ስለ ፍትሕ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አለህ?
“የይሖዋን ስም አውጃለሁ . . . እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው።”—ዘዳ. 32:3, 4
1, 2. (ሀ) ናቡቴና ልጆቹ ምን ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ሁለት ባሕርያት እንመረምራለን?
እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። አንድ ሰው በሞት በሚያስቀጣ ወንጀል ተከሷል። በዚህ ሰው ላይ ፍርድ የተበየነው፣ የማይረቡ እንደሆኑ የሚታወቁ ሰዎች የሰጡትን የሐሰት ምሥክርነት መሠረት በማድረግ ነው፤ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ ይህን ማወቃቸው ምን ያህል እንደሚያስደነግጣቸውና እንደሚያሳዝናቸው መገመት ይቻላል። ፍትሕን የሚወዱ ግለሰቦች፣ ይህ ንጹሕ ሰውና ልጆቹ ሲገደሉ በማየታቸው ስሜታቸው በጣም እንደሚረበሽ ጥያቄ የለውም። ይህ ታሪክ ልበ ወለድ አይደለም። በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ዘመን ይኖር የነበረ ናቡቴ የተባለ የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ ያጋጠመው ሁኔታ ነው።—1 ነገ. 21:11-13፤ 2 ነገ. 9:26
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ ናቡቴ ስለደረሰበት ግፍ እንመለከታለን፤ በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ ታማኝ የጉባኤ ሽማግሌ ስለፈጸመው ስህተት እንወያያለን። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ስንመረምር ስለ ፍትሕ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ትሕትና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንማራለን። ከዚህም ሌላ በጉባኤ ውስጥ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ስንመለከት ይቅር ባይ መሆናችን፣ ፍትሕ በማሳየት ረገድ ይሖዋን ለመምሰል እንዴት እንደሚረዳን እናያለን።
ከባድ የፍትሕ መጓደል
3, 4. ናቡቴ ምን ዓይነት ሰው ነበር? የወይን እርሻውን ለንጉሥ አክዓብ መሸጥ ያልፈለገውስ ለምንድን ነው?
3 አብዛኞቹ እስራኤላውያን የንጉሥ አክዓብንና ክፉ የሆነችውን የንግሥት ኤልዛቤልን መጥፎ ምሳሌ ይከተሉ በነበረበት ወቅት ናቡቴ ይሖዋን በታማኝነት ያገለግል ነበር። እነዚህ የባአል አምላኪዎች ለይሖዋም ሆነ እሱ ላወጣቸው መሥፈርቶች ምንም ዓይነት አክብሮት አልነበራቸውም። በሌላ በኩል ግን ናቡቴ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ከሕይወቱ እንኳ ይበልጥ ከፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር።
4 አንደኛ ነገሥት 21:1-3ን አንብብ። አክዓብ የናቡቴን የወይን እርሻ ለመግዛት አሊያም የተሻለ የወይን እርሻ ቦታ በምትኩ ለናቡቴ ለመስጠት ፈልጎ ነበር፤ ናቡቴ ግን በዚህ አልተስማማም። ለምን? “የአባቶቼን ርስት ለአንተ መስጠት በይሖዋ ፊት ተገቢ ስላልሆነ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው” በማለት ለአክዓብ በአክብሮት መለሰለት። ናቡቴ የአክዓብን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነው፣ ይሖዋ የአንድ ነገድ ውርስ ለዘለቄታው እንዳይሸጥ ለእስራኤል ብሔር የሰጠውን ሕግ ስለሚያውቅ ነው። (ዘሌ. 25:23፤ ዘኁ. 36:7) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ናቡቴ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ነበረው።
5. ኤልዛቤል የናቡቴን የእርሻ ቦታ ለማግኘት ስትል ምን አደረገች?
5 የሚያሳዝነው ነገር ናቡቴ የወይን እርሻውን ለመሸጥ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ንጉሥ አክዓብና ሚስቱ መጥፎ የሆነ እርምጃ ወሰዱ። ኤልዛቤል፣ ባሏ የናቡቴን የወይን እርሻ እንዲያገኝ ለማድረግ ስትል ናቡቴ በሐሰት እንዲወነጀል ሴራ ጠነሰሰች፤ በዚህም ምክንያት ናቡቴና ልጆቹ ተገደሉ። ታዲያ ይሖዋ ከዚህ ከባድ የፍትሕ መጓደል ጋር በተያያዘ ምን እርምጃ ወሰደ?
