የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 10/8 ገጽ 28-29
  • ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በሰማይ የማይገኙ ሰዎች
  • ኢየሱስ መንገዱን ከፈተ
  • ሰማያዊ መንግሥት
  • የተመረጠ የገዢዎች አካል
  • ወደ ሰማይ እነማን ይሄዳሉ? ለምንስ?
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ታማኝ ክርስቲያኖች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1997
g97 10/8 ገጽ 28-29

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?

በአሸባሪዎች የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ አንድን በመብረር ላይ ያለ አውሮፕላን ብትንትኑን በማውጣት ተሳፋሪዎቹን በሙሉ ገደለ። የሟቾቹ ዘመዶችና ጓደኞች እነዚህ የሚወዷቸው ሰዎች ያለጊዜያቸው በአሠቃቂ ሁኔታ በመሞታቸው ይህን ለማካካስ ወደ ሰማይ እንደተወሰዱ ተደርጎ ተነግሯቸዋል።

አንድ ታዋቂ ሙዚቀኛ ከሞተ በኋላ ‘በሰማይ ከመላእክት ጋር መለከት እየነፋ’ ነው ተብሎ ተነግሮለታል።

ሕፃናት በበሽታ፣ በረሀብ ወይም በአደጋዎች ሲቀጠፉ ቀሳውስት እነዚህ ሕፃናት በአሁኑ ጊዜ ሰማያዊ ተድላና ደስታ አግኝተው፣ ምናልባትም መላእክት ሆነው በመኖር ላይ ናቸው ብለው ይናገራሉ!

አምላክ በልጆችና በአረጋውያን ላይ የሚፈጸመውን ግፍ የሚያካክሰው ራሱ ወደሚኖርበት ወደ ሰላማዊው ሰማይ በመውሰድ ነውን? ወደ ሰማይ መውሰድ አምላክ ከሰዎች መካከል ጥሩ የሆኑትን በሕይወት ጠብቆ ለማቆየት የሚጠቀምበት መንገድ ነውን? የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው?

በሰማይ የማይገኙ ሰዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ ግልጽ ነው:- “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን?” (1 ቆሮንቶስ 6:9) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጻድቃንና ግፍ የተፈጸመባቸው ሰዎች ወደ ሰማይ እንዳልሄዱ ጭምር ይናገራል።

ኢየሱስ ራሱ በቅርብ ሰማዕት ሊሆን ያለውን መጥምቁ ዮሐንስን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” (ማቴዎስ 11:11) ጨካኝ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ሕፃኑን ኢየሱስን ለማጥፋት ባደረገው ሙከራ በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙትን ዕድሜያቸው ሁለትና ከዚያም በታች የሆናቸውን ወንድ ልጆች ያለ ርኅራኄ እንዲታረዱ አድርጓል። (ማቴዎስ 2:16) ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም [ወንድ ወይም ሴት ወይም ሕፃን] የለም፣ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ [ኢየሱስ] ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13) ኢየሱስ እነዚህ የግፍ ሰለባ የሆኑ ልጆች በሰማይ እንደሚገኙ ያልተናገረው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ መንገዱን ከፈተ

ኢየሱስ ራሱን “መንገድና እውነት ሕይወትም” በማለት ሲጠራ ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ‘ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን የተነሣ’ መሆኑን ገልጿል። (ዮሐንስ 14:6፤ 1 ቆሮንቶስ 15:20) ስለዚህ ማንም ከእሱ ቀድሞ ወደ ሰማይ መሄድ አይችልም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሳ ከ40 ቀናት በኋላ ወደ ሰማይ ሲያርግ ቀደም ሲል ሞተው የነበሩ ብቁ የእምነት ሰዎች ተከትለውት ይሆን? ሐዋርያው ጴጥሮስ ከአሥር ቀናት በኋላ ንጉሥ ዳዊትን አስመልክቶ ሲናገር “እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም . . . መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና” ብሎ ነበር።—ሥራ 2:29, 34

ስለዚህ ወደ ሰማይ መሄድ የግፍ ካሣ ወይም የግል ታማኝነት ዋጋ ከመሆን የበለጠ ነገርን የሚነካ ነው። በዚህ ፋንታ ተቀማጭነቱ በሰማይ የሆነ ከሰዎች የተውጣጣና በክርስቶስ የሚመራ የገዢዎች አካል ለመመሥረት የሚያስችል ይሆናል።—ሮሜ 8:15-17፤ ራእይ 14:1-3

ሰማያዊ መንግሥት

ኢየሱስ ይህን አገዛዝ ወይም መንግሥት “መንግሥተ ሰማያት” ወይም የ“እግዚአብሔር መንግሥት” በማለት ጠርቶታል። (ማቴዎስ 5:3, 20፤ ሉቃስ 7:28) ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዚህ አስተዳደራዊ አካል ውስጥ እንዲታቀፉ ምንም የታቀደ ነገር አልነበረም። ስለዚህ ኢየሱስ ይህን አካል “ታናሽ መንጋ” ሲል ጠርቶታል። (ሉቃስ 12:32) በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የሚገኘው “ታናሽ” (ማይክሮስ) የሚለው ቃል “ታላቅ” (ሜጋስ) የሚለው ቃል ተቃራኒ ሲሆን በሉቃስ 12:32 ላይ የገባበት አጠቃቀሙ መጠንን ወይም በቁጥር ማነስን ያመለክታል። ስለዚህ “የመንግሥተ ሰማያት” አባሎች ቁጥር ገደብ የሌለው አይደለም። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- በአንድ ብርጭቆ ውስጥ ትንሽ ውኃ እንድትጨምር ብትጠየቅ ብርጭቆው ሞልቶ ውኃው እስኪፈስ ድረስ እንዳትጨምር ትጠነቀቃለህ። በተመሳሳይም “ታናሹ መንጋ” ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሊኖሩት አይችልም። የአምላክ መንግሥት የተወሰነ (“ትንሽ”) ቁጥር ያላቸው የክርስቶስ ተባባሪ ገዢዎች አሉት።

ሐዋርያው ዮሐንስ የእነዚህ ገዢዎች ትክክለኛ ቁጥር 144,000 እንደሚሆን ተነግሮት ነበር። (ራእይ 14:1, 4) ቀደም ሲል በራእይ ውስጥ እነዚህ ሰዎች ‘ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት እንዲሆኑ የተመረጡና’ በሰማይ ነገሥታት በመሆን ምድርን እንደሚገዙ ተገልጿል። (ራእይ 5:9, 10) ተከታዮቹ እንዲጸልዩለት ያስተማራቸው መንግሥት ይህን የአስተዳደር አካልና ኢየሱስ ክርስቶስን ያቀፈ ነው። በተጨማሪም ይህ ድርጅት በምድር ላይ ያለውን ብልሹ አገዛዝ ወደ ፍጻሜው በማምጣት ፍትህንና ሰላምን የሰዎች መኖሪያ ወደ ሆነችው ወደ ምድር የሚመልስና ለነዋሪዎቿ ዘላለማዊ ሕይወትን የሚሰጥ ይሆናል።—መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 6:9, 10

የተመረጠ የገዢዎች አካል

በአምላክ መንግሥት የሚተካው የሰዎች አገዛዝ በምግባረ ብልሹነት የተጨማለቀ መሆኑ በሰማያዊው መንግሥት ውስጥ የሚካተቱ ሰዎች በአምላክ በጥንቃቄ መመረጥና መፈተን እንዳለባቸው አያመለክተንምን? በጊዜያችን ያለው የሰው ልጆች ሁኔታ በመጥፎ የአየር ሁኔታ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳፍሮ ከሚጓዝ ከአንድ የተበላሸ አውሮፕላን ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ወቅት ወጣት የሆኑና ልምድ የሌላቸው የበረራ ሠራተኞችን ትፈልጋላችሁ? በፍጹም አትፈልጉም! ሁኔታው ጥብቅ በሆኑ የችሎታ መመዘኛዎች ተለክተው በጥንቃቄ የተመረጡ ሠራተኞችን የሚጠይቅ ነው።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን ሰዎች “እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸውን በአካል” እንዳደረገ ማወቃችን እፎይታ ሰጥቶናል። (1 ቆሮንቶስ 12:18) የግል ፍላጎታችን ወይም በመንግሥቱ ውስጥ ቦታ እንዲኖረን መመኘታችን ወሳኝ ነገሮች አይደሉም። (ማቴዎስ 20:20-23) አምላክ ብቃቱን የማያሟሉ ሰዎች እንዳይገቡ ለመከላከል ሲል እምነትንና አኗኗርን በተመለከተ የተወሰኑ መሥፈርቶችን አውጥቷል። (ዮሐንስ 6:44፤ ኤፌሶን 5:5) በኢየሱስ የተራራ ስብከት መክፈቻ ቃላት ላይ እንደተገለጸው ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙ ሰዎች መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው፣ ትሑቶች፣ ጽድቅ ወዳዶች፣ ርኅሩኆች፣ ንጹህ ልብ ያላቸውና ሰላማውያን መሆናቸውን ማስመስከር እንዳለባቸው ጠቅሷል።—ማቴዎስ 5:3-9፤ በተጨማሪም ራእይ 2:10⁠ን ተመልከት።

አብዛኛው የሰው ዘር ከእነዚህ ሰማያዊ የገዢዎች አካል ወኪሎች መካከል እንዲሆን በአምላክ ባይመረጥም ያለምንም ተስፋ ያልተተወ መሆኑ የሚያስደስት ነው። ይህችን ውብ ምድር በመውረስ የአምላክን መለኮታዊ አመራር ጥቅሞች በማግኘት ይደሰታሉ። በተፈጸመባቸው ግፍ ምክንያት ከረዥም ጊዜ በፊት ሞተው የነበሩ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ሙሉ በሙሉ “ስትመጣ” በሕይወት ተርፈው ከተመለከቱ ሰዎች ጋር አንድ ላይ ለመኖር ይነሳሉ። “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና” የሚለው ተስፋ ፍጻሜውን ያገኛል።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ምሳሌ 2:21፤ ሥራ 24:15

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