ንቁ! የአንድን ሰው ሕይወት ከሞት አተረፈ
በኢኳዶር የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር አንድ መካኒክ መኪናዋን ጠግኖ እስኪጨርስላት እየተጠባበቀች ሳለ የመካኒኩ ባለቤት ባይሮን የተባለው ሕፃን ልጅዋ ጤንነት እንደሚያሳስባት ነገረቻት። በሳምንት ውስጥ አምስት ወይም ስድስት ጊዜ ያንቀጠቅጠዋል። ሐኪሞች በሽታውን ሊያውቁት አልቻሉም። እንዲያውም ባይሮን ዋና ከተማ በሆነው ኩዊቶ ወደሚገኙ ስፔሻሊስቶች ዘንድ ተወስዶ ነበር።
“ከእናትዮዋ ጋር እየተነጋገርኩ ሳለ” ትላለች ምሥክሯ “ሠራተኛው አንድ መኪና ቀለም ሲቀባ አየሁ፤ በሊድ ስለመመረዝ የሚናገር የአንድ ንቁ! መጽሔት ርዕስ ትዝ አለኝ። በሊድ የተመረዘ ሰው የሚታይበት አንዱ ምልክት መንቀጥቀጥ እንደሆነ መጽሔቱ ይናገራል። መጽሔቱን ይዤላት እንደምመጣ ለሴትዮዋ ነገርኳት።”
የባይሮን ወላጆች ርዕሱን ካነበቡ በኋላ ልጃቸው በሊድ መመረዝ አለመመረዙን ለማረጋገጥ የሕክምና ምርመራ እንዲደረግለት አደረጉ። ከፍተኛ መጠን ያለው ሊድ በባይሮን ደም ውስጥ ተገኘ። በጥሩ ሁኔታ ከታከመና ለሊድ እንዳይጋለጥ ከተደረገ በኋላ የባይሮን ጤንነት አስገራሚ በሆነ መንገድ ተሻሻለ። “ባለፉት አራት ወራት አንድም ጊዜ አላንቀጠቀጠውም” ስትል ምሥክሯ ጽፋለች። “ከዚያ ወዲህ አባትየው ሁኔታውን ለብዙ ሐኪሞች ገልጾላቸዋል፤ የልጁን ሕይወት ከሞት ያተረፈለት ንቁ! የተባለው መጽሔት እንደሆነ ዘወትር ይናገራል። በአሁን ጊዜ ከእነዚህ ሐኪሞች መካከል አንዳንዶቹ ንቁ! መጽሔት ያነባሉ።”
እርስዎም ንቁ! የተባለውን መጽሔት ቢያነቡ ብዙ ጥቅም እንደሚያገኙ እርግጠኞች ነን። ይህን መጽሔት ለማግኘት ወይም አንድ ሰው እቤትዎ መጥቶ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያወያይዎ የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖ.ሣ.ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም ገጽ 5 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች ወደ ሚቀርብዎ ይጻፉ።