የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g17 ቁጥር 6 ገጽ 12-13
  • አልሃዘን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አልሃዘን
  • ንቁ!—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • የአባይን ወንዝ መገደብ
  • ቡክ ኦቭ ኦፕቲክስ የተባለው መጽሐፍ
  • ጥንታዊ ካሜራ
  • ሳይንሳዊው ዘዴ
ንቁ!—2017
g17 ቁጥር 6 ገጽ 12-13

የታሪክ መስኮት

አልሃዘን

አልሃዘን

አቡ አሊ አል-ሃሰን ኢብን አል-ሃይታም ስለተባለው ሰው ከዚህ በፊት ሰምተህ አታውቅ ይሆናል። በምዕራቡ ዓለም የሚታወቀው አልሃዘን በሚለው ስም ሲሆን ይህ ስም የተወሰደው አል-ሃሰን ከሚለው የአረብኛ ስሙ የላቲን አጠራር ነው። ያም ሆነ ይህ፣ አልሃዘን በሕይወቱ ከሠራቸው ሥራዎች ተጠቃሚ እንደሆንክ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ግለሰብ “በሳይንስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸውና ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩ ሰዎች መካከል አንዱ” እንደሆነ ይነገርለታል።

አጭር መረጃ

  • አልሃዘን ምርምር በሚያደርግበት ጊዜ የተከተላቸው ዘዴዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገባቸው ከመሆናቸው የተነሳ “የዓለም የመጀመሪያው እውነተኛ ሳይንቲስት” ተብሏል።

  • ዘመናዊው የፎቶግራፍ ጥበብ የተመሠረተባቸውን መሠረታዊ ሕጎች ለይቶ አሳውቋል።

  • በሌንስ ላይ ያደረገው ምርምር ለመነጽር፣ ለአጉሊ መነጽርና ለቴሌስኮፕ መፈልሰፍ መነሻ ሆኗል።

አልሃዘን የተወለደው በ965 ዓ.ም. ሲሆን የትውልድ ቦታውም በአሁኗ ኢራቅ ውስጥ የምትገኘው ባስራ የተባለች ከተማ ናት። በሥነ ፈለክ፣ በኬሚስትሪ፣ በሒሳብ፣ በሕክምና፣ በሙዚቃ፣ በሥነ ብርሃን፣ በፊዚክስና በሥነ ግጥም መስኮች ጥናት አድርጓል። ለዚህ ግለሰብ አመስጋኝ የሆንነው በተለይ በየትኞቹ መስኮች ላበረከተው አስተዋጽኦ ነው?

የአባይን ወንዝ መገደብ

ከአልሃዘን ጋር በተያያዘ ለረጅም ጊዜ ሲነገር የቆየ አንድ ታሪክ አለ። ታሪኩ አልሃዘን የአባይን ወንዝ ፍሰት ለመቆጣጠር ስላወጣው ዕቅድ የሚገልጽ ነው፤ አልሃዘን ይህን ዕቅድ ያወጣው በ1902 አስዋን ላይ የአባይ ወንዝ ግድብ ከመሠራቱ ከ1,000 ዓመታት ገደማ በፊት ነው።

ታሪኩ እንደሚገልጸው አልሃዘን የአባይን ወንዝ በመገደብ በግብፅ ምድር ላይ ይከሰት የነበረውን የጎርፍና የድርቅ መፈራረቅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማስወገድ ትልቅ ራእይ ነበረው። የካይሮ ገዢ የነበረው አል-ሐኪም የተባለው ከሊፋ ይህን ሐሳብ ሲሰማ አልሃዘን ወደ ግብፅ መጥቶ ግድቡን እንዲሠራ ግብዣ አቀረበለት። ሆኖም አልሃዘን ግብፅ ሄዶ ወንዙን በገዛ ዓይኑ ሲመለከት ይህ ፈጽሞ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ተገነዘበ። በተለዋዋጭ ባሕርይው የሚታወቀው ከሊፋ አል-ሐኪም የሚያደርስበትን ቅጣት ስለፈራ ይህ ገዢ እስከሞተበት እስከ 1021 ድረስ ለ11 ዓመታት እንደ እብድ ሆኖ ኖረ። የአእምሮ በሽተኛ ነው በሚል በአንድ ቦታ ተገድቦ እንዲቆይ በተደረገባቸው ዓመታት ውስጥ ሌሎች ምርምሮችን የሚያደርግበት ሰፊ ጊዜ አግኝቷል።

ቡክ ኦቭ ኦፕቲክስ የተባለው መጽሐፍ

አልሃዘን በተለቀቀበት ወቅት ቡክ ኦቭ ኦፕቲክስ የተባለውን ባለ ሰባት ጥራዝ መጽሐፉን ወደማጠናቀቁ ደርሶ ነበር፤ ይህ መጽሐፍ “በፊዚክስ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ” እንደሆነ ይነገርለታል። በዚህ የጽሑፍ ሥራው ላይ በብርሃን ውስጥ የሚገኙት ቀለማት የሚነጣጠሉበትን መንገድ፣ ብርሃን ከመስተዋት ላይ ተንጸባርቆ የሚመለስበትን መንገድና ከአንድ የብርሃን አስተላላፊ ወደ ሌላው በሚያልፍበት ጊዜ አቅጣጫውን የሚቀይርበትን መንገድ ጨምሮ ብርሃን ስላሉት የተለያዩ ባሕርያት ያደረጋቸውን ምርምሮች አብራርቷል። በተጨማሪም የምናየው ምስል በአእምሯችን ውስጥ ስለሚተረጎምበት መንገድ፣ ስለ ዓይናችንና ዓይናችን ስለሚሠራበት መንገድ አጥንቷል።