ጽድቅ የተንጸባረቀበት የአምላክ ፍርድ
6, 7. ይሖዋ ፍትሕን እንደሚወድ ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ የናቡቴን ዘመዶችና ወዳጆች ያጽናናቸው ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ ወዲያውኑ ኤልያስን በመላክ አክዓብ በወሰደው እርምጃ አለመደሰቱን እንዲያሳውቀው አደረገ። ኤልያስም ለአክዓብ ነፍሰ ገዳይና ዘራፊ መሆኑን ነገረው። ታዲያ ይሖዋ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያስተላለፈው ፍርድ ምን ነበር? አክዓብ፣ ሚስቱና ልጆቹ የናቡቴና የልጆቹ ዕጣ ይደርስባቸዋል።—1 ነገ. 21:17-25
7 የናቡቴ ቤተሰቦችና ወዳጆች፣ አክዓብ የእነዚህን ንጹሐን ሕይወት በማጥፋቱ ከባድ ሐዘን እንደተሰማቸው ጥያቄ የለውም፤ ያም ቢሆን ይሖዋ የተፈጸመውን ኢፍትሐዊ ድርጊት እንደተመለከተና ወዲያውኑ ፍርድ እንዳስተላለፈ ማወቃቸው አጽናንቷቸው መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የተፈጸሙትን ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲመለከቱ ትሕትናቸውና በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነት ሳይፈተን አልቀረም።
8. አክዓብ ይሖዋ ያስተላለፈውን ፍርድ ሲሰማ ምን እርምጃ ወሰደ? ይሖዋስ ይህን ሲያይ ምን አደረገ?
8 አክዓብ፣ ይሖዋ ያስተላለፈውን ኃይለኛ ፍርድ ሲሰማ ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ “ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ ጾመ፤ እንዲሁም ማቅ ላይ ይተኛና በሐዘን ተኮራምቶ ይሄድ ነበር” ይላል። አክዓብ ራሱን አዋረደ! ታዲያ ይሖዋ ይህን ሲያይ ምን አደረገ? ይሖዋ ለኤልያስ እንዲህ አለው፦ “ራሱን በፊቴ ስላዋረደ ላመጣበት የነበረውን ጥፋት በእሱ ዘመን አላመጣም። ከዚህ ይልቅ በእሱ ቤት ላይ ጥፋት የማመጣው በልጁ ዘመን ነው።” (1 ነገ. 21:27-29፤ 2 ነገ. 10:10, 11, 17) “ልብን የሚመረምር” አምላክ የሆነው ይሖዋ ለአክዓብ በተወሰነ መጠን ምሕረት አሳይቶታል።—ምሳሌ 17:3
ትሕትና ጥበቃ ያስገኛል
9. የናቡቴ ቤተሰብና ወዳጆቹ ትሕትናን ማዳበራቸው ጠቅሟቸው ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
9 አክዓብ የፈጸመውን አስከፊ ድርጊት የሚያውቁ ሰዎች የይሖዋን ውሳኔ ሲሰሙ ምን ተሰምቷቸው ይሆን? የናቡቴ ቤተሰብና ወዳጆች፣ በአክዓብ ቤተሰብ ላይ የተላለፈው ፍርድ እሱ በሕይወት እያለ እንደማይፈጸም ሲያውቁ እምነታቸው ተፈትኖ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ትሕትና እምነታቸውን እንዳያጡ ረድቷቸው መሆን አለበት፤ ትሑት ከሆኑ አምላካቸው ፈጽሞ ፍትሕን እንደማያጓድል በመተማመን ይሖዋን በታማኝነት ማምለካቸውን ይቀጥላሉ። (ዘዳግም 32:3, 4ን አንብብ።) ናቡቴ፣ ልጆቹና ቤተሰቦቻቸው ይሖዋ ጻድቃንን ከሞት በሚያስነሳበት ወቅት ፍትሕ በተሟላ ሁኔታ ሲፈጸም ያያሉ። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐ. 5:28, 29) ከዚህም በተጨማሪ ትሑት የሆነ ሰው “እውነተኛው አምላክ እያንዳንዱን የተሰወረ ነገር ጨምሮ ማንኛውንም ሥራ፣ ጥሩም ይሁን መጥፎ ወደ ፍርድ [እንደሚያመጣው]” ይገነዘባል። (መክ. 12:14) በእርግጥም ይሖዋ ፍርድ ሲያስተላልፍ፣ እኛ የማናውቃቸውን ጉዳዮችም ግምት ውስጥ ያስገባል። በመሆኑም ትሑት መሆናችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እንዳናጣ ጥበቃ ይሆንልናል።
10, 11. (ሀ) ከፍትሕ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ሁኔታዎች ፈታኝ ሊሆኑብን ይችላሉ? (ለ) ትሕትና ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?
