-
የተሳሳተ ትምህርት 1፦ ነፍስ አትሞትምመጠበቂያ ግንብ—2009 | ኅዳር 1
-
-
የተሳሳተ ትምህርት 1፦ ነፍስ አትሞትም
ይህ የተሳሳተ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው?
“የጥንቶቹ የክርስትና ፈላስፎች፣ ነፍስ አትሞትም የሚለውን የግሪክ ጽንሰ ሐሳብ እንዲሁም አምላክ ነፍስን ከፈጠረ በኋላ አንድ ሰው በሚፀነስበት ጊዜ ወደ አካሉ ያስገባታል የሚለውን ትምህርት ተቀብለው ነበር።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1988)፣ ጥራዝ 11፣ ገጽ 25
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።”—ሕዝቅኤል 18:4
መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን ሰው አፈጣጠር በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ [በዕብራይስጥ፣ ነፈሽ] ሆነ።”—ዘፍጥረት 2:7
“ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ‘የሚተነፍስ ፍጡር’ የሚል ፍቺ አለው። አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ሲፈጥረው ወደ አካሉ ያስገባው ሕይወቱን የሚያቆይ ኃይል እንጂ የማትሞት ነፍስ አይደለም፤ ይህ የሕይወት ኃይል በሰውነቱ ውስጥ እንዲቆይ አዳም መተንፈስ ነበረበት። ከዚህ አንጻር “ነፍስ” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያመለክተው የአንድን ሰው የተወሰነ ክፍል ሳይሆን በሕይወት ያለውን ግለሰብ እንዳለ ነው። አምላክ መጀመሪያ ለሰው የሰጠው ሕይወትን የሚያቆይ ኃይል ከሰው ከወጣ ነፍስ ማለትም ሰውየው ይሞታል።—ዘፍጥረት 3:19፤ ሕዝቅኤል 18:20
ነፍስ አትሞትም የሚለው መሠረተ ትምህርት የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስነስቷል፦ ከሞት በኋላ ነፍስ ወዴት ትሄዳለች? የክፉዎች ነፍስ ምን ይሆናል? ስመ ክርስትና፣ ነፍስ አትሞትም የሚለውን የተሳሳተ ትምህርት መቀበሏ ሌላ የተሳሳተ ትምህርት ይኸውም የመቃጠያ እሳት አለ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ወደ መቀበል መርቷታል።
እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አወዳድር፦ መክብብ 3:19፤ ማቴዎስ 10:28፤ የሐዋርያት ሥራ 3:23
እውነታው፦
አንድ ሰው ሲሞት ከሕልውና ውጪ ይሆናል
-
-
የተሳሳተ ትምህርት 2፦ ክፉዎች በእሳት ይቃጠላሉመጠበቂያ ግንብ—2009 | ኅዳር 1
-
-
የተሳሳተ ትምህርት 2፦ ክፉዎች በእሳት ይቃጠላሉ
ይህ የተሳሳተ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው?
“ቀደምት ከሆኑት የግሪክ ፈላስፎች መካከል ስለ መቃጠያ እሳት የሚገልጸው በስፋት ተቀባይነት ያገኘ አመለካከት እንዲዳብር ከሁሉ ይበልጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ፕላቶ ነው።”—በዦርዥ ሚንዋ የተዘጋጀው ሂስትዋር ዴዝ ኦንፌር (የመቃጠያ እሳት ታሪካዊ አመጣጥ) የተባለው መጽሐፍ ገጽ 50
“የግሪክን ፍልስፍና በተወሰነ ደረጃ የተማሩ ክርስቲያኖች ከ2ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አጋማሽ አንስቶ . . . እምነታቸውን ከግሪክ ፍልስፍና አኳያ መግለጽ እንዳለባቸው ሆኖ ተሰማቸው። . . . ይህንን ለማድረግ ይበልጥ የተስማማቸው የፕላቶ ፍልስፍና ነበር።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1988)፣ ጥራዝ 25፣ ገጽ 890
“የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የመቃጠያ እሳት እንዳለና ዘላለማዊ እንደሆነ ያረጋግጣል። ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ነፍሳቸው ወዲያውኑ ወደ ሲኦል ይወርዳል፤ በዚያም ነፍሳቸው ‘በዘላለማዊ እሳት’ ይሠቃያል። በሲኦል ውስጥ ያለው ዋነኛ ቅጣት ከአምላክ ለዘላለም እንዲለዩ መደረግ ነው።”—ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች፣ የ1994 እትም፣ ገጽ 270
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም። . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።”—መክብብ 9:5, 10 የ1954 ትርጉም
‘የሙታን ማደሪያን’ የሚያመለክተው ሺኦል የሚለው የዕብራስይጥ ቃል በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ “ሲኦል” ተብሎ ተተርጉሟል። ከላይ ያለው ጥቅስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ምን ይጠቁማል? ሙታን የሠሩት ኃጢአት እንዲሰረይላቸው በሺኦል ይሠቃያሉ? በፍጹም፤ ምክንያቱም ‘ሙታን አንዳች አያውቁም።’ በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብ የተባለ የአምላክ አገልጋይ በደረሰበት ከባድ ሕመም እጅግ በመሠቃየቱ “በሲኦል [በዕብራይስጥ፣ ሺኦል] ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ” በማለት አምላክን የለመነው ለዚህ ነው። (ኢዮብ 14:13 የ1954 ትርጉም) ሺኦል፣ ሰዎች ለዘላለም የሚሠቃዩበት ቦታ ቢሆን ኖሮ ኢዮብ ያቀረበው ልመና ምን ትርጉም ይኖረዋል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲኦል፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማይኖርበትን የሰው ልጆች መቃብር ያመለክታል።
