የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bhs ምዕ. 3 ገጽ 29-39
  • አምላክ ለሰዎች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ ለሰዎች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • በየመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንብብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክ ጠላት
  • ይህን ዓለም የሚገዛው ማን ነው?
  • የሰይጣን ዓለም የሚጠፋው እንዴት ነው?
  • አዲስ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ቀርቧል!
  • መከራና ሥቃይ የበዛው ለምንድን ነው?
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • ከእኛ በላይ የሆኑ አሉ
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
    አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
  • በገነት ውስጥ የነበረው ሕይወት ምን ይመስል ነበር?
    አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ
ለተጨማሪ መረጃ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
bhs ምዕ. 3 ገጽ 29-39

ምዕራፍ ሦስት

አምላክ ለሰዎች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

1. አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

አምላክ ለሰው ልጆች አስደሳች ዓላማ አለው። የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን የፈጠረው ውብ በሆነ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንዲኖሩ ነበር። የአምላክ ዓላማ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ፣ መላዋን ምድር ገነት እንዲያደርጉና እንስሳትን እንዲንከባከቡ ነበር።—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 9, 15፤ ተጨማሪ ሐሳብ 6⁠ን ተመልከት።

2. (ሀ) አምላክ ዓላማውን እንደሚፈጽም እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) አምላክ በምድር ላይ እንዲኖሩ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? የሚኖሩትስ ለምን ያህል ጊዜ ነው?

2 በገነት ውስጥ የምንኖርበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል? ይሖዋ “ይህን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አደርገዋለሁም” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:9-11፤ 55:11) አዎ፣ አምላክ ዓላማውን ይፈጽማል፤ ደግሞም እንዲህ እንዳያደርግ ሊከለክለው የሚችል ምንም ነገር የለም። ይሖዋ ምድርን የፈጠረው በዓላማ እንደሆነ ተናግሯል። ‘ምድርን የፈጠረው ለከንቱ’ አይደለም። (ኢሳይያስ 45:18) አምላክ የሰው ልጆች በመላዋ ምድር ላይ እንዲኖሩ ይፈልጋል። በምድር ላይ እንዲኖሩ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? የሚኖሩትስ ለምን ያህል ጊዜ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን [ታዛዥ የሆኑ ሰዎች] ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4

3. የሰው ልጆች መታመማቸውና መሞታቸው ምን ጥያቄ ያስነሳል?

3 ሆኖም በዛሬው ጊዜ ሰዎች ይታመማሉ እንዲሁም ይሞታሉ። በብዙ ቦታዎች ሰዎች እርስ በርስ ይዋጋሉ እንዲሁም ይገዳደላሉ። የአምላክ ዓላማ ይህ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? መልሱን ሊሰጠን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።

የአምላክ ጠላት

4, 5. (ሀ) በኤደን የአትክልት ስፍራ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያናገራት ማን ነው? (ለ) ሐቀኛ የነበረ ሰው ሌባ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

4 አምላክ፣ “ዲያብሎስና ሰይጣን” ተብሎ የሚጠራ ጠላት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሰይጣን፣ በኤደን የአትክልት ስፍራ ሔዋንን ለማነጋገር በእባብ ተጠቅሞ ነበር። (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:1) ሰይጣን፣ እባቡ እያወራ ያለ እንዲመስል አድርጎ ነበር።—ተጨማሪ ሐሳብ 7⁠ን ተመልከት።

5 ይህን መንፈሳዊ ፍጡር ሰይጣን ዲያብሎስ አድርጎ የፈጠረው አምላክ ነው? በፍጹም! አምላክ ምድርን ለአዳምና ለሔዋን ምቹ መኖሪያ አድርጎ ሲያዘጋጃት አንድ መልአክ በሰማይ ሆኖ ይመለከት ነበር፤ ይህ መልአክ ከጊዜ በኋላ ተለውጦ ዲያብሎስ ሆነ። (ኢዮብ 38:4, 7) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በአንድ ወቅት ሐቀኛ የነበረ ሰው ከጊዜ በኋላ ተለውጦ ሌባ ሊሆን ይችላል። ይህ ሰው ሲወለድ ጀምሮ ሌባ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ የእሱ ያልሆነን ነገር ለማግኘት ይመኛል። ስለዚያ ነገር ማሰቡን ሲቀጥል ያን ነገር ለማግኘት ያለው ምኞት እየጨመረ ይሄዳል። ከዚያም ሁኔታዎች ሲመቻቹለት የተመኘውን ነገር ይሰርቃል። በዚህ መንገድ ሐቀኛ የነበረው ሰው ተለውጦ ሌባ ይሆናል።—ያዕቆብ 1:13-15⁠ን አንብብ፤ ተጨማሪ ሐሳብ 8⁠ን ተመልከት።

6. አንድ መልአክ የአምላክ ጠላት የሆነው እንዴት ነው?

