‘የእስራኤልን ቤት የሠሩት’ እህትማማቾች ጭንቀት
ልያ ጎሕ ሲቀድ እውነቱ እንደሚጋለጥ ታውቅ ነበር። ያዕቆብ በእቅፉ ያለችው ሴት ልያ እንጂ ታናሽ እህቷ ራሔል አለመሆኗን ሊያውቅ ነው። ልያ በሠርጉ ምሽት የአባቷን ፈቃድ ለመፈጸም ስትል፣ እንዳትታወቅ ፊቷን ሸፍና ለያዕቆብና ለራሔል በተዘጋጀው አልጋ ላይ ተኝታ ነበር።
ጎሕ ሲቀድና እውነታው ገሐድ ሲወጣ ያዕቆብ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! ያዕቆብ በሁኔታው በጣም ስለተናደደ የልያን አባት ላባን በቁጣ አናገረው። በዚህ መሃል ልያ፣ ያዕቆብን በማታለል ረገድ ስለነበራት ድርሻ እንዲሁም ይህ ድርጊት ለዘለቄታው ስለሚያስከትለው ውጤት ሳታስብ አትቀርም። የልያና የራሔል ታሪክ አስፈላጊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። ከዚህም ባሻገር ከአንድ በላይ ማግባት የሚያስከትለውን ችግር እንዲሁም በጋብቻ ውስጥ ታማኝ መሆን የጥበብ አካሄድ እንደሆነ ያስገነዝበናል።
በውኃ ጉድጓድ አጠገብ የተገኘ እንግዳ
ይህ ከመሆኑ ከሰባት ዓመታት በፊት ራሔል ወደ አባቷ ሮጣ በመሄድ በውኃው ጉድጓድ አጠገብ ከአንድ ሰው ጋር እንደተገናኘችና እሱም ዘመዳቸው መሆኑን እንደገለጸላት ነግራው ነበር። በኋላም ይህ ሰው የአባቷ እህት ልጅ እንደሆነና ያዕቆብ እንደሚባል እንዲሁም ይሖዋን እንደሚያመልክ ታወቀ። ይህ ከሆነ ከወር በኋላ ያዕቆብ፣ ራሔልን ለማግባት ሲል ላባን ሰባት ዓመት ሊያገለግለው ፈቃደኛ መሆኑን ገለጸለት። ላባም የእህቱ ልጅ ትጉህ ሠራተኛ መሆኑን በመመልከቱ በባሕላቸው መሠረት ዘመዳሞች መጋባታቸው የተለመደ ነገር ስለነበር በያዕቆብ ሐሳብ ተስማማ።—ዘፍጥረት 29:1-19
ያዕቆብ ለራሔል የነበረው ፍቅር የወረት አልነበረም። ‘አጥብቆ ይወዳት ስለ ነበረ’ ከተጫጩ በኋላ ያሳለፉት ሰባት ዓመት “እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ” ታይቶታል። (ዘፍጥረት 29:20) ያዕቆብ፣ ራሔልን እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ መውደዱ በርካታ መልካም ባሕርያት እንደነበሯት ያሳያል።
ልያስ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ እንደምታገባ ተስፋ አድርጋ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የሚናገረው ነገር ባይኖርም ላባ ስለ ልያ ጋብቻ የነበረው አመለካከት ግን በግልጽ ሰፍሯል። ራሔልና ያዕቆብ እጮኛሞች ሆነው የቆዩባቸው ሰባት ዓመታት ሲያበቁ ላባ ሠርግ ደገሰ። ሲመሽ ግን ልያን ለያዕቆብ እንደሰጠውና ‘አብሮአት እንደተኛ’ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይነግረናል።—ዘፍጥረት 29:23
ልያ ያዕቆብን ለማታለል አስባ ነበር? ወይስ ይህን ያደረገችው አባቷን መታዘዝ ግድ ሆኖባት ነው? በዚህ ጊዜ ራሔል የት ነበረች? ምን እየተደረገ እንዳለ ታውቅ ነበር? ከሆነስ ምን ተሰምቷት ይሆን? ግትር የሆነው አባቷ የሰጣትን ትእዛዝ መጣስ ትችል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ የለም። ራሔልና ልያ ስለ ጉዳዩ የነበራቸው ስሜት ምንም ይሁን ምን ይህ የተንኮል ድርጊት ያዕቆብን በጣም አናዶታል። ያዕቆብ በጉዳዩ አለመስማማቱን የገለጸው ለላባ እንጂ ለልጆቹ አልነበረም፤ “ያገለገልኹህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው። ላባ ምን ምላሽ ሰጠ? “ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤ ይህን የጫጕላ ሳምንት ፈጽምና፣ ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን” አለው። (ዘፍጥረት 29:25-27) ላባ፣ በዚህ መንገድ ያዕቆብን በማታለል ሁለት ሴቶች እንዲያገባ ያደረገው ሲሆን ይህም ከፍተኛ ቅናት አስከትሏል።
