የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች፣ መጋቢት-ሚያዝያ 2021
ከመጋቢት 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 7–8
“ከእስራኤላውያን ሰፈር የምናገኘው ትምህርት”
it-1 497 አን. 3
ጉባኤ
እስራኤል ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ተወካዮች ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ወክለው አንዳንድ ነገሮችን ያደርጉ ነበር። (ዕዝራ 10:14) ለምሳሌ የማደሪያ ድንኳኑ ከተተከለ በኋላ “የየነገዱ አለቆች” መባ አቅርበዋል። (ዘኁ 7:1-11) በነህምያ ጊዜም ሕዝቡን በመወከል ‘ጽኑ ስምምነቱን’ በማኅተም ያጸደቁት ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና “የሕዝቡ መሪዎች” ነበሩ። (ነህ 9:38–10:27) እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅትም ‘የማኅበረሰቡ አለቆች ይኸውም ከጉባኤው መካከል የተመረጡ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች’ ነበሩ፤ ከእነዚህ መካከል 250ዎቹ ከቆሬ፣ ከዳታን፣ ከአቤሮንና ከኦን ጋር ተባብረው በሙሴና በአሮን ላይ ዓምፀዋል። (ዘኁ 16:1-3) ሙሴ መለኮታዊ አመራር በመከተል አለቆች ከሆኑት የእስራኤል ሽማግሌዎች መካከል 70ዎቹን በመምረጥ ብቻውን ሊሸከም ያልቻለውን “የሕዝቡን ሸክም” በመሸከም እንዲረዱት አድርጓል። (ዘኁ 11:16, 17, 24, 25) ዘሌዋውያን 4:15 ‘የማኅበረሰቡን ሽማግሌዎች’ ይጠቅሳል፤ የሕዝቡ ተወካዮች ሆነው የሚያገለግሉት ሽማግሌዎቹ፣ መሪዎቹ፣ ዳኞቹና አለቆቹ የነበሩ ይመስላል።—ዘኁ 1:4, 16፤ ኢያሱ 23:2፤ 24:1
it-2 796 አን. 1
ሮቤል
በእስራኤል ሰፈር ውስጥ ሮቤላውያን ከስምዖንና ከጋድ ዘሮች ጋር በመሆን በማደሪያ ድንኳኑ በስተ ደቡብ ይሰፍሩ ነበር። በሚጓዙበት ወቅት በሮቤል የሚመራው ሦስት ነገዶችን ያቀፈው ምድብ ይሁዳ፣ ይሳኮርና ዛብሎን የሚገኙበትን ሦስት ነገዶችን ያቀፈ ምድብ ተከትሎ ይጓዝ ነበር። (ዘኁ 2:10-16፤ 10:14-20) የማደሪያ ድንኳኑ በተመረቀበት ዕለት ነገዶቹ መባ ያቀረቡበት ቅደም ተከተልም ይኸው ነበር።—ዘኁ 7:1, 2, 10-47
የዘኍልቍ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
8:25, 26፦ በዕድሜ የገፉት ሌዋውያን እንዲያርፉና ሥራውን በብቃት ማከናወን የሚችሉ ወንዶች በዚህ አገልግሎት እንዲካፈሉ ሲባል ሌዋውያን ከተወሰነ ዕድሜ በኋላ ከመደበኛው አገልግሎት ጡረታ እንዲወጡ ታዝዘው ነበር። ያም ሆኖ ሌሎቹን ሌዋውያን በፈቃደኝነት ማገዝ ይችሉ ነበር። በዛሬው ጊዜ ከመንግሥቱ ስብከት ሥራ ጡረታ ባይወጣም የዚህ ሕግ መሠረታዊ ሥርዓት ጠቃሚ ትምህርት ይዟል። አንድ ክርስቲያን በዕድሜ መግፋት ምክንያት አንዳንድ ግዴታዎቹን መወጣት ካቃተው አቅሙ በሚፈቅድለት የአገልግሎት መስክ መሰማራት ይችላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 835
በኩር
የእስራኤላውያን በኩር ወንዶች የቤተሰብ ራስ ስለሚሆኑ መላውን ብሔር ይወክሉ ነበር። እንዲያውም ይሖዋ መላውን ብሔር “የበኩር ልጄ” በማለት ጠርቶታል፤ እንዲህ ያለው በአብርሃም ቃል ኪዳን ምክንያት የተገኘ የበኩር ብሔር ስለሆነ ነው። (ዘፀ 4:22) ይሖዋ የእስራኤላውያን በኩሮችን ሕይወት ስላተረፈላቸው “ከእስራኤል ሕዝብ መካከል . . . ከሰውም ሆነ ከእንስሳ መካከል በኩር የሆነው ወንድ ሁሉ” ለእሱ እንዲቀደስለት አዟል። (ዘፀ 13:2) በመሆኑም በኩር የሆኑ ወንዶች ልጆች ለአምላክ የተለዩ ነበሩ።
ከመጋቢት 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 9–10
“ይሖዋ ሕዝቡን የሚመራው እንዴት ነው?”