6 በተመሳሳይም ይህ መልአክ ከጊዜ በኋላ ተለውጦ ዲያብሎስ ሆነ። ይሖዋ፣ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ልጆች እንዲወልዱና ‘ምድርን እንዲሞሏት’ ነግሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28) ይህ መልአክ፣ ‘ሰዎች በይሖዋ ፋንታ እኔን እንዲያመልኩ ማድረግ እኮ እችላለሁ!’ ብሎ አስቦ ይሆናል። ስለዚህ ነገር ባሰበ ቁጥር፣ ይህ ምኞቱ እየጨመረ ሄደ። መልአኩ ለይሖዋ የሚገባውን አምልኮ ለራሱ መውሰድ ፈለገ። ሰዎች እሱን እንዲያመልኩት ስለፈለገ ሔዋንን ውሸት በመናገር አታለላት። (ዘፍጥረት 3:1-5⁠ን አንብብ።) ይህ መልአክ እንዲህ በማድረግ ሰይጣን ዲያብሎስ ሆነ፤ በሌላ አነጋገር የአምላክ ጠላት ሆነ።

7. (ሀ) አዳምና ሔዋን የሞቱት ለምንድን ነው? (ለ) የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?

7 አዳምና ሔዋን አምላክን አልታዘዙም፤ አትብሉ የተባሉትን ፍሬ በሉ። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:6) በይሖዋ ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው ልክ ይሖዋ እንደተናገረው ከጊዜ በኋላ ሞቱ። (ዘፍጥረት 3:17-19) የአዳምና የሔዋን ልጆችም ኃጢአተኞች በመሆናቸው ሞተዋል። (ሮም 5:12⁠ን አንብብ።) የአዳምና የሔዋን ልጆች ኃጢአተኛ የሆኑበትን ምክንያት ለመረዳት እንድንችል እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንዲት ሴት ስንጥቅ ባለው ምጣድ ላይ እንጀራ እየጋገረች ነው እንበል። እንጀራው በምጣዱ ላይ ያለውን ስንጥቅ ይዞ መውጣቱ አይቀርም። አዳም አምላክን ባለመታዘዙ ኃጢአተኛ ሆኗል። ሁላችንም የአዳም ልጆች ነን፤ በመሆኑም እንጀራው የምጣዱን ስንጥቅ ይዞ እንደሚወጣ ሁሉ እኛም እንደ አዳም ኃጢአተኞች ሆነናል። ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን እናረጃለን ደግሞም እንሞታለን።—ሮም 3:23፤ ተጨማሪ ሐሳብ 9⁠ን ተመልከት።

8, 9. (ሀ) ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ምን ብለው እንዲያስቡ ለማሳመን ጥረት አድርጓል? (ለ) ይሖዋ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?

8 ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ይሖዋን መታዘዝ እንደሌለባቸው ሲነግራቸው በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ እያደረጋቸው ነበር። አዳምና ሔዋን፣ ይሖዋን ውሸታምና ለእነሱ የማያስብ ክፉ ገዢ እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት ለማሳመን ጥረት አድርጓል። በተዘዋዋሪ ሰይጣን ‘የሰው ልጆች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አምላክ ሊነግራቸው አይገባም’ ያለ ያህል ነው፤ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር በራሳቸው ቢወስኑ የተሻለ እንደሆነ ገልጿል። ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ማጥፋት ይችል ነበር። ይሁንና እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ሰይጣን የተናገረው ነገር ውሸት እንደሆነ ሊረጋገጥ ይችል ነበር? በፍጹም።