ደስታ የራቀው ቤተሰብ
ያዕቆብ ራሔልን ይወዳት ነበር። አምላክ፣ ልያ “እንዳልተወደደች” ሲያይ ማሕፀኗን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። ይሁን እንጂ ልያ ልጅ ብቻ ሳይሆን የያዕቆብን ፍቅርም ማግኘት ትፈልግ ነበር። ያዕቆብ የሚወደው ራሔልን ብቻ መሆኑ ደስታ እንድታጣ አደረጋት። ያም ሆኖ ልያ፣ የበኩር ልጁን ሮቤልን ስለወለደችለት ያዕቆብ እንደሚወዳት ተስፋ አድርጋ ነበር፤ ሮቤል የሚለው ስም “እነሆ፣ ወንድ ልጅ!” የሚል ትርጉም አለው። ልያ ለልጇ እንዲህ ዓይነት ስም ያወጣችው “እግዚአብሔር መከራዬን ስለ ተመለከተልኝ፣ ከእንግዲህ ባሌ ይወደኛል” ብላ ነበር። ያዕቆብ ግን በዚህ ጊዜም ሆነ ሌላ ልጅ ስትወልድለት ልያን አልወደዳትም። ልያ ሁለተኛውን ልጇን ስምዖን ያለችው ሲሆን ትርጉሙም “የሚሰማ” ማለት ነው። እንዲህ ያለችበትን ምክንያት ስትገልጽ “እግዚአብሔር እንዳልተወደድኩ ሰምቶ ይህን ልጅ በድጋሚ ሰጠኝ” ብላለች።—ዘፍጥረት 29:30-33
ልያ፣ አምላክ እንደሰማት መግለጿ ስለ ሁኔታዋ ጸልያ እንደነበር ያሳያል። ልያ ታማኝ ሴት የነበረች ይመስላል። ያም ሆኖ ሌዊ የተባለውን ሦስተኛ ልጇን ከወለደች በኋላም እንኳ ሥቃይዋ አልተወገደም። የሌዊ ስም “መጣበቅ” ወይም “መቅረብ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ልያም “ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት ከእንግዲህ ባሌ ያቀርበኛል” ብላ ነበር። ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ግን ያዕቆብ ወደ እሷ አልቀረበም። ልያም አራተኛውን ልጇን ስትወልድ ከያዕቆብ ጋር ያላት ግንኙነት እንደሚሻሻል ያላትን ተስፋ የሚገልጽ ምንም ነገር አለመናገሯ ሁኔታውን እንደተቀበለችው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተለየ መልኩ የይሁዳን ስም ስታወጣ አምላክን እንደምታመሰግን ገልጻለች። “ይሁዳ” የሚለው ስም “የተመሰገነ” ወይም “ምስጉን” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ልያም “እንግዲህ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ብላለች።—ዘፍጥረት 29:34, 35
ልያ በሕይወቷ ትማረር እንደነበር ግልጽ ነው፤ የራሔልም ሁኔታ ቢሆን ከዚህ የተሻለ አልነበረም። ያዕቆብን “ልጅ ስጠኝ፤ አለበለዚያ እሞታለሁ” በማለት ተማጽናዋለች። (ዘፍጥረት 30:1) ራሔል፣ ያዕቆብ እንደሚወዳት ብታውቅም ልጆች መውለድ በጣም ትፈልግ ነበር። ልያ ደግሞ ልጆች ቢኖሯትም ያዕቆብ እንዲወዳት ትመኝ ነበር። ሁለቱም የሌላቸውን ነገር ለማግኘት ይፈልጉ ስለነበር አንዳቸውም ደስተኛ አልነበሩም። ሁለቱም ያዕቆብን ይወዱትና ከእሱ ልጆች ለመውለድ ይመኙ ነበር። እህትማማቾቹ እርስ በርስ ይቀናኑ ነበር። ቤተሰቡ የነበረበት ሁኔታ እንዴት አሳዛኝ ነው!
ራሔል ልጆች አገኘች?
