የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bhs ምዕ. 11 ገጽ 116-123
  • መከራና ሥቃይ የበዛው ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መከራና ሥቃይ የበዛው ለምንድን ነው?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • በየመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንብብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መከራና ሥቃይ የበዛው ለምንድን ነው?
  • አምላክ መከራ እንዲደርስብን የፈቀደው ለምንድን ነው?
  • ይሖዋ ይህን ያህል ጊዜ የታገሠው ለምንድን ነው?
  • የመምረጥ ነፃነትህን የምትጠቀምበት እንዴት ነው?
  • ሰዎች ችግርና መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • አምላክ ለሰዎች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
ለተጨማሪ መረጃ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
bhs ምዕ. 11 ገጽ 116-123

ምዕራፍ አሥራ አንድ

መከራና ሥቃይ የበዛው ለምንድን ነው?

1, 2. ብዙ ሰዎች የትኛውን ጥያቄ ይጠይቃሉ?

ኃይለኛ ጎርፍ አንድን መንደር አወደመ። መሣሪያ የታጠቀ አንድ ሰው፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተኩስ ከፍቶ ብዙ ሰዎችን አቆሰለ፤ የሞቱ ሰዎችም አሉ። አምስት ልጆች ያሏት አንዲት እናት በካንሰር በሽታ ሕይወቷ አለፈ።

2 ብዙ ሰዎች እንዲህ ያሉ አደጋዎች ወይም አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲከሰቱ “ይህ ሁሉ መከራ የሚደርሰው ለምንድን ነው?” ብለው ይጠይቃሉ። ብዙዎች ዓለም በጥላቻና በመከራ የተሞላው ለምን እንደሆነ ግራ ይገባቸዋል። አንተስ እንዲህ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ?

3, 4. (ሀ) ዕንባቆም የትኞቹን ጥያቄዎች ጠይቋል? (ለ) ይሖዋ ምን መልስ ሰጠው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎችም እንኳ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን እንዳነሱ ይናገራል። ለምሳሌ ነቢዩ ዕንባቆም ይሖዋን እንዲህ ሲል ጠይቆት ነበር፦ “ለምን በደል ሲፈጸም እንዳይ ታደርገኛለህ? ጭቆናንስ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ የሚፈጸመው ለምንድን ነው? ጠብና ግጭትስ ለምን በዛ?”—ዕንባቆም 1:3

4 በዕንባቆም 2:2, 3 ላይ እንደተገለጸው፣ አምላክ ዕንባቆም ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጠ ከመሆኑም ሌላ ሁኔታውን እንደሚያስተካክል ቃል ገብቷል። ይሖዋ ሰዎችን በጣም ይወዳል። መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ ስለ እናንተ ያስባል” በማለት ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 5:7) እንዲያውም አምላክ መከራን እኛ ከምንጠላው በላይ ይጠላል። (ኢሳይያስ 55:8, 9) ታዲያ በዓለም ላይ መከራ የበዛው ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ እስቲ እንመልከት።

መከራና ሥቃይ የበዛው ለምንድን ነው?

5. አብዛኞቹ የሃይማኖት መሪዎች መከራን በተመለከተ ምን ይላሉ? መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል?

5 አብዛኛውን ጊዜ ፓስተሮች፣ ቄሶችና የሃይማኖት መሪዎች ‘በሰዎች ላይ መከራና ሥቃይ የሚደርሰው የአምላክ ፈቃድ ስለሆነ ነው’ ብለው ያስተምራሉ። አንዳንዶች ደግሞ አሳዛኝ ሁኔታዎችን ጨምሮ በሰዎች ላይ የሚደርሱትን ነገሮች በሙሉ አምላክ አስቀድሞ እንደወሰነና ይህ የሆነበትን ምክንያት ፈጽሞ መረዳት እንደማንችል ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ‘ሕፃናትም ሆኑ ትላልቅ ሰዎች የሚሞቱት አምላክ ከእሱ ጋር እንዲሆኑ ስለሚፈልግ ነው’ ይላሉ። ሆኖም ይህ እውነት አይደለም። በሰዎች ላይ መጥፎ ነገር የሚያመጣው ይሖዋ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!” በማለት ይናገራል።—ኢዮብ 34:10

6. ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ ያለውን መከራ ሁሉ ያመጣው አምላክ እንደሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

6 ብዙ ሰዎች ‘ምድርን የሚገዛው አምላክ ነው’ የሚል እምነት ስላላቸው በዓለም ላይ ያለውን መከራ ሁሉ ያመጣው አምላክ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና በምዕራፍ 3 ላይ እንደተመለከትነው የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።

7, 8. በዓለም ላይ መከራ የበዛው ለምንድን ነው?

