የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ታኅሣሥ 2018
ከታኅሣሥ 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት| የሐዋርያት ሥራ 9-11
“ቀንደኛ አሳዳጅ የነበረው ሰው ቀናተኛ ክርስቲያን ሆነ”
(የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2) ሳኦል ግን አሁንም በጌታ ደቀ መዛሙርት ላይ በመዛትና እነሱን ለመግደል ቆርጦ በመነሳት ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤ 2 የጌታን መንገድ የሚከተሉትን በዚያ የሚያገኛቸውን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በደማስቆ ለሚገኙ ምኩራቦች ደብዳቤ እንዲጽፍለት ጠየቀው።
ጉባኤው “ሰላም አገኘ”
ፊታቸው ላይ የብስጭት ስሜት የሚነበብባቸው መንገደኞች ክፉ ዓላማቸውን ለመፈጸም ወዳሰቡበት ወደ ደማስቆ እየተቃረቡ ነው። በሕዝቡ ዘንድ የሚጠሉትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከቤታቸው እየጎተቱ በማውጣት ለማሰርና ለማዋረድ አልፎ ተርፎም ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በማቆም ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ ለማድረግ አቅደዋል።
2 ቡድኑን የሚመራው ሳኦል የተባለው ሰው ቀድሞውንም ቢሆን የንጹሕ ሰው ደም እንዲፈስ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ ቀናተኛ የሆኑት ባልንጀሮቹ ታማኝ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረውን እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ሲገድሉት በድርጊታቸው ተባባሪ ነበር። (ሥራ 7:57 እስከ 8:1) ሳኦል በኢየሩሳሌም በሚኖሩት የኢየሱስ ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ስደት ስላላረካው የስደቱን እሳት በሌሎች ቦታዎችም ለማቀጣጠል ቀንደኛ መሪ ሆኗል። ‘የጌታ መንገድ’ ተብሎ የሚጠራውን እንደ መቅሰፍት የሚታይ ኑፋቄ ጠራርጎ ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል።—ሥራ 9:1, 2፤ “ሳኦል በደማስቆ ዓላማውን ዳር ለማድረስ የተሰጠው ሥልጣን” የሚል ርዕስ ያለውን በገጽ 61 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
(የሐዋርያት ሥራ 9:15, 16) ጌታ ግን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን እንዲሸከም ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ስለሆነ ወደ እሱ ሂድ። 16 እኔም ስለ ስሜ ሲል ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት በግልጽ አሳየዋለሁ።”
ይሖዋ እንደሚቀርጸን መገንዘባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
4 ይሖዋ ሰዎችን ሲመለከት ትኩረት የሚሰጠው ለውጫዊ ገጽታቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ልባቸውን ይኸውም ውስጣዊ ማንነታቸውን ይመረምራል። (1 ሳሙኤል 16:7ለን አንብብ።) አምላክ የክርስቲያን ጉባኤን ሲያቋቁም ያደረገው ነገር ይህን በግልጽ ያሳያል። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር እምብዛም የማይፈለጉ የሚመስሉ ብዙ ሰዎችን ወደ ራሱና ወደ ልጁ ስቧል። (ዮሐ. 6:44) ‘አምላክን የሚሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ’ የነበረውን ሳኦል የተባለ ፈሪሳዊ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። (1 ጢሞ. 1:13) ‘ልብን የሚመረምረው’ አምላክ ሳኦልን ዋጋ እንደሌለው ሸክላ አድርጎ አልቆጠረውም። (ምሳሌ 17:3) ከዚህ ይልቅ ውድ ዕቃ ተደርጎ ሊቀረጽ እንደሚችል የሸክላ አፈር አድርጎ ተመልክቶታል፤ እንዲያውም “በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት” የሚመሠክር “የተመረጠ ዕቃ” ተብሎ ተጠርቷል። (ሥራ 9:15) በተጨማሪም አምላክ ቀደም ሲል ሰካራሞች፣ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙና ሌቦች የነበሩ አንዳንድ ሰዎችን “ክቡር ለሆነ አገልግሎት” ሊውሉ እንደሚችሉ ዕቃዎች አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (ሮም 9:21፤ 1 ቆሮ. 6:9-11) እነዚህ ሰዎች ከአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት እየቀሰሙና እምነታቸው እያደገ ሲሄድ በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ሆነዋል።
(የሐዋርያት ሥራ 9:20-22) ወዲያውም ስለ ኢየሱስ እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በምኩራቦቹ ውስጥ መስበክ ጀመረ። 21 የሰሙት ሁሉ ግን እጅግ በመደነቅ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረው አይደለም? ወደዚህስ የመጣው እነሱን እያሰረ ለካህናት አለቆች ለማስረከብ አልነበረም?” 22 ሳኦል ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ የሚኖሩ አይሁዶችን ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር።
ጉባኤው “ሰላም አገኘ”
15 ሳኦል በምኩራቦች ውስጥ ስለ ኢየሱስ መስበክ ሲጀምር እዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች ምን ያህል ተደንቀው፣ ደንግጠውና ተበሳጭተው ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ? እነዚህ ሰዎች “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረ አይደለም?” ይሉ ነበር። (ሥራ 9:21) ሳኦል ስለ ኢየሱስ የነበረው አመለካከት እንዲለወጥ ያደረገው ምን እንደሆነ ሲያብራራ ኢየሱስ “እሱ ክርስቶስ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ” ያቀርብ ነበር። (ሥራ 9:22) ይሁንና አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ብቻ የሰዎች አመለካከት እንዲለወጥ ያደርጋል ማለት አይደለም። በወግ የተተበተበ አእምሮ ወይም በኩራት የተሞላ ልብ ያላቸውን ሰዎች አስተሳሰብ መቀየር አስቸጋሪ ነው። ያም ሆኖ ሳኦል ተስፋ አልቆረጠም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 9:4) እሱም መሬት ላይ ወደቀ፤ ከዚያም “ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ።
ጉባኤው “ሰላም አገኘ”
5 ኢየሱስ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ሳኦልን ከጉዞው በገታው ጊዜ “ደቀ መዛሙርቴን ለምን ታሳድዳለህ?” አላለውም። ከዚህ ይልቅ ከላይ እንደተመለከትነው “ለምን ታሳድደኛለህ?” ብሎታል። (ሥራ 9:4) አዎ፣ ኢየሱስ በተከታዮቹ ላይ የሚደርሰው መከራ በራሱ ላይ እንደደረሰ ሆኖ ይሰማዋል።—ማቴ. 25:34-40, 45
6 በክርስቶስ በማመንህ የተነሳ መከራ እየደረሰብህ ከሆነ ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ያለህበትን ሁኔታ እንደሚረዱልህ እርግጠኛ ሁን። (ማቴ. 10:22, 28-31) የሚደርስብህ መከራ ለጊዜው ላይወገድልህ ይችላል። ሳኦል በእስጢፋኖስ መገደል ሲተባበር እንዲሁም በኢየሩሳሌም የነበሩትን ታማኝ ደቀ መዛሙርት ከቤታቸው እየጎተተ ሲያወጣ ኢየሱስ ሁኔታውን ይመለከት እንደነበር አስታውስ። (ሥራ 8:3) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በወቅቱ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ አልወሰደም። ያም ሆኖ ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት ለእስጢፋኖስም ሆነ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በታማኝነት ለመጽናት የሚያስችላቸውን ብርታት ሰጥቷቸዋል።
(የሐዋርያት ሥራ 10:6) ይህ ሰው፣ ቤቱ በባሕሩ አጠገብ በሚገኘው በቆዳ ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት አርፏል።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 10:6
