የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g16 ቁጥር 6 ገጽ 4-6
  • ከበሽታ ራስህን ጠብቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከበሽታ ራስህን ጠብቅ
  • ንቁ!—2016
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • 1 ውኃ
  • 2 ምግብ
  • 3 ነፍሳት
  • 4 እንስሳት
  • 5 ሰዎች
  • ጤንነትህን ማሻሻል የምትችልባቸው መንገዶች
    ንቁ!—2015
  • 4ኛው ቁልፍ—ጤንነትህን ጠብቅ
    ንቁ!—2011
  • እንደገና ያገረሸው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2003
  • ጤንነትህን መጠበቅ የምትችልባቸው ስድስት መንገዶች
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2016
g16 ቁጥር 6 ገጽ 4-6

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በሽታን መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?

ከበሽታ ራስህን ጠብቅ

በርካታ ጥንታዊ ከተሞች በትላልቅ ግንቦች የታጠሩ ነበሩ። ጠላት የተወሰነውን የግንቡን ክፍል እንኳ ማፍረስ ከቻለ መላው ከተማ አደጋ ላይ ይወድቃል። ሰውነትህም በግንብ እንደታጠረ ከተማ ነው። በመሆኑም ጤንነትህ የተመካው ለመከላከያህ በምታደርገው እንክብካቤ ላይ ነው። ለበሽታ ሊያጋልጡህ የሚችሉ አምስት ነገሮችንና ከሁሉ በተሻለ መንገድ በሽታን መከላከል የምትችልባቸውን መንገዶች እስቲ እንመልከት።

አንዲት ሴት ከልጇ ጋር በገበያ ስፍራ ስትዘዋወር

1 ውኃ

አደጋው፦ ጎጂ ሕዋሳት በተበከለ ውኃ አማካኝነት ሰውነትህን “ሊወርሩ” ይችላሉ።

መከላከያው፦ ከሁሉ የተሻለው መከላከያ የምትጠቀምበት ውኃ እንዳይበከል ማድረግ ነው። የምትጠቀምበት ውኃ የተበከለ እንደሆነ ካወቅክ ወይም ከተጠራጠርክ ውኃውን ቤትህ ውስጥ በማጣራት ከብክለት የጸዳ እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ።a የመጠጥ ውኃን ከድነህ አስቀምጥ፤ እንዲሁም ውኃውን ለማውጣት ንጹሕ መቅጃ ተጠቀም፤ አሊያም ለውኃ ማጠራቀሚያህ ቧንቧ ግጠምለት። ንጹሕ ውኃ የተቀመጠበት ዕቃ ውስጥ በፍጹም እጅህን አታስገባ። ከተቻለ ዓይነ ምድር በተገቢው መልኩ በሚወገድበት አካባቢ ለመኖር ሞክር፤ እንዲህ ማድረግህ በአካባቢህ የንጹሕ ውኃ አቅርቦት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያበረክታል።

2 ምግብ

አደጋው፦ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን፣ ምግብህ ውስጥ ወይም ምግብህ ላይ ሊገኙ ይችላሉ።

መከላከያው፦ የተበከለ ምግብ ከላይ ሲታይ ንጹሕና ገንቢ ሊመስል ይችላል። ስለሆነም ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን በደንብ የማጠብ ልማድ አዳብር። ምግብ ስታዘጋጅ ወይም ስታቀርብ ምግብ ለማብሰል የምትጠቀምባቸው ዕቃዎች፣ ጠረጴዛው እንዲሁም እጆችህ ንጹሕ መሆናቸውን አረጋግጥ። አንዳንድ ምግቦች በውስጣቸው የሚገኙ አደገኛ ተሕዋስያንን ለማስወገድ በተወሰነ የሙቀት መጠን ሊበስሉ ይገባል። አንድ ምግብ ቀለሙን መቀየሩ አሊያም ደስ የማይል ሽታ ወይም ጣዕም ማምጣቱ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን አድፍጠው እየጠበቁህ መሆኑን ሊያሳይ የሚችል ምልክት ስለሆነ ጥንቃቄ አድርግ። የተረፈህን ምግብ ወዲያውኑ ማቀዝቀዣ ውስጥ አስገባ። በታመምክበት ወቅት ለሌሎች ምግብ አታዘጋጅ።b

