የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • lvs ምዕ. 4 ገጽ 45-59
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
  • ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • በከአምላክ ፍቅር አንብብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን ሥልጣን ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?
  • በቤተሰብ ውስጥ ሥልጣንን ማክበር
  • በጉባኤ ውስጥ ሥልጣንን ማክበር
  • የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማክበር
  • ለሌሎች አክብሮት አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በእናንተ ላይ ሥልጣን የተሰጣቸውን አክብሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ ነህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • አክብሮት ማሳየት ቀረ እንዴ?
    ንቁ!—2024
ለተጨማሪ መረጃ
ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
lvs ምዕ. 4 ገጽ 45-59
አንድ አባት ለልጆቹ በፍቅር እርማት ሲሰጥ

ምዕራፍ 4

ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

“ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ፤ አምላክን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።”—1 ጴጥሮስ 2:17

1, 2. (ሀ) ማን የሚሰጠንን መመሪያ መታዘዝ አለብን? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?

ልጅ ሳለህ ወላጆችህ ያዘዙህን ነገር ማድረግ ከብዶህ ያውቃል? ወላጆችህን የምትወዳቸው ከመሆኑም ሌላ እነሱን መታዘዝ እንዳለብህ ታውቃለህ። ያም ቢሆን ወላጆችህን መታዘዝ ያልፈለግክባቸው ጊዜያት እንደነበሩ የታወቀ ነው።

2 አባታችን ይሖዋ እንደሚወደን እናውቃለን። ይሖዋ ይንከባከበናል፤ እንዲሁም አስደሳች ሕይወት ለመምራት የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ ያሟላልናል። በተጨማሪም ስኬታማ ለመሆን የሚረዳ መመሪያ ይሰጠናል። ይሖዋ ለእኛ መመሪያ ለመስጠት በሌሎች ሰዎች የሚጠቀምበት ጊዜ አለ። የይሖዋን ሥልጣን ማክበር ይኖርብናል። (ምሳሌ 24:21) ሆኖም መመሪያ መቀበል አንዳንድ ጊዜ ከባድ የሚሆንብን ለምንድን ነው? የሚሰጠንን መመሪያ እንድንታዘዝ ይሖዋ የሚጠብቅብን ለምንድን ነው? የይሖዋን ሥልጣን እንደምናከብር ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው?—ተጨማሪ ሐሳብ 9⁠ን ተመልከት።

ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?

3, 4. ሰዎች ፍጹም ያልሆኑት ለምንድን ነው? ሌሎች የሚሰጡንን መመሪያ መቀበል አስቸጋሪ የሚሆንብን ለምን ሊሆን ይችላል?

3 የሰው ልጆች ስንባል አለመታዘዝ ይቀናናል። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ማለትም አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ የኖሩ ሰዎች በሙሉ ያለመታዘዝ ዝንባሌ አላቸው። አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ፍጹማን የነበሩ ቢሆንም በአምላክ ሥልጣን ላይ ዓምፀዋል። በመሆኑም የአዳምና የሔዋን ዘሮች በሙሉ ፍጽምና የጎደላቸው ናቸው። ይሖዋም ሆነ ሰዎች የሚሰጡንን መመሪያ መቀበል አስቸጋሪ እንዲሆንብን የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ፍጹማን አለመሆናችን ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ይሖዋ መመሪያ ለማስተላለፍ የሚጠቀምባቸው ሰዎችም እንደ እኛው ፍጽምና የጎደላቸው መሆናቸው ነው።—ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:1-7፤ መዝሙር 51:5፤ ሮም 5:12

4 ፍጹማን ባለመሆናችን የኩራት ዝንባሌ ይታይብናል። ኩራት ደግሞ መመሪያን መቀበል ከባድ እንዲሆንብን ያደርጋል። በጥንቷ እስራኤል የተፈጸመን አንድ ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋ ሕዝቡን እንዲመራ ሙሴን መርጦት ነበር። ይሁንና ቆሬ የተባለ ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ አንድ ሰው፣ ኩራት በውስጡ እያደገ እንዲሄድ በመፍቀዱ ለሙሴ አክብሮት ማሳየት ከበደው። ሙሴ የአምላክን ሕዝቦች የመምራት መብት ቢኖረውም ኩሩ አልነበረም። እንዲያውም በወቅቱ በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ትሑት እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ቆሬ ግን የሙሴን አመራር ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም። ይባስ ብሎም ብዙ ሰዎች ከእሱ ጋር ተባብረው በሙሴ ላይ እንዲያምፁ አደረገ። ታዲያ ቆሬና አብረውት ያመፁት ሰዎች መጨረሻቸው ምን ሆነ? ሕይወታቸውን አጡ። (ዘኁልቁ 12:3፤ 16:1-3, 31-35) ኩራት አደገኛ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን።—2 ዜና መዋዕል 26:16-21፤ ተጨማሪ ሐሳብ 10⁠ን ተመልከት።

