ከዓለም አካባቢ
በግብረ ገብነት መጥፋት የሚሰማው እሮሮ
‘ብልግና፣ ስድ አደግነት፣ ዝርክርክ ወይም ቅጥ ያጣ አለባበስ፣ መራገም፣ ማጭበርበርና ጭካኔ ሕይወትን አስተማማኝ ያልሆነ፣ አስጨናቂና አሳዛኝ አድርገውታል’ ሲል ዘ ታይምስ የተባለው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። በአንዳንድ አገሮች በአንደኛ ደረጃ እንደ ጋጠ ወጥነት ከሚቆጠሩት አንዱ ሆን ብሎ ለአለባበስና ለሰውነት አቋም ግዴለሽ መሆን ነው። “የቆዳ ጃኬቶች ማድረግ፣ ራስ ላይ ጨርቅ ማሰር፣ አፍንጫን መበሳት፣ ብረት የተለጠፈባቸው ቡትስ ጫማዎች ማድረግና ሰውነትን መነቀስ ጦርነት እንደ ማወጅ የሚቆጠሩ ናቸው” ሲል የአቴናው የሊዮሲ የሪዲንግ ዩኒቨርሲቲ ገልጿል። የሊዮሲ ዩኒቨርሲቲ እንዳለው ከሆነ እንደዚህ ዓይነቱ አለባበስ ለሰዎች ያላቸውን ንቀት በግልጽ የሚያሳይ ምልክት ነው። ዘ ታይምስ የተባለው መጽሔት ‘የትሕትና፣ የቁጥጥር ማነስና የሥርዓት መጥፋት ምናልባት ኅብረተሰቡን ከወንጀል ይበልጥ ሳያሰጋው አይቀርም’ ብሏል። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? ግብረ ገብነት “በቤተሰብ ተቋም ውስጥ መኮትኮት ይኖርበታል” ይላል ጋዜጣው። “ግብረ ገብነትን ለልጆች ማስረዳት ብቻ ሳይሆን በምሳሌነትም ጭምር ማስተማር ያስፈልጋል።”
ጭንቀት የያዛቸው ልጆች
ኦ ስታዶ ደ ኤስ ፖሎ የተባለ አንድ የብራዚል ጋዜጣ የአንጀትና የጨጓራ ቁስለት ወይም ሕመም የያዛቸው ልጆች ቁጥር ባለፉት አሥር ዓመታት በእጥፍ እንደጨመረ ዘግቧል። የሳኦ ፖሎ ዩኒቨርሲቲ ባደረጋቸው ጥናቶች ላይ የተመሠረቱት እነዚህ ግኝቶች ከዋናዎቹ ችግሮች አንዱ የስሜት ውጥረት እንደሆነ ይጠቁማሉ። “አንድ ልጅ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚያጋጥመው ችግር ለበሽታ እስከ መዳረግ ድረስ . . . በስሜቱ ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል” ሲሉ ዶሪና ባርቤሪ የተባሉ ጋስትሮኢንተሮሎጂስት ተናግረዋል። ጋዜጣው የቤተሰብ ግጭቶች፣ በቤተሰብ ላይ የሚደርሱ አደጋዎች ወይም ሞት፣ ፍጽምናን መጠበቅ፣ የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ፣ የፉክክር መንፈስና የመዝናኛ ጊዜ ማጣት እንዲሁም እነዚህን የመሳሰሉት ሁኔታዎች በልጆች ላይ ጭንቀት እንደሚያስከትሉ ጠቅሷል።
ካራቴ የሚማሩ ሴት መነኮሳት
በሴቶች ላይ የሚፈጸመው የኃይል ድርጊት እየጨመረ በመሄዱ ሳቢያ በደቡባዊው ሕንድ በማድሃቫራም ታሚል ናዱ ግዛት በሴንት ኤና ፕሮቪንሼት የሚገኙ በርካታ ሴት መነኮሳት የካራቴ ሥልጠና መውሰድ ጀምረዋል። የኦል ኢንዲያ ኢሺንርዩ ካራቴ አሶሴሽን (የመላው ሕንድ ኢሺንርዩ የካራቴ ማኅበር) ፕሬዚዳንት የሆኑት ሺሃን ሁሳኒ ሴት መነኮሳቱ ላለፉት 24 ዓመታት ካራቴ ካስተማሯቸው ሌሎች ሴቶች ሁሉ ከፍተኛ ብልጫ እንዳሳዩ ተናግረዋል። ‘ያላቸው ቅምጥ ኃይልና በዲሲፕሊን የታነጹ መሆናቸው ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል ብዬ አምናለሁ’ ይላሉ። ሴት መነኮሳቱ የሠለጠኑበት አንዱ መሣሪያ ሴን ኮ የሚባል ነው። ይህ መሣሪያ ስቅለትን የሚያሳይ ቅርጽ ያለው ሲሆን “በዚህ መሣሪያ በመጠቀም ጥቃት ሰንዛሪውን ለመግደል እንኳ ይቻላል” ይላሉ ሁሳኒ።