it-1 398 አን. 3
ሰፈር
ግዙፍ የሆነው የእስራኤላውያን ሰፈር ከቦታ ቦታ (ሙሴ በዘኁልቁ 33 ላይ ሕዝቡ የሰፈረባቸውን 40 ቦታዎች ጠቅሷል) የሚጓዝበት መንገድም አስደናቂ መደራጀት የሚታይበት ነበር። ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ በሚቆይባቸው ቀናት ሁሉ እስራኤላውያን በሰፈሩበት ቦታ ይቆዩ ነበር። ደመናው ከድንኳኑ ላይ ሲነሳ ደግሞ እስራኤላውያን ተነስተው ይጓዙ ነበር። “እነሱም የሚሰፍሩት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር፤ ተነስተውም የሚጓዙት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር።” (ዘኁ 9:15-23) ከብር ተጠፍጥፈው የተሠሩ ሁለት መለከቶች ይሖዋ በዚህ ረገድ የሚሰጠውን ትእዛዝ ለሕዝቡ ለማስተላለፍ ያገለግሉ ነበር። (ዘኁ 10:2, 5, 6) መለከቶቹ ድምፃቸው እየተለዋወጠ ሲነፋ እስራኤላውያን ከሰፈሩበት ተነስተው መጓዝ ነበረባቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ መንገድ የተጓዙት “በሁለተኛው ዓመት [1512 ዓ.ዓ.] ሁለተኛ ወር፣ ከወሩም በ20ኛው ቀን” ነበር። ከፊት ይጓዝ የነበረው የቃል ኪዳኑ ታቦት ሲሆን ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የይሁዳ ምድብ ይከተላል፤ በመጀመሪያ የይሁዳ ነገድ፣ ከዚያም የይሳኮርና የዛብሎን ነገዶች ይጓዛሉ። ቀጥሎ ደግሞ ጌድሶናውያንና ሜራራውያን ለእነሱ የተመደቡትን የማደሪያ ድንኳኑን ዕቃዎች ተሸክመው ይከተላሉ። ከዚያም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የሮቤል ምድብ ይከተላል፤ በመጀመሪያ የሮቤል ከዚያም የስምዖንና የጋድ ነገዶች ይከተላሉ። ከእነሱ በኋላ ቀአታውያን የመቅደሱን ዕቃዎች ተሸክመው ይጓዛሉ፤ ቀጥሎም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የኤፍሬም ምድብ ይጓዛል፤ በመጀመሪያ የኤፍሬም ነገድ ከዚያም የምናሴና የቢንያም ነገዶች ይከተላሉ። በመጨረሻም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የዳን ምድብ የኋላ ደጀን በመሆን ይጓዛል፤ በመጀመሪያ የዳን ነገድ ከዚያም የአሴርና የንፍታሌም ነገዶች ይከተላሉ። ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ከፊት የሚጓዙትና የኋላ ደጀን የሚሆኑት ብዙ ቁጥር ያላቸውና ኃያል የሆኑት ምድቦች ነበሩ።—ዘኁ 10:11-28
አምላክ እንደሚመራን የሚያሳየውን ማስረጃ ታስተውላለህ?
የአምላክን አመራር እንደምናደንቅ እንዴት ማሳየት እንችላለን? ሐዋርያው ጳውሎስ “በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ” ብሏል። (ዕብ. 13:17) እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ራስህን በሙሴ ዘመን በነበረ አንድ እስራኤላዊ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክር። ለተወሰነ ጊዜ ስትጓዙ ከቆያችሁ በኋላ ዓምዱ ቆመ እንበል። ዓምዱ በዚህ ቦታ ላይ ምን ያህል ጊዜ ይቆይ ይሆን? ለአንድ ቀን? ለአንድ ሳምንት? ወይስ ለበርካታ ወራት? ‘ጓዜን በሙሉ መፍታት ይኖርብኝ ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። መጀመሪያ ላይ በጣም የሚያስፈልጉህን ነገሮች ብቻ ታወጣ ይሆናል። ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ስትል ተሸክፎ የተቀመጠውን ዕቃህን መበርበር ያታክትህና ዕቃህን በሙሉ ማውጣት ትጀምራለህ። ይሁንና ዕቃህን አወጣጥተህ ልትጨርስ ስትል ዓምዱ ሲንቀሳቀስ ትመለከታለህ፤ በመሆኑም ጓዝህን እንደገና መሸከፍ ይኖርብሃል! ይህን ማድረግ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው። እንደዚያም ሆኖ እስራኤላውያኑ “ወዲያውኑ ተነስተው [መጓዝ]” ነበረባቸው።—ዘኍ. 9:17-22
ታዲያ እኛስ መለኮታዊ መመሪያ ሲሰጠን ምላሻችን ምንድን ነው? መመሪያውን “ወዲያውኑ” ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን? ወይስ ነገሮችን በለመድነው መንገድ መሥራታችንን እንቀጥላለን? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስለ ማስጠናት፣ የውጭ አገር ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ስለ መስበክ፣ አዘውትሮ የቤተሰብ አምልኮ ስለ ማድረግ፣ ከሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ጋር ስለ መተባበር እንዲሁም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ተገቢ ምግባር ስለ ማሳየትና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች በቅርብ የተሰጡንን መመሪያዎች በሚገባ ተረድተናቸዋል? የአምላክን መመሪያ እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ምክር መቀበል ነው። ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች በምናደርግበት ጊዜ በራሳችን ጥበብ ከመታመን ይልቅ መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋና ወደ ድርጅቱ ዘወር እንላለን። አንድ ልጅ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ ወደ ወላጆቹ እንደሚጠጋ ሁሉ እኛም በዚህ ዓለም ላይ ያሉት ችግሮች እንደ ኃይለኛ ወጀብ በሚዥጎደጎዱብን ጊዜ ጥበቃ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ድርጅት እንጠጋለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 199 አን. 3
