የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች፣ ኅዳር 2021-ጥር 2022
ከኅዳር 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 18–19
“ይሖዋ ምድሪቱን ያከፋፈለበት ጥበብ የሚንጸባረቅበት መንገድ”፦
it-1 359 አን. 1
ወሰን
ምድሪቱ ለነገዶቹ የተከፋፈለችው ሁለት ነገሮችን መሠረት በማድረግ ይመስላል፦ ዕጣና የነገዶቹ ትልቅነት። በዕጣ የሚወሰነው ለየነገዱ የሚሰጠው ርስት የሚገኝበት አካባቢ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ በስተ ሰሜን፣ በስተ ደቡብ፣ በስተ ምሥራቅ፣ በስተ ምዕራብ፣ በባሕር ዳርቻ ወይም በተራራማ አካባቢ የሚለው የሚወሰነው በዕጣ ሊሆን ይችላል። የዕጣው ውሳኔ የሚተላለፈው ከይሖዋ መሆኑ በነገዶቹ መካከል ቅናት ወይም ክርክር እንዳይኖር ያደርጋል። (ምሳሌ 16:33) በዚህ መንገድ አምላክ እያንዳንዱ ነገድ የሚደርሰው ርስት፣ ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት በመንፈስ ተመርቶ ከተናገረው በዘፍጥረት 49:1-33 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር የሚስማማ እንዲሆን ለማድረግ ሁኔታዎችን ተቆጣጥሯል።
it-1 1200 አን. 1
ውርስ
በውርስ የሚተላለፍ ርስት። ለእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን ውርስ አድርጎ የሰጣቸው ይሖዋ ነው፤ ይሖዋ በሙሴ በኩል የምድሪቱን ወሰን ነግሯቸዋል። (ዘኁ 34:1-12፤ ኢያሱ 1:4) የጋድ ልጆች፣ የሮቤል ልጆችና የምናሴ ነገድ እኩሌታ የሚወርሱትን መሬት በዕጣ ያከፋፈላቸው ሙሴ ነው። (ዘኁ 32:33፤ ኢያሱ 14:3) ለቀሩት ነገዶች በዕጣ ርስት ያከፋፈሉት ኢያሱና አልዓዛር ናቸው። (ኢያሱ 14:1, 2) ያዕቆብ በዘፍጥረት 49:5, 7 ላይ በተናገረው ትንቢት መሠረት ለስምዖንና ለሌዊ የተለየ መሬት ርስት ተደርጎ አልተሰጣቸውም። ለስምዖን የተሰጠው ክልል፣ በይሁዳ ክልል ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን (እና የተከለሉ ከተሞችን) የሚያካትት ነበር (ኢያሱ 19:1-9)፤ ለሌዊ የተሰጠው ደግሞ በመላው የእስራኤል ምድር የሚገኙ 48 ከተሞች ናቸው። ሌዋውያን በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ልዩ የአገልግሎት መብት ተሰጥቷቸዋል፤ ስለዚህ ውርሻቸው ይሖዋ እንደሆነ ተገልጿል። እስራኤላውያን የሚያመጡት አሥራት ለሌዋውያኑ እንደ ድርሻ ወይም ውርሻ ነበር። (ዘኁ 18:20, 21፤ 35:6, 7) ቤተሰቦች ለነገዳቸው ከተሰጠው መሬት ላይ ተቆርሶ ይሰጣቸዋል። የቤተሰቦች ቁጥር ሲጨምርና ልጆች ውርስ ሲረከቡ ያው መሬት እየተሸነሸነ ይከፋፈላል።
it-1 359 አን. 2
ወሰን
ለአንድ ነገድ የሚደርሰው ርስት የሚገኝበት አካባቢ በዕጣ ከተወሰነ በኋላ የርስቱ ስፋት መወሰን ይኖርበታል፤ ይህ የሚደረገው ሁለተኛውን ነገር ይኸውም የነገዱን ትልቅነት መሠረት በማድረግ ነው። “ምድሪቱንም በየቤተሰባችሁ ውርስ አድርጋችሁ በዕጣ ተከፋፈሉ። ተለቅ ላለው ቡድን በዛ ያለውን፣ አነስ ላለው ቡድን ደግሞ አነስ ያለውን ውርስ አድርጋችሁ ስጡት። ሁሉም በወጣለት ዕጣ መሠረት የተሰጠውን ቦታ ይወርሳል።” (ዘኁ 33:54) ርስቱ የሚገኝበት አካባቢ በዕጣው መሠረት የሚጸና ቢሆንም የርስቱ ስፋት ማስተካከያ ሊደረግበት ይችላል። ለምሳሌ ለይሁዳ ነገድ የተሰጠው ርስት በጣም ብዙ ስለነበር የተወሰነው ክፍል ተቀንሶ ለስምዖን ነገድ ተሰጥቶ ነበር።—ኢያሱ 19:9
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 359 አን. 5
ወሰን
ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለው መሬት ስለተከፋፈለበት መንገድ የሚገልጸው ዘገባ እንደሚያሳየው መጀመሪያ ላይ በዕጣ መሬት የተሰጣቸው ይሁዳ (ኢያሱ 15:1-63)፣ ዮሴፍ (ኤፍሬም) (ኢያሱ 16:1-10) እና ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ የሰፈሩት የምናሴ ነገድ እኩሌታ ናቸው (ኢያሱ 17:1-13)፤ ወሰናቸውና የሚወርሷቸው ከተሞች በዝርዝር ተነገሯቸው። ይህ ከሆነ በኋላ መሬት የማከፋፈሉ ሥራ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ተቋርጦ የነበረ ይመስላል፤ ምክንያቱም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ከጊልጋል ተነስቶ በሴሎ ሰፍሮ እንደነበር የሚገልጽ ዘገባ እናገኛለን። (ኢያሱ 14:6፤ 18:1) መሬት የማከፋፈሉ ሥራ ተቋርጦ የቆየው ምን ያህል ጊዜ እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም፤ የሆነው ሆኖ ከጊዜ በኋላ ኢያሱ፣ ቀሪውን የምድሪቱን ክፍል ለመውረስ የቸልተኝነት መንፈስ በማሳየታቸው የቀሩትን ሰባት ነገዶች ወቅሷቸዋል። (ኢያሱ 18:2, 3) የቀሩት ሰባት ነገዶች እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ለማሳየት ምክንያት የሆናቸውን ነገር በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። አንዳንድ ተንታኞች እንደሚያስረዱት ከሆነ እስራኤላውያን ብዙ ምርኮ ማግኘታቸውና ከነአናውያን ጥቃት ይሰነዝሩብናል ከሚለው ስጋት ነፃ መሆናቸው የቀረውን ምድር ለመውረስ መጣደፍ እንደማያስፈልጋቸው እንዲሰማቸው አድርጎ ሊሆን ይችላል። ወደኋላ እንዲሉ ያደረጋቸው ሌላው ነገር ደግሞ እዚያም እዚህም በጠላት ቁጥጥር ሥር ያሉ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ሲሉ መዋጋቱን ስላልፈለጉ ሊሆን ይችላል። (ኢያሱ 13:1-7) በተጨማሪም እስካሁን ከወረሱት ክልል አንጻር ይህን የተስፋይቱን ምድር ክፍል ያን ያህል አያውቁት ይሆናል።
