የጥያቄ ሣጥን
◼ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወይም በአገልግሎት ላይ ስንሆን የሞባይል ስልክ አጠቃቀምን በተመለከተ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?
“ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።” (መክ. 3:1)፦ የሞባይል ስልኮች በማንኛውም ጊዜ ማለት ይቻላል ከሰዎች ጋር መልእክት ለመለዋወጥ ወይም ለመነጋገር ያስችላሉ። ይሁንና ክርስቲያኖች ስልካቸው ትኩረታቸውን እንዲሰርቅባቸው የማይፈልጉባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ስብሰባዎቻችን ይሖዋን የምናመልክባቸው፣ መንፈሳዊ መመሪያ የምናገኝባቸውና እርስ በርስ የምንበረታታባቸው ወቅቶች ናቸው። (ዘዳ. 31:12፤ መዝ. 22:22፤ ሮም 1:11, 12) ታዲያ ስብሰባ ቦታ ስንደርስ ስልካችንን ማጥፋት አይኖርብንም? የመጡልንን መልእክቶች ከስብሰባ ከወጣን በኋላ ማየታችንስ ተገቢ አይሆንም? አንገብጋቢ የሆነ የምንጠብቀው ስልክ ካለና ስልካችንን ሳናጠፋ ማቆየታችን የግድ አስፈላጊ ከሆነ ሌሎችን በማይረብሽ መንገድ ልናስተካክለው ይገባል።
“ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።” (1 ቆሮ. 9:23)፦ በአገልግሎት ላይ ሞባይል ስልክ መጠቀም አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ የስብከት እንቅስቃሴውን የሚመራው ወንድም ክልሉ ውስጥ በሌላ አቅጣጫ እያገለገሉ ያሉ ወንድሞች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ በሞባይል ስልክ ሊጠቀም ይችላል። አንዳንዴ አስፋፊዎች ፍላጎት ያለው ሰው ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ጋር ከመሄዳቸው በፊት በተለይ ግለሰቡ ራቅ ያለ ቦታ የሚገኝ ከሆነ በቅድሚያ መኖሩን ለማረጋገጥ በሞባይል ስልካቸው ተጠቅመው ሊደውሉ ይችላሉ። ስልክ የምንይዝ ከሆነ የቤቱን ባለቤት እያናገርን እያለ እንዳይረብሸን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 6:3) ሌሎች አስፋፊዎችን በምንጠብቅበት ጊዜ ለጓደኛችን ስልክ ከመደወል ወይም መልእክት ከመላክ ይልቅ ትኩረታችንን በአገልግሎታችን እና አብረውን በሚሠሩት አስፋፊዎች ላይ ማድረጋችን የተሻለ አይሆንም?
ለሌሎች አሳቢነት አሳዩ፦ (1 ቆሮ. 10:24፤ ፊልጵ. 2:4)፦ በማንኛውም ጊዜ ደውዬ ወይም መልእክት ልኬ ወንድሞች የት አካባቢ እያገለገሉ እንዳለ ማወቅ እችላለው ብለን በማሰብ ለመስክ አገልግሎት ስብሰባ በሰዓቱ የመገኘትን አስፈላጊነት በፍጹም ችላ ማለት የለብንም። አርፍደን የምንደርስ ከሆነ ምደባውን እንደገና ማቀናጀት ሊያስፈልግ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ልናረፍድ እንችላለን። ሆኖም በጊዜ የመድረስን ልማድ የምናዳብር ከሆነ ይሖዋ ላደረጋቸው ዝግጅቶች አክብሮት እንዳለን እንዲሁም ስምሪቱን ለሚመሩትና ለእምነት ባልጀሮቻችን አሳቢዎች እንደሆንን እናሳያለን።