በቆዳ ፋቂው በስምዖን፦ ቆዳ ፋቂዎች፣ ከእንስሳት ቆዳ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚያከናውኑ ሲሆን የኖራ ውህድ በመጠቀም በእንስሳት ቆዳ ላይ ያለውን ፀጉር እንዲሁም ሥጋና ስብ ያስወግዳሉ። ከዚያም ቆዳው ለተለያዩ ነገሮች ጥቅም ላይ መዋል እንዲችል ከዕፀዋት የተቀመመ ኃይለኛ ኬሚካል በመጠቀም ያለሰልሱታል። ቆዳ ፋቂዎች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ መጥፎ ጠረን የሚፈጠር ከመሆኑም ሌላ ሥራው ብዙ ውኃ ይፈልጋል፤ ስምዖን በባሕሩ አጠገብ ምናልባትም በኢዮጴ ከተማ ዳርቻ ላይ ይኖር የነበረው ለዚህ ሊሆን ይችላል። በሙሴ ሕግ መሠረት የእንስሳት በድን የሚነካ ሰው ርኩስ ይሆናል። (ዘሌ 5:2፤ 11:39) በዚህም የተነሳ በርካታ አይሁዳውያን፣ ቆዳ ፋቂዎችን የሚንቋቸው ከመሆኑም ሌላ ቤታቸው ለማረፍ ፈቃደኞች አልነበሩም። እንዲያውም የአይሁዳውያን ታልሙድ ቆዳ መፋቅ አዛባ ከመዛቅ ይበልጥ የተናቀ ሥራ እንደሆነ ይገልጻል። ይሁንና ቆዳ ፋቂዎች የተናቁ መሆናቸው ጴጥሮስ በስምዖን ቤት እንዳያርፍ አላገደውም። ጴጥሮስ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጠባብ አመለካከት ያልነበረው መሆኑ በኋላ ላይ የተሰጠውን ተልእኮ እንዲቀበል ማለትም ከአሕዛብ ወገን ወደሆነ ሰው ቤት እንዲሄድ ረድቶታል። አንዳንድ ምሁራን “ቆዳ ፋቂ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ቢርሰስ) የስምዖን መጠሪያ እንደነበር ይናገራሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 9:10-22) በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ “ሐናንያ!” አለው። እሱም “ጌታ ሆይ፣ እነሆኝ” አለ። 11 ጌታም እንዲህ አለው፦ “ተነስተህ ‘ቀጥተኛ’ ወደተባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳም ቤት ሳኦል የሚባለውን የጠርሴስ ሰው ፈልግ። እሱም አሁን እየጸለየ ነው፤ 12 ሐናንያ የሚባል ሰው እንደሚመጣና ዓይኑ ይበራለት ዘንድ እጁን እንደሚጭንበት በራእይ አይቷል።” 13 ሐናንያ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ፣ ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳን አገልጋዮችህ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ከብዙዎች ሰምቻለሁ። 14 ወደዚህ ስፍራ የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተሰጥቶት ነው።” 15 ጌታ ግን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን እንዲሸከም ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ስለሆነ ወደ እሱ ሂድ። 16 እኔም ስለ ስሜ ሲል ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት በግልጽ አሳየዋለሁ።” 17 ስለዚህ ሐናንያ ሄደ፤ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ እጁንም በላዩ ጭኖ እንዲህ አለው፦ “ወንድሜ ሳኦል፣ ወደዚህ ስትመጣ መንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ የዓይንህ ብርሃን እንዲመለስልህና በመንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ እኔን ልኮኛል።” 18 ወዲያውም ከዓይኖቹ ላይ ቅርፊት የሚመስሉ ነገሮች ወደቁ፤ እሱም እንደገና ማየት ቻለ። ከዚያም ተነስቶ ተጠመቀ፤ 19 እንዲሁም ምግብ በልቶ ብርታት አገኘ። በደማስቆ ካሉ ደቀ መዛሙርት ጋር የተወሰኑ ቀናት ቆየ፤ 20 ወዲያውም ስለ ኢየሱስ እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በምኩራቦቹ ውስጥ መስበክ ጀመረ። 21 የሰሙት ሁሉ ግን እጅግ በመደነቅ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረው አይደለም? ወደዚህስ የመጣው እነሱን እያሰረ ለካህናት አለቆች ለማስረከብ አልነበረም?” 22 ሳኦል ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ የሚኖሩ አይሁዶችን ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር።
ከታኅሣሥ 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት| የሐዋርያት ሥራ 12-14
“በርናባስና ጳውሎስ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ደቀ መዛሙርት አፈሩ”
(የሐዋርያት ሥራ 13:2, 3) እነዚህ ይሖዋን እያገለገሉና እየጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “በርናባስንና ሳኦልን አንድ ሥራ እንዲሠሩ ስለመረጥኳቸው ለዩልኝ” አለ። 3 እነሱም ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ ከዚያም አሰናበቷቸው።
‘በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ’
4 ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ በርናባስና ሳኦል ‘ለሥራው እንዲለዩ’ በቀጥታ መመሪያ የሰጠው ለምንድን ነው? (ሥራ 13:2) መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አይገልጽም። የምናውቀው ነገር ቢኖር እነዚህ ሰዎች የተመረጡት መንፈስ ቅዱስ በሰጠው መመሪያ መሠረት መሆኑን ነው። በአንጾኪያ የነበሩት ነቢያትና አስተማሪዎች ውሳኔውን ለመቀበል አንገራግረው እንደነበር የሚጠቁም ምንም ነገር አናገኝም። ከዚህ ይልቅ የእነሱን መመረጥ ሙሉ በሙሉ ደግፈዋል። በርናባስና ሳኦል መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ምንም የቅናት ስሜት ሳያድርባቸው “ጾመውና ጸልየው እጃቸውን ከጫኑባቸው በኋላ” ሲያሰናብቷቸው ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል አስብ። (ሥራ 13:3) እኛም የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆነው የሚሾሙትን ወንድሞች ጨምሮ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን ለሚቀበሉ ሁሉ ሙሉ ድጋፍ መስጠት ይኖርብናል። እንዲህ ዓይነት መብቶችን ባገኙ ወንድሞች ላይ ከመቅናት ይልቅ “በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር የላቀ አክብሮት” ልናሳያቸው ይገባል።—1 ተሰ. 5:13
(የሐዋርያት ሥራ 13:12) አገረ ገዢውም ስለ ይሖዋ በተማረው ነገር ተደንቆ ስለነበር ይህን ባየ ጊዜ አማኝ ሆነ።
(የሐዋርያት ሥራ 13:48) ከአሕዛብ ወገን የሆኑት ይህን ሲሰሙ እጅግ በመደሰት የይሖዋን ቃል አከበሩ፤ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ።
(የሐዋርያት ሥራ 14:1) በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁዳውያን ምኩራብ ገቡ፤ በዚያም ጥሩ ንግግር ስለሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና ግሪካውያን አማኞች ሆኑ።
‘በይሖዋ ሥልጣን በድፍረት መናገር’
5 በመጀመሪያ ጳውሎስና በርናባስ የግሪክ ባሕል ማዕከልና በሮም ግዛት በገላትያ ካሉት ዋና ዋና ከተሞች አንዷ ወደሆነችው ወደ ኢቆንዮን መጡ። በዚህች ከተማ ውስጥ ብዙ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ጳውሎስና በርናባስም እንደ ልማዳቸው ወደ ምኩራብ ገብተው መስበክ ጀመሩ። (ሥራ 13:5, 14) “በዚያም ጥሩ ንግግር ስለሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና ግሪካውያን አማኞች ሆኑ።”—ሥራ 14:1
(የሐዋርያት ሥራ 14:21, 22) በዚያች ከተማ ምሥራቹን ሰብከው በርካታ ደቀ መዛሙርት ካፈሩ በኋላ ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። 22 በዚያም “በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አለብን” እያሉ በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት ደቀ መዛሙርቱን አጠናከሩ።
“ብዙ መከራ” ቢኖርም አምላክን በታማኝነት አገልግሉ
4 ቀጥሎም ጳውሎስና በርናባስ ደርቤን ጎበኙ፤ ከዚያም “ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። ደቀ መዛሙርቱን በማጠናከርና በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት ‘ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን’ አሏቸው።” (ሥራ 14:21, 22) የተናገሩት ነገር ግራ የሚያጋባ ሊመስል ይችላል። ምክንያቱም “በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ” የሚለው ሐሳብ የሚያበረታታ ሳይሆን የሚያስጨንቅ ይመስላል። ታዲያ ጳውሎስና በርናባስ መከራ እንደሚደርስባቸው ለደቀ መዛሙርቱ በመንገር ‘ያጠናከሯቸው’ እንዴት ነው?