ስብሰባ
የመሰብሰብ አስፈላጊነት። ሕዝቡ መንፈሳዊ ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ ይሖዋ ለስብሰባ ባደረጋቸው ዝግጅቶች በሙሉ መጠቀማቸው ያለው አስፈላጊነት ከዓመታዊው የፋሲካ በዓል ጋር በተያያዘ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። አንድ ሰው ንጹሕ ሆኖ ሳለ ወይም ሩቅ መንገድ ሳይሄድ በቸልተኝነት ፋሲካን ሳያከብር ቢቀር ተለይቶ መጥፋት ማለትም መገደል ነበረበት። (ዘኁ 9:9-14) ንጉሥ ሕዝቅያስ የይሁዳና የእስራኤል ነዋሪዎች ፋሲካን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ በጋበዘበት ወቅት የላከው መልእክት በከፊል እንዲህ ይል ነበር፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፣ . . . ወደ ይሖዋ ተመለሱ፤ . . . እንደ አባቶቻችሁ አንገታችሁን አታደንድኑ። የሚነድ ቁጣው ከእናንተ እንዲመለስ ለይሖዋ ተገዙ፤ ለዘላለም ወደቀደሰው መቅደሱ ኑ፤ አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ። . . . አምላካችሁ ይሖዋ ሩኅሩኅና መሐሪ ነውና፤ ወደ እሱም ከተመለሳችሁ ፊቱን አያዞርባችሁም።” (2ዜና 30:6-9) ሆን ብሎ ከበዓሉ መቅረት አምላክን እንደመተው ይቆጠር ነበር። ክርስቲያኖች እንደ ፋሲካ ያሉትን በዓላት ባያከብሩም ጳውሎስ የአምላክ ሕዝቦች አዘውትረው መሰብሰባቸውን ችላ እንዳይሉ ያሳሰባቸው መሆኑ ተገቢ ነው፤ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።”—ዕብ 10:24, 25፤ ጉባኤ የሚለውን ተመልከት።
ከመጋቢት 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 11–12
“ከአጉረምራሚነት መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?”
ሰምታችሁ የምትረሱ አትሁኑ
20 ብዙዎቹ ክርስቲያኖች በፆታ ብልግና አይሸነፉም። ሆኖም የአምላክን ሞገስ ሊያሳጣ የሚችል አጉረምራሚ ወደ መሆን የሚያደርስ ጎዳና እንዳንከተል ጠንቃቆች መሆን አለብን። ጳውሎስ እንዲህ በማለት አጥብቆ መክሮናል:- “ከእነርሱም [ከእስራኤላውያን] አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጐራጐሩ [“እንዳጉረመረሙ፣” የ1980 ትርጉም] በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐራጒሩ [“አታጉረምርሙ፣” የ1980 ትርጉም]።” (1 ቆሮንቶስ 10:9, 10) እስራኤላውያን ተዓምራዊ በሆነ መንገድ በሚያገኙት መና ላይ በማማረር በሙሴና በአሮን አልፎ ተርፎም በአምላክ ላይ አጉረምርመዋል። (ዘኁልቁ 16:41፤ 21:5) ይሖዋ ዝሙት በፈጸሙት ሰዎች ያዘነውን ያህል ባጉረመረሙት ሰዎች አዝኗልን? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ያጉረመረሙ በርካታ ሰዎች በእባብ ተገድለዋል። (ዘኁልቁ 21:6) ከዚህ ቀደም ብሎ በደረሰ አንድ ክስተት ከ14,700 የሚበልጡ ዓመፀኛ አጉረምራሚዎች ተገድለዋል። (ዘኁልቁ 16:49) ስለዚህ ለይሖዋ ዝግጅቶች አክብሮት በማጣት የይሖዋን ትዕግሥት አንፈታተን።
‘አታጉረምርሙ’
7 የእስራኤላውያን አመለካከት ምንኛ ተለውጦ ነበር! ቀደም ሲል፣ ይሖዋ ከግብፅ ስላወጣቸውና ቀይ ባሕርን በተአምር ስላሻገራቸው የተሰማቸው የአመስጋኝነት መንፈስ በመዝሙር እንዲያወድሱት አነሳስቷቸው ነበር። (ዘፀአት 15:1-21) ነገር ግን በምድረ በዳ ችግር ስላጋጠማቸውና ከነዓናውያንን በመፍራታቸው ምክንያት የአመስጋኝነት መንፈሳቸው ወደ ቅሬታ ተቀየረ። ላገኙት ነፃነት አምላክን ከማመስገን ይልቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደነፈጋቸው አድርገው በተሳሳተ መንገድ ነቅፈውታል። ማጉረምረማቸው ለይሖዋ ዝግጅቶች አድናቆት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው። ይሖዋ “ይህ ክፉ ማኅበረ ሰብ በእኔ ላይ የሚያጕረመርመው እስከ መቼ ነው?” ብሎ መናገሩ ምንም አያስገርምም።—ዘኍልቍ 14:27፤ 21:5
it-2 719 አን. 4
ጭቅጭቅ