10 ሽማግሌዎች፣ ምክንያቱ ግልጽ ያልሆነልህ ምናልባትም የማትስማማበት አንድ ውሳኔ ቢያስተላልፉ ምን ታደርጋለህ? ለምሳሌ፣ ከፍ አድርገህ የምትመለከተውን የአገልግሎት መብት ብታጣ ወይም አንድ የምትወደው ሰው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመው ምን ይሰማሃል? የትዳር ጓደኛህ፣ ልጅህ ወይም የቅርብ ወዳጅህ ከጉባኤ ቢወገድና በውሳኔው ባትስማማስ? ኃጢአት ለሠራ ሰው የተደረገለት ምሕረት ተገቢ እንዳልሆነ ቢሰማህስ? እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለን እምነት እንዲፈተን ሊያደርጉ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ፈተና ቢያጋጥምህ ትሕትና ጥበቃ የሚሆንልህ እንዴት ነው? ሁለት መንገዶችን እንመልከት።
ሽማግሌዎች አንተ የማትስማማበት አንድ ውሳኔ ቢያስተላልፉ ምን ታደርጋለህ? (አንቀጽ 10, 11ን ተመልከት)
11 በመጀመሪያ፣ ትሕትና የማናውቀው ነገር ሊኖር እንደሚችል አምነን እንድንቀበል ይረዳናል። ስለ አንድ ሁኔታ በደንብ እንደምናውቅ ቢሰማንም እንኳ የሰዎችን ልብ ማንበብ የሚችለው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (1 ሳሙ. 16:7) ይህን እውነታ መገንዘባችን ትሑት እንድንሆን፣ የማናውቀው ነገር ሊኖር እንደሚችል አምነን እንድንቀበል እንዲሁም አመለካከታችንን እንድናስተካክል ያነሳሳናል። ሁለተኛ፣ ፍትሕ የጎደለው ነገር በሚፈጸምብን ወይም በምንመለከትበት ጊዜ ትሑት መሆናችን፣ ይሖዋ ነገሮችን ለማስተካከል እርምጃ እስኪወስድ በትዕግሥት እንድንጠብቅና ታዛዥ እንድንሆን ይረዳናል። ጠቢቡ ሰለሞን “እውነተኛውን አምላክ የሚፈሩ ሰዎች አምላክን በመፍራታቸው የኋላ ኋላ መልካም [ይሆንላቸዋል]” ሲል ጽፏል፤ አክሎም ‘ክፉ ሰው ግን የኋላ ኋላ መልካም አይሆንለትም፤ የሕይወት ዘመኑንም ማራዘም አይችልም’ ብሏል። (መክ. 8:12, 13) በእርግጥም ትሑት ከሆንን ራሳችንንም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሁሉ እንጠቅማለን።—1 ጴጥሮስ 5:5ን አንብብ።
በጉባኤ ውስጥ የታየ ግብዝነት
12. ቀጥሎ የምንመረምረው የትኛውን ዘገባ ነው? ለምንስ?
12 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሶርያዋ አንጾኪያ የነበሩ ክርስቲያኖች፣ ምን ያህል ትሑትና ይቅር ባይ እንደሆኑ የሚፈትን ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። እስቲ እነዚህ ክርስቲያኖች የገጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት፤ ይህም ስለ ይቅር ባይነት ያለንን አመለካከት ለመመርመር ብሎም ይቅር ባይነት ይሖዋ ስለ ፍትሕ ካለው አመለካከት ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ለመገንዘብ ይረዳናል።
13, 14. ሐዋርያው ጴጥሮስ ምን ዓይነት መብቶች አግኝቷል? ድፍረት ያሳየውስ እንዴት ነው?
