የጥናት ርዕስ 48
ተነዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ ተማምናችሁ መኖር ትችላላችሁ
“‘በርቱ . . . እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”—ሐጌ 2:4
መዝሙር 118 “እምነት ጨምርልን”
ማስተዋወቂያa
1-2. (ሀ) እኛ ባለንበት ሁኔታና ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን በነበሩበት ሁኔታ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ? (ለ) የጥንቶቹ አይሁዳውያን ያጋጠሟቸውን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ግለጽ። (“የሐጌ፣ የዘካርያስና የዕዝራ ዘመን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
አልፎ አልፎ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ትጨነቃለህ? ምናልባትም ከሥራህ በመፈናቀልህ የተነሳ ቤተሰብህን የማስተዳደር ጉዳይ ያስጨንቅህ ይሆናል። የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ስደት ወይም በስብከቱ ሥራ ላይ ተቃውሞ በመነሳቱ ምክንያት የቤተሰብህ ደህንነት ያሳስብህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞሃል? ከሆነ፣ የጥንቶቹ እስራኤላውያን እንዲህ ያሉ ችግሮች ባጋጠሟቸው ወቅት ይሖዋ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ መመርመርህ ይጠቅምሃል።
2 ዕድሜ ልካቸውን ባቢሎን ውስጥ የኖሩት አይሁዳውያን የተደላደለ ሕይወታቸውን ትተው ወደማያውቁት አገር መጓዝ እምነት ጠይቆባቸዋል። እዚያ ከደረሱ ብዙም ሳይቆይ የኢኮኖሚ ችግር፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም ተቃውሞ አጋጠማቸው። በዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ በመገንባቱ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ ከብዷቸው ነበር። በመሆኑም ይሖዋ የሕዝቡን ቅንዓት መልሶ ለማቀጣጠል በ520 ዓ.ዓ. ገደማ ሁለት ነቢያትን ማለትም ሐጌንና ዘካርያስን ላከላቸው። (ሐጌ 1:1፤ ዘካ. 1:1) ቀጥሎ እንደምንመለከተው እነዚህ ነቢያት የሰጧቸው ማበረታቻ ግሩም ውጤት አስገኝቷል። ይሁንና ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ከ50 ዓመት ገደማ በኋላ በድጋሚ ማበረታቻ አስፈልጓቸው ነበር። የተካነ የሕጉ ገልባጭ የሆነው ዕዝራ በዚያ ወቅት ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ የአምላክ ሕዝቦች ለእውነተኛው አምልኮ ቅድሚያ እንዲሰጡ አበረታታቸው።—ዕዝራ 7:1, 6
3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን? (ምሳሌ 22:19)
3 የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች በጥንት ዘመን የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው በይሖዋ መታመናቸውን እንዲቀጥሉ እንደረዷቸው ሁሉ እኛም ተነዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ ስንኖር ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኞች እንድንሆን ይረዱናል። (ምሳሌ 22:19ን አንብብ።) ሐጌና ዘካርያስ የተናገሩትን የአምላክ መልእክት እንዲሁም የዕዝራን ምሳሌ በመመርመር የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን የደረሰባቸው ችግር ምን ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል? ተነዋዋጭ በሆነ ጊዜ ውስጥ ስንኖር የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ትኩረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? በመከራ ውስጥ ስንሆን በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
አይሁዳውያን የደረሰባቸው ችግር ምን ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል?
4-5. አይሁዳውያኑ ቤተ መቅደሱን ለመገንባቱ ሥራ የነበራቸው ቅንዓት እንዲቀዘቅዝ ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል?
