ዮናስ
1 የይሖዋ ቃል ወደ አሚታይ ልጅ ወደ ዮናስ*+ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “ተነስተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ+ ሂድና በእሷ ላይ የፍርድ መልእክት አውጅ፤ ክፋታቸውን አስተውያለሁና።”
3 ዮናስ ግን ከይሖዋ ፊት ኮብልሎ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ተነሳ፤ ወደ ኢዮጴም ወረደ፤ ከዚያም ወደ ተርሴስ የምትሄድ መርከብ አገኘ። ከይሖዋም ፊት ሸሽቶ፣ በመርከቡ ውስጥ ከነበሩት ጋር ወደ ተርሴስ ለመሄድ የጉዞውን ዋጋ ከፍሎ ተሳፈረ።
4 ከዚያም ይሖዋ በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ነፋስ አመጣ፤ ከባድ ማዕበል ስለተነሳ መርከቧ ልትሰበር ተቃረበች። 5 መርከበኞቹ እጅግ ከመፍራታቸው የተነሳ እርዳታ ለማግኘት እያንዳንዳቸው ወደየአምላካቸው ይጮኹ ጀመር። የመርከቧንም ክብደት ለመቀነስ በውስጧ የነበሩትን ዕቃዎች ወደ ባሕሩ መጣል ጀመሩ።+ ዮናስ ግን ወደ መርከቧ* ውስጠኛ ክፍል ወርዶ ተኝቶ ነበር፤ ጭልጥ ያለ እንቅልፍም ወስዶት ነበር። 6 የመርከቧ አዛዥ ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ “እንዴት ትተኛለህ? ተነስተህ ወደ አምላክህ ጩኽ! ምናልባት እውነተኛው አምላክ ለእኛ አስቦ ከጥፋት ያድነን ይሆናል።”+
7 ከዚያም እርስ በርሳቸው “ይህ መከራ የደረሰብን በማን ምክንያት እንደሆነ ማወቅ እንድንችል፣ ኑ ዕጣ እንጣጣል”+ ተባባሉ። በመሆኑም ዕጣ ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ።+ 8 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ይህ መከራ የደረሰብን በማን ምክንያት እንደሆነ እባክህ ንገረን። ሥራህ ምንድን ነው? የመጣኸው ከየት ነው? አገርህስ የት ነው? ከየትኛውስ ሕዝብ ነህ?”
9 እሱም መልሶ “እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማያትን አምላክ ይሖዋን የምፈራ* ሰው ነኝ” አላቸው።
10 በዚህ ጊዜ ሰዎቹ የባሰ ፈሩ፤ “ያደረግከው ነገር ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። (ሰዎቹ ዮናስ ነግሯቸው ስለነበር ከይሖዋ ፊት እየሸሸ እንዳለ አወቁ።) 11 የባሕሩ ማዕበል እያየለ በመሄዱ “ባሕሩ ጸጥ እንዲልልን በአንተ ላይ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉት። 12 እሱም “አንስታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል፤ ይህ ከባድ ማዕበል የመጣባችሁ በእኔ የተነሳ መሆኑን አውቃለሁና” በማለት መለሰላቸው። 13 ሰዎቹ ግን መርከቧን ወደ የብስ ለመመለስ በኃይል ቀዘፉ፤* ይሁንና ማዕበሉ ይበልጥ እያየለባቸው ስለሄደ ሊሳካላቸው አልቻለም።
14 ከዚያም ወደ ይሖዋ በመጮኽ እንዲህ አሉ፦ “እንግዲህ ይሖዋ ሆይ፣ በዚህ ሰው ምክንያት* እንዳንጠፋ እንለምንሃለን! ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ደስ እንዳሰኘህ ስላደረግክ ለንጹሕ ሰው ደም ተጠያቂ አታድርገን!” 15 ከዚያም ዮናስን አንስተው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም መናወጡን አቆመ። 16 በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ይሖዋን እጅግ ፈሩ፤+ ለይሖዋም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ስእለትም ተሳሉ።
17 ይሖዋም ዮናስን እንዲውጠው አንድ ትልቅ ዓሣ ላከ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ቆየ።+
2 ከዚያም ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ ይሖዋ ጸለየ፤+ 2 እንዲህም አለ፦
“ተጨንቄ ሳለሁ ወደ ይሖዋ ተጣራሁ፤ እሱም መለሰልኝ።+
በመቃብር* ጥልቅ* ውስጥ ሆኜ እርዳታ ለማግኘት ጮኽኩ።+
አንተም ድምፄን ሰማህ።
3 ወደ ጥልቁ፣ ወደ ታችኛው የባሕሩ ወለል በጣልከኝ ጊዜ
ፈሳሹ ውኃ ዋጠኝ።+
ማዕበሎችህና ሞገዶችህ ሁሉ በላዬ አለፉ።+
4 እኔም ‘ከፊትህ አባረርከኝ!
