ። 46 በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ “ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?” ብሎ ጮኸ፤ ይህም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። 47 በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ “ይህ ሰው ኤልያስን እየተጣራ ነው” ይሉ ጀመር። 48 ወዲያውኑም ከመካከላቸው አንዱ ሮጦ በመሄድ ሰፍነግ ወስዶ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ ውስጥ ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠው። 49 የቀሩት ግን “ተወው! ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ። 50 ኢየሱስ ዳግመኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ። 51 በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጣጠቁ። 52 መቃብሮችም ተከፈቱ፤ በሞት ካንቀላፉት ቅዱሳን ሰዎች መካከልም የብዙዎቹ አስከሬኖች ወጡ፤ 53 ብዙ ሰዎችም አዩአቸው። (ኢየሱስ ከተነሳ በኋላ ሰዎች ከመቃብር ስፍራው ወጥተው ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ገቡ።) 54 ሆኖም መኮንኑና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች የምድር ነውጡንና የተከሰቱትን ነገሮች ሲመለከቱ እጅግ ፈርተው “ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” አሉ።
ከሚያዝያ 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 1-2
“ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል”
(ማርቆስ 2:3-5) ሰዎችም አንድ ሽባ በአራት ሰዎች አሸክመው ወደ እሱ አመጡ። 4 ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሽባውን ወደ ኢየሱስ ማቅረብ ስላልቻሉ ከኢየሱስ በላይ ያለውን ጣሪያ ከነደሉ በኋላ ሽባው የተኛበትን ቃሬዛ ወደ ታች አወረዱት። 5 ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት ሽባውን “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።
“ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል”
ኢየሱስ በቤቱ ውስጥ የተሰበሰቡትን ብዙ ሰዎች እያስተማረ እያለ አራት ሰዎች ሽባ የሆነ አንድ ሰው በቃሬዛ ይዘው መጡ። ኢየሱስ ጓደኛቸውን እንዲፈውስላቸው ፈልገዋል። ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሽባውን “ወደ ኢየሱስ ማቅረብ” አልቻሉም። (ማርቆስ 2:4) እንዴት የሚያበሳጭ ነው! ሰዎቹ ግን ጠፍጣፋ ወደሆነው ጣሪያ ወጡና ነደሉት። ከዚያም ሽባውን ሰው ቃሬዛው ላይ እንደተኛ በቀዳዳው በኩል ወደታች አወረዱት።
ኢየሱስ ንግግሩን ስላቋረጡት ተናደደ? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው በጣም ተገረመ፤ ሽባውን ሰውም “ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው። (ማቴዎስ 9:2) ይሁንና ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ሊል ይችላል? ጻፎችና ፈሪሳውያን ይህን ማድረግ እንደሚችል አልተሰማቸውም፤ በመሆኑም “ይህ ሰው እንዲህ ብሎ የሚናገረው ለምንድን ነው? አምላክን እየተዳፈረ እኮ ነው። ከአንዱ ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?” ብለው አሰቡ።—ማርቆስ 2:7
ኢየሱስም ሐሳባቸውን ስላወቀ እንዲህ አላቸው፦ “በልባችሁ እንዲህ እያላችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው? ሽባውን ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነሳና ቃሬዛህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?” (ማርቆስ 2:8, 9) በእርግጥም ኢየሱስ ወደፊት የሚያቀርበውን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ የሰውየውን ኃጢአት ይቅር ማለት ይችላል።