4 አይሁዳውያኑ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱበት ወቅት ብዙ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር። ወዲያውኑ የይሖዋን መሠዊያ መልሰው ሠሩ፤ እንዲሁም የቤተ መቅደሱን መሠረት ጣሉ። (ዕዝራ 3:1-3, 10) ሆኖም መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ቅንዓት ብዙም ሳይቆይ ቀዘቀዘ። ለምን? ቤተ መቅደሱን ከመገንባቱ ሥራ በተጨማሪ ለራሳቸው ቤት መሥራት፣ እህል ማምረት እንዲሁም ቤተሰባቸውን መመገብ ነበረባቸው። (ዕዝራ 2:68, 70) ከዚህም ሌላ፣ የቤተ መቅደሱን ግንባታ ለማስቆም የሚያሴሩት ጠላቶቻቸው ይቃወሟቸው ነበር።—ዕዝራ 4:1-5
5 ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን በወቅቱ የነበረው የኢኮኖሚና የፖለቲካ አለመረጋጋትም ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ነበር። አሁን አገራቸው በፋርስ ግዛት ሥር ነች። የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ በ530 ዓ.ዓ. ከሞተ በኋላ እሱን ተክቶ የነገሠው ካምቢሰስ ግብፅን ለመቆጣጠር ወታደራዊ ዘመቻ አካሄደ። ወታደሮቹ ወደ ግብፅ ሲጓዙ እስራኤላውያን ምግብ፣ ውኃና መጠለያ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋቸው ሊሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ችግር ፈጥሮባቸው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። ካምቢሰስን ተክቶ የነገሠው የቀዳማዊ ዳርዮስ የግዛት ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት በሕዝባዊ ዓመፅና በፖለቲካ አለመረጋጋት የተሞሉ ነበሩ። ወደ አገራቸው የተመለሱት ብዙዎቹ አይሁዳውያን በእነዚህ ሁኔታዎች የተነሳ ቤተሰቦቻቸውን የማስተዳደር ጉዳይ አስጨንቋቸው መሆን አለበት። የነበሩበት ሁኔታ በጣም ተነዋዋጭ በመሆኑ አንዳንዶቹ አይሁዳውያን የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ ለመገንባት ጊዜው እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ነበር።—ሐጌ 1:2
6. በዘካርያስ 4:6, 7 መሠረት አይሁዳውያኑ ሌላ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል? ዘካርያስ ምን ዋስትና ሰጣቸው?
6 ዘካርያስ 4:6, 7ን አንብብ። አይሁዳውያኑ ከኢኮኖሚ ችግርና ከፖለቲካ አለመረጋጋት በተጨማሪ ስደትን መጋፈጥ አስፈልጓቸዋል። በ522 ዓ.ዓ. ጠላቶቻቸው የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ የመገንባቱ ሥራ እንዲታገድ አደረጉ። ሆኖም ዘካርያስ፣ ይሖዋ ኃያል የሆነውን መንፈሱን ተጠቅሞ ማንኛውንም እንቅፋት እንደሚያስወግድላቸው ለአይሁዳውያኑ ዋስትና ሰጣቸው። በ520 ዓ.ዓ. ንጉሥ ዳርዮስ በቤተ መቅደሱ የግንባታ ሥራ ላይ የተጣለውን እገዳ ያነሳ ከመሆኑም ሌላ አይሁዳውያኑ የገንዘብ እርዳታና የባለሥልጣናቱን ድጋፍ እንዲያገኙ አደረገ።—ዕዝራ 6:1, 6-10
7. ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቅድሚያ ሲሰጡ የትኞቹን በረከቶች አገኙ?