5 ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ ብለን ከመረመርነው የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን። ጳውሎስ “በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን” ብቻ አላለም። ከዚህ ይልቅ “ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን” በማለት ተናግሯል። በመሆኑም ጳውሎስ ታማኝ መሆን የሚያስገኘውን ወሮታ በማጉላት ደቀ መዛሙርቱን አጠናክሯቸዋል። ይህ ሽልማት የሕልም እንጀራ አይደለም። ኢየሱስም ቢሆን “እስከ መጨረሻው የጸና . . . እሱ ይድናል” ብሏል።—ማቴ. 10:22
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 12:21-23) አንድ ልዩ ዝግጅት በተደረገበት ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ለሕዝቡ ንግግር መስጠት ጀመረ። 22 የተሰበሰበውም ሕዝብ “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው አይደለም!” እያለ ይጮኽ ጀመር። 23 በዚህ ጊዜ፣ ለአምላክ ክብር ባለመስጠቱ ወዲያውኑ የይሖዋ መልአክ ቀሰፈው፤ በትል ተበልቶም ሞተ።
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
12:21-23፤ 14:14-18፦ ሄሮድስ ለአምላክ ብቻ የሚገባው ክብር ሲሰጠው ተቀብሏል። የዚህ ሰው ሁኔታ፣ ተገቢ ያልሆነ ውዳሴና ክብር ሲሰጣቸው ወዲያውኑ በኃይል ከተቃወሙት ከጳውሎስና ከበርናባስ ምንኛ የተለየ ነው! እኛም በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ለምናከናውነው ለማንኛውም ነገር ክብር ከመፈለግ መቆጠብ ይኖርብናል።
(የሐዋርያት ሥራ 13:9) በዚህ ጊዜ፣ ጳውሎስ ተብሎ የሚጠራው ሳኦል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ተመለከተው፤
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሥራ 13:9
ጳውሎስ ተብሎ የሚጠራው ሳኦል፦ ከዚህ በኋላ ሳኦል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ጳውሎስ በሚለው ስም ነው። ሐዋርያው፣ በትውልድ ዕብራዊ ሲሆን የሮም ዜግነትም ነበረው። (ሥራ 22:27, 28፤ ፊልጵ 3:5) በመሆኑም ከልጅነቱ ጀምሮ ሳኦል በሚለው የዕብራይስጥ ስም እና ጳውሎስ በሚለው የሮማውያን ስም ይጠራ የነበረ ይመስላል። በዚያ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን በተለይ ደግሞ ከእስራኤል ውጭ የሚኖሩት፣ ሁለት ስም መያዛቸው የተለመደ ነበር። (ሥራ 12:12፤ 13:1) አንዳንድ የጳውሎስ ዘመዶችም በተመሳሳይ ከዕብራይስጥ ስማቸው በተጨማሪ የሮማውያን ወይም የግሪካውያን ስም ነበራቸው። (ሮም 16:7, 21) ጳውሎስ ምሥራቹን አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች የማወጅ ተልእኮ ስለተሰጠው ‘ለአሕዛብ የተላከ ሐዋርያ’ ነበር። (ሮም 11:13) ሐዋርያው፣ ሮማዊ ስሙን ለመጠቀም የመረጠ ይመስላል፤ ይህን ያደረገው በአሕዛብ ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት ለማግኘት እንደሚረዳው በማሰብ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 9:15፤ ገላ 2:7, 8) አንዳንዶች ጳውሎስ ይህን ስም መጠቀም የጀመረው ሰርግዮስ ጳውሎስ ለተባለው አገረ ገዢ ካለው አክብሮት የተነሳ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ሆኖም ጳውሎስ ቆጵሮስን ለቅቆ ከሄደም በኋላ በዚህ ስም መጠቀሙን ስለቀጠለ ይህ ሐሳብ አሳማኝ አይደለም። ሌሎች ደግሞ ጳውሎስ የዕብራይስጥ ስሙን መጠቀም የተወው የስሙ የግሪክኛ አጠራር፣ እየተጀነነ የሚሄድ ሰውን (ወይም እንስሳን) ከሚያመለክት የግሪክኛ ቃል ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ።
ጳውሎስ፦ ፓውለስ ከሚለው የላቲን ቃል የተገኘውና “ትንሽ” የሚል ትርጉም ያለው ፓቭሎስ የሚለው ስም በአማርኛው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስን ለማመልከት 189 ጊዜ፣ የቆጵሮስ አገረ ገዢ የነበረውን ሰርግዮስ ጳውሎስን ለማመልከት ደግሞ አንድ ጊዜ ተጠቅሷል።—ሥራ 13:7
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 12:1-17) በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሄሮድስ በአንዳንድ የጉባኤው አባላት ላይ ስደት ማድረስ ጀመረ። 2 የዮሐንስን ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። 3 ይህ ድርጊቱ አይሁዳውያንን እንዳስደሰተ ባየ ጊዜ ጴጥሮስን ደግሞ በቁጥጥር ሥር አዋለው። (ይህም የሆነው በቂጣ በዓል ሰሞን ነበር።) 4 ከያዘውና እስር ቤት ካስገባው በኋላ በአራት ፈረቃ፣ አራት አራት ሆነው እንዲጠብቁት ለተመደቡ ወታደሮች አስረከበው፤ ይህን ያደረገው ከፋሲካ በኋላ ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው አስቦ ነው። 5 ስለዚህ ጴጥሮስ እስር ቤት እንዲቆይ ተደረገ፤ ሆኖም ጉባኤው ስለ እሱ ወደ አምላክ አጥብቆ ይጸልይ ነበር። 6 ሄሮድስ ጴጥሮስን ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው ካሰበበት ቀን በፊት በነበረው ሌሊት፣ ጴጥሮስ በሁለት ወታደሮች መካከል በሁለት ሰንሰለቶች ታስሮ ተኝቶ ነበር፤ በር ላይ ያሉ ጠባቂዎችም እስር ቤቱን እየጠበቁ ነበር። 7 ይሁንና የይሖዋ መልአክ ድንገት መጥቶ ቆመ፤ በክፍሉም ውስጥ ብርሃን በራ። ጴጥሮስን ጎኑን መታ አድርጎ ከእንቅልፉ ቀሰቀሰውና “ቶሎ ብለህ ተነሳ!” አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ላይ ወደቁ። 8 መልአኩም “በል ልብስህን ልበስ፤ ጫማህንም አድርግ” አለው። እሱም እንደተባለው አደረገ። ከዚያም “መደረቢያህን ልበስና ተከተለኝ” አለው። 9 እሱም ወጥቶ ይከተለው ጀመር፤ ይሁንና መልአኩ እያደረገ ያለው ነገር በእውን እየተከናወነ ያለ አልመሰለውም። እንዲያውም ራእይ የሚያይ መስሎት ነበር። 10 የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ከእስር ቤቱ ወደ ከተማዋ ወደሚያስወጣው የብረት መዝጊያ ደረሱ፤ መዝጊያውም በራሱ ተከፈተላቸው። ከወጡ በኋላ በአንድ ጎዳና አብረው ተጓዙ፤ ወዲያውም መልአኩ ተለይቶት ሄደ። 11 ጴጥሮስም የሆነውን ነገር ሲረዳ “ይሖዋ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁዳውያን በእኔ ላይ ይደርሳል ብለው ካሰቡት ነገር ሁሉ እንደታደገኝ አሁን በእርግጥ አወቅኩ” አለ። 12 ይህን ከተገነዘበ በኋላ ማርቆስ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ በዚያም በርከት ያሉ ሰዎች ተሰብስበው ይጸልዩ ነበር። 