(ማርቆስ 2:6-12) በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ግን እንዲህ ሲሉ በልባቸው አሰቡ፦ 7 “ይህ ሰው እንዲህ ብሎ የሚናገረው ለምንድን ነው? አምላክን እየተዳፈረ እኮ ነው። ከአንዱ ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?” 8 ሆኖም ኢየሱስ በልባቸው ይህን እያሰቡ እንዳሉ ወዲያው በመንፈሱ ተረድቶ “በልባችሁ እንዲህ እያላችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው? 9 ሽባውን ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነሳና ቃሬዛህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል? 10 ይሁንና የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .” ካለ በኋላ ሽባውን እንዲህ አለው፦ 11 “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ።” 12 በዚህ ጊዜ ሽባው ብድግ ብሎ ወዲያው ቃሬዛውን በማንሳት በሁሉ ፊት እየተራመደ ወጣ። ይህን ሲያዩ ሁሉም እጅግ ተደነቁ፤ ደግሞም “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም” በማለት አምላክን አከበሩ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 2:9
የቱ ይቀላል? ‘ኃጢአትን ይቅር ማለት እችላለሁ’ ብሎ መናገር ቀላል ነው፤ ምክንያቱም ይህ አባባል ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በዓይን የሚታይ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም። ‘ተነሳና . . . ሂድ’ ማለት ግን ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ሁሉም ሰው በግልጽ እንዲያይ የሚያደርግ ተአምር መፈጸምን ይጠይቃል። ይህ ጥቅስም ሆነ ኢሳ 33:24 ላይ የሚገኘው ዘገባ በሽታ የኃጢአት ውጤት እንደሆነ ይጠቁማል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማርቆስ 1:11) ከዚያም “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማር 1:11
ልጄ ነህ፦ ኢየሱስ መንፈሳዊ ፍጡር ሳለ የአምላክ ልጅ ነበር። (ዮሐ 3:16) ሰው ሆኖ ከተወለደ በኋላም፣ ፍጹም እንደነበረው እንደ አዳም “የአምላክ ልጅ” ነበር። (ሉቃስ 1:35፤ 3:38) ይሁንና አምላክ እዚህ ላይ የተናገራቸው ቃላት የኢየሱስን ማንነት ከመግለጽ ያለፈ ዓላማ አላቸው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይመስላል። አምላክ እነዚህን ቃላት በመናገርና ቅዱስ መንፈሱን በማፍሰስ ሰው የሆነውን ኢየሱስን መንፈሳዊ ልጁ አድርጎ እንደተቀበለው ጠቁሟል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ‘ዳግመኛ የተወለደ’ ሲሆን በሰማይ ወደነበረው ሕይወት የመመለስ ተስፋ ሊኖረው ችሏል፤ በተጨማሪም በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት በአምላክ የተሾመ ንጉሥና ሊቀ ካህናት ሆኗል።—ከዮሐ 3:3-6፤ 6:51፤ ሉቃስ 1:31-33፤ ዕብ 2:17፤ 5:1, 4-10፤ 7:1-3 ጋር አወዳድር።
በአንተ ደስ ይለኛል፦ ወይም “በአንተ በጣም ደስ እሰኛለሁ፤ በአንተ እጅግ እደሰታለሁ።” ተስፋ ስለተሰጠበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ ከሚናገረው ከኢሳ 42:1 ላይ በተወሰደው በማቴ 12:18 ላይም ተመሳሳይ አገላለጽ ይገኛል። አምላክ መንፈስ ቅዱስን ማፍሰሱ እንዲሁም ልጁን አስመልክቶ ይህን ሐሳብ መናገሩ ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።—ለማቴ 3:17፤ 12:18 የተዘጋጁትን ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች ተመልከት።
ድምፅ ከሰማያት መጣ፦ ይሖዋ በቀጥታ ለሰዎች እንደተናገረ ከሚገልጹት ሦስት የወንጌል ዘገባዎች መካከል ይህ የመጀመሪያው ነው።—ማር 9:7፤ ዮሐ 12:28
(ማርቆስ 2:27, 28) ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰንበት ለሰው ተሰጠ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም። 28 በመሆኑም የሰው ልጅ የሰንበትም እንኳ ጌታ ነው።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 2:28
የሰንበት . . . ጌታ፦ ኢየሱስ ከራሱ ጋር በተያያዘ ይህን አገላለጽ መጠቀሙ (ማቴ 12:8፤ ሉቃስ 6:5) በሰንበት ዕለትም ቢሆን በሰማይ ያለው አባቱ ያዘዘውን ሥራ መሥራት እንደሚችል ይጠቁማል። (ከዮሐ 5:19፤ 10:37, 38 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ የታመሙትን መፈወስን ጨምሮ እጅግ አስደናቂ የሆኑ አንዳንድ ተአምራትን የፈጸመው በሰንበት ዕለት ነው። (ሉቃስ 13:10-13፤ ዮሐ 5:5-9፤ 9:1-14) ይህም ልክ እንደ ሰንበት እረፍት በሚሆነው የመንግሥቱ አገዛዝ ወቅት ለምናገኘው እፎይታ እንደ ቅምሻ ነው ሊባል ይችላል።—ዕብ 10:1