ለረዥም ጊዜ ንቁ አእምሮ ይዞ መኖር
ዕድሜህ ሲገፋ የማሰብ ችሎታህ እንዳይዳከም ትፈልጋለህ? አሜሪካን ሄልዝ የተባለው መጽሔት “ትምህርትህን ችላ አትበል፣ እንቅስቃሴ አድርግ እንዲሁም ሳምባህን ከጉዳት ጠብቅ” ሲል ይገልጻል። በሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ኒውሮሳይኮሎጂስት የሆኑት ማርሊን አልበርት “የአእምሮ ብቃታችን መጠበቅ የምንችልበትን ሁኔታ ለማጎልበት ማድረግ የምንችላቸው ነገሮች አሉ” ይላሉ። ዶክተር አልበርት በዕድሜ መግፋት ምክንያት የአእምሮ ብቃት እንዳይቀንስ ትምህርት በሆነ መንገድ “የአንጎልን አሠራር እንደሚለውጥ” ይገምታሉ። ከዚህም በተጨማሪ የአካል እንቅስቃሴ ለአንጎል የሚደርሰው የደም መጠን ከፍ እንዲልና አንጎል ብዙ ኦክስጅን እንዲያገኝ ሊያደርግ እንደሚችል ይታመናል። በመሆኑም አልበርት እንዲህ ሲሉ መክረዋል:- “በየቀኑ የእግር ጉዞ አድርግ፣ በየወሩ ቢያንስ አንድ አዲስ መጽሐፍ አንብብ እንዲሁም ትንባሆ የምታጨስ ከሆነ ለሳምባህ (እና ለአእምሮህ) ፋታ ለመስጠት ማጨስህን አቁም።”
“በቻይና የአረጋውያን ቁጥር”
ቻይና ቱዴይ የተባለው መጽሔት “በቻይና የአረጋውያን ቁጥር እያደር እየጨመረ ሄዷል” ሲል ዘግቧል። “በቻይና በ1994 መጨረሻ ላይ ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው 116.97 ሚልዮን የዕድሜ ባለጠጎች የነበሩ ሲሆን ይህም በ1990 ከነበረው ቁጥር የ14.16 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።” በአሁኑ ጊዜ አሥር በመቶ የሚያክሉት ነዋሪዎች ከ60 ዓመት በላይ ሲሆኑ የአረጋውያኑ ቁጥር ጭማሪ ከጠቅላላው የሕዝብ ብዛት ዕድገት ጋር ሲወዳደር በሦስት እጥፍ ያህል በልጦ ተገኝቷል። አረጋውያኑ የሚደረግላቸው እንክብካቤ ምን ይመስላል? ብዙዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟሉት በሚያገኙት የአገልግሎት ካሳ፣ ጡረታ፣ የማኅበራዊ መድን ክፍያና እርዳታ ቢሆንም ከቻይና አረጋውያን ዜጎች መካከል ከ57 በመቶ የሚበልጡት የሚጦሩት በልጆቻቸው ወይም በሌሎች ዘመዶቻቸው ነው። ቻይና ቱዴይ እንዳለው “ከሌላው አንጻር ሲታይ በቻይና የቤተሰብ ግንኙነት ትንሽ የተረጋጋ በመሆኑና ቻይና አረጋውያንን የማክበርና የመንከባከብ መልካም ባሕል ስላላት አብዛኞቹ አረጋውያን ዜጎች የሚኖሩትም ሆነ እንክብካቤ የሚደረግላቸው በዘመዶቻቸው ነው። በዕድሜ ከገፉት ቻይናውያን መካከል ራሳቸውን ችለው የሚኖሩት 7 በመቶ የሚያክሉት ብቻ ናቸው።”
ልጆችን ቀጥሮ ማሠራት—እየከፋ የሄደ ችግር
