የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w17 ግንቦት ገጽ 31-32
  • “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ልባችን በቅንዓትና በፍቅር ተሞልቶ ነበር”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ልባችን በቅንዓትና በፍቅር ተሞልቶ ነበር”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
w17 ግንቦት ገጽ 31-32
በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ በሕዝብ የተሞላው አዳራሽ

ከታሪክ ማኅደራችን

“ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ልባችን በቅንዓትና በፍቅር ተሞልቶ ነበር”

መስከረም 1922 ዓርብ ጠዋት 8,000 የሚሆኑ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበዋል፤ አየሩ መሞቅ ጀምሮ ነበር። የስብሰባው ሊቀ መንበር፣ በዚህ ወሳኝ ፕሮግራም ላይ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ማንኛውም ሰው ከፈለገ አዳራሹን ለቅቆ መውጣት እንደሚችል ሆኖም ተመልሶ መግባት እንደማይፈቀድለት ማስታወቂያ ተናገረ።

ስብሰባው የተጀመረው “በውዳሴ ፕሮግራም” ሲሆን የተወሰኑ መዝሙሮች ከተዘመሩ በኋላ ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ወደ አትራኖሱ ተጠጋ። አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ከሙቀቱ የተነሳ ወዲያ ወዲህ እያሉ ነው። ተናጋሪው፣ እነዚህ ተሰብሳቢዎች ቁጭ ብለው ፕሮግራሙን እንዲያዳምጡ ጠበቅ አድርጎ አሳሰበ። ንግግሩ እየቀረበ ሳለ፣ ከፍ ተደርጎ የተሰቀለውን የተጠቀለለ ጨርቅ ተሰብሳቢዎቹ አስተውለውት ይሆን?

የወንድም ራዘርፎርድ ንግግር “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” የሚል ርዕስ ነበረው። ወንድም ራዘርፎርድ በጥንት ጊዜ የነበሩ ነቢያት፣ ስለሚመጣው የአምላክ መንግሥት እንዴት በድፍረት እንደተናገሩ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ያብራራ ሲሆን ኃይለኛ የሆነው ድምፁ በአዳራሹ ውስጥ ያስገመግም ነበር። የንግግሩ መደምደሚያ ላይ ሲደርስ “የክብር ንጉሥ መግዛት እንደጀመረ ታምናላችሁ?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። ተሰብሳቢዎቹም በታላቅ ድምፅ “አዎ!” ብለው መለሱ።

ወንድም ራዘርፎርድም “እንግዲያው እናንት የልዑል አምላክ ልጆች ወደ መስኩ ተመልሳችሁ ሂዱ!” በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ። አክሎም እንዲህ አለ፦ “እነሆ ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው! እናንተ ደግሞ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።”

ይህን ሲናገር፣ ከፍ ተደርጎ የተሰቀለው የተጠቀለለ ጨርቅ ተተረተረ፤ “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ” የሚለው መልእክትም ለሁሉም ታየ።

