-
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 31
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ መልእክት በአምላክ መንግሥት ላይ ያተኮረ ነው። ይሖዋ ምድርን ገነት ለማድረግ ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ ዳር የሚያደርሰው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ነው። ለመሆኑ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ በመግዛት ላይ እንዳለ እንዴት እናውቃለን? እስካሁን ምን ነገሮችን አከናውኗል? ወደፊትስ ምን ነገሮችን ያከናውናል? ይህ ምዕራፍና ቀጣዮቹ ሁለት ምዕራፎች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።
1. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ንጉሡስ ማን ነው?
የአምላክ መንግሥት ይሖዋ አምላክ ያቋቋመው መስተዳድር ነው። የዚህ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የሚገዛውም ከሰማይ ነው። (ማቴዎስ 4:17፤ ዮሐንስ 18:36) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል” ይላል። (ሉቃስ 1:32, 33) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ወደፊት በምድር ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ይገዛል።
2. ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት እነማን ናቸው?
ኢየሱስ የሚገዛው ብቻውን አይደለም። “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ” የተውጣጡ ሰዎች ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።’ (ራእይ 5:9, 10) ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት ሰዎች ምን ያህል ናቸው? ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ ወዲህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች የእሱ ተከታዮች ሆነዋል። ሆኖም ወደ ሰማይ ሄደው ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት 144,000 የሚያህሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። (ራእይ 14:1-4ን አንብብ።) በምድር ላይ የሚቀሩት ሌሎች ክርስቲያኖች በሙሉ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ይሆናሉ።—መዝሙር 37:29
3. የአምላክን መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሯቸው መንግሥታት የተሻለ የሚያደርገው ምንድን ነው?
የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥሩ ነገሮችን ማድረግ ቢፈልጉም እንኳ የፈለጉትን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል የላቸውም። በተጨማሪም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ራስ ወዳድ በሆኑና ሰዎችን መርዳት በማይፈልጉ ሌሎች ባለሥልጣናት መተካታቸው አይቀርም። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ግን በማንም አይተካም። አምላክ ያቋቋመው መንግሥት “ፈጽሞ የማይጠፋ” ነው። (ዳንኤል 2:44) ኢየሱስ መላዋን ምድር የሚገዛ ሲሆን አንዱን ከሌላው አያበላልጥም። አፍቃሪ፣ ደግና ፍትሐዊ ከመሆኑም በላይ ሰዎችም ልክ እንደ እሱ እነዚህን ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ ያስተምራል።—ኢሳይያስ 11:9ን አንብብ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
የአምላክን መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ከየትኛውም መንግሥት የተሻለ የሚያደርገው ምን እንደሆነ እንመለከታለን።
4. መላዋ ምድር በአንድ ታላቅ መስተዳድር ሥር ትሆናለች
ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዛሬ ድረስ በምድር ላይ ከተነሱት ገዢዎች ሁሉ የበለጠ ሥልጣን አለው። ማቴዎስ 28:18ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ኢየሱስ በምድር ላይ ካለ ከየትኛውም ገዢ የበለጠ ሥልጣን አለው የምንለው ለምንድን ነው?
በዓለም ላይ ያሉት መንግሥታት በየጊዜው ይቀያየራሉ፤ ደግሞም አንድ መንግሥት የሚያስተዳድረው የዓለማችንን የተወሰነ ክፍል ነው። የአምላክ መንግሥትስ? ዳንኤል 7:14ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
የአምላክ መንግሥት “የማይጠፋ” መሆኑ ምን ጥቅም አለው?
መላዋን ምድር የሚገዛ መሆኑ ምን ጥቅም አለው?
5. የሰዎች አገዛዝ መተካት አለበት
የሰዎች አገዛዝ በአምላክ መንግሥት ሊተካ የሚገባው ለምንድን ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
የሰዎች አገዛዝ ምን ውጤት አስከትሏል?