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማርቆስ 1:1-15) የአምላክ ልጅ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸው ምሥራች የሚጀምረው እንደሚከተለው ነው፦ 2 ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “(እነሆ፣ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ፤ እሱም መንገድህን ያዘጋጃል።) 3 አንድ ሰው በምድረ በዳ ‘የይሖዋን መንገድ አዘጋጁ፤ ጎዳናዎቹንም አቅኑ’ በማለት ይጮኻል።” 4 አጥማቂው ዮሐንስ ለኃጢአት ይቅርታ፣ የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት በምድረ በዳ እየሰበከ ነበር። 5 መላው የይሁዳ ምድር እንዲሁም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በሙሉ ወደ እሱ ይመጡ ነበር፤ ደግሞም ኃጢአታቸውን በግልጽ እየተናዘዙ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በእሱ ይጠመቁ ነበር። 6 ዮሐንስ የግመል ፀጉር ይለብስ፣ ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ይታጠቅ የነበረ ሲሆን አንበጣና የዱር ማር ይበላ ነበር። 7 እንዲህ እያለም ይሰብክ ነበር፦ “ከእኔ በኋላ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔ ጎንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት አልበቃም። 8 እኔ በውኃ አጠመቅኳችሁ፤ እሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል።” 9 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት መጥቶ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በዮሐንስ ተጠመቀ። 10 ወዲያው ከውኃው እንደወጣ ሰማያት ተከፍተው መንፈስ እንደ ርግብ በእሱ ላይ ሲወርድ አየ። 11 ከዚያም “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ። 12 ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄድ ገፋፋው። 13 በምድረ በዳም 40 ቀን ቆየ። በዚያ ሳለ ሰይጣን ፈተነው፤ ከአራዊትም ጋር ነበረ። መላእክትም ያገለግሉት ነበር። 14 ዮሐንስ ከታሰረ በኋላ ኢየሱስ የአምላክን ምሥራች እየሰበከ ወደ ገሊላ ሄደ። 15 “የተወሰነው ጊዜ ደርሷል፤ የአምላክ መንግሥት ቀርቧል። ንስሐ ግቡ፤ በምሥራቹም እመኑ” ይል ነበር።
ከሚያዝያ 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 3-4
“በሰንበት መፈወስ”
(ማርቆስ 3:1, 2) ዳግመኛ ወደ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበር። 2 ኢየሱስን ሊከሱት ይፈልጉ ስለነበር ሰውየውን በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር።
በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?
በሌላ ሰንበት ኢየሱስ ወደ አንድ ምኩራብ ሄደ፤ ቦታው በገሊላ ሳይሆን አይቀርም። በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ተመለከተ። (ሉቃስ 6:6) ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ኢየሱስን በትኩረት እየተከታተሉት ነው። ለምን? “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል?” በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ዓላማቸው ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።—ማቴዎስ 12:10
የሃይማኖት መሪዎቹ በሰንበት ሕክምና መስጠት የሚቻለው ለሕይወት የሚያሰጋ ሁኔታ ከተፈጠረ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ወለም ቢለው አጥንቱን ቦታው ማስገባት ወይም በጨርቅ መጠቅለል የተከለከለ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ሁኔታዎች ለሕይወት የሚያሰጉ አይደሉም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ለኢየሱስ ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት የዚህ ሰው ሥቃይ ስላስጨነቃቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን የሚከስሱበት ሰበብ ለማግኘት ስለፈለጉ ነው።
(ማርቆስ 3:3, 4) እሱም እጁ የሰለለበትን ሰው “ተነሳና ወደ መሃል ና” አለው። 4 ከዚያም “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። እነሱ ግን ዝም አሉ።
በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?
