የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • foa ርዕስ 4
  • ምርጣቸውን ሰጥተዋል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምርጣቸውን ሰጥተዋል
  • ከታሪክ ማኅደራችን
  • ንዑስ ርዕሶች
  • በሌሎች አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ፈጣን ምላሽ ሰጡ
  • አስደናቂ ውጤት
  • ‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’
ከታሪክ ማኅደራችን
foa ርዕስ 4
የይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ቁሳቁሶችን የያዙ ሣጥኖችን ወደ ጀርመን የሚሄድ ባቡር ላይ ሲጭኑ

ከታሪክ ማኅደራችን

ምርጣቸውን ሰጥተዋል

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 ሲያበቃ አብዛኛው የጀርመን ክፍል የፍርስራሽ ክምር ሆኖ ነበር። ከተሞች ፈራርሰው፣ ትምህርት ቤቶች ባዷቸውን ቀርተው፣ ሆስፒታሎች ከጥቅም ውጭ ሆነው እንዲሁም ያልፈነዱ ቦምቦች በየቦታው ተጥለው ነበር። በተጨማሪም የተከሰተውን የምግብ እጥረት ተከትሎ የምግብ ዋጋ በጣም ጨምሮ ነበር። ለምሳሌ በጥቁር ገበያ፣ ግማሽ ኪሎ ቅቤ ከስድስት ሳምንት ደሞዝ ጋር በሚመጣጠን ዋጋ ይሸጥ ነበር!

በዚህ ሁኔታ ከተጎዱት መካከል በእምነታቸው ምክንያት በርካታ ዓመታትን በእስር ቤትና በማጎሪያ ካምፕ ያሳለፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። በ1945 እነዚህ ምሥክሮች ከእስር ሲለቀቁ፣ ከለበሱት የእስረኛ ልብስ በቀር ምንም ነገር አልነበራቸውም። ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል። አንዳንዶች በረሃብ ክፉኛ ከመጎዳታቸው የተነሳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ራሳቸውን እስከመሳት ደርሰዋል።

በሌሎች አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ፈጣን ምላሽ ሰጡ

በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አስቸኳይ የምግብና የልብስ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ፈጣን ምላሽ ሰጡ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት በበርን፣ ስዊዘርላንድ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ በጀርመን ያሉ ወንድሞችን እንዲረዳ ጥያቄ አቀረበ። የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ የሆነው ናታን ኖር የእርዳታ ሥራውን ለማስተባበርና ለማቀላጠፍ ወደ አውሮፓ ሄደ።

በ1947 ወንድም ናታን ኖር በቪስባደን፣ ጀርመን ላሉ ወንድሞች ንግግር ሲያቀርብ። ከበላዩ “ብሔራት ሁሉ፣ ይሖዋን አወድሱት” የሚለው የዓመት ጥቅስ በጀርመንኛ ተጽፏል

በስዊዘርላንድ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ምግብ፣ ልብስና ገንዘብ በልግስና ሰጡ። የእርዳታ ቁሳቁሶቹ ወደ ጀርመን ከመላካቸው በፊት በዓይነት በዓይነት እንዲለዩና እንዲታሸጉ ወደ በርን ይላኩ ነበር። ስዊድንን፣ ካናዳንና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በሌሎች አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በእርዳታ ሥራው ተካፍለዋል፤ ይህም በጀርመን ብቻ ሳይሆን በጦርነት በተጎዱ በርካታ የአውሮፓና የእስያ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦችን ለመርዳት አስችሏል።

አስደናቂ ውጤት

የስዊዘርላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ በጥቂት ወራት ውስጥ ቡና፣ ወተት፣ ስኳር፣ ጥራጥሬ፣ የደረቀ ፍራፍሬ፣ አትክልት እንዲሁም የታሸገ ሥጋና ዓሣ ላከ። የገንዘብ እርዳታም አደረገ።

በተጨማሪም በስዊዘርላንድ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ካፖርቶችን፣ የሴቶች አልባሳትንና የወንዶች ሙሉ ልብሶችን ጨምሮ አምስት ቶን የሚመዝን ልብስ ሰጡ። የጥር 15, 1946 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “ወንድሞች የሰጡት ሊጥሉ ያሰቧቸውን ነገሮች አልነበረም፤ ሁሉም ነገር ምርጥ የሚባል ነው። በጀርመን ያሉ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት እውነተኛ መሥዋዕትነት ከፍለዋል።”

በስዊዘርላንድ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ 1,000 የሚጠጉ ጫማዎችንም ለግሰዋል፤ እርዳታውን የሚያስተባብሩት ወንድሞች ጫማዎቹን ከመላካቸው በፊት በጥሩ ይዞታ ላይ መሆናቸውን ያረጋግጡ ነበር። በቪስባደን፣ ጀርመን ያሉት ወንድሞችና እህቶች የታሸጉትን ዕቃዎች ሲከፍቱ በጥራታቸውና በዓይነታቸው በጣም ተገረሙ። አንድ ወንድም “ጀርመን ውስጥ እንዲህ ያሉ ጥራት ያላቸው ልብሶች ያሉበትና ብዙ ምርጫ የሚገኝበት የልብስ መደብር ያለ አይመስለኝም” በማለት ጽፏል።

የእርዳታ ቁሳቁሶቹ እስከ ነሐሴ 1948 ድረስ መላካቸውን ቀጠሉ። በስዊዘርላንድ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በአጠቃላይ 25 ቶን የሚመዝኑ 444 ሣጥን የእርዳታ ቁሳቁሶችን በጀርመን ላሉ ወንድሞቻቸው ልከዋል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በዚህ የእርዳታ ሥራ የተካፈሉት፣ በስዊዘርላንድ ያሉ ወንድሞች ብቻ አይደሉም። እንዲያውም በዚህ ሥራ ከተካፈሉት አገሮች መካከል አነስተኛ የአስፋፊ ቁጥር ያላቸው እነሱ ናቸው። በወቅቱ በስዊዘርላንድ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች 1,600 ብቻ ነበሩ!

‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

ኢየሱስ ክርስቶስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:34, 35) የይሖዋ ሕዝቦች ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር፣ ትርፋቸውን ሳይሆን ካላቸው ላይ ምርጡን እንዲሰጡ ገፋፍቷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 8:1-4) ከዙሪክ የተላከ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ምንም የሌላቸው ጥቂት የማይባሉ ወንድሞች በእርዳታ ሥራው መካፈል ስለፈለጉ [የራሳቸውን] የራሽን ካርድና ገንዘብ ሰጥተዋል።”

በጀርመን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስደትና ጦርነት ካስከተለባቸው ጉዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማገገም ችለዋል። ለዚህ አንዱ ምክንያት የእምነት ባልንጀሮቻቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ተነሳስተው በተደራጀ መንገድ ያደረጉላቸው እርዳታ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