የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w17 ሚያዝያ ገጽ 9-13
  • የአምላክ መንግሥት ሲመጣ የትኞቹ ነገሮች ይወገዳሉ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአምላክ መንግሥት ሲመጣ የትኞቹ ነገሮች ይወገዳሉ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ክፉ ሰዎች
  • ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች
  • መጥፎ ድርጊቶች
  • የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች
  • ከአርማጌዶን በኋላ ምድር ገነት ትሆናለች
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የምናገኘው መዳን ቀርቧል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ይህ ዓለም ይጠፋል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2021
  • መከራ የሚወገድበት ጊዜ ቀርቧል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
w17 ሚያዝያ ገጽ 9-13
ኢየሱስ በነጭ ፈረስ ላይ እየጋለበ የሰማይ ሠራዊት ሲከተለው

የአምላክ መንግሥት ሲመጣ የትኞቹ ነገሮች ይወገዳሉ?

“ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐ. 2:17

መዝሙሮች፦ 139, 144

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ይሖዋ ከክፉ ሰዎችና ምግባረ ብልሹ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ምን ያደርጋል?

  • ይሖዋ መጥፎ ድርጊቶችንና የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን ከምድር ላይ የሚያስወግደው እንዴት ነው?

  • ይህ ክፉ ዓለም በሚጠፋበት ጊዜ በሕይወት ለመትረፍ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

1, 2. (ሀ) ይህ ሥርዓት ሞት ከተፈረደበት እስረኛ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ይህ ክፉ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ፍጥረታት ምን ይሰማቸዋል?

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። የወኅኒ ቤት ጠባቂዎች አንድን አደገኛ ወንጀለኛ ከታሰረበት ክፍል አውጥተው እየወሰዱት ነው። እስረኛውን ያጀቡት ጠባቂዎች “የሞተ ሰው እያለፈ ነው!” እያሉ ይጮኻሉ። እንዲህ የሚሉት ለምንድን ነው? እስረኛው ሲታይ ጤናማ ይመስላል፤ ሕይወቱን ሊያሳጣው የሚችል ምንም ዓይነት ሕመም ያለበትም አይመስልም። ሆኖም ጠባቂዎቹ ይህን እስረኛ እየወሰዱት ያሉት ወደሚገደልበት ቦታ ነው። ሞት የተፈረደበት ይህ እስረኛ በሕይወት ያለ ቢሆንም የሞተ ያህል ነው።a

2 ይህ ሥርዓትም ሞት ከተፈረደበት እስረኛ ጋር ይመሳሰላል። የምንኖርበት ክፉ ዓለም ጥፋት ከተፈረደበት ቆይቷል፤ ፍርዱ የሚፈጸምበት ጊዜም በጣም ቀርቧል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለም ያልፋል’ ይላል። (1 ዮሐ. 2:17) ይህ ሥርዓት እንደሚጠፋ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና በዚህ ዓለም እና በእስረኛው መካከል አንድ ትልቅ ልዩነት አለ። ወንጀለኛው ሊገደል ሲል አንዳንዶች ፍርዱን ሊቃወሙና ፍትሐዊ ስለመሆኑ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፤ በዚህ መንገድ በእስረኛው ላይ የተላለፈውን ብያኔ ለማስቀየር ይሞክሩ ይሆናል። ከዚህ ዓለም ሁኔታ ጋር በተያያዘ ግን ፍርዱን ያስተላለፈው ፈጽሞ ፍትሕ የማያጓድለው የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ነው። (ዘዳ. 32:4) በመሆኑም ፍርዱ ሳይፈጸም የሚዘገይበት ምንም ምክንያት የለም፤ ፍትሐዊ ስለመሆኑም ጥያቄ የሚፈጥር ነገር አይኖርም። ፍርዱ ከተፈጸመ በኋላ፣ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኝ የማሰብ ችሎታ ያለው ፍጥረት ሁሉ እርምጃው ፍትሐዊ መሆኑን ጨርሶ አይጠራጠርም። በዚያ ጊዜ ታላቅ እፎይታ ይሆናል!

