ጥናት 12
ወዳጃዊ ስሜትና አሳቢነት ማሳየት
1 ተሰሎንቄ 2:7, 8
ፍሬ ሐሳብ፦ አድማጮችህን እንደምትወዳቸውና እንደምታስብላቸው በሚያሳይ መንገድ ተናገር።
ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ስለ አድማጮችህ አስብ። አድማጮችህ ምን ዓይነት ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ከግምት ማስገባትህ ከልብ እንድታስብላቸው ያደርግሃል። ካሉባቸው ችግሮች ጋር በተያያዘ ምን እንደሚሰማቸው ለመገመት ሞክር።
የምትጠቀምባቸውን ቃላት በጥንቃቄ ምረጥ። አድማጮችህን በሚያጽናና፣ በሚያበረታታ እንዲሁም መንፈሳቸውን በሚያድስ መንገድ ለመናገር ጥረት አድርግ። አድማጮችህን ቅር የሚያሰኝ ነገር ላለመናገር ተጠንቀቅ፤ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችንም ሆነ የሚያምኑባቸውን ነገሮች ከመንቀፍም መቆጠብ ይኖርብሃል።
አሳቢነት አሳያቸው። ደግነት የሚንጸባረቅበት የድምፅ ቃና እንዲሁም ተስማሚ የሆኑ አካላዊ መግለጫዎች ለአድማጮችህ ከልብ እንደምታስብላቸው ያሳያሉ። ፊትህ ላይ የሚንጸባረቀው ስሜት፣ የሚያስተላልፈው መልእክት እንዳለ አስታውስ፤ ፈገግታ አይለይህ።