9 በመሆኑም ይሖዋ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ አላጠፋቸውም። ከዚህ ይልቅ የሰው ልጆች ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ ጊዜ ሰጣቸው። ይሖዋ እንዲህ ማድረጉ፣ ሰይጣን ውሸታም እንደሆነና ለሰው ልጆች የተሻለውን ነገር የሚያውቀው ይሖዋ እንደሆነ ለማሳየት ያስችላል። ምዕራፍ 11 ላይ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ እንማራለን። ይሁንና አዳምና ሔዋን ስላደረጉት ነገር ምን ይሰማሃል? ሰይጣንን ማመናቸውና የአምላክን ትእዛዝ አለማክበራቸው ተገቢ ነው? ለአዳምና ለሔዋን ሁሉንም ነገር የሰጣቸው ይሖዋ ነው። ፍጹም ሕይወት፣ ውብ መኖሪያና አስደሳች ሥራ ሰጥቷቸዋል። ሰይጣን ግን ምንም መልካም ነገር አድርጎላቸው አያውቅም። አንተ በአዳምና በሔዋን ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

10. እያንዳንዳችን ምን ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል?

10 በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዳችን ተመሳሳይ ምርጫ ቀርቦልናል፤ ደግሞም ሕይወታችን የተመካው በምናደርገው ምርጫ ላይ ነው። ይሖዋን በመታዘዝና ለእሱ በመገዛት ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማሳየት እንችላለን። አለዚያ የሰይጣን ተገዢዎች እንሆናለን። (መዝሙር 73:28፤ ምሳሌ 27:11⁠ን አንብብ።) በዚህ ዓለም ላይ አምላክን የሚታዘዙት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። እንዲያውም ይህን ዓለም እየገዛ ያለው አምላክ አይደለም። ታዲያ ማን ነው?

ይህን ዓለም የሚገዛው ማን ነው?

ሰይጣን ለኢየሱስ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ሊሰጠው ግብዣ ሲያቀርብለት

የዓለም መንግሥታት ሁሉ የሰይጣን ባይሆኑ ኖሮ ለኢየሱስ በስጦታ መልክ ሊያቀርብለት ይችል ነበር?

11, 12. (ሀ) ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበለት ግብዣ ምን ያሳያል? (ለ) ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዢ እንደሆነ የሚያሳዩት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

11 ኢየሱስ ዓለምን የሚገዛው ማን እንደሆነ ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት ሰይጣን ለኢየሱስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው።” ከዚያም “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ [ወይም ብትሰግድልኝ] እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” በማለት ቃል ገባለት። (ማቴዎስ 4:8, 9፤ ሉቃስ 4:5, 6) እስቲ አስበው፣ እነዚህ መንግሥታት የሰይጣን ባይሆኑ ኖሮ ለኢየሱስ በስጦታ መልክ ሊያቀርብለት ይችል ነበር? አይችልም። የዓለም መንግሥታት በሙሉ የሰይጣን ናቸው።

12 ይሁንና ‘ሰይጣን እንዴት የዚህ ዓለም ገዢ ሊሆን ይችላል? ጽንፈ ዓለሙን የፈጠረውና ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይሖዋ አይደለም?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። (ራእይ 4:11) እርግጥ ነው፣ ጽንፈ ዓለሙን የፈጠረው ይሖዋ ነው፤ ሆኖም ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዢ” ሰይጣን እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11) ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣን ዲያብሎስን “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ሐዋርያው ዮሐንስም “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” በማለት ጽፏል።—1 ዮሐንስ 5:19

የሰይጣን ዓለም የሚጠፋው እንዴት ነው?

13. አዲስ ዓለም የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

13 በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ሄደዋል። በዓለም ላይ ጦርነት፣ ሙስና፣ አታላይነትና ዓመፅ በጣም ተስፋፍቷል። የሰው ልጆች የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ እነዚህን ችግሮች ሊያስወግዱ አይችሉም። አምላክ ግን ይህን በክፋት የተሞላ ዓለም በአርማጌዶን ጦርነት አስወግዶ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያቋቁማል።—ራእይ 16:14-16፤ ተጨማሪ ሐሳብ 10⁠ን ተመልከት።

14. የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል?