7 ይሖዋ ሕዝቦቹ ቤተ መቅደሱን መልሶ ለመገንባቱ ሥራ ቅድሚያ ከሰጡ እሱ እንደሚረዳቸው በሐጌና በዘካርያስ አማካኝነት አረጋገጠላቸው። (ሐጌ 1:8, 13, 14፤ ዘካ. 1:3, 16) ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን በነቢያቱ ተበረታተው በ520 ዓ.ዓ. ቤተ መቅደሱን መገንባታቸውን ቀጠሉ። ከዚያም አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የግንባታ ሥራውን አጠናቀቁ። አይሁዳውያኑ ተነዋዋጭ በሆነ ጊዜ ውስጥም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቅድሚያ በመስጠታቸው በቁሳዊ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊም የይሖዋን ድጋፍ አግኝተዋል። በዚህም የተነሳ ይሖዋን በደስታ ማምለክ ችለዋል።—ዕዝራ 6:14-16, 22
የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ትኩረት አድርግ
8. በሐጌ 2:4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ትኩረት እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
8 ወደ ታላቁ መከራ ይበልጥ እየተቃረብን ስንሄድ በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል የተሰጠንን ትእዛዝ መፈጸማችን ይበልጥ አንገብጋቢ እንደሆነ መገንዘባችን አስፈላጊ ነው። (ማር. 13:10) ይሁንና የገንዘብ ችግር ካጋጠመን ወይም በስብከቱ ሥራችን ላይ ተቃውሞ ከተነሳ በአገልግሎታችን ላይ ትኩረት ማድረግ ሊከብደን ይችላል። ታዲያ የመንግሥቱን ሥራ እንድናስቀድም የሚረዳን ምንድን ነው? “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ”b ከጎናችን እንደሆነ ምንጊዜም እርግጠኞች መሆናችን አስፈላጊ ነው። ከራሳችን ፍላጎት ይልቅ የመንግሥቱን ሥራ ማስቀደማችንን ከቀጠልን እሱ ይረዳናል። በመሆኑም የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም።—ሐጌ 2:4ን አንብብ።
9-10. አንድ ባልና ሚስት ኢየሱስ በማቴዎስ 6:33 ላይ የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት ያዩት እንዴት ነው?
9 በአቅኚነት የሚያገለግሉ ኦሌግ እና አይሪናc የተባሉ ባልና ሚስት ያጋጠማቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንድን ጉባኤ ለመርዳት ሲሉ ወደ ሌላ አካባቢ ከተዛወሩ በኋላ በአገራቸው ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ እየተባባሰ በመሄዱ ምክንያት የገቢ ምንጫቸውን አጡ። ለአንድ ዓመት ያህል ቋሚ ሥራ ባይኖራቸውም የይሖዋ ፍቅራዊ ድጋፍ ፈጽሞ አልተቋረጠባቸውም፤ አልፎ አልፎ ደግሞ ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው እርዳታ አግኝተዋል። ይህን አስጨናቂ ሁኔታ መቋቋም የቻሉት እንዴት ነው? ኦሌግ መጀመሪያ ላይ በጭንቀት ተውጦ ነበር። ሆኖም እንዲህ ብሏል፦ “በአገልግሎት መጠመዳችን በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ እንድናተኩር ረድቶናል።” እሱና ባለቤቱ ሥራ በሚፈልጉበት ወቅትም በአገልግሎት መጠመዳቸውን ቀጥለዋል።
10 አንድ ቀን ከአገልግሎት ወደ ቤት ሲመለሱ አንድ የቅርብ ጓደኛቸው 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዞ ያመጣላቸውን ሁለት ዘንቢል አስቤዛ አገኙ። ኦሌግ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያ ዕለት የይሖዋንና የጉባኤውን እንክብካቤ በድጋሚ አጣጣምን። ይሖዋ አገልጋዮቹ ምንም ተስፋ የሌለው ሁኔታ ውስጥ ያሉ ቢመስልም እንኳ ፈጽሞ እንደማይረሳቸው እርግጠኞች ነን።”—ማቴ. 6:33
11. የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ትኩረት ካደረግን ምን መጠበቅ እንችላለን?
11 ይሖዋ ሕይወት አድን በሆነው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ላይ እንድናተኩር ይፈልጋል። በአንቀጽ 7 ላይ እንደተመለከትነው ሐጌ የይሖዋ ሕዝቦች የቤተ መቅደሱን መሠረት በድጋሚ የመጣል ያህል እንደ አዲስ በንጹሕ አምልኮ መካፈል እንዲጀምሩ አበረታቷቸዋል። እንዲህ ካደረጉ ይሖዋ ‘እንደሚባርካቸው’ ቃል ገብቶላቸዋል። (ሐጌ 2:18, 19) እኛም ይሖዋ ለሰጠን ሥራ ቅድሚያ ከሰጠን እሱ ጥረታችንን እንደሚባርክልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
12. ዕዝራና አብረውት የተጓዙት አይሁዳውያን ጠንካራ እምነት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?