ሲኦል እንዲህ ዓይነት ፍቺ ያለው መሆኑ ይበልጥ ትርጉም የሚሰጥ እንዲሁም ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚስማማ አይደለም? የሰው ልጆች ምንም ዓይነት ከባድ ኃጢአት ቢሠሩ የፍቅር አምላክ ለዘላለም ያሠቃያቸዋል ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ ይሆናል? (1 ዮሐንስ 4:8) ይሁን እንጂ ክፉዎች በእሳት ይቃጠላሉ የሚለው ትምህርት ስህተት ከሆነ ወደ ሰማይ ስለመሄድ ስለሚገልጸው ትምህርትስ ምን ማለት ይቻላል?
እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አወዳድር፦ መዝሙር 146:3, 4፤ የሐዋርያት ሥራ 2:25-27፤ ሮም 6:7, 23
እውነታው፦
አምላክ ሰዎችን በእሳት በማቃጠል አይቀጣም
-
-
የተሳሳተ ትምህርት 3፦ ጥሩ ሰዎች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉመጠበቂያ ግንብ—2009 | ኅዳር 1
-
-
የተሳሳተ ትምህርት 3፦ ጥሩ ሰዎች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ
ይህ የተሳሳተ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው?
የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች የሚያስተምሩትን ትምህርት በተመለከተ ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ (2003)፣ ጥራዝ 6፣ ገጽ 687 እንዲህ ይላል፦ “ከሞት በኋላ ከሥጋ የተለየው ነፍስ አስፈላጊው የመንጻት ሥርዓት ከተደረገለት በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ይሄዳል የሚለው ትምህርት በስፋት ተቀባይነት አግኝቷል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።”—ማቴዎስ 5:5
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በሰማይ ‘ቦታ እንደሚያዘጋጅላቸው’ ቃል ቢገባላቸውም ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሁሉም ጻድቃን እንዳልሆኑ ጠቁሟል። (ዮሐንስ 3:13፤ 14:2, 3) ኢየሱስ የአምላክ ፈቃድ “በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም” እንዲሆን መጸለዩንም ማስታወስ ያስፈልጋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ለጻድቃን የተዘጋጀው ተስፋ፣ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ መግዛት አሊያም በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ነው፤ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙ ሲሆን አብዛኛው የሰው ዘር በምድር ላይ ይኖራል።—ራእይ 5:10
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ የምታከናውነውን ሥራ በተመለከተ ያላት አመለካከት ተቀየረ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው ቤተ ክርስቲያን፣ ሰዎች የአምላክን መንግሥት መምጣት እንዲጠብቁ ከማበረታታት ይልቅ ተስፋቸውን በእሷ ላይ እንዲጥሉ በማድረግ “የአምላክን መንግሥት ቦታ ወሰደች።” ቤተ ክርስቲያኗ፣ ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል መሆን እንደሌለባቸው’ የሰጠውን ግልጽ ትእዛዝ ችላ ብላ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ሥልጣኗን ማጠናከር ጀመረች። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14-16፤ 18:36) ቤተ ክርስቲያኗ የሮም ንጉሠ ነገሥት በነበረው በቆስጠንጢኖስ ተጽዕኖ በመሸነፍ የምታምንባቸውን አንዳንድ ትምህርቶች ቀየረች፤ ከእነዚህ እምነቶች አንዱ የአምላክን ማንነት የሚመለከት ነው።
እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አወዳድር፦ መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ዮሐንስ 17:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:11, 12
እውነታው፦
አብዛኞቹ ጥሩ ሰዎች በሰማይ ሳይሆን በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ
-
-
የተሳሳተ ትምህርት 4፦ አምላክ ሥላሴ ነውመጠበቂያ ግንብ—2009 | ኅዳር 1
-
-
የተሳሳተ ትምህርት 4፦ አምላክ ሥላሴ ነው
ይህ የተሳሳተ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው?
