የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt አብድዩ 1-21
  • አብድዩ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አብድዩ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አብድዩ

አብድዩ

1 የአብድዩ* ራእይ፦

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ስለ ኤዶም እንዲህ ይላል፦+

“ከይሖዋ የመጣ አንድ መልእክት ሰምተናል፤

በብሔራት መካከል አንድ መልእክተኛ ተልኳል፦

‘ተነሱ፤ እሷን ለመውጋት እንዘጋጅ።’”+

 2 “እነሆ፣ በብሔራት መካከል ከቁብ የማትቆጠር አድርጌሃለሁ፤

አንተ እጅግ ተንቀሃል።+

 3 አንተ በቋጥኝ መሸሸጊያ ውስጥ የምትኖር፣

መኖሪያህን በከፍታ ቦታ ላይ ያደረግክ፣

በልብህ ‘ማን ወደ ምድር ሊያወርደኝ ይችላል?’ የምትል፣

የልብህ እብሪት አታሎሃል።+

 4 መኖሪያህን እንደ ንስር ከፍ ብታደርግ*

ወይም ጎጆህን በከዋክብት መካከል ብትሠራ እንኳ

እኔ ከዚያ አወርድሃለሁ” ይላል ይሖዋ።

 5 “ሌቦች ወደ አንተ ቢመጡ፣ ዘራፊዎች በሌሊት ቢገቡ

(ታላቅ ጥፋት በደረሰብህ ነበር!)*

የሚሰርቁት የሚፈልጉትን ያህል ብቻ አይደለም?

ደግሞስ ወይን ለቃሚዎች ወደ አንተ ቢመጡ

ጥቂት ቃርሚያ አያስቀሩም?+

 6 ኤሳው ምንኛ ተበረበረ!

የተደበቀው ውድ ሀብቱ ምንኛ ተፈለገ!

 7 እስከ ድንበሩ ድረስ እንድትሄድ አስገደዱህ።

አጋሮችህ* ሁሉ አታለውሃል።

ከአንተ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች አይለውብሃል።

ከአንተ ጋር የሚበሉ ሰዎች ከሥርህ መረብ ይዘረጉብሃል፤

አንተ ግን አታስተውለውም።

 8 በዚያ ቀን” ይላል ይሖዋ፣

“ጥበበኞችን ከኤዶም አላጠፋም?+

ማስተዋልንስ ከኤሳው ተራራማ ምድር አላስወግድም?

 9 ቴማን+ ሆይ፣ ተዋጊዎችሽ ይሸበራሉ፤+

ምክንያቱም እያንዳንዳቸው ታርደው ከተራራማው የኤሳው ምድር ይወገዳሉ።+

10 በወንድምህ በያዕቆብ ላይ በተፈጸመው ግፍ የተነሳ+

ኀፍረት ትከናነባለህ፤+

ለዘላለምም ትጠፋለህ።+

11 ዳር ቆመህ ትመለከት በነበረበት ጊዜ፣

እንግዶች ሠራዊቱን ማርከው በወሰዱበትና+

የባዕድ አገር ሰዎች በበሩ ገብተው በኢየሩሳሌም ላይ ዕጣ በተጣጣሉበት ጊዜ፣+

አንተም ልክ እንደ እነሱ አደረግክ።

12 በወንድምህ ቀን ይኸውም ወንድምህ ክፉ ነገር በደረሰበት ቀን መፈንደቅ አይገባህም ነበር፤+

የይሁዳ ሕዝብ በጠፋበት ቀን ሐሴት ማድረግ አልነበረብህም፤+

ደግሞም በጭንቀታቸው ቀን በእብሪት መናገር አይገባህም ነበር።

13 በጥፋታቸው ቀን ወደ ሕዝቤ በር መምጣት አልነበረብህም፤+

በጥፋቱ ቀን በደረሰበት መከራ መፈንደቅ አይገባህም ነበር፤

ደግሞም ጥፋት በደረሰበት ቀን ሀብቱን መውሰድ አልነበረብህም።+

14 የሚሸሹትን የይሁዳ ሰዎች ለመግደል መንታ መንገድ ላይ መቆም አይገባህም ነበር፤+

በጭንቀቱም ቀን በሕይወት የተረፉትን አሳልፈህ መስጠት አልነበረብህም።+

15 ይሖዋ በብሔራት ሁሉ ላይ የሚነሳበት ቀን ቀርቧልና።+

አንተ በእሱ ላይ እንዳደረግከው በአንተም ላይ ይደረጋል።+

በሌሎች ላይ ያደረግከው ነገር በገዛ ራስህ ላይ ይመለሳል።

16 እናንተ በቅዱሱ ተራራዬ ላይ እንደጠጣችሁ፣

ልክ እንደዚሁ ብሔራት በሙሉ ዘወትር ይጠጣሉ።+

ይጠጣሉ፤ ደግሞም ይጨልጡታል፤

ፈጽሞ እንዳልነበሩም ይሆናሉ።

17 ያመለጡት ግን በጽዮን ተራራ ላይ ይሆናሉ፤+

እሱም የተቀደሰ ይሆናል፤+

የያዕቆብ ቤት ሰዎችም የራሳቸው የሆኑትን ነገሮች ይወርሳሉ።+

18 የያዕቆብ ቤት እሳት፣

የዮሴፍም ቤት ነበልባል ይሆናል፤

የኤሳው ቤት ደግሞ እንደ ገለባ ይሆናል፤

እነሱም ያቃጥሏቸዋል፤ ይበሏቸዋልም፤

ከኤሳውም ቤት የሚተርፍ አይኖርም፤+

ይሖዋ ራሱ ተናግሯልና።

19 እነሱ ኔጌብንና የኤሳውን ተራራማ ምድር፣+

ሸፌላንና የፍልስጤምን ምድር ይወርሳሉ።+

የኤፍሬምን መሬትና የሰማርያን መሬት ይወርሳሉ፤+

ቢንያምም ጊልያድን ይወርሳል።

20 እስከ ሰራፕታ+ ድረስ ያለው የከነአናውያን ምድር፣

ከዚህ የመከላከያ ግንብ* በግዞት የተወሰዱት ሰዎች+ ይኸውም የእስራኤል ሕዝብ ይዞታ ይሆናል።

በሰፋራድ የነበሩት ከኢየሩሳሌም በግዞት የተወሰዱ ሰዎችም የኔጌብን ከተሞች ይወርሳሉ።+

21 ሕዝቡን የሚታደጉ ሰዎችም በኤሳው ተራራማ ምድር ላይ ለመፍረድ+

ወደ ጽዮን ተራራ ይወጣሉ፤

ንግሥናውም የይሖዋ ይሆናል።”+

“የይሖዋ አገልጋይ” የሚል ትርጉም አለው።

“እንደ ንስር መጥቀህ ብትበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ምን ያህል ጥፋት ያደርሱ ነበር?” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን የገቡ።”

ወይም “ምሽግ።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