3. የአምላክ መንግሥት ሲመጣ ከሚያስወግዳቸው ነገሮች መካከል የትኞቹን እንመለከታለን?

3 ይሁንና ‘ያልፋል’ የተባለው “ዓለም” የትኞቹን ነገሮች ያካትታል? በዛሬው ጊዜ ብዙዎች፣ በዚህ ዓለም ላይ ምንጊዜም እንደሚኖሩ አድርገው የሚያስቧቸውን በርካታ ነገሮች ያካትታል፤ እነዚህ በሙሉ ይወገዳሉ። ይህ መጥፎ ዜና ነው? በፍጹም! እንዲያውም “የመንግሥቱ ምሥራች” ከሚያካትታቸው ነገሮች አንዱ ይህ ነው። (ማቴ. 24:14) የአምላክ መንግሥት ሲመጣ ከሚያስወግዳቸው ነገሮች መካከል ክፉ ሰዎች፣ ምግባረ ብልሹ ድርጅቶች፣ መጥፎ ድርጊቶች እንዲሁም የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ይገኙበታል። ከእነዚህ ነገሮች ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ (1) እነዚህ ነገሮች በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? (2) ይሖዋ ምን እርምጃ ይወስዳል? (3) እነዚህን ነገሮች በምን ይተካቸዋል?

ክፉ ሰዎች

4. ክፉ ሰዎች በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

4 ክፉ ሰዎች በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የምንኖርበት ጊዜ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” እንደሚሆን ትንቢት ከተናገረ በኋላ “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (2 ጢሞ. 3:1-5, 13) ይህ ትንቢት እየተፈጸመ እንደሆነ አስተውለሃል? ብዙዎቻችን በክፉ ሰዎች ይኸውም በጉልበተኞች፣ ጭፍን ጥላቻ ባላቸው ግለሰቦችና ጨካኝ በሆኑ ወንጀለኞች ጥቃት ደርሶብን ያውቃል። ከእነዚህ አንዳንዶቹ የክፋት ድርጊታቸውን ለመደበቅ እንኳ አይሞክሩም፤ ሌሎች ደግሞ መልካም መስለው በመቅረብ የክፋት ድርጊታቸውን ለመሸፈን የሚሞክሩ አስመሳዮች ናቸው። እንዲህ ያለ ጥቃት ደርሶብን የማያውቅ ቢሆን እንኳ ክፉ ሰዎች በእኛ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። ክፉዎች የሚፈጽሟቸውን ዘግናኝ ድርጊቶች ስንሰማ በጣም እናዝናለን። እነዚህ ሰዎች በልጆች፣ በአረጋውያን እንዲሁም አቅመ ደካማ በሆኑ ሌሎች ሰዎች ላይ ግፍ ሲፈጽሙ ስሜታችን በጣም ይረበሻል። ክፉ ሰዎች የሚፈጽሙት ድርጊት ኢሰብዓዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። (ያዕ. 3:15) የሚያስደስተው ነገር የአምላክ ቃል የሚያጽናና ምሥራች ይዟል።

5. (ሀ) ክፉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ምን አጋጣሚ አላቸው? (ለ) ለመለወጥ እምቢተኛ የሆኑ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆናል?

