የጥያቄ ሳጥን
◼ ተንቀሳቃሽ ስልኮችንና የኤሌክትሮኒክስ መልእክት መቀበያ መሣሪያዎችን (pagers) ስንጠቀም ምን ነገሮችን ማስታወስ ይኖርብናል?
እንደነዚህ ያሉ መሣሪያዎች በየትኛውም ቦታ ሆነን ለማለት ይቻላል ከሌሎች ጋር እንድንገናኝ ያስችሉናል። ይህ ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም ተንቀሳቃሽ ስልኮችና የኤሌክትሮኒክስ መልእክት መቀበያ መሣሪያዎች አገልግሎታችንን እንዳያደናቅፉብን ወይም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እኛንም ሆነ ሌሎችን እንዳይረብሹ ጠንቃቃ መሆን አለብን። ይህ ሊያጋጥም የሚችለው እንዴት ነው?
በመስክ አገልግሎት ላይ ተሰማርተን ምሥክርነት እየሰጠን ሳለ ስልካችን ወይም የኤሌክትሮኒክስ መልእክት መቀበያ መሣሪያችን ቢጮህ ምን እንደሚፈጠር አስቡ። የምናነጋግረው ሰው ምን ብሎ ሊያስብ ይችላል? የጀመርነውን ውይይት አቁመን በስልክ መነጋገር ብንጀምር የቤቱ ባለቤት ምን ይሰማዋል? ሌሎች የመንግሥቱን መልእክት እንዳይሰሙ ምንም ዓይነት እንቅፋት መፍጠር እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (2 ቆሮ. 6:3) በመሆኑም ተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም የኤሌክትሮኒክስ መልእክት መቀበያ መሣሪያ የምንይዝ ከሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ እያለን እኛንም ሆነ ሌሎችን እንዳይረብሽ ልናጠፋው ይገባል።
ምሥክርነቱን የሚሰጠው አብሮን ያለው የአገልግሎት ጓደኛችን በሚሆንበት ጊዜስ? ለመስክ አገልግሎት ብለን እስከወጣን ድረስ አእምሯችን በአገልግሎቱ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ማድረግ አይኖርብንም? ቅዱስ ለሆነው አገልግሎታችን ስትሉ እባካችሁ አስፈላጊ ያልሆኑ የግል ወይም ማኅበራዊ ጉዳዮችን በሌላ ጊዜ አከናውኑ። (ሮሜ 12:7) እንዲህ ስንል ግን ተጨማሪ ምሥክርነት ለመስጠት ወይም ቀጠሮ ለመያዝ ስልክ መጠቀም አይቻልም ማለት አይደለም።
መኪና እያሽከረከሩ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀምን በተመለከተም በጣም ጠንቃቃ መሆን አለብን። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንዲህ ማድረግ ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። መኪና እያሽከረከሩ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀምን የሚከለክሉ ማንኛውንም ዓይነት ሕጎች በጥብቅ መከተል ይኖርብናል።
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ በልዩና በወረዳ ስብሰባዎች እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ይሖዋን ለማምለክና ከእርሱ ለመማር ነው። ቅዱስ ለሆኑት ለእነዚህ ስብሰባዎች ያለን አድናቆት እኛንም ሆነ ሌሎችን እንዳይረብሹ ተንቀሳቃሽ ስልካችንን ወይም የኤሌክትሮኒክስ መልእክት መቀበያ መሣሪያዎችን እንድናጠፋ ሊገፋፋን አይገባም? አንድ አስቸኳይ ጉዳይ ከገጠመን ከስብሰባ ቦታው ወጣ ብለን ማከናወን ይኖርብናል። በተረፈ ከግልና ከሰብዓዊ ሥራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማከናወን ያለብን ለአምልኮ ከመደብነው ጊዜ ውጪ መሆን አለበት።—1 ቆሮ. 10:24
ተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም ሌላ ማንኛውም ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ የምንጠቀምበት መንገድ ለሌሎች አሳቢ እንደሆንና ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥልቅ አድናቆት እንዳለን የሚያሳይ ይሁን።