የምድራችን የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?
“ሰዎች ለዘመናት ‘የአምላክ ቁጣ’ የሚባሉትን እንደ ጎርፍና ድርቅ ያሉትን የተፈጥሮ አደጋዎች እየፈሩ ቢኖሩም አሁን ግን የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ሳቢያ ለሚመጡ የከፉ አደጋዎች ተጋልጠዋል” በማለት ግሎብ ኤንድ ሜይል የተሰኘው የካናዳ ጋዜጣ ዘግቧል። የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UNEP) ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስብ አንድ ሰፊ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። የፕሮግራሙ ዳይሬክተር የሆኑት ክላውስ ቶይፈር እንዲህ ይላሉ:- “እርምጃ መውሰዳችን ወይም አለመውሰዳችን በ2032 ዕጹብ ድንቅ በሆነችው ፕላኔታችንና በነዋሪዎቿ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚኖረው ለመገመት የሚያስችል ግንዛቤ አግኝተናል።”
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም በ1972 ከተቋቋመ ወዲህ አንዳንድ መሻሻሎች ታይተዋል። ዘ ቶሮንቶ ስታር እንደዘገበው “በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የአየርና የወንዝ ውኃ ንጽሕናው የተሻሻለ ሲሆን ወደ ከባቢ አየር በሚለቀቁ ኬሚካሎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥርም በኦዞን ሽፋን ላይ የደረሰው ጉዳት በመጠኑ እንዲያገግም አስችሏል።” በተጨማሪም በካናዳ፣ በፊንላንድ፣ በኖርዌይና በዩናይትድ ስቴትስ እንደሚገኙት ያሉ የደን ጥበቃ ፕሮግራሞች “የደን መጨፍጨፍ የሚያስከትለውን ጎጂ ተጽዕኖ ለመቀነስ ተግባራዊ እርምጃ እየወሰዱ ነው።” ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ያወጣው ሪፖርት እንደሚለው የኢኮኖሚው እድገት በዚሁ ከቀጠለና ከተሞች እየሰፉ ከሄዱ በዱር እንስሳትና በሕይወታዊ ሀብት ሕልውና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ግሎብ ኤንድ ሜይል እንዲህ ብሏል:- “ከዓለማችን ወንዞች መካከል ወደ ግማሽ የሚጠጉት ወይ ተበክለዋል አሊያም የውኃ መጠናቸው በጣም ቀንሷል። አርባ በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ የሚኖርባቸው 80 አገሮች ከፍተኛ የውኃ እጥረት አለባቸው።”
ክላውስ ቶይፈር “ወሳኝ እርምጃ ከተወሰደ ጥሩ ውጤት ሊገኝ ይችላል” ብለው ያምናሉ። አክለውም “በግልጽ የሰፈረ የድርጊት መርሃ ግብር . . . አስተማማኝ ፕሮጄክቶችና . . . ከምንም ነገር በላይ ቁርጥ ያለ አቋም ሊኖረን ይገባል” ብለዋል። ይሁን እንጂ የዓለም መሪዎች ምድራችንን ለመንከባከብ በሚደረገው ጥረት ለመተባበር ፈቃደኛ ካልሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?
ሁኔታው ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን አይገባም! ይሖዋ አምላክ በዚህ ረገድ “ቁርጥ ያለ አቋም” ያለው ሲሆን “ወሳኝ እርምጃ” ለመውሰድም ተዘጋጅቷል። እንዲያውም ሁኔታዎቹን ለማስተካከል ጣልቃ እንደሚገባና ‘ምድርን የሚያጠፏትን እንደሚያጠፋ’ በግልጽ ተናግሯል። (ራእይ 11:18) በተጨማሪም የምድራችን ሥርዓተ ምህዳር ወደ ቀድሞ ይዞታው እንደሚመለስ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። በረሃማ ቦታዎች እንኳን ይለመልማሉ። (ኢሳይያስ 35:1) እንዲሁም ምግብ ይትረፈረፋል። ወንዞች ከብክለት ይጸዳሉ። (መዝሙር 72:16፤ 98:8) በምድር ላይ የሚኖረው ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ የአምላክን በረከት ያገኛል።—መዝሙር 96:11, 12
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
NASA photo