ማጉረምረም። ማጉረምረም አያንጽም እንዲሁም ሰዎችን ተስፋ ያስቆርጣል። እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ላይ አጉረመረሙ፤ ይህን ያደረጉት ይሖዋ በአገልጋዮቹ በሙሴና በአሮን አማካኝነት የሚሰጠውን አመራር በመተቸት ነው። (ዘፀ 16:2, 7) በኋላም ሙሴ በእነሱ አጉረምራሚነት ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ሞትን እስከመመኘት ደርሷል። (ዘኁ 11:13-15) ማጉረምረም በአጉረምራሚው ላይም ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። ይሖዋ አጉረምራሚዎቹ በሙሴ ላይ የሰነዘሩትን ትችት በእሱ መለኮታዊ አመራር ላይ እንደማመፅ ቆጥሮታል። (ዘኁ 14:26-30) ስህተት ለቃቃሚ በመሆናቸው የተነሳ ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች ብዙ ናቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 309
መና
መግለጫ። መና “እንደ ድንብላል ዘር ነጭ” ሲሆን “መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር”፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሙጫ የዕንቁ ዓይነት ቅርጽ ያለው ብርሃን የሚያሳልፍ ነገር ነው። የመና ጣዕም “ማር እንደተቀባ ቂጣ” ወይም “በዘይት ተለውሶ እንደተጋገረ ጣፋጭ ቂጣ” ነበር። መና በወፍጮ ከተፈጨ ወይም በሙቀጫ ከተወቀጠ በኋላ ይቀቀል አሊያም እንደ ቂጣ ይጋገር ነበር።—ዘፀ 16:23, 31፤ ዘኁ 11:7, 8
ከመጋቢት 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 13–14
“እምነት ደፋሮች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?”
እምነትና አምላካዊ ፍርሃት የሚያስገኘው ድፍረት
5 ይሁን እንጂ ከሰላዮቹ መካከል ሁለቱ ማለትም ኢያሱና ካሌብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። በመሆኑም ከነዓናውያንን “እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለን . . . ጥላቸው ተገፎአል፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነውና አትፍሯቸው” ሲሉ ተናገሩ። (ዘኍልቍ 14:9) ኢያሱና ካሌብ እንዲህ ያለ አዎንታዊ አመለካከት የያዙት ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ ነበር? በጭራሽ አልነበረም። እንደማንኛውም እስራኤላዊ ይሖዋ አሥሩን መቅሰፍት በማምጣት ኃያሏን ግብጽንና አማልክቶቿን እንዴት አድርጎ እንዳዋረዳቸው ተመልክተዋል። በኋላም ይሖዋ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ሲያሰጥማቸው እማኞች ነበሩ። (መዝሙር 136:15) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አሥሩ ሰላዮችም ሆኑ ወሬያቸውን አምነው የተቀበሉት ሰዎች መፍራታቸው ተገቢ አልነበረም። ስለሆነም ይሖዋ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው?” በማለት በሁኔታው በጥልቅ ማዘኑን ገልጿል።—ዘኍልቍ 14:11
6 ይሖዋ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ምን እንደነበር በግልጽ ተናግሯል፤ ሕዝቡ በፍርሃት መርበድበዳቸው እምነት ማጣታቸውን የሚያጋልጥ ነበር። አዎን፣ እምነትና ድፍረት በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው። ይህም በመሆኑ ሐዋርያው ዮሐንስ የክርስቲያን ጉባኤንና የሚያደርገውን መንፈሳዊ ውጊያ አስመልክቶ “ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:4) በዛሬው ጊዜ፣ ወጣት አረጋዊ፣ ብርቱ ደካማ ሳይባል ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብኩ የገፋፋቸው የኢያሱና የካሌብ ዓይነት እምነት ነው። ይህን ኃያልና ደፋር ሠራዊት ማንኛውም ዓይነት ጠላት ዝም ሊያሰኘው አይችልም።—ሮሜ 8:31
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 740
አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ምድር
አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ምድር በእርግጥም መልካም ምድር ነበር። ሙሴ ከብሔሩ አስቀድመው ተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉና ከምድሪቱ ፍሬ ጥቂት እንዲያመጡ ሰላዮች በላከበት ወቅት ሰላዮቹ የሮማን ፍሬዎችንና የበለስ ፍሬዎችን እንዲሁም የወይን ዘለላ አምጥተው ነበር፤ የወይን ዘለላው ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሁለት ሰዎች በዱላ መሸከም አስፈልጓቸዋል። ሰላዮቹ በእምነት ማጣት የተነሳ ፈርተው የነበረ ቢሆንም “በእርግጥም ምድሪቱ ወተትና ማር የምታፈስ ናት” በማለት ተናግረዋል።—ዘኁ 13:23, 27
ከመጋቢት 29–ሚያዝያ 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 15–16
“ከኩራትና ከልክ በላይ በራስ ከመተማመን ራቁ”
ይሖዋ ያውቃችኋል?