13 ሐዋርያው ጴጥሮስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ሽማግሌ ነበር። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የነበረ ሲሆን የተለያዩ ከባድ ኃላፊነቶችም ተሰጥተውታል። (ማቴ. 16:19) ለምሳሌ ያህል፣ በ36 ዓ.ም. ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ ምሥራቹን የመስበክ መብት አግኝቷል። ቆርኔሌዎስ ከአሕዛብ ወገን የሆነ ያልተገረዘ ሰው ከመሆኑ አንጻር በዚህ ወቅት የተከናወነው ነገር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። በቆርኔሌዎስና በቤተሰቡ ላይ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ ጴጥሮስ “እንደ እኛው መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን እነዚህን ሰዎች በውኃ እንዳይጠመቁ ሊከለክላቸው የሚችል አለ?” ብሎ ነበር።—ሥራ 10:47
14 በ49 ዓ.ም. ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የነበሩ ሽማግሌዎች፣ ግርዘት ወደ ክርስትና ከተለወጡ አሕዛብ የሚጠበቅ ብቃት ስለመሆኑ ለመወያየት ተሰብስበው ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ጴጥሮስ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ ያልተገረዙ አሕዛብም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንደተቀበሉ በዚያ የነበሩትን ወንድሞች በማስታወስ በድፍረት ተናግሯል። ጴጥሮስ በዚያ ወቅት የተመለከተውን ነገር መናገሩ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ረድቶታል። (ሥራ 15:6-11, 13, 14, 28, 29) አይሁዳውያኑም ሆኑ ከአሕዛብ ወገን የመጡ ክርስቲያኖች፣ ጴጥሮስ ማስረጃዎቹን ያለምንም ፍርሃት በማቅረቡ ተደስተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። እነዚያ ክርስቲያኖች እንዲህ ባለው ታማኝና የጎለመሰ ወንድም ላይ እምነት መጣል ከባድ እንደማይሆንባቸው ግልጽ ነው!—ዕብ. 13:7
15. ጴጥሮስ በሶርያዋ አንጾኪያ በነበረበት ወቅት ምን ስህተት ሠራ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
15 በ49 ዓ.ም. ከተካሄደው ስብሰባ ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስ ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ ሄደ። በዚያም ከአሕዛብ ከመጡት ወንድሞች ጋር በነፃነት ይቀራረብ ነበር። እነዚህ ወንድሞች ጴጥሮስ ካካበተው እውቀትና ተሞክሮ ጥቅም እንዳገኙ ግልጽ ነው። በመሆኑም ጴጥሮስ ከእነሱ ጋር መብላቱን በድንገት ሲያቆም ምን ያህል እንደተገረሙና እንዳዘኑ መገመት ይቻላል። አይሁዳውያን የሆኑ ሌሎች የጉባኤው አባላትም ሌላው ቀርቶ በርናባስ እንኳ የጴጥሮስን የተሳሳተ አካሄድ ተከተለ። ጎልማሳ ክርስቲያን የሆነው ጴጥሮስ፣ ጉባኤውን ሊከፋፍል የሚችል እንዲህ ያለ የተሳሳተ ውሳኔ ያደረገው ለምን ይሆን? በሌላ በኩል ደግሞ ይበልጥ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ሌላም ጥያቄ አለ፦ በአንድ ሽማግሌ ንግግር ወይም ድርጊት ተጎድተን ከሆነ ጴጥሮስ ከሠራው ስህተት ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
16. ጴጥሮስ ምን ዓይነት እርማት ተሰጥቶታል? የትኞቹ ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?
