-
ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?ንቁ!—2017 | ቁጥር 6
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?
ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?
ሳይንቲስቶች በ2017 መጀመሪያ ላይ አንድ አስደንጋጭ መግለጫ አውጥተው ነበር። በጥር ወር አንድ የሳይንቲስቶች ቡድን ዓለማችን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጥፋት ወደሚከሰትበት ጊዜ ይበልጥ እንደቀረበ አስታወቀ። ሳይንቲስቶቹ ዓለም አቀፍ ጥፋት ወደሚከሰትበት ጊዜ ምን ያህል እንደቀረብን የሚያሳየውን ምሳሌያዊ የጥፋት ቀን ሰዓት 30 ሴኮንድ ወደፊት እንዲሄድ አድርገውታል። በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰዓት እኩለ ሌሊት ሊል የቀረው ሁለት ደቂቃ ተኩል ብቻ ነው፤ ዓለማችን ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ሲታይ ለዓለም አቀፍ ጥፋት ይህን ያህል የተቃረበበት ጊዜ የለም!
ሳይንቲስቶች ዓለማችን በተለምዶ የዓለም መጨረሻ ተብሎ ለሚጠራው ጊዜ ምን ያህል እንደተቃረበ ለማወቅ በ2018 ድጋሚ ግምገማ ለማካሄድ እቅድ ይዘዋል። የጥፋትን ቀን የሚያመለክተው ሰዓት አሁንም ከዚህ በፊት ተከስቶ የማያውቅ ታላቅ ጥፋት መከሰቱ እንደማይቀር ይጠቁም ይሆን? አንተ ምን ይመስልሃል? ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም? ምናልባት ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ መስጠት ይከብድህ ይሆናል። በመስኩ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎችም እንኳ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው። በዓለማችን ላይ ጥፋት መከሰቱ አይቀርም ብለው የሚያምኑት ሁሉም አይደሉም።
እንዲያውም ወደፊት ብሩህ ጊዜ እንደሚመጣ የሚያምኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች የሰው ዘር ተጠራርጎ እንደማይጠፋና ፕላኔታችን ለዘላለም እንደምትኖር እንዲሁም የኑሮ ሁኔታችን እንደሚሻሻል የሚጠቁም ማስረጃ እንዳላቸው ይናገራሉ። የሚያቀርቡት ማስረጃ አሳማኝ ነው? በእርግጥ ዓለማችን ተስፋ አለው ወይስ የለውም?
-
-
መልሱ የሚገኘው ከየት ነው?ንቁ!—2017 | ቁጥር 6
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?
መልሱ የሚገኘው ከየት ነው?
ከየአቅጣጫው የሚሰማው መጥፎ ዜና አስፈርቶህ ምናልባትም ሽብር ለቆብህ ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በ2014 በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት የነበሩት ባራክ ኦባማ፣ በዜና ማሰራጫዎች በሚተላለፉት መጥፎ ዜናዎች ምክንያት በርካታ ሰዎች “ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት . . . እየተሽከረከረ ከመሆኑ የተነሳ ማንም ሊቆጣጠረው አይችልም” የሚል መደምደሚያ ላይ እንደደረሱ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ይህን ሐሳብ ከተናገሩ ብዙም ሳይቆይ ፕሬዚደንቱ በዓለማችን ላይ ያሉትን አብዛኞቹን ችግሮች ለማስተካከል ስለተያዙት ዕቅዶች በጋለ ስሜት ተናግረዋል። መንግሥት የወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች “የምሥራች” እንደሆኑ ከገለጹ በኋላ “ተስፋ አለኝ” እንዲሁም “ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ የሆነ ነገር ይታየኛል” ብለዋል። በሌላ አነጋገር ሰዎች በበጎ ዓላማ ተነሳስተው የሚያደርጉት ጥረት የዓለምን ሁኔታዎች ለመቆጣጠርና ዓለም አቀፋዊ ጥፋት እንዳይደርስ ለመከላከል እንደሚያስችል መጠቆማቸው ነው።