12 ይሁንና የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር እየተጓዘ ሳለ፣ ቆሬ የይሖዋ ዝግጅት አንዳንድ ችግሮች እንዳሉት ሆኖ ተሰማው። ከዚያም የማኅበረሰቡ መሪዎች የነበሩ 250 ሰዎች ለውጥ ለማምጣት በማሰብ ከቆሬ ጋር አበሩ። ቆሬና ግብረ አበሮቹ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳላቸው እርግጠኞች ነበሩ። ሙሴን እና አሮንን እንዲህ አሏቸው፦ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም! የማኅበረ ሰቡ አባላት ሁሉ እያንዳንዳቸው የተቀደሱ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነው።” (ዘኍ. 16:1-3) ይህ እንዴት ያለ ከልክ ያለፈ በራስ የመተማመን ስሜትና ኩራት የሚንጸባረቅበት አነጋገር ነው! ሙሴም፣ ይሖዋ ‘የእርሱ የሆነውን ይለያል’ አላቸው። (ዘኍልቍ 16:5ን አንብብ።) በቀጣዩ ቀን አመሻሹ ላይ ቆሬና ከእሱ ጋር ያመፁት ሰዎች ሁሉ ሞቱ።—ዘኍ. 16:31-35
ይሖዋ ያውቃችኋል?
11 ሙሴና ቆሬ፣ ለይሖዋ ዝግጅት እንዲሁም እሱ ላደረገው ውሳኔ አክብሮት ከማሳየት ጋር በተያያዘ ያላቸው አመለካከት ፈጽሞ የተለያየ ነበር። ያደረጉት ውሳኔ ይሖዋ ለእነሱ ባለው አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ቆሬ ከቀዓት ወገን የሆነ ሌዋዊ ሲሆን በርካታ መብቶችም ነበሩት። እነዚህም እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ መመልከትን፣ ይሖዋ በሲና ተራራ በዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ መደገፍንና የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክሞ መሄድን የሚያካትቱ ይመስላል። (ዘፀ. 32:26-29፤ ዘኍ. 3:30, 31) ቆሬ ለብዙ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገለ ሲሆን በዚህም የተነሳ በበርካታ እስራኤላውያን ዘንድ አክብሮት አትርፎ ነበር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ ስጡ!
ይሖዋ ጉዳዩን እንዲህ አቅልሎ አልተመለከተውም። “እግዚአብሔርም ሙሴን:- ሰውየው ፈጽሞ ይገደል . . . አለው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘኁልቁ 15:35) ይሖዋ ሰውዬው ያደረገውን ነገር ይህን ያህል አክብዶ የተመለከተው ለምንድን ነው?
ሕዝቡ እንጨት ለመልቀምም ሆነ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለማግኘት የሚሠሩባቸው ስድስት ቀናት አሏቸው። ሰባተኛውን ቀን ግን ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ማዋል ነበረባቸው። እንጨት መልቀሙ ምንም ስህተት የሌለበት ቢሆንም ለይሖዋ አምልኮ የተወሰነውን ጊዜ ለዚህ ሥራ ማዋሉ ግን ፈጽሞ ስህተት ነበር። ምንም እንኳ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም ይህ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ቅድሚያ ልንሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች ጥሩ ትምህርት አይሰጠንም?—ፊልጵስዩስ 1:10
ከሚያዝያ 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 17–19
“የአንተ . . . ውርሻ እኔ ነኝ”
ይሖዋን ድርሻህ አድርገኸዋል?
9 በተስፋይቱ ምድር ርስት ያልተሰጣቸውን ሌዋውያንን አስብ። በዋነኝነት የሚያሳስቧቸው ከንጹሕ አምልኮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ስለነበሩ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በተመለከተ በይሖዋ መታመን ነበረባቸው፤ እሱ “ድርሻህ . . . እኔ ነኝ” ብሏቸው ነበር። (ዘኍ. 18:20) ካህናትና ሌዋውያን ያደርጉት እንደነበረው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባናገለግልም ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን በመተማመን የእነሱን ዓይነት አመለካከት ማዳበር እንችላለን። ወደ መጨረሻው ዘመን ማብቂያ ይበልጥ በቀረብን መጠን አምላክ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን መተማመናችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው።—ራእይ 13:17
ድርሻዬ ይሖዋ ነው
4 ይህ ኃላፊነት ለሌዋውያኑ ምን ትርጉም ነበረው? ይሖዋ ድርሻቸው እንደሚሆን ነግሯቸዋል፤ ይህም ሲባል በተስፋይቱ ምድር ርስት ከመቀበል ይልቅ በዋጋ ሊተመን የማይችል የአገልግሎት መብት በአደራ ተሰጥቷቸዋል ማለት ነው። ርስታቸው “ለእግዚአብሔር የሚሰጡት የክህነት አገልግሎት” ነበር። (ኢያሱ 18:7) በዘኍልቍ 18:20 ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ይህ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ለችግር የሚዳርጋቸው አልነበረም። (ዘኍልቍ 18:19, 21, 24ን አንብብ።) ይሖዋ “ለሚሠሩት ሥራ ደመወዝ እንዲሆናቸው ከእስራኤል የሚወጣውን ዐሥራት ሁሉ ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ” ብሏል። እስራኤላውያን ከምርታቸው እንዲሁም ከቤት እንስሶቻቸው ካገኙት ጭማሪ ላይ 10 በመቶውን ለሌዋውያን እንዲሰጡ ታዝዘው ነበር። ሌዋውያኑም በተራቸው ካገኙት ነገር መካከል “ምርጥ” የሆነውን ለካህናቱ ዐሥራት ይሰጡ ነበር። (ዘኍ. 18:25-29) በተጨማሪም የእስራኤል ልጆች ወደ ይሖዋ የአምልኮ ስፍራ ይዘው የሚመጡት ‘የተቀደሰ ቍርባን ሁሉ’ ለካህናቱ ይሰጣቸው ነበር። በመሆኑም ካህናቱ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጣቸው የሚተማመኑበት በቂ ምክንያት ነበራቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