7 መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:19) የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን አረመኔና ጨካኝ ነው። “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው። (ራእይ 12:9) ብዙዎች የሰይጣንን ባሕርይ እያንጸባረቁ ነው። ዓለም በውሸት፣ በጥላቻና በጭካኔ ሊሞላ የቻለበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

8 ይሁንና በዓለም ላይ መከራ የበዛው በዚህ ምክንያት ብቻ አይደለም። አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ካመፁ በኋላ ኃጢአትን ለልጆቻቸው አወረሱ። ሰዎች ኃጢአትን ስለወረሱ አንዳቸው ሌላውን ያሠቃያሉ። ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ሰዎች በልጠው መታየት ይፈልጋሉ። በመሆኑም እርስ በእርስ ይጋጫሉ፣ ይዋጋሉ እንዲሁም አንዳቸው ሌላውን ይጨቁናሉ። (መክብብ 4:1፤ 8:9) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎች “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።” (መክብብ 9:11) በመጥፎ ጊዜ የማይሆን ቦታ ላይ በመገኘታቸው ለአደጋ ይጋለጣሉ፤ ወይም መከራና ሥቃይ ይደርስባቸዋል።

9. አምላክ መከራን ያላስወገደበት በቂ ምክንያት አለው የምንለው ለምንድን ነው?

9 ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ መከራ አያመጣም። በዓለም ላይ ለሚካሄደው ጦርነት እንዲሁም በየቦታው ለሚፈጸመው ወንጀልና ግፍ ተጠያቂው አምላክ አይደለም። እንደ ምድር ነውጥ፣ አውሎ ነፋስና ጎርፍ የመሳሰሉ አደጋዎች እንዲከሰቱ የሚያደርገውም እሱ አይደለም። ይሁንና ‘ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስ ዝም ብሎ የሚያየው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አምላክ በጣም እንደሚያስብልን እናውቃለን፤ ይህን ማወቃችን ‘መከራን ያላስወገደበት በቂ ምክንያት አለው’ ብለን እንድንደመድም ያደርገናል።—1 ዮሐንስ 4:8

አምላክ መከራ እንዲደርስብን የፈቀደው ለምንድን ነው?

10. ሰይጣን ይሖዋን ምን ብሎ ከሶታል?

10 ዲያብሎስ በኤደን የአትክልት ስፍራ አዳምንና ሔዋንን አሳስቷቸዋል። ሰይጣን አምላክን ‘ክፉ ገዢ ነው’ ሲል ከሶታል። አዳምንና ሔዋንን ጥሩ የሆነ ነገር እንደከለከላቸው ተናግሯል። የአምላክ አገዛዝ እንደማያስፈልጋቸው እንዲሁም ከይሖዋ ይልቅ ለእሱ ቢገዙ እንደሚጠቀሙ ሊያሳምናቸው ፈልጎ ነበር።—ዘፍጥረት 3:2-5፤ ተጨማሪ ሐሳብ 27⁠ን ተመልከት።

11. ለየትኛው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርብናል?

11 አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ ዓመፁ። ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ተሰምቷቸዋል። ታዲያ ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን እንደተሳሳቱና ለእኛ የሚጠቅመውን የሚያውቀው እሱ እንደሆነ ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?

12, 13. (ሀ) ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ፣ ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዢ እንዲሆን እንዲሁም የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የፈቀደው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ወዲያውኑ አላጠፋቸውም። ከዚህ ይልቅ ልጆች እንዲወልዱ ፈቅዶላቸዋል። ይህም ልጆቻቸው የራሳቸውን ምርጫ እንዲያደርጉ በር ከፍቷል፤ ይሖዋ ለእሱ አለዚያም ለሰይጣን እንዲገዙ ምርጫ ሰጥቷቸዋል። የይሖዋ ዓላማ ምድር ፍጹም በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ነው፤ ዲያብሎስ ምንም ቢያደርግ የይሖዋ ዓላማ መፈጸሙ አይቀርም።—ዘፍጥረት 1:28፤ ኢሳይያስ 55:10, 11

13 ሰይጣን ይሖዋን የከሰሰው በሚሊዮን በሚቆጠሩ መላእክት ፊት ነው። (ኢዮብ 38:7፤ ዳንኤል 7:10) በመሆኑም ይሖዋ፣ ሰይጣን ያነሳው ክስ እውነት መሆን አለመሆኑ እንዲታይ በቂ ጊዜ ሰጥቷል። የሰው ልጆችም በሰይጣን አመራር ሥር ሆነው የራሳቸውን መስተዳድር በማቋቋም ያለአምላክ እርዳታ ስኬታማ መሆን ይችሉ እንደሆነ እንዲያሳዩ ጊዜ ሰጥቷል።

14. ይሖዋ ጊዜ መስጠቱ ምን ነገር እንዲረጋገጥ አድርጓል?