መክብብ 8:9ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
የሰዎች አገዛዝ በአምላክ መንግሥት ሊተካ እንደሚገባ ይሰማሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
6. የአምላክ መንግሥት ገዢዎች ያለንበትን ሁኔታ ይረዱልናል
ንጉሣችን ኢየሱስ በአንድ ወቅት ሰው ሆኖ ስለኖረ ‘በድካማችን ይራራልናል።’ (ዕብራውያን 4:15) ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የመረጣቸው 144,000 ታማኝ ወንዶችና ሴቶች “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ” የተውጣጡ ናቸው።—ራእይ 5:9
ኢየሱስና ከእሱ ጋር የሚገዙት ሰዎች በሙሉ በአንድ ወቅት እንደ እኛው ሰው የነበሩ መሆናቸውን ማወቃችን የሚያጽናናን ለምንድን ነው?
ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የመረጣቸው ወንዶችና ሴቶች የተለያየ ዘርና አስተዳደግ ያላቸው ናቸው
7. የአምላክ መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ከየትኛውም መንግሥት የላቁ ሕጎች አሉት
መንግሥታት ለዜጎቻቸው ጥቅምና ጥበቃ ያስገኛሉ ብለው የሚያስቧቸውን ሕጎች ያወጣሉ። የአምላክ መንግሥትም ተገዢዎቹ ሊያከብሯቸው የሚገቡ ሕጎች አሉት። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ሁሉም ሰው አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር ደንቦች ቢከተል ዓለማችን ምን መልክ የሚኖራት ይመስልሃል?a
ይሖዋ የመንግሥቱ ተገዢዎች እነዚህን ሕጎች እንዲያከብሩ መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
እነዚህን ሕጎች የማይታዘዙ ሰዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?—ቁጥር 11ን ተመልከት።
መንግሥታት ለዜጎቻቸው ጥበቃና ጥቅም የሚያስገኙ የተለያዩ ሕጎችን ያወጣሉ። የአምላክ መንግሥት ለተገዢዎቹ ጥበቃና ጥቅም የሚያስገኙ የላቁ ሕጎች አሉት
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ማጠቃለያ
የአምላክ መንግሥት በሰማይ ያለ መስተዳድር ሲሆን ወደፊት መላዋን ምድር ይገዛል።
ክለሳ
የአምላክ መንግሥት ገዢዎች እነማን ናቸው?
የአምላክ መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ከየትኛውም መንግሥት የተሻለ የሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ይሖዋ ከመንግሥቱ ተገዢዎች የሚጠብቃቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ምርምር አድርግ
ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት የሚገኝበትን ቦታ በተመለከተ ምን አስተምሯል?
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከሰዎች መንግሥት ይልቅ ለአምላክ መንግሥት ታማኝ ለመሆን የሚመርጡት ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የመረጣቸውን 144,000 ሰዎች አስመልክቶ ምን ይላል?
እስር ቤት የነበረች አንዲት ሴት በዓለም ላይ ፍትሕ ሊያሰፍን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው ብላ እንድታምን ያደረጋት ምንድን ነው?
-
-
የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀምሯል!ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 32
የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀምሯል!
የአምላክ መንግሥት ከ1914 አንስቶ በሰማይ መግዛት ጀምሯል። የሰዎች አገዛዝ መደምደሚያ የሆኑት የመጨረሻዎቹ ቀናትም የጀመሩት በዚሁ ዓመት ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንመለከታለን፤ በተጨማሪም ከ1914 አንስቶ በዓለም ላይ እየተከናወኑ ያሉትን ነገሮችና ሰዎች እያሳዩ ያሉትን ባሕርይ እንመረምራለን።
1. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ምን ይጠቁማሉ?
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዳንኤል ትንቢት የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀምረው “ሰባት ዘመናት” ተብሎ የተገለጸው ጊዜ ሲያበቃ እንደሆነ ተናግሯል። (ዳንኤል 4:16, 17) በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ እነዚህኑ ሰባት ዘመናት “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ብሎ የጠራቸው ሲሆን በዚያ ወቅት እነዚህ ዘመናት እንዳላበቁ አስተምሯል። (ሉቃስ 21:24) በኋላ ላይ እንደምንመለከተው እነዚህ ዘመናት ያበቁት በ1914 ነው።
2. በዓለም ላይ ከሚከናወኑት ነገሮችና ሰዎች ከሚያሳዩት ባሕርይ ጋር በተያያዘ ከ1914 አንስቶ ምን ለውጥ ታይቷል?
