የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g16 ቁጥር 2 ገጽ 8-9
  • ልጃችሁ የጉርምስናን ዕድሜ እንዲወጣ መርዳት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልጃችሁ የጉርምስናን ዕድሜ እንዲወጣ መርዳት
  • ንቁ!—2016
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተፈታታኙ ነገር
  • ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
  • ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
  • በጉርምስና ዕድሜ የሚከሰቱ ለውጦችን ማስተናገድ የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ‘ምን እየሆንኩ ነው?’
    ንቁ!—2004
  • በሰውነቴ ላይ የማየው ለውጥ ምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2016
g16 ቁጥር 2 ገጽ 8-9
አባት ከልጁ ጋር ሲነጋገር

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጃችሁ የጉርምስናን ዕድሜ እንዲወጣ መርዳት

አባትና ልጅ ከልጅነት ሙሉ ሰው ወደመሆን በሚመራ ጎዳና ላይ ጉርምስና የሚለው ምልክት ጋር ቆመው

ተፈታታኙ ነገር

ልጃችሁን ተወልዶ ያቀፋችሁት ገና ትናንት እንደሆነ ይሰማችኋል። አሁን ግን ታዳጊ ወጣት ሊሆን ምንም አልቀረውም፤ እርግጥ አሁንም ልጅ ነው። ሆኖም ሙሉ ሰው ወደ መሆን የሚያሸጋግረውን የጉርምስና ዕድሜ የሚጀምርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

ልጃችሁ ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሔዋን የሚበቃበት ይህ ጊዜ ልጁን ግራ ሊያጋባው አንዳንድ ጊዜም ሊያስጨንቀው ይችላል፤ ታዲያ ይህን ለውጥ በጥሩ ሁኔታ ማስተናገድ እንዲችል መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ጉርምስና የሚጀምርበት ዕድሜ የተለያየ ነው። ጉርምስና ፈጠነ ከተባለ በስምንት ዓመት፣ ዘገየ ከተባለ ደግሞ በአሥራዎቹ አጋማሽ ላይ ሊጀምር ይችላል። ሌቲንግ ጎ ዊዝ ላቭ ኤንድ ኮንፊደንስ የተባለው መጽሐፍ “ጉርምስና በተለያየ ዕድሜ ላይ መጀመሩ የተለመደ ነገር ነው” ይላል።

ጉርምስና በራስ የመተማመን ስሜት ሊያሳጣ ይችላል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ሌሎች ስለ እነሱ ያላቸው አመለካከት በጣም ሊያሳስባቸው ይችላል። ጃሬድa የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ስለ መልኬና ስለ አኳኋኔ መጨነቅ ጀመርኩ። ከሌሎች ጋር ስሆን ከሰው የተለየሁ እንደሆንኩ አድርገው ያስቡ ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ።” ብጉር ካወጡ ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜታቸው ይባስ ያሽቆለቁላል። የ17 ዓመቷ ኬሊ “ፊቴ ትርምስምሱ እንደወጣ ተሰማኝ!” ብላለች። “ብዙ ጊዜ እንደማለቅስ እንዲሁም ‘አቤት ሳስጠላ!’ እል እንደነበረ ትዝ ይለኛል።”

ቀድመው የሚጎረምሱ ልጆች የተለየ ፈተና ያጋጥማቸዋል። በተለይ ሴት ልጆች ጡት ወይም ዳሌ ሲያወጡ የሌሎች መቀለጃ ይሆናሉ። ኤ ፓሬንትስ ጋይድ ቱ ዘ ቲን ይርስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው እነዚህ ሴቶች “ወሲብ መፈጸም የጀመሩ በዕድሜ የሚበልጧቸው ወንዶች ልጆች ዓይን ውስጥ ይገባሉ።”

አንድ ልጅ ጎረመሰ ማለት ጎለመሰ ማለት አይደለም። የምሳሌ 22:15 የግርጌ ማስታወሻ “ሞኝነት በወጣት ልብ ውስጥ ታስሯል” ይላል። ልጁ መጎርመሱ ይህን ሐቅ አይቀይረውም። አንድ ወጣት ሲታይ አዋቂ ሊመስል ይችላል፤ ይህ ግን “ማስተዋል የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ ስለመቻሉ፣ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ስለመሆኑ፣ ስሜቱን መቆጣጠር ስለመቻሉ ወይም ጎልማሳ መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች ተግባሮችን ማከናወን ስለመቻሉ የሚገልጸው ነገር” እንደሌለ ዩ ኤንድ ዮር አዶለሰንት የተባለው መጽሐፍ ይናገራል።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ጉርምስና ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሰለ ጉዳዩ ተነጋገሩ። ልጆቻችሁ ምን ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አሳውቋቸው፤ ሴት ከሆነች የወር አበባ ልታይ እንደምትችል፣ ወንድ ከሆነ ደግሞ በእንቅልፉ ዘሩ ሊፈስ እንደሚችል ንገሯቸው። ቀስ በቀስ ከሚታዩት የጉርምስና ለውጦች በተለየ እነዚህ ለውጦች ድንገት ስለሚከሰቱ ልጃችሁ ግራ ሊጋባ አልፎ ተርፎም ሊደነግጥ ይችላል። እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን ስትነጋገሩ አዎንታዊ ሁኑ፦ ጉርምስና ሙሉ ሰው ወደ መሆን የሚያደርሳቸው አስፈላጊ ለውጥ የሚጀምርበት ጊዜ እንደሆነ አሳውቋቸው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መዝሙር 139:14