13 የውጭውን በር ሲያንኳኳ ሮዳ የተባለች አንዲት አገልጋይ በሩን ለመክፈት መጣች። 14 የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑን ባወቀች ጊዜ በጣም ከመደሰቷ የተነሳ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ በመግባት ጴጥሮስ በር ላይ መቆሙን ተናገረች። 15 እነሱም “አብደሻል እንዴ!” አሏት። እሷ ግን ያንኑ አስረግጣ መናገሯን ቀጠለች። እነሱም “ከሆነም የእሱ መልአክ ይሆናል” አሉ። 16 ጴጥሮስ ግን እዚያው ቆሞ ማንኳኳቱን ቀጠለ። በሩን ከከፈቱም በኋላ ሲያዩት በጣም ተገረሙ። 17 እሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ምልክት ከሰጣቸው በኋላ ይሖዋ ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው በዝርዝር ነገራቸው፤ ከዚያም “ይህን ነገር ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሯቸው” አላቸው። ይህን ካለም በኋላ ወጥቶ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ።
ከታኅሣሥ 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት| የሐዋርያት ሥራ 15-16
“በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተው በአንድ ልብ ወሰኑ”
(የሐዋርያት ሥራ 15:1, 2) አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው “በሙሴ ሥርዓት መሠረት ካልተገረዛችሁ በቀር ልትድኑ አትችሉም” እያሉ ወንድሞችን ያስተምሩ ጀመር። 2 በዚህ የተነሳ ጳውሎስና በርናባስ ከሰዎቹ ጋር የጦፈ ክርክርና ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ። በመሆኑም ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም አንዳንድ ወንድሞች ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ጉዳዩን በዚያ ለሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ።
‘የጦፈ ክርክር’ ተነሳ
8 ሉቃስ እንዲህ በማለት ዘገባውን ይቀጥላል፦ “ይህም ጳውሎስንና በርናባስን ከሰዎቹ [“አንዳንድ ሰዎች” ከተባሉት] ጋር ወደ ጦፈ ክርክርና ጭቅጭቅ በመራቸው ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም ከመካከላቸው አንዳንድ ወንድሞች ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ጉዳዩን በዚያ ለሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ።” (ሥራ 15:2) “ክርክርና ጭቅጭቅ” የሚለው አገላለጽ በሁለቱም ወገን በያዙት ሐሳብ ድርቅ የማለት ሁኔታ እንደነበር ይጠቁማል፤ የአንጾኪያ ጉባኤ ጉዳዩን ሊፈታው አልቻለም። ጉባኤው ለሰላምና ለአንድነት ሲል ጥያቄው ኢየሩሳሌም ለሚገኙት “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች” ማለትም ለበላይ አካሉ እንዲቀርብ ወሰነ። በአንጾኪያ ከሚገኙት ሽማግሌዎች ምን ልንማር እንችላለን?
(የሐዋርያት ሥራ 15:13-20) እነሱ ተናግረው ካበቁ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞች፣ ስሙኝ። 14 አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ለእነሱ ትኩረት እንደሰጠ ሲምዖን በሚገባ ተርኳል። 15 እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል፦ 16 ‘ከዚህ በኋላ ተመልሼ የፈረሰውን የዳዊትን ድንኳን ዳግመኛ አቆማለሁ፤ ፍርስራሹንም አድሼ ዳግም እገነባዋለሁ፤ 17 ይህን የማደርገው የቀሩት ሰዎች፣ ከብሔራት ከመጡት በስሜ የተጠሩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች የሚያደርገው ይሖዋ ተናግሯል፤ 18 እነዚህም ነገሮች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ይታወቃሉ።’ 19 ስለዚህ እንደ እኔ ሐሳብ ከሆነ፣ ተለውጠው አምላክን ማምለክ የጀመሩትን አሕዛብ ባናስቸግራቸው ይሻላል፤ 20 ከዚህ ይልቅ በጣዖት ከረከሱ ነገሮች፣ ከፆታ ብልግና፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከደም እንዲርቁ እንጻፍላቸው።
እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል አክብሮት አላቸው
6 ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጉዳዩን ለመፍታት የረዳቸው ጥቅስ አሞጽ 9:11, 12 ነበር። ይህ ጥቅስ በሐዋርያት ሥራ 15:16, 17 ላይ እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፦ “ተመልሼ የፈረሰውን የዳዊትን ዳስ ዳግመኛ እገነባለሁ፤ ፍርስራሹንም ዳግም በመገንባት እንደገና አቆመዋለሁ፤ ይህንም የማደርገው የቀሩት ሰዎች በስሜ ከተጠሩት ይኸውም ከአሕዛብ ከመጡት ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች የሚያከናውነው ይሖዋ ተናግሯል።”
7 ይሁንና አንዳንድ ሰዎች ‘እንዴ፣ ይህ ጥቅስ እኮ ከአሕዛብ የመጡ አማኞች ሊገረዙ አይገባም አይልም’ የሚል የተቃውሞ ሐሳብ ይሰነዝሩ ይሆናል። ልክ ነው፣ ጥቅሱ እንደዚያ አይልም፤ ክርስቲያን የሆኑ አንዳንድ አይሁዳውያንም ጥቅሱን የተረዱት በዚህ መንገድ ነበር። እነዚህ አይሁዳውያን፣ ተገርዘው ወደ ይሁዲነት የተቀየሩትን ሰዎች የሚመለከቷቸው ‘ከአሕዛብ እንደመጡ ሰዎች’ ሳይሆን እንደ ወንድሞቻቸው ነበር። (ዘፀ. 12:48, 49) ለምሳሌ ያህል፣ በባግስተር የተዘጋጀው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም አስቴር 8:17ን “ከአሕዛብ መካከል ብዙዎቹ ተገርዘው አይሁዳዊ ሆኑ” በማለት ተርጉሞታል። በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው በተናገሩት መሠረት ከእስራኤል ቤት የቀሩት (አይሁዳውያንና ተገርዘው ወደ ይሁዲነት የተለወጡት አሕዛብ) “ከአሕዛብ ከመጡት ሰዎች” (ካልተገረዙት አሕዛብ) ጋር በመሆን በአምላክ ስም የሚጠሩ አንድ ሕዝብ ይሆናሉ፤ ስለዚህ ጥቅሱ የሚያስተላልፈው መልእክት ግልጽ ነበር። ከአሕዛብ የመጡ ሰዎች፣ ክርስቲያን ለመሆን የግድ መገረዝ አይኖርባቸውም።
(የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር፣ ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ ወስነናል፦ 29 ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋና ከፆታ ብልግና ራቁ። ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ጤና ይስጣችሁ!”
(የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5) በየከተሞቹ ሲያልፉም በዚያ ለሚያገኟቸው ሁሉ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዲጠብቁ ጉዳዩን ያሳውቋቸው ነበር። 5 ጉባኤዎቹም በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።
‘ጉባኤዎቹን ማበረታታት’
18 ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ለዓመታት አብረው አገልግለዋል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንደመሆናቸው መጠን የበላይ አካሉን በመወከል የተለያዩ ተልእኮዎችን ፈጽመዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በየከተማዎቹ ሲያልፉም በዚያ ለሚያገኟቸው ሁሉ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዲጠብቁ ያሳውቋቸው ነበር።” (ሥራ 16:4) ጉባኤዎቹ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የሰጧቸውን መመሪያ ይታዘዙ እንደነበር ግልጽ ነው። ከዚህም የተነሳ “ጉባኤዎቹ በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ” ይሄዱ ነበር።—ሥራ 16:5
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 16:6-9) ከዚህም ሌላ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በእስያ አውራጃ እንዳይናገሩ ስለከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አድርገው አለፉ። 7 ደግሞም ወደ ሚስያ በወረዱ ጊዜ ወደ ቢቲኒያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ሆኖም የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም። 8 ስለዚህ በሚስያ በኩል አልፈው ወደ ጥሮአስ ወረዱ። 9 ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው በዚያ ቆሞ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ።
ነቅቶ ስለመጠበቅ ከኢየሱስ ሐዋርያት ተማሩ
8 ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? የአምላክ መንፈስ ጣልቃ የገባው ጳውሎስ ወደ እስያ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ በኋላ እንደሆነ ልብ በሉ። ኢየሱስም መመሪያ የሰጠው ጳውሎስ ወደ ቢቲኒያ ከተቃረበ በኋላ ነበር። በመጨረሻም፣ ኢየሱስ ጳውሎስን ወደ መቄዶንያ የመራው ጥሮአስ ከደረሰ በኋላ ነበር። ኢየሱስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል። (ቆላ. 1:18) ለምሳሌ፣ አቅኚ ለመሆን ወይም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውራችሁ ለማገልገል ታስቡ ይሆናል። ኢየሱስ በአምላክ መንፈስ አማካኝነት የሚመራችሁ ግን እዚህ ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚያስችሏችሁን የተወሰኑ እርምጃዎች ከወሰዳችሁ በኋላ ሊሆን ይችላል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ አሽከርካሪ መኪናውን ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ሊጠመዝዝ የሚችለው መኪናው እየተንቀሳቀሰ ከሆነ ብቻ ነው። በተመሳሳይም ኢየሱስ አገልግሎታችንን ልናሰፋ የምንችልበትን መንገድ የሚመራን ቢሆንም ይህን የሚያደርገው የምንንቀሳቀስ ይኸውም ግባችን ላይ ለመድረስ ከልብ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው።
(የሐዋርያት ሥራ 16:37) ጳውሎስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እኛ የሮም ዜጎች ሆነን ሳለ ያለፍርድ በሕዝብ ፊት ገርፈው እስር ቤት ወረወሩን። ታዲያ አሁን በድብቅ አስወጥተው ሊጥሉን ይፈልጋሉ? እንዲህማ አይሆንም! እነሱ ራሳቸው መጥተው ይዘውን ይውጡ።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 16:37
የሮም ዜጎች ሆነን፦ ጳውሎስ የሮም ዜጋ ነበር፤ ሲላስም ቢሆን ሮማዊ የነበረ ይመስላል። በሮም ሕግ መሠረት ሮማዊ የሆነ ማንኛውም ሰው ጉዳዩ ችሎት ፊት እንዲታይለት የመጠየቅ መብት ነበረው፤ ደግሞም ጥፋተኛ ተብሎ እስካልተፈረደበት ድረስ በሕዝብ ፊት ሊቀጣ አይችልም። የሮም ዜግነት ያለው አንድ ሰው በሮም ግዛት ውስጥ የትም ቦታ ቢሄድ ዜግነቱ አንዳንድ መብቶችና ጥቅሞች ያስገኝለት ነበር። የሮም ዜጋ የሆነ ሰው የሚተዳደረው በሮም ሕግ እንጂ በሚኖርበት አውራጃ ሕግ አይደለም። ተከስሶ ለፍርድ በሚቀርብበት ጊዜ በአካባቢው ሕግ ለመዳኘት ሊስማማ ይችላል፤ ያም ቢሆን ጉዳዩ በሮም ፍርድ ቤት እንዲታይለት የመጠየቅ መብት አለው። ጥፋቱ በሞት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ የማለት መብት ነበረው። ሐዋርያው ጳውሎስ በመላው የሮም ግዛት ውስጥ በስፋት ሰብኳል። ጳውሎስ የሮም ዜጋ መሆኑ ያስገኘለትን መብት እንደተጠቀመበት የሚያሳዩ ሦስት ዘገባዎች አሉ። ይህን መብቱን እንደተጠቀመበት የሚገልጸው የመጀመሪያው ዘገባ የሚገኘው በሐዋርያት ሥራ 16:37 ላይ ሲሆን ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ከተማ የነበሩት ሕግ አስከባሪዎች እሱን መደብደባቸው መብቱን የሚጥስ ድርጊት መሆኑን ገልጿል።—ሌሎቹን ሁለት ዘገባዎች ለማግኘት ሥራ 22:25ን እና 25:11ን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 16:25-40) ይሁንና እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና አምላክን በመዝሙር እያወደሱ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር። 26 ድንገት ከባድ የምድር ነውጥ በመከሰቱ የእስር ቤቱ መሠረት ተናጋ። በተጨማሪም በሮቹ ወዲያውኑ የተከፈቱ ሲሆን ሁሉም የታሰሩበት ማሰሪያ ተፈታ። 27 የእስር ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ ነቅቶ የእስር ቤቱ በሮች መከፈታቸውን ሲያይ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ። 28 ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ “በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርግ! ሁላችንም እዚህ አለን” ሲል ተናገረ። 29 በዚህ ጊዜ የእስር ቤቱ ጠባቂ መብራት እንዲያመጡለት ጠይቆ ወደ ውስጥ ዘሎ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ ፊት ተደፋ። 30 ወደ ውጭ ካወጣቸውም በኋላ “ጌቶቼ፣ ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” አለ። 31 እነሱም “በጌታ ኢየሱስ እመን፤ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ትድናላችሁ” አሉት። 32 ከዚያም ለእሱና በቤቱ ላሉት ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ቃል ነገሯቸው። 33 ጠባቂውም ሌሊት በዚያው ሰዓት ይዟቸው ሄዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው። ከዚያም እሱና መላው ቤተሰቡ ወዲያውኑ ተጠመቁ። 34 ወደ ቤቱም ወስዶ ማዕድ አቀረበላቸው፤ በአምላክ በማመኑም ከመላው ቤተሰቡ ጋር እጅግ ተደሰተ። 35 ሲነጋም የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች “እነዚያን ሰዎች ልቀቃቸው” ብለው እንዲነግሩት መኮንኖቹን ላኩበት። 36 የእስር ቤቱ ጠባቂ የላኩትን መልእክት እንዲህ ሲል ለጳውሎስ ነገረው፦ “የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ሁለታችሁ እንድትፈቱ ሰዎች ልከዋል። ስለዚህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ።” 37 ጳውሎስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እኛ የሮም ዜጎች ሆነን ሳለ ያለፍርድ በሕዝብ ፊት ገርፈው እስር ቤት ወረወሩን። ታዲያ አሁን በድብቅ አስወጥተው ሊጥሉን ይፈልጋሉ? እንዲህማ አይሆንም! እነሱ ራሳቸው መጥተው ይዘውን ይውጡ።” 38 መኮንኖቹም ይህን ነገር ለከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ነገሯቸው። እነሱም ሰዎቹ የሮም ዜጎች መሆናቸውን ሲሰሙ ፍርሃት አደረባቸው። 39 በመሆኑም መጥተው ለመኗቸው፤ ከእስር ቤቱም ይዘዋቸው ከወጡ በኋላ ከተማዋን ለቀው እንዲሄዱ ጠየቋቸው። 40 እነሱ ግን ከእስር ቤቱ ወጥተው ወደ ሊዲያ ቤት አመሩ፤ እዚያም ወንድሞችን አግኝተው ካበረታቷቸው በኋላ ከተማዋን ለቀው ሄዱ።