12 በ468 ዓ.ዓ. ዕዝራ ከሌሎች አይሁዳውያን ጋር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ። ዕዝራና ሌሎቹ አይሁዳውያን ይህን ጉዞ ለማድረግ ጠንካራ እምነት አስፈልጓቸዋል። የሚጓዙት በአደገኛ መንገድ ላይ ነው። በተጨማሪም ለቤተ መቅደሱ መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ብዙ ወርቅና ብር ይዘዋል። ይህም ለዘራፊዎች ጥቃት ሊያጋልጣቸው ይችላል። (ዕዝራ 7:12-16፤ 8:31) ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ኢየሩሳሌምም አደገኛ ቦታ እንደሆነች ተገነዘቡ። የከተማዋ ነዋሪዎች ጥቂት ነበሩ። ቅጥሮቿና በሮቿም ጥገና ያስፈልጋቸው ነበር። ታዲያ በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት ከማጠናከር ጋር በተያያዘ ከዕዝራ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13. ዕዝራ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ያጠናከረው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
13 ዕዝራ በፈተና ወቅት ይሖዋ ሕዝቦቹን የደገፋቸው እንዴት እንደሆነ አይቷል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በ484 ዓ.ዓ. ንጉሥ አሐሽዌሮስ በፋርስ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ አይሁዳውያን በሙሉ እንዲጠፉ አዋጅ ባወጣበት ወቅት ዕዝራ ይኖር የነበረው በባቢሎን ሳይሆን አይቀርም። (አስ. 3:7, 13-15) የዕዝራ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር! ይህ አደጋ ሲደቀንባቸው ‘በሁሉም አውራጃዎች’ ያሉት አይሁዳውያን በመጾምና በማልቀስ ይሖዋ እንዲረዳቸው ለመኑ። (አስ. 4:3) አይሁዳውያንን ለማጥፋት ያሴሩት ሰዎች ተንኮላቸው በራሳቸው ላይ ሲመለስባቸው ዕዝራና ሌሎቹ አይሁዳውያን ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! (አስ. 9:1, 2) ዕዝራ በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ያየው ነገር ወደፊት ለሚያጋጥሙት ፈተናዎች አዘጋጅቶት ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቦቹን የመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ይበልጥ እንዲተማመን አድርጎት መሆን አለበት።d
14. አንዲት እህት በአስቸጋሪ ወቅት የይሖዋን እንክብካቤ በማጣጣሟ ምን ትምህርት አግኝታለች?
