-
ማቴዎስ 6:25-30አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
25 “ስለዚህ እላችኋለሁ፦ ስለ ሕይወታችሁ* ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ+ አትጨነቁ።*+ ሕይወት* ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥም?+ 26 የሰማይ ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤+ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም? 27 ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ* መጨመር የሚችል ይኖራል?+ 28 ስለ ልብስስ ቢሆን ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤ 29 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን+ እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም። 30 አምላክ ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን የሜዳ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?
-