16 ገላትያ 2:11-14ን አንብብ። ጴጥሮስ የሰው ፍርሃት ወጥመድ ሆኖበት ነበር። (ምሳሌ 29:25) ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት በሚገባ ቢያውቅም በኢየሩሳሌም ባለው ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ የተገረዙ አይሁዳውያን ምን ይሉኛል የሚል ፍርሃት አደረበት። በ49 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም በተደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ በአንጾኪያ ጴጥሮስን በግልጽ የተቃወመው ሲሆን ግብዝነቱንም አጋልጧል። (ሥራ 15:12፤ ገላ. 2:13) ታዲያ ጴጥሮስ የሠራው ስህተት በቀጥታ የሚነካቸው ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን የፍትሕ መጓደል ሲመለከቱ ምን ተሰማቸው? በዚህ ተሰናክለው ይሆን? ጴጥሮስስ በሠራው ስህተት የተነሳ፣ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸውን መብቶቹን ያጣ ይሆን?
ይቅር ባይ ሁን
17. የይሖዋ ይቅር ባይነት ጴጥሮስን የጠቀመው እንዴት ነው?
17 ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ የሰጠውን እርማት በትሕትና እንደተቀበለ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ጴጥሮስ መብቶቹን እንዳጣ የሚገልጽ ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑ ሁለት ደብዳቤዎችን በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ጴጥሮስ በሁለተኛው ደብዳቤው ላይ ጳውሎስን “የተወደደው ወንድማችን” ብሎ መጥራቱ ትኩረት የሚስብ ነው። (2 ጴጥ. 3:15) ጴጥሮስ የሠራው ስህተት ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን የጉባኤውን አባላት አሳዝኖ ሊሆን ቢችልም የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ በእሱ መጠቀሙን ቀጥሎ ነበር። (ኤፌ. 1:22) በመሆኑም የጉባኤው አባላት ይቅር ባይ በመሆን ኢየሱስንና አባቱን መምሰል የሚችሉበት አጋጣሚ ነበራቸው። ፍጽምና የጎደለው ሰው በሠራው ስህተት ምክንያት፣ ከጉባኤው አባላት መካከል የተሰናከለ እንደማይኖር ተስፋ እናደርጋለን።
18. ከፍትሕ ጋር በተያያዘ የይሖዋን አመለካከት ማንጸባረቅ የሚያስፈልገን በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው?
18 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዘመናችን ባለው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ፍጹም የሆነ የጉባኤ ሽማግሌ የለም፤ ምክንያቱም “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን።” (ያዕ. 3:2 ግርጌ) ማናችንም ይህን ሐቅ መቀበል አይከብደንም፤ ይሁን እንጂ አንድ ወንድም የፈጸመው ስህተት በግለሰብ ደረጃ የሚነካን ሲሆን ሁኔታው ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ ስለ ፍትሕ ያለውን አመለካከት እናንጸባርቃለን? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሽማግሌ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እንደሚያዳላ የሚጠቁም ሐሳብ ቢሰነዝር ምን ይሰማሃል? አሊያም ደግሞ አንድ ሽማግሌ አንተን የሚጎዳ ወይም የሚያሳዝን ነገር ሳያስበው ቢናገር በዚህ ትደናቀፋለህ? ይህ ወንድም ከዚህ በኋላ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቁ እንዳልሆነ ቸኩለህ ከመደምደም ይልቅ የጉባኤው ራስ የሆነውን ኢየሱስን በትዕግሥት ትጠባበቃለህ? ይህ ሽማግሌ በሠራው ስህተት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ለረጅም ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ለማስታወስ ትሞክራለህ? አንተን የበደለህ ወንድም በሽምግልና ማገልገሉን ቢቀጥል እንዲያውም ተጨማሪ መብቶች ቢያገኝ አብረኸው ትደሰታለህ? ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆንህ ከፍትሕ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳለህ ያሳያል።—ማቴዎስ 6:14, 15ን አንብብ።
19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
19 ፍትሕን የሚወዱ ሰዎች፣ ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ክፉ ሥርዓት በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሱትን ኢፍትሐዊ ድርጊት ሁሉ ይሖዋ የሚያስወግድበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። (ኢሳ. 65:17) እስከዚያው ድረስ ግን ሁላችንም፣ የማናውቀው ነገር ሊኖር እንደሚችል በትሕትና አምነን በመቀበል እንዲሁም የበደሉንን በነፃ ይቅር በማለት ከፍትሕ ጋር በተያያዘ የይሖዋን አመለካከት ለማንጸባረቅ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።