ኢየሱስ ግን አስተሳሰባቸው ጠማማ እንደሆነ አውቋል። ‘በሰንበት መሥራትን የሚከለክለው ሕግ ተጣሰ’ የሚባለው መቼ እንደሆነ ያላቸው አመለካከት ከቅዱስ ጽሑፉ የራቀና ሚዛናዊነት የጎደለው እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ዘፀአት 20:8-10) መልካም ሥራ በመሥራቱ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ የተሳሳተ ትችት ተሰንዝሮበታል። ስለዚህ ኢየሱስ እጁ የሰለለበትን ሰው “ተነሳና ወደ መሃል ና” ብሎ በመጋበዝ በጉዳዩ ላይ ፊት ለፊት ለመነጋገር የሚያስችል መድረክ አመቻቸ።—ማርቆስ 3:3
(ማርቆስ 3:5) በልባቸው ደንዳናነት በጣም አዝኖ በዙሪያው ያሉትን በብስጭት ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እሱም በዘረጋ ጊዜ እጁ ዳነለት።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 3:5
በጣም አዝኖ . . . በብስጭት፦ ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን ልበ ደንዳናነት በተመለከተበት በዚህ ወቅት እንዲህ እንደተሰማው የዘገበው ማርቆስ ብቻ ነው። (ማቴ 12:13፤ ሉቃስ 6:10) ማርቆስ የኢየሱስን ስሜት እንዲህ ባለ ሕያው የሆነ መንገድ የገለጸው፣ እሱ ራሱ ስሜቱን መግለጽ ይቀናው የነበረው ጴጥሮስ በሰጠው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ሊሆን ይችላል።—“የማርቆስ መጽሐፍ ማስተዋወቂያ” የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማርቆስ 3:29) ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ሁሉ ለዘላለም ይቅር አይባልም፤ ከዚህ ይልቅ ለዘላለም የሚጠየቅበት ኃጢአት ይሆንበታል።”
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማር 3:29
መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ፦ ይህ አገላለጽ በአምላክ ወይም ቅዱስ በሆኑ ነገሮች ላይ የሚሰነዘርን ዘለፋ፣ ስም ማጥፋት ወይም ነቀፋ ያመለክታል። የመንፈስ ቅዱስ ምንጭ አምላክ ራሱ ስለሆነ መንፈስ ቅዱስ የሚያከናውነውን ሥራ ሆን ብሎ መቃወም ወይም መካድ አምላክን ከመሳደብ ተለይቶ አይታይም። ማቴ 12:24, 28 እና ማር 3:22 ላይ እንደተገለጸው የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ተአምር በፈጸመበት ወቅት የአምላክ መንፈስ በእሱ ላይ እየሠራ እንዳለ ቢመለከቱም ኢየሱስ ይህን ያደረገው በሰይጣን ዲያብሎስ ኃይል እንደሆነ ተናግረዋል።
ለዘላለም የሚጠየቅበት ኃጢአት፦ ዘላለማዊ መዘዝ የሚያስከትልን ሆን ተብሎ የሚሠራ ኃጢአት ያመለክታል፤ እንዲህ ያለውን ኃጢአት የሚሸፍን ምንም ዓይነት መሥዋዕት የለም።—በዚህ ጥቅስ ሥር የሚገኘውን መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ የሚለውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።
(ማርቆስ 4:26-29) ከዚያም እንዲህ አለ፦ “የአምላክ መንግሥት መሬት ላይ ዘር የሚዘራን ሰው ይመስላል። 27 ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ማለዳም ይነሳል፤ እንዴት እንደሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅልና ያድጋል። 28 መሬቱም ራሱ ቀስ በቀስ ፍሬ ያፈራል፤ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ከዚያም ዛላውን በመጨረሻም በዛላው ላይ የጎመራ ፍሬ ይሰጣል። 29 ሰብሉ እንደደረሰ ግን የመከር ወቅት በመሆኑ ሰውየው ማጭዱን ይዞ ያጭዳል።”
‘የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም ትረዳለህ?’