ከኅዳር 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 20–22
“በአንድ ወቅት ከተፈጠረው አለመግባባት የምናገኘው ትምህርት”
ከትዳር ጓደኛህ ጋር በግልጽ ለመነጋገር የሚረዱ ነጥቦች
በግልጽ መነጋገር አለመግባባት እንዳይፈጠር ከማድረጉም በላይ ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ይጠብቃል። የጥንት እስራኤላውያን ታሪክ እንደሚያሳየው ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ይኖሩ የነበሩት የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ “ግዙፍ መሠዊያ” ሠርተው ነበር። ሌሎቹ ነገዶች ድርጊታቸውን በተሳሳተ መንገድ ተረዱት። በምዕራቡ በኩል ያሉት ነገዶች፣ በዮርዳኖስ ማዶ ያሉት ወንድሞቻቸው የክህደት እርምጃ እንደወሰዱ በማሰብ “ዐመፀኞቹን” ለመውጋት ተዘጋጁ። ሆኖም ወደ ውጊያው ከመዝመታቸው በፊት በስተ ምሥራቅ በኩል የሚገኙትን ነገዶች ለማነጋገር ተወካዮችን ላኩ። ይህ እንዴት ያለ የጥበብ ድርጊት ነበር! መልእክተኞቹ መሠዊያው ከይሖዋ ሕግ ጋር የሚጋጭ የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ የሚያገለግል አለመሆኑን ተገነዘቡ። ከዚህ ይልቅ በስተ ምሥራቅ ያሉት ነገዶች፣ ወደፊት ሌሎቹ ነገዶች “ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም” እንዳይሏቸው በመፍራት የሠሩት መሠዊያ ሲሆን ይህ ደግሞ እነርሱም የይሖዋ አምላኪዎች እንደሆኑ የሚያሳይ ምሥክር ነበር። (ኢያሱ 22:10-29) መሠዊያው፣ ይሖዋ ለእነሱ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ስለሚያሳውቅ ምሥክር ብለው ጠሩት።—ኢያሱ 22:34
‘ሰላም የሚገኝበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ’
አንዳንድ እስራኤላውያን ጥፋት ለመሠራቱ በቂ ማስረጃ እንዳለና ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘር ደግሞ ከራሳቸው ወገን ብዙ ሰው እንዳይሞት እንደሚያስችል አስበው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉት ነገዶች የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ከወንድሞቻቸው ጋር ለመወያየት ልዑካን ላኩ። እነሱም “በእስራኤል አምላክ ላይ እንዲህ ያለ ክህደት የፈጸማችሁት ለምንድን ነው? እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ከመከተልስ እንዴት ወደ ኋላ ትላላችሁ?” ሲሉ ጠየቋቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መሠዊያውን የገነቡት ነገዶች ክህደት መፈጸማቸው አልነበረም። ይሁንና ለቀረበባቸው ክስ ምን ምላሽ ይሰጡ ይሆን? ክስ ባቀረቡባቸው ሰዎች ላይ ኃይለ ቃል ይናገሩ ወይም እነሱን ለማነጋገር እምቢ ይሉ ይሆን? ክስ የተሰነዘረባቸው ነገዶች መሠዊያውን የሠሩት ይሖዋን ለማገልገል ካላቸው ፍላጎት በመነሳሳት እንደሆነ በግልጽ በማስረዳት በገርነት መንፈስ ምላሽ ሰጡ። የሰጡት ምላሽ ከአምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዳይበላሽ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ አስችሏል። በረጋ መንፈስ መወያየታቸው ችግሩ እልባት እንዲያገኝና ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል።—ኢያሱ 22:13-34
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 402 አን. 3
ከነአን
ከእስራኤላውያን የጦርነት ግስጋሴ የተረፉና በእነሱ ቁጥጥር ስር ያልወደቁ ብዙ ከነአናውያን ቢኖሩም ይሖዋ ለእስራኤላውያን “ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማለላቸውን ምድር በሙሉ” ሰጥቷቸዋል እንዲሁም “በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ እረፍት” ሰጥቷቸዋል ቢባል ስህተት አይደለም፤ “ይሖዋ ለእስራኤል ቤት ከገባው መልካም ቃል ሁሉ ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም፤ ሁሉም ተፈጽሟል።” (ኢያሱ 21:43-45) በእስራኤላውያን ዙሪያ ያሉት ጠላት ሕዝቦች በፍርሃት ተሽመድምደው ስለነበር ለእስራኤላውያን ደህንነት ስጋት የሚፈጥር ምንም ዓይነት አቅም አልነበራቸውም። ቀደም ሲል አምላክ ከነአናውያንን የሚያስወጣቸው “ጥቂት በጥቂት” እንደሆነ ተናግሮ ነበር፤ ይህን ያደረገው ባድማ በሆነው ምድር ላይ የዱር አራዊት እንዳይበዙ ነው። (ዘፀ 23:29, 30፤ ዘዳ 7:22) እርግጥ ነው፣ ከነአናውያን የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው የጦር ሠረገሎችን ጨምሮ ከእስራኤላውያን የተሻለ የጦር መሣሪያ ነበራቸው፤ ይሁንና እስራኤላውያን አንዳንድ አካባቢዎችን መቆጣጠር ያልቻሉት ይሖዋ ቃሉን መጠበቅ ስላቃተው አይደለም። (ኢያሱ 17:16-18፤ መሳ 4:13) ከዚህ ይልቅ ዘገባው እንደሚጠቁመው፣ እስራኤላውያን አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሽንፈት የደረሰባቸው ባለመታዘዛቸው ነው።—ዘኁ 14:44, 45፤ ኢያሱ 7:1-12