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን ‘የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምንድን ነው?’ በማለት ጠይቀውት ነበር። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ ለጥያቄያቸው መልስ ሲሰጥ፣ እሱ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ በኋላ የሚከናወኑ በርካታ ነገሮችን ነግሯቸዋል። ከነገራቸው ነገሮች መካከል ጦርነት፣ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይገኙበታል። (ማቴዎስ 24:7ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ሰዎች ከሚያሳዩት ባሕርይ የተነሳ ‘ለመቋቋም የሚያስቸግር ዘመን’ እንደሚመጣም አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በትንቢቶቹ ላይ የተጠቀሱት ነገሮች፣ በተለይ ከ1914 ወዲህ ጉልህ በሆነ መንገድ መታየት ጀምረዋል።
3. የአምላክ መንግሥት መግዛት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዓለም ሁኔታ ይህን ያህል የተባባሰው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ ብዙም ሳይቆይ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ በሰማይ ጦርነት ከፈተ። ሰይጣን በጦርነቱ ተሸነፈ። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ በኋላ ስለሆነው ነገር ሲናገር ‘ሰይጣን ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ’ ይላል። (ራእይ 12:9, 10, 12) ሰይጣን መጥፋቱ እንደማይቀር ስለሚያውቅ በጣም ተቆጥቷል። በመላው ምድር ላይ ሥቃይና መከራ እያደረሰ ያለው በዚህ ምክንያት ነው። ከዚህ አንጻር፣ የዓለም ሁኔታ ይህን ያህል የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱ ምንም አያስገርምም! የአምላክ መንግሥት እነዚህን ሁሉ ችግሮች ያስወግዳል።
ጠለቅ ያለ ጥናት
የአምላክ መንግሥት በ1914 መግዛት እንደጀመረ የምናውቀው እንዴት እንደሆነና ይህ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው እንመለከታለን።
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ወደ 1914 ይጠቁማሉ
አምላክ የጥንቷ ባቢሎን ንጉሥ የነበረውን ናቡከደነጾርን ትንቢታዊ ትርጉም ያለው ሕልም እንዲያይ አድርጎታል። እሱ ካየው ሕልምና ዳንኤል ከሰጠው ትርጓሜ እንደምንረዳው፣ ሕልሙ የናቡከደነጾርን አገዛዝና የአምላክን መንግሥት የሚመለከት ነው።—ዳንኤል 4:17ን አንብቡ።a
ዳንኤል 4:20-26ን አንብቡ፤ ከዚያም ሰንጠረዡን ተጠቅማችሁ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
(ሀ) ናቡከደነጾር በሕልሙ ምን አይቷል?—ቁጥር 20 እና 21ን ተመልከት።
(ለ) ዛፉ ምን ይሆናል?—ቁጥር 23ን ተመልከት።
(ሐ) ‘በሰባቱ ዘመናት’ መጨረሻ ላይ ምን ይፈጸማል?—ቁጥር 26ን ተመልከት።
ስለ ዛፉ የሚገልጸው ሕልም ከአምላክ መንግሥት ጋር ምን ግንኙነት አለው?
ትንቢቱ (ዳንኤል 4:20-36)
አገዛዝ
(ሀ) ግዙፍ ዛፍ
አገዛዙ ተቋረጠ
(ለ) ‘ዛፉን ቁረጡ’ እንዲሁም ‘ሰባት ዘመናት ይለፉበት’
አገዛዙ መልሶ ተቋቋመ
(ሐ) “መንግሥትህ ይመለስልሃል”
በዚህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜ መሠረት . . .
(መ) ዛፉ የሚያመለክተው ማንን ነው?—ቁጥር 22ን ተመልከት።
(ሠ) አገዛዙ የተቋረጠው እንዴት ነው?—ዳንኤል 4:29-33ን አንብቡ።
(ረ) ‘ሰባቱ ዘመናት’ ሲያበቁ ናቡከደነጾር ምን ሆነ?—ዳንኤል 4:34-36ን አንብቡ።
የመጀመሪያው ፍጻሜ
አገዛዝ
(መ) የባቢሎን ንጉሥ የሆነው ናቡከደነጾር
አገዛዙ ተቋረጠ
(ሠ) ከ606 ዓ.ዓ. በኋላ ናቡከደነጾር አእምሮውን የሳተ ሲሆን ቃል በቃል ለሰባት ዓመታት መግዛት አልቻለም
አገዛዙ መልሶ ተቋቋመ
(ረ) ናቡከደነጾር አእምሮው ተመለሰለት፤ ዳግመኛም መግዛት ጀመረ
በዚህ ትንቢት ሁለተኛ ፍጻሜ መሠረት . . .
