በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ የሆነ ጣፋጭ ፍሬ
በሜክሲኮ የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ይህን ፍሬ የቀመሱት የመጀመሪያዎቹ አውሮፓውያን በ1493 የዌስት ኢንዲስን ደሴቶች በመርከብ ያስሱ የነበሩት ክርስቶፈር ኮሎምቦስና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ይህ ፍሬ ወደ ስፔይኑ ንጉሥ ተልኮ የነበረ ሲሆን ንጉሡም ጣዕሙን በጣም ወደዱት። መርከበኞች በመላው አሜሪካ በሰፊው እንዲታወቅ ከማድረጋቸውም ሌላ በፊሊፒንስ ደሴቶች ላይ እንዲለማ በ1548 ወደዚያ ወሰዱት።
ከዚያም በ1555 ገደማ ይህ ጣፋጭ ፍሬ ወደ ፈረንሳይ ተጓዘ። በ1700ዎቹ በአንዳንድ የአውሮፓ ነገሥታት ማዕድ ላይ በክብር የሚቀርብ ውድ የነገሥታት ምግብ ነበር። በጣም ተወዳጅ እየሆነ በመምጣቱ ወደ ቀረው የአውሮፓ ክፍል፣ ወደ እስያና አፍሪካ ተሠራጨ። በአሁኑ ጊዜ በግንባር ቀደምትነት የዚህ ፍሬ አብቃይ የሆኑት አገሮች ብራዚል፣ ሃዋይ፣ ሜክሲኮ፣ ፊሊፒንስ፣ ታይላንድ እንዲሁም ተስማሚ የአየር ንብረትና አፈር ያላቸው ሌሎች ጥቂት አገሮች ናቸው።
በዚህ መንገድ ከአምስት መቶ ዘመናት ጉዞ በኋላ፣ ከተገኘበት ከአሜሪካ እጅግ ርቀው ወደሚገኙ ቦታዎች ሁሉ ደርሷል። ይህ ፍሬ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ጣፋጭ የሆነው የአናናስ ፍሬ ነው።
ሜክሲኮ ውስጥ ማትሳትሊ በመባል ሲታወቅ በካሪቢያን አገሮች አናና፣ በመካከለኛውና በደቡብ አሜሪካ ደግሞ ናና እየተባለ ይጠራል። ከፈረንጅ ጥድ (በእንግሊዝኛ ፓይን ዛፍ) ፍሬ ጋር ቅርጹ ይመሳሰላል በሚል ፒንያ የሚለውን ስያሜ የሰጡት የስፔይን ተወላጆች ሳይሆኑ አይቀሩም። ዛሬ በስፔይን ቋንቋ ፒና ወይም አናናስ በመባል ሲታወቅ በእንግሊዝኛ ደግሞ ፓይንአፕል እየተባለ ይጠራል። ስሙ ቢለያይም ይህን ፍሬ የቀመሱ ሁሉ በጣፋጭነቱ ይስማማሉ።
አናናስና ተክሉ
የአናናስ ፍሬ ምን ይመስላል? ሞላላ ቅርጽ ያለው በተክሉ መሀል ላይ የሚበቅል ፍሬ ነው። የአናናስ ፍሬ ጠንካራ ሽፋን ያለው ሲሆን አናቱ ላይ እንደ ዘውድ ችፍግ ብለው የበቀሉ ጠንከር ያሉ ትናንሽ አረንጓዴ ቅጠሎች አሉት። ተክሉ ራሱ ደግሞ በግንዱ ዙሪያ እንደ ሰይፍ ያለ ቅርጽ ያላቸውን ረጃጅም ቅጠሎች ያወጣል። ከ60 እስከ 90 ሴንቲ ሜትር ድረስ የሚያድግ ሲሆን ፍሬውም ከሁለት እስከ አራት ኪሎ ድረስ ይመዝናል።
ፍሬው ገና ትንሽ እያለ ከፈረንጅ ጥድ ፍሬ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን የልጣጩ ቀለም የወይን ጠጅ እንደሆነ ይቆያል። ፍሬው እየደረሰ ሲመጣ አረንጓዴ ይሆናል፤ ሲበስል ደግሞ ብዙውን ጊዜ ወደ ቢጫ የሚወስደው አረንጓዴ፣ ወደ አረንጓዴ የሚወስደው ብርቱካንማ ወይም ቀይ ይሆናል። የበሰለው አናናስ ግሩም መዓዛ ያለውና ውኃ የሞላው ጣፋጭ ፍሬ ይሆናል።
የአናናስ ፍሬ የሚበቅለው እንዴት ነው?
