-
2 ነገሥት 22:14-20አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
14 በመሆኑም ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ አክቦር፣ ሳፋንና አሳያህ ወደ ነቢዪቱ ሕልዳና+ ሄዱ። ሕልዳና የሃርሐስ ልጅ፣ የቲቅዋ ልጅ፣ የአልባሳት ጠባቂው የሻሉም ሚስት ስትሆን ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍል ትኖር ነበር፤ እነሱም በዚያ አነጋገሯት።+ 15 እሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ የላካችሁን ሰው እንዲህ በሉት፦ 16 “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ መከራ አመጣለሁ፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ+ ላይ የሰፈረውን ቃል ሁሉ እፈጽማለሁ። 17 እኔን በመተው በእጆቻቸው ሥራ+ ሁሉ ያስቆጡኝ ዘንድ ለሌሎች አማልክት የሚጨስ መሥዋዕት ስለሚያቀርቡ+ ቁጣዬ በዚህ ቦታ ላይ ይነዳል፤ ደግሞም አይጠፋም።’”+ 18 ይሖዋን እንድትጠይቁ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማኸውን ቃል በተመለከተ፣ 19 ይህን ቦታም ሆነ ነዋሪዎቹን መቀጣጫ እንደማደርግና እንደምረግም የተናገርኩትን ነገር ስትሰማ ልብህ ስለተነካ፣* በይሖዋም ፊት ራስህን ስላዋረድክ+ እንዲሁም ልብስህን ስለቀደድክና+ በፊቴ ስላለቀስክ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል ይሖዋ። 20 ወደ አባቶችህ የምሰበስብህ* በዚህ የተነሳ ነው፤ አንተም በሰላም በመቃብርህ ታርፋለህ፤ በዚህ ቦታ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም።’”’” ከዚያም ሰዎቹ መልሱን ለንጉሡ አመጡለት።
-