ቅዱስ የሆነውን ቤተ መቅደስህን ዳግመኛ እንዴት መመልከት እችላለሁ?’ አልኩ።
የባሕር አረም ራሴ ላይ ተጠመጠመ።
6 ወደ ተራሮች መሠረት ሰመጥኩ።
የምድር መቀርቀሪያዎች ለዘላለም ተዘጉብኝ።
ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ አንተ ግን ሕይወቴን ከጉድጓዱ ውስጥ አወጣህ።+
7 ሕይወቴ* እየተዳከመች ስትሄድ ይሖዋን አስታወስኩ።+
ጸሎቴም ወደ አንተ፣ ቅዱስ ወደሆነው ቤተ መቅደስህ ገባ።+
8 ለማይረቡ ጣዖቶች ያደሩ ሰዎች ታማኝ ፍቅር የሚያሳያቸውን ይተዋሉ።*
9 እኔ ግን በምስጋና ድምፅ መሥዋዕት አቀርብልሃለሁ።
የተሳልኩትን እከፍላለሁ።+
መዳን ከይሖዋ ነው።”+
10 በኋላም ይሖዋ ዓሣውን አዘዘው፤ ዓሣውም ዮናስን በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።
3 ከዚያም የይሖዋ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፦+ 2 “ተነስተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ+ ሂድ፤ የምነግርህንም መልእክት በመካከሏ አውጅ።”
3 ዮናስም የይሖዋን ቃል በመታዘዝ ተነስቶ ወደ ነነዌ+ ሄደ።+ ነነዌ እጅግ ታላቅ ከተማ የነበረች ስትሆን* በእግር የሦስት ቀን ያህል መንገድ ታስኬድ ነበር። 4 ዮናስም ወደ ከተማዋ ገብቶ የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በ40 ቀን ውስጥ ትደመሰሳለች” ብሎ አወጀ።
5 የነነዌም ሰዎች በአምላክ አመኑ፤+ ከትልቁም አንስቶ እስከ ትንሹ ድረስ ጾም አወጁ፤ ማቅም ለበሱ። 6 የነነዌ ንጉሥ መልእክቱን በሰማ ጊዜ ከዙፋኑ ተነስቶ ልብሰ መንግሥቱን አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ አመድ ላይ ተቀመጠ። 7 በተጨማሪም በመላው ነነዌ አዋጅ አስነገረ፤
“ንጉሡና መኳንንቱ ያወጡት ድንጋጌ፦ ሰውም ሆነ እንስሳ፣ ከብትም ሆነ መንጋ ምንም ነገር አይቅመስ። ምግብ አይብሉ፤ ውኃም አይጠጡ። 8 ሰውም ሆነ እንስሳ ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ አምላክ ይጩኽ፤ ክፉ መንገዳቸውንና የሚፈጽሙትን ግፍ ይተዉ። 9 እኛ እንዳንጠፋ፣ እውነተኛው አምላክ ሊያመጣው ያሰበውን ነገር እንደገና በማጤን* ከሚነደው ቁጣው ይመለስ እንደሆነ ማን ያውቃል?”
