-
ሉቃስ 7:1-9አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
7 ኢየሱስ ለሕዝቡ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። 2 በዚያም አንድ የጦር መኮንን* ነበር፤ በጣም የሚወደው ባሪያውም በጠና ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር።+ 3 እሱም ስለ ኢየሱስ ሲሰማ መጥቶ ባሪያውን እንዲፈውስለት ይለምኑለት ዘንድ የተወሰኑ አይሁዳውያን ሽማግሌዎችን ላከ። 4 እነሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ በማለት ተማጸኑት፦ “ይህን ሰው ልትረዳው ይገባል፤ 5 ምክንያቱም ሕዝባችንን ይወዳል፤ ምኩራባችንንም ያሠራልን እሱ ነው።” 6 ስለዚህ ኢየሱስ አብሯቸው ሄደ። ሆኖም ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ መኮንኑ ወዳጆቹን እንዲህ ሲል ወደ ኢየሱስ ላከ፦ “ጌታዬ፣ በቤቴ ጣሪያ ሥር ልትገባ የሚገባኝ ሰው ስላልሆንኩ አትድከም።+ 7 ከዚህም የተነሳ አንተ ፊት መቅረብ የሚገባኝ ሰው እንደሆንኩ አልተሰማኝም። ስለዚህ አንተ አንድ ቃል ተናገርና አገልጋዬ ይፈወስ። 8 እኔ ራሴ የምታዘዛቸው የበላይ አዛዦች አሉ፤ ለእኔም የሚታዘዙ የበታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” 9 ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ በሰውየው በጣም ተደንቆ ይከተለው ወደነበረው ሕዝብ ዞር በማለት “እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ውስጥ እንኳ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት አላገኘሁም” አለ።+
-