(ሰ) ዛፉ የሚያመለክተው እነማንን ነው?—1 ዜና መዋዕል 29:23ን አንብቡ።
(ሸ) አገዛዛቸው የተቋረጠው እንዴት ነው? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜም ጭምር ይህ አገዛዝ ተቋርጦ እንደነበር በምን እናውቃለን?—ሉቃስ 21:24ን አንብቡ።
(ቀ) ይህ አገዛዝ መልሶ የተቋቋመው መቼና እንዴት ነው?
ሁለተኛው ፍጻሜ
አገዛዝ
(ሰ) የአምላክን አገዛዝ የሚወክሉ እስራኤላውያን ነገሥታት
አገዛዙ ተቋረጠ
(ሸ) ኢየሩሳሌም ጠፋች፤ በዳዊት የዘር ሐረግ የሚመጡት የእስራኤላውያን ነገሥታት መስመር ለ2,520 ዓመታት ተቋረጠ
አገዛዙ መልሶ ተቋቋመ
(ቀ) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን በሰማይ መግዛት ጀመረ
ሰባቱ ዘመናት ምን ያህል ርዝማኔ አላቸው?
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ያለው ሐሳብ በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ያለውን ሐሳብ ለመረዳት ያስችለናል። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ሦስት ተኩል ዘመናት የ1,260 ቀናት ርዝማኔ እንዳላቸው ይገልጻል። (ራእይ 12:6, 14) ሰባት ዘመናት፣ የሦስት ተኩል ዘመናትን እጥፍ ማለትም 2,520 ቀናትን ያመለክታሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ቀን አንድ ዓመትን ለማመልከት የሚሠራበት ጊዜ አለ። (ሕዝቅኤል 4:6) በዳንኤል ትንቢት ላይ ከተጠቀሱት ሰባት ዘመናት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ሰባቱ ዘመናት 2,520 ዓመታትን ያመለክታሉ።
5. ከ1914 ወዲህ የዓለም ሁኔታ ተቀይሯል
ኢየሱስ እሱ ንጉሥ ከሆነ በኋላ በዓለም ላይ የሚታዩትን ሁኔታዎች አስቀድሞ ተናግሯል። ሉቃስ 21:9-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
እዚህ ጥቅስ ላይ ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል አንተ ያየኸው ወይም የሰማኸው የትኞቹን ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ልጆች አገዛዝ ከመደምደሙ በፊት ባሉት ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ እንደሚኖራቸው ገልጿል። ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በዛሬው ጊዜ ሰዎች የትኞቹን ባሕርያት ሲያንጸባርቁ ተመልክተሃል?
6. የአምላክ መንግሥት እየገዛ መሆኑን ማወቃችን ለተግባር ያነሳሳናል
ማቴዎስ 24:3, 14ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
የአምላክ መንግሥት በመግዛት ላይ መሆኑን የሚያሳየው የትኛው አስፈላጊ ሥራ መከናወኑ ነው?
በዚህ ሥራ መሳተፍ የምትችለው እንዴት ነው?
የአምላክ መንግሥት አሁን በመግዛት ላይ ይገኛል፤ በቅርቡ ደግሞ መላዋን ምድር በቁጥጥሩ ሥር ያደርጋል። ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
“ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ” እያንዳንዳችን ምን ማድረግ አለብን?
አንድ ነገር ሌሎችን ሊጠቅምና ሕይወታቸውን ሊያድን እንደሚችል ስታውቅ ምን ለማድረግ ትነሳሳለህ?
