ምዕራፍ 52
አለባበሳችንና ውጫዊ ገጽታችን ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?
ሁላችንም ከአለባበሳችንና ከውጫዊ ገጽታችን ጋር በተያያዘ የየራሳችን ምርጫ ይኖረናል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተላችን የራሳችንን ምርጫ መተው ሳያስፈልገን ይሖዋን ማስደሰት እንድንችል ይረዳናል። እስቲ ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
1. ከአለባበሳችንና ከውጫዊ ገጽታችን ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ በየትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንመራ ይገባል?
“በልከኝነትና በማስተዋል፣ ተገቢ [የሆነ] ልብስ” መልበስ ይኖርብናል፤ በተጨማሪም “ለአምላክ ያደርን ነን የሚሉ [ሰዎች] ሊያደርጉት እንደሚገባ” ምንጊዜም ንጽሕናችንን መጠበቅ አለብን። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) የሚከተሉትን አራት መሠረታዊ ሥርዓቶች ልብ በል፦ (1) አለባበሳችን “ተገቢ” ሊሆን ይገባል። በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ እንዳየኸው የይሖዋ ሕዝቦች በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ረገድ የየራሳቸው ምርጫ አላቸው፤ ሆኖም ምርጫቸው የሚያመልኩትን አምላክ እንደሚያከብሩ የሚያሳይ ነው። (2) “በልከኝነት” መልበስ ሲባል የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ወይም ወደ ራሳችን ከልክ ያለፈ ትኩረት የሚስብ ልብስ ከመልበስ መቆጠብ ማለት ነው። (3) በየጊዜው የሚመጣውን እያንዳንዱን ፋሽን ባለመከተል ‘አስተዋይ’ እንደሆንን እናሳያለን። (4) ውጫዊ ገጽታችን ‘ለአምላክ ያደርን እንደሆንን’ ማለትም እውነተኛውን አምላክ እንደምናመልክ የሚያሳይ ሊሆን ይገባል።—1 ቆሮንቶስ 10:31
2. አለባበሳችንን ስንመርጥ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ለምንድን ነው?
የምንለብሰውን ልብስ የመምረጥ ነፃነት ቢኖረንም የእኛ ምርጫ በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማሰብ አለብን። ማንንም ቅር ላለማሰኘት፣ ከዚህ ይልቅ ‘ባልንጀራችንን የሚጠቅመውንና የሚያንጸውን ነገር በማድረግ ለማስደሰት’ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን።—ሮም 15:1, 2ን አንብብ።
3. አለባበሳችን ሌሎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ ሊስብ የሚችለው እንዴት ነው?
ሁሌም ሥርዓታማ አለባበስ እንዲኖረን ጥረት ብናደርግም በተለይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝና በስብከቱ ሥራ ስንካፈል ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት እንሰጣለን። አለባበሳችን ሰዎች በያዝነው አስፈላጊ መልእክት ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ እንቅፋት እንዲሆንባቸው አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ‘የአዳኛችን ትምህርት ውበት እንዲጎናጸፍ’ በማድረግ ሰዎችን ወደ እውነት የሚስብ ሊሆን ይገባል።—ቲቶ 2:10
ጠለቅ ያለ ጥናት
ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ አለባበስና ውጫዊ ገጽታ እንዲኖረን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
አለባበሳችን ሥልጣን ላላቸው ሰዎች አክብሮት እንዳለን ወይም እንደሌለን ሊጠቁም ይችላል። ይሖዋ የልባችንን የሚያውቅ ቢሆንም ለእሱ አክብሮት እንዳለን በአለባበሳችንም ማሳየት አለብን
4. ጥሩ አለባበስ ለይሖዋ አክብሮት እንዳለን ያሳያል
ለአለባበሳችን ትኩረት የምንሰጥበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? ራእይ 4:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
አለባበሳችን ሰዎች ለይሖዋ ባላቸው አመለካከት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ማወቃችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?
በስብሰባዎች ላይ ስንገኝና በስብከቱ ሥራ ስንካፈል ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
5. ከአለባበስና ከውጫዊ ገጽታ ጋር በተያያዘ ጥሩ ምርጫ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ልብሶቻችን ውድ ሆኑም አልሆኑ ንጹሕና ለሁኔታው ተስማሚ መሆን አለባቸው። አንደኛ ቆሮንቶስ 10:24ን እና 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10ን አንብቡ። ከዚያም የሚከተሉትን ዓይነት ልብሶች መልበስ የሌለብን ለምን እንደሆነ ተወያዩ፦
የቆሸሸና የተዝረከረከ
የተጣበቀ፣ ሰውነትን የሚያሳይ ወይም የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ
እኛ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ሕጉ የይሖዋን አመለካከት ለማወቅ ይረዳናል። ዘዳግም 22:5ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ወንዶች ሴት የሚያስመስል፣ ሴቶች ደግሞ ወንድ የሚያስመስል ልብስ መልበስ የሌለባቸው ለምንድን ነው?
አንደኛ ቆሮንቶስ 10:32, 33ን እንዲሁም 1 ዮሐንስ 2:15, 16ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
አለባበሳችን በጉባኤያችን ወይም በአካባቢያችን ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ቅር የሚያሰኝ መሆን አለመሆኑን ማሰባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አንተ በምትኖርበት አካባቢ የተለመደው ምን ዓይነት አለባበስ ነው?
ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ለክርስቲያኖች ተገቢ ያልሆኑ ይመስሉሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያላቸው የተለያዩ አለባበሶች አሉ
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የፈለግኩትን ልብስ መልበስ መብቴ ነው።”
አንተ በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ማጠቃለያ
በአለባበስ ረገድ ጥሩ ምርጫ ማድረጋችን ለይሖዋም ሆነ ለሰዎች አክብሮት እንዳለን ያሳያል።
ክለሳ
ይሖዋ በአለባበስ ረገድ ጥሩ ምርጫ እንድናደርግ የሚፈልገው ለምንድን ነው?
ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ በየትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንመራ ይገባል?
አለባበሳችን ሌሎች ለእውነተኛው አምልኮ ባላቸው አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
ምርምር አድርግ
አለባበስህ ለሌሎች ምን መልእክት ያስተላልፋል?
ከመነቀስህ በፊት ቆም ብለህ ማሰብህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?