3 ነፍሳት

አደጋው፦ አንዳንድ ነፍሳት በውስጣቸው የሚኖሩ ጎጂ ተሕዋስያንን ሊያስተላልፉብህ ይችላሉ።

መከላከያው፦ በሽታ ተሸካሚ ነፍሳት በሚበዙበት ወቅት ቤት ውስጥ በመሆን አሊያም ደግሞ ሱሪና ረጅም እጅጌ ያላቸው ልብሶችን በመልበስ ከእነዚህ ነፍሳት ራስህን መከላከል ትችላለህ። ስትተኛ አጎበር አድርግ፤ እንዲሁም የነፍሳት መከላከያ ተጠቀም። የወባ ትንኞች የሚራቡት ውኃ በሚያቁሩ ቦታዎች ላይ ስለሆነ እንዲህ ያሉ ቦታዎችን አጽዳ።c

4 እንስሳት

አደጋው፦ በእንስሳት ውስጥ ሲኖሩ ምንም ጉዳት የማያስከትሉ አንዳንድ ተሕዋስያን በሰዎች ላይ በሽታ ሊያመጡ ይችላሉ። የቤት እንስሳን ጨምሮ ማንኛውም እንስሳ ከነከሰህ ወይም ከቧጨረህ አሊያም ዓይነ ምድሩን ከነካህ ለበሽታ ልትጋለጥ ትችላለህ።

መከላከያው፦ አንዳንድ ሰዎች ከእንስሳት ጋር የሚኖራቸውን ንክኪ ለመቀነስ ሲሉ እንስሳቱ ከቤት ውጭ እንዲኖሩ ያደርጋሉ። አንድ የቤት እንስሳ ከነካህ በኋላ እጅህን በሳሙና ታጠብ፤ የዱር እንስሳትን ደግሞ ጨርሶ አትንካ። በአንድ እንስሳ ከተነከስክ ወይም ከተቧጨርክ ቁስሉን በሚገባ ማጠብ እንዲሁም ሐኪም ማማከር አለብህ።d

5 ሰዎች

አደጋው፦ አንዳንድ ጀርሞች አንድ ሰው ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ በሚወጡ ጥቃቅን ጠብታዎች አማካኝነት ወደ ሰውነትህ ሊገቡ ይችላሉ። በመተቃቀፍ፣ በመጨባበጥ ወይም በሌላ ዓይነት የቆዳ ንክኪም ጀርሞች ሊተላለፉ ይችላሉ። በተጨማሪም ረቂቅ ተሕዋስያን በበር መዝጊያ፣ በደረጃ እጀታ፣ በስልክ፣ በሪሞት ኮንትሮል ወይም በኮምፒውተር ስክሪንና ኪቦርድ ላይ ተጣብቀው ሊቆዩ ይችላሉ።

መከላከያው፦ እንደ ጺም መላጫ፣ የጥርስ ብሩሽ ወይም ፎጣ ያሉ የግል ዕቃዎችህን ለሌሎች ሰዎች አታውስ። የእንስሳትን ወይም የሰዎችን ደም ወይም ደም ያለባቸውን የሰውነት ፈሳሾች እንዳትነካ ተጠንቀቅ። እንዲሁም እጅን አዘውትሮ በሚገባ መታጠብ ያለውን ጥቅም አቅልለህ አትመልከት። እንዲያውም በሽታ እንዳይዛመት ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ይህ ሳይሆን አይቀርም።

የምትችል ከሆነ ስትታመም ከቤት አትውጣ። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል፣ ስታስል ወይም ስታስነጥስ አፍህን በእጅህ ከመሸፈን ይልቅ በሶፍት ወይም በእጅጌህ ብትሸፍን የተሻለ እንደሆነ ይናገራል።

አንድ ጥንታዊ ጥቅስ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) በእርግጥም ይህ ምክር አደገኛ በሽታዎች በተስፋፉበት በዛሬው ጊዜ በጣም ጠቃሚ ነው! ስለሆነም በአካባቢህ ወደሚገኙ የጤና ተቋማት በመሄድ እውቀት ለመቅሰም ሞክር፤ እንዲሁም ለንጽሕና ትኩረት በመስጠት ራስህን ከአደጋ ጠብቅ። መከላከያህን በማጠናከር በበሽታ የምትያዝበትን አጋጣሚ መቀነስ ትችላለህ!