የአናናስ ፍሬ የሚበቅለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በሐሩር ክልል ያለው ዓይነት አሸዋማ የሆነ፣ ካርቦናዊ ቁስ የበዛበት፣ የአሲድነት ባሕርይ ያለው፣ ዝቅተኛ የጨው መጠን ያለውና ከፍተኛ እርጥበት ያዘለ አፈር ሊኖር ይገባል። ከዚያ በኋላ ከፍሬው ሥር የምታቆጠቁጠውንና ፍሬው ከተቆረጠ በኋላም በተክሉ ላይ የሚቀረውን ግንጫፍ ወስዶ መትከል ያስፈልጋል። ወይም ዘውድ የሚመስለውን የአናናስ ፍሬውን አናት ቆርጦ መትከል ይቻላል። ይሁን እንጂ ተክሉ አድጎ ፍሬውን ለመቁረጥ ከአንድ ዓመት በላይ የሚሆን ጊዜ ስለሚጠይቅ ፍሬውን ማግኘት ትዕግሥት ይጠይቃል።
አናናስ በማምረት ከ25 ዓመታት በላይ ያሳለፈው አንቶኒዮ በዚህ መስክ የሚሠራበትን ዘዴ በሚመለከት እንዲህ በማለት ያስረዳል:- “ፍሬው ማደግ ከመጀመሩ በፊት ተክሉ መሃል ላይ ጥቂት ካልሲየም ካርባይድ ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ይህ የሚደረገው ሁሉም የአናናስ ፍሬ በተመሳሳይ ጊዜ እንዲደርስ ለማድረግ ነው፤ እንዲሁ ከተተወ ግን አንዳንዶቹ ፍሬዎች ከሌላው ቀደም ብለው ስለሚደርሱ የመሰብሰቡ ሥራ አስቸጋሪ ይሆናል።”
የአናናስ ፍሬ ሲደርስና መብሰል ብቻ ሲቀረው የፀሐይ ትኩሳት እንዳያቃጥለው መሸፈን ይኖርበታል። በወረቀት ወይም በአናናስ ዛፍ ቅጠል ይሸፈናል። የሚበስልበት ጊዜ ሲደርስ ፍሬው የሚሰበሰብበት ጊዜ ደረሰ ማለት ነው። ከላይ ያለውን ቅርፊት ከላጥህ በኋላ አናናሱን በስሱ እየቆረጥህ ብላው! ግን ተጠንቀቅ። የፍሬውን መካከለኛ ክፍል ከበላኸው ምላስህን ሊያቃጥልህ ይችላል። ብዙ ሰዎች መሀል ላይ ያለውን ክፍል ሳይበሉ የሚተውት ለዚህ ነው።
ጣፋጭና ውኃ የሞላው የአናናስ ፍሬ ማግኘት ከፈለግህ መልኩን ዓይተህ አትፍረድ። አንቶኒዮ አንዱን አናናስ አንስቶ እያሳየን እንዲህ በማለት አስረዳን:- “አንዳንድ ሰዎች የቅርፊቱ ቀለም አረንጓዴ ወይም ቢጫ ነው ብለው በማየት አናናስ ይመርጣሉ። ይሁን እንጂ ቅርፊቱ አረንጓዴም ሆኖ ፍሬው የበሰለ ሊሆን ይችላል። በጣቶቻችሁ መታ መታ አድርጋችሁ ማየት ይኖርባችኋል። ባዶ እንደሆነ የሚያሳይ ድምፅ ከሰጠ ውስጡ ነጭ እና ጣዕም የለሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ ውኃ እንደሞላው የሚያሳይ ወፍራም ድምፅ ከፈጠረ ለመብል ደርሷል ማለት ነው፤ ጣፋጭና ብዙ ፈሳሽ ያለው ይሆናል።” ይህ ፍሬ በርካታ ዓይነት ያለው ሲሆን ከእነዚህ መካከል ይበልጥ ተወዳጅ የሆነው ስሙዝ ኬይን (ኬይና) በመባል የሚታወቀው ዓይነት ነው።
ግሩም ጣዕም
ጭማቂውን በመጠጣት ወይም የተቆራረጠውን ፍሬ በመግመጥ ከምታገኘው እርካታ ሌላ በአንዳንድ አገሮች ታሽጎ የሚሸጠውን ከአናናስ ፍሬ የሚዘጋጅ ፈሳሽ በመጠጣት ልትደሰት ትችላለህ። ከዚህም ሌላ የአናናስ ፍሬ እንደ ካርቦሃይድሬት፣ አሰር (ፋይበር) እንዲሁም ቫይታሚኖችን በተለይ ቫይታሚን ኤ እና ሲ ይዟል።
ሜክሲኮ ውስጥ ከአናናስ ልጣጭ የሚዘጋጀውን የሚያረካ መጠጥ ታገኛለህ። አንተ ራስህ ይህንን መጠጥ ለመሥራት ከፈለግህ ልጣጩን መስታወትነት ባለው ዕቃ ውስጥ አስቀምጥና ውኃና ስኳር ጨምረህ ለሁለትና ሦስት ቀናት አቆየው። ይህ አንድ ላይ ከተብላላ በኋላ በረዶ ጨምረህ እንደ ቀዝቃዛ መጠጥ ልታቀርበው ትችላለህ። ይህ ቴፓቼ በመባል የሚታወቅ የሚያረካ መጠጥ ሲሆን ጣፋጭ ሆኖ ኮስተር ያለ ጣዕም አለው። አንድ ብርጭቆ መቅመስ አትፈልግም? ፊሊፒንስ ውስጥ አናናስ የሚለማው ከቅጠሎቹ ለሚገኘው ቃጫ ሲባል ነው። ከቅጠሎቹ የሚገኘው ቃጫ ደብዘዝ ያለ ነጭ ቀለም ያለው፣ ብርሃን የሚያሳልፍ እና በጣም ለስላሳ የሆነ ጨርቅ ለመሥራት ያገለግላል። መሀረቦች፣ ፎጣዎች፣ ቀበቶዎች፣ ሸሚዞች እንዲሁም የልጆችንና የሴቶች ልብስ ለመሥራት ያገለግላል።
አናናስ ባለፉት ጥቂት መቶ ዘመናት ውስጥ ወደ ማይበቅልባቸው ብዙ አገሮች ሲላክ ቆይቷል። አናናስ የሚወዱ ሰዎች ሁሉ የሰውን ልጅ ስሜት እያረካ ዓለምን ማዳረሱን እንዲቀጥል ይመኛሉ።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከላይ:- አናናስ፤ Century Dictionary