5 ይሖዋ ምን እርምጃ ይወስዳል? ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ክፉ ሰዎች እንዲለወጡ አጋጣሚውን ሰጥቷቸዋል። (ኢሳ. 55:7) በግለሰብ ደረጃ ፍርድ አልተበየነባቸውም። ጥፋት የተፈረደበት ይህ ሥርዓት ነው። ይሁንና ለመለወጥ እምቢተኛ የሆኑና ታላቁ መከራ እስኪጀምር ድረስ ይህን ሥርዓት የሚደግፉ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆናል? ይሖዋ ክፉ ሰዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድር ላይ እንደሚያስወግዳቸው ቃል ገብቷል። (መዝሙር 37:10⁠ን አንብብ።) ክፉዎች ከዚህ ፍርድ ማምለጥ እንደሚችሉ ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች፣ የሚሠሩት መጥፎ ድርጊት እንዳይታወቅባቸው ማድረግ በመቻላቸው አብዛኛውን ጊዜ ከቅጣት ያመልጣሉ። (ኢዮብ 21:7, 9) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ዓይኖች የሰውን መንገድ ይመለከታሉና፤ ደግሞም እርምጃውን ሁሉ ያያል። ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የሚደበቁበት ጨለማም ሆነ ፅልማሞት የለም።” (ኢዮብ 34:21, 22) ከይሖዋ አምላክ መሰወር አይቻልም። ማንኛውም አስመሳይ እሱን ማታለል አይችልም፤ የትኛውም ዓይነት ድርጊት ከእሱ እይታ ውጪ አይደለም። በመሆኑም ከአርማጌዶን በኋላ ክፉዎችን በቀድሞ ቦታቸው ብንፈልጋቸው ልናገኛቸው አንችልም። ከዚያ በኋላ ደብዛቸው አይገኝም!—መዝ. 37:12-15

6. ክፉዎች ሲጠፉ በምድር ላይ የሚቀሩት እነማን ይሆናሉ? ይህስ የምሥራች ነው የምንለው ለምንድን ነው?

6 ክፉ ሰዎች ሲጠፉ በምድር ላይ የሚቀሩት እነማን ይሆናሉ? ይሖዋ “የዋሆች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል” የሚል አስደሳች ተስፋ ሰጥቷል። በዚሁ መዝሙር ላይ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል ሐሳብ ሰፍሮ እናገኛለን። (መዝ. 37:11, 29) “የዋሆች” እና “ጻድቃን” የተባሉት እነማን ናቸው? የዋሆች የተባሉት ይሖዋ የሚሰጠውን ትምህርትና መመሪያ በትሕትና የሚቀበሉ ሰዎች ናቸው፤ ጻድቃን የተባሉት ደግሞ በይሖዋ አምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የሚወዱ ሰዎች ናቸው። በዛሬው ጊዜ የክፉዎች ቁጥር ከጻድቃን በእጅጉ ይበልጣል። ይሁንና በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ንጽጽር አይኖርም፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩት የዋሆችና ጻድቃን ብቻ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ምድርን ወደ ገነትነት ይቀይራሉ!

ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች

7. ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው?

7 ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? በዚህ ዓለም ላይ አብዛኛውን የክፋት ድርጊት የሚፈጽሙት ግለሰቦች ሳይሆኑ ድርጅቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የሃይማኖት ድርጅቶች ስለ አምላክ ማንነት፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት፣ ስለ ምድርና ስለ ሰው ልጆች የወደፊት ዕጣ እንዲሁም ስለ ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የተሳሳተ ትምህርት በማስተማር ብዙዎችን ያታልላሉ። ምግባረ ብልሹ የሆኑ መንግሥታት ደግሞ ጦርነትንና የጎሳ ግጭትን ይቆሰቁሳሉ፤ እንዲሁም ድሆችንና ደካሞችን ይበዘብዛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ስግብግብ የሆኑ የንግድ ድርጅቶች አካባቢን ይበክላሉ፣ የተፈጥሮ ሀብትን ይመዘብራሉ እንዲሁም ደንበኞቻቸውን ያጭበረብራሉ፤ በዚህም ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት እየማቀቁ ጥቂቶች ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ያጋብሳሉ። በእርግጥም በዓለም ላይ ላሉት በርካታ ችግሮች ተጠያቂ የሚሆኑት ምግባረ ብልሹ ድርጅቶች ናቸው።

8. መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ያሉትን የማይናወጡ መስለው የሚታዩ ድርጅቶች አስመልክቶ ምን ይላል?

