የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g17 ቁጥር 4 ገጽ 3-7
  • ሥራ ይበዛብሃል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሥራ ይበዛብሃል?
  • ንቁ!—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • 1 ቤተሰባቸው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ለማቅረብ ያላቸው ፍላጎት
  • 2 ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት የሚደረግ ጥረት
  • 3 ሌሎች የሚጠብቁባቸውን ነገሮች ሁሉ ለማሟላት የሚያደርጉት ጥረት
  • 4 እርካታ ለማግኘትና አክብሮት ለማትረፍ ያላቸው ፍላጎት
  • ሚዛናዊ ሁን
  • 1 ግልጽ የሆነ ግብና አቋም ይኑርህ
  • 2 የመግዛት አባዜ እንዳይጠናወትህ ተጠንቀቅ
  • 3 ለሥራህ ገደብ አብጅለት
  • 4 ከቤተሰብህ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው
  • በሥራህ መደሰት ትችላለህ
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
    ንቁ!—2010
  • ከሥራህ እርካታን ማግኘት ትችላለህ
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • ሥራ ሲታክትህ መፍትሔው ምንድን ነው?
    ንቁ!—2014
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2017
g17 ቁጥር 4 ገጽ 3-7
አንድ ሰው በሥራ ቦታው አምሽቶ ሲሠራ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ሥራ ይበዛብሃል?

ሥራ እንደሚበዛብህ ይሰማሃል? ከሆነ እንደዚህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት “በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ሕይወታቸው በሩጫ የተሞላ ነው ማለት ይቻላል” ብሏል።

በ2015 በስምንት አገሮች በሚኖሩ ሠራተኞች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው አብዛኞቹ ሰዎች ሥራቸውና የቤተሰብ ሕይወታቸው ያስከተለባቸውን ኃላፊነት በተሟላ ሁኔታ መወጣት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ለዚህ ሁኔታ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል በሥራ ቦታም ሆነ በቤት ውስጥ የሚያከናውኗቸው ነገሮች መብዛት፣ ወጪያቸው እየጨመረ መሄዱና የሥራ ሰዓት መራዘም ይገኙባቸዋል። ለምሳሌ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ ቀን የሚሠሩ ሠራተኞች በሳምንት በአማካይ 47 ሰዓት ይሠራሉ። ከአምስት ሠራተኞች አንዱ ማለት ይቻላል፣ በሳምንት 60 ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ይሠራል።

ሠላሳ ስድስት አገሮችን ያካተተ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየው ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆኑት ሰዎች በእረፍት ጊዜያቸው ጭምር ያለመረጋጋትና የጥድፊያ ስሜት ይሰማቸዋል። ወላጆች የሚያወጡት የተጣበበ ፕሮግራም በልጆቻቸውም ላይ ውጥረት ሊያስከትል ይችላል።

ያለን ጊዜ ከሚፈቅድልን በላይ ለመሥራት የምንጣጣር ከሆነ ጊዜ በማጣት ከባድ ውጥረት ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ታዲያ ጊዜያችንን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንችል ይሆን? አመለካከታችን፣ የምናደርጋቸው ምርጫዎችም ሆኑ የምናወጣቸው ግቦች በዚህ ረገድ ምን ሚና ይጫወታሉ? በመጀመሪያ አንዳንዶች ብዙ ለመሥራት እንዲነሳሱ የሚያደርጓቸውን አራት ምክንያቶች እንመልከት።

1 ቤተሰባቸው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ለማቅረብ ያላቸው ፍላጎት

ጋሪ የተባለ አንድ አባት “በሳምንት ውስጥ ሰባቱንም ቀን የማሳልፈው በሥራ ነው” ብሏል። “እንዲህ የማደርገው ምንጊዜም ቢሆን ልጆቼ የተሻለ ነገር እንዲኖራቸው ስለምፈልግ ነው። እኔ ያልነበሩኝ ነገሮች እንዲኖሯቸው እፈልጋለሁ።” ወላጆች ይህን የሚያደርጉት በቅን ልቦና ተነሳስተው ቢሆንም ለየትኞቹ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ቆም ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለገንዘብና ለቁሳዊ ነገሮች እምብዛም ትኩረት የማይሰጡ አዋቂዎችም ሆኑ ልጆች ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ ከሚሰጡት ጋር ሲነጻጸሩ ይበልጥ ደስተኞችና ጤናሞች ናቸው።