14 አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ውስጥ የይሖዋን እንክብካቤ ስናጣጥም በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይጠናከራል። በምሥራቅ አውሮፓ የምትኖረው አናስታሲያ ምን እንዳጋጠማት እንመልከት። የገለልተኝነት አቋሟን ለመጠበቅ ስትል ሥራዋን ለቀቀች። እንዲህ ብላለች፦ “ከዚያ በፊት ገንዘብ አጥቼ አላውቅም ነበር። ሆኖም ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ተውኩት። በዚህ ጊዜ የእሱን ፍቅራዊ እንክብካቤ ማየት ችያለሁ። ከዚህ በኋላ ሥራ ባጣ አልፈራም። የሰማዩ አባቴ ዛሬ ከተንከባከበኝ ነገም ይንከባከበኛል።”
15. ዕዝራ በይሖዋ መታመኑን እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው? (ዕዝራ 7:27, 28)
15 ዕዝራ የይሖዋን እጅ በገዛ ሕይወቱ ተመልክቷል። ዕዝራ የይሖዋን እርዳታ ያየባቸውን ጊዜያት ማስታወሱ በእሱ መታመኑን እንዲቀጥል እንደረዳው ጥያቄ የለውም። ‘የአምላኬ የይሖዋ እጅ በላዬ ነበር’ የሚለውን አገላለጽ ልብ በል። (ዕዝራ 7:27, 28ን አንብብ።) ዕዝራ በስሙ በተጠራው መጽሐፍ ውስጥ ስድስት ቦታዎች ላይ ተመሳሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል።—ዕዝራ 7:6, 9፤ 8:18, 22, 31
በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን እጅ በግልጽ የምናየው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ሊሆን ይችላል? (አንቀጽ 16ን ተመልከት)e
16. በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን እጅ በግልጽ የምናየው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ሊሆን ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
16 ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ በክልል ስብሰባ ላይ መገኘት እንድንችል እረፍት እንዲሰጠን ወይም በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንድንችል የሥራ ፕሮግራማችንን እንዲያስተካክልልን አለቃችንን ስንጠይቅ የይሖዋን እጅ በሕይወታችን ውስጥ የምናይበት አጋጣሚ እንፈጥራለን። በዚህ ጊዜ አስገራሚ ውጤት ልናገኝ እንችላለን። በዚህም የተነሳ በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት ይጠናከራል።
ዕዝራ በሕዝቡ ኃጢአት የተነሳ በሐዘን ተውጦ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያለቅስና ሲጸልይ። ሕዝቡም እያለቀሱ ነው። ከዚያም ሸካንያህ “እስራኤል አሁንም ተስፋ አለው። . . . እኛም ከጎንህ ነን” በማለት ዕዝራን አጽናናው።—ዕዝራ 10:2, 4 (አንቀጽ 17ን ተመልከት)
17. ዕዝራ በአስቸጋሪ ወቅት ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
17 ዕዝራ በትሕትና የይሖዋን እርዳታ ጠይቋል። ዕዝራ ኃላፊነቱ ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት ሲሰማው በትሕትና ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር። (ዕዝራ 8:21-23፤ 9:3-5) ዕዝራ በዚህ መንገድ በይሖዋ መታመኑ በዙሪያው ያሉት ሰዎችም እንዲደግፉትና እምነቱን እንዲኮርጁ አነሳስቷቸዋል። (ዕዝራ 10:1-4) እኛም ቁሳዊ ፍላጎታችንን ወይም የቤተሰባችንን ደህንነት በተመለከተ በጭንቀት ስንዋጥ በይሖዋ በመታመን ወደ እሱ መጸለይ ይኖርብናል።
18. በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት ለማጠናከር ምን ይረዳናል?
18 በትሕትና የይሖዋን እርዳታ ከጠየቅን እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚያደርጉልንን ድጋፍ ከተቀበልን በአምላክ ላይ ያለን ትምክህት ይጠናከራል። የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ኤሪካ አስከፊ መከራ ቢያጋጥማትም በይሖዋ መታመኗን ቀጥላለች። በመጀመሪያ ልጇ ጨነገፈባት፤ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ውድ ባለቤቷን በሞት አጣች። ያሳለፈችውን ሁኔታ መለስ ብላ ስታስብ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እንዴት እንደሚረዳን አስቀድመን ማወቅ አንችልም። ባልጠበቅነው መንገድ እርዳታ ልናገኝ እንችላለን። ብዙዎቹ ጸሎቶቼ የተመለሱልኝ ጓደኞቼ በተናገሯቸውና ባደረጓቸው ነገሮች አማካኝነት እንደሆነ አስተውያለሁ። ለጓደኞቼ ስሜቴን በግልጽ ከነገርኳቸው እኔን መርዳት ይበልጥ ይቀላቸዋል።”
እስከ መጨረሻው በይሖዋ ታመኑ
19-20. ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ካልቻሉት አይሁዳውያን ምን ትምህርት እናገኛለን?