ሬይ ቦፕ “ተሰብሳቢዎቹ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ተዋጡ” ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል። አና ጋርድነርም “ከጭብጨባው የተነሳ የቤቱ ምሰሶዎች ተነቃነቁ” ብላለች። ፍሬድ ትዋሮሽ ደግሞ “ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ ከተቀመጡበት በአንድ ላይ ተነሱ” በማለት ተናግሯል። ኢቫንጄሎስ ስኩፋስ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር “አንድ ታላቅ ኃይል ከወንበራችን አስፈንጥሮ ያስነሳን ያህል ነበር፤ ሁላችንም ብድግ ያልን ሲሆን ዓይኖቻችን በእንባ ተሞሉ” ብሏል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኙት መካከል ብዙዎች ከዚያ ቀደምም የመንግሥቱን ምሥራች በማዳረሱ ሥራ ይካፈሉ ነበር። ከስብሰባው በኋላ ግን ምሥራቹን ለመስበክ እንደ አዲስ ተነሳሱ። ኤተል ቤነኮፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ስለነበራቸው ስሜት ስትናገር “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ [ልባቸው] በቅንዓትና በፍቅር ተሞልቶ ነበር” ብላለች። በወቅቱ የ18 ዓመት ወጣት የነበረችው ኦዴሳ ታክ ከስብሰባው ስትመለስ፣ ‘ማን ይሄዳል?’ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቆርጣ ነበር። እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “የት፣ ምን ወይም እንዴት እንደምሰብክ አላውቅም ነበር። የማውቀው ነገር ቢኖር ልክ እንደ ኢሳይያስ ‘እነሆኝ! እኔን ላከኝ’ ማለት እንደምፈልግ ነበር።” (ኢሳ. 6:8) ራልፍ ሌፍለር ደግሞ “በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ተስፋፍቶ ያለው የአምላክን መንግሥት የማስታወቅ ዘመቻ በደንብ የጀመረው በዚያ አስደሳች ቀን ነው” ሲል ተናግሯል።

በእርግጥም በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ የተደረገው ስብሰባ በታሪክ ውስጥ ወሳኝ ቲኦክራሲያዊ ክንውን እንደተፈጸመበት ተደርጎ የሚታይ መሆኑ አያስገርምም! ወንድም ጆርጅ ጋንጋስ “ያ ስብሰባ፣ ከዚያ በኋላ አንድም ስብሰባ እንዳያመልጠኝ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደርግ አነሳስቶኛል” ሲል ተናግሯል። ደግሞም ወንድም ጋንጋስ፣ ከዚያ በኋላ አንድም ስብሰባ አላመለጠውም። ጁልያ ዊልኮክስ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “በጽሑፎቻችን ላይ በ1922 በሴዳር ፖይንት ስለተደረገው ስብሰባ የሚጠቅስ ሐሳብ ባነበብኩ ቁጥር በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ደስታ ይሰማኛል። ምንጊዜም ቢሆን ‘ይሖዋ፣ በዚያ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ስለፈቀድክልኝ አመሰግናለሁ’ ለማለት ያነሳሳኛል።”

ብዙዎቻችን ለታላቁ አምላካችንና እሱ ለሾመው ንጉሥ ያለን ፍቅርና ቅንዓት እንዲቀጣጠል ብሎም ልባችን በደስታ እንዲሞላ የሚያደርግ ልዩ ትዝታ የፈጠረብን ትልቅ ስብሰባ ወደ አእምሯችን ይመጣ ይሆናል። እኛም በእነዚህ ትዝታዎች ላይ ስናሰላስል “ይሖዋ፣ በዚያ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ስለፈቀድክልኝ አመሰግናለሁ” ለማለት እንገፋፋለን።

እንቆቅልሽ የሆኑት ምልክቶች

“ADV” የሚሉት ፊደላት በስብሰባው አዳራሽ አካባቢ በብዙ ቦታዎች ይኸውም በዛፎቹ፣ በሕንፃዎቹ አልፎ ተርፎም በስብሰባው ፕሮግራም ላይ ይገኙ ነበር! ተሰብሳቢዎቹ የእነዚህን ፊደላት ትርጉም ለማወቅ በጣም ጓጉተው ነበር።a

“በእያንዳንዱ ምሰሶና በር ላይ ‘ADV’ የሚሉት ፊደላት በጥቁር ቀለም በትላልቁ የተጻፉባቸው ነጭ ካርዶች ተለጥፈው ነበር። ፊደላቱ ምን ትርጉም እንዳላቸው ብንጠይቅም ማንም ሰው የሚያውቅ አይመስልም ነበር፤ ካወቁም ደግሞ አልነገሩንም።”—ኢደት ብሬነሰን

a በማኅደራችን ውስጥ እነዚህን ምልክቶች የሚያሳይ ፎቶግራፍ እስከ ዛሬ ድረስ አልተገኘም። በመሆኑም ምልክቶቹ አሁንም እንቆቅልሽ ናቸው ማለት ይቻላል። “ADV” የሚሉት ፊደላት “advertise” (“አስታውቁ”) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የመጀመሪያ ሆህያት ናቸው።