ልጁ ቁሳዊ ነገሮች ቢሟሉለትም ደስተኛ መሆን አልቻለም

ለቁሳዊ ነገሮች ቅድሚያ የሚሰጡ ወላጆች ያሏቸው ልጆች የሌሎች ልጆችን ያህል ደስተኞች አይደሉም

አንዳንድ ወላጆች የልጆቻቸው የወደፊት ሕይወት የተደላደለ እንዲሆን ለማድረግ ሲሉ ራሳቸውንም ሆነ ልጆቻቸውን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ያስጠምዳሉ። በዚህ የተነሳ የወላጆቹም ሆነ የልጆቻቸው ሕይወት ውጥረት የበዛበት ይሆናል።

2 ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት የሚደረግ ጥረት

የንግድ ማስታወቂያዎች በየጊዜው ለገበያ የሚቀርቡትን አዳዲስ ምርቶች ካልገዛን ትልቅ ነገር እንደቀረብን ሆኖ እንዲሰማን ለማድረግ ይሞክራሉ። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት ሸማቾች ባላቸው ጥቂት ጊዜ ውስጥ “ምን እንደሚገዙ ወይም ምን እንደሚያዩ አሊያም ምን እንደሚበሉ ለመወሰን ስለሚቸገሩ የሸቀጦች መብዛት ጊዜያቸውን ይበልጥ አጣቦባቸዋል” ብሏል።

በ1930 አንድ እውቅ ኢኮኖሚስት ‘ቴክኖሎጂ እያደገ ሲሄድ ሠራተኞች የበለጠ ትርፍ ጊዜ ይኖራቸዋል’ በማለት ተንብዮ ነበር። ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው። ኒው ዮርከር የተባለው መጽሔት ጸሐፊ የሆኑት ኤሊዛቤት ኮልበርት እንደገለጹት ሰዎች “ማግኘት የሚፈልጓቸው ነገሮች እየበዙ ስለመጡ ቀደም ብለው ከሥራ ከመውጣት ይልቅ” ብዙ ሰዓት ይሠራሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃሉ።

3 ሌሎች የሚጠብቁባቸውን ነገሮች ሁሉ ለማሟላት የሚያደርጉት ጥረት

አንዳንድ ተቀጣሪዎች አሠሪዎቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ ብዙ ሰዓት ይሠራሉ። የሥራ ባልደረቦቻቸውም ተጨማሪ ሰዓት ካልሠሩ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ተጽዕኖ ያሳድሩባቸዋል። በተጨማሪም የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በመኖሩ ምክንያት ሰዎች ረጅም ሰዓት ለመሥራት ወይም በማንኛውም ሰዓት ሥራ ለመግባት ፈቃደኛ ይሆናሉ።

ከዚህም ሌላ ወላጆች የሌሎች ቤተሰቦችን የአኗኗር ዘይቤ በመኮረጅ እነሱም ሩጫ የበዛበት ሕይወት መምራት ሊጀምሩ ይችላሉ። ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ ካላደረጉ ልጆቻቸውን የሆነ ነገር እንዳስቀሩባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል።

4 እርካታ ለማግኘትና አክብሮት ለማትረፍ ያላቸው ፍላጎት

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ቲም “ሥራዬን በጣም ስለምወደው በትጋት እሠራ ነበር። ማንነቴን ማሳየት እንዳለብኝ ሆኖ ይሰማኝ ነበር” ብሏል።

ብዙ ሰዎች፣ ልክ እንደ ቲም በሥራ ሲወጠሩ ተፈላጊ እንደሆኑ ስለሚሰማቸው ለራሳቸው ያላቸው ግምት ይጨምራል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ኤሊዛቤት ኮልበርት “ሰዎች በሥራ መወጠራቸው በሌሎች ዘንድ አክብሮት እንዲያተርፉ ያስችላቸዋል” ብለዋል። አክለውም “ሥራ በበዛብህ መጠን ሰዎች ይበልጥ ተፈላጊ እንደሆንክ አድርገው ይመለከቱሃል” ሲሉ ገልጸዋል።