8 ይሖዋ ምን እርምጃ ይወስዳል? የፖለቲካ ኃይሎች አመንዝራ በሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን በተመሰሉት በሁሉም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሲነሱ ታላቁ መከራ ይጀምራል። (ራእይ 17:1, 2, 16፤ 18:1-4) እነዚህ የሃይማኖት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ። ምግባረ ብልሹ ስለሆኑት ሌሎች ድርጅቶችስ ምን ማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ያሉትን የማይናወጡ መስለው የሚታዩ በርካታ ድርጅቶችና ተቋማት በተራሮችና በደሴቶች ይመስላቸዋል። (ራእይ 6:14⁠ን አንብብ።) የአምላክ ቃል መንግሥታትና የአምላክን መንግሥት የማይደግፉ ሌሎች ድርጅቶች በሙሉ ከመሠረታቸው እንደሚናጉ ይናገራል። በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ ያሉ መንግሥታትም ሆነ ከእነሱ ጎን የተሰለፉ ድርጅቶች በሙሉ ሲጠፉ ታላቁ መከራ ይደመደማል። (ኤር. 25:31-33) ከዚያ በኋላ አንድም ምግባረ ብልሹ ድርጅት አይኖርም!

9. አዲሱ ምድር በሥርዓት የተደራጀ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

9 ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች በምን ይተካሉ? ከአርማጌዶን በኋላ በምድር ላይ የሚቀር ድርጅት ይኖራል? መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል” ይላል። (2 ጴጥ. 3:13) አሮጌው ሰማይና ምድር ማለትም ምግባረ ብልሹ መንግሥታትም ሆኑ በእነሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ክፉው ኅብረተሰብ ይወገዳሉ። ከዚያም ‘በአዲስ ሰማያትና በአዲስ ምድር’ ይተካሉ። “አዲስ ሰማያት” የሚለው አገላለጽ አዲስ መንግሥትን የሚያመለክት ሲሆን “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ ደግሞ በዚህ መንግሥት የሚተዳደርን በምድር ላይ የሚኖር አዲስ ኅብረተሰብ ያመለክታል። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው ይህ መንግሥት፣ ሁሉ ነገር በሥርዓት እንዲከናወን የሚፈልገውን የይሖዋ አምላክን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል። (1 ቆሮ. 14:40) “አዲስ ምድር” የተባለው በምድር ላይ የሚኖረው ኅብረተሰብም በሥርዓት የተደራጀ ይሆናል። በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያከናውኑ መልካም ምግባር ያላቸው ወንዶች ይሾማሉ። (መዝ. 45:16) እነዚህን ወንዶች የሚመሯቸው ክርስቶስና ከእሱ ጋር የሚገዙት 144,000ዎች ይሆናሉ። ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች በሙሉ ተወግደው መልካም ምግባር ባለው አንድ ድርጅት ሲተኩ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር እስቲ አስበው!

መጥፎ ድርጊቶች

10. በምትኖርበት አካባቢ የትኞቹ መጥፎ ድርጊቶች ተስፋፍተዋል? ይህስ በአንተና በቤተሰብህ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

10 መጥፎ ድርጊቶች በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? የምንኖረው መጥፎ ድርጊቶች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። የሥነ ምግባር ብልግና፣ ማጭበርበር እንዲሁም ጭካኔ የሚንጸባረቅባቸው ድርጊቶች የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲህ ካለው መጥፎ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ከፍተኛ ትግል ማድረግ አለባቸው። የመዝናኛው ኢንዱስትሪ፣ ትክክልና ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በማቃለል መጥፎ ድርጊቶችን ማራኪ አድርጎ እያቀረበ ነው። (ኢሳ. 5:20) እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህ ዓይነቱ አመለካከት እንዳይጋባባቸው ይጠነቀቃሉ። ሰዎች ለይሖዋ መሥፈርቶች ያላቸው አክብሮት እየቀነሰ እንዲሄድ በሚያደርግ ዓለም ውስጥ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው ለመኖር ይታገላሉ።

11. ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ ከወሰደው እርምጃ ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 ይሖዋ ምን እርምጃ ይወስዳል? በሰዶምና በገሞራ ተስፋፍቶ ከነበረው መጥፎ ድርጊት ጋር በተያያዘ ይሖዋ ምን እርምጃ እንደወሰደ አስታውስ። (2 ጴጥሮስ 2:6-8⁠ን አንብብ።) ጻድቁ ሎጥና ቤተሰቡ በአካባቢያቸው በሚፈጸመው መጥፎ ድርጊት ይሳቀቁ ነበር። ይሖዋ ያንን አካባቢ በማጥፋት የወሰደው እርምጃ በዚያ የነበረውን ክፋት ከማስወገዱም ሌላ ዛሬ ባሉት ‘ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች’ ላይ ምን እንደሚያደርግ የሚያሳይ “ምሳሌ” ሆኗል። ይሖዋ በዚያ ወቅት ይፈጸም የነበረውን ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት በሙሉ እንዳስወገደው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያለውን ሥርዓት በማጥፋት ምድርን ከማንኛውም መጥፎ ድርጊት ያጸዳል።

12. ይህ አሮጌ ሥርዓት ሲወገድ በየትኞቹ ሥራዎች ለመካፈል ትጓጓለህ?

12 መጥፎ ድርጊቶች በምን ይተካሉ? ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች አስደሳች በሆኑ ሥራዎች ይጠመዳሉ። ይህችን ፕላኔት ወደ ገነትነት መቀየር እንዲሁም ለራሳችንም ሆነ ለምንወዳቸው ሰዎች ቤቶችን መሥራት ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው። በተጨማሪም ከሞት የሚነሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የመቀበልና እነዚህን ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲሁም ለሰው ልጆች ስላደረጋቸው ነገሮች የማስተማር አጋጣሚ ይኖረናል። (ኢሳ. 65:21, 22፤ ሥራ 24:15) በዚያን ጊዜ ለእኛ ደስታ ለይሖዋ ደግሞ ውዳሴ በሚያመጡ ሥራዎች እንጠመዳለን!

የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች

13. ሰይጣን እንዲሁም አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ ማመፃቸው ምን አስጨናቂ ሁኔታ አስከትሏል?

13 የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? ክፉ ሰዎች፣ ምግባረ ብልሹ የሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም መጥፎ ድርጊቶች አንድ ላይ ተዳምረው በምድር ላይ ያለው ሁኔታ የሚያስጨንቅ እንዲሆን አድርገዋል። በጦርነት፣ በድህነት፣ በዘር መድልዎ ወይም በበሽታ ያልተጎዳ አሊያም ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን ያልቀመሰ ማን አለ? ከእነዚህ ችግሮች ማናችንም ማምለጥ አንችልም። ለእነዚህ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች መንስኤ የሆነው ሰይጣን እንዲሁም አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ ማመፃቸው ነው። ይህ ዓመፅ ያስከተለው መዘዝ ለእኛም ተርፏል።

14. ይሖዋ ከሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ምን እርምጃ ይወስዳል? ምሳሌ ስጥ።

14 ይሖዋ ምን እርምጃ ይወስዳል? እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። ይሖዋ ጦርነትን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 46:8, 9⁠ን አንብብ።) ስለ ሕመምስ ምን ማለት ይቻላል? ሕመምንም ቢሆን ጨርሶ ያስቀረዋል። (ኢሳ. 33:24) ሞትን ለዘላለም ይውጣል! (ኢሳ. 25:8) ድህነትንም ያስወግዳል። (መዝ. 72:12-16) በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆች ሕይወት በሥቃይ የተሞላ እንዲሆን ያደረጉ ሌሎች የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋቸዋል። ሰይጣንና አጋንንቱ በመላው ዓለም ላይ እያሳደሩ ያሉት መጥፎ ተጽዕኖ ስለሚወገድ በዚህ ዓለም ውስጥ ያለው መጥፎ “አየር” ያን ጊዜ አይኖርም።—ኤፌ. 2:2