በዚያን ዘመን ልጅ መውለድ አለመቻል እንደ እርግማን ይታይ ነበር። አምላክ ለአብርሃምና ለይስሐቅ እንዲሁም ለያዕቆብ፣ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በእነሱ ‘ዘር’ አማካኝነት እንደሚባረኩ ቃል ገብቶላቸዋል። (ዘፍጥረት 26:4፤ 28:14) ራሔል ግን ልጅ አልነበራትም። ያዕቆብ፣ ለራሔል ልጅ በመስጠት በዚህ በረከት ውስጥ ድርሻ እንዲኖራት ሊያደርጋት የሚችለው አምላክ ብቻ መሆኑን ቢነግራትም ራሔል ግን ትዕግሥት በማጣቷ “እነሆ፤ አገልጋዬ ባላ አለችልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም ደግሞ በእርሷ አማካይነት ልጆች እንዳገኝ ከእርሷ ጋር ተኛ” አለችው።—ዘፍጥረት 30:2, 3
በዛሬው ጊዜ የራሔልን አመለካከት መረዳት ይከብደን ይሆናል። ሆኖም በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢዎች በሙሉ የተገኙ የጥንት የጋብቻ ውሎች እንደሚያሳዩት መካን የሆነች ሴት ወራሽ ለማግኘት አገልጋይዋን ለባሏ መስጠቷ ተቀባይነት ያለው ልማድ ነበር።a (ዘፍጥረት 16:1-3) አንዳንድ ጊዜ የአገልጋይዋ ልጆች ከሚስትየዋ እንደተወለዱ ልጆች ተደርገው ይታዩ ነበር።
ባላ ወንድ ልጅ ስትወልድ ራሔል “እግዚአብሔር ፈርዶልኛል፣ ልመናዬንም ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጥቶኛል” በማለት በደስታ ተናገረች። ስሙን ዳን ብላ የጠራችው ሲሆን ትርጉሙም “ፈራጅ” ማለት ነው። እሷም ስለ ገጠማት ችግር ጸልያ ነበር። ባላ ሁለተኛ ልጅ ስትወልድ ራሔል “እኅቴን ብርቱ ትግል ገጥሜ አሸነፍሁ” በማለት ንፍታሌም የሚል ስም አወጣችለት፤ ይህ ስም “ያደረግሁት ትግል” የሚል ትርጉም አለው። እህትማማቾቹ ለልጆቹ ያወጧቸው ስሞች በመካከላቸው ከፍተኛ ፉክክር እንደነበረ ያሳያሉ።—ዘፍጥረት 30:5-8
ራሔል፣ ባላን ለያዕቆብ ስትሰጠው ከጸሎቷ ጋር የሚስማማ እርምጃ እንደወሰደች ተሰምቷት ይሆናል፤ ሆኖም አምላክ፣ ልጆች የሚሰጣት በዚህ መንገድ አልነበረም። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት አለ። ይሖዋ አንድ ነገር እንዲያደርግልን ስንለምነው ትዕግሥት ማጣት የለብንም። እኛ ባላሰብነው ወቅትና ባልጠበቅነው መንገድ ለጸሎታችን መልስ ሊሰጠን ይችላል።
ልያም ላለመበለጥ ስትል አገልጋይዋን ዘለፋን ለያዕቆብ ሰጠችው። ዘለፋም በመጀመሪያ ጋድን ቀጥላም አሴርን ወለደች።—ዘፍጥረት 30:9-13
የልያ ልጅ ሮቤል እንኮይ ባገኘ ጊዜ፣ በራሔልና በልያ መካከል የነበረው የፉክክር መንፈስ በግልጽ ታይቷል። ይህ ፍሬ ለመጸነስ እንደሚረዳ ይታመን ነበር። ራሔል እንኮይ እንድትሰጣት ልያን ስትጠይቃት ልያ በምሬት “ባሌን የቀማሽኝ አነሰና የልጄን እንኮይ ደግሞ ልትወስጂ አማረሽ?” አለቻት። አንዳንዶች ይህ የልያ አነጋገር ያዕቆብ ከልያ ይልቅ ከራሔል ጋር ብዙ ጊዜ ያሳልፍ እንደነበር የሚጠቁም እንደሆነ ይሰማቸዋል። ራሔል፣ የልያ ቅሬታ ትክክል እንደሆነ ሳትገነዘብ አልቀረችም፤ በመሆኑም “ስለ ልጅሽ እንኮይ ዛሬ ከአንቺ ጋር ይደር” ብላ መለሰችላት። በዚህም ምክንያት ያዕቆብ ምሽት ላይ ቤቱ ሲገባ ልያ “በልጄ እንኮይ ስለ ተከራየሁህ የዛሬው አዳርህ ከእኔ ጋር ነው” አለችው።—ዘፍጥረት 30:15, 16
ልያ፣ ይሳኮር የተባለውን አምስተኛ ልጇንና ዛብሎን የተባለውን ስድስተኛ ልጇን ከወለደች በኋላ “ስድስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት፣ ከእንግዲህ ባሌ አክብሮ ይይዘኛል” በማለት ተናገረች።b—ዘፍጥረት 30:17-20