14 የሰው ልጆች በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ራሳቸውን ለማስተዳደር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ሰይጣን ውሸታም መሆኑ ተረጋግጧል። የሰው ልጆች ያለአምላክ እርዳታ ሊሳካላቸው አይችልም። ነቢዩ ኤርምያስ “ይሖዋ ሆይ፣ የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” በማለት ይህን በግልጽ ተናግሯል።—ኤርምያስ 10:23

ይሖዋ ይህን ያህል ጊዜ የታገሠው ለምንድን ነው?

15, 16. (ሀ) ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ ለረጅም ጊዜ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ሰይጣን ያስከተለውን ችግር ያላስተካከለው ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ፣ በሰው ልጆች ላይ ለረጅም ጊዜ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? መጥፎ ነገሮችን የማያስወግደው ለምንድን ነው? የሰይጣን አገዛዝ ለሰው ልጆች ጥቅም እንደማያስገኝ ለማረጋገጥ ጊዜ መስጠት አስፈልጓል። የሰው ልጆች የተለያዩ የአገዛዝ ሥርዓቶችን ቢሞክሩም ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ከፍተኛ እድገት ያደረጉ ቢሆንም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጦርነት በዝቷል፤ እንዲሁም የፍትሕ መጓደል፣ ድህነትና ወንጀል ተስፋፍቷል። ያለአምላክ እርዳታ ራሳችንን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር አንችልም።

16 ይሁንና ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ ሰይጣን ያስከተለውን ችግር ለማስተካከል አልሞከረም። እንዲህ ማድረግ የሰይጣንን አገዛዝ እንደመደገፍ ይቆጠራል፤ ይሖዋ ደግሞ እንዲህ እንደማያደርግ የታወቀ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ አሁን ያሉትን ችግሮች ቢያስተካክል፣ ሰይጣን እንዳለው የሰው ልጆች በተሳካ ሁኔታ ራሳቸውን ማስተዳደር እንደቻሉ አድርገው ያስቡ ነበር። ሆኖም ይህ ውሸት ነው፤ ይሖዋ ይህን ውሸት የሚደግፍ ነገር አያደርግም። ይሖዋ ፈጽሞ አይዋሽም።—ዕብራውያን 6:18

17, 18. ይሖዋ፣ ሰይጣን ያስከተለውን ጉዳት ለማስተካከል ምን እርምጃ ይወስዳል?

17 ይሖዋ፣ ሰይጣንና ሰዎች ማመፃቸው ያስከተለውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ ማስተካከል ይችላል? አዎ። አምላክ ማድረግ የማይችለው ነገር የለም። ይሖዋ፣ ሰይጣን የሰነዘረው ክስ በተሟላ ሁኔታ ምላሽ ካገኘ በኋላ እርምጃ ይወስዳል። በዚያን ጊዜ አምላክ ምድርን ወደ ገነትነት ይለውጣል፤ በዚህ መንገድ የአምላክ ዓላማ ይፈጸማል። “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ” ከሞት ይነሳሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) ሰዎች ፈጽሞ አይታመሙም እንዲሁም አይሞቱም። ኢየሱስ፣ ሰይጣን ያመጣውን መጥፎ ነገር ሁሉ ያስወግዳል። ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ‘የዲያብሎስን ሥራ ያፈርሳል።’ (1 ዮሐንስ 3:8) ይሁንና ይሖዋ ወዲያውኑ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ስለታገሠ አመስጋኞች ነን። ምክንያቱም እሱን ማወቅ ችለናል፤ እንዲሁም እሱ ገዢያችን እንዲሆን እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ አግኝተናል። (2 ጴጥሮስ 3:9, 10⁠ን አንብብ።) ይሖዋ መከራ ቢደርስብንም እንኳ መጽናት እንድንችል ይረዳናል።—ዮሐንስ 4:23፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13⁠ን አንብብ።

18 ይሖዋ ለእሱ እንድንገዛ አያስገድደንም። ለሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ይህ ውድ ስጦታ ለእኛ ምን ጥቅም እንዳለው እስቲ እንመልከት።

የመምረጥ ነፃነትህን የምትጠቀምበት እንዴት ነው?