g 7/02 20 አን. 2
ጨው—ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ሸቀጥ
በተጨማሪም ጨው የሚለው ቃል አስተማማኝና ዘላቂ የሆነን ነገር ያመለክት ነበር። ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይለወጥና የማይሻር ቃል ኪዳን “የጨው ቃል ኪዳን” ተብሎ ተጠርቷል። ቃል ኪዳን ተጋቢዎቹ ጨው ያለበት ምግብ አብረው በመብላት ቃል መጋባታቸውን ያረጋግጡ ነበር። (ዘኁልቁ 18:19) በሙሴ ሕግ በመሠዊያ ላይ በሚቀርቡ መሥዋዕቶች ላይ ጨው መጨመር አስፈላጊ ነበር። ይህም ከመበላሸትና ከመበስበስ የጸዳ መሆኑን ያመለክት እንደነበረ አያጠራጥርም።
ከሚያዝያ 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 20–21
“ውጥረት ውስጥ ብትሆኑም የዋህነት አሳዩ”
የዋህነትን በመፈለግ ይሖዋን ደስ አሰኙ
19 የዋህነትን መፈለጋችን ስህተት ከመሥራት ይጠብቀናል። እስቲ የሙሴን ሁኔታ በድጋሚ እንመልከት። ሙሴ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የዋህ በመሆን የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝቷል። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለ40 ዓመት ያህል ያደረጉት አስቸጋሪ ጉዞ ሊደመደም ጥቂት ሲቀረው ግን የዋህነት ማሳየት ተስኖት ነበር። እህቱ ሞታ በቃዴስ ከተቀበረች ብዙ ጊዜ አላለፈም፤ በግብፅ ውስጥ ሕይወቱን ያተረፈችለት እሷ ሳትሆን አትቀርም። አሁን ደግሞ እስራኤላውያን፣ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንዳልተሟሉላቸው በመናገር በድጋሚ ማጉረምረም ጀመሩ። ሕዝቡ የሚጠጣ ውኃ በማጣቱ “ከሙሴ ጋር ተጣላ።” ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በርካታ ተአምራትን ፈጽሟል፤ ሙሴም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ እስራኤላውያንን ለረጅም ጊዜ ሲመራ ቆይቷል። ሕዝቡ ይህን ሁሉ ቢያውቅም ከማጉረምረም ወደኋላ አላለም። እስራኤላውያን ውኃ በማጣታቸው ብቻ ሳይሆን በሙሴ ምክንያት ውኃ ያጡ ይመስል በእሱ ላይ ጭምር አጉረምርመዋል።—ዘኁ. 20:1-5, 9-11
የዋህነትን በመፈለግ ይሖዋን ደስ አሰኙ
20 ሙሴ በጣም ስለተበሳጨ እንደ ወትሮው ገር መሆን ሳይችል ቀረ። በይሖዋ በመታመን ልክ እንደታዘዘው ዓለቱን ከመናገር ይልቅ በምሬት ሕዝቡን የተቆጣ ከመሆኑም ሌላ ተአምሩን የሚፈጽመው እሱ ራሱ እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ ተናገረ። ከዚያም ዓለቱን ሁለቴ ሲመታው ውኃው እየተንዶለዶለ ይወጣ ጀመር። ኩራትና ብስጭት፣ ሙሴን አሳዛኝ ስህተት እንዲሠራ አድርገውታል። (መዝ. 106:32, 33) ሙሴ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የዋህነት ማሳየት ስላቃተው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከልክሏል።—ዘኁ. 20:12
21 ከዚህ ታሪክ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። አንደኛ፣ ምንጊዜም የዋህ ሆነን ለመቀጠል ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለብን። ለአፍታ እንኳ ከተዘናጋን ወዲያውኑ ኩራት ሊጠናወተንና ሞኝነት የሚንጸባረቅበት ነገር ልንናገር ወይም ልናደርግ እንችላለን። ሁለተኛ፣ ውጥረት ውስጥ ስንሆን የዋህነት ማሳየት ከባድ ሊሆንብን ይችላል፤ ስለዚህ ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ የዋህነት ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይል ዳኛ
በመጀመሪያ ደረጃ ሙሴ ዓመፀኞች ናችሁ ብሎ መፍረድ ይቅርና ሕዝቡን እንዲናገር እንኳ ትእዛዝ አልተሰጠውም ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ሙሴና አሮን ለአምላክ ክብር ሳይሰጡ ቀርተዋል። አምላክ ‘እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ አላከበራችሁኝም’ ብሏቸዋል። (ቁጥር 12) ሙሴ “እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” በማለት ውኃውን በተአምራዊ መንገድ የሚሰጣቸው አምላክ ሳይሆን እሱና አሮን እንደሆኑ የሚያስመስል ሐሳብ ተናግሯል። በሦስተኛ ደረጃ በዚህ ጊዜ የተበየነው ፍርድ ይሖዋ ከዚህ ቀደም ከሰጠው ፍርድ ጋር የሚጣጣም ነው። አምላክ ዓመፀኛ የነበረውን የቀድሞውን ትውልድ ወደ ከነዓን እንዳይገባ እንደከለከለው ሁሉ ሙሴንና አሮንንም ከልክሏቸዋል። (ዘኍልቍ 14:22, 23) በአራተኛ ደረጃ ሙሴና አሮን የእስራኤል መሪዎች ነበሩ። ብዙ ኃላፊነት ከተሰጠው ሰው ደግሞ ብዙ ይጠበቅበታል።—ሉቃስ 12:48
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ደካሞችን የምትመለከቱት በይሖዋ ዓይን ነው?