ምንም ነገር አትደብቋቸው። ጆን የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ከወላጆቼ ጋር ስለዚህ ጉዳይ ስንነጋገር አንዳንድ ነገሮችን ይሸፋፍኑ ነበር። በግልጽ ፊት ለፊት ቢነግሩኝ ደስ ይለኝ ነበር።” የ17 ዓመቷ አላናም ተመሳሳይ ስሜት አላት። እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ በሰውነቴ ላይ ስለሚታዩት ለውጦች በሚገባ አስረድታኛለች። ሆኖም በስሜቴ ላይ የሚኖሩትንም ለውጦች በጥሩ ሁኔታ መቀበል እንድችል ብትረዳኝ ደስ ይለኝ ነበር።” ነጥቡ ምንድን ነው? የሚያሳፍር ቢሆንም እንኳ ለልጆቻችሁ ስለ ጉርምስና ምንም ነገር ሳትደብቁ ንገሯቸው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ የሐዋርያት ሥራ 20:20

ለውይይት የሚጋብዙ ጥያቄዎችን ጠይቁ። መተፋፈሩን ለማስወገድ ሌሎች ልጆች ከጉርምስና ጋር በተያያዘ ስላጋጠሟቸው ነገሮች አውሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ሴት ልጃችሁን “አብረውሽ የሚማሩ ልጆች የወር አበባ እንዳዩ ሲያወሩ ሰምተሽ ታውቂያለሽ?” ወይም “አንዳንድ ተማሪዎች፣ ከሌሎች ቀድመው ጡት ባወጡ ልጆች ላይ ይቀልዳሉ እንዴ?” ብላችሁ ልትጠይቋት ትችላላችሁ። ወንድ ልጃችሁን ደግሞ “ተማሪዎች ከእኩዮቻቸው በተለየ ገና ባልጎረመሱ ልጆች ላይ ይቀልዱባቸዋል?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች በእኩዮቻቸው ላይ የታዩት ለውጦች ምን እንዳስከተሉባቸው ማውራት ከጀመሩ ስለራሳቸው ስሜትና ስላጋጠሟቸው ነገሮች ለመናገር ይበልጥ ነፃነት ይሰማቸዋል። ልጆቻችሁ ስሜታቸውን አውጥተው መናገር ሲጀምሩ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርጉ። —ያዕቆብ 1:19

ልጆቻችሁ “ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን” እንዲያዳብሩ እርዷቸው። (ምሳሌ 3:21) የጉርምስና ዕድሜ አካላዊና ስሜታዊ ለውጦች የሚታዩበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ልጆቻችሁ ሙሉ ሰው ሲሆኑ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳቸውን የማመዛዘን ችሎታ የሚያዳብሩበት ጊዜም ነው። በመሆኑም ይህን አጋጣሚ መልካም እሴቶችን እንዲያዳብሩ ለመርዳት ተጠቀሙበት።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ዕብራውያን 5:14

ተስፋ አትቁረጡ። በርካታ ወጣቶች ጉርምስናን አስመልክቶ ከወላጆቻቸው ጋር ለመነጋገር የሚያቅማሙ ቢመስሉም እንኳ በዚህ አትዘናጉ። ዩ ኤንድ ዮር አዶለሰንት የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ውይይቱ “ደስ ያላለው፣ የሰለቸው፣ ያስጠላው ወይም ጆሮውን የደፈነ የሚመስለው በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ የምትነግሩትን ነገር ሁሉ ልቅም አድርጎ እያዳመጠ ሊሆን ይችላል።”

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

ቁልፍ ጥቅሶች

  • “በሚያስደምም ሁኔታ ግሩምና ድንቅ ሆኜ [ተፈጥሬአለሁ]።” —መዝሙር 139:14

  • “የሚጠቅማችሁን ማንኛውንም ነገር ከመንገር . . . ወደኋላ ብዬ አላውቅም።”—የሐዋርያት ሥራ 20:20

  • ‘ጎልማሳ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት አሠልጥነዋል።’—ዕብራውያን 5:14

“በጉርምስና ዕድሜ ላይ ሳለሁ የወላጆቼ በተለይ ደግሞ የእናቴ እርዳታ አልተለየኝም። እናቴ ጊዜ ወስዳ ሁሉንም ነገር አስረድታኝ ነበር። ምን እንደሚያጋጥመኝ ጠንቅቄ አውቅ ስለነበረ ጊዜው ሲደርስ አልተደናገጥኩም። በዚያ ላይ ደግሞ እናቴ ምንጊዜም እሷን ማናገር እንዲቀለኝ ጥረት ታደርግ ነበር። ወላጆቼ ሳንተፋፈር እንድንነጋገር ረድተውኛል።”—መሪ፣ 16 ዓመት

“ወላጆቼ ስሜቴን ይረዱልኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በጉርምስና ዕድሜ የሚያጋጥሙኝ ነገሮች ሊያሳፍሩኝ እንደሚችሉ ስለተረዱ ለስሜቴ ይጠነቀቁ ነበር። ስለ ጉዳዩ ለሌሎች አለመናገራቸው በራሱ በጣም ረድቶኛል። በተጨማሪም ምን እንደሚያጋጥመኝ ቀደም ብለው ነግረውኛል።”—ጆአን፣ 18 ዓመት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