ከኅዳር 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 23–24
“ኢያሱ ለብሔሩ የሰጠው የመጨረሻ ማሳሰቢያ”
it-1 75
ጥምረት
እስራኤላውያን ወደ ከነአን ማለትም ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ሉዓላዊው አምላክ፣ ለቀድሞ አባቶቻቸው በገባው ቃል መሠረት ለእስራኤላውያን በምድሪቱ ላይ የመኖር ሙሉ መብት ሰጥቷቸዋል። ስለዚህ ወደ ምድሪቱ የገቡት የባዕድ አገር ሰዎች ሆነው አይደለም፤ እንዲሁም ይሖዋ ምድሪቱ ላይ ከሚኖሩት አረማውያን ብሔራት ጋር ጥምረት እንዳይፈጥሩ ከልክሏቸዋል። (ዘፀ 23:31-33፤ 34:11-16) መታዘዝ የሚጠበቅባቸው የአምላክን ሕጎችና ደንቦች ብቻ ነው፤ ይሖዋ ከምድሪቱ እንዲባረሩ የወሰነባቸውን ብሔራት ደንቦች መከተል አይጠበቅባቸውም ነበር። (ዘሌ 18:3, 4፤ 20:22-24) አምላክ በተለይ ከእነዚህ ብሔራት ጋር በጋብቻ እንዳይጣመሩ አስጠንቅቋቸዋል። እንዲህ ያለው ጥምረት አረማዊ ከሆኑት ሚስቶቻቸው ብቻ ሳይሆን አረማዊ ከሆኑ ዘመዶቻቸው ጋር ያቀራርባቸዋል እንዲሁም እነሱ ለሚከተሏቸው የሐሰት ሃይማኖታዊ ልማዶች ያጋልጣቸዋል፤ ይህ ደግሞ ክህደት እንዲፈጽሙ በማድረግ ወጥመድ ይሆንባቸዋል።—ዘዳ 7:2-4፤ ዘፀ 34:16፤ ኢያሱ 23:12, 13
የይሖዋ ቃል ምንጊዜም ይፈጸማል
19 በእርግጥም እኛ ራሳችን ከተመለከትናቸው ነገሮች አንጻር እንዲህ ማለት እንችላለን:- “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ . . . ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 23:14) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹን ነጻ ያወጣቸዋል፣ ጥበቃ ያደርግላቸዋል እንዲሁም ይንከባከባቸዋል። ይሖዋ በቀጠረው ጊዜ ሳይፈጽመው የቀረ ተስፋ ልትጠቅስ ትችላለህ? በፍጹም አትችልም። በመሆኑም አስተማማኝ በሆነው የአምላክ ቃል ላይ ሙሉ እምነት ማሳደራችን አስተዋይነት ነው።
20 ስለ ወደፊቱ ጊዜስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ፣ አብዛኞቻችን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንደምንኖር ተስፋ ሰጥቶናል። ከመካከላችን ጥቂቶች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ አላቸው። ተስፋችን ምንም ይሁን ምን እንደ ኢያሱ ታማኝ ሆነን ለመኖር የሚያበቃ ምክንያት አለን። ተስፋችን እውን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። ያን ጊዜ ይሖዋ የሰጠንን ተስፋዎች መለስ ብለን በማሰብ እኛም “አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል” እንላለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኢያሱ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
24:2—የአብርሃም አባት ታራ ጣዖት አምላኪ ነበር? ታራ በመጀመሪያ ይሖዋን አያመልክም ነበር። ሲን የተባለው የዑር ከተማ ተወዳጅ የጨረቃ አምላክ አምላኪ የነበረ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የአይሁዳውያን አፈ ታሪክ እንደሚገልጸው ታራ ጣዖት ሠሪ ሳይሆን አይቀርም። ነገር ግን አብርሃም በአምላክ ትእዛዝ ዑርን ለቅቆ ሲወጣ ታራ ወደ ካራን አብሮት ተጉዟል።—ዘፍጥረት 11:31
ከኅዳር 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 1–3
“በድፍረትና በብልሃት ጀብዱ የፈጸመው ሰው ታሪክ”
ናዖድ የአስገባሪውን ቀንበር ሰበረ
ናዖድ እቅዱ ሊሰምርለት የቻለው የረቀቀ ጥበብ በመጠቀሙ ወይም ደግሞ የጠላት ወገን ድክመት በማሳየቱ አይደለም። የአምላክ ዓላማ ፍጻሜውን ማግኘቱ በሰዎች ላይ የተመካ አይደለም። ናዖድ ስኬት እንዲያገኝ ያስቻለው ዋናው ነገር መለኮታዊ ድጋፍ ማግኘቱ ነው። ምንም ነገር ሊያግደው ከማይችለው ይሖዋ ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት ካለው ፈቃድ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰዱ የእርሱን ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል። ናዖድን ያስነሳው አምላክ ከመሆኑም በላይ ‘መሳፍንትን ለሕዝቦቹ ባስነሣላቸው ቁጥር ከመስፍኑ ጋር ይሆን’ ነበር።—መሳፍንት 2:18፤ 3:15