5. አንዳንድ ሰዎች ሥልጣናቸውን አላግባብ የተጠቀሙበት እንዴት ነው?

5 “ሥልጣን ያባልጋል” ሲባል ሰምተህ ታውቅ ይሆናል። ብዙ ሰዎች ሥልጣናቸውን አላግባብ እንደተጠቀሙበት ታሪክ በግልጽ ያሳያል። (መክብብ 8:9⁠ን አንብብ።) የሳኦልን ሁኔታ እንመልከት፤ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ይሖዋ በመረጠው ጊዜ ሳኦል ትሑትና ጥሩ ሰው ነበር። ውሎ አድሮ ግን ሳኦል ኩራትና ቅናት በልቡ ውስጥ እንዲያድግ ፈቀደ፤ ይህም ምንም ያልበደለውን ዳዊትን እንዲያሳድድ አድርጎታል። (1 ሳሙኤል 9:20, 21፤ 10:20-22፤ 18:7-11) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዳዊት ንጉሥ ሆነ፤ ዳዊት በጣም ጥሩ ከሚባሉት የእስራኤል ነገሥታት መካከል አንዱ ነው። ዳዊትም ቢሆን ግን ሥልጣኑን አላግባብ የተጠቀመበት ጊዜ ነበር። የኦርዮ ሚስት ከሆነችው ከቤርሳቤህ ጋር የፆታ ብልግና የፈጸመ ሲሆን ይህን ኃጢአቱን ለመደበቅ ሲል ደግሞ ኦርዮን በጦር ሜዳ አስገድሎታል።—2 ሳሙኤል 11:1-17

የይሖዋን ሥልጣን ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

6, 7. (ሀ) ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምን ለማድረግ ያነሳሳናል? (ለ) ይሖዋን መታዘዝ ቀላል በማይሆንበት ጊዜም ጭምር ታዛዥ ለመሆን የኢየሱስ ምሳሌ የሚረዳን እንዴት ነው?

6 ይሖዋን ስለምንወደው እሱ የሚሰጠንን መመሪያ እንታዘዛለን። ይሖዋን ከምንም ወይም ከማንም በላይ ስለምንወደው እሱን ማስደሰት እንፈልጋለን። (ምሳሌ 27:11⁠ን እና ማርቆስ 12:29, 30⁠ን አንብብ።) ሰይጣን፣ ሰዎች የይሖዋን ሥልጣን እንዳይቀበሉ ለማድረግ ይፈልጋል፤ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በኤደን ገነት ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ሰዎች በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ ለማነሳሳት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ዲያብሎስ፣ ‘ይሖዋ እኛን የማዘዝ ሥልጣን የለውም’ ብለን እንድናስብ ይፈልጋል። ሆኖም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ትክክል እንዳልሆነ እናውቃለን። “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እንስማማለን።—ራእይ 4:11

7 ልጅ ሳለህ፣ ምንጊዜም ወላጆችህን መታዘዝ እንዳለብህ ሳይነገርህ አልቀረም፤ እነሱን መታዘዝ በማትፈልግበት ጊዜም ጭምር ይህን ማድረግ ይጠበቅብህ ነበር። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች የይሖዋን ትእዛዝ ማክበር አንዳንድ ጊዜ ቀላል ላይሆንልን ይችላል። ይሁንና ይሖዋን ስለምንወደውና ስለምናከብረው እሱን ለመታዘዝ ልባዊ ጥረት እናደርጋለን። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ የይሖዋን መመሪያ መታዘዝ አስቸጋሪ ወይም ከባድ በሆነበት ጊዜም ጭምር ይሖዋን ታዟል። ወደ አባቱ ሲጸልይ “የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” ብሏል።—ሉቃስ 22:42፤ ተጨማሪ ሐሳብ 11⁠ን ተመልከት።