12 በእነዚህ ወቅቶች ይሖዋ፣ አሮን ላይ ወዲያውኑ እርምጃ ሊወስድ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ አሮን መጥፎ ሰው እንዳልሆነ ያውቃል። አሮን መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ሁኔታዎች ወይም ሌሎች ሰዎች ባሳደሩበት ተጽዕኖ በመሸነፉ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ ጥፋተኛ እንደሆነ ሲነገረው ወዲያውኑ ስህተቱን ያመነ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን የፍርድ ውሳኔ ደግፏል። (ዘፀ. 32:26፤ ዘኍ. 12:11፤ 20:23-27) ይሖዋ ትኩረት ያደረገው በአሮን እምነትና ከልብ ንስሐ በመግባቱ ላይ ነው። እንዲያውም ዘመናት ካለፉ በኋላም አሮንና ዘሮቹ ይሖዋን እንደሚፈሩ ተገልጿል።—መዝ. 115:10-12፤ 135:19, 20
ከሚያዝያ 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 22–24
“ይሖዋ እርግማንን ወደ በረከት ይቀይራል”
“ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች” ማወጅ
5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም የአምላክ ሕዝቦች የሚደርስባቸው ስደት ምሥራቹን ከመስበክ ወደኋላ እንዲሉ አላደረጋቸውም። በተደጋጋሚ እንደታየው ክርስቲያኖችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ ማስገደድ (ከአንድ እስር ቤት ወደ ሌላ ወይም ከአንድ አገር ወደ ሌላ ሊሆን ይችላል) በሌላ አካባቢ ያሉ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰሙ አጋጣሚውን ከፍቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ አስደናቂ ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘ አንድ አይሁዳዊ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክር የሆኑ እስረኞች ያላቸው ጥንካሬ እምነታቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ስላሳመነኝ እኔም ራሴ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።”
it-2 291
እብደት
ይሖዋን መቃወም እብደት ነው። ነቢዩ በለዓም የሞዓባውያን ንጉሥ ከሆነው ከባላቅ ገንዘብ ለመቀበል ሲል እስራኤላውያንን መርገም ፈልጎ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ይህን የሞኝነት አካሄዱን አክሽፎበታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ በለዓም ሲጽፍ “መናገር የማትችል አህያ እንደ ሰው ተናግራ የነቢዩን የእብደት አካሄድ ለመግታት ሞከረች” ብሏል። ሐዋርያው ስለ በለዓም እብደት ለመግለጽ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ፓራፍሮኒያ ሲሆን ቃሉ “አእምሮን መሳት” የሚል ትርጉም ያስተላልፋል።—2ጴጥ 2:15, 16፤ ዘኁ 22:26-31
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የዘኍልቍ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
22:20-22—ይሖዋ በበለዓም ላይ የተቆጣው ለምን ነበር? ይሖዋ ነቢዩ በለዓም እስራኤላውያንን መርገም እንደሌለበት ነግሮት ነበር። (ዘኍልቍ 22:12) ሆኖም ነቢዩ እስራኤላውያንን ለመርገም በማሰብ ባላቅ ከላካቸው ሰዎች ጋር ሄደ። በለዓም የሞዓባውያኑን ንጉሥ ለማስደሰትና በምላሹ ጥቅም ለማግኘት ፈልጎ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:15, 16፤ ይሁዳ 11) በለዓም እስራኤላውያንን ከመርገም ይልቅ ለመመረቅ ቢገደድም እንኳ የንጉሡን ሞገስ ለማግኘት ሲል በዓል አምላኪ የሆኑት ሴቶች የእስራኤልን ወንዶች እንዲያስቱ ሐሳብ አቀረበ። (ዘኍልቍ 31:15, 16) አምላክ በበለዓም ላይ የተቆጣው ስለራሱ ጥቅም ብቻ የሚያስብ ስግብግብ በመሆኑ ነበር።
ከሚያዝያ 26–ግንቦት 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘኁልቁ 25–26
“አንድ ሰው ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?”
