ከታሪክ ማኅደራችን
‘በፈተና ሰዓት’ በአቋማቸው ጸንተዋል
አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 ሲፈነዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚከተሉትን የገለልተኝነት አቋም ዓለም በይፋ አወቀ። (ኢሳ. 2:2-4፤ ዮሐ. 18:36፤ ኤፌ. 6:12) በዚህ ወቅት በብሪታንያ የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች ምን አጋጠማቸው?
ሄንሪ ሃድሰን
በ1916 በብሪታንያ ከ18 እስከ 40 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ያላገቡ ወንዶች በውትድርና አገልግሎት እንዲካፈሉ የሚያዝ ሕግ ወጣ። ይህ ሕግ “በሃይማኖት ወይም በሥነ ምግባር አቋም” ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ከግዳጅ ነፃ እንዲሆኑ የሚያስችል ዝግጅት ነበረው። የብሪታንያ መንግሥት ከግዳጅ ነፃ ሊሆኑ የሚገባቸው እነማን እንደሆኑና ምን ዓይነት ነፃነት እንደሚሰጣቸው የሚወስን ልዩ ችሎት ሰየመ።
በአጭር ጊዜ ውስጥ 40 የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በወታደራዊ ወኅኒ ቤት የታሰሩ ሲሆን 8 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ደግሞ ለውጊያ ወደ ፈረንሳይ ተላኩ። ይህ ኢፍትሐዊ ድርጊት በብሪታንያ የሚገኙ ወንድሞች እስራቱን እንደሚቃወሙ የሚገልጽ ደብዳቤና እስረኞቹ እንዲፈቱ የሚጠይቅ የ5,500 ሰዎችን ፊርማ የያዘ ሰነድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኸርበርት አስክዊዝ እንዲልኩ አነሳሳቸው።
ወደ ፈረንሳይ የተላኩት ስምንቱ አንዋጋም በማለታቸው እንዲረሸኑ እንደተፈረደባቸው የሚገልጽ ወሬ ተሰማ። ይሁንና ወንድሞች ሊረሸኑ ቆመው ሳለ ውሳኔው ተለውጦ ከባድ የጉልበት ሥራ እየሠሩ ለአሥር ዓመት እንዲታሰሩ ተበየነባቸው። የእስራት ዘመናቸውን ወታደራዊ ባልሆነ እስር ቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ ወደ እንግሊዝ መልሰው ላኳቸው።
ጄምስ ፍሬድሪክ ስኮት
ጦርነቱ እየተራዘመ ሲሄድ ያገቡ ወንዶችንም ለጦርነት መመልመል ተጀመረ። በማንቸስተር፣ እንግሊዝ ለሌሎች ተመሳሳይ ክሶችም መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ብያኔ ለመስጠት ሲባል የሕክምና ዶክተርና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሆነው ሄንሪ ሃድሰን የተከሰሰበት ጉዳይ ችሎት ፊት ቀርቦ ነበር። በነሐሴ 3, 1916 ፍርድ ቤቱ ሄንሪ ለሕግ ባለመገዛት ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል የሚል ብያኔ አስተላለፈ፤ በዚህም ምክንያት የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ከመሆኑም ሌላ ለጦር ኃይሉ አሳልፈው ሰጡት። በዚሁ ጊዜ በኤድንበርግ፣ ስኮትላንድ ለተመሳሳይ ጉዳዮች መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ደንብ ለማውጣት ሌላ ችሎት ተሰይሞ ነበር። ችሎቱ ኮልፖርተር ሆኖ የሚያገለግለው የ25 ዓመቱ ጄምስ ፍሬድሪክ ስኮት ምንም ጥፋት የለበትም የሚል ብያኔ ሰጠ። አቃቤ ሕጉ ይግባኝ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ይግባኙን በመተው በለንደን የተመሠረተውን ተመሳሳይ ክስ ለመከራከር መረጠ። በዚህ ጊዜ ኸርበርት ኪፕስ የተባለ ወንድም ጥፋተኛ ነው የሚል ብያኔ ስለተላለፈበት የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ከመሆኑም ሌላ ለጦር ኃይሉ አሳልፈው ሰጡት።
በመስከረም 1916 በድምሩ 264 የሚሆኑ ወንድሞች ከውትድርና አገልግሎት ነፃ ለመሆን ማመልከቻ አስገቡ። ከእነዚህ መካከል 5ቱ ከግዳጅ ነፃ እንዲሆኑ ተፈቀደላቸው፤ 154ቱ “በአገር ግንባታ ሥራ” እንዲካፈሉ፣ 23ቱ ደግሞ በሠራዊቱ ውስጥ ሆነው ጦር ግንባር መሰለፍ የማይጠይቅ ሥራ እንዲያከናውኑ ተወሰነባቸው። የተቀሩትን 82 ወንድሞች ለጦር ኃይሉ አሳልፈው የሰጧቸው ሲሆን አንዳንዶቹ የተሰጣቸውን መመሪያ ሳይታዘዙ ቀርተዋል በሚል ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዲታይ ተደርጓል። እነዚህ ሰዎች እስር ቤት ከደረሰባቸው ግፍ የተነሳ ሕዝቡ ተቃውሞ በማሰማቱ መንግሥት ከወታደራዊ እስር ቤት አውጥቶ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች አዛወራቸው።
ፕራይስ ሂዩዝ
ኤድገር ክሌይ እና ከጊዜ በኋላ በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለው ፕራይስ ሂዩዝ በዌልስ ይካሄድ በነበረው የግድብ ፕሮጀክት ላይ እንዲሠሩ ተደርገዋል። በሌላ በኩል ከፈረንሳይ እንዲመለሱ ከተደረጉት ከስምንቱ መካከል አንዱ የሆነው ኸርበርት ሲንየር በዮርክሺር ወደሚገኘው ዌክፊልድ እስር ቤት ተላከ። ሌሎች ደግሞ በአስከፊነቱ በሚታወቀው የዳርትሙር እስር ቤት ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ተወስኖባቸዋል፤ በዚህ እስር ቤት ከሕሊናቸው የተነሳ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወንድሞች ታስረው ነበር።
ፍራንክ ፕላት የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከጦርነት ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ሥራዎች ለመሥራት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ወደ ጦር ግንባር ተወስዶ እንዲዋጋ ሲታዘዝ ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ለረጅም ጊዜ ከባድ መከራ ደርሶበታል። ለውትድርና አገልግሎት ከተመዘገበ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እውነትን የሰማው አትከንሰን ፓጀት አልዋጋም በማለቱ ወታደራዊ ባለሥልጣናቱ ከባድ ሥቃይ አድርሰውበታል።
ኸርበርት ሲንየር
በዚያ ዘመን የነበሩት ወንድሞቻችን ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋምን በተመለከተ የተሟላ ግንዛቤ ያልነበራቸው ቢሆንም ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት ጥረት አድርገዋል። በዚህ ሪፖርት ውስጥ በስም የተጠቀሱት ወንድሞቻችን በዓይነቱ ልዩ የሆነ “የፈተና ሰዓት” በገጠማቸው ጊዜ በገለልተኝነት አቋም ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተዋል። (ራእይ 3:10)—ከታሪክ ማኅደራችን፣ ብሪታንያ