በርካታ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንዲህ ያለ ብሩህ አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ አንዳንዶች በቴክኖሎጂ መስክ የሚደረገው ፈጣን እድገት የዓለምን ችግሮች ያስወግዳል ብለው ስለሚያስቡ ተስፋቸውን በሳይንስ ላይ ይጥላሉ። ስለ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያጠኑ አንድ ባለሙያ በ2030 “ቴክኖሎጂያችን አሁን ካለው አቅም አንድ ሺህ እጥፍ፣ በ2045 ደግሞ አንድ ሚሊዮን እጥፍ ያድጋል” በማለት በእርግጠኝነት ተንብየዋል። አክለውም “በጣም ጥሩ እድገት እያደረግን ነው። የተጋረጡብን ችግሮች የአሁኑን ያህል ከባድ ሆነው ባያውቁም ችግሮቹን የመፍታት አቅማችን ከችግሮቹ ክብደት አልፎ ሄዷል” ብለዋል።
ለመሆኑ ዓለም የሚገኝበት ሁኔታ ምን ያህል የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል? በእርግጥ የሰው ዘር ዓለም አቀፋዊ ጥፋት ተጋርጦበታል? አንዳንድ ሳይንቲስቶችና ፖለቲከኞች ተስፋ ያዘለ መልእክት ቢያውጁም የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ስጋት የሚያድርባቸው በርካታ ሰዎች አሉ። ምክንያታቸው ምንድን ነው?
ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች የኑክሌር መሣሪያዎችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። እንዲያውም አንዳንድ ማን አለብኝ ባይ መሪዎች የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕጎችን ከቁብ አይቆጥሯቸውም። ቀድሞውኑም ቢሆን የኑክሌር መሣሪያ ያላቸው አገሮች አሮጌዎቹን ይበልጥ አጥፊ በሆኑ አዳዲስ ቦምቦች ለመተካት ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ናቸው። ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ያልነበሯቸው አገሮች ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በጣም ብዙ ሕዝብ የማጥፋት አቅም ያላቸው የጦር መሣሪያዎች ባለቤት ሆነዋል።
መንግሥታት የኑክሌር ጦርነት ለማካሄድ ከምንጊዜውም በላይ የታጠቁ መሆናቸው ዓለማችን “በሰላሙ” ጊዜም እንኳ በጣም አደገኛ ስፍራ እንዲሆን አድርጓል። ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተባለው መጽሔት “በተለይ ደግሞ የማንም ሰው ቁጥጥርና ትእዛዝ ሳያስፈልጋቸው የመጨረሻ ውሳኔ የሚያደርጉ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያዝዙ ገዳይ መሣሪያዎች ዓለማችንን ከፍተኛ ስጋት ላይ ይጥላሉ” በማለት አስጠንቅቋል።
በጤናችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት። ጥሩ ጤንነት እንዲኖረን በማስቻል ረገድ ሳይንስ ሊያደርግልን የሚችለው ነገር በጣም ውስን ነው። ከፍተኛ የደም ግፊትን፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን፣ የአየር ብክለትንና ዕፅን ያላግባብ መጠቀምን የመሳሰሉ ለሕመም ሊዳርጉ የሚችሉ ችግሮች በእጅጉ እየተስፋፉ ነው። እንደ ካንሰር፣ ስኳር በሽታ እንዲሁም የልብና የደም ዝውውር ችግር ባሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚሞቱት ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ ነው። በተጨማሪም በአእምሮ ሕመምና በሌሎች በሽታዎች የሚሠቃዩ በርካታ ሰዎች አሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንደ ኢቦላና ዚካ ቫይረስ ያሉ ያልተጠበቁ ወረርሽኞች ከባድ ጉዳት ሲያስከትሉ ተመልክተናል። ይህን ሁሉ ስንመለከት በሽታ ከሰዎች ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ እንገነዘባለን፤ ሙሉ በሙሉ የሚወገድበት ጊዜ ይመጣል የሚል የተስፋ ጭላንጭልም አይታይም!