10 እውነተኛው አምላክ ያደረጉትን ነገር ይኸውም ከክፉ መንገዳቸው እንዴት እንደተመለሱ አየ፤+ በእነሱም ላይ አመጣዋለሁ ያለውን ነገር መልሶ በማጤን* ጥፋቱን ከማምጣት ተቆጠበ።+
4 ሆኖም ይህ ጉዳይ ዮናስን ፈጽሞ አላስደሰተውም፤ በመሆኑም እጅግ ተቆጣ። 2 ወደ ይሖዋም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በገዛ አገሬ ሳለሁ ያሳሰበኝ ጉዳይ ይህ አልነበረም? መጀመሪያውኑም ወደ ተርሴስ ለመሸሽ የሞከርኩት ለዚህ ነበር፤+ አንተ ሩኅሩኅና* መሐሪ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየህና ታማኝ ፍቅርህ የበዛ፣+ አዝነህም ጥፋት ከማምጣት የምትቆጠብ እንደሆንክ አውቃለሁና። 3 አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ በሕይወት ከመኖር ይልቅ መሞት ስለሚሻለኝ እባክህ ግደለኝ።”*+
4 ይሖዋም “እንዲህ መቆጣትህ ተገቢ ነው?” ብሎ ጠየቀው።
5 ከዚያም ዮናስ ከከተማዋ ወጥቶ በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ። በዚያም ለራሱ መጠለያ ሠርቶ በከተማዋ ላይ የሚደርሰውን ነገር ለማየት በጥላው ሥር ተቀመጠ።+ 6 በዚህ ጊዜ ይሖዋ አምላክ፣ ዮናስ ራሱን እንዲያስጠልልባትና ከሥቃዩ እንዲያርፍ ሲል አንዲት የቅል ተክል* ከበላዩ እንድታድግ አደረገ። ዮናስም በቅል ተክሏ እጅግ ተደሰተ።
7 ይሁን እንጂ እውነተኛው አምላክ በሚቀጥለው ቀን፣ ማለዳ ላይ አንድ ትል ላከ፤ ትሉም የቅል ተክሏን በላት፤ ተክሏም ደረቀች። 8 ፀሐይ መውጣት ስትጀምር አምላክ የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አመጣ፤ ፀሐይዋም የዮናስን አናት አቃጠለችው፤ እሱም ተዝለፈለፈ። እንዲሞትም* ለመነ፤ ደግሞ ደጋግሞም “በሕይወት ከምኖር ብሞት ይሻለኛል” አለ።+
9 አምላክም ዮናስን “ስለ ቅል ተክሏ እንዲህ መቆጣትህ ተገቢ ነው?” ሲል ጠየቀው።+
እሱም “መቆጣት ሲያንሰኝ ነው፤ እንዲያውም ብሞት ይሻለኛል” አለ። 10 ይሖዋ ግን እንዲህ አለው፦ “አንተ በአንድ ሌሊት አድጋ በአንድ ሌሊት ለጠፋችው፣ ላልደከምክባት ወይም ላላሳደግካት የቅል ተክል አዝነሃል። 11 ታዲያ እኔ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር* ለይተው የማያውቁ ከ120,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎችና በርካታ እንስሶቻቸው ለሚኖሩባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ+ ላዝን አይገባም?”+
ስሙ “ርግብ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ከመርከቧ ወለል በታች ወደሚገኘው።”
ወይም “የማመልክ።”
ወይም “ማዕበሉን ሰንጥቀው ወደ የብስ ለመመለስ ጥረት አደረጉ።”
ወይም “በዚህ ሰው ነፍስ ምክንያት።”
ወይም “በሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሆድ።”
ወይም “ውኃው እስከ ነፍሴ ድረስ ሸፈነኝ።”
ወይም “ነፍሴ።”
“ታማኝነታቸውን ይተዋሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ለአምላክ ታላቅ ከተማ ነበረች።”
ወይም “ሊያመጣ ባሰበው ነገር ተጸጽቶ።”
ወይም “አመጣዋለሁ ባለው ነገር ተጸጽቶ።”
ወይም “ቸርና።”
ወይም “ነፍሴን ውሰድ።”
“የጉሎ ዛፍ” ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሱ እንድትሞትም።”
ወይም “ቀኝና ግራ እጃቸውን።”