6 ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው ሰው የሚያደርገው መንፈሳዊ እድገት ከእኛ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። በዚህ ረገድ ትሑት መሆናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን እንዲጠመቅ ከመገፋፋት ወይም ከመጫን እንድንቆጠብ ያደርገናል። አንድን ሰው ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ ራስን ለይሖዋ የመወሰኑ ጉዳይ ግን ሙሉ በሙሉ ለግለሰቡ የተተወ እንደሆነ ማመን ይኖርብናል። አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ የሚወስነው ለአምላክ ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ ነው። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው እንዲህ ያለው ውሳኔ ብቻ ነው።—መዝ. 51:12 NW፤ መዝ. 54:6፤ 110:3
7 በሁለተኛ ደረጃ፣ የዚህን ምሳሌ ትርጉም መረዳታችን የሥራችንን ውጤት ቶሎ ባናይ ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። በዚህ ረገድ ትዕግሥተኛ መሆን ይኖርብናል። (ያዕ. 5:7, 8) ዘሩ ፍሬ ባያፈራም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችንን ለመርዳት የተቻለንን ያህል ጥረት እስካደረግን ድረስ የእኛ ታማኝነት የሚለካው በሚገኘው ውጤት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልገናል። ይሖዋ የእውነት ዘር ፍሬ እንዲያፈራ የሚያደርገው፣ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ በሆኑ ትሑት ሰዎች ልብ ውስጥ ብቻ ነው። (ማቴ. 13:23) በመሆኑም የአገልግሎታችንን ስኬት በምናገኘው ውጤት ብቻ መለካት የለብንም። ይሖዋ የአገልግሎታችንን ውጤታማነት የሚመዝነው የምናስተምራቸው ሰዎች በሚሰጡት ምላሽ አይደለም። የምናገኘው ውጤት ምንም ይሁን ምን ይሖዋ በታማኝነት የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ሉቃስ 10:17-20ን እና 1 ቆሮንቶስ 3:8ን አንብብ።
8 በሦስተኛ ደረጃ፣ ምሳሌው ሰዎች የሚያደርጉትን ለውጥ የምናስተውለው ሁልጊዜ አለመሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ከአንድ ሚስዮናዊ ጋር ያጠኑ የነበሩ ባልና ሚስትን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እነዚህ ባልና ሚስት ያልተጠመቁ አስፋፊዎች መሆን እንደሚፈልጉ ለአስጠኚያቸው ይነግሩታል። እሱም ለአስፋፊነት ብቁ እንዲሆኑ ማጨሳቸውን ማቆም እንዳለባቸው ገለጸላቸው። ባልና ሚስቱ ማጨስ ካቆሙ የተወሰኑ ወራት እንዳለፋቸው ሲነግሩት ሚስዮናዊው በጣም ተገረመ። ማጨስ ያቆሙት ለምንድን ነው? ይሖዋ ሲያጨሱ እንደሚመለከታቸውና ግብዝነትን እንደሚጠላ በመገንዘባቸው ነበር። በመሆኑም እነዚህ ባልና ሚስት ውሳኔ ማድረግ እንዳለባቸው ተሰማቸው፤ የሚያጨሱ ከሆነ በሚስዮናዊው ፊትም ቢሆን ማጨስ፣ ካልሆነ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማቆም እንዳለባቸው አሰቡ። ለይሖዋ ፍቅር ማዳበራቸው ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። ሚስዮናዊው ባያስተውለውም እንኳ እነዚህ ባልና ሚስት መንፈሳዊ እድገት አድርገው ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማርቆስ 3:1-19ሀ) ዳግመኛ ወደ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበር። 2 ኢየሱስን ሊከሱት ይፈልጉ ስለነበር ሰውየውን በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር። 