የሰው ልጆች በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት። ፋብሪካዎች የምድርን ከባቢ አየር መበከላቸውን ቀጥለዋል። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተበከለ አየር በመሳባቸው ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ።
ግለሰቦች፣ በርካታ ማኅበረሰቦች እንዲሁም መንግሥታዊ ድርጅቶች ፍሳሾችን፣ ከሕክምናና ከግብርና ምርቶች የሚወጡ ዝቃጮችን፣ ፕላስቲኮችንና ሌሎች በካይ ነገሮችን ውቅያኖስ ውስጥ መድፋታቸውን አላቆሙም። “እነዚህ መርዛማ ዝቃጮች የባሕር እንስሳትንም ሆነ ዕፀዋትን እንዲሁም የተበከሉትን የባሕር እንስሳት የሚመገቡትን ሰዎች ይመርዛሉ” በማለት ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ማሪን ሳይንስ ያብራራል።
በምድራችን ላይ ያለው ጨዋማ ያልሆነ ውኃ መጠንም በእጅጉ እየቀነሰ ነው። ብሪታንያዊው የሳይንስ ጸሐፊ ሮቢን ማኪ “ዓለማችን ሁሉንም የምድር ክፍሎች የሚነካ የውኃ ችግር ተጋርጦበታል” በማለት አስጠንቅቀዋል። ፖለቲከኞች የውኃ እጥረት በዋነኝነት ሰው ሠራሽ ችግር እንደሆነና በዚህም የተነሳ ምድራችን ከባድ አደጋ ላይ እንደወደቀች አምነው ይቀበላሉ።
ተፈጥሮ በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት። እንደ ማዕበል፣ ከባድ አውሎ ንፋስና የምድር ነውጥ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች አውዳሚ ለሆነ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ከፍተኛ ጉዳት ለሚያደርስ የመሬት መንሸራተትና ለሌሎች የተለያዩ ጥፋቶች መንስኤ ይሆናሉ። በእነዚህ የተፈጥሮ ኃይሎች የተነሳ የሚሞቱት ወይም ለከባድ ጉዳት የሚዳረጉት ሰዎች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ጨምሯል። ናሳ (ናሽናል ኤሮኖቲክስ ኤንድ ስፔስ አድሚኒስትሬሽን) ያወጣው ጥናት ወደፊት “እስካሁን ከተከሰቱት የበለጠ ኃይል ያላቸው ማዕበሎች፣ ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ የሙቀት ወጀቦች እንዲሁም ጎርፍና ድርቅ የሚፈራረቅባቸው ዑደቶች” የሚከሰቱበት አጋጣሚ እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቁሟል። ታዲያ ተፈጥሮ አንድ ቀን መላውን የሰው ዘር ጠራርጎ ያጠፋ ይሆን?
ሕልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሌሎች ሁኔታዎችም ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። ሆኖም በዛሬው ጊዜ እየተከሰቱ ያሉትን መጥፎ ነገሮች አንድ በአንድ በመመርመር የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አጥጋቢ መልስ ማግኘት አትችልም። አንዳንዶች ፖለቲከኞችና ሳይንቲስቶች የሚናገሩትን መስማትም ቢሆን ምንም ፋይዳ እንደሌለው ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ብዙ ሰዎች ከዓለም ሁኔታና ከወደፊቱ ጊዜ ጋር በተያያዘ ለሚነሱባቸው ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ ማግኘት ችለዋል። ይህን መልስ ማግኘት የቻሉት ከየት ነው?