ናዖድ የአስገባሪውን ቀንበር ሰበረ
ናዖድ በመጀመሪያ ደረጃ በልብሱ ውስጥ ሊደብቀው የሚችል በሁለቱም በኩል ስለታም የሆነ አጠር ያለ ‘ሰይፍ አዘጋጀ።’ ፍተሻ ሊኖር እንደሚችል ሳይጠብቅ አልቀረም። በቀኝ እጃቸው የሚዋጉ ሰዎች ሰይፋቸውን በፍጥነት መምዘዝ እንዲችሉ የሚታጠቁት በግራ በኩል ነበር። ናዖድ ግራኝ በመሆኑ ሰይፉን “በልብሱ ውስጥ በቀኝ ጭኑ” በኩል የደበቀው ሲሆን የንጉሡ ጠባቂዎች በዚያ በኩል ይፈትሻሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። በመሆኑም ምንም ዓይነት ችግር ሳያጋጥመው “ግብሩን . . . ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን አቀረበ።”—መሳፍንት 3:16, 17
ናዖድ ወደ ዔግሎን ቤተ መንግሥት እንደገባ ምን ነገሮች እንደተከናወኑ በዝርዝር አልተገለጸም። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሠፍሮ የምናገኘው “ናዖድም ግብሩን ካቀረበ በኋላ፣ ግብር ተሸክመው የመጡት ሰዎች ተመልሰው እንዲሄዱ አደረገ” የሚል አጭር መግለጫ ብቻ ነው። (መሳፍንት 3:18) ናዖድ ግብሩን ካቀረበና ዕቃውን ተሸክመው የመጡትን ሰዎች ከዔግሎን ቤተ መንግሥት ራቅ ወዳለ አካባቢ ወስዶ ካሰናበታቸው በኋላ ተመልሶ መጣ። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? እነዚህን ሰዎች ይዟቸው የመጣው ጥበቃ እንዲያደርጉለት ነው? ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲገባ ማሟላት ያለበት ግዴታ ስለሆነ ነው? ወይስ ግብሩን ተሸክመው እንዲያደርሱለት ብቻ ብሎ ነው? ደግሞስ እቅዱን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ለደኅንነታቸው በማሰብ ከአካባቢው ርቀው እንዲሄዱ ፈልጎ ይሆን? ናዖድ ሰዎቹን ያሰናበተበት ምክንያት የትኛውም ቢሆን ብቻውን ወደ ቤተ መንግሥቱ በድፍረት ተመልሷል።
“[ናዖድ] ጌልጌላ አጠገብ ድንጋዮች ተጠርበው ከሚወጡበት አካባቢ ሲደርስ ወደ ኋላ በመመለስ ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ ‘ንጉሥ ሆይ፤ በምስጢር የምነግርህ ነገር አለኝ’ አለው።” ዔግሎን ፊት እንደገና ሊቀርብ የቻለው እንዴት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ጠባቂዎቹ ጥርጣሬ ሊያድርባቸው አይገባም ነበር? አንድ እስራኤላዊ ብቻውን በንጉሣቸው ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት የለም ብለው አስበው ይሆን? ናዖድ ብቻውን መመለሱ የአገሩን ሰዎች ከድቷል የሚል ግምት አሳድሮ ይሆን? ያም ሆነ ይህ ናዖድ ንጉሡን ለብቻው ማነጋገር ፈልጓል፤ አጋጣሚውም ተፈቅዶለታል።—መሳፍንት 3:19
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የመሳፍንት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
2:10-12፦ የይሖዋን ‘ውለታ እንዳንረሳ’ መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናበት ቋሚ ፕሮግራም ሊኖረን ይገባል። (መዝሙር 103:2) ወላጆች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ የአምላክን ቃል እውነት መትከል ይገባቸዋል።—ዘዳግም 6:6-9
ከኅዳር 29–ታኅሣሥ 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 4–5
“ይሖዋ ሁለት ሴቶችን ተጠቅሞ ሕዝቡን አዳነ”
“እኔ በእስራኤል እናት ሆኜ እስክነሳ”
ሲሳራ! ስሙ ብቻ እንኳ ሲጠራ በእስራኤል ውስጥ ሽብር ይነግሣል። የከነአናውያን ሃይማኖትና ባሕል በጭካኔ ድርጊት የተሞላ ሲሆን ልጆችን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብንና በቤተ መቅደስ ውስጥ ዝሙት መፈጸምን ይጨምር ነበር። ከነአናዊ የሆነ የጦር አዛዥና ሠራዊቱ የእስራኤልን ምድር ማስተዳደሩ በሕዝቡ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር? በምድሪቱ ላይ እንደ ልብ መዘዋወር አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ መንደሮቹ ሁሉ ጭር ብለው እንደነበር ዲቦራ ካቀናበረችው መዝሙር መረዳት ይቻላል። (መሳፍንት 5:6, 7) ሰዎች በግብርና ሥራ መሰማራትም ሆነ ቅጥር በሌላቸው መንደሮች ውስጥ መኖር በመፍራት በየጥሻውና በየኮረብታው ውስጥ ተሸሽገው ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ጥቃት ሊሰነዘርብን፣ ልጆቻችንን ልንነጠቅ እንዲሁም ሴቶቻችን ሊደፈሩ ይችላሉ በሚል ስጋት በጎዳናዎች ላይ እንደ ልብ ከመጓዝ ተቆጥበው እንደሚሆን መገመት እንችላለን።
“እኔ በእስራኤል እናት ሆኜ እስክነሳ”
