ዓርብ፣ ነሐሴ 8
አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው ይሖዋን ይፈራል።—ምሳሌ 14:2
በዛሬው ጊዜ ዓለም የሚከተለውን የሥነ ምግባር መሥፈርት ስናይ እንደ ጻድቁ ሎጥ ዓይነት ስሜት ይሰማናል። ሎጥ የሰማዩ አባታችን መጥፎ ምግባርን እንደሚጠላ ስለሚያውቅ “ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በማንአለብኝነት በሚፈጽሙት ድርጊት እጅግ እየተሳቀቀ” ይኖር ነበር። (2 ጴጥ. 2:7, 8) ሎጥ ለአምላክ ያለው ፍርሃትና ፍቅር በዙሪያው የሚኖሩት ሰዎች ከነበራቸው ያዘቀጠ ሥነ ምግባር እንዲርቅ ረድቶታል። እኛም ለይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አክብሮት በሌላቸው ሰዎች ተከበናል። ያም ቢሆን ለአምላክ ፍቅርና ጤናማ ፍርሃት ካዳበርን የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቅ እንችላለን። ይሖዋ በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ሲል በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ጠቃሚ ማበረታቻ አስፍሮልናል። ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ አረጋዊ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር መመርመራቸው ይጠቅማቸዋል። ይሖዋን የምንፈራው ከሆነ መጥፎ ምግባር ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ወዳጅነት አንመሠርትም። w23.06 20 አን. 1-2፤ 21 አን. 5
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 9
ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት በየዕለቱ ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።—ሉቃስ 9:23
ቤተሰቦችህ ይቃወሙህ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ስትል አንዳንድ ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት አድርገህ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 6:33) ከሆነ፣ ይሖዋ በታማኝነት ያከናወንከውን ሥራ እንደተመለከተ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ዕብ. 6:10) ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ በሕይወትህ ተመልክተህ ይሆናል፦ “ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።” (ማር. 10:29, 30) ያገኘሃቸው በረከቶች መሥዋዕት ካደረግካቸው ነገሮች በእጅጉ እንደሚበልጡ ምንም ጥያቄ የለውም።—መዝ. 37:4፤ w24.03 9 አን. 5
እሁድ፣ ነሐሴ 10
እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።—ምሳሌ 17:17
በይሁዳ ታላቅ ረሃብ ተከስቶ ክርስቲያኖች በተቸገሩበት ወቅት በአንጾኪያ ያሉ ክርስቲያኖች “እያንዳንዳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ወሰኑ።” (ሥራ 11:27-30) በረሃብ የተጎዱት ወንድሞቻቸው የሚኖሩት ርቀው ቢሆንም የአንጾኪያ ክርስቲያኖች እነሱን ለመርዳት ቆርጠው ነበር። (1 ዮሐ. 3:17, 18) እኛም የእምነት አጋሮቻችን በአደጋ እንደተጎዱ ስንሰማ ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን። ቶሎ ልንደርስላቸው እንፈልጋለን፤ ለምሳሌ በእርዳታ እንቅስቃሴው መካፈል እንችል እንደሆነ ሽማግሌዎችን መጠየቅ፣ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ ወይም በአደጋው ለተጎዱት መጸለይ እንችላለን። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ ለማግኘት እገዛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ ለፍርድ ሲመጣ ርኅራኄ ስናሳይ እንዲያገኘን እንፈልጋለን፤ ምኞታችን ‘መንግሥቱን እንዲወርሱ’ ከሚጋብዛቸው ሰዎች መካከል መሆን ነው።—ማቴ. 25:34-40፤ w23.07 4 አን. 9-10፤ 6 አን. 12