a የዓለም የጤና ድርጅት በቤት ውስጥ ውኃን ማጣራት የሚቻልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ጠቁሟል፤ ከእነዚህ መካከል ክሎሪን መጠቀም፣ በፀሐይ ብርሃን ተጠቅሞ ውኃን ማጣራት፣ ማፍላት እንዲሁም የውኃ ማጣሪያ መጠቀም ይገኙበታል።

b ከምግብ ንጽሕና ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሰኔ 2012 ንቁ! ከገጽ 3-9⁠ን ተመልከት።

c ወባን መከላከል ስለሚቻልባቸው ዘዴዎች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የሐምሌ 2015 ንቁ! ገጽ 14-15⁠ን ተመልከት።

d መርዝ ባላቸው እንስሳት ከተነደፍክ አብዛኛውን ጊዜ አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልግሃል።

ወረርሽኝ ሲከሰት ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

አንዲት ሴት እጇን ስትታጠብ

በ2014 በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ቫይረስ በፍጥነት ተሰራጭቶ የነበረ ሲሆን ይህም በዓለም ዙሪያ ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር። በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ስለ በሽታው መረጃ ለመስጠት ዘመቻ አካሂደው ነበር፤ በርካታ ሰዎች ከዚህ ዘመቻ ጥቅም አግኝተዋል። የይሖዋ ምሥክሮችን ተወካዮች፣ በወረርሽኙ ወቅት ምን እንዳደረጉ ጠይቀናቸው ነበር፦

  • ትምህርት ሲሰጥ

    ሰዎች የወረርሽኙን አደገኝነት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ምን አደረጋችሁ?

    ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ትምህርት በመስጠት ሰዎች የሚሰማቸውን ፍርሃትና ግራ መጋባት ለማስወገድ ሞክረናል፤ እንዲሁም ቫይረሱ የሚሰራጨውና በሽታውን መከላከል የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ማብራሪያ ሰጥተናል።

  • እጅ መታጠብ

    የይሖዋ ምሥክሮች ምን እርምጃ ወስደዋል?

    ወደምንሰበሰብባቸው ቦታዎች የሚመጡትን ሰዎች የሙቀት መጠን ለመለካት የኢንፍራሬድ ሙቀት መለኪያዎችን እንጠቀም ነበር። ሁሉም ሰዎች እንደ መጨባበጥና መተቃቀፍ ያሉ አላስፈላጊ ንክኪዎችን ላለማድረግ ይጠነቀቁ እንዲሁም በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ እጃቸውን ይታጠቡ ነበር። በአካባቢው በሚገኙ ማዕከላዊ ቦታዎች ላይ በውኃ የተበረዘ በረኪና የሚገኝባቸው የእጅ መታጠቢያ ቦታዎች ተዘጋጅተው ነበር።

  • ቤት ውስጥ ያለ ስልክ

    ሕዝባዊ ስብሰባችሁንና መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራችሁን መቀጠል የቻላችሁት እንዴት ነበር?

    መንግሥት በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ ስላዘዘ በእነዚህ ቦታዎች ለጊዜው ሕዝባዊ ስብሰባ ተቋርጦ ነበር። እንዲህ ባሉ አካባቢዎች ቤተሰቦች አንድ ላይ በመሆን ቤታቸው ውስጥ አምልኳቸውን አከናውነዋል። አንዳንዶች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች ለማስተማር በስልክ ይጠቀሙ ነበር፤ ይህም አካላዊ ንክኪን ለመቀነስ ይረዳል።

  • የቀን መቁጠሪያ

    አንድ ሰው የበሽታው ምልክት ከታየበት ምን ታደርጋላችሁ?

    ለሚመለከታቸው አካላት እናሳውቅ ነበር። ኢቦላ ከያዘው ሰው ጋር ንክኪ የነበረው፣ በኢቦላ በሽታ በሞተ ሰው ቀብር ላይ የተገኘ እንዲሁም የበሽታው ምልክት የታየበት ሰው ለ21 ቀናት ከሰው ተገልሎ ይቆይ ነበር፤ ምክንያቱም በአብዛኛው የኢቦላ ቫይረስ ምልክት እስኪታይ 21 ቀናት ድረስ ሊፈጅ ይችላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