14 ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን በሰማይ ያለው መስተዳድር ወይም መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ “የሰላም መስፍን” ሆኖ እንደሚገዛና መንግሥቱም መጨረሻ እንደማይኖረው በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ኢየሱስ ተከታዮቹ ስለዚህ መንግሥት እንዲጸልዩ አስተምሯል፤ እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።” (ማቴዎስ 6:10) በምዕራፍ 8 ላይ የአምላክ መንግሥት፣ የዓለምን መንግሥታት አጥፍቶ ብቻውን የሚገዛው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። (ዳንኤል 2:44⁠ን አንብብ።) የአምላክ መንግሥት ምድር ውብ ገነት እንድትሆን ያደርጋል።—ተጨማሪ ሐሳብ 11⁠ን ተመልከት።

አዲስ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ቀርቧል!

ሰዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሲዘምሩ፣ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ሲጫወቱና ሲደሰቱ

15. “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?

15 መጽሐፍ ቅዱስ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል” በማለት ቃል ገብቷል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 65:17) አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር” የሚለውን ቃል በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ለማመልከት ይጠቀምበታል። (ዘፍጥረት 11:1) በመሆኑም ጽድቅ የሰፈነበት “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ አምላክን የሚታዘዙና የእሱን በረከት የሚያገኙ ሰዎችን ያመለክታል።

16. አምላክ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ምን ልዩ ስጦታ ይሰጣቸዋል? ይህን ስጦታ ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ኢየሱስ፣ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች “የዘላለም ሕይወት” እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። (ማርቆስ 10:30) ይህን ስጦታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት እባክህ ዮሐንስ 3:16⁠ን እና 17:3⁠ን አንብብ። ምድር ገነት ስትሆን ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይኖሩ ይሆን? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ እንመልከት።

17, 18. ወደፊት በምድር ሁሉ ላይ ሰላም እንደሚሰፍንና ተረጋግተን እንደምንኖር እንዴት ማወቅ እንችላለን?

17 ክፋት፣ ጦርነት፣ ወንጀልና ዓመፅ አይኖርም። በምድር ላይ ክፉ ሰዎች ፈጽሞ አይኖሩም። (መዝሙር 37:10, 11) አምላክ “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።” (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4) ምድር አምላክን በሚወዱና እሱን በሚታዘዙ ሰዎች ትሞላለች። በምድር ላይ ለዘላለም ሰላም ይሰፍናል።—መዝሙር 72:7

18 የይሖዋ ሕዝቦች ተረጋግተው ይኖራሉ። በጥንት ዘመን እስራኤላውያን አምላክን ሲታዘዙ ጥበቃ ያደርግላቸው ስለነበር ተረጋግተው ይኖሩ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:18, 19) ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ የሚያስፈራን ነገር አይኖርም። ምንጊዜም ተረጋግተን እንኖራለን!—ኢሳይያስ 32:18⁠ን እና ሚክያስ 4:4⁠ን አንብብ።

19. አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የተትረፈረፈ ምግብ እንደሚኖር እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

19 የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል። “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።” (መዝሙር 72:16) ይሖዋ “አምላካችን ይባርከናል”፤ በመሆኑም “ምድር ፍሬዋን ትሰጣለች።”—መዝሙር 67:6

20. ምድር ገነት እንደምትሆን እንዴት እናውቃለን?

20 መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። ሰዎች የሚያማምሩ ቤቶችና የአትክልት ቦታዎች ይኖሯቸዋል። (ኢሳይያስ 65:21-24⁠ን እና ራእይ 11:18⁠ን አንብብ።) መላዋ ምድር እንደ ኤደን ገነት ውብ ትሆናለች። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታሟላለህ” ይላል።—መዝሙር 145:16

21. ወደፊት ሰዎችና እንስሳት በሰላም እንደሚኖሩ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

21 ሰዎችና እንስሳት በሰላም ይኖራሉ። በዚያን ጊዜ እንስሳት በሰው ልጆች ላይ ጉዳት አያደርሱም። አሁን የምንፈራቸውን አደገኛ እንስሳት ወደፊት ትናንሽ ልጆች እንኳ አይፈሯቸውም።—ኢሳይያስ 11:6-9⁠ን እና 65:25⁠ን አንብብ።

22. ወደፊት ኢየሱስ ለታመሙ ሰዎች ምን ያደርጋል?

