ክፍል 3
በፊት በገነት ውስጥ ምን ዓይነት ኑሮ ነበር?
ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ብዙ ጥሩ ነገሮች ሰጥቷቸዋል። ዘፍጥረት 1:28
ይሖዋ የመጀመሪያዋን ሴት ማለትም ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ሚስት እንድትሆነው ለአዳም ሰጠው።—ዘፍጥረት 2:21, 22
ይሖዋ ምንም እንከን የሌለበት ፍጹም የሆነ አእምሮና አካል ሰጥቷቸው ነበር።
አዳምና ሔዋን ይኖሩ የነበረው ገነት በሆነው በኤደን የአትክልት ስፍራ ሲሆን ይህ ቦታ ወንዝ፣ የፍራፍሬ ዛፎችና እንስሳት ያሉበት እጅግ የተዋበ ስፍራ ነበር።
ይሖዋ ያነጋግራቸውና ያስተምራቸው ነበር። እሱን ቢሰሙት ኖሮ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር።
አምላክ ከዛፎቹ መካከል የአንደኛውን ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ አዟቸው ነበር። ዘፍጥረት 2:16, 17
ከመላእክት መካከል አንዱ በአምላክ ላይ ዓመፀ። ይህ ክፉ መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።
ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን በአትክልት ቦታው ካሉት ዛፎች መካከል አንዱን አሳይቶ ፍሬውን ቢበሉ እንደሚሞቱ ነገራቸው።
ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ይሖዋን እንዲታዘዙ አልፈለገም ነበር። ስለዚህ እባብን መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም የዛፉን ፍሬ ብትበላ እንደማትሞት ይልቁንም እንደ አምላክ እንደምትሆን ለሔዋን ነገራት። እርግጥ ይህ ውሸት ነበር።—ዘፍጥረት 3:1-5