ከታኅሣሥ 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት| የሐዋርያት ሥራ 17-18
“በመስበክና በማስተማር ረገድ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ተከተሉ”
(የሐዋርያት ሥራ 17:2, 3) ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ ምኩራብ ገባ፤ ለሦስት ሰንበትም ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤ 3 ክርስቶስ መከራ መቀበሉና ከሞት መነሳቱ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ በማብራራትና በማስረዳት “ይህ እኔ የማውጅላችሁ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ ነው” አላቸው።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሥራ 17:2, 3
ተወያየ፦ ጳውሎስ ለሰዎቹ ምሥራቹን በመናገር ብቻ አልተወሰነም። መልእክቱን ያብራራላቸው ከመሆኑም ሌላ ከቅዱሳን መጻሕፍት ማለትም በመንፈስ መሪነት ከተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ማስረጃ አቅርቦላቸዋል። ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ከማንበብም ባለፈ ጥቅሶቹን መሠረት በማድረግ ትምህርቱን አስረድቷቸዋል፤ እንዲሁም የአድማጮቹን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ትምህርቱን አብራርቶላቸዋል። ዲያሌዎሜ የሚለው የግሪክኛ ግስ “መወያየት፤ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ፤ መነጋገር” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህ የግሪክኛ ቃል በሥራ 17:17፤ 18:4, 19፤ 19:8, 9፤ 20:7, 9 ላይም ተሠርቶበታል።
ማስረጃ እየጠቀሰ . . . በማስረዳት፦ የግሪክኛው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ከጎን ማስቀመጥ” የሚል ፍቺ አለው። ይህም ጳውሎስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶችን በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ከተፈጸሙ ክንውኖች ጋር በማነጻጸር ትንቢቶቹ በኢየሱስ ላይ እንዴት እንደተፈጸሙ ማብራራቱን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።
(የሐዋርያት ሥራ 17:17) ስለዚህ በምኩራብ ከአይሁዳውያንና አምላክን ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎች ጋር እንዲሁም በየዕለቱ በገበያ ስፍራ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይወያይ ጀመር።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 17:17
በገበያ ስፍራ፦ ከአክሮፖሊስ በስተ ሰሜን ምዕራብ የሚገኘው የአቴንስ የገበያ ስፍራ (በግሪክኛ ኣጎራ) 200 ሜትር በ250 ሜትር ገደማ ይሆናል። ይህ ቦታ መገበያያ ብቻ አልነበረም። የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ ማዕከል ነበር። የአቴንስ ነዋሪዎች በዚያ ተገናኝተው ጥልቅ እውቀት በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ መወያየት ያስደስታቸው ነበር።
(የሐዋርያት ሥራ 17:22, 23) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ “የአቴንስ ሰዎች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ እናንተ አማልክትን እንደምትፈሩ ማየት ችያለሁ። 23 ለአብነት ያህል፣ እየተዘዋወርኩ ሳለሁ የምታመልኳቸውን ነገሮች በትኩረት ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁ። ስለዚህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ አሳውቃችኋለሁ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 17:22, 23
ለማይታወቅ አምላክ፦ በአቴንስ በሚገኝ መሠዊያ ላይ አግኖስቶ ቴኦ የሚሉት የግሪክኛ ቃላት ተቀርጸው ነበር። የአቴንስ ሰዎች አማልክትን ይፈሩ ስለነበር በርካታ ቤተ መቅደሶችንና መሠዊያዎችን ሠርተዋል፤ ሌላው ቀርቶ እንደ ዝና፣ ትሕትና፣ ኃይል፣ የማሳመን ችሎታና ርኅራኄ ላሉት የማይጨበጡ ነገሮች እንኳ መሠዊያዎችን ሠርተው ነበር። “ለማይታወቅ አምላክ” መሠዊያ ያቆሙት፣ የማያውቁት አምላክ ኖሮ ይህ አምላክ አክብሮት ስላልሰጡት እንዳይቆጣቸው በመፍራት ሊሆን ይችላል። ሕዝቡ እንዲህ ያለ መሠዊያ መሥራታቸው ጨርሶ የማያውቁት አምላክ መኖሩን አምነው እንደተቀበሉ ያሳያል። ጳውሎስ ይህን መሠዊያ በመጥቀስ አድማጮቹ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ስለማያውቁት እውነተኛ አምላክ በዘዴ መሥክሮላቸዋል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 18:18) ይሁንና ጳውሎስ በዚያ ለተወሰኑ ቀናት ከቆየ በኋላ ወንድሞችን ተሰናብቶ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋር በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ። ስእለት ስለነበረበትም ክንክራኦስ በተባለ ቦታ ፀጉሩን በአጭሩ ተቆረጠ።
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
18:18—ጳውሎስ የተሳለው ስእለት ምን ነበር? አንዳንድ ምሑራን ጳውሎስ፣ ናዝራዊ ለመሆን ተስሎ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ። (ዘኁ. 6:1-21) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ተሳለው ስእለት ምንም ፍንጭ አይሰጥም። ከዚህም በላይ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ጳውሎስ ስእለቱን የተሳለው ወደ ክርስትና ከመለወጡ በፊት ይሁን ወይም ከዚያ በኋላ እንዲሁም ስእለቱን ገና መሳሉ ይሁን ወይም መፈጸሙ ምንም አይናገሩም። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን እንዲህ ዓይነቱን ስእለት መሳል ኃጢአት አልነበረም።
(የሐዋርያት ሥራ 18:21) ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ ከፈቀደ ተመልሼ እመጣለሁ” ብሎ ተሰናበታቸው። ከዚያም ከኤፌሶን መርከብ ተሳፍሮ
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሥራ 18:21
ይሖዋ ከፈቀደ፦ ማንኛውንም ነገር ከማድረጋችን ወይም ከማቀዳችን በፊት የአምላክን ፈቃድ ከግምት የማስገባትን አስፈላጊነት የሚያጎላ አገላለጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ሁልጊዜ ይጠቀምበት ነበር። (1ቆሮ 4:19፤ 16:7፤ ዕብ 6:3) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብም አንባቢዎቹን “ይሖዋ ከፈቀደ በሕይወት እንኖራለን፤ ደግሞም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” እንዲሉ አበረታቷቸዋል። (ያዕ 4:15) ይህ አባባል እንዲሁ በዘልማድ የምንጠቀምበት ሊሆን አይገባም፤ “ይሖዋ ከፈቀደ” ብሎ የሚናገር ማንኛውም ሰው ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ይህን አባባል ሁልጊዜ ድምፃችንን አውጥተን እንድንናገር አይጠበቅብንም፤ አብዛኛውን ጊዜ ይህን የምንለው በልባችን ነው።—ተጨማሪ መረጃ ሀ5ን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 17:1-15) ከዚያም በአምፊጶሊስና በአጶሎንያ በኩል ተጉዘው የአይሁዳውያን ምኩራብ ወዳለበት ወደ ተሰሎንቄ መጡ። 2 ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ ምኩራብ ገባ፤ ለሦስት ሰንበትም ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤ 3 ክርስቶስ መከራ መቀበሉና ከሞት መነሳቱ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ በማብራራትና በማስረዳት “ይህ እኔ የማውጅላችሁ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ ነው” አላቸው። 