-
-
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?ንቁ!—2017 | ቁጥር 6
-
-
ከጥፋት ቀን ሰዓት ጋር በተያያዘ የሚሰጡት መላ ምቶች ፍጻሜያቸውን ሊያገኙ አይችሉም፤ ምክንያቱም አምላክ ምድርንም ሆነ የሰው ልጆችን በተመለከተ ብሩህ ተስፋ ሰጥቷል
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ የሚገኝበት አሳሳቢ ሁኔታ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት ተነግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ወደፊት ብሩህ የሆነ ጊዜ እንደሚጠብቃቸውም ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የሚናገረውን ነገር ውድቅ ለማድረግ መቸኮል ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም ዝርዝር መረጃ የያዙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በአስደናቂ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።
ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተመልከት፦
“ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል።”—ማቴዎስ 24:7
“በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4
እነዚህ ትንቢቶች በአንዳንዶች አመለካከት ከቁጥጥር ውጭ የሆነውን ዓለም ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። በአንድ በኩል ሲታይ በእርግጥም ዓለማችን ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም የዓለም ሁኔታ ከሰው ልጆች ቁጥጥር ውጭ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው የሰው ልጆች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችል ጥበብም ሆነ አቅም የላቸውም። የሚከተሉት ጥቅሶች ይህን በግልጽ ያሳያሉ፦
“ለሰው ትክክለኛ መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።”—ምሳሌ 14:12
“ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።”—መክብብ 8:9
“[ሰው] አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።”—ኤርምያስ 10:23
የዓለም ሁኔታ በዚሁ እንዲቀጥል ከተተወ በምድራችን ላይ ዓለም አቀፍ ጥፋት የሚከሰትበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሁኔታ ፈጽሞ አይከሰትም! ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጣል፦
“[አምላክ] ምድርን በመሠረቶቿ ላይ መሠረታት፤ እሷም ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም።”—መዝሙር 104:5
“ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—መክብብ 1:4
“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
“በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:16
እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የማያሻማ መልስ ይሰጣሉ። የሰው ዘር በአየር ብክለት፣ በምግብና በውኃ እጦት ወይም በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት ከምድር ገጽ ተጠራርጎ አይጠፋም። በኑክሌር ፍንዳታም ቢሆን ይጠፋል ብለን የምንሰጋበት ምንም ምክንያት የለም። ለምን? ምክንያቱም የፕላኔታችን የወደፊት ዕጣ በአምላክ ቁጥጥር ሥር ነው። እርግጥ ነው፣ አምላክ ለሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል፤ ሆኖም ያደረጉት ውሳኔ የሚያስከትልባቸውን መዘዝ ማጨዳቸው አይቀርም። (ገላትያ 6:7) እንዲህ ሲባል ግን ዓለማችን ከሹፌሩ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነና ለከባድ አደጋ መዳረጉ እንደማይቀር ባቡር ሆኗል ማለት አይደለም። አምላክ ያስቀመጠው ድንበር ወይም ገደብ ስላለ የሰው ልጆች በራሳቸው ላይ ከልክ ያለፈ ጉዳት ሊያደርሱ አይችሉም።—መዝሙር 83:18፤ ዕብራውያን 4:13
ይሁን እንጂ አምላክ ከዚህም የበለጠ ነገር ያደርጋል። በዓለማችን ላይ “ብዙ ሰላም” እንደሚያሰፍን ቃል ገብቷል። (መዝሙር 37:11) በዚህ ርዕስ ውስጥ የተገለጹት ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቁ ትንቢቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በመማራቸው ካገኟቸው በርካታ አስደሳች ተስፋዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና የተለያየ ብሔር ያላቸው ወንዶችንና ሴቶችን ያካተተ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ ይሖዋ እንደሆነ የተገለጸውን እውነተኛውን አንድ አምላክ ያመልካሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ፍርሃት አያድርባቸውም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይላል፦ “ሰማያትን የፈጠረው፣ እውነተኛው አምላክ፣ ምድርን የሠራትና ያበጃት፣ አጽንቶም የመሠረታት፣ መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ ያልፈጠራት ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።’”—ኢሳይያስ 45:18
በዚህ ርዕስ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ምድርንና የሰው ልጆችን በተመለከተ የሚያስተምራቸውን አንዳንድ ትምህርቶች ተመልክተናል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለውን ብሮሹር ትምህርት 5 ተመልከት። ብሮሹሩን www.jw.org/am ላይ ማግኘት ትችላለህ
በተጨማሪም www.jw.org/am ላይ የሚገኘውን አምላክ ምድርን የፈጠረው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ መመልከት ትችላለህ (የሕትመት ውጤቶች > ቪዲዮዎች በሚለው ሥር ይገኛል)
-