3 እሱም እጁ የሰለለበትን ሰው “ተነሳና ወደ መሃል ና” አለው። 4 ከዚያም “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። እነሱ ግን ዝም አሉ። 5 በልባቸው ደንዳናነት በጣም አዝኖ በዙሪያው ያሉትን በብስጭት ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እሱም በዘረጋ ጊዜ እጁ ዳነለት። 6 ፈሪሳውያኑ ወጥተው ከሄዱ በኋላ ወዲያው ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ጋር በመሰብሰብ እንዴት እንደሚገድሉት መመካከር ጀመሩ። 7 ኢየሱስ ግን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላና ከይሁዳ የመጣ ብዙ ሕዝብም ተከተለው። 8 ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች የሰሙ ብዙ ሰዎች ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስና ከዮርዳኖስ ማዶ እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ እንኳ ሳይቀር ወደ እሱ መጡ። 9 ኢየሱስም ሕዝቡ እንዳያጨናንቀው አንዲት ትንሽ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። 10 ብዙ ሰዎችን ፈውሶ ስለነበር ከባድ በሽታ የያዛቸው ሁሉ እሱን ለመንካት በዙሪያው ይጋፉ ነበር። 11 ርኩሳን መናፍስት እንኳ ሳይቀሩ ባዩት ቁጥር በፊቱ ወድቀው “አንተ የአምላክ ልጅ ነህ” በማለት ይጮኹ ነበር። 12 ሆኖም የእሱን ማንነት ለሌሎች እንዳይገልጹ በተደጋጋሚ አጥብቆ አዘዛቸው። 13 ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ሰዎች ጠራ፤ እነሱም ወደ እሱ መጡ። 14 ከዚያም 12 ሰዎች መርጦ ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነዚህ አብረውት የሚሆኑ ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ለስብከት ሥራ የሚልካቸውና 15 አጋንንትን የማስወጣት ሥልጣን የሚሰጣቸው ናቸው። 16 የመረጣቸውም 12 ሐዋርያት እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፣ 17 የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስ (እነዚህን ቦአኔርጌስ ብሎ የሰየማቸው ሲሆን ትርጉሙም “የነጎድጓድ ልጆች” ማለት ነው)፣ 18 እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀነናዊው ስምዖን 19 እንዲሁም በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 4:9
የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፦ ኢየሱስ የዘሪውን ምሳሌ ከመናገሩ በፊት “ስሙ” ብሏል። (ማር 4:3) ምሳሌውን ሲደመድምም “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል፤ ይህም ተከታዮቹ ምክሩን በጥንቃቄ መስማታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል። በማቴ 11:15፤ 13:9, 43፤ ማር 4:23፤ ሉቃስ 8:8፤ 14:35፤ ራእይ 2:7, 11, 17, 29፤ 3:6, 13, 22፤ 13:9 ላይም ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ይገኛል።
ከሚያዝያ 30–ግንቦት 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 5-6
“ኢየሱስ በሞት ያጣናቸውን ሰዎች ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል አለው”
(ማርቆስ 5:38) ወደ ምኩራብ አለቃው ቤት በደረሱም ጊዜ ትርምሱን እንዲሁም የሚያለቅሱትንና ዋይ ዋይ የሚሉትን ሰዎች ተመለከተ።