ይሖዋ አንገተ ደንዳና የነበሩት ሕዝቦቹ ለመለወጥ ፈቃደኞች መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እስኪያገኝ ድረስ ወይም “እኔ ዲቦራ እስክነሳ ድረስ፣ እኔ በእስራኤል እናት ሆኜ እስክነሳ ድረስ” የሚለው ዲቦራና ባርቅ የዘመሩት በመንፈስ መሪነት የተጻፈው መዝሙር እስኪፈጸም ድረስ ለ20 ዓመት በእስራኤል ውስጥ ሽብር ነግሦ ነበር። የላጲዶት ሚስት የነበረችው ዲቦራ ቃል በቃል የልጆች እናት የነበረች ትሁን አትሁን የምናውቀው ነገር የለም፤ ይሁንና ይህ አባባል የተሠራበት በምሳሌያዊ ሁኔታ ነው። ይሖዋ፣ ዲቦራ እንደ እናት ሆና ብሔሩን እንድትታደግ ኃላፊነት የሰጣት ያህል ነው። ደፋር የእምነት ሰው የሆነውን መስፍኑን ባርቅን ጠርታ በሲሳራ ላይ እንዲዘምት መመሪያ እንድትሰጠው ይሖዋ ተልእኮ ሰጥቷት ነበር።—መሳፍንት 4:3, 6, 7፤ 5:7
“እኔ በእስራኤል እናት ሆኜ እስክነሳ”
ኢያዔል ምን እርምጃ እንደምትወስድ በፍጥነት መወሰን ነበረባት። እሷም ሲሳራ ገብቶ አረፍ እንዲል ጋበዘችው። ማንም ሰው እሱን ፈልጎ ቢመጣ እዚያ መኖሩን እንዳትናገር አዘዛት። ጋደም ሲል ብርድ ልብስ አለበሰችው፤ የሚጠጣ ውኃ ሲጠይቃትም ወተት ሰጠችው። ወዲያው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደው። ከዚያም ኢያዔል በድንኳን የሚኖሩ ሴቶች አዘውትረው የሚጠቀሙባቸውን ሁለት መሣሪያዎች ይኸውም ካስማና መዶሻ ይዛ መጣች። ራስጌው አጠገብ በርከክ ብላ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ በመሆን አስፈሪ እርምጃ ልትወስድ ነው። በዚህ ጊዜ ለቅጽበት እንኳ ብታመነታ ወይም ፈራ ተባ ብትል ከባድ መዘዝ ሊያስከትልባት ይችላል። ታዲያ ይህን እርምጃ የወሰደችው ይህ ሰው ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስላደረሰው ጭቆና አስባ ይሆን? ወይስ ከይሖዋ ጎን መቆም ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ አስባ? ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚለው ነገር የለም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ወዲያውኑ እርምጃ መውሰዷንና ሲሳራ መገደሉን ነው!—መሳፍንት 4:18-21፤ 5:24-27
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የመሳፍንት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
5:20—ከዋክብት ከሰማይ ሆነው ለባርቅ የተዋጉለት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሁኔታ ባርቅ መላእክታዊ ድጋፍ እንዳገኘ ወይም የሲሣራ ጠቢባን እንዳሰቡት መጥፎ ገድን የሚያመለክት የተወርዋሪ አካላት ናዳ እንደነበረ አሊያም ሲሣራ የታመነባቸው የኮከብ ቆጠራ ትንበያዎች ከንቱ ሆነው እንደቀሩ እንደሚያመለክት በግልጽ አይነግረንም። ይሁን እንጂ አምላክ በሆነ መንገድ ጣልቃ ገብቶ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።
ከታኅሣሥ 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 6–7
“በል ባለህ ኃይል ሂድ”
ከአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥቅም ማግኘት ትችላለህ
ከጥንቶቹ ዕብራውያን መሳፍንት አንዱ የሆነው ጌዴዎን ስለ ራሱ ጤናማ አመለካከትና ያልተጋነነ ግምት የነበረው ሰው ነው። የእስራኤል መሪ ለመሆን አልፈለገም። ይሁን እንጂ ጌዴዎን መሪ እንዲሆን በተመረጠ ጊዜ ለቦታው እንደሚበቃ ሆኖ አልተሰማውም። “ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ” በማለት መለሰ።—መሳፍንት 6:12-16
‘የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ’
በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ከፍተኛ ሽብር ውስጥ የሚከት ሁኔታ ገጠማቸው! በድንገት 300 ማሰሮዎች ሲሰባበሩ የሚያሰሙት ድምፅ፣ ከ300 ቀንደ መለከቶች የሚወጣው ጩኸት እንዲሁም የ300 ሰዎች ሁካታ ሰፍኖ የነበረውን ፀጥታ ሰበረው። በተለይ ምድያማውያን ‘የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ’ በሚለው ድምፅ በመደናገጣቸው ያሰሙት ጩኸት ሁካታውን አባባሰው። የተፈጠረው ትርምስ ጠላትን ከወዳጅ መለየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። አምላክ የጠላት ሠራዊት በሰይፍ እርስ በርሱ እንዲጨራረስ ሲያደርግ እነዚህ 300 ሰዎች ከተመደቡበት ቦታ ንቅንቅ አላሉም። ከዚያም ሠራዊቱ ደንግጦ እንዲሸሽ በማድረግ፣ ማምለጫ ቀዳዳ በማሳጣት እንዲሁም ያመለጡትን አሳድዶ በመማረክና በመግደል የምድያማውያንን ጥቃት ለዘለቄታው አስወገዱ። ለረጅም ጊዜ የቆየው የጭቆና አገዛዝ በዚህ ሁኔታ ተደመደመ።—መሳፍንት 7:19-25፤ 8:10-12, 28
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የመሳፍንት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
6:25-27፦ ጌዴዎን ሳያስፈልግ ተቃዋሚዎቹን ላለማስቆጣት ጥንቃቄ አድርጓል። እኛም ምሥራቹን በምንሰብክበት ጊዜ ሌሎችን በአነጋገራችን እንዳናስቀይም መጠንቀቅ ይገባናል።
ከታኅሣሥ 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 8–9
“የቱ ይሻላል? ትሕትና ወይስ ኩራት?”