8. ይሖዋ እኛን ለመምራት የሚጠቀምባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (“ምክርን ስማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

8 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች መመሪያ ይሰጠናል። ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መመሪያዎችን አስፍሮልናል። በተጨማሪም የጉባኤ ሽማግሌዎችን ሾሞልናል። ይሖዋ ለእኛ መመሪያ ለመስጠት የሚጠቀምባቸውን ሰዎች ስናከብር ለይሖዋ ሥልጣን አክብሮት እንዳለን እናሳያለን። የእነዚህን ሰዎች ሥልጣን አለመቀበል የይሖዋን ሥልጣን ካለማክበር ተለይቶ አይታይም። እስራኤላውያን የሙሴን ሥልጣን ለመቀበል እንቢተኞች በሆኑ ጊዜ ይሖዋ ጉዳዩን አቅልሎ አልተመለከተውም። እስራኤላውያን እሱን እንደናቁት ተሰምቶታል።—ዘኁልቁ 14:26, 27፤ ተጨማሪ ሐሳብ 12⁠ን ተመልከት።

ምክርን ስማ

አንዳንድ ጊዜ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ምክር ይሰጠናል። ሆኖም የሚሰጠንን ምክር መቀበል ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ ሦስት ነገሮችን እስቲ እንመልከት።—ምሳሌ 19:20

  • ምክሩ ለእኛ እንደማይሠራ ሲሰማን። ምክር የሰጠን ሰው እኛ ያለንበት ሁኔታ እንዳልገባው እናስብ ይሆናል። (ዕብራውያን 12:5) ይሁን እንጂ ግለሰቡ ያንን ምክር ለመስጠት ያነሳሳው በቂ ምክንያት ይኖር እንደሆነ ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 19:3) ግለሰቡ ምክሩን የሰጠን ለምን እንደሆነ መረዳታችን ምክሩን መቀበል ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል።—ምሳሌ 4:13⁠ን አንብብ።

  • ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ተገቢ እንዳልሆነ ሲሰማን። ፍጹም በሆነ መንገድ ፍጹም የሆነ ምክር ሊሰጠን የሚችለው ፍጹም የሆነ ሰው ብቻ ነው። (ሮም 3:23፤ ያዕቆብ 3:2) ግለሰቡ ምክሩን በሰጠበት መንገድ ላይ ከማተኮር ይልቅ በተናገረው ነገርና ሐሳቡን በተግባር ማዋል በምንችልበት መንገድ ላይ ትኩረት ማድረጋችን ይጠቅመናል።

  • ከዕድሜያችን ወይም ካካበትነው ተሞክሮ አንጻር ምክር እንደማያስፈልገን ሲሰማን። በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ነገሥታትም ጭምር ምክር ይሰጣቸው ነበር፤ ነቢያት፣ ካህናትና በግዛታቸው ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎች ነገሥታቱን ይመክሯቸው ነበር። (2 ሳሙኤል 12:1-13፤ 2 ዜና መዋዕል 26:16-20) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጠን በትሕትና መቀበላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል።—ቲቶ 3:2

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር፣ ከሚወደንና ለእኛ ከሁሉ የተሻለውን ነገር ከሚመኝልን አምላካችን ያገኘነው ስጦታ እንደሆነ እናስታውስ። ምክሩን ተቀብለን በተግባር ለማዋል ጥረት እናድርግ።—ዕብራውያን 12:6-11

9. ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር መመሪያ እንድንታዘዝ የሚያነሳሳን እንዴት ነው?