(ማርቆስ 5:39-41) ወደ ውስጥ ከገባም በኋላ “የምታለቅሱትና የምትንጫጩት ለምንድን ነው? ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። 40 በዚህ ጊዜ በማፌዝ ይስቁበት ጀመር። እሱ ግን ሁሉንም ወደ ውጭ ካስወጣ በኋላ የልጅቷን አባትና እናት እንዲሁም ከእሱ ጋር የነበሩትን አስከትሎ ልጅቷ ወዳለችበት ገባ። 41 ከዚያም የልጅቷን እጅ ይዞ “ጣሊታ ቁሚ” አላት፤ ትርጉሙም “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” ማለት ነው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 5:39
ተኝታለች እንጂ አልሞተችም፦ ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሞት ከእንቅልፍ ጋር ተመሳስሏል። (መዝ 13:3፤ ዮሐ 11:11-14፤ ሥራ 7:60፤ 1ቆሮ 7:39፤ 15:51፤ 1ተሰ 4:13) ኢየሱስ ልጅቷን ከሞት እንደሚያስነሳት ያውቃል፤ በመሆኑም እንዲህ ብሎ የተናገረው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የወሰደው ሰው ከእንቅልፉ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ሁሉ የሞቱ ሰዎችም ከሞት ሊነሱ እንደሚችሉ ለማሳየት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ልጅቷን ከሞት ያስነሳው ‘ሙታንን ሕያው ከሚያደርገውና የሌለውን እንዳለ አድርጎ ከሚጠራው’ አባቱ ባገኘው ኃይል ነው።—ሮም 4:17
(ማርቆስ 5:42) ልጅቷም ወዲያው ተነስታ መራመድ ጀመረች። (ዕድሜዋ 12 ዓመት ነበር።) ወዲያውም እጅግ ከመደሰታቸው የተነሳ የሚሆኑት ጠፋቸው።
አንዲት ልጅ ከሞት ተነሳች!
ከዚህ ቀደም ኢየሱስ የፈወሳቸውን ሰዎች ስለ ጉዳዩ ለሌሎች እንዳያወሩ ያዝዛቸው ነበር፤ ለኢያኢሮስና ለባለቤቱም ተመሳሳይ መመሪያ ሰጣቸው። ያም ቢሆን እጅግ የተደሰቱት የልጅቷ ወላጆችና ሌሎች ሰዎች ወሬውን “በዚያ አገር ሁሉ በሰፊው” አዳረሱት። (ማቴዎስ 9:26) አንተስ የምትወደው ሰው ከሞት ሲነሳ ብትመለከት ይህን ለማውራት አትጓጓም? ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘው ኢየሱስ የፈጸመው ሁለተኛው ትንሣኤ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማርቆስ 5:19, 20) ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ከዚህ ይልቅ “ወደ ቤት ሄደህ ይሖዋ ያደረገልህን ነገር ሁሉና ያሳየህን ምሕረት ለዘመዶችህ ንገራቸው” አለው። 20 ሰውየውም ሄዶ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር በሙሉ በዲካፖሊስ ያውጅ ጀመር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተደነቁ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 5:19
ንገራቸው፦ በሌሎች ጊዜያት ኢየሱስ የፈወሳቸውን ሰዎች ስለ ጉዳዩ ለሌሎች እንዳያወሩ ያዝዛቸው ነበር። (ማር 1:44፤ 3:12፤ 7:36) ይህን ሰው ግን ስለተደረገለት ነገር ለዘመዶቹ እንዲናገር አዞታል። ኢየሱስ ይህን ያደረገው አካባቢውን ለቆ እንዲሄድ ስለተጠየቀና በዚያ ያሉትን ሰዎች አግኝቶ ሊመሠክርላቸው የሚችልበት አጋጣሚ ስለሌለው ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውየው ኢየሱስ ስላደረገለት ነገር መናገሩ በአሳማዎቹ ላይ ከተከሰተው ነገር ጋር በተያያዘ መጥፎ ወሬ እንዳይዛመት ስለሚረዳ ሊሆን ይችላል።
(ማርቆስ 6:11) ነገር ግን የሚቀበላችሁ ወይም የሚሰማችሁ ካጣችሁ ከዚያ ቦታ ስትወጡ ምሥክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 6:11