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የይሖዋ ምሥክሮች ለ1914 ይህን ያህል ትኩረት የሚሰጡት ለምንድን ነው?”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ማጠቃለያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲሁም በዓለም ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች የአምላክ መንግሥት አሁን በመግዛት ላይ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ስለዚህ ጉዳይ በመስበክና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት የአምላክ መንግሥት እየገዛ መሆኑን እንደምናምን እናሳያለን።
ክለሳ
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዳንኤል መጽሐፍ ላይ በተገለጹት ሰባት ዘመናት ማብቂያ ላይ ምን ተከናውኗል?
የአምላክ መንግሥት በ1914 መግዛት ጀምሯል ብለህ እንድታምን የሚያደርግህ ምንድን ነው?
የአምላክ መንግሥት በመግዛት ላይ መሆኑን እንደምታምን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
ምርምር አድርግ
የታሪክ ምሁራንና ሌሎች ሰዎች ከ1914 ወዲህ በዓለም ላይ ስለታየው ለውጥ ምን ይላሉ?
በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘው ትንቢት በአንድ ሰው ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጣው እንዴት ነው?
“ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስተኝ ቤዝቦል መጫወት ነበር!” (መጠበቂያ ግንብ ቁጥር 3 2017)
ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የሚገኘው ትንቢት ስለ አምላክ መንግሥት እንደሚናገር ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
“የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ክፍል 1)” (መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 1, 2014)
ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የተጠቀሱት ሰባት ዘመናት በ1914 እንዳበቁ የሚጠቁም ምን ማስረጃ አለ?
“የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ክፍል 2)” (መጠበቂያ ግንብ ኅዳር 1, 2014)
a በዚህ ምዕራፍ “ምርምር አድርግ” በሚለው ክፍል ሥር የተጠቀሱትን የመጨረሻዎቹን ሁለት የማመሣከሪያ ጽሑፎች ተመልከት።
-
-
የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 33
የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?
የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀምሯል። በቅርቡ በምድር ላይ ሥር ነቀል ለውጦችን ያደርጋል። እስቲ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የምታገኛቸውን አንዳንድ በረከቶች እንመልከት።
1. የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያደርገው እንዴት ነው?
የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ ክፉ ሰዎችንና መንግሥታትን ያጠፋል። (ራእይ 16:14, 16) በዚያ ወቅት “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። (መዝሙር 37:10) ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት በመላዋ ምድር ላይ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል።—ኢሳይያስ 11:4ን አንብብ።
2. የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ በሚፈጸምበት ጊዜ ምን ዓይነት ሕይወት ይኖረናል?
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) ክፉዎች በሌሉበት እንዲሁም ይሖዋን የሚወዱና እርስ በርስ የሚዋደዱ ሰዎች ብቻ ባሉበት ዓለም ውስጥ መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው! በሕመም የሚሠቃይ ሰው አይኖርም፤ ሁሉም ሰው ለዘላለም ይኖራል።
3. ክፉዎች ከጠፉ በኋላ የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?
ክፉዎች ከጠፉ በኋላ ኢየሱስ ለ1,000 ዓመት ያህል ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። በዚያ ወቅት ኢየሱስና አብረውት የሚገዙት 144,000 ገዢዎች፣ ሰዎች ፍጹምና ከኃጢአት ነፃ እንዲሆኑ ይረዳሉ። የሺህ ዓመቱ ግዛት መጨረሻ ላይ ምድር የይሖዋን ሕጎች በሚታዘዙ ደስተኛ ሰዎች የተሞላች ውብ ገነት ትሆናለች። ከዚያም ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ ለይሖዋ ያስረክባል። የይሖዋ ስም ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ ‘ይቀደሳል።’ (ማቴዎስ 6:9, 10) ይሖዋ ለተገዢዎቹ የሚያስብ ጥሩ ገዢ እንደሆነ ይረጋገጣል። ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንንና አጋንንቱን ጨምሮ በእሱ አገዛዝ ላይ የሚያምፁትን ሁሉ ያጠፋል። (ራእይ 20:7-10) የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸው በረከቶች ለዘላለም ይቀጥላሉ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚፈጽም እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።
4. የአምላክ መንግሥት የሰዎችን አገዛዝ ያስወግዳል
“ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 8:9) ይሖዋ በፍትሕ መጓደል ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን በመንግሥቱ አማካኝነት ያስተካክላል።
ዳንኤል 2:44ን እና 2 ተሰሎንቄ 1:6-8ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ ሰዎች በሚያስተዳድሯቸው መንግሥታትና በደጋፊዎቻቸው ላይ ምን እርምጃ ይወስዳሉ?
ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ የተማርከው ነገር እነሱ የሚወስዱት እርምጃ ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደሆነ እንድትተማመን የሚያደርግህ እንዴት ነው?
5. ኢየሱስ ከሁሉ የተሻለ ንጉሥ ነው
ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ ላሉ ተገዢዎቹ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ያከናውናል። ኢየሱስ ከዚህ በፊት ያደረጋቸው ነገሮች እንዲህ ለማድረግ ፍላጎቱ እንዳለውና አምላክም ኃይል እንደሰጠው ያሳያሉ። ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ቪዲዮው ላይ ተመልከቱ።
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአምላክ መንግሥት ወደፊት የሚያከናውናቸውን ነገሮች በጥቂቱም ቢሆን አሳይቷል። አንተ በግልህ እዚህ ላይ ከተዘረዘሩት ነገሮች መካከል የትኛው ሲፈጸም ለማየት ትጓጓለህ? ከእያንዳንዱ ተስፋ ጋር አብረው የተጠቀሱትን ጥቅሶች አንብቡ።
ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ . . .
ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ . . .
የአየሩን ጠባይ ተቆጣጥሯል።—ማርቆስ 4:36-41
በፕላኔቷ ምድራችን ላይ የደረሰውን ጉዳት ያስተካክላል።—ኢሳይያስ 35:1, 2
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መግቧል።—ማቴዎስ 14:17-21
ከዓለም ላይ ረሃብን ያስወግዳል።—መዝሙር 72:16
ብዙዎችን ከሕመማቸው ፈውሷል።—ሉቃስ 18:35-43
ሁሉም ሰው ፍጹም ጤንነት እንዲኖረው ያደርጋል።—ኢሳይያስ 33:24
የሞቱ ሰዎችን አስነስቷል።—ሉቃስ 8:49-55
ሞትን ያስወግዳል፤ የሞቱትን ያስነሳል።—ራእይ 21:3, 4
6. የአምላክ መንግሥት ወደፊት አስደሳች ጊዜ ያመጣል
የአምላክ መንግሥት ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው የመጀመሪያ ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ያደርጋል። ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት ዓላማውን ዳር ለማድረስ እየሠራ ያለው እንዴት እንደሆነ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ።
መዝሙር 145:16ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ሁላችንም ተባብረን ከሠራን የዓለማችንን ችግሮች ማስወገድ እንችላለን።”
ሰዎች ከሚያስተዳድሯቸው መንግሥታት አቅም በላይ የሆኑ ሆኖም የአምላክ መንግሥት የሚያስወግዳቸው ችግሮች የትኞቹ ናቸው?
ማጠቃለያ
የአምላክ መንግሥት ዓላማውን ዳር ያደርሳል። መላዋ ምድር ይሖዋን ለዘላለም በሚያመልኩ ጥሩ ሰዎች እንድትሞላና ገነት እንድትሆን ያደርጋል።
ክለሳ
የአምላክ መንግሥት የይሖዋ ስም እንዲቀደስ የሚያደርገው እንዴት ነው?
የአምላክ መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ተስፋዎች እንዲፈጸሙ እንደሚያደርግ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
የአምላክ መንግሥት ከሚያመጣቸው በረከቶች መካከል አንተ ለማየት የምትጓጓው የትኛውን ነው?
ምርምር አድርግ
‘አርማጌዶን’ የሚለው ቃል ምን ያመለክታል?
ኢየሱስ “ታላቅ መከራ” ብሎ በጠራው ወቅት ምን ነገሮች ይከናወናሉ?—ማቴዎስ 24:21
የአምላክ መንግሥት ወደፊት በሚያመጣቸው በረከቶች ላይ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ማሰላሰል የሚቻለው እንዴት ነው?
“አእምሮዬን የሚረብሹ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ” በሚለው ርዕስ ሥር ዓማፂ የነበረ አንድ ሰው ለጥያቄዎቹ መልስ ያገኘው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።
-