9 ለሥልጣን አክብሮት ለማሳየት የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር ነው። ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ ያህል፣ የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ሕይወት ለማዳን በቡድን የሚሠሩ ሰዎችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ ያለው ቡድን ውጤታማ እንዲሆን የቡድኑን አባላት የሚያደራጅ ሰው ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ የቡድኑ አባል ይህ ግለሰብ የሚሰጠውን መመሪያ መከተል ይኖርበታል። ይሁን እንጂ አንድ የቡድኑ አባል የተሰጠውን መመሪያ ችላ ብሎ ራሱ የፈለገውን ነገር ብቻ ቢያደርግስ? ግለሰቡ ያሰበው ነገር መልካም ቢሆንም እንኳ መመሪያ አለመቀበሉ በሌሎቹ የቡድኑ አባላት ላይ ችግር ሊፈጥርና ለከባድ ጉዳት ሊዳርጋቸው ይችላል። በተመሳሳይም ይሖዋም ሆነ እሱ የሾማቸው ሰዎች የሚሰጡንን መመሪያ ካልተከተልን ሌሎችን ለጉዳት ልንዳርግ እንችላለን። ይሖዋን ስንታዘዝ ግን ወንድሞቻችንን እንደምንወድና የይሖዋን ዝግጅት እንደምናከብር እናሳያለን።—1 ቆሮንቶስ 12:14, 25, 26

10, 11. ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?

10 ይሖዋ የሚሰጠንን የትኛውንም መመሪያ መታዘዛችን ጥቅሙ ለራሳችን ነው። በቤተሰብና በጉባኤ ውስጥ ሥልጣን ላላቸው ሰዎች እንዲሁም ለመንግሥት ባለሥልጣናት አክብሮት ስናሳይ ሁሉም ሰው ይጠቀማል።—ዘዳግም 5:16፤ ሮም 13:4፤ ኤፌሶን 6:2, 3፤ ዕብራውያን 13:17

11 ይሖዋ የሌሎችን ሥልጣን እንድናከብር የሚፈልገው ለምን እንደሆነ ማወቃችን ሥልጣናቸውን ለማክበር ያነሳሳናል። በሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በቤተሰብ ውስጥ ሥልጣንን ማክበር

12. ባሎች ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ቤተሰብን የመሠረተው ይሖዋ ሲሆን ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የየራሱን ድርሻ ሰጥቶታል። ሁሉም የቤተሰብ አባላት ይሖዋ ምን እንደሚጠብቅባቸው ከተገነዘቡ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ይኖራቸዋል፤ እንዲሁም መላው ቤተሰብ ይጠቀማል። (1 ቆሮንቶስ 14:33) ባል የቤተሰቡ ራስ እንዲሆን ይሖዋ ሾሞታል። በመሆኑም ባለቤቱንና ልጆቹን እንዲንከባከብና በፍቅር እንዲመራቸው ይሖዋ ይጠብቅበታል። አንድ ባል ቤተሰቡን የሚይዝበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ነው። ክርስቲያን የሆነ ባል፣ ደግና አፍቃሪ ለመሆን እንዲሁም ኢየሱስ ጉባኤውን በያዘበት መንገድ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ይጥራል። ባሎች ይህን ማድረጋቸው ይሖዋን እንደሚያከብሩ ያሳያል።—ኤፌሶን 5:23፤ ተጨማሪ ሐሳብ 13⁠ን ተመልከት።

አንድ አባት፣ ከታላቁ አስተማሪ ተማር ከተባለው መጽሐፍ ላይ ለልጆቹ ሲያነብላቸው

ክርስቲያን አባቶች የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ቤተሰባቸውን ይንከባከባሉ

13. ክርስቲያን ሚስቶች ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

13 ክርስቲያን ሚስቶችም የተከበረና አስፈላጊ የሆነ ድርሻ አላቸው። አንዲት ክርስቲያን ሚስት፣ ባሏ ጥሩ የቤተሰብ ራስ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት ትደግፋለች። ሚስት ከባለቤቷ ጋር ሆና ልጆቿን የማሠልጠን ኃላፊነት ተሰጥቷታል። ልጆቿ አባታቸውን እንዲያከብሩ ማሠልጠን የምትችልበት አንዱ መንገድ እሷ ራሷ ምሳሌ በመሆን ነው። (ምሳሌ 1:8) ባሏን የምታከብር ከመሆኑም ሌላ የሚያደርጋቸውን ውሳኔዎች ትደግፋለች። በአንድ ጉዳይ ላይ ከባሏ ጋር ባትስማማ እንኳ ሐሳቧን የምትገልጸው ደግነትና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ባል ያላት ክርስቲያን ሚስት ለየት ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ እንደሚያጋጥማት የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ለባሏ ምንጊዜም ፍቅርና አክብሮት የምታሳየው ከሆነ ይሖዋን ለማወቅና ለማምለክ ሊነሳሳ ይችላል።—1 ጴጥሮስ 3:1⁠ን አንብብ።