ራሔል የወሰደችው እንኮይ እንድትጸንስ አልረዳትም። ካገባች ከስድስት ዓመታት በኋላ አርግዛ ዮሴፍ የተባለ ልጅ ልትወልድ የቻለችው ይሖዋ ‘ስላሰባትና’ ለጸሎቷ መልስ ስለሰጣት ነበር። ራሔል “እግዚአብሔር ዕፍረቴን አስወገደልኝ” ማለት የምትችለው በዚህ ጊዜ ነበር።—ዘፍጥረት 30:22-24
ሞትና ውርስ
ራሔል፣ ብንያም የተባለውን ሁለተኛ ልጇን ስትወልድ ሕይወቷ አለፈ። ያዕቆብ ራሔልን በጣም ይወዳት ነበር፤ ለሁለቱ ልጆቿም ልዩ ፍቅር ነበረው። ከዓመታት በኋላ ያዕቆብ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ውድ ባለቤቱ ራሔል አለዕድሜዋ መሞቷን አስታውሶ ነበር። (ዘፍጥረት 30:1፤ 35:16-19፤ 48:7) የልያን ሞት በተመለከተ ያዕቆብ በዋሻ ውስጥ እንደቀበራት ከመገለጹ በቀር ምንም የምናውቀው ነገር የለም፤ እሱንም በዚያው ዋሻ ውስጥ እንዲቀብሩት ጠይቋል።—ዘፍጥረት 49:29-32
ያዕቆብ ባረጀ ጊዜ፣ የቤተሰብ ሕይወቱን ጨምሮ ሕይወቱ በአጠቃላይ ችግር የበዛበት እንደነበረ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 47:9) ልያና ራሔልም ሕይወታቸው ችግር የሞላበት እንደነበረ ጥርጥር የለውም። የእነርሱ ታሪክ ከአንድ በላይ ማግባት የሚያስከትለውን አሳዛኝ ውጤት እንዲሁም ይሖዋ፣ አንድ ወንድ አንዲት ሚስት ብቻ እንዲያገባ ያዘዘበትን ምክንያት ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ማቴዎስ 19:4-8፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2, 12) አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት ከትዳር ጓደኛቸው ውጭ ሌላ ሰው መውደዳቸው ወይም ከሌላ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸማቸው በባልና ሚስቱ መካከል ቅናት እንዲፈጠር ያደርጋል። አምላክ ዝሙትንና ምንዝርን የሚከለክልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።—1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ዕብራውያን 13:4
ሁኔታው ምንም ይሁን ምን አምላክ ዓላማውን ለመፈጸም፣ ፍጹማን ባይሆኑም ታማኝ በሆኑ ወንዶችና ሴቶች ሲጠቀም የቆየ ሲሆን ወደፊትም እንዲህ ማድረጉን ይቀጥላል። እህትማማቾቹ ልክ እንደ እኛ ድክመቶች ነበሯቸው። ሆኖም ይሖዋ ለአብርሃም የገባውን ቃል መፈጸም የጀመረው በእነዚህ ሴቶች አማካኝነት ነው። በእርግጥም ራሔልና ልያ ‘የእስራኤልን ቤት እንደሠሩ’ መገለጹ ተገቢ ነው።—ሩት 4:11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እንደነዚህ ካሉት የጋብቻ ውሎች መካከል በኖዚ፣ ኢራቅ የተገኘው ውል እንዲህ ይላል:- “ቀሊምኒኖ ለሸኒማ ተድራለች። . . . ቀሊምኒኖ [ልጆች] ካልወለደች፣ ለሸኒማ ሚስት የምትሆነው ሌላ ሴት [አገልጋይ] ከሉሉ ምድር ታመጣለታለች።”
b ሌላዋ የልያ ልጅ ዲና ስትሆን ከያዕቆብ ሴቶች ልጆች መካከል ስሟ የተጠቀሰው እሷ ብቻ ናት።—ዘፍጥረት 30:21፤ 46:7
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልያና ራሔል የሌላቸውን ነገር ለማግኘት ይፈልጉ ስለነበር አንዳቸውም ደስተኛ አልነበሩም
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእስራኤል ብሔር የተገኘው ከአሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ነው