ከመድረክ በስተጀርባ —ጸሎታቸው ምላሽ አገኘ

አርተርና ኔሊ ክላውስ፣ ጥሩ መቀመጫዎች ለማግኘት ሲሉ ወደ ስብሰባው ቦታ በጊዜ ደርሰዋል። አርተር “እያንዳንዱን ቃል በትኩረት እየተከታተልኩ ነበር” ሲል ተናግሯል። ሆኖም በድንገት የሆድ ቁርጠት ጀመረው። ወደ አዳራሹ ተመልሶ መግባት እንደማይችል ስላወቀ እያመነታ ከአዳራሹ ወጣ። ከአስተናጋጆቹ አንዱ “እንዴት በዚህ ሰዓት ትወጣለህ?” ሲል ጠየቀው። አርተር ግን የግድ መውጣት ነበረበት።

አርተር ሲመለስ ከመሰብሰቢያ አዳራሹ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ሰማ። በአዳራሹ ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ነገር ለመስማት የሚያስችለው ቦታ ከውጭ ሆኖ እየፈለገ ሳለ 4.8 ሜትር የሚሆን ከፍታ ወዳለው ጣሪያ መውጣት የሚችልበት መንገድ አገኘ። ከዚያም በጣሪያው ላይ ወደሚገኝ ብርሃን ለማስገባት የተዘጋጀ ትልቅ መስኮት አቀና።

አርተር፣ ክፍት በሆነው በዚህ መስኮት በኩል ቁልቁል ወደተናጋሪው የሚመለከቱ ግራ የተጋቡ የተወሰኑ ወንድሞች አገኘ። እነዚህ ወንድሞች አንድ ማስታወቂያ የታሰረባቸውን የተለያዩ ገመዶች እኩል እንዲበጥሱ መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። ሁሉንም ገመዶች እኩል ለመበጠስ ግን አንድ ተጨማሪ መቁረጫ ያስፈልጋቸው ነበር። ታዲያ አርተር በኪስ የሚያዝ ሰንጢ ይኖረው ይሆን? አርተር ሰንጢ እንዳለው ሲያውቁ ወንድሞች እፎይ አሉ። ከዚያ በኋላ አርተርና ሌሎቹ ወንድሞች በየቦታቸው ላይ ሆነው የሚሰጣቸውን ምልክት መጠባበቅ ጀመሩ። ወንድም ራዘርፎርድ “አስታውቁ!” የሚለውን ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ሲናገር ገመዶቹን መቁረጥ ነበረባቸው።

የዓይን ምሥክሮች፣ ባለ ሦስት ቀለሙ ትልቅ ማስታወቂያ በአንድ ጊዜ እንደተዘረጋ ገልጸዋል። ማስታወቂያው መሃል ላይ ደግሞ የኢየሱስ ሥዕል ነበር።

ወንድሞች ወደ ጣሪያው ለመውጣት መሰላል ተጠቅመው እንደነበረና ከዚያ በኋላ ግን መሰላሉ እንደተወሰደ በኋላ ላይ ለአርተር ነገሩት። ተጨማሪ መቁረጫ ለማግኘት መውረድ የሚችሉበት መንገድ አልነበረም፤ በመሆኑም መቁረጫ የያዘ አንድ ወንድም እንዲልክላቸው ወደ ይሖዋ ጸልየው ነበር። እነዚያ ወንድሞች ይሖዋ በጣም አስገራሚ በሆነ መንገድ ለጸሎታቸው ምላሽ እንደሰጣቸው ተሰምቷቸዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