በአሁኑ ጊዜ ያሉት ችግሮች ወደፊት ምን ይሆናሉ?
የዓለማችን ሁኔታ ምን የሚሆን ይመስልሃል?
ባለበት የሚቀጥል?
እየተባባሰ የሚሄድ?
ወይስ እየተሻሻለ የሚሄድ?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4 አዲስ ዓለም ትርጉም
ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ጥቅም አለው?
ትርጉም ያለውና አርኪ ሥራ ይኖርሃል።—ኢሳይያስ 65:21-23
ከሕመምና ከመከራ ነፃ የሆነ ሕይወት ይኖርሃል።—ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24
ከቤተሰብህና ከወዳጆችህ ጋር ለዘላለም በደስታ ትኖራለህ።—መዝሙር 37:11, 29
መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ እምነት መጣል እንችላለን?
አዎ፣ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦
አምላክ የገባውን ቃል የመፈጸም ችሎታ አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሁሉን ቻይ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም እሱ ገደብ የለሽ ኃይል አለው። (ራእይ 15:3) በመሆኑም ዓለማችንን እንደሚለውጥ የገባውን ቃል መፈጸም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል።”—ማቴዎስ 19:26
አምላክ የገባውን ቃል ለመፈጸም ፍላጎቱ አለው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት ‘ይናፍቃል።’—ኢዮብ 14:14, 15
በተጨማሪም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የታመሙትን እንደፈወሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት ስላለው ነው። (ማርቆስ 1:40, 41) ኢየሱስ ችግር ላይ የወደቁትን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ያለው መሆኑ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ እንዳንጸባረቀ ያሳያል።—ዮሐንስ 5:19
በመሆኑም ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ የወደፊቱ ጊዜ አስደሳች እንዲሆንልን የሚፈልጉ መሆናቸውን እርግጠኞች መሆን እንችላለን!—መዝሙር 72:12-14፤ 145:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:9
ምን ይመስልሃል?
አምላክ ዓለማችን የተሻለች እንድትሆን የሚያደርገው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ማቴዎስ 6:9, 10 እና ዳንኤል 2:44 ላይ ይገኛል።