አለመግባባቶችን የምትፈቱት እንዴት ነው?
ከምድያማውያን ጋር በከባድ ሁኔታ በመዋጋት ላይ የነበረው ጌዴዎን የኤፍሬም ነገድ እንዲረዳው ጠየቀ። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ኤፍሬማውያን ወደ ጌዴዎን በመምጣት በፍልሚያው መጀመሪያ ላይ ለምን አልጠራኸንም በማለት አምርረው ተናገሩ። ታሪኩ “ጽኑ ጥልም ተጣሉት” ይላል። ጌዴዎንም እንዲህ ሲል መለሰ:- “እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችሁት አይበልጥምን? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዝር ወይን መከር አይሻልምን? እግዚአብሔር የምድያምን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፤ እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖሮአል?” (መሳፍንት 8:1-3) ጌዴዎን በጥሩ ሁኔታ መርጦ በተናገራቸው የሚያረጋጉ ቃላት አማካኝነት ሊቀሰቀስ የነበረውን አሰቃቂ የጎሳ ግጭት አስቀርቷል። ምናልባትም እነዚያ የኤፍሬም ነገድ አባላት ራሳቸውን በጣም ተፈላጊ አድርገው የመመልከት ወይም የኩራት ችግር የነበረባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ጌዴዎንን ሰላማዊ መፍትሄ ለማግኘት ከመጣር ወደ ኋላ እንዲል አላደረገውም። እኛስ እንዲህ ማድረግ እንችላለን?
ልክን ማወቅ ዛሬም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ጌድዮን ልክን በማወቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። የይሖዋ መልአክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገለጠለት ወቅት ጌድዮን ያን ያህል ቦታ የሚሰጠው ሰው እንዳልሆነና የተሰጠውን ተልእኮ ለመቀበል ብቃት እንደሌለው ተናግሯል። (መሳ. 6:15) ይሖዋ የሰጠውን ኃላፊነት ከተቀበለ በኋላ ደግሞ ሥራው ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በሚገባ ለመረዳት እንዲሁም የይሖዋን አመራር ለማግኘት ጥረት አድርጓል። (መሳ. 6:36-40) ጌድዮን ደፋርና ቆራጥ የነበረ ቢሆንም ማንኛውንም ነገር የሚያከናውነው በጥንቃቄና በማስተዋል ነበር። (መሳ. 6:11, 27) የተሰጠውን ተልእኮ ለራሱ ክብር ለማግኘት አልተጠቀመበትም። ከዚህ ይልቅ ተልእኮውን እንዳጠናቀቀ በደስታ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል።—መሳ. 8:22, 23, 29
በይሖዋ መንገድ ሂድ
9 የአምላክ ወዳጅ ለመሆን ከፈለግን ‘ትሑት’ መሆን አለብን። (1 ጴጥ. 3:8፤ መዝ. 138:6) በመሳፍንት ምዕራፍ 9 ላይ የትሕትናን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ምሳሌ ይገኛል። የጌዴዎን ልጅ የሆነው ኢዮአታም “ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ” ብሏል። በዚህ ምሳሌ ላይ የወይራ ዛፍና በለስ እንዲሁም የወይን ተክል ተጠቅሰዋል። እነዚህ ተክሎች ወንድሞቻቸው በሆኑት በእስራኤላውያን ላይ ለመንገሥ ያልፈለጉትን ብቃት ያላቸው ሰዎች ያመለክታሉ። ከማገዶነት ያለፈ ፋይዳ የሌለው የእሾህ ቍጥቋጦ ግን ኩራተኛውን ንጉሥ አቤሜሌክን ያመለክታል። አቤሜሌክ ሌሎችን የመጨቆን ፍላጎት የነበረው ነፍሰ ገዳይ ሰው ነበር። አቤሜሌክ ‘እስራኤልን ሦስት ዓመት የገዛ’ ቢሆንም ያለ ዕድሜው ሞቷል። (መሳ. 9:8-15, 22, 50-54) በእርግጥም ‘ትሑት’ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 753 አን. 1
ኤፉድ
ጌድዮን ኤፉዱን የሠራው ይሖዋ ለእስራኤል የሰጠውን ድል ለማሰብና አምላክን ለማክበር በቀና ልብ ተነሳስቶ ነበር፤ ሆኖም እስራኤላውያን ኤፉዱን በማምለክ መንፈሳዊ ምንዝር ስለፈጸሙ ኤፉዱ “ለጌድዮንና ለቤተሰቡ ወጥመድ” ሆነባቸው። (መሳ 8:27) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ጌድዮን ራሱ ኤፉዱን እንዳመለከ አይናገርም፤ እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ በቅድመ ክርስትና ዘመን ስለኖሩ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ሲናገር ጌድዮንን በስም ጠቅሶታል።—ዕብ 11:32፤ 12:1
ከታኅሣሥ 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 10–12
“መንፈሳዊ ሰው የሆነው ዮፍታሔ”
በይሖዋ ላይ እምነት ማሳደር የእሱን ሞገስ ያስገኛል
9 እንደ ዮሴፍ ያሉ የእምነት ምሳሌዎችም በዮፍታሔ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድሩ አልቀሩም፤ ዮሴፍ ወንድሞቹ ‘ቢጠሉትም’ ምሕረት አሳይቷቸዋል። (ዘፍ. 37:4፤ 45:4, 5) ዮፍታሔ እንዲህ ያሉ ሰዎች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ፣ ይሖዋን የሚያስደስት እርምጃ እንዲወስድ ረድቶታል። ወንድሞቹ ያደረጉት ነገር በጣም እንደጎዳው ግልጽ ነው፤ ይሁንና ይህ ሁኔታ ይሖዋንና ሕዝቦቹን ከማገልገል ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። (መሳ. 11:9) ዮፍታሔ ከሌሎች ሰዎች ጋር ከተፈጠረው ግጭት ይልቅ ትልቅ ቦታ የሰጠው የይሖዋን ስም ለማስከበር ሲል ለሚያደርገው ውጊያ ነው። ምንጊዜም በይሖዋ ለመታመን ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር፤ ይህ ደግሞ ለእሱም ሆነ ለሌሎች በረከት አምጥቷል።—ዕብ. 11:32, 33