በቅርቡ የዓለም የሥራ ድርጅት ያወጣው አንድ ሪፖርት እንደገለጸው ከ10 እስከ 14 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉት የዓለም ሕፃናት መካከል 13 በመቶ ማለትም 73 ሚልዮን የሚያክሉት ሕፃናት ተቀጥረው ለመሥራት ተገደዋል። በተጨማሪም ሪፖርቱ ከአሥር ዓመት በታች ያሉት ልጆችና በቤት ውስጥ ሥራ ላይ የተሠማሩት ልጃገረዶች ቢቆጠሩ ኖሮ ተቀጥረው የሚሠሩት ሕፃናት ቁጥር በመቶ ሚልዮኖች የሚቆጠር ይሆን እንደነበር ጨምሮ ገልጿል። መቀመጫውን ጄኔቫ ያደረገው ድርጅት 80 ለሚያክሉ ዓመታት ልጆችን ቀጥሮ ማሠራትን ሲዋጋ የኖረ ቢሆንም ችግሩ በተለይ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ውስጥ እያደገና እየሰፋ መሄዱን ቀጥሏል። ከእነዚህ ልጆች መካከል ከባድና ለሕይወት አደገኛ የሆኑ ሥራዎችን መሥራት የብዙዎቹ ዕጣ ፋንታ ቢሆንም እንደ ዋነኛ ችግር ሆኖ የቀረበው የሕፃናት ዝሙት አዳሪነት ነው። ሪፖርቱ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ “አዋቂዎቹ ከልጆች ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸሙን [በኤች አይ ቪ] ላለመለከፍ ከሁሉ የተሻለ አማራጭ አድርገው ወስደውታል” ሲል ይገልጻል። በፓሪስ የሚታተመው ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡን ድርጅቱ “ለጉዳዩ ተወቃሽ ያደረገው ይህን ችግር ቸል ያሉትን . . . የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ነው” ሲል ዘግቧል።
የትምህርት ቤት ወመኔዎችን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
በትምህርት ቤት ውስጥ ወመኔነት እየተስፋፋ በመሄዱ በቅርቡ የጃፓን የትምህርት ሚንስቴር በ9,420 ተማሪዎች እና በወላጆቻቸው እንዲሁም በአስተማሪዎች ላይ አንድ ጥናት አካሂዶ ነበር። የጥናቱ ውጤት እንደጠቆመው ከአንደኛ ደረጃ አንስቶ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድረስ ልጆቻቸውን ወመኔ ተማሪዎች ከሚያስቸግሯቸው ወላጆች መካከል 70 በመቶ የሚያክሉት አንድም ስለ ሁኔታው የሚያውቁት ነገር የለም አለዚያም ደግሞ የልጆቻቸውን ምሬት ከቁም ነገር ሳይቆጥሩ አልፈዋል። የዚህ ችግር ሰለባ የሆኑ ብዙ ተማሪዎች የበቀል እርምጃ እንዳይወሰድባቸው ስለሚፈሩ ወመኔዎች እያስቸገሯቸው እንዳሉ ለአስተማሪዎቻቸው አይናገሩም። ይሁን እንጂ ጥናቱ እንደጠቆመው አንድ አስተማሪ ጉዳዩን አምርሮ በመከታተሉ የበቀል ጥቃት የሚደርስባቸው ተማሪዎች 2 በመቶ ብቻ ሲሆኑ 40 በመቶ የሚሆኑት ልጆች ግን ጥቃቱ ያቆምላቸዋል። የኦሳካ ከተማ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ዮጂ ሞሪታ “የወመኔነት ጥቃት የሚፈጸምባቸው ልጆች ለአስተማሪዎቻቸው ቢናገሩና አስተማሪዎችም ጉዳዩን በሚገባ ቢከታተሉት ወመኔነትን መቋቋም እንደሚቻል ጠንካራ እምነት አድሮብኛል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
ሕፃናት የሚያስልጋቸውን ማሟላት