“ከፆታ ብልግና ሽሹ!”
ዓሣ አጥማጁ መያዝ የሚፈልገው ዓይነት ዓሣ ወደሚገኝበት ቦታ ሄዷል። ዓሣውን ሊስበው የሚችል ምግብ መንጠቆው ጫፍ ላይ ካደረገ በኋላ ማጥመጃውን ውኃው ውስጥ አስገባው። ከዚያም በትዕግሥት መጠበቅ ጀመረ፤ ዓሣው መንጠቆው ላይ ያለውን ምግብ ሲጎርሰው አጥማጁ ዓሣውን በፍጥነት ጎትቶ አወጣው።
2 እንዲህ ዓይነቱ ዘዴ ሰዎችን ለማጥመድም ሊሠራበት ይችላል። እስራኤላውያን ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በጣም ተቃርበው ሳለ በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፍረው ነበር። በዚህ ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ፣ በለዓም የተባለውን ሰው ካስጠራ በኋላ እስራኤላውያንን ከረገመለት ብዙ ገንዘብ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። በለዓም እስራኤላውያንን መርገም ባይችልም ሕዝቡ በራሳቸው ላይ እርግማን እንዲያመጡ ማድረግ የሚችልበት መንገድ አዘጋጀ። በለዓም ሕዝቡን ለማታለል የሚያስችለው ወጥመድ የመረጠው በደንብ አስቦበት ነው። የእስራኤልን ወንዶች ለማሳሳት ሲል ወጣት ሞዓባውያን ሴቶችን ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ላከ።—ዘኁልቁ 22:1-7፤ 31:15, 16፤ ራእይ 2:14
“ከፆታ ብልግና ሽሹ!”
4 በርካታ እስራኤላውያን በለዓም ባዘጋጀው ወጥመድ የወደቁት ለምንድን ነው? የራሳቸውን ፍላጎት ስለማርካት ብቻ ስላሰቡ ነው፤ ይሖዋ ያደረገላቸውን ነገሮች ሁሉ ረስተው ነበር። እስራኤላውያን ለአምላክ ታማኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሷቸው ብዙ ምክንያቶች ነበሯቸው። አምላክ ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል እንዲሁም በምድረ በዳ እያሉ ተንከባክቧቸዋል፤ በተጨማሪም አንዳች ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበዋል። (ዕብራውያን 3:12) ያም ሆኖ በፆታ ብልግና ተሸነፉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከእነሱ አንዳንዶቹ የፆታ ብልግና እንደፈጸሙ እኛም የፆታ ብልግና አንፈጽም’ ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 10:8
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 359 አን. 1-2
ወሰን
ምድሪቱ ለነገዶቹ የተከፋፈለችው ሁለት ነገሮችን መሠረት በማድረግ ይመስላል፦ ዕጣና የነገዶቹ ትልቅነት። በዕጣ የሚወሰነው ለየነገዱ የሚሰጠው ርስት የሚገኝበት አካባቢ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ በስተ ሰሜን፣ በስተ ደቡብ፣ በስተ ምሥራቅ፣ በስተ ምዕራብ፣ በባሕር ዳርቻ ወይም በተራራማ አካባቢ የሚለው የሚወሰነው በዕጣ ሊሆን ይችላል። የዕጣው ውሳኔ የሚተላለፈው ከይሖዋ መሆኑ በነገዶቹ መካከል ቅናት ወይም ክርክር እንዳይኖር ያደርጋል። (ምሳሌ 16:33) በዚህ መንገድ አምላክ እያንዳንዱ ነገድ የሚደርሰው ርስት፣ ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት በመንፈስ ተመርቶ ከተናገረው በዘፍጥረት 49:1-33 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር የሚስማማ እንዲሆን ለማድረግ ሁኔታዎችን ተቆጣጥሯል።
ለአንድ ነገድ የሚደርሰው ርስት የሚገኝበት አካባቢ በዕጣ ከተወሰነ በኋላ የርስቱ ስፋት መወሰን ይኖርበታል፤ ይህ የሚደረገው ሁለተኛውን ነገር ይኸውም የነገዱን ትልቅነት መሠረት በማድረግ ነው። “ምድሪቱንም በየቤተሰባችሁ ውርስ አድርጋችሁ በዕጣ ተከፋፈሉ። ተለቅ ላለው ቡድን በዛ ያለውን፣ አነስ ላለው ቡድን ደግሞ አነስ ያለውን ውርስ አድርጋችሁ ስጡት። ሁሉም በወጣለት ዕጣ መሠረት የተሰጠውን ቦታ ይወርሳል።” (ዘኁ 33:54) ርስቱ የሚገኝበት አካባቢ በዕጣው መሠረት የሚጸና ቢሆንም የርስቱ ስፋት ማስተካከያ ሊደረግበት ይችላል። ለምሳሌ ለይሁዳ ነገድ የተሰጠው ርስት በጣም ብዙ ስለነበር የተወሰነው ክፍል ተቀንሶ ለስምዖን ነገድ ተሰጥቶ ነበር።—ኢያሱ 19:9