14. ልጆች ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ልጆች በይሖዋ ፊት ውድ ናቸው፤ ደግሞም ለየት ያለ ጥበቃና አመራር ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ልጆች ወላጆቻቸውን ሲታዘዙ ወላጆች ይደሰታሉ። ከዚህም በላይ ታዛዥ መሆናቸው ለይሖዋ አክብሮት እንዳላቸው ያሳያል፤ የይሖዋንም ልብ ያስደስታል። (ምሳሌ 10:1) አንድ ወላጅ ብቻ ያለባቸው ብዙ ቤተሰቦች አሉ። ይህ ሁኔታ፣ ብቻውን ልጆች ለሚያሳድገው ወላጅም ሆነ ለልጆቹ ተፈታታኝ እንደሆነ አያጠራጥርም። ሆኖም ልጆቹ ወላጃቸውን የሚታዘዙና የሚያግዙ ከሆነ ጥሩ የቤተሰብ ሕይወት ይኖራቸዋል። የትኛውም ቤተሰብ ቢሆን ፍጹም አይደለም። ይሁን እንጂ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ የይሖዋን መመሪያ የሚከተሉ ከሆነ ማንኛውም ቤተሰብ ደስተኛ መሆን ይችላል። ይህም የቤተሰብ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ ክብር ያመጣል።—ኤፌሶን 3:14, 15

በጉባኤ ውስጥ ሥልጣንን ማክበር

15. በጉባኤ ውስጥ ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 ይሖዋ መመሪያ የሚሰጠን በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ነው፤ የጉባኤው ራስ እንዲሆንም ኢየሱስን ሾሞታል። (ቆላስይስ 1:18) ኢየሱስ ደግሞ በምድር ላይ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችን የመንከባከቡን ኃላፊነት ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 24:45-47) በዛሬው ጊዜ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆኖ የሚያገለግለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ነው። የበላይ አካሉ እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን የሚያስፈልገንን እርዳታ በተገቢው ጊዜ ያቀርብልናል። ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ከበላይ አካሉ መመሪያ የሚቀበሉ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ላሉ ጉባኤዎች ድጋፍ ይሰጣሉ። እነዚህ ወንድሞች በሙሉ እኛን የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው። ይህን ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ናቸው። እነዚህን ወንድሞች ስናከብር ይሖዋን እንደምናከብር እናሳያለን።—1 ተሰሎንቄ 5:12⁠ን እና ዕብራውያን 13:17⁠ን አንብብ፤ ተጨማሪ ሐሳብ 14⁠ን ተመልከት።

16. ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች የሚሾሙት በመንፈስ ቅዱስ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

16 ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች፣ የጉባኤው አባላት ይሖዋን በታማኝነትና በአንድነት እንዲያገለግሉ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። እርግጥ እነሱም እንደ እኛው ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። ታዲያ እነዚህ ወንድሞች የሚሾሙት እንዴት ነው? ወንድሞች፣ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ለመሾም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን መሥፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7, 12፤ ቲቶ 1:5-9) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እነዚህን ብቃቶች በአምላክ ቃል ውስጥ ያሰፈሩት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ነው። በተጨማሪም የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው ለማገልገል ብቃቱን የሚያሟሉት ወንድሞች እነማን እንደሆኑ ሽማግሌዎች ውይይት ሲያደርጉ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጣቸው ይጸልያሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጉባኤዎችን የሚመሩት ኢየሱስና ይሖዋ ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) ጉባኤውን እንዲረዱና እንዲንከባከቡ የሚሾሙት ወንድሞች የአምላክ ስጦታ ናቸው።—ኤፌሶን 4:8

17. አንዲት እህት ለሥልጣን አክብሮት ለማሳየት አንዳንድ ጊዜ ምን ማድረግ ሊኖርባት ይችላል?