19 ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ካልቻሉት አይሁዳውያንም ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አንዳንዶቹ መመለስ ያልቻሉት በዕድሜ መግፋት፣ በከባድ ሕመም ወይም በቤተሰብ ኃላፊነት የተነሳ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን የገንዘብ መዋጮ በማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱትን አይሁዳውያን በፈቃደኝነት ደግፈዋል። (ዕዝራ 1:5, 6) የመጀመሪያዎቹ ተመላሾች ኢየሩሳሌም ከደረሱ ከ19 ዓመታት ገደማ በኋላም እንኳ በባቢሎን የቀሩት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም በፈቃደኝነት ስጦታ መላካቸውን የቀጠሉ ይመስላል።—ዘካ. 6:10
20 በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምንችለው ነገር ውስን እንደሆነ ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ልባዊ ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህን እንዴት እናውቃለን? በዘካርያስ ዘመን ይሖዋ በባቢሎን ያሉት አይሁዳውያን የላኩትን ወርቅና ብር ተጠቅሞ አክሊል እንዲሠራ ለነቢዩ ነግሮት ነበር። (ዘካ. 6:11) ይህ ‘ታላቅ አክሊል’ በልግስና ላደረጉት መዋጮ “ማስታወሻ” ሆኖ ያገለግላል። (ዘካ. 6:14 ግርጌ) ይሖዋ ተነዋዋጭ በሆነ ጊዜ ውስጥ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ልባዊ ጥረት መቼም እንደማይረሳው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብ. 6:10
21. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ለመጋፈጥ የሚረዳን ምንድን ነው?
21 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ስንኖር ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችም እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን፤ ወደፊት ደግሞ ሁኔታዎች ይበልጥ ሊባባሱ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:1, 13) ያም ቢሆን በጭንቀት ልንዋጥ አይገባም። ይሖዋ በሐጌ ዘመን ለነበሩት ሕዝቦቹ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ . . . አትፍሩ” እንዳላቸው አስታውስ። (ሐጌ 2:4, 5) እኛም የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም አቅማችን የፈቀደውን እስካደረግን ድረስ እሱ ከእኛ ጋር እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከሐጌና ከዘካርያስ ትንቢቶች እንዲሁም ከዕዝራ ምሳሌ ያገኘናቸውን ትምህርቶች በሥራ ላይ ካዋልን ወደፊት ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመን በይሖዋ መታመናችንን እንቀጥላለን።
መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!
a ይህ ርዕስ የተዘጋጀው የኢኮኖሚ ችግር፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም በስብከቱ ሥራችን ላይ ተቃውሞ ሲያጋጥመን በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት እንድናጠናክር ለመርዳት ታስቦ ነው።
b “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” የሚለው አገላለጽ በሐጌ መጽሐፍ ውስጥ 14 ጊዜ ይገኛል። ይህም፣ ይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይል እንዳለው እንዲሁም መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈ ግዙፍ ሠራዊት እንደሚመራ ለአይሁዳውያኑም ሆነ ለእኛ ማሳሰቢያ ይሆናል።—መዝ. 103:20, 21
c አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
d ዕዝራ የተካነ የአምላክ ሕግ ገልባጭ እንደመሆኑ መጠን ወደ ኢየሩሳሌም ከመጓዙ በፊትም ቢሆን በይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ላይ ጠንካራ እምነት አዳብሯል።—2 ዜና 36:22, 23፤ ዕዝራ 7:6, 9, 10፤ ኤር. 29:14
e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም በክልል ስብሰባ ላይ ለመገኘት እረፍት እንዲሰጠው አለቃውን ሲጠይቅ ተከለከለ። የይሖዋን እርዳታና አመራር ለማግኘት ከጸለየ በኋላ አለቃውን ድጋሚ ለማነጋገር ተዘጋጀ። የክልል ስብሰባውን መጋበዣ ለአለቃው በማሳየት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያለውን ጥቅም አብራራለት። አለቃው በሁኔታው ተገርሞ ውሳኔውን ይቀይራል።