“ካሉት መረጃዎች አንጻር የሥላሴ ቀኖና በ4ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የተፈጠረ ትምህርት እንደሆነ መደምደም ይቻላል። በአንድ በኩል ሲታይ ይህ መደምደሚያ እውነት ነው፤ . . . ‘አንድ አምላክ በሦስት አካላት’ የሚለው ድንጋጌ ጠንካራ መሠረት ያገኘውና በክርስትና ሕይወት ብሎም ሃይማኖታዊ እምነት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የተዋሃደው ከ4ኛው መቶ ዘመን በኋላ ነበር።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ (1967)፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 299
“የኒቂያ ጉባኤ የተካሄደው ግንቦት 20, 325 [ዓ.ም.] ነበር። የስብሰባው ሊቀ መንበር ቆስጠንጢኖስ ራሱ ሲሆን ውይይቱን በመምራት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ ከዚህም በላይ ጉባኤው ባስተላለፈው ድንጋጌ ላይ የሚገኘውን ክርስቶስ ከአምላክ ጋር ስላለው ዝምድና ማለትም ‘ከአብ ጋር አንድ አካል ስለመሆኑ’ የሚገልጸውን ወሳኝ ሐሳብ ያቀረበው እሱ ራሱ . . . ነው። . . . ከሁለቱ በስተቀር ጳጳሳቱ በሙሉ ንጉሠ ነገሥቱን በመፍራት እንዲያውም አብዛኞቹ አለፍላጎታቸው ድንጋጌውን በፊርማቸው አረጋገጡ።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1970)፣ ጥራዝ 6፣ ገጽ 386
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣ ‘እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ’ አለ።”—የሐዋርያት ሥራ 7:55, 56 አ.መ.ት
እስጢፋኖስ የተመለከተው ነገር ምን ያስገነዝበናል? እስጢፋኖስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ኢየሱስን “በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ” ተመልክቶታል። ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ እግዚአብሔር አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ከእግዚአብሔር የተለየ መንፈሳዊ አካል ሆኗል። በዚህ ዘገባ ላይ ከእግዚአብሔር ጎን ሌላ ሦስተኛ አካል እንዳለ አልተጠቀሰም። የሥላሴን መሠረተ ትምህርት የሚደግፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለማግኘት ጥረት ቢደረግም የዶሚኒካን ነዋሪ የሆኑት ማሪ ኤሚል ቡዋማር የተባሉ ቄስ እንደጻፉት “በአንድ አምላክ ውስጥ ሦስት አካል . . . አለ የሚለውን ሐሳብ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በየትም ቦታ ላይ ማግኘት አይቻልም።”—አ ለኦብ ዱ ክሪስቲያኒዝም—ላ ኔሶንስ ዴ ዶግም (በክርስትና አጥቢያ ላይ—የቀኖናዎች መፈጠር)
ቆስጠንጢኖስ የሥላሴ ትምህርት እንዲስፋፋ ያደረገበት ምክንያት በአራተኛው መቶ ዘመን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን የጦፈ ክርክር ለማስቆም ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ትምህርት ሌላ ጥያቄ አስነስቷል፦ ኢየሱስን የወለደችው ማሪያም “ወላዲተ አምላክ” ወይም “የአምላክ እናት” ናት?
እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አወዳድር፦ ማቴዎስ 26:39፤ ዮሐንስ 14:28፤ 1 ቆሮንቶስ 15:27, 28፤ ቆላስይስ 1:15, 16
እውነታው፦
የሥላሴ ቀኖና በ4ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የተፈጠረ ትምህርት ነው
-