it-2 27 አን. 2
ዮፍታሔ
የተግባር ሰው የሆነው ዮፍታሔ፣ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ ብቃት ካለው አንድ መሪ የሚጠበቀውን ነገር አደረገ። ለአሞን ንጉሥ መልእክት በመላክ የእስራኤልን ምድር በመውረር ጠብ ፈልጎ የመጣው ራሱ አሞን እንደሆነ ተናገረ። የአሞን ንጉሥ፣ ይህ ምድር እስራኤል ቀደም ሲል ከአሞን የወሰደበት መሬት እንደሆነ በመግለጽ መልስ ሰጠ። (መሳ 11:12, 13) ዮፍታሔ በዚህ ጊዜ የሰጠው መልስ እንዲሁ ጀብደኛ ተዋጊ ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ታሪክ በተለይም አምላክ ቀደም ባሉት ጊዜያት ለሕዝቡ ስላደረገው ነገር ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው እንደሆነ አሳይቷል። ጌድዮን፣ የአሞን ንጉሥ ላቀረበው ክስ የሚከተሉትን የመከራከሪያ ሐሳቦች አቀረበ፦ (1) እስራኤል አሞንን፣ ሞዓብንም ሆነ ኤዶምን አልተነኮሰም። (መሳ 11:14-18፤ ዘዳ 2:9, 19, 37፤ 2ዜና 20:10, 11) (2) እስራኤላውያን ምድሪቱን ድል አድርገው በተቆጣጠሩበት ወቅት፣ የይገባኛል ጥያቄ የተነሳበት ይህ መሬት የአሞናውያን አልነበረም፤ በወቅቱ መሬቱ በከነአን ይኖሩ የነበሩት የአሞራውያን የነበረ ሲሆን አምላክ፣ ሲሖን የተባለውን ንጉሣቸውንም ሆነ ምድሩን ለእስራኤላውያን ሰጥቷል። (3) እስራኤል ላለፉት 300 ዓመታት በዚህ መሬት ላይ ሲኖር አሞን የይገባኛል ጥያቄ አንስቶ አያውቅም፤ ታዲያ አሁን ይህን ጥያቄ የሚያነሳበት ምን መሠረት አለው?—መሳ 11:19-27
it-2 27 አን. 3
ዮፍታሔ
ዮፍታሔ ጉዳዩ ከአምልኮ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በመግለጽ መሠረታዊውን ነገር አነሳ። ይሖዋ አምላክ ይህን ምድር ለእስራኤል ርስት አድርጎ እንደሰጠና በዚህም ምክንያት የሐሰት አምላክ ለሚያመልኩ ሰዎች ስንዝር መሬት እንኳ አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ገለጸ። ዮፍታሔ የአሞናውያንን አምላክ ከሞሽ ብሎ ጠርቶታል። አንዳንዶች ይህ ስህተት እንደሆነ ያስባሉ። እርግጥ ነው፣ የአሞናውያን አምላክ ሚልኮም ሲሆን ከሞሽ የሞዓባውያን አምላክ ነው፤ ያም ቢሆን እርስ በርስ የሚዛመዱት እነዚህ ብሔራት የሚያመልኩት አንድ አምላክ ብቻ አልነበረም። ሌላው ቀርቶ ሰለሞን እንኳ በባዕድ አገር ሚስቶቹ የተነሳ የከሞሽን አምልኮ ወደ እስራኤል ምድር አምጥቷል። (መሳ 11:24፤ 1ነገ 11:1, 7, 8, 33፤ 2ነገ 23:13) በተጨማሪም አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ ከሞሽ የሚለው ቃል “አስገባሪ፣ ድል አድራጊ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ምናልባት ዮፍታሔ በዚህ አምላካቸው ላይ ትኩረት ማድረግ የፈለገው አሞናውያን ይህን አምላክ በተመለከተ ሌሎች ሕዝቦችን ‘ገባር እንደሚያደርግላቸው’ ወይም ‘ድል እንደሚያደርግላቸው’ እንዲ ሁም መሬት እንደሚሰጣቸው ስለሚናገሩለት ሊሆን ይችላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 26
ዮፍታሔ
ዮፍታሔ ዲቃላ ልጅ አይደለም። የዮፍታሔ እናት “ዝሙት አዳሪ” ነበረች፤ ይህ ሲባል ግን እሱን የወለደችው ዝሙት አዳሪ ሆና ነው ወይም ዮፍታሔ ዲቃላ ልጅ ነው ማለት አይደለም። እናቱ ዝሙት አዳሪ የነበረችው የጊልያድ ሁለተኛ ሚስት ከመሆኗ በፊት ነው፤ ረዓብ ሰልሞንን ከማግባቷ በፊት ዝሙት አዳሪ እንደነበረችው ማለት ነው። (መሳ 11:1፤ ኢያሱ 2:1፤ ማቴ 1:5) ጊልያድ ከመጀመሪያ ሚስቱ የወለዳቸው የዮፍታሔ ወንድሞች ዮፍታሔን ውርስ እንዳይካፈለን ብለው ማባረራቸው በራሱ ዮፍታሔ ዲቃላ አለመሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (መሳ 11:2) በተጨማሪም ዮፍታሔ በኋላ ላይ የጊልያድ ሰዎች መሪ ሆኗል፤ መሪ አድርገው ከተቀበሉት የጊልያድ ሰዎች መካከል ዋነኞቹ የአባቱ ልጆች የሆኑት ወንድሞቹ ሳይሆኑ አይቀሩም። (መሳ 11:11) ከዚህም ሌላ ዮፍታሔ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ለአምላክ መሥዋዕት አቅርቧል። (መሳ 11:30, 31) ዮፍታሔ ዲቃላ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ማድረግ አይችልም ነበር፤ ምክንያቱም ሕጉ “ዲቃላ ወደ ይሖዋ ጉባኤ አይግባ። ሌላው ቀርቶ እስከ አሥረኛ ትውልድ ድረስ ዘሮቹ ወደ ይሖዋ ጉባኤ አይግቡ” በማለት በቀጥታ ይናገራል።—ዘዳ 23:2
ከታኅሣሥ 27–ጥር 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መሳፍንት 13–14
“ወላጆች፣ ከማኑሄና ከሚስቱ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?”