ሚዛናዊ ሁን

መጽሐፍ ቅዱስ ትጉዎች እንድንሆንና ጠንክረን እንድንሠራ ያበረታታናል። (ምሳሌ 13:4) ይሁንና ሚዛናዊ እንድንሆንም ይመክረናል። መክብብ 4:6 “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል” ይላል።

ሚዛናዊ የሆነ ሕይወት መምራት ለአእምሮም ሆነ ለአካላዊ ጤንነት ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ በሥራ የምናሳልፈውን ሰዓት መቀነስ እንችላለን? አዎ፣ እንችላለን። ይህን ለማድረግ የሚረዱ አራት ነጥቦችን እንመልከት፦

1 ግልጽ የሆነ ግብና አቋም ይኑርህ

ማንኛውም ሰው በቂ የሆነ ገንዘብ ማግኘት እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በቂ የሚባለው ምን ያህል ገንዘብ ነው? አንድን ሰው ተሳክቶለታል የሚያሰኘውስ ምንድን ነው? ስኬት የሚለካው በገቢ መጠን ወይም በቁሳዊ ንብረት ብቻ ነው? በእረፍት ወይም በመዝናኛ ብዙ ጊዜ ማሳለፍም ቢሆን ለሌሎች ነገሮች ጊዜ እንድናጣ በማድረግ ውጥረት ሊያስከትልብን ይችላል።

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቲም እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ አኗኗራችንን በሚገባ ከመረመርን በኋላ ኑሯችንን ለማቅለል ወሰንን። አሁን ያለንበትን ሁኔታና አዳዲሶቹን ግቦቻችንን የሚያሳይ ሰንጠረዥ ሠራን። ቀደም ሲል ያደረግናቸው ውሳኔዎች ምን ውጤት እንዳስከተሉብን እንዲሁም አዳዲሶቹ ግቦቻችን ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ተወያየን።”

2 የመግዛት አባዜ እንዳይጠናወትህ ተጠንቀቅ

መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዓይን አምሮትን’ እንድንቆጣጠር ይመክረናል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ማስታወቂያዎች እንዲህ ዓይነቱን ፍላጎት ይበልጥ ስለሚያነሳሱ ብዙ ሰዓት እንድንሠራ ወይም ብዙ ጊዜና ወጪ በሚጠይቁ መዝናኛዎች እንድንካፈል ሊያደርጉ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ማስታወቂያዎችን ማየታችን አይቀርም። ማስታወቂያዎችን የማየት ልማድ እንዳይጠናወተን መጠንቀቅ ግን እንችላለን። በተጨማሪም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ከምንፈልጋቸው ነገሮች መለየት መቻል ይኖርብናል።

ከዚህም ሌላ ጓደኞችህ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ እንደሚችሉ አስታውስ። ጓደኞችህ ቁሳዊ ነገሮችን የሚያሳድዱ ከሆኑ ወይም ስኬትን የሚለኩት በቁሳዊ ነገሮች ከሆነ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ቅድሚያ የሚሰጡ ጓደኞችን ብትመርጥ የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል።—ምሳሌ 13:20

3 ለሥራህ ገደብ አብጅለት

ስለ ሥራችሁም ሆነ ቅድሚያ ስለምትሰጧቸው ነገሮች ከአሠሪያችሁ ጋር ተነጋገሩ። ከሥራችሁ ውጭ የምታሳልፉት ጊዜ መኖሩ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማችሁ ሊያደርጋችሁ አይገባም። ወርክ ቱ ሊቭ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ለሥራቸው ገደብ በማበጀት በቤታቸው ጊዜ የሚያሳልፉ ወይም እረፍት የሚወስዱ ሰዎች አንድ የሚገነዘቡት ሐቅ አለ፦ ሥራ ባለመግባታቸው የሚፈጠር ቀውስ የለም።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጋሪ የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንደማይከብደው ስለተሰማው የሥራ ሰዓቱን ለመቀነስ ወሰነ። እንዲህ ብሏል፦ “አኗኗራችንን ቀለል እንድናደርግ ለቤተሰቤ ሐሳብ አቀረብኩ። ከዚያም ይህን ለማድረግ የሚያስችሉንን እርምጃዎች መውሰድ ጀመርን። በተጨማሪም በሳምንት ውስጥ ሥራ የምገባባቸውን ቀናት መቀነስ እንደምፈልግ ለአሠሪዬ ነገርኩት፤ እሱም በሐሳቤ ተስማማ።”