4 ከዚህም የተነሳ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ አማኞች በመሆን ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ ከግሪካውያንም መካከል አምላክን የሚያመልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የታወቁ ሴቶች እንዲሁ አደረጉ። 5 ሆኖም አይሁዳውያን ቅናት ስላደረባቸው በገበያ ስፍራ የሚያውደለድሉ አንዳንድ ክፉ ሰዎችን አሰባስበው አሳደሙ፤ ከተማዋንም በሁከት አመሷት። ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ለረብሻ የተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ለማቅረብ የያሶንን ቤት ሰብረው ገቡ። 6 ባጧቸው ጊዜም ያሶንንና አንዳንድ ወንድሞችን እየጎተቱ ወስደው የከተማዋ ገዢዎች ፊት በማቅረብ እንዲህ እያሉ ጮኹ፦ “ዓለምን ሁሉ ያናወጡት እነዚያ ሰዎች እዚህም መጥተዋል፤ 7 ያሶንም በእንግድነት ተቀብሏቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሳርን ሕግ የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ።” 8 ሕዝቡና የከተማዋ ገዢዎች ይህን ሲሰሙ ተሸበሩ፤ 9 ያሶንን እና ሌሎቹን የዋስትና ገንዘብ እንዲያስይዙ ካደረጓቸው በኋላ ለቀቋቸው። 10 ወንድሞችም እንደመሸ ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤርያ ላኳቸው። እነሱም እዚያ እንደደረሱ ወደ አይሁዳውያን ምኩራብ ገቡ። 11 በቤርያ የነበሩት አይሁዳውያን በተሰሎንቄ ከነበሩት ይልቅ ቀና አስተሳሰብ ስለነበራቸው የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀበሉ። 12 ስለዚህ ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የተከበሩ ግሪካውያን ሴቶችና የተወሰኑ ወንዶች አማኞች ሆኑ። 13 ሆኖም በተሰሎንቄ ያሉት አይሁዳውያን ጳውሎስ የአምላክን ቃል በቤርያም እንዳወጀ ባወቁ ጊዜ ሕዝቡን ለማነሳሳትና ለማወክ ወደዚያ መጡ። 14 በዚህ ጊዜ ወንድሞች ወዲያውኑ ጳውሎስን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ላኩት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ። 15 ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴንስ አደረሱት፤ ከዚያም ጳውሎስ ‘ሲላስና ጢሞቴዎስ በተቻለ ፍጥነት ወደ እኔ እንዲመጡ ንገሯቸው’ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፤ ሰዎቹም ተመልሰው ሄዱ።
ከታኅሣሥ 31–ጥር 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት| የሐዋርያት ሥራ 19-20
‘ለራሳችሁም ሆነ ለመንጋው ሁሉ ትኩረት ስጡ’
(የሐዋርያት ሥራ 20:28) ለራሳችሁም ሆነ አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን እረኛ ሆናችሁ እንድትጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ትኩረት ስጡ።
“በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ”
5 ሐዋርያው “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ” በማለት ለሽማግሌዎች ጽፎላቸዋል። እነዚህ ሽማግሌዎች መንጋው የይሖዋና የኢየሱስ ክርስቶስ ንብረት እንደሆነ መገንዘባቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። ሽማግሌዎቹ የአምላክን በጎች የያዙበትን መንገድ በተመለከተ ለይሖዋ መልስ መስጠት ነበረባቸው። ለምሳሌ አንድ የቅርብ ጓደኛችሁ የሆነ ቦታ ሲሄድ ልጆቹን እንድትጠብቁለት አደራ ቢላችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ልጆቹን በደንብ ለመንከባከብና ለመመገብ ጥረት አታደርጉም? ከልጆቹ መካከል አንዱ ቢታመም አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኝ አታደርጉም? በተመሳሳይም የጉባኤ ሽማግሌዎች “አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን [መጠበቅ]” አለባቸው። (ሥራ 20:28) ሽማግሌዎች እያንዳንዱ በግ ውድ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የተገዛ መሆኑን ይገነዘባሉ። በተጨማሪም በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ መሆናቸውን ስለሚረዱ መንጋውን ይመግባሉ፣ ይጠብቃሉ እንዲሁም ይንከባከባሉ።
(የሐዋርያት ሥራ 20:31) “ስለዚህ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ ሌሊትና ቀን እያንዳንዳችሁን በእንባ ከማሳሰብ ወደኋላ እንዳላልኩ አስታውሱ።
‘ለደስታችን ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩት’ ክርስቲያን ሽማግሌዎች
15 እረኝነት በጣም ከባድ ሥራ ነው። ሽማግሌዎች ስለ ወንድሞቻቸው ሲያስቡና ሲጸልዩ ወይም የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በመንፈሳዊ ለመርዳት ሲሉ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩበት ጊዜ አለ። (2 ቆሮ. 11:27, 28) ያም ቢሆን ሽማግሌዎች ልክ እንደ ጳውሎስ ኃላፊነታቸውን በደስታ ስሜት ሙሉ በሙሉ ይወጣሉ። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ስለ ነፍሳችሁ ያለኝን ሁሉ፣ ራሴንም ጭምር ብሰጥ እጅግ ደስ ይለኛል።” (2 ቆሮ. 12:15) በእርግጥም ጳውሎስ ለወንድሞቹ ካለው ፍቅር የተነሳ እነሱን ለማበረታታት ራሱን ሙሉ በሙሉ ሰጥቶ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 2:4ን አንብብ፤ ፊልጵ. 2:17፤ 1 ተሰ. 2:8) ጳውሎስ በወንድሞቹ ዘንድ በጣም የተወደደ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም!—ሥራ 20:31-38
(የሐዋርያት ሥራ 20:35) እናንተም እንዲሁ እየሠራችሁ ደካማ የሆኑትን መርዳት እንዳለባችሁ በሁሉም ነገር አሳይቻችኋለሁ፤ እንዲሁም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል።”
‘ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ ነኝ’
20 የጳውሎስ የሕይወት ጎዳና በኋለኞቹ ዘመናት መንጋውን መጠቀሚያ ያደረጉት ሰዎች ከነበራቸው አኗኗር ፈጽሞ የተለየ ነው። ጳውሎስ በጉባኤው ላይ ሸክም ላለመሆን ሥራ እየሠራ ራሱን ይደግፍ ነበር። ለእምነት ባልንጀሮቹ ሲል ይደክም የነበረው የግል ጥቅም ለማግኘት ብሎ አይደለም። ጳውሎስ የኤፌሶን ሽማግሌዎች የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንዲያሳዩ አበረታቷቸዋል። “ደካማ የሆኑትን መርዳት [አለባችሁ] . . . እንዲሁም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል” ብሏቸዋል።—ሥራ 20:35
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 19:9) ሆኖም አንዳንዶቹ ግትሮች ስለነበሩ ለማመን ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የጌታን መንገድ በሕዝቡ ፊት ባጥላሉ ጊዜ ከእነሱ በመራቅ ደቀ መዛሙርቱን ለይቶ ወሰዳቸው፤ በጢራኖስ የትምህርት ቤት አዳራሽም በየዕለቱ ንግግር ይሰጥ ነበር።
ተቃውሞ ቢኖርም ‘የይሖዋ ቃል እያደገና እያሸነፈ ሄደ’
11 ጳውሎስ በዚያ የትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ንግግር ይሰጥ የነበረው ከ5:00 ሰዓት እስከ 10:00 ሰዓት ድረስ ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 19:9) ይህ ሰዓት ሰዎች ሥራቸውን አቁመው ምግብ የሚበሉበትና የሚያርፉበት ከመሆኑም ሌላ ጸጥታ የሚሰፍንበት ሆኖም ሙቀቱ እጅግ የሚያይልበት ወቅት ነው። ጳውሎስ ሁለት ዓመት ሙሉ ይህን ፕሮግራም በጥብቅ ተከትሎ ከነበረ በማስተማር ሥራው ከ3,000 ሰዓት በላይ አሳልፎ ነበር ማለት ነው። የይሖዋ ቃል እያደገና እያሸነፈ የሄደበት ሌላው ምክንያት ይህ ነው። ጳውሎስ በትጋት የሚሠራና እንደ ሁኔታው ማስተካከያ ለማድረግ የሚጥር ሰው ነበር። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል መንገድ አገልግሎቱን ማከናወን ይችል ዘንድ ፕሮግራሙን እንደ ሁኔታው አስተካክሏል። ይህ ምን ውጤት አስገኝቷል? “በእስያ አውራጃ የሚኖሩ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ የጌታን ቃል ሰሙ።” (ሥራ 19:10) በእርግጥም ጳውሎስ የተሟላ ምሥክርነት ሰጥቷል!