የእግራችሁን አቧራ አራግፉ፦ ይህ ድርጊት ደቀ መዛሙርቱ አምላክ በሰዎቹ ላይ ለሚወስደው እርምጃ ተጠያቂ እንደማይሆኑ የሚያመለክት ነው። በማቴ 10:14፤ ሉቃስ 9:5 ላይም ተመሳሳይ አገላለጽ ይገኛል። ማርቆስ እና ሉቃስ ይህን አገላለጽ ሲጠቀሙ ምሥክር እንዲሆንባቸው የሚለውን መግለጫ ጨምረዋል። ጳውሎስና በርናባስ በጵስድያ በምትገኘው አንጾኪያ በሰበኩበት ጊዜ ይህን መመሪያ ተግባራዊ አድርገዋል። (ሥራ 13:51) በተጨማሪም ጳውሎስ በቆሮንቶስ ልብሱን በማራገፍ ተመሳሳይ ነገር ካደረገ በኋላ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን። እኔ ንጹሕ ነኝ” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 18:6) እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ለደቀ መዛሙርቱ አዲስ ላይሆኑባቸው ይችላሉ፤ ምክንያቱም ወግ አጥባቂ የሆኑ አይሁዳውያን በአሕዛብ ክልል አቋርጠው ሲያልፉ በእግራቸው ላይ የሚያርፈውን እንደ ርኩስ አድርገው የሚቆጥሩትን አቧራ ወደ አይሁዳውያን ክልል ከመግባታቸው በፊት ያራግፉ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ይህን መመሪያ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው በአእምሮው ሌላ ነገር ይዞ እንደሆነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማርቆስ 6:1-13) ከዚያ ተነስቶ ወደ ትውልድ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 2 እሱም በሰንበት ቀን በምኩራብ ማስተማር ጀመረ፤ የሰሙትም አብዛኞቹ ሰዎች በመገረም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች የተማረው ከየት ነው? ይህን ጥበብ ያገኘውስ እንዴት ነው? ደግሞስ እንዲህ ያሉ ተአምራትን ማከናወን የቻለው እንዴት ነው? 3 ይህ አናጺው የማርያም ልጅ እንዲሁም የያዕቆብ፣ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለም? እህቶቹስ የሚኖሩት ከእኛው ጋር አይደለም?” ከዚህም የተነሳ ተሰናከሉበት። 4 ኢየሱስ ግን “ነቢይ በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ ዘንድና በገዛ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ሁሉ ይከበራል” አላቸው። 5 ስለሆነም ጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን በመጫን ከመፈወስ በቀር በዚያ ሌላ ተአምር መፈጸም አልቻለም። 6 እንዲያውም ባለማመናቸው እጅግ ተደነቀ። ከዚህ በኋላ በዙሪያው ባሉት መንደሮች እየተዘዋወረ አስተማረ። 7 አሥራ ሁለቱን ከጠራ በኋላ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያዝዙም ሥልጣን ሰጣቸው። 8 ደግሞም ከበትር በስተቀር ለጉዟቸው ዳቦም ሆነ የምግብ ከረጢት እንዲሁም በመቀነታቸው ገንዘብ እንዳይዙ አዘዛቸው፤ 9 በተጨማሪም ሁለት ልብስ እንዳይዙ፣ ጫማ ግን እንዲያደርጉ ነገራቸው። 10 አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አንድ ቤት ስትገቡ አካባቢውን ለቃችሁ እስክትሄዱ ድረስ እዚያው ቆዩ። 11 ነገር ግን የሚቀበላችሁ ወይም የሚሰማችሁ ካጣችሁ ከዚያ ቦታ ስትወጡ ምሥክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።” 12 እነሱም ከዚያ ወጥተው ሰዎች ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰበኩ፤ 13 ብዙ አጋንንትም አስወጡ፤ እንዲሁም ብዙ ሕመምተኞችን ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።