4 ከቤተሰብህ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው

ባሎችና ሚስቶች አብረው ጊዜ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል፤ ልጆችም ከወላጆቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፋቸው አስፈላጊ ነው። ስለዚህ በሥራ የተወጠሩ ቤተሰቦች የሚከተሉትን የአኗኗር ዘይቤ ለመኮረጅ አትሞክሩ። ጋሪ “አረፍ የምትሉበትና የምትዝናኑበት ጊዜ ይኑራችሁ። ያን ያህል ቅድሚያ ሊሰጣቸው በማይገቡ ነገሮች ራሳችሁን አታስጠምዱ” የሚል ምክር ሰጥቷል።

ቤተሰባችሁ አንድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ ቴሌቪዥን፣ ሞባይል ስልክ ወይም ሌሎች ነገሮች ከቤተሰባችሁ አባላት ጋር የምታሳልፉትን ጊዜ እንዲሻሙባችሁ አትፍቀዱ። በቀን ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ አብራችሁ ለመመገብ ጥረት አድርጉ፤ የምግብ ሰዓቱን ከቤተሰባችሁ አባላት ጋር ለመጫወት ተጠቀሙበት። ወላጆች ይህን ምክር ተግባራዊ ካደረጉ ልጆቻቸው ይበልጥ ደስተኛ ይሆናሉ፤ በትምህርታቸውም የተሻለ ውጤት ያገኛሉ።

የአንድ ቤተሰብ አባላት በምግብ ሰዓት እርስ በርስ ሲጨዋወቱ

የምግብ ሰዓታችሁን ከቤተሰባችሁ አባላት ጋር ለመጫወት ተጠቀሙበት

በመሆኑም ‘በሕይወቴ ማግኘት የምፈልገው ነገር ምንድን ነው? ለቤተሰቤስ የምመኘው ነገር ምንድን ነው?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ከፈለጋችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ቅድሚያ ስጡ።

ቴክኖሎጂ ውጥረት ሊፈጥር ይችላል?

አንዲት እናት ልቧ ያለው ሞባይል ስልኳ ላይ ስለሆነ ለልጇ ተገቢውን ትኩረት መስጠት አልቻለችም

ዘመናዊ ሞባይል ስልኮችና ታብሌቶች ጊዜያችንን በመሻማት ውጥረት ይፈጥሩብናል ወይስ ጊዜ ለመቆጠብ ይረዱናል? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ በአጠቃቀማችን ላይ የተመካ ነው።

በሥራ ቦታ፦ ሞባይል ስልኮችና ታብሌቶች ሠራተኞች በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉበት አጋጣሚ ይፈጥሩላቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ዘመናዊ መሣሪያዎች መኖራቸው አሠሪዎች በማንኛውም ሰዓት ሠራተኞቻቸውን ማግኘት እንደሚችሉ እንዲሰማቸው ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ በሠራተኞቹ ላይ ውጥረት ሊያስከትል ይችላል።

በቤት ውስጥ፦ ሞባይል ስልኮች ቤተሰቦች ሁኔታዎችን በቀላሉ በማመቻቸት አንድን ነገር በጋራ ማከናወን እንዲችሉ ስለሚረዷቸው ጊዜ በመቆጠብ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ መሣሪያዎች የቤተሰቡን ጊዜ ሊሻሙም ይችላሉ። ወላጆች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ተጠምደው ለልጆቻቸው ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጡ ሊቀሩ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ የልጆቹን ስሜት ሊጎዳና የባሕርይ ችግር ሊያስከትልባቸው እንደሚችል አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