(የሐዋርያት ሥራ 19:19) ደግሞም አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ። የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ 50,000 የብር ሳንቲሞች ሆኖ አገኙት።
ተቃውሞ ቢኖርም ‘የይሖዋ ቃል እያደገና እያሸነፈ ሄደ’
15 በአስቄዋ ልጆች ላይ የደረሰባቸው ውርደት ብዙዎች አምላክን እንዲፈሩ ያደረገ ሲሆን በዚህም የተነሳ መናፍስታዊ ድርጊታቸውን እርግፍ አድርገው በመተው አማኞች ሆነዋል። የኤፌሶን ባሕል በአስማታዊ ድርጊቶች የተሞላ ነው። መተት ማድረግና ክታብ ማሰር እንዲሁም ድግምት መድገም የተለመዱ ነገሮች ነበሩ። በዚህ ወቅት ብዙ የኤፌሶን ነዋሪዎች ለአስማታዊ ድርጊቶች ይጠቀሙባቸው የነበሩ መጻሕፍትን አምጥተው በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ እነዚህ መጻሕፍት አሁን ባለው የዋጋ ተመን መሠረት በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ያወጡ ነበር። ሉቃስ “በዚህ መንገድ የይሖዋ ቃል በኃይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ” በማለት ዘግቧል። (ሥራ 19:17-20) እውነት በሐሰት ትምህርትና በአጋንንታዊ ድርጊት ላይ ድል እንደተቀዳጀ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ማስረጃ ነው! እነዚያ ታማኝ ሰዎች ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። እኛም የምንኖረው በመናፍስታዊ ድርጊት በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው። ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ያለው ነገር ካለን የኤፌሶን ነዋሪዎች እንዳደረጉት ወዲያውኑ ማስወገድ ይኖርብናል! ምንም ዓይነት ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍለን ቢሆን እንዲህ ካለው አስጸያፊ ድርጊት መራቅ አለብን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 19:1-20) ከጊዜ በኋላ፣ አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በመሃል አገር አቋርጦ ወደ ኤፌሶን ወረደ። በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አገኘ፤ 2 እነሱንም “አማኞች በሆናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ተቀብላችሁ ነበር?” አላቸው። እነሱም “ኧረ እኛ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰማነው ነገር የለም” ሲሉ መለሱለት። 3 እሱም “ታዲያ ምን ዓይነት ጥምቀት ነው የተጠመቃችሁት?” አላቸው። እነሱም “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት። 4 ጳውሎስም እንዲህ አላቸው፦ “ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት ነበር፤ ሰዎች ከእሱ በኋላ በሚመጣው ይኸውም በኢየሱስ እንዲያምኑ ይነግራቸው ነበር።” 5 እነሱም ይህን ሲሰሙ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠመቁ። 6 ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ እነሱም በባዕድ ቋንቋዎች መናገርና መተንበይ ጀመሩ። 7 ሰዎቹም በአጠቃላይ 12 ገደማ ነበሩ። 8 ጳውሎስም ወደ ምኩራብ እየገባ ንግግር በመስጠትና ስለ አምላክ መንግሥት አሳማኝ በሆነ መንገድ በማስረዳት ለሦስት ወራት ያህል በድፍረት ሲናገር ቆየ። 9 ሆኖም አንዳንዶቹ ግትሮች ስለነበሩ ለማመን ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የጌታን መንገድ በሕዝቡ ፊት ባጥላሉ ጊዜ ከእነሱ በመራቅ ደቀ መዛሙርቱን ለይቶ ወሰዳቸው፤ በጢራኖስ የትምህርት ቤት አዳራሽም በየዕለቱ ንግግር ይሰጥ ነበር። 10 ይህም ለሁለት ዓመት ያህል ቀጠለ፤ ከዚህም የተነሳ በእስያ አውራጃ የሚኖሩ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ የጌታን ቃል ሰሙ። 11 አምላክም በጳውሎስ እጅ በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን መፈጸሙን ቀጠለ፤ 12 ሰዎችም የጳውሎስን ሰውነት የነኩ ጨርቆችንና ሽርጦችን ወደታመሙት ሰዎች ሲወስዱ ሰዎቹ በሽታቸው ይለቃቸው ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር። 13 ይሁንና እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁዳውያን አንዳንዶቹም “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጣ አጥብቄ አዝሃለሁ” እያሉ ክፉ መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ የጌታ ኢየሱስን ስም ለመጥራት ሞከሩ። 14 አስቄዋ የተባለ የአንድ አይሁዳዊ የካህናት አለቃ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህን ያደርጉ ነበር። 15 ክፉው መንፈስ ግን መልሶ “ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ማን ናችሁ?” አላቸው። 16 ከዚያም ክፉው መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ጉብ አለባቸው፤ አሸነፋቸውም፤ ስለዚህ ራቁታቸውን ሆነውና ቆስለው ከዚያ ቤት ሸሹ። 17 በኤፌሶን የሚኖሩት አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ ይህን ሰሙ፤ በመሆኑም ሁሉም ፍርሃት አደረባቸው፤ የጌታ ኢየሱስ ስምም ይበልጥ እየገነነ ሄደ። 18 አማኞች ከሆኑት መካከል ብዙዎቹም እየመጡ ያደረጉትን ይናዘዙና በግልጽ ይናገሩ ነበር። 19 ደግሞም አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ። የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ 50,000 የብር ሳንቲሞች ሆኖ አገኙት። 20 በዚህ መንገድ የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ።