የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g16 ቁጥር 2 ገጽ 3-7
  • መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ መጽሐፍ ብቻ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ መጽሐፍ ብቻ ነው?
  • ንቁ!—2016
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መመሪያ ይዟል
  • መጽሐፍ ቅዱስ የመከራንና የግጭቶችን መንስኤ ይገልጻል
  • መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል
  • ትክክል ወይስ ስህተት? መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መመሪያ ይሰጠናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2024
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው?
    ንቁ!—2007
  • አምላክን የሚያስደስቱ እውነተኛ ትምህርቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ ይስማማሉ?
    ንቁ!—2011
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2016
g16 ቁጥር 2 ገጽ 3-7
አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ መጽሐፍ ብቻ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካለቀ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ሆኖታል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መጻሕፍት ተጽፈዋል፤ ይሁንና እነዚህ መጻሕፍት ደብዛቸው ጠፍቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ዓይነት ዕጣ አልገጠመውም። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት።

  • በርካታ ኃያላን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም መጽሐፉ አልጠፋም። ለምሳሌ ያህል፣ አን ኢንትሮዳክሽን ቱ ዘ ሜዲቭል ባይብል የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው በመካከለኛው ዘመን በአንዳንድ “ክርስቲያን” አገሮች ውስጥ “አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋው [ተራው ሕዝብ በሚጠቀምበት ቋንቋ] ይዞ ከተገኘ ወይም ካነበበ፣ መናፍቅና አፈንጋጭ እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።” መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የሚተረጉሙ ወይም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የሚያበረታቱ ምሁራን ይህን የሚያደርጉት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ተገድለዋል።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጥቃት ቢሰነዘርበትም፣ ጥንትም ሆነ ዛሬ በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት መጽሐፍ ነው። በሙሉ ወይም በከፊል ከ2,800 በሚበልጡ ቋንቋዎች አምስት ቢሊዮን ገደማ በሚሆኑ ቅጂዎች ታትሟል። መጽሐፍ ቅዱስ በፍልስፍና፣ በሳይንስና በሌሎች መስኮች ዙሪያ ከተጻፉ እንዲሁም ስርጭታቸው ውስን ከሆነና ጊዜ ከሚያልፍባቸው በርካታ መጻሕፍት ፈጽሞ የተለየ ነው።

  • መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎሙ አንዳንድ ቋንቋዎች እንዳይጠፉ እንዲያውም እንዲዳብሩ አግዟል። ለምሳሌ በማርቲን ሉተር የተዘጋጀው ጀርመንኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለቋንቋው ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የኪንግ ጄምስ ቨርዥን የመጀመሪያው እትም በእንግሊዝኛ “ከታተሙት መጻሕፍት ሁሉ በቋንቋው ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ መጽሐፍ ሳይሆን አይቀርም” ተብሎ ይነገርለታል።

  • መጽሐፍ ቅዱስ “በምዕራቡ ዓለም ባሕል ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ በሃይማኖታዊ ልማድና እምነት ላይ ብቻ ሳይሆን በሥነ ጥበብ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሕግ፣ በፖለቲካና ዘርዝረን በማንጨርሳቸው በርካታ መስኮች ላይ ተጽዕኖውን ማየት እንችላለን።”—ዚ ኦክስፎርድ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ዘ ቡክስ ኦቭ ዘ ባይብል

መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ ከሚያደርጉት ነጥቦች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? ሰዎች ለዚህ መጽሐፍ ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉት ለምንድን ነው? ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ምክንያቶች ይገኙበታል፦ መጽሐፍ ቅዱስ ወደር የሌለው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ትምህርት ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸውም ሆነ እርስ በርስ የሚጋጩት ለምን እንደሆነ እንድናውቅ ይረዳናል። ከዚህም በላይ እነዚህ ችግሮች እንደሚወገዱ ተስፋ ይሰጣል፤ እንዲያውም ይህ ለውጥ የሚመጣው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል።

አጭር መረጃ

የተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ 66 መጻሕፍትን ይዟል፤ ተጽፎ ያለቀው በ1,600 ዓመታት ገደማ ውስጥ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት 40 የሚያህሉ ሰዎች ናቸው፤ አንዳንዶቹ ገበሬዎች፣ ዓሣ አጥማጆች፣ መሳፍንት፣ ነገሥታትና ሙዚቀኞች ነበሩ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ የአምላክ መንግሥት ነው፤ ይህ መንግሥት ከሰማይ ሆኖ ምድርን የሚገዛ መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) መንግሥቱ፣ የሰው ዘር ሉዓላዊ ገዢ በሆነው በፈጣሪያችን በይሖዋ አምላክ አገዛዝ ሥር እንዲሆን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ክፋትን፣ መከራንና ሞትን ያስወግዳል።—1 ቆሮንቶስ 15:24-26

መጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መመሪያ ይዟል

ሰዎች የቀለም ትምህርት መቅሰማቸው አስፈላጊ እንደሆነ አይካድም። ሆኖም “አንድ ሰው ተምሮ አንድ ዓይነት ማዕረግ ማግኘቱ ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖረው ዋስትና አይሆንም” በማለት ኦታዋ ሲቲዝን የተባለው የካናዳ ጋዜጣ ዘግቧል። ኤድልማን የተባለ የሕዝብ ግንኙነት ተቋም ያሳተመው ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳሳየው በንግዱና በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ጨምሮ በርካታ የተማሩ ሰዎች ያታልላሉ፣ ያጭበረብራሉ እንዲሁም ይሰርቃሉ። ይህም ማኅበረሰቡ በመሪዎቹ ላይ “እምነት እንዲያጣ” አድርጓል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጣል። “ጽድቅ፣ ፍትሕና ትክክል የሆነውን ነገር ይኸውም የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ” እንድናስተውል ይረዳናል። (ምሳሌ 2:9) ፖላንድ ውስጥ ታስሮ የነበረውን የ23 ዓመቱን ስቲቨንንa እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እስር ቤት ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በውስጡ የሚገኘውን ጠቃሚ ምክር በሥራ ላይ ማዋል ጀመረ። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “‘አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለው መመሪያ ምን ትርጉም እንዳለው የገባኝ አሁን ነው። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ስሜቴን መቆጣጠር ችያለሁ፤ በቁጣ መገንፈልም ትቻለሁ።”—ኤፌሶን 4:31፤ 6:2

ስቲቨን በምሳሌ 19:11 ላይ የሚገኘው “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል፤ በደልንም መተዉ ውበት ያጎናጽፈዋል” የሚለው ጥቅስ ልቡን ነክቶታል። በአሁኑ ጊዜ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመው ጉዳዩን በእርጋታ ለማጤንና ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ያደርጋል። “መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የተሻለ መመሪያ የያዘ መጽሐፍ መሆኑን ተረድቻለሁ” ብሏል።

ጭፍን ጥላቻ ያላት አንዲት ሴት ማሪያ የተባለችን የይሖዋ ምሥክር አንድ ቀን በአደባባይ ሰደበቻት፤ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ግርግር ተፈጠረ። ማሪያ ግን አጸፋ ከመመለስ ይልቅ መንገዷን ቀጠለች። ሴትየዋ ባደረገችው ነገር ተጸጽታ የይሖዋ ምሥክሮችን መፈለግ ጀመረች። ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ማሪያን ስታገኛት አቅፋ ይቅርታ ጠየቀቻት። በተጨማሪም ሴትየዋ፣ ማሪያ ገር እንድትሆንና ስሜቷን መቆጣጠር እንድትችል የረዳት ሃይማኖቷ እንደሆነ አስተዋለች። ውጤቱ ምን ሆነ? ጭፍን ጥላቻ የነበራት ሴትና አምስት የቤተሰቧ አባላት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆኑ።

ኢየሱስ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ ባስገኘችው ውጤት እንደተረጋገጠ ገልጿል። (ሉቃስ 7:35) በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጠቃሚ ናቸው! መልካም ባሕርያትን እንድናዳብር ያስችሉናል። “ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ” ያደርጋሉ፤ “ልብን ደስ ያሰኛሉ” እንዲሁም ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ እይታችን የጠራ እንዲሆን በማድረግ ‘ዓይናችንን ያበሩልናል።’—መዝሙር 19:7, 8

መጽሐፍ ቅዱስ የመከራንና የግጭቶችን መንስኤ ይገልጻል

ተመራማሪዎች ስለ በሽታ ወረርሽኝ ሲያጠኑ መንስኤውን ይኸውም ‘እንዴት ጀመረ?’ የሚለውን ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። የሰው ልጆች ካጋጠማቸው እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋ መከራና ግጭት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ከጥንት ይኸውም ችግሮቹ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ታሪክ ስለሚዘግብ ጠቃሚ ሐሳብ እናገኝበታለን።

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ የሰው ልጆች መከራ የጀመረው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በአምላክ ላይ ባመፁበት ወቅት እንደሆነ ይናገራል። በዚህ ወቅት ከሠሯቸው ጥፋቶች መካከል ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሳቸው ለመወሰን መምረጣቸው ይገኝበታል፤ ይህ ፈጣሪ ብቻ ያለው መብት ነው። (ዘፍጥረት 3:1-7) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሰዎች በራሳቸው አስተሳሰብ መመራታቸው ያሳዝናል። ይህስ ምን አስከተለ? የሰው ዘር የነፃነትና የደስታ ታሪክ ሳይሆን የግጭት፣ የጭቆና እንዲሁም የሥነ ምግባርና የመንፈሳዊ ውድቀት ታሪክ አስመዝግቧል። (መክብብ 8:9) መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው . . . አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” ማለቱ የተገባ ነው። (ኤርምያስ 10:23) ደስ የሚለው ነገር የሰው ዘር፣ ጉዳት የሚያስከትል የዓመፅ ጎዳና መከተሉ የሚያበቃበት ጊዜ እጅግ ተቃርቧል።

መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል

አምላክ ለሥልጣኑና ላወጣቸው ደንቦች አክብሮት ላላቸው ሰዎች ፍቅር ስላለው ክፋትንና በዚያ ሳቢያ የሚመጣውን መከራ ለዘላለም ዝም ብሎ እንደማያይ መጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና ይሰጣል። ክፉዎች “መንገዳቸው የሚያስከትለውን መዘዝ ይቀበላሉ።” (ምሳሌ 1:30, 31) “የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11

ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ የተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስና ቡና

“[የአምላክ] ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

አምላክ ባቋቋመው “መንግሥት” በኩል ምድር ላይ ሰላም ለማስፈን ያለውን ዓላማ ያስፈጽማል። (ሉቃስ 4:43) ይህ መንግሥት ዓለም አቀፍ መስተዳድር ሲሆን አምላክ የሰው ዘርን የመግዛት መብት እንዳለው በመንግሥቱ አማካኝነት ያረጋግጣል። ኢየሱስ ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ ይህ መንግሥት ከምድር ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም” ብሏል።—ማቴዎስ 6:10

በእርግጥም የአምላክ መንግሥት ዜጎች፣ የመግዛት መብት ያለው ሰው ሳይሆን ፈጣሪ እንደሆነ በመገንዘብ የእሱን ፈቃድ ያደርጋሉ። ሙስና፣ ስግብግብነት፣ የኑሮ ልዩነት፣ የዘር ጥላቻና ጦርነት ይወገዳል። በዚያን ጊዜ ቃል በቃል አንድ ዓለም፣ አንድ መንግሥት እንዲሁም አንድ ዓይነት ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ደንብ ይኖራል።—ራእይ 11:15

መጪውን አዲስ ዓለም ለማየት የሚያስችለው ቁልፍ ነገር እውቀት ነው። አንደኛ ጢሞቴዎስ 2:3, 4 “[የአምላክ] ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው” ይላል። ይህ እውነት፣ የመንግሥቱ ሕገ መንግሥት ብለን ልንጠራቸው የምንችላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ያካተተ ነው። ሕገ መንግሥቱ፣ የአምላክ መንግሥት የሚመራባቸውን ሕጎችና ደንቦች የያዘ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በኢየሱስ ክርስቶስ የተራራ ስብከት ላይ ይገኛሉ። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7) እነዚህን ሦስት ምዕራፎች ስታነብ ሁሉም ሰው ኢየሱስ ያስተማረውን ጥበብ ያዘለ ትምህርት ተግባራዊ ሲያደርግ የሚኖረውን ሕይወት በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር።

መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ በስርጭቱ ወደር የሌለው መጽሐፍ መሆኑ ሊያስደንቀን ይገባል? በጭራሽ! በውስጡ የያዛቸው ትምህርቶች መጽሐፉ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ ያረጋግጣሉ። በስፋት የተሰራጨ መሆኑ ደግሞ አምላክ የትኛውም ቋንቋና ብሔር ያላቸው ሰዎች ስለ እሱ እንዲያውቁና መንግሥቱ ከሚያመጣቸው በረከቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

a ስሙ ተቀይሯል።

በከዋክብት የተሞላ ሰማይ

መጽሐፍ ቅዱስ ሰማያት የሚመሩት በሕግ እንደሆነ ይናገራል

አጉል እምነትን የሚያጋልጥ መጽሐፍ

ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሳይንስ ኤንድ ሪሊጅን እንደገለጸው ጥንት የነበሩ ሰዎች “ጽንፈ ዓለም በስሜት በሚነዱ አማልክት ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ያምኑ ነበር።” መጽሐፍ ቅዱስ ግን ጽንፈ ዓለም የሚንቀሳቀሰው በተፈጥሮ ሕጎች እየተመራ መሆኑን ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰማያትና ምድር ስለሚመሩባቸው ሕጎች’ ተናግሯል። (ኢዮብ 38:33) ኤርምያስ 31:35 “የጨረቃንና የከዋክብትን ሕጎች” ይጠቅሳል። ይህን ትክክለኛ እውቀት አምነው የተቀበሉ ሰዎች ለሐሰት አምልኮና ለአጉል እምነት ተጽእኖ አልተጋለጡም።—ኢዮብ 31:26-28፤ ኢሳይያስ 47:1, 13

ሐቁን የሚናገር መጽሐፍ

የመጽሐፍ ቅዱስን ጸሐፊዎች ለየት የሚያደርጋቸው አንዱ ነገር የራሳቸውን ድክመት እንኳ ሳይሸሽጉ በሐቀኝነት መናገራቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት ቤርሳቤህ ከተባለች ሴት ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ “በአንተ [በአምላክ] ዓይን ክፉ የሆነውን ነገር ፈጸምኩ” በማለት ሐቁን ተናግሯል። (መዝሙር 51:4) ሐዋርያው ዮሐንስ በሁለት አጋጣሚዎች ለመልአክ በመስገድ አምልኮ ሊያቀርብ እንደነበረ ሳይሸሽግ ተናግሯል። መልአኩ “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው! . . . ለአምላክ ስገድ!” ብሎታል። (ራእይ 19:10፤ 22:8, 9) ጥንት የነበሩ ጸሐፊዎች እንዲህ ዓይነቱ ግልጽነት የሚጎድላቸው መሆኑ ቢያሳዝንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግን በሐቀኝነታቸው ተለይተው ይታወቃሉ።

ለአእምሮ ጤና የሚጠቅም መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ርኅራኄና ይቅር ባይነት ያሉ ጤናማ አእምሮ እንዲኖረን የሚረዱ ባሕርያትን እንድናዳብር ያበረታታናል። ኤፌሶን 4:32 “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ . . . እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ” ይላል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ማዮ ክሊኒክ ያዘጋጀው ጽሑፍ “ይቅር ባይ ካልሆንክ ከማንም በላይ የምትጎዳው ራስህን ነው” ይላል። ጽሑፉ እንደገለጸው ከሆነ ይቅር ባይ መሆን “ከሌሎች ጋር ጤናማ ግንኙነት እንድንመሠርትና የተሻለ መንፈሳዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ጤንነት እንዲኖረን የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ የሚሰማን ጭንቀት እንዲቀንስ፣ ለሌሎች የጥላቻ ስሜት ከማዳበር እንድንቆጠብ፣ የደም ግፊታችን እንዳይጨምር፣ ለመንፈስ ጭንቀት እንዳንጋለጥ እንዲሁም የአልኮልና የሌሎች ንጥረ ነገሮች ሱሰኛ እንዳንሆን ይረዳናል።”

አሳሳቢ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ የያዘ መጽሐፍ

በማህፀን ውስጥ ያለ ሽል

በማህፀን ውስጥ ያለ ሽል

ሳይንስ ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ደግሞም የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቅ መሆኑ አይካድም፤ ያም ቢሆን ሳይንስ የማይመልሳቸው ጥያቄዎች አሉ። ባዮቴክኖሎጂ—ቼንጂንግ ላይፍ ስሩ ሳይንስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አብዛኞቹ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ዶክተሮችና ፈላስፎች ሳይንስ ከሥነ ምግባር፣ ከግብረገብ ወይም ከሃይማኖት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች መልስ እንደሌለው ይስማማሉ።”

  • ሳይንስ የተፈጥሮ ሕጎችን የሚያብራሩ የሒሳብ ቀመሮችን ሊያሳውቀን ይችላል፤ ሆኖም ጽንፈ ዓለም ሊኖር የቻለው ወይም ዝንፍ በማይሉ ሕጎች የሚመራው ለምን እንደሆነ ሊነግረን አይችልም።

  • ሳይንስ የመራቢያ አካሎች የሚሠሩት እንዴት እንደሆነ ሊገልጽ ይችላል፤ ሆኖም ስለ ፆታ ሥነ ምግባር የሚናገረው ነገር የለም።

  • ሳይንስ ፅንስ የሚፈጠረውና የሚያድገው እንዴት እንደሆነ ማብራሪያ ሊሰጥ ይችላል፤ ሆኖም ፅንስ ማስወረድን በተመለከተ ሰዎች ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ሊረዳ አይችልም።

መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህና ለሌሎች አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፤ በመሆኑም “ጽድቅ፣ ፍትሕና ትክክል የሆነውን ነገር ይኸውም የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ [እንድንረዳ]” ያስችለናል።—ምሳሌ 2:9

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