የዓለም ሕፃናት ሁኔታ 1995 በሚል ርዕስ የወጣው የዩኒሴፍ (የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት) ሪፖርት እንደገለጸው ዓለማችን ሕፃናት የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ማሟላት አትችልም ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ዩኒሴፍ ይህንን ነጥብ በምሳሌ ለማስረዳት የሚከተለውን አኅዝ አቅርቧል:- በዓለም ዙሪያ የተመጣጠነ ምግብና የመሠረታዊ ጤና እንክብካቤን ለማሟላት የሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪ በዓመት 13 ቢልዮን፣ ለመደበኛ ትምህርት 6 ቢልዮን፣ ለንጹሕ የመጠጥ ውኃና ንጽሕና አጠባበቅ 9 ቢልዮን፣ ለቤተሰብ ምጣኔ 6 ቢልዮን ሲሆን በድምሩ በዓመት 34 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ይገመታል። ይህንንም ቀጥሎ ለተዘረዘሩት ነገሮች በየዓመቱ እየወጣ ካለው ወጪ ጋር እንድናወዳድረው አቅርቧል:- ለጎልፍ ጨዋታ 40 ቢልዮን፣ ለቢራና ወይን 245 ቢልዮን፣ ለትንባሆ 400 ቢልዮን፣ ለወታደራዊ ወጪዎች 800 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ነው። በእርግጥም ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ ያሉት ሕፃናት በሙሉ በቂ እንክብካቤ ያገኙ ነበር ሲል ዩኒሴፍ ዘግቧል።
ካርዲናሉ የምሥክሮቹን እንቅስቃሴ ደግፈውታል
የካቶሊክ የሃይማኖታዊ ውህደትና ተዓምራዊ ስጦታዎች እንቅስቃሴ አራማጅ የሆኑት የቤልጅየሙ ካርዲናል ስዌነንስ በቅርቡ በ91 ዓመታቸው አርፈዋል። ሄት ቤላንግ ቫን ሊምበርግ የተባለው የቤልጅየም ጋዜጣ እንዳለው ስዌነንስ ብዙ ነገሮችን ቢያከናውኑም የሌት ተቀን ሕልማቸው እውን ሳይሆን ቀርቷል። በእርሳቸው እግር የተተኩት ካርዲናል ዳኒልስ ስለ ስዌነንስ እንዲህ ብለዋል:- “ሁል ጊዜ ክርስቲያኖች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይመኝ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት ከቤት ወደ ቤት መሄድ ይኖርብን ይሆን? . . . እያለ ከራሱ ጋር ይሟገት ነበር። የኋላ ኋላ ግን ይህ መጥፎ እንዳልሆነ ተገንዝቧል። ‘እውነተኛ ክርስቲያን የምትባለው ሌላውን ክርስቲያን እንዲሆን ስትረዳ ብቻ ነው’ የሚሉትን ቃላት ብዙ ጊዜ ሲናገር ይሰማ ነበር።”
በእርግዝና ወቅት የሚወሰድ አልኮል
“አንድ አዲስ ምርምር በእርግዝና ወቅት እናቶች የሚወስዱት አልኮል ሕፃኑ በሉኪሚያ በሽታ ከመጠቃቱ ጋር በከፍተኛ ደረጃ ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል አረጋግጧል” ሲል በካናዳ የሚታተመው ዘ ሜዲካል ፖስት ዘግቧል። ጥናቱ የተደረገው ዕድሜያቸው 18 ወር ወይም ከዚያም በታች እያለ በሽታው እንዳለባቸው በታወቀ 302 ሰዎች ላይና በሌሎች 558 ሕፃናት ላይ ነበር። በእርግዝናቸው ወቅት በመጀመሪያው ወይም በተከታዩ ሦስት ወራት ውስጥ እናቶቻቸው አልኮል የወሰዱት ልጆች እናቶቻቸው አልኮል ካልወሰዱት ሌሎች ልጆች ይልቅ በማዬሎይድ ሉኪሚያ የመጠቃታቸው አጋጣሚ አሥር እጥፍ ያህል ከፍ ያለ ሆኖ ነበር። አዲሱ የምርምር ውጤት ከአሁን ቀደም ከተደረጉትና አልኮል የሚወስዱ ነፍሰ ጡር እናቶች ልጆች በሉኪሚያ ሊጠቁ የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍተኛ እንደሆነ ከሚጠቁሙት ሌሎች ጥናቶች ጋር ይስማማል።