ወላጆች—ልጆቻችሁን ከጨቅላነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
ከዳን ነገድ የሆነውን ማኑሄን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ማኑሄ የሚኖረው በጥንቷ እስራኤል በምትገኘው ጾርዓ የተባለች ከተማ ነበር። የይሖዋ መልአክ፣ መካን ለሆነችው የማኑሄ ሚስት ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት። (መሳ. 13:2, 3) ታማኙ ማኑሄና ሚስቱ ይህን ሲሰሙ በጣም ተደስተው መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ያሳሰቧቸው ነገሮችም ነበሩ። ስለዚህ ማኑሄ እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ “ጌታ ሆይ፤ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ [እ]ንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ።” (መሳ. 13:8) ማኑሄና ሚስቱ ልጃቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ አሳስቧቸው ነበር። ለልጃቸው ለሳምሶን የአምላክን ሕግ እንዳስተማሩት ምንም ጥርጥር የለውም፤ ደግሞም ከሁኔታዎቹ ማየት እንደሚቻለው ጥረታቸው መና አልቀረም። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔርም መንፈስ . . . [ሳምሶንን] ያነቃቃው ጀመር” ይላል። በመሆኑም ሳምሶን የእስራኤል መስፍን ለመሆን የበቃ ሲሆን በርካታ አስገራሚ ነገሮችን አከናውኗል።—መሳ. 13:25፤ 14:5, 6፤ 15:14, 15
ሳምሶን ከይሖዋ ባገኘው ብርታት ድል አደረገ!
ሳምሶን እያደገ ሄደ፤ “እግዚአብሔርም ባረከው።” (መሳፍንት 13:24) አንድ ቀን ሳምሶን ወደ አባቱና እናቱ ቀርቦ “በተምና አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አይቻለሁና አሁኑኑ አጋቡኝ” አላቸው። (መሳፍንት 14:2) ይህን ሲሰሙ ክው ብለው እንደቀሩ ልትገምት ትችላለህ። ልጃቸው እስራኤላውያንን ከጨቋኞቻቸው እጅ ነፃ ከማውጣት ይልቅ ከእነርሱ ጋር በጋብቻ ለመተሳሰር ፈለገ። ጣዖት አምላኪ ከሆነ ሕዝብ መካከል ሚስት ማግባት ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጭ ድርጊት ነው። (ዘፀአት 34:11-16) በዚህም ምክንያት ወላጆቹ “ከዘመዶችህ ወይም ከሕዝባችን ሁሉ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት መች ታጣችና ነው ወዳልተገረዙት ፍልስጥኤማውያን ሚስት ፍለጋ የሄድኸው?” በማለት ተቃወሙት። ይሁንና ሳምሶን አባቱን “ልቤን የማረከችው እርሷ ናትና እርሷን ኣጋባኝ” በማለት በአቋሙ ጸና።—መሳፍንት 14:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ሳምሶን ከይሖዋ ባገኘው ብርታት ድል አደረገ!
ይህች ፍልስጥኤማዊት የሳምሶንን ‘ልብ የማረከችው’ ወይም ለእርሱ ተስማሚ የሆነችው በምን መንገድ ነው? በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ እርሷ ልቡን የማረከችው “ቆንጆ፣ ማራኪና ውብ ስለሆነች ሳይሆን ተስማሚ ሆኖ ያገኛት ከአንድ ዓላማ ወይም ግብ አንፃር ነው” የሚል ሐሳብ ይሰጣል። ዓላማው ምን ነበር? መሳፍንት 14:4 ሳምሶን “ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጠብ እንዲፈጠር” አጋጣሚ ይፈልግ እንደነበር ይገልጻል። ሳምሶን ሴቲቱን የፈለጋት ለዚህ ዓላማ ነበር። ሳምሶን ሙሉ ሰው ሲሆን ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያነቃቃው ጀመር’ ወይም እርምጃ እንዲወስድ አነሳሳው። (መሳፍንት 13:25) ስለዚህ ያልተለመደ የጋብቻ ጥያቄ እንዲያነሳም ሆነ በእስራኤል ላይ መስፍን ሆኖ ያከናወናቸውን ሥራዎች እንዲሠራ ያስቻለው የይሖዋ መንፈስ ነበር። ታዲያ ሳምሶን ሲጠብቀው የነበረውን አጋጣሚ አገኘ? በመጀመሪያ ይሖዋ መለኮታዊ ድጋፍ እንደሚሰጠው እንዴት እንዳረጋገጠለት እንመልከት።