በ13ኛው መቶ ዘመን የአልሃዘን የጽሑፍ ሥራ ከአረብኛ ወደ ላቲን የተተረጎመ ሲሆን ከዚያ በኋላ ባሉት መቶ ዓመታት የአውሮፓ ምሁራን በዋቢነት ሲጠቅሱት ቆይተዋል። አልሃዘን በሌንስ ባሕርያት ላይ ያደረገው ጥናት ለአውሮፓውያን መነጽር ሠሪዎች እንደ መነሻ ሆኗል፤ እነዚህ ሰዎች አንዱን ሌንስ ከሌላው ትይዩ አድርገው በመያዝ አጉሊ መነጽርና ማይክሮስኮፕ ሊፈለስፉ ችለዋል።

ጥንታዊ ካሜራ

አልሃዘን በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሊባል የሚችለውን ካሜራ ኦብስኩራ በመሥራት ለፎቶግራፍ ጥበብ መነሻ የሆነውን መሠረታዊ ሕግ አሳውቋል። ይህ ሣጥን መሰል መሣሪያ ውስጡ ጨለማ ሲሆን የብርሃን ጨረር ሣጥኑ ላይ ባለ ጠባብ ቀዳዳ በኩል አልፎ ወደ ውስጥ ሲገባ ከውጭ ያለው ነገር ምስል በሣጥኑ ውስጠኛ ግድግዳ ላይ ተገልብጦ ይታያል።

ካሜራ ኦብስኩራ

አልሃዘን በታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ የሚገመተውን ካሜራ ኦብስኩራ ሠርቷል

በ1800ዎቹ ምስል ይዘው ማስቀረት የሚችሉ ሰሌዳዎች ካሜራ ኦብስኩራ ውስጥ የተጨመሩ ሲሆን ይህም መሣሪያው ምስሎችን ቀርጾ ማስቀረት እንዲችል አድርጓል። በውጤቱም ካሜራ ሊፈለሰፍ ችሏል። ሁሉም ዘመናዊ ካሜራዎች ሌላው ቀርቶ ዓይናችን ጭምር የሚሠራበት መንገድ ከካሜራ ኦብስኩራ ጋር ተመሳሳይ ነው።a

ሳይንሳዊው ዘዴ

የአልሃዘንን ሥራዎች ልዩ ከሚያደርጓቸው ገጽታዎች አንዱ በተፈጥሮ ክስተቶች ላይ ያደረጋቸው ጥናቶች ሥርዓት ባለውና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የተደረጉ መሆናቸው ነው። እሱ የተከተለው አካሄድ በዚያ ዘመን ጨርሶ ያልተለመደ ነበር። አልሃዘን ንድፈ ሐሳቦችን በሙከራ ለማረጋገጥ ጥረት ካደረጉ ቀደምት ተመራማሪዎች መካከል አንዱ ነው፤ በተጨማሪም ተቀባይነት አግኝተው የኖሩ ሐሳቦችም እንኳ በማስረጃ የተደገፉ እስካልሆኑ ድረስ በእነዚህ ሐሳቦች ላይ ጥያቄ ከማንሳት ወደኋላ አይልም ነበር።

የዘመናዊ ሳይንስ ዋነኛ መርሕ “የምታምነውን ነገር በማስረጃ አረጋግጥ!” በሚለው አባባል ሊጠቃለል ይችላል። አንዳንዶች አልሃዘንን “የዘመናዊው ሳይንሳዊ ዘዴ አባት” በማለት የሚጠሩት ለዚህ ነው። በእርግጥም ለአልሃዘን አመስጋኝ የምንሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ።

a በ17ኛው መቶ ዘመን ዮሐንስ ኬፕለር ማብራሪያ እስከሰጠበት ጊዜ ድረስ የካሜራ ኦብስኩራና የዓይን ተመሳሳይነት በምዕራቡ ዓለም እምብዛም አይታወቅም ነበር።

‘ሳይንሳዊ ምርምር የምናደርግበትን ዘዴ አስተምሮናል’

ጂም አል-ካህሊሊ የተባሉ ጸሐፊ፣ የአልሃዘን ታላቅነት “ሥር ነቀል በሆነ አንድ አስገራሚ ግኝት የመጣ አይደለም። . . . እሱን ልዩ የሚያደርገው በአጠቃላይ ሳይንሳዊ ምርምር የምናደርግበትን ዘዴ ያስተማረን መሆኑ ነው” ብለዋል። ቡክ ኦቭ ኦፕቲክስ የተባለው የአልሃዘን መጽሐፍ “እውነተኛ የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ” ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህ መጽሐፍ አልሃዘን ያደረጋቸውን ምርምሮች፣ የተጠቀመባቸውን መሣሪያዎች፣ የወሰዳቸውን ልኮችና ያገኛቸውን ውጤቶች በዝርዝርና በትክክል ያብራራል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