19. ይሖዋ ምን ውድ ስጦታ ሰጥቶናል? ለዚህ ስጦታ አመስጋኞች መሆን ያለብንስ ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ ውድ ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ነፃነት ስለሰጠን ከእንስሳት በጣም የተለየን ነን። እንስሳት የሚንቀሳቀሱት በደመ ነፍስ ነው፤ እኛ ግን በመረጥነው መንገድ የመኖር ነፃነት ተሰጥቶናል፤ ይሖዋም በራሳችን ፍላጎት ተነሳስተን ስናመልከው ይደሰታል። (ምሳሌ 30:24) በተጨማሪም የተሠሩበትን ዓላማ ብቻ እንደሚያከናውኑ ማሽኖች አይደለንም። የፈለግነውን ዓይነት ሰው የመሆን፣ የፈለግነውን ጓደኛ የመምረጥ እንዲሁም ሕይወታችንን በፈለግነው መንገድ የመጠቀም ነፃነት አለን። ይሖዋ ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል።

20, 21. አሁን ልታደርገው የምትችለው ከሁሉ የተሻለ ምርጫ ምንድን ነው?

20 ይሖዋ እንድንወደው ይፈልጋል። (ማቴዎስ 22:37, 38) አንድ አባት፣ ልጁ ተገዶ ሳይሆን ከልቡ ተነሳስቶ “እወድሃለሁ” ሲለው በጣም እንደሚደሰት ሁሉ ይሖዋም ከልብ ተነሳስተን ስንወደው ደስ ይለዋል። ይሖዋን የምናገለግለው በምርጫችን ነው። ሰይጣንም ሆነ አዳምና ሔዋን ይሖዋን ላለማገልገል መርጠዋል። የአንተስ ምርጫ ምንድን ነው?

21 ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን ለማስደሰትና ሰይጣንን ለመቃወም መርጠዋል። (ምሳሌ 27:11) ታዲያ አምላክ መከራን ሁሉ ካስወገደ በኋላ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር አሁን ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የሚቀጥለው ምዕራፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

ክለሳ

እውነት 1፦ ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ መከራ አያመጣም

“‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።”—ኢዮብ 34:10

በዓለም ላይ መከራ የበዛው ለምንድን ነው?

  • 1 ዮሐንስ 5:19

    የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።

  • መክብብ 8:9

    የሰው ልጆች፣ አንዳቸው ሌላውን ያሠቃያሉ።

  • መክብብ 9:11

    አንዳንድ ጊዜ፣ ሰዎች በመጥፎ ጊዜ የማይሆን ቦታ ላይ በመገኘታቸው መከራና ሥቃይ ይደርስባቸዋል።

  • 1 ጴጥሮስ 5:7

    ይሖዋ ሰዎችን በጣም ይወዳል። ሰዎች እንዲሠቃዩ አይፈልግም።

እውነት 2፦ ሰይጣን በይሖዋ የመግዛት መብት ላይ ጥያቄ አንስቷል

“አምላክ . . . ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።”—ዘፍጥረት 3:5

ይሖዋ፣ ሰይጣንን ወዲያውኑ ያላጠፋው ለምንድን ነው?

  • ዘፍጥረት 3:2-5

    ሰይጣን አምላክን ‘ክፉ ገዢ ነው’ ሲል ከሶታል። ሰይጣን፣ የሰው ልጆች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ እንዲሰማቸው ማድረግ ፈልጎ ነበር። አምላክ፣ ሰይጣን የሰነዘረው ክስ ውሸት መሆኑ እንዲረጋገጥ ሲል ጊዜ ሰጥቷል።

  • ኢዮብ 38:7

    ሰይጣን ይሖዋን የከሰሰው በሚሊዮን በሚቆጠሩ መላእክት ፊት ነው።

እውነት 3፦ ሰይጣን የሰነዘረው ክስ ውሸት መሆኑ ተረጋግጧል

“[ሰው] አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።”—ኤርምያስ 10:23

ይሖዋ፣ በሰው ልጆች ላይ ለረጅም ጊዜ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?

  • ኢሳይያስ 55:9

    የሰው ልጆች የተለያዩ የአገዛዝ ሥርዓቶችን ቢሞክሩም ያለአምላክ እርዳታ ምድርን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር አልቻሉም።

  • 2 ጴጥሮስ 3:9, 10

    ይሖዋ ታጋሽ ነው፤ እሱን ማወቅ እንዲሁም ገዢያችን እንዲሆን እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ ሰጥቶናል።

  • 1 ዮሐንስ 3:8

    ይሖዋ፣ በኢየሱስ አማካኝነት ሰይጣን ያመጣውን መጥፎ ነገር ሁሉ ያስወግዳል።

እውነት 4፦ የመምረጥ ነፃነትህን ተጠቅመህ ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ

“ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን።”—ምሳሌ 27:11

ይሖዋ እሱን እንድናገለግለው የማያስገድደን ለምንድን ነው?

  • ምሳሌ 30:24

    እንስሳት የሚንቀሳቀሱት በደመ ነፍስ ነው፤ እኛ ግን የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቶናል። ይሖዋን የምናገለግለው በምርጫችን ነው።

  • ማቴዎስ 22:37, 38

    ይሖዋ በፍቅር ተነሳስተን እንድናገለግለው ይፈልጋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