ጦርነት፣ በሽታ ወይም ሞት በሌለበት ዓለም ውስጥ በደስታ የሚኖሩ አዋቂዎችና ልጆች

ጦርነት፣ በሽታ ወይም ሞት የሌለበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል አስበው! (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. ከአርማጌዶን በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሚወገዱት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

15 ጦርነት፣ በሽታ ወይም ሞት የሌለበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ትችላለህ? በዚያን ጊዜ የምድር ጦር፣ የባሕር ኃይል ወይም የአየር ኃይል የሚባል ነገር አይኖርም! የጦር መሣሪያም ሆነ የጦርነት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሚዘጋጅ መታሰቢያ አይኖርም። ሆስፒታሎች፣ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ የጤና መድን፣ የአስከሬን ማቆያ ቦታዎች፣ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅቶች ወይም የመቃብር ቦታዎች አያስፈልጉም! በተጨማሪም ወንጀል ስለሚወገድ ዘራፊዎችን ለመከላከል የሚገጠሙ የማስጠንቀቂያ ደወሎችም ሆኑ ፖሊሶች አይኖሩም፤ ሌላው ቀርቶ ቁልፍ እንኳ ላያስፈልግ ይችላል! አእምሯችንን እና ልባችንን የሚያስጨንቁት እነዚህ ነገሮች ሲወገዱ ምን ያህል እፎይ እንደምንል እስቲ አስበው።

16, 17. (ሀ) ከአርማጌዶን የሚተርፉ ሰዎች ምን ዓይነት እፎይታ ያገኛሉ? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ይህ ክፉ ዓለም በሚጠፋበት ጊዜ በሕይወት ለመትረፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲወገዱ በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል? ይህን መገመት ሊከብደን ይችላል። ሕይወታችንን በሙሉ ያሳለፍነው በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ከመሆኑ አንጻር በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች ምን ያህል ጭንቀት እንደሚፈጥሩብን ላናስተውል እንችላለን። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ሕዝብ በሚበዛበት የባቡር ጣቢያ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁካታውን ይለምዱት ይሆናል፤ በቆሻሻ መጣያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችም እንዲሁ ሽታው ላይረብሻቸው ይችላል። በአሁኑ ጊዜ ያሉት አስጨናቂ ሁኔታዎች በሙሉ ሲወገዱ እንዴት ያለ እፎይታ እናገኝ ይሆን!

17 በዛሬው ጊዜ የሚሰማን ጭንቀት ሲወገድ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማን ይሆን? መዝሙር 37:11 ‘የዋሆች በብዙ ሰላም እጅግ ደስ ይላቸዋል’ በማለት መልሱን ይሰጠናል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ደስታ እንድናገኝ እንደሚፈልግ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! እንግዲያው በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ከይሖዋ አምላክና ከድርጅቱ ጋር ተቀራርበህ ለመኖር የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ውድ የሆነውን ተስፋህን ከፍ አድርገህ ተመልከተው፤ በተስፋህ ላይ በማሰላሰል እውን ሆኖ እንዲታይህ አድርግ፤ እንዲሁም ስለ ተስፋህ ለሌሎች ተናገር። (1 ጢሞ. 4:15, 16፤ 1 ጴጥ. 3:15) እንዲህ ካደረግህ ከዚህ አሮጌ ዓለም ጋር አብረህ አትጠፋም። ከዚህ ይልቅ በሕይወት ተርፈህ ለዘላለም በደስታ ትኖራለህ!

a ይህ አንቀጽ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት በአንዳንድ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች በሚገኙ እስር ቤቶች ውስጥ የነበረውን ልማድ የሚገልጽ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