22 የሚታመም ሰው አይኖርም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብዙ ሰዎችን ፈውሷል። (ማቴዎስ 9:35፤ ማርቆስ 1:40-42፤ ዮሐንስ 5:5-9) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ወደፊት የታመሙትን ሁሉ ይፈውሳል። በዚያን ጊዜ “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም።—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6

23. የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?

23 የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ። አምላክ በሞት ያንቀላፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት እንደሚያስነሳ ቃል ገብቷል። ‘ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት ይነሳሉ።’—ዮሐንስ 5:28, 29⁠ን አንብብ፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

24. በገነት ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት በተመለከተ ምን ይሰማሃል?

24 ሁላችንም ምርጫ ቀርቦልናል። ስለ ይሖዋ መማርና እሱን ማገልገል እንችላለን፤ አለዚያ ደግሞ በመረጥነው መንገድ መኖር እንችላለን። ይሖዋን ለማገልገል ከመረጥን አስደሳች ተስፋ ይጠብቀናል። ኢየሱስ ከጎኑ ተሰቅሎ ለነበረው ሰው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት ቃል ገብቶለታል። (ሉቃስ 23:43) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንማራለን፤ በተጨማሪም ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠንን አስደሳች ተስፋዎች የሚፈጽመው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ክለሳ

እውነት 1፦ አምላክ እኛን የፈጠረው በዓላማ ነው

“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29

አምላክ ለሰዎች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

  • ዘፍጥረት 1:28

    የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች ምድርን ገነት እንዲያደርጉና እንስሳትን እንዲንከባከቡ ነበር።

  • ኢሳይያስ 46:9-11፤ 55:11

    አምላክ ዓላማውን ይፈጽማል፤ ደግሞም እንዲህ እንዳያደርግ ሊከለክለው የሚችል ምንም ነገር የለም።

እውነት 2፦ ሕይወት በመከራ የተሞላው ለምንድን ነው?

“መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።” —1 ዮሐንስ 5:19

ዓለምን የሚገዛው ማን ነው?

  • ዮሐንስ 12:31

    ኢየሱስ የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን እንደሆነ ተናግሯል።

  • ያዕቆብ 1:13-15

    ሰይጣን የራሱ ያልሆነውን ነገር ተመኝቷል።

  • ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-6

    ሰይጣን ሔዋንን አታለላት፤ አዳምና ሔዋን አምላክን ባለመታዘዛቸው ከጊዜ በኋላ ሞቱ።

  • ሮም 3:23፤ 5:12

    ከአዳም ኃጢአት ስለወረስን እኛም እንሞታለን።

  • 2 ቆሮንቶስ 4:3, 4

    ሰይጣን ሰዎችን ያሳስታል።

እውነት 3፦ የአምላክ መንግሥት መፍትሔ ይሰጣል

“መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም።”—ማቴዎስ 6:10

ይሖዋ ወደፊት ምን ያደርጋል?

  • ዳንኤል 2:44

    አምላክ ያቋቋመው መስተዳድር የዓለምን መንግሥታት ሁሉ አጥፍቶ ብቻውን ይገዛል።

  • ራእይ 16:14-16

    አምላክ በክፋት የተሞላውን ይህን ዓለም በአርማጌዶን ጦርነት ያጠፋዋል።

  • ኢሳይያስ 9:6, 7

    ይሖዋ ኢየሱስን በሰማይ ያለው መስተዳድር ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። ኢየሱስ ምድርን ይገዛል።

እውነት 4፦ የአምላክ መንግሥት ምድርን ገነት ያደርጋታል

“አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታሟላለህ።”—መዝሙር 145:16

የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያደርግልናል?

  • መዝሙር 46:9

    ጦርነት፣ ወንጀልና ዓመፅ ይወገዳል።

  • ኢሳይያስ 32:18፤ 65:21-24

    በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሰዎች ሁሉ የሚያማምሩ ቤቶችና የአትክልት ቦታዎች ይኖሯቸዋል፤ በዚያም ተስማምተው በሰላም ይኖራሉ።

  • መዝሙር 72:16

    የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል።

  • ኢሳይያስ 11:6-9

    ሰዎችና እንስሳት በሰላም ይኖራሉ።

  • ኢሳይያስ 33:24፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

    የሚታመም ሰው አይኖርም፤ የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