17 አንዳንድ ጊዜ፣ በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች አይኖሩ ይሆናል። በዚህ ወቅት፣ ሽማግሌዎች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ሥራዎችን ሌሎች የተጠመቁ ወንድሞች ሊሠሩ ይችላሉ። በጉባኤ ውስጥ የተጠመቀ ወንድም ከሌለ ግን አንዲት እህት እነዚህን ሥራዎች ታከናውናለች። አንዲት እህት፣ የተጠመቁ ወንድሞች ሊያከናውኑት የሚገባውን ሥራ በምትሠራበት ጊዜ ራሷን መሸፈን ይኖርባታል፤ ለምሳሌ ሻርፕ ወይም ኮፍያ ልታደርግ ትችላለች። (1 ቆሮንቶስ 11:3-10) ይህን ማድረጓ ይሖዋ ለቤተሰብም ሆነ ለጉባኤ ያዘጋጀውን የራስነት ሥርዓት እንደምታከብር ያሳያል።—ተጨማሪ ሐሳብ 15⁠ን ተመልከት።

የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማክበር

18, 19. (ሀ) በሮም 13:1-7 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ለመንግሥታትና ሥልጣን ላላቸው ሌሎች ሰዎች አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉት መንግሥታት አንጻራዊ ሥልጣን እንዲኖራቸው ፈቅዷል፤ በመሆኑም ልናከብራቸው ይገባል። መንግሥታት፣ በምንኖርበት አገር ወይም ማኅበረሰብ ውስጥ ሥርዓት እንዲሰፍን የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። ክርስቲያኖች በሮም 13:1-7 ላይ የሚገኘውን መመሪያ ተግባራዊ ያደርጋሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) “ለበላይ ባለሥልጣናት” እንገዛለን፤ እንዲሁም በምንኖርበት አገር ወይም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉትን ሕጎች እናከብራለን። እነዚህ ሕጎች ቤተሰባችንን፣ ሥራችንን ወይም ንብረታችንን የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ የተጣለብንን ግብር እንከፍላለን እንዲሁም መንግሥት እንድንሞላ የሚጠይቀንን ማንኛውንም ቅጽ ወይም ሰነድ በተገቢው ሁኔታ እንሞላለን። ሆኖም መንግሥት ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጭ ነገር እንድናደርግ ቢጠይቀንስ? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዳለው “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።”—የሐዋርያት ሥራ 5:28, 29

19 ከፖሊሶች፣ ከዳኞች ወይም ከሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የሚያገናኝ ጉዳይ ሲያጋጥመን ምንጊዜም አክብሮት ማሳየት ያስፈልገናል። ተማሪ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ አስተማሪዎቻቸውንም ሆነ ሌሎች የትምህርት ቤቱን ሠራተኞች ማክበር አለባቸው። በሥራ ቦታም ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያስፈልጋል፤ አብረውን የሚሠሩት ሰዎች የበላዮቻቸውን ባያከብሩም እንኳ እኛ ለአሠሪያችን አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። በዚህ መንገድ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንከተላለን፤ ጳውሎስ አስቸጋሪ ለሆኑ ባለሥልጣናትም ጭምር አክብሮት አሳይቷል። (የሐዋርያት ሥራ 26:2, 25) ሌሎች ሰዎች በተገቢው መንገድ ባይዙንም እንኳ እኛ እናከብራቸዋለን።—ሮም 12:17, 18⁠ን አንብብ፤ 1 ጴጥሮስ 3:15

20, 21. ሌሎችን ማክበራችን ምን ጥሩ ውጤት ያስገኛል?

20 ለሌሎች አክብሮት አለማሳየት በመላው ዓለም እየተለመደ መጥቷል። የይሖዋ ሕዝቦች ግን በዚህ ረገድ የተለየን ነን። ሁሉንም ሰው ለማክበር ጥረት እናደርጋለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ” በማለት የሰጠውን ምክር እንከተላለን። (1 ጴጥሮስ 2:17) ለሌሎች አክብሮት የምናሳይ ከሆነ ሰዎች ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም። ኢየሱስ፣ “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሎናል።—ማቴዎስ 5:16

21 በቤተሰብና በጉባኤ ውስጥ እንዲሁም በሌሎች የሕይወታችን ዘርፎች ለሥልጣን አክብሮት የምናሳይ ከሆነ ሰዎች መልካም ምግባራችንን በመመልከት ስለ ይሖዋ ለመማር ሊነሳሱ ይችላሉ። ሌሎችን ስናከብር ይሖዋንም እያከበርን ነው። አክብሮት ማሳየታችን ይሖዋን ያስደስተዋል፤ ለእሱ ፍቅር እንዳለንም ያረጋግጣል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች

1 ይሖዋ እኛን ለመምራት በሌሎች ሰዎች ይጠቀማል

“ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤ . . . አምላክን ፍሩ።”—1 ጴጥሮስ 2:17

መመሪያ መከተል ከባድ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

  • ዘኁልቁ 16:1-3፤ መክብብ 8:9፤ ሮም 5:12

    ፍጽምና የሚጎድለን በመሆናችን ነው፤ ይሖዋ መመሪያ ለማስተላለፍ የሚጠቀምባቸው ሰዎችም ቢሆኑ ፍጹማን አይደሉም።

  • ሉቃስ 22:42

    በታዛዥነት ረገድ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል። ይሖዋን ሁልጊዜ ይታዘዝ ነበር።

  • ምሳሌ 27:11፤ ማርቆስ 12:29, 30

    ለይሖዋ ያለን ፍቅር እሱ ያደረገውን ዝግጅት ለማክበር ያነሳሳናል። በቤተሰብ ውስጥ የቤተሰቡን ራስ፣ በትምህርት ቤት አስተማሪዎችን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎችን ልናከብር ይገባል።

2 ቤተሰብን ያቋቋመው ይሖዋ ነው

“በአብ ፊት ለመጸለይ እንበረከካለሁ፤ . . . እያንዳንዱ ቤተሰብ ስያሜውን ያገኘው ከእሱ ነው።”—ኤፌሶን 3:14, 15

ይሖዋ በቤተሰብ ውስጥ ለሥልጣን አክብሮት እንድናሳይ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

  • ምሳሌ 10:1

    ይሖዋ ቤተሰብን ያቋቋመው ልጆች ያለስጋት ማደግ እንዲችሉ እንዲሁም ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በፍቅር እንዲኖሩ ለማድረግ ነው።

  • ምሳሌ 1:8፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 6:1-3፤ 1 ጴጥሮስ 3:1

    ሁሉም የቤተሰብ አባል የራሱን ድርሻ የሚወጣ ከሆነ ቤተሰቡ ይጠቀማል።

3 ይሖዋ ኢየሱስን የጉባኤው ራስ አድርጎ ሾሞታል

‘ክርስቶስ የጉባኤው ራስ ነው።’—ኤፌሶን 5:23

በጉባኤ ውስጥ ላለው ሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

  • ማቴዎስ 24:45-47

    ኢየሱስ በምድር ላይ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች እንዲንከባከብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾሟል።

  • 1 ተሰሎንቄ 5:12፤ ዕብራውያን 13:17

    የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ጉባኤው በመንፈሳዊ ጠንካራ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ከእነዚህ ወንድሞች ጋር ስንተባበር የይሖዋን ሥልጣን እንደምናከብር እናሳያለን።

  • የሐዋርያት ሥራ 20:28

    የጉባኤውን ዝግጅት በሙሉ ልባችን ስንደግፍ ሁሉም ሰው ይጠቀማል። ጉባኤው ይሖዋን ለማምለክ የሚያስችለን እሱ ያደረገልን ዝግጅት ነው።

4 ይሖዋ መንግሥታት አንጻራዊ ሥልጣን እንዲኖራቸው ፈቅዷል

“ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።”—ሮም 13:1

ለመንግሥት ባለሥልጣናት አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

  • ማቴዎስ 5:16፤ 1 ጴጥሮስ 3:15

    በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን አክብሮት ማሳየት አለብን። ይህም ይሖዋን ያስከብረዋል።

  • የሐዋርያት ሥራ 26:2, 25፤ ሮም 12:17, 18

    ክርስቲያኖች የሚኖሩበትን አገር ሕጎች ያከብራሉ። አንዳንድ ባለሥልጣናት በተገቢው መንገድ ባይዟቸውም እንኳ ክርስቲያኖች አክብሮት ያሳያሉ።

  • ሮም 13:1-4

    የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለባለሥልጣናት አክብሮት እንድናሳይ ይረዱናል።

  • ማቴዎስ 22:37-39፤ 26:52፤ ዮሐንስ 18:36፤ የሐዋርያት ሥራ 5:27-29፤ ዕብራውያን 10:24, 25

    መንግሥታት ከይሖዋ ሕጎች ጋር የሚጋጭ ነገር እንድታደርግ ከጠየቁህ ማንን እንደምትታዘዝ መምረጥ ይኖርብሃል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